ብሄርተኝነትን ታጥቀው አገራችንን ወደ አደገኛ ጠርዝ ከሚገፏት ምሁራን መካከል፣ የተወሰኑት ላይ የአቅሜን ያህል ሂስ ለመሰንዘር ሞክሬያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የፕሮፌሰር ጌታቸውን አንዳንድ የተዛቡ ሀሳቦች ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው አንቱ የሚባሉ ምሁርና አንተ የሚባሉ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ጥናቶቻቸውን አንብቦ በእውቀታቸው ስፋት እና በጽሁፍ ችሎታቸው የማይደነቅ ሰው ማግኘት ይከብዳል፡፡ ያም ሆኖ ጌቾ በመጣጥፎቻቸው፣ በግለ ታሪካቸው፣ እንዲሁም የአባ ባህርይ ድርሰቶችን በሰበሰቡበትና ባሰናዱበት ጥራዛቸው የሚያንጸባርቋቸው አንዳንድ የተዛቡና አደገኛ ሐሳቦች አብረው የሚያኗኑሩ አይደሉም:፡
ለምሳሌ በቅርቡ፣ በአንዳንድ የኦሮሞ ብሄርተኞች በኩል ለሚሰነዘሩ ዘለፋዎች ምላሽ እንዲሆን የጻፉትን “ዕርቅና ሰላም፣ የሕይወት ቅመም” የተባለ መጣጥፋቸውን ያነበበ ሰው፤ አንጋፋ ምሁራኖቻችን ከዕርቅና ከሰላም ጋራ እንዴት አድርገው እንዳቆራረጡን መረዳት አያቅተውም፡፡
ጌቾ፣ ለአገሪቱ ቅርስ ውድመት የእስልምና እምነትና የኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ እርግጥ ነው፣ የግራኝ አህመድ ጦር ወደ መሀል አገር በዘመተ ጊዜ እንዲሁም የኦሮሞ ገዳ ጦር አንዳንድ የአገሪቱን ክፍሎች በጦር ባስገበረ ጊዜ አያሌ ሰብአዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች ላይ ውድመት መድረሱ የተረጋገጠ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አውዳሚነትን ከአንድ ብሄረሰብ እና ከአንድ ሀይማኖት ጋር አያይዞ ማቅረብ አድልኦ እንጂ እውቀት ሊሆን አይችልም፡፡ ዋናው የውድመት ምንጭ ሁሉም ብሄረሰቦችና ሁሉም ሀይማኖቶች የሚጋሩት የጦርነት ባህላችን ነው፡፡ በጦርነት ወቅት ክርስትያን ነገስታትም ቤተ-ክርስትያን አቃጥለዋል፡፡ ቅርስ በዝብዘዋል፡፡ ለምሳሌ፣ አለቃ ወልደማርያም በጻፉት ዜናመዋእል ውስጥ በጎንደር ስለተካሄደ አንድ ጦርነት ሲዘግቡ “(ቴዎድሮስ) በጎንደር ቤተክርስትያን በከተማው ውስጥ ያለውን አቃጠሉ፡፡ ከከተማው የራቀው ግን በእግዜር ትእዛዝ ተረፈ” ይላሉ፡፡
ቴዎድሮስ እና አብዛኞቹ ወታደሮቻቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ኦርቶዶክስነታቸው፣ ከሙስሊሙ ወይም ከአገር-በቀል እምነት ተከታዩ የተሻለ ለቅርስ እንዲራሩ አላደረጋቸውም፡፡ ስለዚህ አንዱን እምነት በቅርስ ፈጣሪነት፣ ሌላውን በቅርስ አውዳሚነት መፈረጅ ኢ-ታሪካዊ ይመስለኛል፡፡
ፕሮፌሰሩ በብሄረሰቦች ጥናት ላይ ያላቸውን እውቀት ለማዋጣት ደክመዋል፡፡ ይሁን እንጂ እውቀታቸው በፍርዳቸው ሲበላሽ እናያለን፡፡ የትግራይ ብሄር ተወላጆችን ሳያስቆጡ ስለ ትግራይ፣ የኦሮሞ ተወላጆችን ሳያስቆጡ ስለ ኦሮሞ መናገር ያቅታቸዋል፡፡ ለምሳሌ በአባ ባህርይ መጽሐፋቸው፣ ኦሮሞ የሚለውን መጠርያ በነውረኝነት ከሚጠቀሰው መጠርያ በኋላ የመጣ አስመስለው ለማሳመን ሞክረዋል፡፡ ያ ቃል ከጥንት የኖረ ለመሆኑ ጥንታውያን ጸሐፊዎቹን እነ አባ ባህርይን፣ አለቃ አጥሜንና አለቃ ታዬን በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡
ምክንያታቸው ምንም ይሁን የተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በኦሮሞ ጥናት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን መጽሀፋቸውን ያነበበ ሁሉ የሚረዳው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአድልኦ የነጹ አልነበሩም፡፡ የሚበይኑት ብያኔ፣ የሚጠቀሙት ስያሜ ሁሉ በባእድ አስተያየት የተቃኘ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ በዘመነ መሳፍንት ማክተሚያ ላይ በኦሮሞ መካከል ኖሮ፣ የመስክ ጥናት ያካሄደው አንቶኒዮ ደ አባዲ ኦሮሞዎች ራሳቸውን ኦሮሞ ብለው እንደሚጠሩ ጽፏል፡፡ “የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ” በተባለው ስራው ውስጥ ቃሉን ቸል ብሎ ኦሮሞ የሚለውን ቃል ይጠቀማል፡፡ እንዲሁም የአለቃ አጥሜና የአለቃ ታዬ ዘመነኛ የሆነው ቦረሊ በመጽሐፉ ኦሮሞ የሚለውን ቃል ሲገለገልበት እናያለን፡፡ ይህ የሚያሳየው ቃሉ ዘመን አመጣሽ ሳይሆን የብሄረሰቡ ቤተሰባዊ መጠርያ ሆኖ ከጥንት የነበረ መሆኑን ነው፡፡
ጌቾ፣ ስለ ጥንታዊው የኦሮሞ ወታደር የጦር ዘይቤ ሲጽፉ ያቀረቡት ፍርድ ከርሳቸው የሚጠበቅ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እንዲህ ይላሉ፤
“ድንገት ካልተደረሰባቸው በቀር ምንም ቢሆን ከጠላት ጦር ጋራ ፊት ለፊት ውጊያ አይገጥሙም፡፡ የጦር ሀይል መምጣቱን ሲሰሙ በተገኘው አቅጣጫ ሁሉ ይሸሻሉ፡፡ ሲሸሹ ገደል አይመልሳቸውም”
ይህን ፍርድ፣ በጌቾ አእምሮ ውስጥ እንጂ በእውነተኛው ታሪክ ውስጥ አናገኘውም፡፡ የአባ ባህርይ ዘመነኛ የሆኑት የኦሮሞ ተዋጊዎች ስመ-ጥር ጀግኖችና ድል ነሺዎች እንደነበሩ ከጠላት ወገን የሆኑ መንገደኞች ሳይቀር መስክረውላቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ፓንክረስት በገላውድዮስና በኦሮሞ አስገባሪዎች መካከል የተደረጉ ጦርነቶችን በማስመልከት ቤርድሙዝን ጠቅሶ ሲጽፍ ይህን ይላል
“ስለ ኦሮሞዎች ችሎታና በንጉስ ገላውዲዎስ ላይ የተቀዳጁትን ድል አስመልክቶ ቤርድሙዝ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ከአንድ ውጊያ በኋላ ንጉሱ የረባ ነገር ሳይፈጽም፣ ተረትቶና ደካክሞ ወደ ሰፈሩ ተመለሰ፡፡ ከጥቂት አለፍ ብሎ ቤርድሙዝ፣ ንጉሱ በኦሮሞዎች ተሸንፎ በውርደት ለመሸሽ መገደዱን መዝግቧል›› (The Ethiopian borderlands. ገፅ 284)
(Testimony to the prowess of the Oromo, and some of their victories over Emperor Gelawdewos is given by Berdumus. He records that the Monarch after one battle against the Oromos returned to his camp “wearied and almost defeated without accomplishing anything of value. Not long after this he reports that the Emperor had been defeated by the Oromos..Galawdeos had been obliged to flee “with great indignity”)
ኦሮሞ እንደ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች የጀግንነት ተሰጥኦ እንደታደለ የሚየሳዩ ብዙ ምስክርነቶች አሉ፡፡ ጌቾ እኒህን ምስክርነቶች አይተው እንዳላዩ ሆነው፤ “ካልተደረሰባቸው በቀር ፊትለፊት አይገጥሙም፡፡ ሲሸሹ ገደል አይመልሳቸውም” እያሉ መጻፍ እርሳቸውን ለሚያክል አንጋፋ አረጋዊ ምሁር አይመጥንም እላለሁ፡፡
ጌቾ በቅርቡ በኢንተርኔት ሚድያ ላይ በለጠፉት መጣጥፋቸው “የኦሮሞ ወረራ” ስለሚሉት ሲጽፉ፤ “ከግድያቸው ሰለባቸው ይብስ ነበረ። ባለቅኔው “ጃዊ ቀደደ ሆድ ሆዶሙ ወሰለበሙ እስከ ሕምብርት (ጃዊ ሆድ ሆዳቸውን ቀደደው ሰለባቸው እምብርታቸው ድረስ ሰለባቸው”) ያለው በጎንደር ቤተመንግስት የደረሰውን መቅሰፍት አይቶ ነው፡፡” ብለዋል።
ጌቾ በጎንደር ቤተ-መንግስት ደረሰ የሚሉትን መቅሰፍት ያስረዳልኛል ብለው ይህንን ቅኔ መጥቀሳቸው አስገራሚ ነው፡፡ የቅኔው መነሻ ታሪክ እርሳቸው ከሚሉት እንደሚለይ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ንጉስ ዳዊት በተባሉ የጎንደር ንጉስ ዘመን በቅባቶችና በደብረሊባኖሶች መካከል የሀይማኖት ውጥረት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ንጉስ ዳዊት ለቅባት ወገኖች አዳልተው፣ እምነታቸውን አልቀበል ብለው አሻፈረኝ ያሉትን የደብረሊባኖስ ባህል ተከታይ ካህናትና ከነ እጨጌያቸው ለመቅጣት ጃዊ የተባለውን ሰራዊታቸውን ላኩባቸው፡፡ የጃዊ ሰራዊት አባላት ካህናቱን ከመግደል አልፈው በመስለባቸው የተደሰተ አንድ የቅባት ባለቅኔ፤
“ሶበ እንቢ ለግዜር ይቤሉ ወእንቢ ለንጉስ ዳዊት
ጃዊ ቀደደ ሆድ ሆዶሙ ወሰለቦሙ እስከሕንብርት” እያለ አላገጠ፡፡ ትርጉሙም፣
“እግዜርንና ንጉስ ዳዊትን እምቢ ባሉ ጊዜ
ጃዊ ሆድ ሆዳቸውን ቀደደው፣ እስከእንብርታቸው ሰለባቸው›› የሚል ነው፡፡
ይህ ሁነት ዳዊት የተባለ የጎንደር ንጉስ በሱ አይን አማጺ ሆነው ያገኛቸውን ዜጎች በግፍ ማስቀጣቱን ከመግለጽ አልፎ የኦሮሞ ወረራን ለማስረዳት የሚጠቀስ ታሪክ አይሆንም፡፡ የጃዊ ጦርም ልክ ዛሬ፣ አጋዚ እንደሚባለው ልዩ ሀይል የቤተ-መንግስት ፈቃድ አስፈጻሚ እንጂ ነጻ ሚና አልነበረውም፡፡
መስለብም ቢሆን የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የትግራይና የአማራ እንዲሁም የከፋ ተወላጅ ወታደሮች ሁሉ ባህሪ ነበር፡፡ ጌቾ፣ በስራዎቻቸው ላይ ደጋግመው በሚጠቅሱት እሸቴ ሐይሉ ባስጻፉት ዜና መዋእል ላይ፣ የአድዋው ራስ ሚካኤል ስኡል ሰራዊት ሰለባ ማቅረቡ ተመዝግቧል፡፡ በወላይታ ዘመቻ የተሳተፈው ፈረንሳዊው መንገደኛ ቫንዳየር፣ ምኒልክ የመስለብ ባህልን በአዋጅ ለማስቀረት ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው፣ በዘመቻው ላይም አማሮችና ኦሮሞ ወታደሮች በሰለባ መሳተፋቸውን ጽፏል፡፡ ስለዚህ ሰላባን የአንድ ብሄረሰብ ገጽታ ብቻ አድርጎ ማየት ልክ አይደለም፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው የታሪክ እውነት ሲመሰክሩ እንኳን ሞገደኛ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም ይመርጣሉ፡፡ ይህ አቀራረብ ሰዎች እውነት የሚባለውን ነገር እንዲጠየፉና እንዲፈሩ እንጂ እንዲቀበሉ አያደርጋቸውም፡፡
ለምሳሌ ከላይ በጠቀስኩት መጣጥፋቸው ጌቾ፣ “አጤ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጨ ስፍር ቁጥር በሌለው ጎሳ የተበታተኑትንና የርስ-በርሳቸው የሚባሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አንድ ያደረጉበትን ቀን (የኦሮምኛ ተናጋሪዎች) ማክበር አለባቸው” ይላሉ፡፡ የምኒልክ የማስገበር ጦርነት የማታ የማታ ርስበርስ የተበታተኑት በርስበርስ ወጊያ የሚታመሱትን ጎሳዎች መሀል አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ማስገኘቱ እውነት ነው፡፡
አፍቃሬ ኦሮሞ የሆነው ደ ሳልቪያክ የኦሮሞ ጎሳዎችን የርስ-በርስ ብጥብጥ ታሪክ በሰፊው ካተተ በኋላ፤ “የኢትዮጵያ ተጻራሪ የሆኑ ዘሮችን ወደ አንድ ትልቅ አገርነት በመለወጥ ንጉሱ (ምኒልክ) አቢሲኒያን ያለ ማቋረጥ ሲያምሳት የነበረውንና የኦሮሞ ጎሳቸዎችን ወንድም በወንድሙ ላይ የሚያስነሳ ትግል እንዲቆም ማድረግ ችለዋል” የሚል ነው፡፡ (By uniting the divided enemies of the Ethiopian races into an all immense nation the Negus has stopped the scourge of feudal wars which endlessly ravaged Abyssinia, and has suffocated the fratricidal struggle of the Oromo tribes) ይላል፡፡
ጌቾ ይህንን ብርቅ እውነት፣ በብሽሽቅ መንፈስ አቅርበው አረከሱት፡፡
asfaw_damte
ደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ ናደው፣ የተወለዱት መጋቢት 1ዐ ቀን 1927 ዓ.ም. አዲስ አበባ ጊዮርጊስ አካባቢ፣ መርሐ ጥበብ
ማተሚያ ቤት ግቢ ከሚባለው ቦታ ነው፡፡
አቶ አስፋው የቤተ ክህነት ትምህርት ለጥቂት ጊዜ ከተማሩ በኋላ፣ በዘመናዊ ትምህርት፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃን፣ በኮከበ
ፅባሕ ቀ.ኃ.ሥ. አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በመጀመሪያ ዲግሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ
በእንግሊዙ ኪምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተምረው ተመርቀዋል፡፡
ወደሥራ ዓለም ከተቀላቀሉ በኋላ፣አብዛኛውን የሥራ ጊዜያቸው በገንዘብ ሚኒስቴር በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ያገለገሉ ሲሆን፣
ከገንዘብ ሚኒስቴር እንደለቀቁ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ድርጅትና በኩራዝ አሳታሚ ሠርተዋል፡፡
አቶ አስፋው ከኢትዮጵያ ውጭ ካሳለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ፣ በእንግሊዝ ለትምህርት ሶስት ዓመት፣ ቀሪውን አራት ዓመት
ደግሞ በአሜሪካ በሥራ ነበር::

በድርሰቱ ዓለምም፣ “አንድ ለአምስት” የተሰኘ ረጅም ልቦለድ ያበረከቱ ሲሆን፣ በደራሲያን ማኀበር ካሳተመው በ“የዘመነ
ቀለማት” መፍሐፍ ላይ በአጫጭር ግጥሞቻቸው፣ በ‹‹እነሆ››መድብል ደግሞ በአጫጭር ታሪኮች ተሳትፈዋል፡፡ከዚህም
በተጨማሪ ከ1970 እስከ 90ዎቹ ዓመታት ድረስ ስለ አማርኛ ጥበበ ቃላት አንዳንድ ነጥቦችን ከስር ጀምረው መጣጥፎችን

አበርክተዋል፡፡
ደራሲና ሐያሲ አቶ አስፋው ዳምጤን የረጅም ጊዜ ጓደኛቸው ከነበረውና የደርግ ጅቦች ሰለባ ከሆነው ታዋቂውና ተወዳጁ ደራሲ
በዓሉ ግርማ ከሚወደው ሕዝብ ጋር የመጨረሻው በነበረችው ምሽት ከአቶ አስፋው ዳምቴ ጋር በሰላም አብረው ከተዝናኑ
በኋላ ፣ተሰነባብተው ሌላ ታሪክ እስኪፈጠር ድረስ፣በአንዲት ግሮሰሪ ደጅ ላይ አብረው አብረው ነበሩ፣
መጽሔታችንም “ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የቀበረ” እንደሚባለው፣ስለበዓሉ ግርማ የመጨረሻዋ ምሽት በዝርዝር
እንዲነግሩን አቶ አስፋው ዳምጤን ጋብዘናቸዋልና እነሆ::
bealu-girma1ፍቱን፦- የደራሲ በዓሉ ግርማ ባለቤት፣ ወ/ሮ አልማዝ አበራ፣ ‹‹…የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም. ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ
እቤት ስልክ ደወለ :: በዓሉ ቤት አልነበረምና፣ ስልኩን አንሥቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ :: የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን
በኋላ፣ ‹… በዓሉ እንደመጣ እዚያ እቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ …› ብሎ ስልኩን ዘጋ ::››
ብለዋል:: እውነት ነው ?

አቶ አስፋው፦ የዚህ አጭር መልሱ ‹ሐሰት ነው› ነው:: ይኸንኑ መልስ ለሚያዚያ 8 ቀን ውንጀላቸው፣ በሚያዝያ 15 ቀን
1989 እፎይታ ጋዜጣ ላይ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት ሰጥቼያለሁ ::
በዚያው ወቅት ስለዚያች ዕለት የበዓሉ ከቤት አወጣጥ ፣ Black Lions (ብላክ ላየንስ) የተባለ፣ የበርካታ ኢትዮጳውያን
ደራስያንን የሕይወት ታሪክ እና ሥራዎ ቻቸውን ለማስተዋወቅ የሚጥር መጽሐፍ ደራሲ፣ ሞልቬር፣ እርሳቸዉ ነገሩኝ ብሎ
የጻፈው፣ አንድ ጓደኛው እቤቱ መጥቶ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ እርሳቸው አንድ መጥፎ ነገር ይሆናል የሚል ስሜት
ተሰምቷቸው መሔዱን ቢቃወሙም ይዞት ሔደ፤ በዚያውም ቀረ የሚል ነው::
እንግዲህ ስለ እዛች ዕለት ከቤት አወጣጡ የቀረበው መረጃ የተጋጨ ስለሆነ ወይ ስልክ ደውሎ ጠራውና ሔደ ወይም
መጥቶ ይዞት ሔደ ይበሉ፣ አንዱን ይምረጡ የሚል ነበር የኔ የዚያን ወቅት ጥያቄ::
ሐቁ ግን፣ በዚያች ዕለት እንዳጋጣሚ ሆኖ፣ ስልክ አልደወልኩለትም፣ ቤቱም አልሔድኩም ነበር:: ምክንያቱም፣ የአዲስ አበባ
ክልልን የዐሥር ዓመት የአብዮት ታሪክ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ ተሳታፊ በመደረጌ፣ የሥራ ውጥረት ገጥሞኝ አመሽ ስለ
ነበረ ነበር::
በዚያችው ምሽት ግን፣ ስድሰት ኪሎ በሚገኘው በአዲስ አበባ ኢሠፓአኮ በስብሰባ ቢሮ ሌሎቹ ከሔዱም በኋላ አመሻሽቼ
ወደ ቤቴ ስጓዝ ማምሻ ቦታችን አካባቢ ስደርስ፣ ‹ለመንገድ› ለማለት በተለመደችው ቦታችን ለማቆም አዙሬ አቆምኩ:: አንድ
ወጥ ጽሑፍ ለማቀናበር እንድንችል በቀረቡልን የየቀበሌ፣ ከፍተኛ፣ ቃጣና እና የተቋማት የ10 ዓመታት የታሪክ ዘገባ
መረጃዎች ጭንቅላቴ ተሞልቶና ስቆዝም ቆየሁ:: ወደ ሦስት ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል ፣ የበዓሉን የመኪና ክላክስ ሰምቼ ዞር
ስል፣ መኪናው ውስጥ አየሁት:: የመጣበት አግጣጫ የቤቱ ስላልነበረ፣ የት እንዳመሸ ገመትኩ:: መኪናዋን ባለችበት ትቶ፣
በእግሩ መንገዱን ረጋ ብሎ አቋርጦ መጣና እኔ መኪና ውስጥ ገባ:: ብዙም የረባ ነገር የምናወራው ስላልነበረን ይሆናል ትዝ
የሚለኝ የለም:: እንደኔው ደከም ያለው መሰለኝ:: ካሰብኩት በላይ በመቆየቴና እሱም የሚሔደው ወደ ቤቱ ስለነበር ብዙ
አልቆየንም:: ሃያ ቢበዛ ሠላሳ ደቂቃ ቢሆን ነው:: መኪናዬን አዙሬ መኪናው ጎን አቁሜለት ሲወርድ እኔ ወደፊቴ ቀጠልኩ::
እየተጠባብቅን አልነበረም የምንሔደው ሁሌም ቢሆን::
ስለዚህ፣ ተቀጣጥረን ሳይሆን በእንደዚያ ዐይነት አጋጣሚ ግን ተገናኝተን ነበር ያችን ዕለት::
አሁን ደግሞ በአበራ ለማ በተበተነው የ16 ገጽ ሐተታ ውስጥ በገጽ 6 ላይ ጓድ ቁጥር ኀምሳ ሦስት ከተሰኘ ባለሥልጣን፣
‹‹…ወደ ማታ በዓሉን የደህንነት ሰዎች ይዘውት እንደሄዱ ከቤተሰቡ ሰማሁ…›› የሚል ባለቤቲቱን ያይን ምስክርነት የሚሰጡ
የሚያስመስላቸው ‹መረጃ› ያስነብበናል:: ምን ማለት ነው; በእርግጥ ባለቤቲቱ ለባለ ሥልጣኑ ይኸን መረጃ ሰጥተዋል ሊለን
ነው ዐላማው; ሞኙ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ ሆነበትሳ !
ፍቱን፦ በዓሉ እርሶ ጋ ከመድረሱ በፊት የት ቆየ ብለው ነበር የገመቱት?
አቶ አስፋው፦ ጥቂት ቀደም ብሎ እዚያው አካባቢ ወዳጅ እንደነበረው ተገንዝቤ ነበር ::
ፍቱን፦ የማን ቤት ነው ?
አቶ አስፋው፦ እሱን አላውቅም ::
ፍቱን፦ ወንድ ሴት?
አቶ አስፋው፦ ሴት::
ፍቱን፤ በዚያች ዕለት ምሽት እዚያ ቆይቶ ከተመለሰ በኋላ ነበር ከእርሶ ጋር የተገናኛችሁት?
አቶ አስፋው፦ እንደዚያ ነበር አመጣጡን ሳይ የገመትኩት::
ፍቱን፦ የቅርብ ጓደኛ እንደመሆንዎ ምናልባት ለመምከርም ለመገሠጽም አልሞከሩም?
አቶ አስፋው፦ በአዘቦቱ ከምንወያይባቸው ርእሰ ጉዳዮች ውጭ ነበረ:: የእኔና የርሱ ቁልፍ ጉዳይ ድርሰትንና ተዛማጅ
ጉዳዮችን የሚመለከት እንጂ ሌላውን የሕይወቱን ክፍል የግሉ ብቻ አድርጌ ነበር የማየው:: ከዚያ ያለፈ ነገር እርሱ
በአጋጣሚ በሚያነሣቸው ጉዳዮች ነው የምናተኩረውና ይኸ ተነሥቶ አያውቅም፡፡
ፍቱን ፦ እርሶና በዓሉ በየሳምንቱ ሮብ ካልሆነ ኀሙስ አለዚያ ዐርብ ትገናኙ የነበረበት የተለየ ምክንያት ነበራችሁ?
አቶ አስፋው፦ አዎን፤ እኔንና እርሱን የሚመለከት ትንሽ የግል ጉዳይ ነበረች::
ፍቱን፦ አሁን መግለጽ አይፈልጉም?
አቶ አስፋው፦ ከዋናው ጉዳያችን ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌለውና ለማንም የሚጠቅም (ወይም የሚጎዳ) መረጃ አይደለም::
ግን የግል ነገር ነው::
ፍቱን ፦በዚያች ምሽት ስንት ሰዓት ላይ ተገናኛችሁ?
አቶ አስፋው፦ ወደ ሦስት ሠዓት ግድም ነው :: በትክክል አላሳተውስም ::
ፍቱን፦ የዚያን ምሽት የበዓሉ አለባበስ እንዴት ነበር?
አስፋው፡- እንደ ሁሌውም ሽቅርቅር ያለ ነበር ማለት ይቻላል:: ቡላ ቀለም የሆነ ሙሉ ልብስ መሰለኝ:: ልብ ብዬ
ያተኩርኩበት አልነበረም:: ዐይኑ ላይ ኦይንትመንት ብጤ ያየሁ መስሎኛል::
ፍቱን፦ ድካም ያዩበት ለምን ይመስልዎታል?
አቶ አስፋው፦ እንደርሱ ንቁ የሆነ ተንቀሳቃሽና በሥራ ውጥረት ውስጥ የቆየ ሰው ያለ ፈታኝ ሥራ ውሎ ሲያመሽ ይህ
ዐይነት ስሜት የሚያድርበት ይመስለኛል:: ጊዜውም እየተማሸ በመሔድ ላይ መሆኑን ማሰብ ይኖርብናል:: የኔም መንፈስ
ብዙ የነቃ መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም:: በውሎዬ ስላጋጠሙኝ አንዳንድ መንፈስ መሳጭ ስሜት ቀስቀሽ ስለሆኑ የቀበሌና
የከፍተኛ የታሪክ ሰነዶችና መረጃዎች እርሱ ከነበረበት ሁኔታ ለመወያያ አመቺ አልነበሩና የሚነሡ አልነበሩም ከርሱ ጋር::
ፍቱን፦ ከበዓሉ ሁኔታ ወይም ከአካባቢው የታዘቡት የተለየ ነገር ነበር?
አቶ አስፋው፦ ምንም የታዘብኩት ነገር አልነበረም:: መኪናዬን ሲያይ ምንም ሳይል ዐልፎኝ መሔድ ስለማይችል መጣ
እንጂ ጊዜው ለተለምዶው ዐይነት
ውይይት አመቺ ሆኖ አልነበረም የመጣው:: እንዳልኩህ ያኔ ሰዓቱ ሁለታችንም ወደየቤታችን ለመሔድ መንፈሳችን
ያዘነበለበት ሁኔታ ነበር::
ፍቱን፦ ስንት ሰዓት አካባቢ ተንቀሳቀሳችሁ?
አቶ አስፋው፦ ከሦስት ሠዓት ቢያልፍም ብዙ አይመስለኝም::
ፍቱን፡- ስትለያዩ፣ በዓሉ ወዴት እንደሚሔድ ያውቁ ነበር?
አቶ አስፋው፦ ወደ ቤቱ ነዋ! የእኔን መኪና አይቶ የቆመው ወደ ቤቱ አግጣጫ እየነዳ ሳለ ነበር:: መኪናው ዘንድ ሳደርሰው
ጉዞውን ነው የሚቀጥለው:: ለእኛ ያቺ ምሽት እንደሌሎቹ ሁሉ አንድ ሌላ ምሽት ነበረች! ከመምጣቱ ዐምስት
ደቂቃዎች ቀደም ብዬ ሔጄ ቢሆን ኖሮ፣ በዚያች ማታ አንተያይም ነበር::
ፍቱን፦ የበዓሉን መሰወር የሰሙት በምን ሁኔታ ላይ ሆነው ነበር?
አቶ አስፋው፦ በማግሥቱ ጧት ወደ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ ነበር:: ወደ አዲስ አበባ ኢሠፓአኮ ለመሔድ እየተደራጀሁ
ሳለ፣ ባለቤቱ ደወለችልኝ ::
ፍቱን፦ወ/ሮ አልማዝ፣‹‹በዓሉ የማታ ማታ ወደቤት ይመለሳል ብዬ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብጠብቅም የውሃ ሽታ
እንደሆነ ቀረ፡፡ ቢቸግረኝ አስፋው ቤት ደወልኩ፡፡ ሚስቱ ስልኩን አነሳች፡፡ ’…አስፋው እቤት ገብቷል?…’ ስል ጠየቅኋት፡፡
’…አዎን ገብቷል…’ አለችኝ፡፡ ይሄኔ ግራ በመጋባት፤ ’…ባሌን ከቤት ጠርቶ ወስዶት የት ጥሎት ነው እሱ ተቤቱ የገባው?…’
እያልኩ አፋጠጥኳት፡፡ ቀጥዬም ’እስኪ አቅርቢልኝና ላናግረው…’ ስላት፤ ’የገባ ምስሎኝ ነበር እንጂ አልገባም’ ብላ
የመጀመሪያ ቃልዋን አጠፈችብኝ፡፡ የስልክ ንግግራችንም በዚሁ ተቋጨ›› ብለዋል እውነት ነው?
አቶ አስፋው፦ ሐሰት ነው
ፍቱን፦ መሥረያ ቤት ነበር የደወሉት?
አቶ አስፋው፦ አዎን፣ ኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት እኮ ነው ! እዚያኛውማ ገና ልሔድ ነው ::
ከዚያ፣ ‹‹በዓሉ እኮ ትላንት ማታ አልገባም:: አልተገናችሁም ነበር ወይ;›› ስትለኝ ያመሸበት ትዝ ብሎኝ ነበርና፣ ‹‹አይቸዋለሁ፣
ግን›› ብዬ የምለው ጠፋኝና፣ ‹‹አሁን የምሔደው አንድ ትልቅ ባለሥልጣን ዘንድ ለስብሰባ እንዲህ ዐይነቱን ነገር ለማጣራት
ችሎታ አለው:: በከተማው ውስጥ የሚካሔደው ነገር ሁሉ የሚዘገብለት እርሱ ስለሆነ አነጋግሬ ሁኔታውን አጣራለሁ››
አልኳት:: አዲስ አበባ ኢሠፓአኮ ጽሕፈት ቤት እንደረስኩ በቀጥታ ወደ በላይ ኀላፊው ቢሮ ገብቼ ነገሩን አነሣሁ:: ‹‹አንድ
ቦታ (ጾታን ጠቁሞ) አድሮ ይሆናል ነገ ብቅ ይላል ››አለኝ አቃሎ:: እኔም ይኸ ሊሆን እንደማይችልና ማታ ከዚህ ወደ ቤቴ
ስሔድ እንደተገናኘንና ስንለያይ ወደ ቤቱ እያመራ እንደ ነበር አጠንክሬ ገለጽሁ:: ከዚያ፣ ቆይ ብሎ አንድ ቦታ ደውሎ ጥቂት
ከተነጋገረ በኋላ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ገለጸልውልኛል፣ አሁንም ጥቂት አሰብ አደረገና ሌላ ቦታ ደውሎ ተናጋገረ::
ውጤቱ ምንም ለውጥ አልነበረውም:: በዓሉን የሚያህል ሰው ጠፍቶ የአዲስ አበባን አጠቃላይ ሁኔታ የማወቅ ዐቅም ካለው
ከዚህ ቢሮ ተሰውሮ ብዙ እንደማይቆይ ተስፋ ያለኝ መሆኑን ተናግሬ ወደ ስብሰባ ቢሮው ሔድኩ ::
ፍቱን፦ ያ ባለሥልጣን ማን ነበር ?
አቶ አስፋው፦ ኮማንደር ለማ ጉተማ ነበር :: በትምህርት ቤት ዕውቂያ ስለነበረን ነው የሚቻለውን ያህል ሊጥርልኝ ይችላል
የሚል ተስፋ የነበረኝ ::
ፍቱን፦ ኮማንደር ለማ የት እና የት የደወሉ መሰለዎት?
አቶ አስፋው፦ ስለ አዲስ አበባ የየዕለት ሁኔታ የሚያሳውቁት አካላት ዘንድ ነው ብዬ ነበር የገምኩት::
ፍቱን፦ ደህንነት መሥሪያት ቤት ማለት ነው?
አቶ አስፋው፦ ሊሆን ይችላል:: ልዩ ክፍሎችም ሊኖሩት ይችላሉ፣ አላውቅም::
ፍቱን፦ ያንለት ወ/ሮ አልማዝን በድጋሚ አግኝተዋቸው ነበር?
አቶ አስፋው፦ አዎን፣ በስልክ ይሁን በግምባር፣ ምንም ፍንጭ ለጊዜው ባላገኝም፣ ተስፋ እንዳልቆረጥኩ ነግሬያት ነበር ::
ፍቱን፦ የበዓሉን መሰወር ጉዳይ እርስዎ የምር ነበር ያዩት ወይስ …?
አቶ አስፋው፦ አዎን ግን ደግሞ አንዳንድ የገለጻቸውን ሁኔታዎች የሚከርር አይሆን ይሆን የሚል ልብ ከፋይ ስሜት
መነሻው ላይ ልቤን ያሟግት ነበር:: ለምሳሌ፣ ቀደም ብሎ ባንድ ወቅት ታሰረ የሚል ወሬ ተነዝቶ ነበር:: ያን ወቅት ኢትዮጵያ
መጻሕፍት ድርጅት ድረስ ይመጣ በነበረበት ጊዜ፣ ልክ ከእኛ ዘንድ ተመልሶ እንደሔደ፣ አንድ ሰው ደውሎ ስለ መታሰሩ
ነገረኝ:: ግን፣ እኛ ዘንድ መጥቶ እንደነበርና ዝም ብሎ ወሬ ነው ማለቴን አስታውሳለሁ:: ከዚያ በኋላም እርሱው ከቤተ
መንግሥት አካባቢ ቤቱ ተደውሎ ስለ ደህንነቱ የተጠየቀ መሆኑን ነግሮኝ ነበር:: ሆኖም ሙሉ ለሙሉ መተማማን አስቸጋረ
ነበር:: ከኦሮማይ ጋር መያያዙ ታሳቢ ጉዳይ ስለሆነ ስለ ነገሩ ክብደት ማመን ፍጽም አልነበረም::
ፍቱን፦ መንግሥቱ ናቸው የደወሉት?
አቶ አስፋው፦ ማን እንደሆነ ተነግሮት እንደሁ አልነገረኝም:: እኔ ግን ሊሆን ይችላል ብዬ አላሰብኩም፣ አልመሰለኝም::
ፍቱን፦ ስለዚህ የምር ይሆናል ብለው አላሰቡትም ነበር?
አቶ አስፋው፦ አጽናኝነት ያላቸው ምልክቶች ሆነው ቢታዩም ቀላል አድርጎ የሚታይ ነገር አልነበረም :: እርግጥ መንፈስን
አዋዥቋል:: ከዚያ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ፈልጉ አፋልጉ የሚል ቴሌግራም እንደተበተነ ሰማሁ:: በዚያው ሰሞን
ከበዓሉ ጋር ቅርብ ግንኙነት አላቸው ተብለው ከታሰቡ ውስጥ ይመስለኛል ሦስት ሰዎች በተናጠል ተጠርተው ስለ ጉዳዩ
የሚጠረጥሩት ነገር እንዳለ እንዲጠቁሙ ፍንጭ ካገኙ ደውለው እንዲያሳውቁ ስልክ ቁጥር ተሰጣቸው :: ከሦስቱ ሁለቱ
ባለቤቱና እኔ ነበርን ::
ፍቱን፦ ማን ነበር የጠየቀዎ?
አቶ አስፋው፦ መልኩን እንጂ ስሙን አላውቀውም ::
ፍቱን፦ ወ/ሮ አልማዝ በርስዎ ላይ ቅያሜ ለምን ሊያድርባቸው ቻለ?
አቶ አስፋው፦ በዓሉ ከተሰወረ በርከት ያለ ቀናት ቆይቶ፣ ወ/ሮ አልማዝ ‹‹የበዓሉ መኪና ቃለቲ መንገድ ላይ ቆማለች አሉ፣
ሔደን እናምጣት›› አለችኝ ቤቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ደውላ :: ‹‹ይኸንማ ማድረግ አንችልም:: በተሰጠሸ ስልክ ቁጥር ደውለሽ
አሳውቂ እንጂ ከነረው ሁኔታ እንደፈለገን ማድረግ አንችልም ::››፣
ከዚያ በነገሯ ሁሉ የማላውቃት ሰው ዐይነት ሆነችብኝ:: ከመነሻው ብዙ ትውውቅም አግባብም አልነበረንም:: የኔ ጉዳይ
ከባዓሉና ከድርሰቱ ጋር እና በውጭ ነበር ::
ከሥራ ከታገደ በኋላ ቤቱ መሔድ ግድ ሆነ ፤ እኔና እርሱ መገናኘት የምንችልበት ዋና ቦታ ያ ብቻ ሆና ነው :: እርሱ ሳይኖር
ቤቱ ከማን ለመወያየት ነው እንድሔድ ይጠበቅ የነበረው:: ቀድሞም ቤት ለቤት የመጠያየቅ እና ያን ዐይነት ማኅበራዊ
ግንኙነት አልነበረንም :: ያኛው ለሁለታችንም ሌላ ዐውድ ነበር :: እርሱ የራሱ እኔም የራሴ ነው የነበረን::
ስለዚህ፤ ለዚህ እና ለተለያዩ የእርሷ ውንጀላዎችም ሆኑ ስሞታዎች
ትክክለኛው መልሱ የሚገኘው ከእኔና ከበዓሉ የግንኙነት ዐይነትና መሠረታዊ ባሕርይ ነው :: ነገር በመደጋገም አዲስ እውነት
አይፈልቅም:: ስለ እርሳቸው አመለካከት ትክክሉን ነገር ለማግኘት የምር ለማወቅ በየጊዜው የሰጧቸውን በርካታ ቃለ
መጠይቆች እያገናዘቡ ማንበብ ነው::
አሁን የተበተነውና መጽሔቶችን እያጣበበ ያለው ሰፊ ሐተታ ገሐድ ያወጣው ቁምነገር፣ ሚያዝያ 8 ቀን 1989 በወ/ሮ
አልማዝ ስም ከመነሻ የውንጀላ ጽሑፍ አንሥቶ ሐተታው ውስጥ በስማቸው የወጣው ሐሳብ ሁሉ ከነቃላቱ የእርሳቸው
እንዳልነበረ ነው :: ሰው ትኩረት እንዲሰጠው የበዓሉን ስም ሽፋን አድርጎ የራሱን ቂም፣ በቀልና እና ብሶት ለማሰተላለፊያ
የተጠቀመበት ሆኖ ነው የሚገኘው ጽሑፉን በታኙ :: እውነት ፈላጊ ፈልፍሎ እንደሚደርስበት ጥርጥር የለኝምና፣ ይኸኛውን
በዚህ ጨርሻለሁ::
ፍቱን፦ በዚህ ጉደይ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጠይቀው ያውቃሉ?
አቶ አስፋው፦ አልተጠየቅሁም:: የፍርድ ቤትን ፍጹም አሉቧልታ መች ይቋቋመዋል; ቀደም ሲል አሉቧልታን ይዞ ወደ
መገናኛ ብዙኃን መሔድ ይቀል ነበር:: አሁን ያ በር እየጠበበ ይመስለኛል::
ፍቱን፦ በእርስዎና በበዓሉ መካከል ቅያሜ ወይንም አነሥተኛ ቁርሾ ነበር?
አቶ አስፋው፦ የምን ቁርሾ አመጣህብኝ:: ቀድሞ መች ለበቂ ጊዜስ ተገናኝትን:: በጽሑፉ አድናቂው ነኝ ፤ ሒሳዊ ትችት
የሚጠላ ሰው አልነበረም:: በሙያና በመሥሪያ ቤት የተለያየን ነን:: ስለዚህ፣ ላልከው ነገር ሰበብም አልነበረም::
ፍቱን፦ ኩራዝ እንዲገቡ በዓሉ ከፍተኛ ውትወታ አድርጎ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው፣ ኋላ በምን የተለየ ምክንያት እዚያ
ገቡ?
አቶ አስፋው፦ ወደ ኩራዝ የመግባቱ ጥያቄ ረዘም ያለ የጊዜ ሒደት የነበረውና ከዚህ ቀደም መልስ የሰጠሁበት ነው:: በዚህ
ረገድ በዓሉ ከብዙዎች አንዱ ነበር::
ይሁንና፣ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው ተስፋዬ አያሌው አንድ የጥበባት ጉዳይ መጽሔት
ለመመሥረት ተነሣሥቶ ከያለበት ጽሑፍ የሚያቀርቡ ሰዎች ሲያፈላልግ በዚያ ሳቢያ ተገናኝተን ተዋወቅን:: ከዚያ፣ ሥነ
ጽሑፍን ለማሳደግ ከልብህ ካሰብክ፣ አሰታሚ ዋና ክፍሉን አጠናክረህ ምራው ብሎ፣ ሊያሠራ የሚችል ሁኔታ
እንደሚያመቻችልኝ አሳመነኝ:: እኔም በኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት ላራት ዓመታት ያህል በተግባርም በንባብም
የቀሰምኩትን ዕውቀትና ልምድ ሰፋ ባለ መድረክ ተግባር ላይ ለማዋል አጓጓኝ:: ከባድ ውሳኔ እያደረግሁ መሆኔም እየተሰማኝ
ነበር :: ይሁን እንጂ ስበቱ አየለና፣ ተደራድሬ የአሳታሚ ዋና ክፍሉ ኃላፊ ሆኜ ተቀጥሬ ገባሁ::
ከ1977 እስከ 1983 የነበረውን የኩራዝ አሰታሚ ድርጅት እንቅስቃሴና ተጨባጭ ውጤት ሳሰተውል ያደረግሁት ትክክለኛ
ውሳኔ እንደነበረ እና በውጤቱም እርካታ ይሰማኛል::
ፍቱን፦ ወዳጅዎን የኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት ባለቤት እንዴት አሳመኗቸው?
አቶ አስፋው፦ ከእርሱ ጋር ቀደም ሲል ከገንዘብ ሚኒስቴር ዘመኔ ጀምሮ ነበርና የምንተዋወቀው፣ ስለሁኔታዎች የጋራ
መግባባት ነበረን:: በዚያው ተወስኜ እስከ ዘለቄታው እንደማልቆይ አስቀድሞ የታወቀ ነበር:: ስለዚህ ለመልቀቅ ችግር
አልነበረም ::
ፍቱን፦ ለበዓሉ መሰወር ከኦሮማይ ሌላ መንሥኤ ይኖራል?
አቶ አስፋው፦ የግንኙነታችን አግጣጫ ሥነ ጽሑፍ አንድ ጠበብ ያለ ገጽታው ነው:: ከዚያ ውጭ ያለ ገጽታው ነው
የሚበልጠው፣ የሚሰፋው:: በዓሉ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረ በዚያ አግጫም ኃላፈነቶች ነበሩበት :: ስለዚህ ከቁንጽል
እይታ ተነሥቶ ትልቅ ድምዳሜ መድረስ አስቸጋሪ ነው::
ፍቱን፦ በእርሶ ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች መካከል አንዱ፣ አቶ አስፋው ሰኔና ሰኞ የሚባለው ገጥሞባቸው ነው እንጂ ፣
ጓደኛቸውን አሳልፈው የሚሰጥ ሰብእና የላቸውም የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ አቶ አስፋው ጓደኛቸውን የሚሸጡ
ሰው አይደሉም፣ ነገር ግን፣ የዚያች ዕለት ምሽት ያዩትን አይተው ለሕይወታቸው ሠግተው ዝም ብለዋል የሚል ነው?
አቶ አስፋው፦ በኔ ትሑት አስተያየት ከግለሰቡ ሰብእና ተነሥቶ፣ አንድ ሰው ምን ዐይነት ተግባር ለመፈጸም እንሚችል እና
እንደማይችል ለመመዘን ለማየት መነሣት ትክክለኛ የብየና መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ:: እኔን በሚመለከት ከነገርከኝ
የሁለተኛው ወገን መላምት እንዳጋጣሚ ሁኖ የተከሰተ ሐቅ አልነበረም:: ያመሸንበት አካባቢ ለዚህ ግብ የሚመረጥ ይሆናል
ብዬ አልገምተውም:: የሆነው ሁኖ፣ ያችን ምሽት በዓሉን የሚመለከት እኔ ያየሁትና ያስፈራኝ ክስተት አልነበረም:: ስለዚህ፣
አይቼ ዝም ያልኩት ወይም የደበቅሁት ነገር እንደሌለ በእርግጠኝነት እናገራለሁ:: ይኸን መቀበል አለመቀበል የእምነት ጉዳይ
ሊሆን ይችላል::
ነገር ግን፣ ከዚህ ዘልዬ አጋጥሞኝ የነበረ ቢሆን ኖሮ የሚለውን ማሰብ አያስልገኝም:: አላጋጠመም በቃ! ብዬ አቆማለሁ::
ፍቱን፦ ሰው በበዓሉ መሰወር እኔን ተጠያቂ አድርጓል የሚል ቅሬታ ወይ ምሬት አድሮቦታል;
አስፋው፦ ፈጽሞ! ኅሊናዬ ንጹህ እና የውስጥ ሰላም ያለኝ ሰው ነው :: ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ፣ በሕግ ፊት ከምኑም ነጻ የሆንኩ
ዜጋ ነኝ:: ከታወቁት ሁለት ወንጃዮቼ ሌላ የማውቀው ሌላ የለም:: የሚጠረጥር ቢኖር መብቱ ነው:: እውነቱን ፈላጊ ከሆነ
ይደርስበታል ብዬ አስባለሁ::
ፍቱን፦በዓሉን በተመለከተ ሕሊናዎ ነጻ ነው?
አቶ አስፋው፦ Absolutely, ምንም:: በበዓሉ ግርማ ጉዳይ ላይ ከሕሊና ዕዳ ነፃ ነኝ:: ለምኑ ብዬ እኮ ነው የምልህ? እንዲህ
አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚጨምረኝን ነገር ለምን አደርጋለሁ? እኔ ሰዎች በጥረታቸው ሲሳካላቸው ደስ ይለኛል:: የሆነ
እርካታ ይሰማኛል፣ ይሄ ባህሪዬ ተቃራኒ ስሜትና ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎችን ያናድዳቸው ይሆን ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ::
እነሱ ተመኝተውት ያጡትን እኔ ሳልፈልግ አግኝቼ ይሆን?
ፍቱን፦ አቶ አበራ ለማ ጋር ከዚህ በፊት ቅራኔ ነበራችሁ?
አቶ አስፋው፦ እኔ ከእሱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቻለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም:: የተገናኘነው ኢትዮጵያ መጽሐፍ ድርጅት ሆኜ
“ሕይወትና ሞት” የምትለው መጽሐፍ እንዲታተምለት የበኩሌን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ:: የ“ማለዳ ስንቅ” የምትለዋን
ኩራዝ እንድትታተም አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ:: በድርሰት በኩል ግንኙነታችን ይሄ ነው::
አንድ ጊዜ ኩራዝ የጀመርናት መጽሔት የመጀመሪያው ሕትም የመሆኑ ጽሑፎች ሰዎች እዲያመጡልን በአዘጋጁተ በስብሐት
ገ/እግዚአብሔር ጥሪ ተደርጐ ስለነበር ጽሑፋቸውን ካመጡልን ሰዎች መካከል አበራ ለማ አንዱ ነበር::
የሆነ ቀን ስብሐት ቢሮዬ ይመጣና “ይሄንን ነገር አንብበው፣second opinion እፈልጋለሁ” ብሎ የአበራ ለማን ጽሑፍ
ይሰጠኛል:: አነበዋለሁ:: የተጻፈው “ሂስ” ተብሎ ነው:: ሂሱም የሚካሄደው በታዋቂው ገጣሚ በሰይፉ መታፈሪያ “የተስፋ
እግር ብረት” ውስጥ ባለ አንድ ግጥም ላይ ነው:: እንደአጋጣሚ “የተስፋ እግር ብረትን” ሰይፉ መታፈሪያ ሸልሞኝ እጄ ላይ
ስለነበር አውቀዋለሁ:: ሂሱን ሳነበው ትንታው ጥሩ አልነበረም:: ያን ጊዜ አበራ ለማ ገና የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ
መግባቱ ነበር መሰለኝ:: የተማረውን ተግባራዊ ለማድረግ ነው መሰለኝ ያንን ጽፏል:: መደምደሚያውግን ፍጹም ትክክል
ስላልነበረ ይሄንኑ ለስብሐት ነበርኩት:: ስብሐትም የእኔም ሃሣብ ነው ብሎ ተስማማ:: በሁለቱም መጽሐፎቹ ሳቢያ
እንተዋወቃለን በሚል ደውለን አናናግረው ብለን ደውዬ ነበርኩት:: በፍፁም አልተስማማም:: “ተሳስተሃል” አለኝ::
ፍቱን፦ አቶ አበራ ለማ በግጥሙ ላይ የሰጡት ድምዳሜ ምን ነበር?
አቶ አስፋው፦ የግጥሙ መልዕክት ብር ቁፈራ ነው የሚል ነበር የእሱ ድምዳሜ:: በእርግጥ ግጥም ገጣሚ ስለብር መቆፈር
ሊጽፍ ይችላል:: አበራን ወደዚያ ድምዳሜ የመራው ግን የሰይፉ አንዳንድ ፊደሎችን የመደጋገም ስልቱ ነው:: በዚያ ላይ
ተመስርቶ የፈጸመው ስህተት ነው እኔ የመሰለኝ::
(ግጥሙን ቀጥሎ ያለው ነው)
አድካሚ የሕይወትን መልክ ፍለጋ
እፍ እፍ፤ እፍ የጉሽ ገፈት
የጥራት ከለላ
እንትፍትፋት::
..
እፍ እፍ ስልባቦት
የወተት ላይ ውፍረት
እኝካት::
..
እፍ እፍ ግግርት
የውሃ ላይ ቅርፊት
አረንጉዋዴ በቀልት::
..
እንደ ጉሽ ገፈቱ
እንደ ስልባቦቱ
የውሃ ግግርቱ
..
እንደዚያ ደዚያ
እፍልኝ ምሥጢር ከለላ
ሰዋዊ ዐይነ – ጥላ::
..
የሕይወት ምሥጢር
በዘመናት ክምር
ቅበርብርብርብርብር
(እሱን ነው እምቆፍር)::
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው (መስከረም 1969 ዓ.ም)
ፍቱን፦ ከዚህ ሁሉ በኋላ ልትግባቡ አልቻላችሁም?
አቶ አስፋው፦ ‹‹ተሳስተሃል››አለኝ:: ነገሩ እኔ እኮ የስነ ጽሑፍ ተማሪ ነኝ ነው:: “አይ በአንተ ድምዳሜ ያልተስማማሁት እኔ
ብቻ ሳልሆን የመጽሔቱ አዘጋጅ ስብሐትም ጭምር ነው፣ ስብሐትም እንደዚሁ ነው ያሰበው›› አልኩት:: “ሁለታችሁም
ተሳስታችኋል” ሲለኝ፣ “እኛ ስህተት ነው ብለን የምናስበውን መተው እንችላለን፣ ወይም ደግሞ ከComment ጋር
ልናቀርበው እንችላለን:: ‹‹እንዲህ ብለነው ነበር፣ አንባቢ ራስህ ፍረድ›› ብለን ማውጣት እንችላለን፣”ብዬው በመሐሉ፣‹‹
ገጣሚው ራሱ ስላለ ልደውልለት›› ስለው፣ ‹‹ደውልና ጠይቀው›› አለኝ::
ሰይፉ መታፈሪያን ደውዬ የአበራን ድምዳሜ አነበብኩለትና አስተያየቱን ጠየቅኩት::
“እንዴ ብሩን ከየት አመጣችሁት?” ነው ያለው:: ግጥሙ ውስጥ እኮ ብር የለም፣ ማለቱ ነው::
ይሄንን ነገርኩት::
አበራ ለማ አሁንም፣“እሱም ተሳስቷል” አለኝ:: ‹‹ባለግጥሙ?›› ስለው፣ ‹‹አዎን አያሲው እኮ ደራሲው ያላየውን የግጥሙን
አንድ መልክ ፈልፍሎ ያወጣል›› አለ:: ይሄንን መርህ እንደ መርህ አውቀዋለሁ:: እውነትም ይሆናል፣ ይሄኛው ግጥም ግን
በጣም ግልጽ ነው:: የመጀመሪያው አንጓ፣ የሁለተኛው፣ የሶስተኛው አንጓ በግልጽ ያስቀምጠዋል:: አራተኛው ላይ ሲመጣ
ያንኑ ነው:: ያ የሚቆፈረው የህይ ወትን ሚስጢርን ለማግኘት ነው፣ የሚል ነው:: ግጥሙ ራሱ ግልጽ ነው ››አልኩት:: ይሄ
ነው ያስቀየመው::
የነገሩ መቋጫ ይሄ ብቻ አይደለም:: ለካ ማታ ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ ለጓደኞቹ “ሁለት ግጥም የማይገባቸው ሽማግ ሌዎች” እያለ
ወረፍ አድርጐናል:: ሌላው ክፋቱ በዚያን ሰዓት ፣ ስለ ሁለቱ “ግጥም የማይገባቸው ሽማግሌዎች” ማንነትና ስለየትኛው
ግጥም ማለቱ እንደሆነ እየጮኸ ሲያወራ በዚያ በኩል ያልፍ የነበረ አስተማሪው ይሰማዋል ፣አስተማሪው ደግሞ ግጥሙን
ያውቀዋል:: ወዲያውወደ አበራ ቀረብ ብሎ ፣ “የሚያሳፍሪው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ ? አንተ የእኛ ተማሪ ነህ መባሉ
ነው” ብሎት ይሄዳል:: ይኼ መቼም ቅስም የሚሰብር ነው:: ያቺ ትሆን እንዲህ የምታደርገው ብዬ አስባለሁ:: ያ ነው እንግዲህ
በእኔና በእሱ መካከል ተከሰተ የምለው ነገር::

አገሬ ታማለች!


(በካሣሁን ዓለሙ)
እማማ ታማለች፣
አገሬ ታማለች፣
ሆስፒታል ተኝታ
እ!እ!…ህእ!ም!…ህም!!! ትለኛለች፤
ከህቅታዋም ውስጥ ጣሯ ይሰማኛል፣
ህመሟን ስቃዩዋን፣
ዝም ብዬ እየሰማሁ፣
እማዬ! እላታለሁ፤
ህመሟ ያመኛል፣
ጧሯ ይነዝረኛል፣
አዎ! እማማ ታማለች፣
ይኸው በሆስፒታል
እ!!…ህ!!!.. እህ!!!… ትለኛለች፤

በዚህ በሽታዋም፡
የሩቁ ሰው ዐይቶ ምራቁን ይመጣል፣
የተጠጋውም ሰው መርዶውን ይነግራል፤
‹እሷማ አትተርፍም› ብሎ ያሟርታል፤
በደንብ የሚያውቃትም እንባውን ይዘራል፣
በ‹እንዲህ ሆነች በቃ!› ተስፋዬን ይገድላል፤
እማማ! ታማለች፣
ሆስፒታል አልጋ ላይ
‹እ!ህ!… እ!..ም!!!› ትለኛለች፤
ሐኪሙም ብቅ ብሎ ጉዴን ይነግረኛል፣
‹ከእንግዲህ እወቀው በሽታዋ! ከፍቷል፣
የተበከለው ደም በውስጥ ተሠራጭቷል፤
የመቋቋም አቅሟም ከእንግዲህ አብቅቷል፤
ዝውውሩም ሊቆም የቀረው ትንሽ ነው፣
የተበከለው ደም በሙሉ ሲሠራጭ አበቃ ማለት ነው፤›
ብሎ ጉዴን ይነግረኛል፤
አዎ! በጠና ታማለች፣
ሆስፒታል ተኝታ
‹እ!ህ!!… እ!..እ!!!› ትለኛለች፤
ሐኪሙም በሐዘን ሁኔታየን ዐይቶ፣
ልቦናዬን በልቶ
‹ምናልባት ከቻልከው፣
ደሟን አስጠርገህ በጤነኛ አስተካው፣
ወይ ካንሠሩን ክፍል ቆርጠን እንጣለው፣
ይህነን የማድረግ ምርጫው የራስህ ነው፤›
ብሎ ይመክረኛል፤
ግና እንዴት ተደርጎ፣
‹እናቴን ላደርጋት አካለ ‹ጎደሎ›?
ይሁን እንኳ ቢባል የገንዘብ ክፍያው ከየት ተፈልጎ?
ደግሞስ የትኛው ነው ከእሷ የሚቆረጥ፣
አንጀቷ ነው፣ ልቧ ወይስ እግር እጇ
በሐኪም የሚፈለጥ?
ይህንን ተደርጎስ የመዳን እድሏ፣
ብትድንስ እንኳ ጤናው መመለሱ
የቀረው አከሏ፤›
ዋስትናው ምንድን ነው?
በእናቴ አካላት ላይ የምደራደረው?›
እያለ ውስጤ ይወቅሰኛል፤
ያም አለ ያም አለ!
እናቴ ታማለች፣
ሆስፒታል ውስጥ ነች፣
በሚያንቋርር ድምፅዋ ‹እ!ህ!…እ!!!…› ትለኛለች፡፡
እኔም ዝም ብዬ ዐይን ዐይኗን ዐያለሁ፤
በታሪክ ሰምጬ የእናቴን ማንነት፣
የባህል ዕንቁነት፣ የጠባይ ኩሩነት፣
አብሰለስላለሁ፣
የ‹ህእ!!..›ታ ድምፅዋን በውስጤ እያዳመጥኩ፣
የልቧን ት..ር..ታ በእጄ እየደባበስኩ፤
እጠባበቃለሁ፤
ዐይኔ እንዲህ እያየ እናቴ ልትሞት ነው?
ይህንን እያሰብኩ፣
ሳትሞት እየገደልኩ
መብሰልሰል መብሰልሰል ሥራዬ መራድ ነው፤
ግና እንደዚያም ሆና!
ዐይኗ ትክ አድርጎ ዐይን ዐይኔን ያየኛል፣
ስሜቷ እየጮኸ ፍቅሯን ይነግረኛል፤
የፍቅሯ ቃጠሎ ውስጤን ይነዝረዋል፤
እንዴት እየሞተ ሰው ፍቅር ያወራል?
እንዳው ዝም ብዬ በሙጣጭ ተስፋ ውስጥ
እኔም ዐያታለሁ፣
እንዳው ዝም ብዬ
በልብ ትርታዋ ሕይወት እለካለሁ፤
አዎ! እማዬ ታማለች፣
‹እ!..ህ!!…› ብቻ ትላለች፤
በህቅታዋም ውስጥ
የእናትነት ፍቅሯን እያመላለሰ፣
ውስጤ እያስታወሰ፣
ልዩ እናት መሆኗን እየመሰከረ፣
ከአንጀት እስከ ጀርባ እየደረደረ
‹እሷ እኮ! ናት! አንተ! አልጋ ላይ የዋለች!
እሷ! እኮ! ናት! አንተ! እየጣረች ያለች!›
በማለት ውስጤን ያቆስለዋል፣
ከህመሟ ብሶም ይለበልበኛል፤
ብጨነቅ ብጠበብ አልቻልኩም ላድናት፣
ሆስፒታል ውስጥ ናት፤
ብቻ ‹እ!.ህ!!..እ!..ም!!..እ!..ህ!…› ትለኛለች፣
በእውነት! በእውነት! አገሬ-እማማ! ታማለች፡፡
ኧረ! ሐኪም!ኧረ ሐኪም!
ኧረ! ሐኪም! ኧረ! ሐኪም!…
አካሏን ጠባቂ እግዜር የሚፈራ፣
ብክለት የሚያጠራ፣
እናቴን የሚያድን! እናቴን የሚያክም!!!
ኧረ! ሐኪም! ኧረ! ሐኪም!…
(ግንቦት 1፣ 2006 ዓ.ም.)

| Copyright © 2013 Lomiy Blog