ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበለው አስታወቀ።

ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር በሚያደርገው ቀጣይ ትግል ህብረተሰቡ ከጎኑ እንዲቆምም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

የፓርቲው አመራሮች “‹‹ነጻነት በሌለባት ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አስተዳደር መትከል ዘበት ነው!›› በሚል ርእስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በምርጫው ሂደት በመቆየታቸው የኢህአዴግን አውሬነት ማሳየታቸውን በመጥቀስ፤
‹‹በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስት በህዝብ ተቀባይነት የለውም››ብለዋል።
‹‹ምርጫው ከዚህ ቀደም ከተካሔዱት ምርጫዎች ጋር እንኳ ሊወዳደር የማይችል እጅግ ኢ-ፍትኃዊ፣ ወገንተኛና ተዓማኒነት የሌለው በመሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ሂደቱንም ሆነ ውጤቱን አይቀበለውም፡፡›› ብለዋል-የፓርቲው አመራሮች።
ፓርቲው በ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት እንደሌሉና ገዥው ፓርቲም እውነተኛ ምርጫ እንደማይፈቅድ እያወቀ መሆኑን የገለፀሱት አመራሮቹ፤ ፓርቲው በሂደቱ የተሳተፈው የስርዓቱን
ችግሮች ለማጋለጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹በሂደቱ ውስጥ በመቆየታችን እጩዎቻችን በህገ ወጥ መንገድ ሲታገዱ፣ ታዛቢዎች ሲከለከሉና ሲታሰሩ አሳይተናል፡፡ በሂደቱ በመቆየታችን የኢህአዴግን አውሬነት አሳይተናል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮም
ሆነ በምርጫው ወቅት የነበረውን ማጭበርበር ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም አጋልጠንበታል፡፡›› ብለዋል፡፡
የፓርቲው ም/ሊቀመንበር እና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስለሽ ፈይሳ በበኩላቸው ምርጫው መትረየስ ተጠምዶ፣ ብረት ለበስ በየመንገዱ ቆሞ፣ የአጋዚ ጦር አባላት ከተማ ውስጥ ተሰማርተው ከመካሄዱም ባሻገር ከፍተኛ የድምጽ ማጭበርበር
የነበረበት ነው ብለዋል፡፡ የምርጫው ብቸኛ የውጭ ታዛቢ የሆነውን የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድንም ራሱንም ሌላም ማዳን የማይችል ‹‹የእንጨት ድምጽ ነው!›› ሲሉም ተችተዋል፡፡
ምርጫው በህገ ወጥ አሰራሮች የታጀበ፣ በማንኛውም መመዘኛ ፍትሃዊ፣ ነፃና ተአማኒ ሊሆን እንደማይችል ሒደቱ በግልፅ አመላካች ነበር ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹በውጤቱም በሐገራችን የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖርን ወደ
መቃብር የከተተና ኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ ስርዓት ሐገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው፡፡”ነው ብሏል።
ፓርቲው አያይዞም በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስትም በሕዝብ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጾአል፡፡
“የዜጎች ነፃነት ሳይከበር ነጻና ፍትኃዊ ምርጫ ሊደረግ አይችልም” ያለውሰማያዊ ፓርቲ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን እስከሚከበሩ ድረስ ፓርቲው በሚያካሂደው የነጻነት ትግል ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አድርጓል፡፡

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog