"ለአማርኛ ስነፅሁፍ ቅርብ ነኝ ለማለት አልችልም። የሚታተሙ መጻሕፍትን እንደልቤ ለማግኘት ስለምቸገር ስለታተሙ መጻሕፍት በልበ ሙሉነት አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ። በጥቅሉ ግን የአማርኛ ስነፅሁፍ አደጋ ላይ የወደቀ ሆኖ ይሰማኛል። አማርኛ በአዲሳባና በአማራ ክልል ቋንቋነት ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ብዙ ተሰርቶበታል። ይህ ሁኔታ የአማርኛ ስነፅሁፍን ክፉኛ ጎድቶታል። አማርኛ ቋንቋ ጠላት ስለበዛበት ስነፅሁፉም ባለቤት አጥቶአል። ይህ አሳዛኝ እውነት ነው።" ተስፋዬ ገብረአብ ከላይፍ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ
(ይህ ቃለመጠይቅ አዲስ አበባ ላይ በየ15 ቀኑ ከሚታተመው "ላይፍ" መጽሔት ጋር የተደረገ ሲሆን፤ ቃለመጠይቁ የተካሄደው ከመጽሔቱ ጋዜጠኛ ጋር በጽሑፍ ነው።)
ላይፍ፦ አዲሱ "የስደተኛው ማስታወሻ" መጽሐፍህ ከ"የደራሲው ማስታወሻ" እና ከ"የጋዜጠኛው ማስታወሻ" በምን ይለያል?
ተስፋዬ፦ "የስደተኛው ማስታወሻ" ከቀዳሚዎቹ ማስታወሻዎች የቀጠለ ነው። በዚህ ቅፅ በተመሳሳይ ገጠመኞቼን ነው ያሰፈርኩት።
በርግጥ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ የአውሮፓ የስደት ገጠመኞቼ ተተርከውበታል። ይህ ቅፅ የማስታወሻዎቼ መደምደሚያ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ወደ ስነፅሁፍ ስራዎች ነው የምገባው።
ላይፍ፦ "የስደተኛው ማስታወሻ" አሳታሚ ማነው? መቼ ለገበያ ይቀርባል?
ተስፋዬ፦ "ነፃነት አሳታሚ" ይባላል። ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ የኢትዮጵያውያን ንብረት የሆነ አሳታሚ ድርጅት ነው። ውል አድርገን መጽሐፉን አስረክቤያለሁ። የጀርባና የፊት ሽፋኑን ዲዛይን ሰርተው ልከውልኝ አፅድቄያለሁ። መጽሐፉ በህትመት ፕሮሰስ ላይ እንደሆነ መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ነግረውኛል። ጥቅምት ገበያ ላይ ይውል ይሆናል። በትክክል ቀኑን አላውቅም። መረጃዎቹን በድረገፃቸው በኩል ይፋ ያደርጉታል።
ላይፍ፦ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ስራዎችህ የሁለት የተለያዩ ሰዎች ተጽዕኖ ውጤት ነው ይላሉ። ከአሰፋ ጫቦ ሽሙጥን፣ ከበዓሉ ግርማ ጀብደኝነትን። ምን ትላለህ?
ተስፋዬ፦ አሰፋ ጫቦ አሽሟጣጭ ነው ብዬ አላስብም። በአሉ ግርማም ጀብደኛ አይመስለኝም። ስለሁለቱ ብእረኞች በዚህ መንገድ ማሰብ ስህተት ነው። የአሰፋ ጫቦን ብዕር አደንቃለሁ። አሽሟጣጭ ሳይሆን እውነታዎችን በቀጥታና በግልፅ የሚናገር ደፋር ብእረኛ ነው። በአሉም የሰከነ ብዕር የነበረው ደራሲ ነው። ጀብደኛ ሊያሰኘው የሚችለው ስራው የቱ ነው? ምናልባት "ኦሮማይ"ን በማሰብ ከሆነ፣ በአሉ ግርማ በዚህ መጽሐፍ ምክንያት ሊገደል እንደሚችል ቢገምት ኖሮ ከዚያ የተሻለ ስራ ይሰራ ነበር። ወደ ጥያቄው ስመለስ የበአሉና የአሰፋ ጫቦ ተፅእኖ የለብኝም ለማለት አልችልም። ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ግን የወርቃማው ዘመን የሩስያ ደራስያን ብእረኞች ይበልጥ ቀልቤን ይስቡታል። እንደምገምተው ማስታወሻዎቼ ይበልጥ የቱርጌኔቭ የህይወት ታሪክ ማስታወሻዎች ተፅእኖ ሳይኖርባቸው አይቀርም። ወደ ትረካው ጥበብ ስንመጣ ስብሃት ገብረእግዚአብሄርና ጎርኪይ ምንግዜም አብረውኝ አሉ። ዞረም ቀረ አንድ የብዕር ሰው በጊዜ ሂደት በተለያዩ ፀሃፊዎች የአፃፃፍ ስልት ሊገነባ ይችላል።
ላይፍ፦ በአሁን ጊዜ ለአማርኛ ስነ ጽሑፍ ምን ያህል ቅርብ ነህ? ከታተሙት መጻሕፍት መካከል የምታደንቀው አለ? 'አብሬው በሰራሁ' ስለምትለው ወይም በልዩ ሁኔታ ስለምታስታውሳቸው ደራስያን የምትገልፀው ካለም እድሉን ልስጥህ?
ተስፋዬ፦ ለአማርኛ ስነፅሁፍ ቅርብ ነኝ ለማለት አልችልም። የሚታተሙ መጻሕፍትን እንደልቤ ለማግኘት ስለምቸገር ስለታተሙ መጻሕፍት በልበ ሙሉነት አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ። በጥቅሉ ግን የአማርኛ ስነፅሁፍ አደጋ ላይ የወደቀ ሆኖ ይሰማኛል። አማርኛ በአዲሳባና በአማራ ክልል ቋንቋነት ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ብዙ ተሰርቶበታል። ይህ ሁኔታ የአማርኛ ስነፅሁፍን ክፉኛ ጎድቶታል። አማርኛ ቋንቋ ጠላት ስለበዛበት ስነፅሁፉም ባለቤት አጥቶአል። ይህ አሳዛኝ እውነት ነው።
ስለ ደራስያን ወይም ስለ ብዕር ሰዎች የጠየቅኸኝ ጥያቄ ስሜታዊ የሚያደርግ ነው። በልጅነቴ ሳመልካቸው የኖርኩት አንዳንዶቹ የብዕር አማልክት ዛሬ በህይወት የሉም። ከጥቂቶቹ ጋር ከመተዋወቅ በላይ አብሬያቸው ለመስራት በቅቻለሁ። የቅርብ ጓደኞቼ የሆኑም አሉ። ከስብሃት ገብረእግዚአብሄር ጋር አብሬ በመስራቴ በምንም ነገር የማይለካ ልምድ አጊንቼያለሁ። የአርትኦትን ጥበብ ከአረፈአይኔ ሃጎስ ተምሬያለሁ። እሸቱ ተፈራ ቤተመጻሕፍት ማለት ነበር። ማሞ ውድነህ ወዳጄ ነበሩ። "እነዚህ አለቆችህ" እያሉ ወያኔን ያሙልኝ ነበር። አበራ ለማ ወጣቶችን በማገዝ ሱስ የተለከፈ ደራሲ ነበር። የሺጥላ ኮከብ ምርጥ ደራሲ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ነካ ያደርገዋል። የእፎይታ መጽሔትን አንደኛ ዓመት ስናከብር መጣና እንዲህ አለኝ፣
"አንድ የማይረባ መጽሔት አንድ ዓመት ስለሞላው ምንድነው ይህ ሁሉ ቸበርቻቻ?"
የሺጥላ ይህን ሲናገር ነጋሶ ጊዳዳ እና አለምሰገድ ገብረአምላክ በአካባቢው ነበሩ።
"ሞቅ ስላለህ ወደ ቤትህ ሂድ" አልኩት።
መአዛ ብሩና አበበ ባልቻ የልብ ወዳጆቼ ነበሩ። ሃይስኩል እያለሁ ከመአዛ ብሩ ድምፅና ሳቅ ጋር ፍቅር ይዞኝ ነበር። አሁንም አልተወኝም። የመአዛን ሳቅ ለመስማት ስል የሸገር ሬድዮ ቁራኛ ነኝ። ተፈሪ አለሙና ማንያዘዋል እንደሻውን አልረሳቸውም። የማንያዘዋል ወንድም ይሁን እንደሻው ራሱ አሪፍ ፀሃፊ ነው። ከሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም እና ከአያልነህ ሙላቱ ጋር ባለመስራቴ በጣም ይቆጨኛል። ከተሰደድኩ በኋላ ግን ለአያልነህ ደወልኩለት። የማክሲም ጎርኪይን የትውልድ ቦታ ኒዥኒይ ኖቭጎሮድን ለመጎብኘት ፈልጌ ስለነበር አስጎብኚ እንዲያዘጋጅልኝ ለመጠየቅ ነበር የደወልኩለት። ሃይለመለኮት መዋእል ከኔ ጀግኖች አንዱ ነው።
በፍቃዱ ሞረዳን አልወደውም። ምክንያቱም ከመሬት ተነስቶ ነገር እየፈለገ ያበሳጨኛል። ተወኝ ብለው ሊተወኝ አልቻለም። 2009 ላይ ጦርነት ገጥመን ነበር። በቅርቡ ግን አሪፍ ግጥም ፅፎ ሳነብ ያናደደኝ ሁሉ ብን ብሎ ስለጠፋ አድናቆቴን በፅሁፍ ገለጥኩለት።
ምነው አብሬያቸው በሰራሁ የምላቸው በርካታ ወጣት የብእር ጀግኖች አሉ። በእውቀቱ ስዩም፣ ኑረዲን ኢሳ፣ ሲሳይ አጌና፣ ኤፍሬም ስዩም፣ አዳም ረታ፣ ይስማእከ ወርቁ፣ ማረፊያ በቀለ ... እንዲህ እያልኩ ትዝታዬን ከቀጠልኩ መቶ ገፅ አይበቃኝም። ጥያቄህን መልሼልህ ይሆን?
ላይፍ፦ ለአንድ ጀማሪ ደራሲ በአንተ አስተውሎት መጠንና ጉልበት እንዲጽፍ ምን ትመክረዋለህ?
ተስፋዬ፦ በርግጥ በአስተውሎትና በብርታት እየፃፍኩ መሆኔን ካመንክ አመሰግናለሁ። ተሰጥኦ ያለው ጀማሪ ደራሲ ጥሩ የሚባሉ መጻሕፍትን በጥንቃቄ መርጦ በዝግታ ያነብ ዘንድ እመክረዋለሁ። ብዙ ማንበብ ብቻውን ጥሩ ደራሲ አያደርግም። መምረጥና በጥልቀት ማንበብ ይገባል። በጥልቀትና በዝግታ ማንበብ ሲባል ታሪኩን ብቻ አይደለም። ቃላት አመራረጥ፣ አረፍተነገር አሰካክ፣ የአገላለፅ ዘዴዎችን በጥንቃቄ መመርመር ማለት ነው። ሌላው ጉዳይ ጀማሪ ደራስያን ያልኖሩበትን ህይወት ለመፃፍ እንዳይሞክሩ እመክራለሁ። ልጅ ያልወለደ ሰው ስለ ልጅ ፍቅር ሊያውቅና ሊፅፍ አይችልም። ቢፅፍም የተሳካለት አይሆንም። ስለ ገበሬ መፃፍ ከፈለጉ ጥቂት ቀናትን ከገበሬዎች ጎጆ ማሳለፍ መቻል አለባቸው። ይህን ጉዳይ ቼኾቭ አጥብቆ መክሮ ነበር። ስሞክረው ልክ እንደሆነ አወቅሁ። "በብርታት መፃፍ" የሚለው መቸም አከራካሪ ነው። እኔ በብርታት እየሰራሁ ያለሁት (በርግጥ ከሆነ) ሙሉ ጊዜዬን በፅሁፍ ስራ ላይ ስላዋልኩ ሊሆን ይችላል። ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ሌላ ምንም ስራ ሳይሰሩ ፅሁፍ ላይ ብቻ የሚያተኩሩበት እድል ካገኙ በብርታት ብዙ ሊሰሩ ይችሉ ይሆናል። ኑሮውን ለመደጎም ሲል የማይወደው ስራ ላይ የሚባክን የብዕር ሰው የተሳካለት ስራ ለመስራት ይቸገር ይሆናል።
ላይፍ፦ ፖለቲካ ውስጥ ባይገባ ኖሮ "ስመጥር" ከሚባሉት ደራስያን መካከል አንዱ ይሆን ነበር ለሚሉት ምን ምላሽ አለህ?
ተስፋዬ፦ በአንድ ወቅት የኢህአዴግ አባል የሆንኩት ከፍላጎቴና ከእውቅናዬ ውጭ መሆኑን ተናግሬያለሁ። ከወያኔ ጋር በቆየሁበት ጊዜም ቢሆን ጋዜጠኛ ሆኜ ነው የሰራሁት። ከዚያ በኋላ ነፃ ሰው ነኝ። የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም። "ፖለቲካ ውስጥ ባይገባ" የሚለው አባባል የተጋነነ ነው። የኛ ዘመን ሰው እንዴት ከፖለቲካ መራቅ ይችላል? እንራቅህ ቢሉትስ መች ይሆናል? እንደ ጭስ ቀዳዳ ፈልጎ መኝታ ቤታችን ድረስ ይገባል። በአጋጣሚ ፖለቲካ ውስጥ ስለገባሁ እንደ ጋዜጠኛ እና እንደ ደራሲ የፖለቲካ ገጠመኞቼን ፅፌያለሁ። ይህን በማድረጌ ስህተቱ ምን ላይ እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም። እርግጥ ነው፣ አምርረው የሚጠሉኝ ወገኖች አሉ። ከፖለቲካ አመለካከታቸው ተነስተው ሊሆን ይችላል። የምሰራው ስራ ዋጋ ካለው ክብር ያገኛል ብዬ አስባለሁ። እኔ ማድረግ ያለብኝ ልቤን መከተል ብቻ ነው።
ላይፍ፦ "የስደተኛው ማስታወሻ" መጽሐፍህ ሃገር ውስጥ እንዲነበብ ምን ጥረት ታደርጋለህ?
ተስፋዬ፦ ለአዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር መልእክት ልኬ ነበር። ምላሽ አላገኘሁም። አንድ የኮክቴል ግብዣ ላይ በወሬ መካከል ስብሃት ነጋ፣ ለበረከት "ለምን አትተወውም? ያሳትም" ብሎት እንደነበር ሰምቻለሁ። በርግጥ ከዚህ አባባል ተነስቼ ችግሩ ያለው በረከት ስምኦን ጋር ብቻ ነው ለማለት አልችልም። በዚያም ሆነ በዚህ ግን ከመነበብ ሊያግዱት አይችሉም። ኮፒው በህገወጥ መንገድ ታትሞ መሰራጨቱ አይቀርም። የሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ግን የታገዱትን መጻሕፍት በድጋሚ አሳትማቸዋለሁ።
ላይፍ፦ ኢሕአፓዎች ይሔንንም መጽሐፍህ እንደማያባዙት ምን ዋስትና አለህ?
ተስፋዬ፦ መሞከራቸው አይቀርም። የሚያሰራጩባቸው ድረገፆችና የፊስቡክ ክፍሎች ስለሚታወቁ ህገወጡን ድርጊት ከፈፀሙ በህግ እንዲጠየቁ ጠበቆችን አዘጋጅተናል። በ'ርግጥ ኮፒ የማድረጉን ስራ የሚሰሩት የኢህአፓ ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም። የምቀኝነት ህመም ያለባቸው አንዳንድ የአእምሮ በሽተኞችም ድርጊቱን ሊፈፅሙት ይችላሉ። በርግጠኛነት የምነግርህ ወያኔዎች ይህን ድርጊት እንደማይፈፅሙት ነው። የማይፈልጉትን መልእክት በማፈን እንጂ በማሰራጨት አይታወቁም። የኢህአፓ አመራር የኮሎኔል መንግስቱን መጽሐፍ ስካን አድርጎ ሲያሰራጭ መንግስቱ ሃይለማርያምን ገንዘብ ማሳጣት ነበር አላማቸው። የሚያስቅ ጅልነት ነው። መንግስቱ ገንዘብ አይፈልግም። ቀዳሚ አላማው መጽሐፉ እንዲነበብ ነው። ስለዚህ ኢህአፓ ማድረግ የነበረበት መጽሐፉን ገዝቶ ማቃጠል ነበር።
ላይፍ፦ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ዕድሉ ያለ ይመስልሃል?
ተስፋዬ፦ የህወሓት ሥርዓት ከወደቀ እመለሳለሁ።
ላይፍ፦ አዲስ አበባ ውስጥ የሚናፍቅህ የትኛው ቦታ ነው? ቁጭ ብለህ ቡና ወይም ቢራ ለመጠጣት የምትመርጠው ቦታስ?
ተስፋዬ፦ አዲስ አበባ ብዙም አይናፍቀኝ። ይልቁን ደብረዘይት እና የስምጥ ሸለቆ ከተሞች ይናፍቁኛል።ጋራቦሩ ኮረብታ ላይ ቆሜ የረር ተራራን በሩቅ ማየት በጣም ይናፍቀኛል። ቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ከሚገኙ መሸታ ቤቶች ተቀምጬ ማምሸት እፈልጋለሁ። የባቦጋያና የሆራ አርሰዲ ዳርቻዎች በህልሜ እንኳ ይታዩኛል። ድፍን አድአ፣ እስከ ጨፌ ዶንሳ፣ እስከ ሎሜ፣ ያደግሁበት አገር ነው። በቢሾፍቱ ገደሎች ደረት ላይ እንደ ወፍ በረናል። ጋራቦሩን ጋልበንበታል። በህይወት ዘመኔ አንድ ጊዜ ወደነዚህ የአድአ ገጠሮች መሄድ እፈልጋለሁ። ርግጥ ነው፣ የወያኔ ሥርዓት ሲወድቅ በሚቀጥለው አይሮፕላን ቦሌ ከሚያርፉት መንገደኞች አንዱ እኔ ነኝ። እና ሽው ወደ ቢሾፍቱ!
ላይፍ፦ በቡርቃ ዝምታ እና በቢሾፍቱ ቆሪጦች መጽሃፍትህ የተጸጸትክበት አጋጣሚ አለ? አሁንም ያለህ አቋም የመጽሐፍቱ ነጸብራቅ ነው?
ተስፋዬ፦ በመጻሕፍቱ የምፀፀትበት ምክንያት የለም። ይህ ማለት ድክመት የለባቸውም ማለት አይደለም። በ20ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ ሆኜ የፃፍኳቸው መጻሕፍት እንደመሆናቸው ድክመት ሊኖርባቸው ይችላል። የህይወት ልምድ ማጣት፣ ሊንፀባረቅባቸው ይችላል። የቢሾፍቱ ቆሪጦች ከስነፅሁፍ አንፃር ሊተች የሚችል ነው። ድክመት አለበት። እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥም ይችላል። በአሉ ግርማ "የቀይ ኮከብ ጥሪ" ተበላሽቶበታል። ጥሩ አልነበረም። ብርሃኑ ዘርይሁን በወጣትነቱ የፃፋቸውን፣ "ጨረቃ ስትወጣ" አይነቶቹን ተመልሰህ ብታነብ ብርሃኑ ነው የፃፋቸው ለማለት ትቸገራለህ። ስነፅሁፋዊ ክህሎት እያደገ ስለሚሄድ በገፀባህርያት ቀረፃ ላይ ድክመት ሊታይ ይችላል። የሃያስያን መኖር አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። የቡርቃ ዝምታ መልእክቱ ላይ ችግር የለበትም። አሁንም የማምንበት ነው። የቡርቃ ዝምታን በመፃፌ እንደማልፀፀት ደጋግሜ ተናግሬያለሁ። የኦሮሞ ህዝብ ሰብእና ላይ የተፈፀመውን ግፍ የሚያሳዩ የጥበብ ስራዎች ወደፊትም መፃፍ አለባቸው። መሸፋፈን መፍትሄ አይሆንም። አብሮ ለመኖር ባለፈው ታሪክ ላይ መተማመን ይገባል። የቡርቃ ዝምታ የጭቆናውን ክብደት ለማሳየት የሞከረ መጽሐፍ ነው። የጭቆናውን ክብደት ማወቅ ተከባብሮ ለመኖር ያግዛል እንጅ የዘር ጦርነትን አይቀሰቅስም።
ላይፍ፦ ተስፋዬ ገብረአብ ጠቡ ከኢህአዴግ ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ነው የሚሉህ ሰዎች ለዚህ እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት መጽሐፍህ በአማራ በትግሬ እና በኦሮሞ ህዝብ ቁርሾዎች ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው ነው ይላሉ? ምን ትላለህ?
ተስፋዬ፦ ስለ ዘር መነጋገር ወቅቱ ያመጣው አጀንዳ ነው። በየትኛውም የፖለቲካ ውይይቶች ላይ ቁርሾዎች የመወያያ አጀንዳ ሆነዋል። እኔ የጀመርኩት አይደለም። ክልላዊነትን ያስቀደመ የፖለቲካ ሥርዓት ነው ያለው። የማንነት ጥያቄ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖአል። አንድ የጥበብ ሰው የዘመኑን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጎ መፃፍ ግዴታው ነው። "በአማራና በኦሮሞ መካከል ፀብ ለመፍጠር" የሚል አባባል እሰማለሁ። ይህ አባባል ከቡርቃ ዝምታ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። የቡርቃ ዝምታ ታሪክ የኦሮሞ ህዝብ ስለ ራሱ ከሚያውቀው አንድ አራተኛውን እንኳ አልያዘም። ታሪኩን፣ አባባሎችን ቃላትን ያገኘሁት ከኦሮሞ ገበሬዎች እንጂ ከራሴ ፈጥሬው አይደለም። ያልተለመደ አቀራረብ ስለሆነ ሰዎች ሊሰጉ ይችላሉ። አዲሱ ወጣት ትውልድ መራራ ቢሆንም እንኳ እውነትን የመስማት ችሎታ አዳብሮአል። የሚደርሱኝ ደብዳቤዎች ይህን ጠቁመውኛል። በግልፅ በመነጋገር ችግሩ ይታወቃል። ችግሩ ከታወቀ ነው መፍትሄው የሚገኘው። በማድበስበስና በመሸፋፈን ግጭቶችን ማስቀረት አልተቻለም። ደርግም ሃይለስላሴም ሞክረውት አልተሳካም። ይልቁን ማፈን መፍትሄ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ሰጡ። የታመቀ ስሜት ቢፈነዳ ይመረጣል።ቢነገር ይሻላል። ሲተነፍስ መፍትሄውም አብሮ ይመጣል።
ላይፍ፦ ከዚህ በፊት በአንተ ብሎግ ላይ ያሰፈርካቸው "የልዑሉ እናት"፣ "የመነን 4ተኛ ባል" እና "የንጉሱ ሴት ልጅ" መጣጥፎች ያነበቡ ሰዎች የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት ለመቀባት ሆን ብለህ ያደረግከው ነው ለሚሉት ምን ትላለህ?
ተስፋዬ፦ በ'ርግጥ የመሪዎች ደካማ ጎኖች ላይ የመፃፍ ፍላጎት አለኝ። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ በጎ እና ጠንካራ ጎናቸው ብቻ ነው ተደጋግሞ የሚፃፈው። መጻሕፍት መሪዎችን በማሞገስ የተሞሉ ናቸው። ደካማ ጎናቸው በግልፅ ቢፃፍ አንባቢ ብዙ ትምህርት ያገኛል ብዬ አምናለሁ። በተለይ ደ'ሞ መሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው ተራ ሰዎች መሆናቸውን ማሳየት እፈልጋለሁ። በአካባቢያችን መሪዎችን የማምለክ ዝንባሌ አለ። ከወረዳ አስተዳዳሪ ጀምሮ ለተቀመጡ መሪዎች መስገድ ባህል ሆኖአል። መነሻዬ ይህ እንጂ ሌላ አይደለም። እንደ ደራሲ ታሪኩ እውነት እስከሆነ ድረስ በማንኛውም ርስሰ ጉዳይ ላይ እንደፈለግሁ አገላብጬ የመፃፍ መብት አለኝ። ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ልሰራባቸውም እችላለሁ። ያም ሆኖ ተፈሪ መኮንን ለመነን 4ኛ ባሏ የመሆኑ መረጃ ስለ ፖለቲካዊ ጋብቻ ግንዛቤ ይሰጣል እንጂ ንጉሱን አያዋርድም። ደጃዝማች ተፈሪ 4 ልጆች ያላት ወይዘሮ በማግባቱ አደንቀዋለሁ። "ልጃገረድ ካልሆነች አናገባም" ለሚሉ አክራሪዎች ጥሩ አርአያነት ነው። መንግስቱ ኃይለማርያም ውባንቺ ቢሻው የተባለች ሚስቱን ያገባው አስገድዶ በጠለፋ ነው። ከዚህ ምንም ትምህርት አይገኝም። አዜብ መስፍን ለመለስ ዜናዊ ሻይ እንድታፈላ በድርጅቱ የተመደበችለት ታጋይ ነበረች። በዚያው ጠቀለላት። ይሄ ጥሩ ነው። እንዲህ ያሉ ታሪኮችን የመፃፍ ፍላጎት አለኝ። እንዳልኩት በመሪዎች ትከሻ ላይ የተቆለለውን የመኮፈስ ካባ ገፍፌ መጣል እፈልጋለሁ። "የልዑሉ እናት" የሚለውን ታሪክ የፃፍኩት የጳውሎስ ኞኞን መጽሐፍ መሰረት አድርጌ ነው። "የመነን 4ኛ ባል" ዘውዴ ረታ ከፃፉት የተወሰደ ነው። እኔ ስፅፈው የተለየ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው? እንዲህ የሚያስቡ ሰዎች ልባቸው ውስጥ የሸሸጉትን የዘረኛነት በሽታ ያክሙት ዘንድ እመክራቸዋለሁ። ሰዎች ስለኔ የሚያስቡትን ግምት ውስጥ እያስገባሁ ልፅፍ አልችልም። በማንኛውም ርእሰ ጉዳይ ላይ በራሴው እይታ እንዳሻኝ እፅፋለሁ። አንባቢዎቼን ለማስደሰት ወይም ለማናደድ ብዬ አይደለም የምፅፈው። ቢታተምም ባይታተምም የኔ ችግር አይደለም። ኳስ መጫወት የሚወዱ ሰዎች ኳስ ይጫወታሉ። እኔም መፃፍ ስለምወድ እፅፋለሁ። ሽማግሌው ቱርጌኔቭ እንደሚለው በጎ ከሰራን፣ ስራችንም ዋጋ ካለው፣ ያን ዋጋ ህዝብ ማስተዋል ከቻለ ለስራችን ክብር ይሰጠናል።
ላይፍ፦ በብዙ ጽሁፎችህ ለኦሮሞ መብት ጥብቅና የመቆም ዝንባሌ ታሳያለህ። ነጋሶ እንዳሉት ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ነኝ ማለትን ታበዛለህ ለሚባለው ምላሽህ ምንድን ነው?
ተስፋዬ፦ የነጋሶን አባባል ሰምቼዋለሁ። More catholic than the Pope የሚለውን አባባል ገልብጠው ሊጠቀሙበት ነው የሞከሩት። ነጋሶ ጭንቅላታቸውን ተናግረው አያውቁም። ሌሎችን ለማስደሰት በማሰብ የመናገር ልማድ አዳብረዋል። ነጋሶ አሁን የአንድነት ሊቀመንበር ናቸው። አራተኛ ድርጅታቸው መሆኑ ነው። ከኦነግ ወደ ወያኔ፣ ከወያኔ ወደ አንድነት ሲዘሉ ምንም አልተደናቀፉም። መርህ ያለው ሰው እንዲህ በቀላሉ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ መዝለል አይቻለውም። ጨለንቆ ላይ ጉድጓድ አስቆፍረው አፅም እየሰበሰቡ "ነፍጠኛውን" ያወግዙ እንዳልነበር፣ አኖሌ ላይ ስለ "ጡት መቆረጥ" ታሪክ ሲያስተምሩ እንዳልነበር አሁን 180 ዲግሪ ተገልብጠው የራስ ጎበና ዳጪ ተከታይ ሆነዋል። ዕድሜ ከሰጣቸው የነገውን አናውቅም። በተቀረ ለኦሮሞ ህዝብ ጥብቅና መቆም ሃጢአት አይደለም። ሃጢአት ሊሆን የሚችለው ከተገፋና ካመፀ ህዝብ ጎን አለመቆም ነው። ለኦሮሞ ህዝብ መቆም ሲባል ሌላውን ህዝብ ማጥቃት ማለት አይደለም። ጥያቄው የክብርና የእውቅና ማግኘት ጥያቄ ነው። የኦሮሞን የሞጋሳ ባህል የሚያውቅ በነጋሶ አባባል በጣም ይገረማል። ያም ሆኖ እኔ በኦሮሞ ህዝብ መካከል ተወልጄ ያደግሁ፤ ራሴን ኦሮሞ ብዬ ለመጥራት የሞራል ብቃት ያለኝ ሰው ነኝ። ልጅ እያለን የኢብሳ ኦሮሞ የጠበል ጠላ ስንቀምስ፣ Ijollee warra Bishoftu ነበር ፉከራችን! በእነዚያ የልጅነት ዘመናት ጋራቦሩ ላይ እርጎ ጠጥተን ስናበቃ ከአህያ እስከ ፈረስ እየጋለብን ነው ያደግነው። ይህ ፖለቲካ አይደለም። ህይወት ነው። ማንነት የተገነባበት ንጥረነገር ነው።
ላይፍ፦ በጹህፎቸህ ውስጥ የበቀል ስሜት የለህም ወይ? ጹህፎችህ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ የሚያደርግ ገንቢ ሃሳብ ምንም ቦታ ላይ የለም ትባላለህ። ለምን?
ተስፋዬ፦ በግልባጩ የኔ ፅሁፎች ለአንድነት የቆሙ ናቸው። ችግሮችን በግልፅ አውጥቶ መፃፍ ለመፍትሄ ፈላጊዎች ግማሹን ስራ እንደሰራሁላቸው ነው የሚቆጠረው። በቀል የሚለው ቃል እኔን አይገልፀኝም። በግል የበደለኝ ሰው ወይም ህዝብ የለም። ለበቀል የሚያበቃ የማስታውሰው ጉዳት አልደረሰብኝም። በቀል ቀርቶ በጥላቻ የማስታውሰው ሰው እንኳ የለም። በቀል የሚኖረው ቂምና ጥላቻ ሲኖር ነው። በኔ ልብ ውስጥ ለቂምና ለጥላቻ ቦታ የለም...
ላይፍ፦ ከኢትዮጵያና ኤርትራ ስሜትህ ለየትኛው ቅርብ ነው?
ተስፋዬ፦ ኢትዮጵያ የትውልድ አገሬ ናት። በደም ኤርትራዊ ነኝ። ማንነት የብዙ ግብአቶች ውጤት እንደመሆኑ ለሁለቱም አገራት ስሜት አለኝ። ቋንቋ፣ ባህል፣ አስተዳደግ፣ ወላጆች እነዚህ ሁሉ ማንነትን የሚገነቡ ግብአቶች ናቸው። ጥያቄው ስለ ዜግነት ከሆነ ሆላንድ የዜግነት አገሬ ሆናለች። በቀሪው የህይወት ዘመን በዚሁ የዜግነት ሰነድ መንቀሳቀስ እችላለሁ።
ላይፍ፦ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደፊት የመዋሃድ ዕድል ይኖራቸው ይሆን?
ተስፋዬ፦ ተመልሰው የሚዋሃዱ ቢሆኑ ኖሮ 30 ዓመት ትግል አይደረግም ነበር። በሰላሳ አመታቱ ጦርነት ከሁለቱም ወገን በአስር ሺዎች ተሰውተዋል። እንደገና በድንበር ጦርነት በተመሳሳይ የብዙ ሺዎች ህይወት ተቀጥፎአል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ስለ አንድነትና ውህደት መነጋገር የሚቻል አይመስለኝም። ከመነሻውም የኤርትራ ጥያቄ የነፃነት ጥያቄ ነበር። ስለዚህ ሁለቱ አገራት ተከባብረው እንደ ጎረቤት በሰላም መኖር ከቻሉ እንኳ ትልቅ ድል ነው። እንደ አውሮፓውያን ድንበራቸውን አፍርሰው፣ የንግድ ህግ ደንግገው በሰላም መኖር ከቻሉ ትልቅ ስኬት ይሆናል። ሁለቱ አገራት የየራሳቸው ፀጋ አላቸው። ከመዋሃድ ባላነሰ ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መልኩ በትብብር መስራት ይችላሉ። ኤርትራና ኢትዮጵያን በተመለከተ የኔ ምኞትና ፍላጎት በአዲሱ መፅሃፌ ላይ በግልፅ ተቀምጦአል። በአፍሪቃ ቀንድ ደረጃ በጋራ ለመስራት ከወዲሁ ጥርጊያ መንገዱን ቢያነጥፉ የአካባቢው 140 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል። የአፍሪቃ ቀንድ ህዝቦች ከጦርነት የሚገኘውን ኪሳራ ከማንም በላይ ይገነዘቡታል። ስለዚህ ሰላማዊ አካባቢ ለመፍጠር በቁርጠኛነት መተባበር ብቻ ነው የሚያዋጣቸው።
ላይፍ፦ "ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ" የተባለው መጽሐፍህ ግነት እንደነበረበት ተናግረህ ነበር። በአሁኖቹ መጽሃፍት በሆነ ወቅት 'ግነት ነበራቸው' ላለማለትህ ምን ዋስትና አለ? ለሚሉ አስተያቶች ምላሽህ ምንድነው?
ተስፋዬ፦ "ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ" በነፃነት የተሰራ ስራ አልነበረም። መጽሐፉ የኔው ፕሮጀክት ቢሆንም በመካከሉ ድርጅታዊ ጣልቃ ገብነት መጣ። ሁዋላ ከፕሮጀክቱ ራሴን ያገለልኩት በትእዛዝ መፃፍ ስላልፈለግሁ ነው። በግሌ በሰራሁዋቸው ስራዎች ላይ ስለ ግነትም ሆነ ስለ መፀፀት ተናግሬ አላውቅም።
ላይፍ፦ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከመፃፍህ አንጻር ስለ ኤርትራ ምንም አለመጻፍህ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው። ለምን?
ተስፋዬ፦ ገና ፅፌ መቼ አበቃሁ? የመሞቻዬ ጊዜም ገና አልደረሰም። የ45 ዓመት ሰው ነኝ። የመፃፊያ ጊዜዬ ገና መጀመሩ ነው። እነዚህ ማስታወሻዎች ወደ ስነፅሁፍ ስራ ለመግባት እንደመንደርደሪያ የተጠቀምኩባቸው ብቻ ናቸው። ከእንግዲህ ቢያንስ በየአመቱ አንድ መጽሐፍ ለማሳተም እቅድ አለኝ። በፕሮግራሜ መሰረት መቼ፣ ስለማን፣ ምን መፃፍ እንዳለብኝ መወሰን ያለብኝ እኔ ነኝ። ከዚህ ቀደም፣ "ስለ እዚህ ጉዳይ ለምን አልፃፍክም?" ተብሎ የተጠየቀ ደራሲ ያለ አይመስለኝም። ስለፃፍኩት እንጂ ስላልፃፍኩት ጉዳይ ልንነጋገር አይገባም። የሚገርመው "ለምን አልፃፍክም?" ተብዬ የምወቀሰው ስለማላውቀው ጉዳይ ነው። የምሰራው መጽሐፍ እንጂ ዜና አይደለም። በርግጥ ይህን ክስ የሚያራግቡት ወያኔዎች መሆናቸውን አውቃለሁ። ያቀረብኩትን መረጃ ማስተባበል ስላልቻሉ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ከአንባቢ ሊነጥሉኝ ይሞክራሉ። ያም ሆኖ ባለፉት ዓመታት ወደ ኤርትራ የተጓዝኩ እንደመሆኑ የኤርትራ ጉዞዬን በአዲሱ መፅሃፌ ተርኬዋለሁ። ጀምሬያለሁ። እቀጥላለሁ...
ላይፍ፦ መለስ ራዕይ ነበራቸው በሚባለው ጉዳይ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው። አንተስ? በቅርቡ በታተመ መጣጥፍህ፣ "መለስ ተመልሰው ቢመጡ አባይ ፀሐዬን እስር ቤት ያስገባው ነበር" ያልክበት ምክንያት ምንድነው?
ተስፋዬ፦ የመለስ ራዕይ የሚባለውን የፕሮፓጋንዳ መፈክር መለስ ሲሞት በተደናበረ ሁኔታ የፈጠሩት ነው። መለስ ሲሞት እንደ ኢህአዴግ ማእከል ሆኖ ሊያሰባስባቸው የሚችል አይዲዮሎጂ አልነበራቸውም። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ ማንም ሳያውቀው አርጅቶ ሞቶ ነበርና አደጋ ላይ ወደቁ። "ምንድነው የመለስ ራዕይ?" ብለህ ብትጠይቅ አንዳንዱ የዋህ ካድሬ፣ "የአባይ ግድብ"፣ "የባቡር ፕሮጀክት" ምናምን ይልሃል። የአባይ ግድብ ጥናት በጃንሆይ ዘመን የተጠና ነው። አቅም እና ምቹ ጊዜ እየተጠበቀ ነበር። ግብፅ ስትዳከም ምቹ ጊዜ ሆኖ ተገኘ። የባቡሩ ፕሮጅክት የሃይሉ ሻውል እቅድ ነው። ቅንጅት በ2005 ምርጫ ሥልጣኑን ቢይዝ ሊፈፅመው ያቀደው ነው። ወያኔ ከአፍ እየቀለበ የመንጠቅ ልዩ ችሎታ አለው። "የመለስ ራዕይ" የሚባል ነገር የለም። አሁን እንኳ ሽኩቻ ውስጥ ስለገቡ የራእዩ ከበሮ ረገብ ብሎአል። በመለስ ራዕይ ስም መለስ የዘረጋውን መዋቅር በመበጣጠስ ላይ የሚገኘው አባይ ፀሃዬ ነው። አንዱ ጠንክሮ እስኪወጣ ድረስ ሽኩቻቸው ይቀጥላል።
ላይፍ፦ በመለስ ራዕይ ስም መለስ የዘረጋውን መዋቅር በመበጣጠስ ላይ የሚገኘው ዓባይ ፀሃዬ ነው ያልክበት ምክንያት ምንድነው?
ተስፋዬ፦ የሽኩቻው ድራማ ዋና አክተር አባይ ፀሃዬ ነው። በአፋቸው "የመለስ ራዕይ" ይላሉ። በተጨባጭ ግን የመለስ ታማኞችን እየመነጠሩ ነው። መለስ ይዞት የነበረውን ብቸኛ አምባገነናዊ ኃይል ለመቆጣጠር እየሰራ ነው። ርግጥ ነው፣ አባይ ፀሃዬ በሚፈፅመው ድርጊት ተቃውሞ የለኝም። ለአገር ደህንነት ሲል አለመሆኑ ግን መታወቅ አለበት። አጤ ምኒልክ ሲሞቱ በደጃዝማች ተፈሪ እና በልጅ ኢያሱ መካከል የተፈጠረውን የሥልጣን ሽኩቻ የሚያስታውስ ሁኔታ ላይ ነን። አባይ ወልዱ እንደ ወራሽ ልጅ እያሱ - አባይ ፀሃዬ እንደ ደጃዝማች ተፈሪ! በትክክል ተመሳሳይ የታሪክ ጊዜ ላይ ነን።
ላይፍ፦ እንደምታውቀው ኢሕአዴጎች "እዚህ ያለነው የመለስን ራዕይ ከግብ ለማድረስ ነው" ብለው ውሳኔ ላይ ደርሰው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዓመት አልፏቸዋል። አንተ ደግሞ "የመለስ ራዕይ" የሚባል ነገር የለም ብለሃልና ብታብራራው?
ተስፋዬ፦ መለስ ለመሞት አንድ ሳምንት ሲቀረው ነው ባለራዕይ የሆነው? ምንድነው የሚያወሩት እነኚ ሰዎች? 20 ዓመታት ከመለስ አመራር የተገኘው ምንነበር? በዘር ከፋፍለው ህዝቡ እንዳይተማመን አደረጉት። ያልነበረበትን የሃይማኖት ግጭት ስር እንዲተክል ጥረት አደረጉ። በሰላም አስከባሪ ስም የዜጎችን ህይወት ቸበቸቡ። የምርጫ ኮሮጆ በመገልበጥ ህዝቡ በዴሞክራሲ ላይ ያለውን እምነት አሳጡት። ምንድነው የመለስ ራዕይ የሚባለው ቀልድ? ጄኔራሎችን ከህወሃት ብቻ መሾም ራዕይ ነው? ቡና ሲወቀጥ ግድግዳቸው የሚሰነጠቅ የኮንደሚንየም ቤቶችን መገንባት ራዕይ ነው? ገበሬዎችን አፈናቅለህ ስታበቃ አንድ ሄክታር መሬት በአንድ ፓኮ ስጋራ ዋጋ መቸብቸብ ራዕይ ነው? አንድ ፍሬ እህቶቻችንን ለአረብ ግርድና አሳልፎ መስጠት ነው ራዕይ? በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ ኦልባና ሌሊሳ ለምን ታሰሩ? በመከላከያ ስም ሸቀጥ ያለቀረጥ በማስገባት የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን መግደል ራዕይ ነው? ምንድነው የመለስ ራዕይ? ውሸትን በመደጋገም እውነት የማስመሰልን ጥበብ ተክነውበታል።
ላይፍ፦ በዚህ ወቅት ህወሓት ለሁለት ተከፍሏል በሚባለው ትስማማለህ? ከሆነስ እነማን በአሸናፊነት የሚወጡ ይመስልሃል?
ተስፋዬ፦ በሁለቱ አባዮች (አባይ ፀሃዬ እና አባይ ወልዱ) መካከል ጦርነት መኖሩን እየሰማን ነው። መረጃው ግን የተረጋገጠ ነው ለማለት አልደፍርም። የምንሰማው እውነት ከሆነ ከመቀሌው አባይ በስተጀርባ ቴዎድሮስ ሃጎስ አለ። ከአዲሳባው አባይ ስር እነ ጌታቸው አሰፋ፣ እነ ደብረፅዮን መሰለፋቸው ይሰማል። ሳሞራ የአዲሳባውን አባይ ተቀላቅሎአል። አዜብ 'አርፈሽ ቁጭ በይ! የመለስን ፋውንዴሽን ተከታተይ' ተብላለች። እብድ ስለሆነች ያልተጠበቀ ነገር እንዳትፈፅም በመስጋት ሰንሰለቷን ሁሉ በጣጥሰውባታል። የዘረፋ ቀዳዳዎቿን እየዘጉባት ነው። ያም ሆኖ አዜብ አርፋ ትቀመጣለች ተብሎ አይታመንም። መሞከሯ አይቀርም። የግል አስተያየቴን ለመስጠት ያህል፣ የመቀሌ - አዲሳባ ሽኩቻ ይፋ ሳይወጣ ውስጥ ውስጡን ሊጠናቀቅ ይችላል። ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ሽጉጥ ከተኮሱ ቤተመንግስቷን ለዘልአለሙ እንደሚያጧት ያውቃሉና ሽጉጥ ወደ መምዘዝ የሚገቡ አይመስለኝም። ከሁለቱ ቡድኖች አንደኛው እስኪያሸንፍ ሃይለማርያም ወንበሩን በታማኝነት ይጠብቅላቸዋል። ማን በአሸናፊነት ሊወጣ እንደሚችል አብረን እናየዋለን። የአዲሳባው ቡድን የሚበረታ ይመስለኛል። ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከሁለቱም ቡድኖች ገለልተኛ ሆኖ የአስታራቂነት ሚና ለመጫወት እሞከረ ነው። ምናልባት እሱን በማንገስ ልዩነታቸውን ይፈቱ ይሆናል።
ላይፍ፦ ህወሓት በምርጫ ሥልጣን የሚለቅ ይመስልሃል?
ተስፋዬ፦ በግልፅ ተናግረዋል። "ጀርባችንን በእሳት ሰንሰለት እያስገረፍን ያገኘነውን ወንበር በምርጫ ካርድ ስም ሳምሶናይት ይዘው ለመጡ ሰዎች አናስረክብም" ብለዋል። በርግጥ የምኒልክን ወንበር በምርጫ አላገኙትም። ስለዚህ በምርጫ መልቀቅ አይፈልጉም። በምርጫ እንደማይለቁትም በ2005 ምርጫ አስመስክረዋል። በተመሳሳይ በ2010 ማንኛውንም አይነት የማጭበርበር ዘዴ በሙሉ ኃይላቸው ስለተጠቀሙበት 99.6 በመቶ በማሸነፍ ወንበሮቹን ሁሉ ያዙ። በምርጫ በኩል ይገኛል የተባለውን የዴሞክራሲ ጭላንጭልም ደፈኑት። ከዚህ በኋላ ምንድነው የሚጠበቀው?
ላይፍ፦ የህወሓት በኃይል ሥልጣን ላይ የመቆየት አባዜ የሚያዛልቅ ይመስልሃል?
ተስፋዬ፦ አዛልቆአቸው 22 ዓመት ሆኖአቸዋል። ሌላ 22 ዓመታት እንደማይገዙ ምንም ዋስትና የለም። ወያኔና ሻዕቢያ በጠመንጃ ባይመጡበት ደርግ እስከዛሬ ሥልጣን ላይ ሊቆይ ይችል ነበር። ሙጋቤ አሁንም አለ። ጋዳፊ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ነበረ። ስዩም መስፍን ቻይና የሚማሩትን የህወሃት የአመራር አባላት ልጆች እያሰለጠነ ነው። በቻይና መንግስት ድጋፍ ተተኪ የአገሪቱ መሪዎች ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ። ይህ ተረት አይደለም። እስከቻሉት ድረስ ይሞክራሉ። ከአንዳንዶቹ ጋር እንዲህ በስልክ ስናወራ "ከዚህ በኋላ 40 ዓመታት መቆየት እንችላለን" ብለው በቀልድ መልክ ጣል ያደርጋሉ። እየቀለዱ ግን አይደለም። "የ65ሺህ ጓዶቻችንን ህይወት የከፈልነው ዋጋው ውድ ነው" ይላሉ። በጨዋታ መሃል ከምኒልክ እስከ ሃይለስላሴ የነበረውን ዘመን ያሰሉታል። የንጉስ ሳህለስላሴ የልጅ ልጆች የቤተሰብ ጥል እየተጣሉም ቢሆን ሥልጣን ከቤተሰባቸው ሳይወጣ እየተተካኩ ቆይተዋል። ህወሃት በተመሳሳይ መንገድ ልዩነት የፈጠሩትን እያስወገደ ሁለት ወይም ሶስት ትውልድ ከዚያም በላይ ለመግዛት ይችላል አይነት ወጎች አሏቸው። በአደባባይ ደግሞ፣ "እኛ በሥልጣን መቀጠል ካልቻልን ኢትዮጵያ ትበታተናለች" ብለው መዛታቸውን ቀጥለዋል። ኢትዮጵያ እንዳትበታተን በመስጋት ህዝቡ ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛላቸው ይመኛሉ።
ላይፍ፦ ህወሓትን ለ22 ዓመታት በሥልጣን እንዲቆይ ያስቻለው ምንድነው ትላለህ?
ተስፋዬ፦ ምስጢሩ ህዝቡን ከፋፍሎ መግዛት በመቻሉ ነው። የፌደራል አገዛዝ ሥርዓቱን ለሥልጣን ማራዘሚያ ተጠቅሞበታል። ክርስትያኑን በሙስሊሙ ያስፈራራዋል። የአማራው ኃይል ሲበረታ በኦሮሞው እየመታ ዘልቆአል። ሌላ ምስጢር የለውም። ከፋፍሎ በመግዛት፣ የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜትን በማዳከም፣ ከተቻለ ጨርሶ በማጥፋት ዝንተ አለም መግዛት እንደሚችሉ አስልተው ጨርሰዋል። በርግጥ 95 በመቶ የመከላከያን አመራር ተቆጣጥረውታል። ደህንነቱ ሙሉ በሙሉ በእጃቸው ነው። ህዝቡ በዘር ተከፋፍሎአል። ለሃያላኑ አገራት ራሳቸውን በአገልጋይነት ስላቀረቡ በጫና ፈንታ እርዳታ እያገኙ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር በሥልጣን እንዲቆዩ አግዞአቸዋል።
ላይፍ፦ አሁን ያሉት ብዙዎቹ የህወሓት ባለሥልጣናት በአባት ወይም በእናት ኤርትራውያን ናቸው ይባላል። የተባለው ትክክል ከሆነ ውሳኔዎቻቸው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ሊሆን አይችልም? ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእነኚሁ ባለሥልጣናት አያቶች ወይም ቅድመ አያቶች የጣሊያን ባለሟሎች የነበሩ ናቸው ስለሚባለው ምን መረጃ አለህ? የባንዳ ልጆች መሆናቸው የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ አይከታቸውም?
ተስፋዬ፦ በአባት ወይም በእናት ኤርትራዊ መሆን የዘመናችን ዋና አጀንዳ መሆኑ ያሳዝነኛል። በረከት ስምኦን በእናቱም ሆነ በአባቱ ኤርትራዊ ነው። ለኤርትራ የፈፀመላት በጎ ነገር አለመኖሩን ግን አረጋግጥልሃለሁ። በረከት በኤርትራውያን ዘንድ እንደ ፖለቲከኛ እንኳ አይታይም። በኢትዮጵያውያንም አይታመንም። እድለኛ አይደለም። ይህ ሊሆን የቻለው በረከት የሚሰራው ለግሉ፣ ለዝናው፣ ለሥልጣን ስለሆነ ነው። ግማሽ የኤርትራ ደም ያላቸው የህወሃት አመራር አባላት ለኤርትራ ያደላሉ ብዬ አስቤ አላውቅም። የተወለዱት እና ያደጉት ትግራይ ነው። ለትግራይ ነው የሚሰሩት። አንድን ሰው "ግማሽ ኤርትራዊ ነው" ብለን ከማሰባችን በፊት "ግማሽ ኢትዮጵያዊ ነው" የሚለውን ማስቀደም ለምን አልተቻለም? በአሉ ግርማ እኮ በአባቱ ህንዳዊ ነው። ገብሩ አስራት ግማሽ ጎጃሜ ነው። ጆሴፍ ስታሊን ሩስያዊ አልነበረም። ኦባማ በአባቱ ኬንያዊ ነው። ጥላሁን ግዛው የፊውዳል ቤተሰብ ነበር።ለኢትዮጵያዊነት ህይወታቸውን የከፈሉ ኤርትራውያንን ስም እንጥራ ብንል ሰአታት አይበቃንም። መለስ በአባቱ ኢትዮጵያዊ ነው። ለምንድነው ወደ እናቱ ጎሳ ያዘነብላል ተብሎ የሚታሰበው? ተወልዶ ያደገው ትግራይ ነው። መለስ ኢትዮጵያን ለመምራት ግማሽ ኢትዮጵያዊነቱ ከበቂ በላይ ነበር። እንደሚመስለኝ ችግሩ ግማሽ ኤርትራውያን መሆናቸው ሳይሆን መርህ አልባ፣ ወይም ሥልጣናቸውን ብቻ የሚያስቀድሙ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል። መለስ ዜናዊ የባንዳ ልጅ ስለመሆኑ ሲነገር የሰማሁት ከገብረመድህን አርአያ ነው። ገብረመድህን ስለሚያጋንን አይመቸኝም። የሆነው ሆኖ መለስ የባንዳ ልጅ ሊሆን ይችላል። የባንዳ ልጅ መሆኑ ግን እሱንም ባንዳ አያደርገውም። የመለስን ወላጆች እና ልጆች እንተዋቸው። መለስን ለመውቀስ የሚያበቃ በአገር ላይ የፈፀመው በርካታ ወንጀል አለ።
ላይፍ፦ መለስ ዜናዊ "የኤርትራ ህዝብ ከየት ወዴት" የሚለውን መጽሐፍ መጻፋቸው፣ ኤርትራ ራስዋን ችላ ነፃ ሐገር ሆና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና እንድታገኝ ለዋና ጸሐፊው ቡትሮስ ጋሊ ደብዳቤ መጻፋቸው፣ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ይገባኛል እንዳትል እንቅፋት መፍጠራቸውና ለኤርትራ ይገባል ማለታቸው ግማሽ ኤርትራዊ ባይሆኑ ኖሮ የሚሞክሩት ተግባር ነበር?
ተስፋዬ፦ ኤርትራን በተመለከተ በተወሰኑ ውሳኔዎች የኤርትራ ደም የሌለባቸውም ተሳትፈው አብረው ወስነዋል። የፖለቲካ አቋማቸውን ነው ያስፈፀሙት። ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር ስለመቀጠሏ እንኳ ሁለት ልብ ስለነበሩ የኤርትራን ነፃነት የማይቀበሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። ከዚያም ባሻገር አቋማቸውን ለመለወጥ ቢያስቡ ኖሮ እንኳ በወቅቱ ምንም ማድረግ አይችሉም ነበር። ተዋጊ የገበሬ ሰራዊትና ፖለቲካ የሚያንበለብሉ ሸምዳጅ ካድሬዎች እንጂ ሌላ አቅም አልነበራቸውም። አዲሳባን እንዴት እንደሚያስተዳድሩ አሳቡ እንኳ አልነበራቸውም። በርግጥ መለስ ዜናዊ ኤርትራን በተመለከተ ስሜቱ ስስ መሆኑ ብዙ የተባለበት ነው። ስለ መለስ የልብ ሚዛን የሚያውቀው ራሱ መለስ ብቻ ነበር። ሳይፅፈው ተሰናብቶአል።
ላይፍ፦ መለስና ጓደኞቻቸው ሽንጣቸውን ገትረው ለኤርትራ ነፃነት ሲዋጉ የነበሩት ለምን ይመስልሃል?
ተስፋዬ፦ እኔ እስከማውቀው ለኤርትራ ነፃነት የተዋጉት ኤርትራውያን ናቸው። መለስና ጓደኞቹ የራሳቸው አጀንዳና አላማ ነበራቸው። በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት ለስልጠና ኤርትራ ሄደው መስዋእትነት እንደገጠማቸው ሰምቻለሁ። የሻዕቢያ ተዋጊዎችም በተመሳሳይ ህወሃትን በማገዝ ሂደት ውጊያ ላይ መስዋእትነትን ከፍለዋል። ይህ የጋራ ጠላትን ለመመከት ከተደረገ ታክቲካዊ ትብብር ያለፈ ስም ሊሰጠው አይችልም። የህወሃት እገዛ አንዳንድ ፀሃፊዎች አጋንነው እንደሚያቀርቡት አይመስለኝም።
ላይፍ፦ በኢትዮጵያ ባለጠመንጃ አስተዳዳሪ መሆኑ የሚቀርበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል?
ተስፋዬ፦ ተስፋ አደርጋለሁ።
ላይፍ፦ የህወሓትን በኃይል ከሥልጣኑ እናባርረዋለን የሚሉት ተቃዋሚዎች ሚሳካላቸው ይመስልሃል?
ተስፋዬ፦ ህዝቡ የወያኔን ሥርዓት ተንኮል ጠንቅቆ ተረድቶ አማፅያኑን በሙሉ አይኑ ማየትና ማመን ከጀመረ የሚሳካላቸው ይመስለኛል። በርግጥ እኔ በግሌ ጠመንጃ እንዲተኮስ አልፈልግም። ወጣቶች በጦርነት እንዲሞቱ አልመኝም። እኔ ራሴ የጦርነት ትራፊ በመሆኔ ህመሙ ይሰማኛል። ጠመንጃ ከማንሳት ባሻገር አማራጭ መጥፋቱ ግን ያሳዝነኛል።
ሰሎሞን ተሰማ ጂ.
የሶሪያ ጉዳይ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ መጥቷል። በስልጣን ላይ ያለው ጎሳ "የአላዊት ጎሳ" ይባላል። አላዊቶችና በደዊኖች በሽፍትነትና በባህር ላይ ውንብድና ስማቸው የገነኑ ናቸው። በደዊኖች፣ ሶሪያን ለዘመናት ያህል ሲፈልጧትና ሲቆርጧት ኖረዋል። እንደነሱ ዘረኛ፣ እንደበደዊኖች ጠባብ፣ አክራሪና ቁመኛ ታይቶም-ተሰምቶም አይታወቅም። አላዊቶችም ቢሆኑ "አልሸሹም ዞር አሉ" ናቸው።

እነዚህ ወገኖች፣ የሶሪያን ሀገረ-መንግሥት (State apparatus) ከተቆጣጠሩበት ዘመን ጀምሮ ለኢትዮጵያ በጎ ተመኝተውላት አያውቁም። ይባስ ብሎ ደግሞ፣ ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ወዲህ እጅግ በከፋ መልኩ የኢትዮጵያን ጥቅምና ሉዓላዊነት በሚፈታተን መልኩ በግትርነት ቆመው ነበር። በጣም በተጋነነና በመረረ ኹናቴ መንቀሳቀስ የጀመሩት ግን ከ1953ዓ/ም ወዲህ ነው። በዚህ
ዓመትም በጂዳ-ሳዑዲት ዓረቢያ የተቋቋመውን "የኤርትራ ነፃ-አውጪ ድርጅት" (ወይም በተለምዶ አጠራሩ ጀ.ብ.ሐ) እየተባለ የሚታወቀው፣ በአሳውርታ የሚኖሩት የቤንአሚር ጎሳ ተወላጆች ቡድን ለመደገፍ በደዊኖች ተሯሯጡ። ከእነርሱም ቀጥሎ ወደስልጣን የመጡት አላዊቶች ተመሳሳይ ተግባር ፈፀሙ። ያለምክንያት አልነበረም፤ በአሳውርታ የሚወለዱት ቤንአሚሮች "የበደዊንና የአላዊት ደም አላቸው" ከሚል ጎሰኛ ቀመር ተነስተው ነው።

ስለሆነም፣ በ1955ዓ/ም በይፋ ለጀ.ብ.ሐ አገናኝ ቢሮ በደማስቆ ከተማ ተከፈተለት። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ፣ በርካታ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴዎችን መደገፍ ጀመሩ። በ1960 እና 1961 ዓ.ም. ብቻ እንኳን፣ "ነፃነትን-መደገፍ" በሚል ስም፣ እ.አ.አ እስከ 1970 ድረስ በበደዊን ጎሳዎች የሚመራው የሶሪያ መንግሥት በርካታ የአጋሚዶ/የውንብድና ተልዕኮዎችን ከአፍ-እስከ-ገደፉ ደግፏል። (ይሄንን በተመለከተ፣ በ1933ዓ/ም በደቀሽሐይ-ሐማሴን የተወለደውና በጀብሐ ውስጥ የ5ተኛው ወታደራዊ ክፍል/ምድብ ዋና መሪ የነበረው፣ ወልዳይ ካህሳይ ብዙ-ብዙ ነገር ያወሳናል። ወደኋላ ላይ እንመለስበታለን።) በዚህ የመቀራረብና የመተሳሰብ ዘመን በሆነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ በደዊኖችና አላዊቶች ከአንድ መንግሥት የሚጠበቀውን ዓለም አቀፍ ኃላፊነት ዘንግተው፣ ዓለም አቀፍ ውንብድና ውስጥ ሙጭጭ አሉ። በዘመናዊ አስተዳደር፣ ሃይማኖትና ጎሳ እምብዛም ቦታ እንደሌላቸው ያልተገነዘቡት በደዊኖችና አላዊቶች፣ በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖት ጥላ ስር የተሰባሰቡትን ወንበዴዎች ሁሉ በወታደራዊ ስልጠናና በትጥቅ ሲረዱ ኖረዋል። በዚህም አቋማቸው የተነሳ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የተነሱትን ማናቸውንም ግጭቶች ቤንዚን በማርከፍከፍ ሲጋግሙት ኖረዋል። ወይም በሀገራችን አባባል ጭድ ሲነሰንሱበት ኖረዋል። ሊባኖስ ቀንደኛዋ ተጎጂ ናት። ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሐሪሪ ሳይቀሩ የተገደሉት በሶሪያ ጎሰኞች መሰሪ ደባ ነው። (በአሜሪካዊያኑና በበርካታ የዓረቡ ዓለም ሰዎች የተጠላውና የተወገዘው-"ጫማ ሳይቀር የተወረወረበት"-ትንሹ ጆርጅ ቡሽ እንኳ፣ "የዳቢሎስ ዛቢያ (Evil Axes)" ብሎ እስኪጠራት ድረስ፣ የበደዊኖቹና የአላዊቶቹ ሶሪያ፣ እጅግ አገደኛ ምሳር ናት።)

ከአላዊቶች ጎሳ/ወገን የሆነው የሶሪያው ፕሬዝዳንት፣ በሺር አላሳድ ይባላል። ከደማስቆ ዩኒቨርሲቲ በዓይን ሕክምና (Ophthalmology) ዶክተር ነው። እ.አ.አ ከ2000ዓ/ም እስካሁን ድረስ በስልጣን ላይ ተፈናጧል። ከእርሱ በፊትም አባትየው ሀፊዝ አላሳድ (እ.አ.አ ከ1971-2000) ሶሪያን አንቀጥቅጦ ገዝቷታል። የጦር ጀነራልና ከ1946 (እ.አ.አ ጀምሮ የባዐዝ ፓርቲ አባልና መሪም ነበር።) አላዊቶችም የበደዊኖቹ በሽታ አለባቸው። እነርሱም ከላይ እንደገለጽነው-ዘረኝነት፣ ጠባብነትና አክራሪነት ናቸው። ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ በኮሚኒዝም ስብከትና አስተምህሮት ናላቸው የዞሩትን ተማሪዎችና ወጣቶች ለመደገፍ የሩሲያ፣ የቼኮዝሎቫኪያና የቻይና መንግሥታት ያልተገደበ ጥረት አድረገዋል። ለዚህም ማሳያው ደግሞ፣ በመጋቢት 4/1961 ዓ.ም. ሁለት የሩሲያ፣ ሦስት የቼኮዝሎቫኪያና ሁለት የቻይና ዜጎች ኢትዮጵያን በ24 ሰዓታት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። ሁሉም፣ ኮሚኒዝምን በየትምህርት ቤቱና በየኮሌጆቹ ለማስረጽ በመሞከራቸውና ወጣቶችን ለዓመጽ በመቀስቀሳቸው ነበር። ይህ ሴራቸው የተደረሰባቸው ሦስቱ አገሮች ጀብደኛውን የሶሪያ ጎሰኛ መንግሥት እንደፈለጉት ተጠቅመውበታል።

እነዚህ ጊዜ የሠጣቸው ኃያላን መንግሥታት፣ የራሳቸውን ተጽዕኖ ኢትዮጵያ ላይ ለመጣልና በሀገራችን ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያልፈነቀሉት ነገር አልነበረም። ያ ስር የማይሰድላቸው ቢመስላቸው፣ የሶሪያን ጣልቃ ገብነት ተማፀኑ። አርቀው የማያዩትም የሶሪያ መሪዎች ዘው ብለው ገቡበት። ምክንያታቸው ግልጽ ነው፤ የሶሪያ ጣልቃ ገብነት ለሌሎች ኃያል ኮሚኒስቶች መሣሪያና ስልጠና መሸጋገ ድልድይ በመሆን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ "ነጋዴ ራሱ ስለተቀማ ሳይሆን፣ ሌላው ነጋዴ ስለዳነ ይቆጫል፤" በሚለው የአገራችን ምሳሌ አማካይነት ሊተረጎምም ይችላል። የሶሪያ መንግሥት በሀገሩ ውስጥ ያለውን ሁከት፣ ትረምስና ብጥብጥ፣ ከዚያም አልፎ ከእስራኤል ጋር ከነበረው የተደጋገመ የተጠቂነት ሽንፈት የዜጎቹን አስተሳሰብ ለማስቀየስ፣ ሌሎች የእስራኤል መንግሥት ወዳጆች ናቸው ያላቸውን አገሮች በመተናኮል ሊወጣ ሞክሯል። ይህ አባዜ፣ "ወድቆ የቆመው እንደመጎተት" ዓይነት ነው።

ከላይ እንደገለጽነው፣ የሶሪያ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ከጀመረና ኢትዮጵያን መተናኮልም ከጀመረ ቆይቷል። በ1958 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ተጠልፎ ወደካርቱም የተወሰደውን የኢትዮጵያ አይሮፕላን የጠለፈው ወጣቱ ከበደ ደበላ፣ መጀመሪያ ጥገኝነት ያገኘው ሶሪያ ደማስቆ ነበር። የፈረንጆቹ 1969 ዓ.ም. ደግሞ የሶሪያ የጠላትነት ሽፍንፍን ቅልጥጥ ብሎ የወጣበት ዓመት ሆነ። በዚሁ ዓመት ከተሞከሩት የኢትዮጵያን አየር መንገድ የማጥቃት አምስት ሙከራዎች ውስጥ አራቱ የሶሪያ መንግሥት ቀጥተኛ ድጋፍ ነበራቸው። በዕለተ ማክሰኞ መጋቢት 2/1961 ዓ.ም. ፈራንክፈርት አይሮፕላን ማረፊያ በቆመበት በሁለት ፈንጂዎች የተቀጣጠለውን ቦይንግ 707 አይሮፕላን በስልጠናና በትጥቅ የደገፈችው ሶሪያ ነበረች። በዚሁ ዓመት፣ በሚያዝያ 2/1961ዓ/ም በካይሮ ከተማ አቅራቢያ (105 ኪ.ሜ በስተደቡብ) ከወደቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋግላስ ሲ-47 አይሮፕላን አደጋ ጀርባም ያለችው መሰሪ ሶሪያ ነበረች። በሰኔ 11/1961 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡15 ላይ ካራቺ አይሮፕላን ማረፊያ እንደቆመ ነበር በእጅ መትረየስ ከ50 ሜትር ርቀት ላይ አደጋውን የያሉት። እነዚህ ሦስት ሽፍቶች ከሶሪያ ተነስተው ካርቱም ላይ ሴራቸውን ካቀነባበሩ በኋላ፣ ወደ ቤይሩት በረሩ። ከዚያም ፓኪስታን ሁለተኛዋ ከተማ ካራቺ ደረሱ፤ አደጋውንም ጣሉ። ስማቸውም-መሐመድ ኢድሪስ፣ ፍስሐዬ አብርሃምና ዓሊ አብደላ የሚባሉ ናቸው። ሦስቱም ስልጠናቸውንና ትጥቃቸውን ከሶሪያ መንግሥት ያገኙ የጀብሐ አባሎች ነበሩ።

ከእነዚህም የሶሪያ ቅጥረኞች ቀጥሎ፣ በዕለተ ሰኞ ነሐሴ 5/1961 ዓ.ም. ከአስመራ ተነስቶ በባሕር ዳር በኩል ወደአዲስ አበባ ይጓዝ የነበረውን ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የበረራ ቁጥር-231፣ DC-3 አይሮፕላን ባህር ዳር ከተማ ላይ ተሳፍረው ሲጠለፉትና ወደካርቱም ሲወስዱት ያሉት ነገር ቢኖር፣ "እኛ በማኦሴቱንግ ፍልስፍና የምናምን ኮሚኒስቶች ነን። አይሮፕላኑንም አስገድደን ወደካርቱም ያመጣነው ወደኮሚኒስት ቻይና ለመሄድ ላቀድነው ጉዞ ልንጠቀምበት ነው፤" ነበር ያሉት። እነዚህም የሲቪል አቬሽን ወንበዴዎች፣ በቀጥታ ከሶሪያ ጋር ግንኙነት ባይኖራቸው በርዕዮተ-ዓለማቸው የግራ ክንፍ አቀንቃኞች ነበሩ። የዚህኛው ጠለፋ አድራጊዎች ደግሞ፣ ሰባት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ በአንዳንድ የባዕዳንን ሴራ ባልተረዱ ወገኖች በበጎ የሚነሱም ናቸው። ለምሳሌ በ1960 እና 1961ዱ የተማሪዎች ዓመጽ ዋነኛ አስበጥባጭና ተከሳሽ የነበሩት ዋለልኝ መኮንንና ማርታ ይገኙበታል። ከኋላቸው የነበሩት አገሮች ሩሲያና ቼኮዝሎቫኪያ ናቸው። በመስከረም 3/1962ዓ/ም ከድሬዳዋ ወደጂቡቲ ሲበር የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ DC-6B አይሮፕላን መንገድ አስቀይረው ወደ የመን-ኤደን የወሰዱት የጀብሐ ሰዎች ተቀማጭነታቸው ሶሪያ-ደማሽቆ ነበር። ይህ አይሮፕላን 39 መንገደኞችና አምስት የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ይዞ የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም በደህና ሁኔታ በመስከረም 5/1962 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ወደአዲስ አበባ ተመልዋል።

አይሮፕላኑን ሳልይዝ ወደኢትዮጵያ አልመለስም ያሉት ካፒቴን ቀፀላ ኃይሌና ጠለፋውን ያከሸፈው ም/የአስር አለቃ ካሳዬ ታደሰ ኤደን ቀርተዋል። (በነገራችን ላይ፣ ካሳዬ ታደሰ የሻለቃ ማዕረግ አግኝተው በጡረታ ከሠራዊቱ ከተገለሉ በኋላ፣ ኑሯቸውን በሎስ አንጀለስ አድርገዋል።) አደጋው በደረሰበት በመስከረም 3/1962 ዓ.ም. አመሻሹ ላይ መቀመጫውን ሶሪያ-ደማስቆ ያደረገው የኤርትራ ነጻ-አውጪ ድርጅት (ጀብሐ) ኃላፊቱን ወሰደ። ጠለፋውን ያደረኩት "እኔ ነኝ" አለ። ከነዚህ "የቻይና ኮሚኒስት ነኝ!" "የአልባኒያ ኮሚኒስትን የሚከተል ከኔ በላይ ላሳር!" "የሩሲያን ኮሚኒዝም ጡት እየመገመገ ያደገ ማን እንደኔ!" ወይም ደግሞ "በመኮሚኒስትነት እኔ የቼኩ ምልምል አሽከር ጋር የሚፎካከር ማነው?" የሚሉት ወገኖች ሁሉ አንድ ናቸው። ሁሉም የግለሰብን መብት ለመደፍጠጥና የመንጋ ("ተራማጅ ነን ባዮችን") መዋቅር እንደሸረሪት ድር ለማቆሸሽ የሚተጉ ናቸው። በጋማል አብደል ናስር ኮትኳችነት የተጀመረውና የዓረቡን ዓለም በኮሚኒዝም ርዕዮት-ዓለም ለማስተሳሰር የጣረው ባአዝ (BAAZ Party) የሶሪያ አውራ ፓርቲ ሆኖ ነበር። በገለልተኛ ሀገሮች ስራችነቷ ፀንታ ለመቆም የምትፍጨረጨረውን ኢትዮጵያን ኮሚኒስቶቹ አገሮች በጥላቻ ነበር የሚመለከቷት።

ለዚህ ብያኔያን ጥሩ ማሳያ የሚሆነን የጀብሐ 5ተኛ ወታደራዊ ምድብ/ክንፍ አላፊ የነበረውና ይህንን ቃለ-ምልልስ ሲያደርግ የ29ዓመት ወጣት የነበረው ወልዳይ ካሕሳይ ነው። እስከ 12ተኛ ክፍል ድረስ በአስመራ ኮምቦኒ ትምህርት ቤት ተምሯል። ከዚያም በትውልድ መንደሩ በደቀሽሐይ-ሐማሴን ለሁለት ዓመታት ያህል አስተምሯል። በጥቅምት 25/1960 ዓ.ም. ካርቱም ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እጁን ሰጠ። ይህም ቃለ-ምልልስ የተደረገለት ካርቱም ሳለ ነበር። ወልዳይ ስለድርጅቱ እንዲህ አለ፤ "የጀብሐ መሪዎች እኔን የ5ተኛው ወታደራዊ ክፍል አላፊ ያደረጉኝ ወደው አይደለም። 'በድርጅቱ ውስጥ አንድም ክርስቲያን ወታደራዊ መሪ የለም!' ለሚለው የደጋው ኤርትራዊ ቅሬታ ማስተንፈሻ ሲሉ ነው እንጂ፤ በእውነተኛነት አስበውት አይደለም። እኔ ከምመራው ወታደራዊ ክፍል ውጪ ያሉት አራቱም ክፍሎች አንድም ክርስያቲያን ተዋጊ እንኳን የላቸውም። ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት አለው፤ ድርጅቱ የሚሠራው ለአንዳንድ የዓረብ አገሮች ነው። ተዋጊዎቹም ሆኑ አመራሮቻቸው ስልጠና የሚያገኙት ወደሶሪያ እየሄዱ ነው። ለሽፍትነት ስልጠና ወደሶሪያ ከሄዱት 300 (ሦስት መቶ) ሰልጣኞች መካከል፣ አንድም ክርስቲያን አልነበረባቸውም። አምስት አረቢኛ ተናጋሪዎች ብንኖር እንኳን፣ ስማችንን እንድንለውጥ ተደርገናል፤" እያለ ያብራራል።

ወልዳይ ለጀብሐ ርዳታ ስለሚያደርጉትም አገሮች ተጠይቆ ሲያብራራ እንዲህ ብሎ ነበር፤ "ሶሪያና ኢራቅ ወታደሮችን በማሰልጠን በኩል ሲረዱ፣ ሶሪያ በተለይ የጦር መሳሪያም በገፍ ታቀብለናለች። እንደሚታወቀው፣ ጀብሐት እ.አ.አ በ1961 ጂዳ-ሳዑዲ የተመሠረተ በመሆኑ፣ የሳዑዲ መንግሥትና ሕዝብ በገንዘብ በኩል ይረዳል። ከጎረቤት አገሮችም መካከል ግብጽ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያና ጅቡቲ ሽፍቶቹ በዓረብ አገሮች በሚዘዋወሩበት ጊዜ የሚያገለግላቸውን ፓስፖርት በመስጠትና በልዩ ልዩ መንገዶችም ይረዳሉ። በተለይም ግብፅ የመሳሪያ እርዳታዋን ነፍጋን አታውቅም፤"በማለት ገልፆ ነበር። "ቻይናም የወታደሮች ልብስ ሰጥታ፣ ልብሱ ግን ለበረሃው ሊያገለግል ሳይችል ቀርቷል። በቅርቡ ለከፍተኛ የወታደራዊ ስልጠና ስኮላርሺፕ ሰጥታ-20 ሰዎች ተመርጠው ወደቻይና ለመሄድ ወደሶሪያ እያመሩ መሆናቸውንም" አመልክቶ ነበር። ወልዳይ እንዲህም ሲል አከለ፣ "በአሁኑ ሰዓት በኤርትራ ውስጥ 65% ክርስቲያኖችና 35% ደግሞ ሙስሊሞች ይገኛሉ። እስከ 4ተኛ ክፍል ድረስብቻ የነበረውም ትምህርት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አድጓል። ታዲያ እኔ ለምን ብዬ ይሄንን እውነታ ከካዱ ሰዎች ጋር እሰለፋለሁ?" ሲል ተደምጧል(አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 1/1960ዓ/ም፣ ገጽ-1፣5 ይመልከቱ)።

ማጠቃለያ፤
ከሰሞኑ፣ የበሺር አላሳድ መንግሥት ላይ የወታደራዊ ጥቃት ለመክፈት አሜሪካንና ፈረንሳይ ቆርጠው ተነስተዋል። የባዝ ፓርቲና የአላሳድ ወዳጆች ሩሲያና ቻይናም እየተከላከሉለት ናቸው። የፀፅታ ምክር ቤትም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሳዳም ሁሴን የተቀበላቸውን የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች የአላሳድ መንግሥት እንዲያስወግድ ቀን ተቆርጦለታል። የምዕራባዊያኑ አካሄድ፤ ወድቆ የቆመውን እንደመጎተት ያለ ነው። ሳዳምንም እንዲሁ ነበር ያደረጉት። ከ80ኪ.ሜ በላይ የሚወነጨፉትን አልሳሙድ ሚሳይሎቹን እንዲያስወግድ ነገሩትና አስወገደ። ከዚያም፣ ወረሩት። ይህ ሶሪያም ላይ እንደሚደገም ቅንጣት ታክል ጥርጠሬ የለኝም። የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ጠላቶች አሳር መከራቸውን ሲበሉ በማየቴ ምንያህል እደለኛነት እንደሚሰማኝ ልሸሽገው አልዳዳም። ኢትዮጵያና ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን በነፃነታቸው ለዘላለም ትኑሩ! ጠላቶቻቸውም ኹሉ በሰፈሩት ቁና ይሠፈሩ!
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ለሆነው ከአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጋር ለሚያገናኘው የአዲስ አበባን ውጫዊ ቀለበት መንገድ ለመገንባት የሚያስፈልገውን 4.3 ቢሊዮን ብር ብድር፣ የቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ ፈቀደ፡፡
በስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘውና በአሁኑ ወቅት ግንባታው 85 በመቶ የተጠናቀቀው በዓይነቱ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የፍጥነት መንገድ፣ በአዲስ አበባና በአዳማ መካከል ያለውን ርቀት ወደ 80 ኪሎ ሜትር የሚያሳጥር ነው፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ በዘንድሮው በጀት ዓመት የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ መግቢያ ላይ ተቀባይና ወደ መሀል ከተማ ሊያስገቡ የሚችሉ ተጨማሪ መንገዶች ካልተገነቡ፣ የፍጥነት መንገዱ እንዲሰጥ የሚፈለገውን ፈጣን ትራንስፖርት እንደሚያስተጓጉለው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተገንዝቦታል፡፡ 

በመሆኑም የፍጥነት መንገዱ መነሻ ወደሆነው አቃቂ ቃሊቲ የሚያደርስ የአዲስ አበባ ውጫዊ የቀለበት መንገድ መገንባት እንዳለበት መወሰኑን፣ ከባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ውጫዊ የቀለበት መንገዱ በፍጥነት ተጀምሮ መጠናቀቅ እንደሚገባው በማመንም፣ የፍጥነት መንገዱን ግንባታ በማከናወን ላይ ለሚገኘው የቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ የቀለበት መንገዱን እንዲገነባ ከወራት በፊት ሰጥቷል፡፡ 
ይህ ኩባንያ የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ከሚጠይቀው ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ ከፍተኛውን ድርሻ በብድር ያቀረበ ሲሆን፣ ውጫዊ የቀለበት መንገዱን እንዲሠራ የተወሰነውም በተመሳሳይ የግንባታውን ወጪ ራሱ በብድር እንዲያቀርብ በተደረሰ ስምምነት ነው፡፡ 
በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ውጫዊ የቀለበት መንገድ በአጠቃላይ 28.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ አጠቃላይ ወጪውም 4.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ 
ኩባንያው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ባደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ላለፉት ወራት የግንባታውን ወጪ በብድር ለማግኘት ሲያፈላልግ መቆየቱን፣ በተጠናቀቀው ሳምንት ውስጥ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ እንደተፈቀደለት የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ 
የቀለበት መንገዱ ግንባታ በሁለት የአዲስ አበባ አቅጣጫዎች የሚካሄድ ሲሆን፣ አንደኛው ከየረር በመነሳት ከፍጥነት መንገድ መነሻ አቃቂ ቃሊቲ የሚያገናኝ 14.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚኖረው፣ ሁለተኛው የቀለበት መንገድ አካል 13.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሆኖ ከለቡ አካባቢ በመነሳት ከፍጥነት መንገዱ የሚያገናኝ መሆኑን መረጃው ያስረዳል፡፡ 
Souce: http://www.ethiopianreporter.com/
-የአፍሪካን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች ዘንግቷል በሚል ተተቸ
የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ምልከታን በመንተራስ በየዓመቱ ይፋ የሚደረገው ሪፖርት (አፍሪካን ኢኮኖሚክ አውትሉክ)፣ እ.ኤ.አ. በ2013 የነበረውንና በ2014 ይኖራል ብሎ የተነበየው የኢኮኖሚ መስተጋብር ይፋ ሲደረግ፣ አሥር ፈጣን አፍሪካ ኢኮኖሚዎች ካላቸው ውስጥ ኢትዮጵያ አለመካተቷ ስህተት መሆኑን ኃላፊዎቹ አመኑ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀውን ሪፖርት ዘንድሮ ይዞ ብቅ ያለው፣ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አሥር አገሮች መካከል ኢትዮጵያን ዘንግቶ ነው፡፡ ይህ የሆነው ግን ሪፖርቱ ከተዘጋጀ አንድ ዓመት በኋላ ይፋ በመደረጉ ነው ተብሏል፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ለማካተት ሳይቻለው መቅረቱ ስህተት እንደሆነ የገለጹት የባንኩ የኢትዮጵያ ተወካይ ላሚን ባሮው፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በሪፖርቱ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ፈጣን አገሮች ውስጥ ስሟ ባይጠቀስም ዕድገቷ አይካድም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የዘንድሮው ሪፖርት በአፍሪካ እየተካሄዱ ያሉ የፖለቲካ ለውጦችን በአግባቡ አላሳየም ሲሉ ከተቹ ምሁራን መካከል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር
ቆስጠንጢኖስ በርሄ አንዱ ናቸው፡፡ ሪፖርቱ በፖለቲካ ጫና ምክንያት እየተለወጡ የሚገኙትን ሕገ መንግሥቶች ከኢኮኖሚ አኳያ ቢመለከት መልካም እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ከአፍሪካ የሚዘረፈው የውጭ ምንዛሪና አኅጉሪቱ ከሙስናና ጋር በተቆራኘ መንገድ የምታጣውን የተፈጥሮ ሀብት ሪፖርቱ ሊተነትን ሲገባው በዝምታ ማለፉም ለወቀሳ ዳርጎታል፡፡
በአጠቃላይ በአፍሪካ አገሮች የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች የዓለም ክፍሎች አኳያ ሲታይ ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በፋይናንስ ቀውስና በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የሚከሰቱ ጋሬጣዎች ሳይገድቡት በየዓመቱ የአምስት ከመቶ አማካይ ዕድገት ሊመዘገብ በመቻሉ አፍሪካውያንን አሞካሽቷል፡፡ ይህም ቢባል ግን የአፍሪካ አገሮች ያስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት ድህነትን በሚፈለገው መጠን ለመቀነስ ያላስቻለ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  
Source: http://www.ethiopianreporter.com

ለህዝብ የሚታየው ፓትሪያርኩ በተገኙበት ነው:: በየእለቱ ከ3ሺህ ሰው በላይ ቦታውን እየጎበኘ ነው
በአቃቂ ቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል ፓትርያርኩ በተገኙበት ለህዝብ እንዲታይ መግቢያ መንገድ እስኪሰራ ድረስ የተራዘመ ሲሆን፣ በመስቀሉ ላይ የሳይንስ ምርመራ እንደማይፈቀድ ተገለፀ፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት በፍንዳታ ድምፅና በብርሃናማ ቀስተደመና ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል፣ በሚቀጥለው ሳምንት መስከረም 19 ቀን ለህዝብ ይታያል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ፓትርያርኩ የሚገኙበት ስነስርዓት ለማዘጋጀት ጊዜው እንደተራዘመ
የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች ተናግረዋል፡፡ መስቀሉ ለህዝብ የሚታየው ቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ በተገኙበት ስነስርዓት መሆን አለበት መባሉን አስተዳዳሪዎች ጠቅሰው፤ መንገዱ ጭቃ ስለሆነ ጠፈፍ ብሎ ለመኪና እስኪስተካከል ድረስ ቀኑ መራዘሙን ገልፀዋል፡፡ ቀኑ ገና እንዳልተወሰነና ለፓትሪያርኩ ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው ያሉት የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች፤ ስነስርዓቱን ህዳር 11 ቀን ለማካሄድ እንደታሰበ ጠቁመዋል፡፡
ከአዲስ አበባና በአቅራቢያዋ ከሚገኙ አካባቢዎች በየእለቱ ከ3ሺ በላይ ሰዎች ቦታውን እየጎበኙ መሆናቸውን የገለፁት የቤተክርስቲያኗ መጋቢ ሃዲስ ፍሰሃ፤ እኛም በየእለቱ ከ15 ጊዜ በላይ ስለ ተከሰተው ተዓምር ገለፃ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ መስቀሉ ባረፈበት ሳር ላይ እንዲሁም ወደ ቤተ መቅደሱ ከገባ በኋላ የተነሱ ፎቶዎችን የያዘ ካርድ ታትሞ ለምዕመናን በ10 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በፎቶግራፍ ላይ የሚታየው መስቀል በሰው የተሰራ የዕደ ጥበብ ውጤት እንደሚመስል በመጥቀስ ከሰማይ ወረደ መባሉን የሚጠረጥሩ መኖራቸውን በተመለከተ መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፣ እውነቱን የሚያውቀው ፈጣሪ ነው ብለዋል፡፡
በምድራችን የተሰራ የሚመስል መስቀል ከሰማይ ሊወርድ አይችልም የምንል ከሆነ፣ በምድራችን የምናረባው አይነት በግ ለአብርሃም ከሰማይ ወርዶለታል የሚለውን የመፅሃፍ ቅዱስ ቃል መጠራጠር ይሆናል ብለዋል መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፡፡ የመስቀሉን ስሪት እንዲሁም መስቀሉ አረፈበት የተባለውን ሳርና አፈር ለመመርመር ሃሳብ ተነስቶ እንደሆነ ተጠይቀው መጋቢ ሃዲስ ሲመልሱ፤ “ይህ መስቀል የቤተክርስቲያኒቱ የክብር መገለጫ ነው” በማለት ተቃውመዋል፡፡
እስካሁን በስፍራው የተፈፀመውን ተአምር ሰምተው የሚያደንቁ እንጂ በመስቀሉና በቦታው ላይ እንመራመራለን የሚሉ ምሁራን አላጋጠሙኝም ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ “እንዲህ ያለ ጥያቄ ያላቸውም ካሉም፣ የማይሞከር ነው” ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ ቦታውን እንፈትሻለን፣ የወረደውን መስቀል እንመረምራለን ለሚሉ የሳይንስ ባለሙያዎች ፈፅሞ አይፈቀድም ብለዋል፡፡ መስቀሉ ከሰማይ ከመውረዱ አስቀድሞ ራዕይ ታይቶኛል የሚል ሰው እስካሁን አላጋጠመን ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ ቤተክርስቲያኒቱን ያቋቋሙት አባት ግን፣ ቦታው የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ እንደሚሆን በራዕይ እንደታያቸው ተናግረው ነበር ብለዋል፡፡
Source: Addis Admass
የፕሬዚዳንትነት ቆይታቸውን በማጠናቀቅ ላለፉት 12 ዓመታት የቆዩበትን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለአዲሱ ፕሬዚዳንት እንደሚያስረክቡ ለሚጠበቁት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ መኖሪያ እንዲሆን በወር 530 ሺሕ ብር የሚከፈልበት ቤት ለመከራየት የተገባው ውል ተሰረዘ፡፡
ምንጮች እንደገለጹት፣ ፕሬዚዳንት ግርማ በቅርቡ ከቤተ መንግሥት ሲለቁ ከነቤተሰቦቻቸው እስከ ሕይወት ፍፃሜያቸው ይኖሩበታል ተብሎ የተመረጠውና በወር 530 ሺሕ ብር ለመክፈል ከቤቱ ባለቤት ጋር የተደረገው ስምምነት፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ቀርቦ ውል ታስሮበት ነበር፡፡ ሆኖም የኪራይ ስምምነቱ ውል ከተፈረመ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ውሉ እንዲቋረጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ 
አዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ የሚገኘውን ለፕሬዚዳንት ግርማ መኖሪያ የተመረጠውን ቤት ለመከራየት
ከአከራዩ ጋር የኪራይ ውል ስምምነት ያደረገው  የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ነበር፡፡ ቀድሞም ቢሆን ስምምነቱ የተጋነነና ለG+1 መኖሪያ ቤት ይህን ያህል ዋጋ ይከፈላል የሚል ሙግት ቀርቦ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ በይፋ ከተፈረመ በኋላ ግን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ኪራይ ተገቢ አይደለም በማለት ውሳኔ በማስተላለፋቸው፣ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት በውሉ ውስጥ የተካተቱትንና ውሉን ለማፍረስ ያስችሉኛል ያላቸውን አንቀጾች በመጥቀስ እንዲሰረዝ አድርጓል፡፡ ይህንንም የመኖሪያ ቤቱን ለማከራየት ውል ለገቡት ባለንብረት በደብዳቤ ማስታወቁንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የኪራይ ስምምነቱን የመዘገበው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤትም ውሉ መሰረዙን እንዲያውቅ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ጽፏል ተብሏል፡፡ 
ሕጋዊ የውል ስምምነት ስለመደረጉ ማረጋገጫ የሰጠውና ምዝገባ ያካሄደው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት፣ ለፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ተብሎ የኪራይ ስምምነት የተደረገበት ውል እንዲሰርዘው በደብዳቤ ተገልፆለታል ተብሏል፡፡ 
ተጋነነ የተባለው የቤት ኪራይ ውል የተፈጸመው በአገሪቱ ሕግ መሠረት ሥልጣናቸውን ለለቀቁት ፕሬዚዳንት ቀሪ ሕይወታቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲያሳልፉ አስፈላጊው ጥቅማ ጥቅም መጠበቅ ስላለበት ቢሆንም በዚህን ያህል ዋጋ ቤት መከራየት ተገቢ አለመሆኑን የሚገልጹም አሉ፡፡ 
እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ ፕሬዚዳንቱ ከቤተ መንግሥት ሲወጡ ሊኖሩበት የሚችለውን ቤት ለማዘጋጀት የቤተ መንግሥት ጽሕፈት ቤት አምስት የተያዩ ቤቶችን በመምረጥ የተሻለ ነው ተብሎ የተመረጠው አሁን ውሉ እንዲቋረጥበት የተደረገው ቤት ነው ተብሏል፡፡ 
ከኃላፊነት የተነሱት የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን የወጣው አዋጅ እንደሚደነግገውም ለተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ቤት እንደሚዘጋጅ ይጠቅሳል፡፡ 
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 መሠረት የመኖሪያ ቤት አገልግሎትን በተመለከተ የተጠቀሰው ከኃላፊነት የተነሳ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ለራሱና ለቤተሰቡ መኖሪያነት የሚያገለግል የሠራተኞች ደመወዝን ጨምሮ በመንግሥት ወጪ የሚተዳደር ከአራት እስከ አምስት መኝታ ክፍሎች ያሉት መኖሪያ ቤት የሚሰጠው መሆኑን ነው፡፡ 
ከሚሰጣቸው መኖሪያ ቤት ባሻገር ደረጃቸውን የጠበቁ ሦስት ለመጓጓዣ የሚያገለግሉ የመንግሥት ተሽከርካሪዎችም ይመደቡላቸዋል፡፡ ለተሽከርካሪው ሹፌር ደመወዝ፣ የነዳጅና የጥገና እንዲሁም ሌላ ወጪ በመንግሥት የሚሸፈን መሆኑንም ያመለክታል፡፡ 
ከኃላፊነቱ የሚነሱ ሦስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተለያዩ የሕዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ከተሰማራ መኖሪያ ቤቱ በሚገኝበት ከተማ የቢሮ አገልግሎት እንደሚሰጠው የሚደነግግ ሲሆን፣ ባለመብቶቹ የሚመርጧቸውና መንግሥት ደመወዛቸውን የሚከፍላቸው አንድ ጸሐፊና አንድ ባለሙያ ጭምር ይኖራቸዋል፡፡ 
በዚሁ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት ከኃላፊነት የተነሳ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር በሞት ሲለይ ጥቅማ ጥቅሙ ለቤተሰቦቻቸው ይተላለፋል፡፡ በዚሁ መሠረት በሞት ሲለዩ የግል ወጪ አበል ለባለቤቱ መክፈሉ የሚቀጥል ሲሆን፣ የባለመብቱ ባቤትም ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩም የመኖሪያ ቤት፣ የሕክምና ክፍያ የግል ደኅንነት ጥበቃ አገልግሎቶች እንደማይቋረጡበትም ይደነግጋል፡፡ 
ፕሬዚዳንት ግርማ የ12 ዓመታት የፕሬዚዳንት ዘመን መጠናቀቅን ተከትሎ በአዋጁ መሠረት መንግሥት የሚያዘጋጅላቸው ቤት አዲሱ ፕሬዚዳንት ማንነት ይፋ ከመሆኑ በፊት ይዘጋጃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡  
Source: Reporter

የተመድ የናይሮቢዉን ጥቃት በጥብቅ አወገዘ

የተመድ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በኬንያ ናይሮቢ፤ ገበያ ማዕከል የተከሰተዉን ደም አፋሳሽ ጥቃት በጥብቅ አወገዘ። አሸባሪነት የዓለማቀፍን ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርስ ግዙፍ ጠንቅ ነዉ ሲል፤ በኒዮርክ የሚገኘዉ የተመድ ጽ/ቤት አስታዉቀዋል።
በናይሮቢ «ዌስት ጌት» በተባለ የገበያ ማዕከል በደረሰዉ አስከፊ ጥቃት እስካሁን 59 ሰዎች መገደላቸዉን እና ወደ 200 ሰዎች መቁሰላቸዉን የሀገሪቱ መንግስት አስታዉቋል።
ከሟቾቹ መካከል የዉጭ አገር ዜጎች ይገኙበታል። የኬንያ ፖሊስ እንዳስታወቀዉ ትናንት ቅዳሜ 18 ጨንበል ያጠለቁ ታጣቂዎች፤ ዊስት ጌት በተሰኘዉ፤ የገበያ ማዕከል ሰርጎ በመግባት የተኩስ ሩምታ ከፍተዋል። የእጅ ቦንብ አፈንድተዉ ከባድ ጥቃት አድርሰዋል። በመገበያያ ማዕከሉ አጋቾች ቦታውን በመቆጣጠር፤ ከፖሊስ ጋር ከበድ ያለ የመሳሪያ ልውወጥ ማድረጋቸውን እና ዛሬ
እሁድ በተደጋጋሚ የማሳሪያ ድምጽ መስማታቸውን በቦታው የሚገኙ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ከሟቾች መካከል የፕሪዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እህት ልጅ እና እጮኛዉ፤ ሳይኖሩበት እንዳልቀረም ተገልጾአል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጥቃቱን አስመልክቶ ባሰሙት ንግግር ሁሉም አጋቾች የትም ቢገቡ ተይዘው ቅጣትን እንደሚቀበሉ ቃል ገብተዋል፡፡ በዚህ ጥቃትም ኡሁሩ ኬንያታ፤
«በዚህ ጥቃት የቤተሰብ አባላትን ላጡ ወገኖች ሃዘኔን እገልጻለሁ። ምን አይነት የሃዘን ስሜት ዉስጥ እንዳሉ መገመት አይሳነኝም፤ ምክንያቱም እኔም በዚህ ጥቃት በጣም ቅርብ ዘመዶቼን አጥቻለሁ» ፖሊስ ምን ያል አጋቾች በህንጻው ውስጥ እንዳሉ መረጃው ባይኖረውም ፤ የኬንያ የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር ጆሴፍ ኦሌ ሊንኩ ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ታጣቂዎች ታጋቾችን ይዘዉ በገበያ ማዕከሉ ህንጻ ዉስጥ ተደብቅዉ ሳይኖሩ እንደማይቀር ገልጸዋል። በኬንያ የሀገር አስተዳደር ሚኒስትር ጆሴፍ ኦሌ ሊንኩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ
« ስለ ዝርዝር ጉዳዮ አሁን ምንም መናገር አንሻም፤ ነገር ግን የኬንያ የፀጥታ ጥበቃ አባላት ሁኔታዉን ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ስር ማድረጋቸዉን መግለፅ እወዳለሁ። አሁን ሁላችሁንም ማመስገን እፈልጋለሁ። በቀጣይ ስለሚፈጠረዉ ክስተት ምናልባትም በአንድ ሰዓት ግዜ ዉስጥ እናሳዉቃችኋለን። አሁን እባካችሁ በቀጣይ መሰራት ያለበት ጉዳይ ተግባራዊ እንድናደርግ ልቀቁን» ብሪታንያ እስካሁን በናይሮኒዉ ጥቃት በጥቂቱ ሶስት ዜጎችዋ እንደተገደሉባት የብሪታንያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታዉቋል።
በሶማልያ የሚንቀሳቀሰዉና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለዉ የሚነገርለት የደፈጣ ተዋጊ ቡድን አልሸባብ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አሳውቋል፡፡
በሌላ በኩል እስካሁን የገበያ ማዕከልን ከአጋቾች ለማስለቀቅ በሚደረግ ጥረት ላይ እስራኤላዉያን አማካሪዎች የኬንያን ወታደራዊ ሃይሎችን በስልታዊ አሰራር ምክርን በመስጠት ላይ መሆናቸዉን የእስራኤል መንግስት ገልጾአል። 59 ሰዎች የተገደሉበት የናይሮቢዉ ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል በከፊል የእስራኤላዉያን እንደሆነ ተመልክቶአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኬንያ ድህረ ፕሬዚደንታው ምርጫ፤ በተከሰተው ግጭት በስብዕና ላይ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ክስ፤ ደን ኻግ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የጦር ወንጀለኞች መርማሪ ፍርድ ቤት የቀረቡት፤ የኬንያ ምክትል ፕሬዚደንት የዊልያም ሩቶ ጠበቆች፤ በኬንያ የተከሰተዉን ጥቃትን ለመከታተል ሩቶ ወደ ሀገራቸዉ መመለስ እንዲችሉና የፍርድ ሂደቱ ለሌላ ግዜ ቀነቀጠሮ እንዲሰጠዉ መጠየቃቸዉ ታዉቋል።
አዜብ ታደሰ
ልደት አበበ
Source: www.dw.de

የውጭ ሀገር ዜጎች ጥላቻ ዳግም በደቡብ አፍሪቃ መቀስቀሱ፣ በፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝ በምትመራው አነስተኛዋ የአፍሪቃ ሀገር የምርጫ ሂደት፣ እንዲሁም ሶማሊያን የሚመለከት ጉባኤ በብራስልስ የተሰኙት ርዕሰ ጉዳዮች በትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን ከተካተቱት ጥንቅሮች ዋነኖቹ ናቸው።
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ፖርት ኤሊዛቤዝ በተሰኘው አካባቢ የውጭ ሀገር ጥላቻ የተጠናወታቸው ግለሰቦች ሰሞኑን የሶማሊያውያን የሆኑ ንብረቶችን ሲመዘብሩ፣ ሲዘርፉ ብሎም እሳት ሲለቁባቸው ቆይተዋል። ከ1200 የሚበልጡ ሶማሊያውያንም ለህይወታቸው በመስጋት ቤት ንብረታቸውን ጣጥለው በሽሽት ላይ ይገኛሉ። አብዛኞቹም ታሪክ እራሱን እንዳይደግም አጥብቀው ሰግተዋል። የዛሬ አምስት ዓመታት ግድም
እጅግ የተቆጡ ስብስቦች በመላ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ጥቁር አፍሪቃውያን ላይ ድንገት ተነስተው ጥፋት ማድረሳቸው ይታወሳል። በያኔው ቁጣ በቀሰቀሰው ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ቤቶች ዶግ አመድ ሆነዋል፣ ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የዶቼ ቬሌው ሰብሪ ገቬንደር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በፍርሀት ተውጠው የሚገኙ ስደተኞችን አነጋግሮ የሚከተለውን ልኮልናል፤ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

የ30 ዓመቱ ፍሬዲ ምባዬ በዜግነት ብሩንዲያዊ ነው። ወደ ደቡብማ አፍሪቃ የመጣው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው። ላለፉት ሶስት ዓመታት የዕለት ጉርሱን የሚያሰባስበው የወደብ ከተማ በሆነችው ደርባን ውስጥ ከተሰማራበት የመኪና ጥበቃ ስራ ከሚያገኘው ገቢ ነው። የሚኖረው ከታናሽ ወንድሙ ጋር በአንድ መጠለያ ውስጥ ነው። ህይወት ሁለቱንም ዕለት በዕለት ታታግላቸዋለች። ጎናቸውን ለሚያሳርፉበት መጠለያ እና ለምግባቸው የሚሆን በቂ ገንዘብ ለማግኘት ሠርክ ተጨማሪ ስራ ፈልገው መታተር አለባቸው። ያም ብቻ አይደለም እንዲያ ላይ እታች ብለው ከሚያገኟት ገቢ ላይም ቆጥበው ሀገር ቤት ለሚገኙት ሰባቱ እህቶቻቸው እና ሁለቱ ወንድሞቻቸው መላክ ይጠበቅባቸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ፍሬዲን እጅግ የሚያጨንቀው ያ አይደለም። ለፍሬዲ ጭንቀቱ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ አፍሪቃውያን ስደተኞች ላይ ዳግም የተቀሰቀሰው ጥላቻና ጥቃት ነው።
«በነገሩበጣምልባችንተነክቷል።እነዛንሰዎችምንእንደነካቸውእንጃ።ምንአለባይሰርቁን፣ምንአለባይመዘብሩን።»

ደቡብ አፍሪቃ የውጭ ዜጎች ጥላቻና ጥቃት

ዴቪድ ፒቶሾም ቢሆን ተመሳሳይ ስሜት ነው ያለው። ከኮንጎ ተነስቶ ደቡብ አፍሪቃ የገባው ከአስር ዓመታት በፊት ነው። የሚተዳደረውም ከጥበቃ በሚያገኘው ገንዘብ ነው። የዛሬ አምስት ዓመታት ግድም በደቡብ አፍሪቃ ተቀስቅሶ ከነበረው የውጭ ሀገር ነዋሪዎች ጥላቻ ቀዳሚውንና ዋነኛውን ያስታውሳል። በቁጣ የተሞሉ ሰዎች በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የሚገኙ አፍሪቃውያን ስደተኞችን ሲያጠቁም ከሚኖርበት ስፍራ ሆኖ ታዝቧል። ንብረትነታቸው የሶማሌያውያን የሆኑ መደብሮች በእሳት ተንቀልቅለዋል። በስተመጨረሻም ጥቃት ፈፃሚዎቹ የ62 ሰዎችን ልሳን እስከወዲያኛው ዘግተዋል፤ 47.000 ሰዎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ጣብያዎች እንዲጎርፉም ተገደዋል። ዳግም ያ ቁጣ አገርሽቶ በርካታ ቤቶችን የእሳት ነበልባል ሲያንቀለቅላቸው ዴቪድ ፍርሀት ገብቶት እጅግ ርዷል።
«ለእኔ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ መቆየት አያስደስተኝም፤ ወይንም ጥሩ ስሜት አይሰጠኝም። እዚህ ተቀምጦ ያን ሁሉ ነገር መመልከትም አልፈልግም። ከእዚህ ሀገር መውጣት ነው የምሻው፤ ምክንያቱም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚሆነው ነገር ሁሉ አንድ ቀን እኔንም መጉዳቱ አይቀርም።»
የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ማናቸውም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች ፈፅሞ ተቀባይነት የላቸውም ባይ ነው። ፖሊስ ከ200 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሎዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ፖሊስ ጥቃቱ የተፈፀመው ከውጭ ሀገር የመጡ ስደተኞችን በሚጠሉ ግለሰቦች አይደለም ሲል አስተባብሏል። ይልቁንስ ጥቃቱ የተፈፀመው በወንጀለኞች ነው ሲል ተደምጧል። የሠብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የሐይማኖት ተቋማት መንግሥት አፍሪቃውያን ስደተኞች በአግባቡ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተገቢውን ስራ አላከናወነም ሲሉ ይተቻሉ። እናም መንግሥት ጥቃት በተፈፀመ ቁጥር ብጥብጡን የሚያወግዝ የመግለጫ ጋጋታ ከሚያቀርብ ይልቅ የበለጠ ሊሰራ ይገባል ይላሉ። ዶክ ፊስመር የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ናቸው።
«እነዚህ ሁሉ ነገሮች በእዚህ መልኩ ከቀጠሉ ለሀገራችን መፃዒ ዕጣ መልካም አይደሉም። ምክንያቱም እንደእነዛ አይነት በርካታ ሰዎች አሉንና። መንግሥት ይህን ጉዳይ እጅግ በጥንቃቄ ሊመለከተውና ምን ሊያደርግ እንደሚገባው ከውሳኔ ላይ መድረስ አለበት፤ ምክንያቱም ነገሩ እየተደጋገመ ነውና። ስለእዚህ የሆነ ነገር ማድረግ አለብን።»
ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳያችን ስንሻገርም ከእዛው ከደቡብ አፍሪቃ ብዙም አልራቅንም። አፍሪቃ ውስጥ ፍፁም ዘውዳዊ በሆነ ስርዓት ወደምትተዳደረው አነስተኛዋ የደቡብ አፍሪቃ ሀገር ስዋዚላንድ ነው የምናቀናው።
በእዚህች አነስተኛ ሀገር መስከረም 10 ቀን 2005 ዓም የምክር ቤት አባላት ምርጫ ተካሂዷል። ሆኖም ፖለቲካዊ ለውጥ የመምጣቱ ነገር ግን እምብዛም ተስፋ የሚጣልበት አይነት አይደለም። ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ በደቡብ አፍሪቃ እና ሞዛምቢክ መሀከል የምትገኘውን ትንሽዬ ሀገር ሲመሩ 27 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ንጉሡ ከስልጣናቸውም ሆነ ከአገዛዝ ስርዓታቸው አንዳች እንዲቀየር የሚፈልጉ አይነት አይደሉም። ሀገሪቱ ግን ዲሚክራሲያዊ ሂደት በአስቸኳይ የሚያሻት ናት። የማኅበረሰቡ ሰቆቃ፣ የምጣኔ ሀብቱ ድቀት ብሎም የንጉሣውያኑ ቅጥ አልባ ብክነት መረን ለቋል። እንዲያም ሆኖ ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ አሁንም ሰጥ ለጥ አድርገው መግዛት ነው የሚሹት። ዓለም ግን ያሸበረቁ ስዕላቸውን እንዲያይላቸው ይፈልጋሉ። ምርጫ በስዋዚላንድ፤ ጁሊያ ሐን የላከችውን ዘገባ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።
የሚጨፍሩት፣ የሚዘምሩት ለንጉሡ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፤ ዳሌያቸው ላይ ጣል ካደረጉት ብጣቂ ጨርቅ ውጪ ከፊል ርቃናቸውን፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ዓርማ በሚወክለው ሠማያዊ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀላማት አጊጠው ለንጉሡ ይጨፍራሉ።
ከምርጫው ቀደም ብሎ በሣምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነ በእዚህ መሰሉ ስነስርዓት ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ የሚሽቶቻቸውን ቁጥር ለማብዛት ከውሳኔ ላይ ደርሰዋል። እናም ትምህርቷን ከአጠናቀቀች ገና ብዙም ያልቆየችው የ18 ዓመቷ ወጣት 15ኛዋ ውሃ አጣጪያቸው ትሆናለች። የምዋሲቲ ምኞት ተሟልቷል። የ45 ዓመቱ ጎልማሳ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ስዋዚላንዶችን ሰጥ ለጥ አድርገው ነው የሚያስተዳድሩት።
ትናንት ስዋዚላንዶች የምክር ቤት አባላትን እንዲመርጡ ተፈቅዶላቸዋል። በእርግጥ ግን ምርጫው አንዳች የሚቀይረው ነገር አይኖርም ሲሉ በስዋዚላንድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሰረት የሚሰራው «የስዋዚላንድ ወጣቶች ምክር ቤት» ዋና ፀሀፊ ማክስዌል ድላሚኒ ይተቻሉ።
«ፍፁም ዘውዳዊ በሆነ አገዛዝ ስር ነው የምንገኘው፤ ምክንያቱም ንጉሡ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው። ሕዝቡን የተጠቀሙበት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በስዋዚላንድ ተዓማኒ ምርጫ ተካሂዷል ብሎ እንዲያምን ለማታለል ነው።»
በምዕራባዊያን መለከያ ሲታይ ምርጫ ተብየው አንዳች ዲሞክራሲያዊ ይዘት የለውም። የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል። «ፑዴሞ» ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ በኅቡዕ እና ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በስደት ነው የሚንቀሳቀሰው። የምክር ቤት ተወካዮቹ ነፃ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተደርገው ነው የሚታዩት ግን ከጎሣ መሪዎች ድጋፍ ሊኖራቸው ይገባል። ከ65ቱ የምክር ቤት አባላት መካከል አስሩ በቀጥታ የሚሰየሙት በንጉሡ በራሳቸው ቀጥተኛ ቀጭን ትዕዛዝ ነው። የተቀሩትም ቢሆኑ የንጉሡ ይሁንታ ያስፈልጋቸዋል። ከእዚያ ባሻገር ንጉሡ ከህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላቱ ሁለት ሶስተኛውን፣ ጠቅላይ ሚንስትሩን፣ ካቢኔውን ብሎም ከፍተኛ ዳኞችን እራሳቸው በቀጥታ ይሾማሉ። ምክር ቤቱ ሙሉ በሙሉ ጥርስ አልባ ነው። ሕግ አውጪውም፣ ሕግ አስተርጓሚውም፣ ሕግ አስፈፃሚውም እኚሁ አንድ ንጉሥ ናቸው። ሠማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ እንዲሉ በስዋዚላንድ ትንፍሽ ማለት አይፈቀድም። የመብት ተሟጋቹ ማክስዌል ድላሚኒ ከጭቆናው ገፈት ቀማሾች አንዱ ነው።
«ንጉሡ በሕዝቡ የሚደረግባቸውን ሂስ በቀና የሚቀበሉ አይነት አይደሉም። ስለእዚህም በየጊዜው ሰዎች በዘፈቀደ ወህኒ ይወረወራሉ፣ አካልን የሚያሰቃይ ተግባር ይፈፀምባቸዋል አለያም ከሀገር እንዲሰደዱ ይገደዳሉ። እኔ እራሴ መንግሥት በሀሰት በመሰረተብኝ ሁለት ክሶች ምክንያት ከተጣልኩበት ዘብጥያ የወጣሁት በዋስ ነው።»
ድላሚኒ እምቢኝ ሲል በተደጋጋሚ ንጉሡ ላይ ተቃውሞ አሰምቷል። ከዛሬ ሁለት ዓመታት በፊት ንጉሡን በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ስዋዚላንዶች ወደ አደባባይ ሲወጡ ድላሚኒም ተቀላቅሏቸው ነበር። በእርግጥ ሕዝቡ በነቂስ «ሆ!» ብሎ የወጣበት ሰልፍ አይደለም። ያኔ በሰሜን አፍሪቃ ሃገራት የተቀሰቀሰው ዓመፅ ያነሳሳቸው ስዋዚላንዶች በሀገሪቱ ላይ የተጫነው የድህነት መርግ እንዳንገፈገፋቸው ለመግለፅ ነበር የተሰለፉት።
ስዋዚላንድ በዓለማችን ከሚገኙት 10 እጅግ ድሀ ሃገራት መካከል ትመደባለች። ከሶስት እጁ ሁለት ያህሉ የሚኖረው እጅግ ከድህነት በታች በሆነ ሁናቴ ውስጥ ነው። የሀገሪቱ የገንዘብ ምንጭ የውጭ ሃገራት በተለይም ደቡብ አፍሪቃ ናት። በዋናነት ስኳርን መሰረት ያደረገው የውጭ ንግድ የስኳር ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ በመውደቁ የተነሳ በከፍተኛ ተጎድቷል። ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ ግን ዛሬም በ13 ቤተመንግስቶቻቸው ውስጥ ተንፈላሰው የተንደላቀቀ ህይወት ይመራሉ። ሲያሻቸው እመር ብለው የግል ጄታቸውን ሊያስነሱ አለያም ቄንጠኛ ሊሞዚናቸውን ሊያሽከረክሩ የሚገዳቸው የለም። ሀገራቸው ግን በሙስና ነቅዛለች። ከነዋሪዎቹ ከሶስቱ አንዱ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር ነው የሚኖረው። በዓለማችን የተዳቀቀች ባሕር አልባዋ ትንሽዬ ሀገር ስዋዚላንድ ትናንት በንጉሡ ጫና ስርም ቢሆን የምክር ቤት አባላት ምርጫ አከናውናለች።
አሁን ደግሞ ሶማሊያንና መካከለኛው አፍሪቃን በአጭሩ እንዳስሳለን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሶማሊያን መልሶ ለመግንባት በሚል 1.8 ቢሊዮን ዩሮ ርዳታ ለመለገስ ቃል መግባቱ በእዚሁ ሣምንት ከወደ ብራስልስ ተሰምቷል። በዕርዳታ መልክ የሚቀርበው ገንዘብ በዋናነት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብትና የፀጥታ ሁናቴ ለማጠናከር ያግዛል ተብሏል። የሶማሌ መሪዎች እና ከ50 ሃገራት የተውጣጡ ልዑካናት ሶማሊያን ለመደገፍ ብራስልስ ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ ተገናኝተው ተነጋግረዋል። በሶማሊያ የፍትሕ ስርዓት እንዲገነባ፣ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲዳብርና የዕለት ተዕለት የፀጥታ ሁናቴው እንዲሻሻል እገዛ ያደርጋል የተባለለትን ዕቅድም መንደፋቸው ታውቋል።
መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ ደግሞ የሴሌካ ጥምረት የተሰኘ አማፂ ቡድን ሀገሪቱን በማመስ እና ሕዝቡን በማስጨነቅ ላይ ይገኛል። ይህ የተለያዩ አማፂያን ኅብረት የፈጠሩበት የሴሌካ አማፂያን ቡድን በሀገሪቱ ስልጣን የተቆናጠጠው መጋቢት 15 ቀን፥ 2005 ዓም ሲሆን፤ የሀገሪቱን ለ10 ዓመታት የመሩትን ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ቦዚዚን በማስወገድ ነበር ወደ መንበሩ የወጣው። የሴሌካ ጥምር የዓማፂያን ቡድን ስርዓት አልባ በሆነው የሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ሲንቀሳቀስ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል። ቡድኑ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ ሚካኤል ጆቶዲያን የሀገሪቱ ርዕሠ ብሔር አድርጎ ሲሾም አማፂያኑ ሀገሪቱን በመዝረፍ፣ በርካቶችን በመግደልና ወደ 180,000 የሚሆኑ ነዋሪዎችን በማፈናቀል ይከሰሳሉ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ
Source www.dw.de
ሰዎች ካለፈ እጅግ መጥፎ ድርጊት ፣ እስከምን ድረስ ትምህርት ይቀስማሉ? በተለያዩ ዘመናት ያጋጠሙ ሁኔታዎችን ፤ ጦርነቶችን ፤ ወረራዎችን ፤ ውዝግቦችን ስንመረምር ፣ ሰው፤ ጭካኔ የሚያሳይባቸው መሣሪያዎች በሥነ ቴክኑኒክ ተሻሽለው ተሠርተው ከመቅረባቸው 
በስተቀር፤ እርሱ ራሱ የባህርይ ለውጥ ያሳየበት ሁኔታ የለም። በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተገለጠው ፤ ቃየል ብቸኛ ታናሽ ወንድሙን፤ አቤልን በድንጋይ ቀጥቅጦ ነው የገደለው። የዛሬው ዘመን ሰው «ወንድሙ» ን ፣ በአብራሪ- የለሽ አኤሮፕላን፣ ወይም በሚሳይል ወይም በመርዘኛ ጋዝ ማጥፋት ይችላል።
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን፤ ሰሞኑን በተደጋጋሚ ካነሱአቸው ጉዳዮች አንዱ በሶሪያ ፣ ረቡዕ ፤ ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ ም፤
በደማስቆ መዳረሻ፣ በተተኮሰ መርዘኛ ጋዝ ፤ ቁጥራቸው በ 500 እና 1,300 መካከል የሚገመት ሰዎች ልጆችና ጎልማሶች የሞቱበት ሌሎች በዛ ያሉም የቆሰሉበትን ሁኔታ ነው።
ማን ይህን ፈጸመው ? ማን ነው ኀላፊው የሚለው ጥያቄ ቢያከራክርም ፤ ማንም ይፈጽመው ድርጊቱ ፤ ፍጹም ዘግናኝና የጭካኔ ሥራ መሆኑ አያጠያይቅም። በደለኛውን አጣርቶ የማወቁ ጉዳይ ለጊዜው ያስቸገረ ይምሰል እንጂ፣ ያጠፋው ተገቢ ቅጣት ማግኘት አይገባውም ብሎ የሚከራከር ይኖራል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል።

እንደ ፀረ ተባይ መድኃኒት በቀላሉ የሚቀመሙ፤ ሆኖም ለሰው ጤንነትም ሆነ ሕልውና እጅግ ጠንቀኞች የሆኑ ጋዞች አሉ ። ጥቂቶችን እንጥቀስ፤ እነርሱም፤ የሚሠነፍግ፣ የሰናፍጭ መሰል ሽታ ያለው መርዘኛ ጋዝ(Mustard Gas)፣ Tabun, Sarin ,እና VX የተሰኙት የጋዞች የቅመማ ጦር መሣሪያዎች ናቸው።
በመጀመሪያ በዋነኛነት ከድኝ የሚቀመመውን የሰናፍጭ ዓይነት ወይም የነጭ ሽንኩርት ዓይነት ሽታ ያለውን ጋዝ እንመልከት።
«ሰልፈር ማስተርድ» ወይም «ማስተርድ ጋዝ»---የተጣራው ቀለም የለውም፤ ሆኖም ፤ ለጥፋት በጦር መሳሪያነት የሚቀመመው ወደ ቢጫ የሚያደላ ቡናማ ቀለም ነው ያለው።
የሥነ -ቅመማ ስሙ C4H8Cl2S ነው። ይህም ማለት ካርበን 4 ፣ ሃይድሮጂን 8፣ ክሎሪን 2 እና አንድ እጅ ድኝ ያለው የቅመማ ውጤት መሆኑ ነው። ይህን እጅግ አደገኛ የጋዝ ጦር መሣሪያ እ ጎ አ በ 1916 ፤ አንደኛው የዓለም ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተ ሙከራ ቀምመው የጀርመንን ንጉሣዊ መንግሥት ጦር ሠራዊት ያስታጠቁት፣ ቪልሄልም ሎመል እና ቪልሄልም ሽታይንኮፍ የተባሉት ሳይንቲስቶች ናቸው። እናም ይህ እጅግ አደገኛ ፤ ጠንቀኛ የቅመማ ጦር መሣሪያ በዓመቱ፤ ማለትን በ 1917 ፣ ኢፕረስ፤ ቤልጅግ ላይ በብሪታንያና በካናዳውያን ወታደሮች ላይ ተረጭቶ ዘግናኝ ዕልቂትና የመቆስል አደጋ አድርሷል። ብሪታንያም በ 1918 ራሷ በቀመመችው መርዘኛ ጋዝ በጀርመናውያኑ ወታደሮች ላይ መበቀሏ አልቀረም።
በጀኔቩ ዓለም አቀፍ ስምምነት ፣ የመርዘኛ ቅመማ ጦር መሣሪያዎች ማምረትን (መቀመምን)፤ ማከማቸትንና መሸጥንም የሚገታ ዓለም አቀፍ ስምምነት ይኑር እንጂ፣ የተለያዩ መንግሥታት በተለያዩ አገሮች ፣ በተለይ መከላከልም መበቀልም በማይችለው ሲቭል ህዝብ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ለምሳሌ ያህል፤

ብሪታንያ፤ እ ጎ አ በ 1919 በሶቭየት ቀይ ጦር ሠራዊት ላይ ፣
እስፓኝና ፈረንሳይ፤ ሞሮኮ ውስጥ በተቃውሞ በተንቀሳቀሱ ወገኖች ላይ፤
ኢጣልያ፤ ከ 1928 እስከ 1932 በኢትዮጵያ ላይ መርዘኛውን ጋዝ በመነስነስ አያሌ ህዝብ ፈጅታለች።
ኢራቅ እ ጎ አ ከ 1983 እስከ 1988 በኢራንና በራሷ የኩርድ ብሔር ተወላጆች ላይ በመርዘኛ ጋዝ ጭፍጨፋ ማካሄዷ የሚታወስ ነው።
የሰናፍጭ ዓይነት ሠፍናጊ ሽታ ያለው የድኝ ጋዝ፤ የሰውነት ቆዳ መርዝ ነው። በ 3 ደቂቃ ውስጥ፤ ጋዙ ልብስ ሳያግደው የሰውነትን ቆዳ ቀስ እያለ ክፉኛ ይጎዳል። ምልክቶቹ፤ በቀጥታ ሳይሆን አንዳንዴ ከ 24 ሰዓት በኋላ ነው የሚታወቁት። መርዙ የነካው ገላ ይቀላል ። የፈላ ውሃ እንዳገኘው ቆዳ ይነፋፋል ፤ ውሃ ይቋጥራል። ከዚያም ቆዳው ይሸለቀቃል። ጋዙ ሲተነፈስ ወደ ጉሮሮ ከገባ ለህይወት አሥጊ ነው። ሳንባን ይበጣጥሳል።
ሳሪን፤ እ ጎ አ በ 1938 ለመጀመሪያ ጊዜ ጌርሃርት ሽራደር በተባሉት ጀርመናዊ የሥነ-ቅመማ ሊቅ ፀረ ተባይ መድኀኒት ይሆን ዘንድ ተዘጋጀ። ይሁን እንጂ እንደ ታቡንና VX ለነርቭ ጠንቅ የሆነ አደገኛ ጋዝ ሆኖ ተገኘ። ሳሪን ፈሳሽነት ያለው ፤ ሽታ ግን የሌለው የቅመማ ውጤት ነው።
የእስትንፋስ አካልን ፤ በልዩ ጭንብል ፣ ሠራ አካላትን በልዩ ቱታ ፣ ግማሽ ሰዓት ያህል ብቻ መከላከል ይቻላል። ሳሪን፤ በመተንፈስ ብቻ ሳይሆን፤ በዓይንና በሰውነት ቆዳም በኩል ገብቶ ነው ብርቱ ጉዳት ነው የሚያደርሰው። ያለማቋረጥ ያሳክካል። የማይቋረጥ ንፍጥ ፤ ዕንባ ፣ የጡንቻ መኮራመትም ያስከትላል ፤ የአየር እጥረት አስከትሎም ለሞት ይዳርጋል። ታቡንም ልክ እንደ ሳሪን ዓይነት ጠባይ ያለው ሲሆን እርሱንም ጌርሃርትሽራደር ናቸው መጀመሪያ የቀመሙት።
VX ን አንድ የብሪታንያ የሥነ ቅመማ ባለሙያ ናቸው የቀመሙት። መርዘኛነቱም ልክ እንደ ታቡንና ሳሪን ኃይለኛ ነው።
ሥነቅመማ፤ለመድኃኒትነትየሚውሉብዙግኝቶችንቢያቀርብም፣በአንጻሩለጥፋትየሚውሉትንምማዘጋጀቷአልቀረም።መርዘኛየጦርመሣሪያእንዲወገድአጥብቀውከሚሹትመካከል፤በታሪካቸውየዚህእኩይቅመማሰለባዎችየሆኑትኢትዮጵያውያንናቸው።በቅድሚያ፣ባለፈውሰሞን በሶሪያስለተፈጸመዘግናኝድርጊት ምንእንደተሰማቸው፣ ዓለም አቀፍ ኅብረት ለፍትኅ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ በመባል የታወቀውን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁን ጠይቄአቸው ነበር።
ተክሌ የኋላ
ሸዋዬ ለገሰ
Source: www.dw.de


ፕሬዝዳት ኦባማ የሚተማመኑበትን እቅዳቸዉ ለማስፈፀም-የሚተማመኑበትን ዘመናይ ጦር ከምርጥ መሳሪያዎቹ ጋር አዝምተዋል።የሶሪያ የቅርብ ወዳጆች ሩሲያ፥ ቻይና እና ኢራን የድብደባዉን ዕቅድና ዘመቻ አጥብቀዉ ይቃወማሉ።የሩሲያዉ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን ከዚሕም አልፈዉ አሜሪካና የተባባሪዎችዋን አቅድ አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።
ሶሪያዎች ሠወስት ዓመት እንደለመዱት ይተለላለቃሉ።ለንደኖች፥ የደማስቆ መንግሥትን በኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ሕዝብን በመጨረስ ወነጀሉ፥ ሶሪያን ለመብደብ ዛቱ፥ ፎከሩና በስተመጨረሻዉ ገሸሽ-ገለል አሉ።ፓሪሶች እንደ ለንደን፥ ዋሽግተኖች ዛቱ ፎከሩና የድብደባ-ነጋሪቱ ዋሽንግተን ላይ እስኪጎሰም አድፈጠዉ ቀሩ።ዋሽግተኖች እንደፎከሩ
ነዉ።ሞስኮዎች፥ ቤጂንጎች፥ ቴሕራኖች የድብደባ ፉከራ፥ ዘመቻ፥ ዝግጅቱን እንደተቃወሙ ነዉ።እነሱንም፥ ድፍን ዓለምንም የሚያስተናብረዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የጋራ ማዕከልነት የተቀበለዉ የለም።የሶሪያን ጦርነት፥ የሐያሉ ዓለም የዉጊያ-ዝግጅት፥ ተቃዉሞ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መጀመሪያ ሶሪያን በጣሙን የሶሪያ መንግሥትን አስጠንቅቀዉ ነበር።
«በዚሕ ሠዓት እዚያ ባለዉ ሁኔታ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ አላዘዝኩም።ግን እንደተጠቀሰዉ የኬሚካዊ እና የባዮሎጂያዊ መሳሪያ (የመጠቀም) ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነዉ።ይሕ ጉዳይ ሶሪያን ብቻ የሚመለከት ዓይደለም።እስራኤልን ጨምሮ ባካባቢዉ ያሉ የቅርብ ተባባሪዎቻችንን የሚያሰጋ፥ እኛንም የሚያሳስብ ነዉ።ኬሚካዊና ባዮሎጂያዊ ጦር መሳሪ ከመጥፎ ሰዎች እጅ እንዲገባ (ልንፈቅድ) አንችልም።»

ነሐሴ ሃያ-ሁለት ሺሕ አስራ ሁለት( ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።ቀጠሉ፥-ለአፀፋ-እንደማያመነቱ ዛቱ ቃል ገቡም።
«ለአሰድ ሥርዓትም ሆነ፥ እዚያ ላሉት ወገኖች ግልፅ ማድረግ የምንፈልገዉ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያን (ለዉጊያ) ማንቀሳቀስ ወይም ጥቅም ላይ ማዋል ለኛ ቀይ መስመር ነዉ።ይሕ ስሌቴን ይቀይረዋል። ይሕ ጥያቄዬን ይለዉጠዋል።ይሕ ለኛ ቀይ መስመር መሆኑን ባካባቢዉ ላሉ ወገኖች በሙሉ አሳዉቀናል።ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ማንቀሳቀስና መጠቀም ከባድ አፀፋ እንደሚገጥመዉ ተናግረናል።»

ነሐሴ-ሃያ-አንድ ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት።ማስጠንቀቂያ፥ ዛቻ ቃሉ ዓመት ደፈነ።ርዕሠ-ከተማ ደማስቆ አጠገብ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ወይም መርዛማ ጋዝ መተኮሱ ተነገረ።በሌላ አባባል የፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ ቀይ መስመር መጣሱ ተወራ።
የተነገረ፥ የተወራዉ መጣራት፥ መረጋገጥ አለበት።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪዎች ቡድን እዚያዉ ደማስቆ ነበረ።ቡድኑ መርዛማዉ ጋዝ ተተኩሷል የተባለበትን አካባቢ ለመመርመር፥ የተኳሾቹን ማንነት ለማጣራት ከሶሪያ መንግሥት ተፈቅዶለት በአራተኛዉ ቀን ወደ አካባቢዉ ተንቀሳቅሷል።«ተልዕኮዉ ዛሬ ነሐሴ ሃያ-ስድስት በሰዓታት ዉስጥ በአካባቢዉ ምርመራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።እያንዳዱ ሰዓት ትርጉም አለዉ።ተጨማሪ ጊዜ እንዲጠፋ አንፈልግም።»

ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን። ዋና ፀሐፊዉ እንዳሉት የዓለም አቀፉ ድርጅት የመርማሪዎች ቡድን በኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ተመትቷል የተባለዉን አካባቢ ለመርመር ወደ አካባቢዉ የተንቀሳቀሱት ነሐሴ-ሃያ ስድስት ነዉ።ቡድኑ ከአካባቢዉ የሰበሰበዉ መረጃ ቢያንስ በይፋ እስከ ዛሬ ተመርምሮ፥ ተጣርቶ አላበቃም።የለንደን ፖለቲከኞች ግን ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ መተኮሱን ለማወጅ፥ የፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ ቀይ መስመር መጣሱን በግልፅ ለመናገር የዓለም ማሕበር የምርመራ ዉጤት መጠበቅ አላስፈለጋቸዉም።
ለንደኖች ዓለም አቀፉን ድርጅት አይደለም የቅርብ ወዳጆቻዉን የዩናይትድ ስቴትስ አቻዎቻቸዉን ለመጠበቅ እንኳን አልታገሱም።በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ የሊቢያዉ የርስ በርስ ጦርነት እንደተጀመረ የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ የያኔዉ የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ወደ ቬኒዙዌላ ኮብልለዋል የሚል መረጃ እንደደረሳቸዉ ተናግረዉ ነበር።ኋላ ዉሸትነቱ ሲረጋገጥ የጠየቃቸዉ የልነበረም።

በቀደምም የተባበሩት መንግሥታት የመርማሪዎች ቡድን ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ተተኩሷል ተብሎ ወደ ሚጠረጠርበት ቦታ ገና ጉዞ ሳይጀምር የታላቅዋ ብሪታንያ ታላቅ ዲፕሎማት ኮሚካዊ ጦር መሳሪያ መተኮሱን አይደለም የተኳሹን ማንነት እንደሚያዉቅም በግልፅ ተናገሩ።ነሐሴ ሃያ-ስድስት ሁለት ሺሕ አስራ-ስድስት።

«ባለፈዉ ሮብ በጣም ከፍተኛ የኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ድብደባዉን የፈፀመዉ የአሳድ ሥርዓት ለመሆኑ ለኛ በብሪታንያ መንግሥት ዉስጥ ላለነዉ ግልፅ ነዉ።መረጃዎቹ በሙሉ ወደዚያ አቅጣጫ ነዉ የሚያመለክቱት፥ የዓይን ምሥክሮቹ፥ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ የተተኮሰዉ፥ የሥርዓቱ ሐይላት ያን አካባቢ ሲደበድቡ መሆኑ (ያንኑ) አመልካች ነዉ።»

የዘመኑ ዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት ቀያይሽ፥ የዓለም ሐያል፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች፥ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባል ትልቅ ዲፕሎማት ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ መተኮሱን አይደለም፥ የተኳሹን ማንነት ጭምር አዉቀዉ፥ ማወቃቸዉን ለዓለም እያሳወቁ የዓለም አቀፉ ድርጅት ሌላ-ምርመራ ለማድረግ ሌላ ገንዘብና ጊዜ ማጥፋቱ በርግጥ አነጋገሪ፥ ግራ አጋቢም ይመመስላል።ነዉም።
ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ ያሉ-የሚናገሩት አነጋገሪ፥ ግራ አጋቢነቱን ማስተንተን በርግጥ አያስፈልጋቸዉም።የምክር ቤት እንደራሴዎቻቸዉን አቋም ለመገምገም እንኳን አልታገሱም፥ ወይም የማስተንተን አቅም ብስለቱ ያጥራቸዉ ነበር።እና ደማስቆ መዳራሻ በመኬሚካዊ ጦር መሳሪያ መደብደቡን፥ ደብዳቢዉ የደማስቆ መንግሥት መሆኑን በይፋ ተናግረዉ አላበቁም።የኦባማን ቃል ለማስከበር መንግሥታቸዉ ቀዳሚ መሆኑን ከራሳቸዉ ከኦባማ ቀድመዉ አረጋገጡም እንጂ።

የተመድ መርማሪዎች

«በሃያ-አንደኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን፥ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ጥፋት እንዲያደርስ፥ በዚሕ መንገድ ሰዎች እንዲገደሉ ልንፈቅ አንችልም።ያለ-አፀፋ እርምጃ አናልፈዉምም።»

ሔግ ለሚያዘምቱ፥ ለሚያስጠነቅቁት ወታደራዊ አፀፋ ከሩቅ የሚወቅስ፥ የሚጠይቃቸዉ ቢኖር እንኳ በርግጥ ደንታም አይሰጣቸዉ።ከዚያዉ ከምክር ቤት እንደራሴዎቻቸዉ ለተንቆረቆሩት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ግን እሳቸዉም አለቃቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንም ግድ ነበረባቸዉ።

«(ካሜሩን) ፕሬዝዳት አሳድ ይሕን አድርገዋል ያሉበትን ምክንያት ለቤቱ ሊያስረዱ ይችላሉ?አሰድ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ይተኩሳሉ ለማለት ተጠያቃዊ ምክንያት አለመኖሩ አንዳዶችን ያሳስባል።»

አሉ-አንዱ የምክር ቤት እንደራሴ።አርብ።ሌለኛዉ ቀጠሉ፥-

«ሶሪያን መደብደብ፥በሐገሪቱ እና ባካባቢዉ ያለዉን ሁኔታ ይበልጥ ላለማባባሱ (ካሜሩን) የሚሰጡት ማረጋገጪያ አለ?»

ሌሎቹም-እንዲሁ።ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን እና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊልያም ሔግ ሶሪያን ለመደብደብ የፈለጉበትን ምክንያት ለማስረዳት፥ ለሚዥጎደጎደዉ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ብዙ ሞከሩ።እንደራሴዎቹን ማሳመን ግን አልቻሉም።እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ በድምፅ ብልጫ ተሸነፉ።

«በቀኝ በኩል የድጋፍ ድምፅ ሁለት መቶ ሰባ-ሁለት፥ በግራ በኩል የተቃዉሞዉ ድምፅ ሁለት መቶ ሰማንያ-አምስት።»

የብሪታንያ መንግሥት የዛተ፥ የፎከረበት የጦርነት ዘመቻ-በሐገሪቱ ምክር ቤት ድምፅ ሲሸከሽፍበት፥ እንደለንደኖች ሁሉ የደማስቆን ገዢዎችን ለመቅጣት ሲጋበዙ የነበሩት የፓሪስ መሪዎችም ከወትሮ አቋማቸዉ ሸብረክ ማለት መጀመሩ።እርግጥ ነዉ ፕሬዝዳት ፍራንሷ ኦላንድ ሌላ ሐገር ለመዉረር ከብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ከዴቪድ ካሜሩን የሚሻሉበት ሁለት፥ ከዩናይትድ ስቴትሱ ደግሞ አንድ ዕድል አላቸዉ።

ኦላንድ እንደ ካሜሩን-የቶኒ ብሌር፥ እንደ ኦባማ የጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እኩይ ምግባር መጥፎ ዉርስ የለባቸዉም።ጠቅላይ ሚንስትር ካሜሩን ራሳቸዉ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት የምክር ቤት እንደራሴዎቻቸዉ የሶሪያዉን የዘመቻ ዕቅድ ዉድቅ ያደረጉት የቀድሞዉ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር እና የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳ ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ኢራቅን በሐሰን መረጃ ወርረዉ በየሐገራቸዉም፥ በኢራቅም በድፍን ዓለምም ያደረሱት ጥፋት በመኖሩ ነዉ።

ኦላንድ ከሳርኮዚ ሊቢያን መደብደብን ቢወርሱም፥ ከዣክ ሺራክ ግን የኢራቅን መወረር ተቃዉሞ እንጂ የወረራ ጥፋት ዉድቀትን አልወረሱም።ይሕ-ከካሜሩንም ከኦባም ይለያቸዋል።ሶሪያን ለመደብደብ ከካሜሩን በሌላም ጉዳይ ይለያሉ፥ምክር ቤታቸዉን ሳያማክሩ ሌላ ሐገር የሚወር ጦር ቢያንስ ለአራት ወራት ማዝመት ይችላሉ።

ያም ሆኖ የብሪታንያ ምክር ቤት የዘመቻዉን ዕቅድ ዉድቅ ካደረገ በሕዋላ ፓሪሶች ያንድ ሳምንት ፉከራ-ዛቻቸዉን ማቀዝቀዝ ግድ ሆኖባቸዋል።የፈረንሳይ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ማኑኤል ቫል ትናንት እንዳሉት ደግሞ ፓሪሶች ከእንግዲሕ የዋሽግተኖችን ኮቴ ማዳመጥ ግድ አለባቸዉ።

«አዲስ ምዕራፍ ዉስጥ እንገኛለን።ብሪታንያ ጣልቃ እንዳትገባ የሐገሪቱ ምክር ቤት ከወሰነ በሕዋላ፥ ማክበር የሚገባን አማራጭ አለ።ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ ምክር ቤታቸዉን ለማማካር መወሰናቸዉን ማክበር አለብን።ላሁኑ ጊዜ አለን።ይሕን ያለንን ጊዜ ጉዳዩ እንዲንቀሳቀስ ልንጠቀምበት ይገባል።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ-የፕሬዝዳትነትነቱን ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ ቀዳሚያቸዉ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ያወደሙትን የሐገራቸዉን ምጣኔ ሐብት ለማሻሻል፥ ያጠፉትን የአሜሪካን ሥም፥ ዝና ክብር ለመመለስ በብዙ ጉዳይ ቃል ገብተዋል።ጥቂቱን እንጠቅስ፥-የእስራኤልና የፍልስጤሞችን ግጭት ዉዝግብ ለማስወገድ ዋሽግተን አይደለም ካይሮ-ድረስ ወርደዉ ቃል ገብተዉ ነበር።ከየሐገሩ ታፍሰዉ ያለፍርድ በርካታ ሰዎች የታሰሩበትን የኹዋንታናሞ ማጎሪያ ጣቢያን በአንድ ዓመት ጊዜ ለመዝጋት ቃል ገብተዉ ነበር።

አምባገነኖች በየሕዝባቸዉ ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ እና በደል ማስቆም ባይችሉ እንኳን መስተዳድራቸዉ ከአምባገነኖች ጋር እንደማይተባበር ቃል ገብተዉ ነበር።የዓለም ብቸኛ ልዕለ-ሐያል ሐገራቸዉ አቅም ጉልበት ሐብቷን በዓለም ሠላም ለማስፈን እንድታዉለዉ ለማድረግ እንደሚጥሩ ቃል ገብተዉ ነበር።ኦባማ ለገቡት በጎ ቃል፥ ተስፋ የዓለምን ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤልን ተሸልበዉበታል።

ከጠቀስናቸዉ መሐል ግን አንዱንም ቃል በከፊል እንኳን ገቢር አላደረጉም።ሶሪያ ላይ በሐሳብ ያሰመሩትን ቀይ-መስመር ለማስከበር የገቡትን ቃል እንደማያጥፉ ግን በቀደም በድጋሚ አረጋግጠዋል።

«ጥንቃቄ ከተሞላበት እሳቤ በሕዋላ ዩናይትድ ስቴትስ በሶሪያ ሥርዓት የተመረጡ ኢላማዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ ወስኛለሁ።ይሕ ማብቂያዉ የማይታወቅ ጣልቃ ገብነት አይሆንም።እግራችንን ሶሪያ ምድር አናሳርፍም።ከዚሕ ይልቅ እርምጃችን በጊዜና በመጠን የተወሰነ ነዉ።ይሁንና የአሰድ ሥርዓት ኬሚካዊ ጦር መሳሪያያ በመጠቀሙ ተጠያቂ ማድረግ፥ እንዲሕ አይነት ባሕሪዉን መግታት፥አቅሙን ማዳካም እንደምንችልም እተማመናለሁ።»

ፕሬዝዳት ኦባማ የሚተማመኑበትን እቅዳቸዉ ለማስፈፀም-የሚተማመኑበትን ዘመናይ ጦር ከምርጥ መሳሪያዎቹ ጋር አዝምተዋል።የሶሪያ የቅርብ ወዳጆች ሩሲያ፥ ቻይና እና ኢራን የድብደባዉን ዕቅድና ዘመቻ አጥብቀዉ ይቃወማሉ።የሩሲያዉ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን ከዚሕም አልፈዉ አሜሪካና የተባባሪዎችዋን አቅድ አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።

«እንዲያዉ ተራ ግምት እንኳን ይመስከራል።የሶሪያ መንግሥት ጦር ድል እየተቀዳጀ ነዉ።ባንዳድ አካባቢዎች አማፂያኑን ከቧል።በዚሕ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ «የምዕራቡ) ጦር ጣልቃ እንዲገባ ለሚጠይቁት ሐይላት ያሸናፊነት ካርድ መሸለም ፍፁም ትርጉመ-ቢስነት ነዉ።በተለይ የዓለም አቀፉ መርማሪ ቡድን በመተለሰበት ባሁኑ ወቅት እርምጃ ይወሰድ መባሉ ከምንም አይነት ተጠይቅ ጋር አይጣጣምም።ሥለዚሕ በሶሪያዉ ጦርነት ሌሎች ጣልቃ እንዲገቡ ለሚፈልጉ ሐይላት፥ ከዓለም አቀፉ ጠንካራ ሐይል-በተለይ ከአሜሪካ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ጠብ አጫሪነት ብዬ ነዉ የማምነዉ።»

የሰማቸዉ እንጂ-የተቀበላቸዉ ምዕራባዉ ሐይል የለም።የዩናይትድ ስቴትስ ቦምብ ሚሳዬል ሶሪያን የሚያነደዉን ዉጊያ የሚያጋጋምበት ዕለት እየተቆጠረ ነዉ።ሶሪያም ኢራቅን፥ አፍቃኒስታንን፥ ፍልስጤም እስራኤልን፥ ሊቢያን ለመቀየጥ-ትጣደፋለች።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ
Source: http://www.dw.de
| Copyright © 2013 Lomiy Blog