ሰማያዊ ፓርቲ እና ዓረና ትግራይ ዕጩዎቻቸው ከጥላቻ ፍረጃ እሰከ ጥብቅ ክትትልና ማሰፈራራት፣ ወከባ፣ ድብደባና እየታሰሩ መሆኑን ገለጹ!

ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ በቀረው አምስተኛው አገርአቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ተወዳዳሪ ከሆኑ ፓርቲዎች መካከል ሰማያዊ ፓርቲ እና በመድረክ ስር ያለው ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ “በአባሎቻችን እና እጩዎቻችን ላይ እንግልት፣ እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው ነው” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስታወቁ።

የዓረናፓርቲሊቀመንበርአቶብርሃኑበርሄ “በቅድመ ምርጫ ዝግጅት ያገጠመን ችግር ከባድና ውስብስብ ነው። ከጥላቻ ፍረጃ እሰከ ጥብቅ ክትትልና ማሰፈራራት፣ ወከባ፣ ድብደባና እስር ተደጋግሞ ያጋጠሙን ችግሮች መሆናቸውን በጊዜው ሲገለፅ ቆይቷል። ቢሆንም የተወሰኑ አብነቶች ለመግለፅ በምእራባዊ ትግራይ ዞን ለህዝብ የሚታደሉ ፅሑፎች ከመቀማት እስከ ከባድ ድብደባ ተፈፅሞብናል” ብለዋል።

ሊቀመንበሩ አያይዘውም በአፅቢ የምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደር፣ በቆላ ተምቤን ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደር፣ ባታሕታይ ማይጨው /አክሱም አካባቢ/ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደር እጩ ተወዳዳሪ መሆናቸው እየታወቀ የምርጫ ህጉ ያረጋገጠላቸውን ያለመከሰስ መብት በመጣስ ታስረው ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደርጎ በስንት አቤቱታ አሁን የተፈቱ ቢሆንም የመቀስቀስ መብታቸው ተገድቦ ቆይቷል” ብለዋል።

ዓረና ትግራይ ፓርቲን ወክለው በመቐለ ከተማ የሚወዳደሩት የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው “ካለፉት ምርጫዎች በበለጠ በዚህ ምርጫ ምህዳሩ የጠበበ ነው” በማለት ተናግረዋል። አቶ ገብሩ አያይዘውም “የምርጫ ታዛቢዎች የተመረጡት የፓርቲያችን ውክልና እና እውቅና ሳይኖረው ነው። ብዙዎቹ የምርጫ ታዛቢዎች በግልጽ የገዥው ፓርቲ አባላት መሆናቸው ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በመራጮች ምዝገባ የመራጭነት ካርድ ገዥው ፓርቲ ለሚፈልጋቸው ሰዎች በየቤታቸው እያንኳኳ ሲያድል ለማይፈልጓቸው ደግሞ ሊመዘገቡ እንኳ ሲሄዱ ካርድ ጨርሰናል በማለት መልሰዋል። ለእዚህ አንዱ ምሳሌ እኔ ነኝ። እኔ ተዋዳዳሪ ብሆንም የመራጭነት ካርድ የለኝም” ብለዋል።

የዘንድሮውን ምርጫ “ከአፍሪካ ህብረት ውጭ ሌላ የውጭ አገር ታዛቢ የሌለበት ምርጫ ነው” ያሉት አቶ ገብሩ በእጩዎቻቸው ላይ እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑንም ተናግረዋል። “በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚወዳደሩ እጩዎቻችን እየተንገላቱ ነው። በአጽብሂ የሚወዳደረው እጯችን ታስረው ቆይተው በቅርቡ ነው የተለቀቁት። ይህንን ሁሉ ስታይ የፖለቲካ ምህዳሩ ካለፉት ዓመታት ምርጫዎች በበለጠ የጠበበ መሆኑን ነው” በማለት ተናግረዋል። ዓረና ትግራይ ፓርቲ በትግራይ ክልል ከሚገኙ 38 ምርጫ ክልሎች በ29 የምርጫ ክልሎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በ28 ምርጫ ክልሎች ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ዕጩዎችን አቅርቦ እንደሚወዳደር ሊቀመንበሩ አቶ ብርሃኑ በርሄ ተናግረዋል። አቶ ገብሩ አስራት ዓረና ትግራይን ወክለው፣ ህወሓት/ኢህአዴግን ወክለው ከሚወዳደሩት አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ ጋር በመቐለ ይወዳደራሉ። አቶ ብርሃኑ በርሄ በመቀሌ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ሲሆን የቀድሞዋ ታጋይ አረጋሽ አዳነ ደግሞ በዚያው መቀሌ ምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወዳደሩ ከፓርቲው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ ዜና ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት ለምርጫ ቅስቀሳ የለጠፍኩት ፖስተርና ባነር እየተቀደደብኝ ነው፤ እኔ የለጠፈኩትን ፖስተር እየገነጠለ በተከለከሉ ቦታዎች የሚለጥፍ ኃይል አለ፤ በፓርቲያችን ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል ሲል አስታውቋል። የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሰንደቅ ጋዜጣ “ለምርጫ ቅስቀሳ በምንወጣበት ጊዜ የምርጫ መቀስቀሻ ወረቀቶችን የመንግስት ካድሬዎች ቀምተው ተሰውረዋል” ሲሉ ተናግረዋል። እንዲሁም በጋምጎፋ ዞን በአንድ ቀን የምርጫ ቅስቀሳ ብቻ 17 የፓርቲው አባላት መታሰራቸውንና እስከትናንት ማክሰኞ ድረስ እንዳልተፈቱ ገልጸዋል።

አቶ ዮናታን ጨምረው ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ተጠርቶ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተከሰተው ሁከትና ረብሻ ምክንያት ተጨማሪ ሶስት የፓርቲው አባላት መታሰራቸውን ተናግረዋል። የታሰሩት የፓርቲው አባላት ናትናኤል የዓለምዘውድ፣ ሜሮን አለማየሁና ደብሬ አሸናፊ ናቸው። የፓርቲው አባላት የታሰሩት ከቤታቸው ተወስደው መሆኑን የገለፁት አቶ ዮናታን ሰላማዊ ሰልፉ ተካሂዶ በነበረበት እለት ከታሰሩት አምስት የፓርቲው አባላት በተጨማሪ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤ እና ማቲያስ መኩሪያ የሚባሉ አባሎች በድጋሚ ተይዘው መታሰራቸውን ተናግረዋል። በቁጥጥር ስር ከሚገኙት 11 የፓርቲው አባላት መካከል አራቱ እስከ ግንቦት 24 ድረስ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የተፈረደባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ስለታሰሩት የፓርቲው አባላት በመንግስት በኩል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ እውነቱ ብላታ ስልክ ስንደውል ስብሰባ ላይ መሆናቸውንና ስለጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸውልናል።

ቀደም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት ዘጠኝ ቀን በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም በእለቱ ለመራጩ ህዝብ የምርጫ ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን በመሆኑ ምንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ የተከለከለ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል። የቦርዱን ውሳኔ ተከትሎ ፓርቲው የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪውን ሰርዟል ወይስ ለሌላ ጊዜ አራዝሟል? ተብለው የተጠየቁት አቶ ዮናታን “ወደ ፊት የምናሳውቅ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

በይርጋአበበ
ምንጭ፦ ሰንደቅ

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog