(በካሣሁን ዓለሙ)

‹ፍልስፍናን እማራለሁ› ብዬ ት/ቤት ብገባ፣ መምህሩ ‹ፍልስፍና ምንድን ናት?› ብሎ መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ፤ ‹ካወቅኳትም ለም
ንስ ልማራት ሒሳብ ከፈልኩ?› አልኩኝ፤ ምን ላድርግ? ቢቸግረኝ ያው ‹የፍልስፍና አስተማሪዎች ናቸው› ከሚባሉት ፋይል የሰማሁትን ስምምነታቸውን ይዤ፡- ፍልስፍና እኮ እንዲህ ነው ማለት ጀመርኩ!
በመሠረቱ ጭንቁ መልሱ ላይ ነው እንጂ የፍልስፍና አዋቂና ምጡቅ የተባለ ሁሉ ይችን ‹ፍልስፍና ምንድን ናት?› የምትል ጥያቄ ሳያነሳት አይቀርም፤ መምህሬም ‹ጥያቄዋ ትንሽ ገብታው ነው› መሰል የጠየቀኝ፤ እንደኔ ያላብላሉት ሳይሆኑ መልሷን ሲጭሩ የኖሩት ሊቃውንት ግን ግምታዊ መልሳቸውን ሰጥተዋል፤ እኔም በመጠኑ ሰምቻለሁ (ከፈለጋችሁ ጆሮ ጠገብ በሉኝ)፡፡ በአጠቃላይ ግን በሊቃውንቷ ‹ፍልስፍና ጥበብን ማፍቀር ናት› የሚል ስምምነት ላይ ተደርሶባታል ብሏል መምህሬ ራሱ፡፡ እንደዚህ ከሆነማ ማጠንጠኛዎቿ እነዚህ ‹ጥበብ› እና ‹ፍቀር› የሚሉ ቃላት (ጽንሣተ-ሐሣብ) ናቸው ማለት ብዬ ያዝኩ፡፡ እነዚህ ሁለት ቃላት ደግሞ ዓለምን በመሠረትነትና በዓምድነት (ምሠሦ ሆነው) ያቆሙ ኃይላት ናቸው፡፡ የፍልስፍናም ድንቅነት የተመሠረተው በእነሱ የውህድነት ጥንጣኔ ላይ ሊሆን ነው፡፡ መምህሬም ጥያቄዎቹን አከታተለ ‹እንዴት ተዋሃዱ? የውህደታቸው ጥብዓትስ እስከምን ድረስ ነው? በምን ያህል አስተውሎትስ ልንረዳቸው ቻልን? የእሴትና የኪን (የውበትን) ተውህቦስ ማን አደላቸው? ነው በራሳቸው በሌጣነት ነው አንክሮ ውስጥ የከተቱን?› የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እያነሳ አስጨነቀን! እንደተረዳሁት ከሆነ በእነሱ የተነሣ ስንቱ ሊቅ ቀውሷል፣ ስንቱም አሰላሳይ ከዘመድ ከወዳጅ ተለይቶ መንኖላቸዋል መሰላችሁ፤ ጥበብን ማፍቀር አያድርስባችሁ እቴ! (እንቢ ካላችሁም የጥበብ ስቃይን ይጣልባችሁ ብሎ መርገም ይቻላል!)
ያሳቢዎቹን ምጥቀት የፈተነውስ ጥበባዊ ፍቅሯ አይደል! ስለዚህ መምህሬም ‹ፍልስፍና ምንድን ናት?› ሲል የፍቅርንና የጥበብን ምንነት ያውቃል ማለት ነው፤ ስለዚህ እኔ ያልገባኝ ‹ፍቅር ራሱ ምንድን ነው? ጥበብስ ለምን ልትፈቀር ቻለች?› አልኩት! እሱም በገፅታው ‹ደደብ!› እያለ በቃላት ተረከልኝ! ትንሽ አሰላስሎም ገለጻውን ‹ፍቅርን› ሊተረጉም በመሞከር ጀመረ!

‹ፍቅር!› አለ ‹ፍቅር ኃያል የማይቋቋሙት ማግኔት ነው፤ ስንቱን በኃይሉ ቀልብ አስቷል፤ አሳብዷል፤ ስንቱ ምንነቱን ለመግለጽ ተቸግሮ ነፍሯል፡፡ የቀመሰው ይመሥክር ማለት ይሻላል መሰል፡- ጥብዓቱን ለመግለጽ ቃላት ሽባ ናቸውና፡፡› ብሎ ዘጋ! የራሱ ጉዳይ በራሳችን እየጠየቅን መምረመር ነው፡፡
ለነገሩ ምንም እንኳን የጥበብ ፍቅርን የበለጠ ሚዛኑ ቢከብድም ጾታዊ ፍቅር እንኳን እንዴት አቅልን እንደሚያስት፣ አካልንና ስሜትን እንደሚሰቅጥ የደረሰበት ያውቀዋል፡፡ ለምሳሌ አንዷን ኮረዳ ያፈቀረ ሸጋዋ፡-
‹የፍቅሯን አረቄ ብቀምሰው ሰክሬ፣
መራመድ አቃተኝ ታሠረ እጅና እግሬ፡፡› ብሏል፤ አትፍረዱበት
እንዲሁም በአንዱ ጉብል ፍቅር ተቸግራ የተጨነቀች ኮረዳ ሐሜታዉ ቢያስቸግራት፡-
‹አበደች ይሉኛል፣ ከነፈች ይላሉ፣
እንደኔ በፍቅር ነደው ያልከሰሉ፡፡› ብላቸዋለች
የፍቅር ኃያልነት አምላክንም ሰው እስከመሆን አድርሶታል፤ ለዚያም ነው አበው ‹ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እም መንበሩ› ያሉት፤ ‹አምላክ የሰው ዘርን ማፍቀሩ ከመንበሩ ጎትቶ ሰውነትን ገንዘብ እስከማድረግ አደረሰው› ሲሉ፤ ፍቅር የትዛዛቱ ሁሉ ማሠሪያ አይደል? ቅዱስ ጳውሎስስ ‹እምነት፣ ተስፋና ፍቅር› ለዘላለም ፀንተው የሚኖሩ የዓለሙ መሠረት መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ ‹ከሁሉም ፍቅር ይበልጣል› ብሎ አደል የደመደመው? ስለዚህ ስንቱ ሊቅ በጥበብ ፍቅር ተነድፎ ቢቀውስ፤ በጥበብ ፍቅር ሰክሮ ቢነባረር፤ በጥበብ ፍቅር ታሥሮ ቢጃጃል፣ ቢቄል፤…. ምን ይደንቃል? የፍቅር ጠባይ አይደለም ወይ?
ግን መጠየቅ ደግሞ አለብን፡- ‹ለምን ያፈቅሯታል?› ብለን፡- ‹ያላወቁ አለቁ› እንዳንሆን፤ ምሥጢሩን ለማወቅ መጣር ይገባል፤ ግን ከባድ ጥያቄ ናት፤ ጠያቂ ምን አለበት? ጭንቁ ያለው መልሱ ላይ!፡፡ ጥያቄዋ እኮ! ‹ጥበብ ምንድን ናት?› የምትል ጥያቄን በውስጧ አነጣጥራለች፡፡ ‹ምንድን ነሽ ይላሉ ምን እንበላቸው?› አለ መግለፅ ያቃተው፡፡ ይህችንስ ጥያቄ በመንግሥቱ ለማ ግጥም፡
‹ከንቱ ነው ወዳጀ መተርጎም ማተት፣
እንዳው ዝም እንበል አናባክን ቃላት፡፡›› ብሎ መደመም ሳይሻል አይቀርም፡፡ ታላቁ ሊቅ ሶቅራጥስም ቢሆን እኮ! በአንክሮ መጠበብ (ፍልስፍና) እንደምትጀመር ተናግሯል አሉ፡፡ ግን ምን ስለሆነች ነው ጥበብ የምታስደምመን? ምን ስለሆነች ነው በፍቅር የምታሳብደው? ‹በቅድሚያ ማወቅ መተዋወቅ› ብሏል ዘፋኙ! እኛም ብንሆን ‹ተይ! ማነሽ! ተይ! ማነሽ!› ብለን ልንጠይቃት፣ ልናውቃት ይገባል! ታዲያ፡፡ ቢያንስ በት/ቤት ከፋይሎች ባገኘነው ተጠቅመን እናወራላታለን! (ስላልገባን እኮ ነው! እንጂማ ቢገባን ተደመን በቀረን ነበር፤ በፍቅሯ ተነድፈን በወደቅን ነበር!)፡፡ ‹ጥበብ ምንድን ናት?› ከጠየቅን አይበቃም!
‹ወይ ጥብብ! ወይ ጥበብ!… አንቺን ያፈቀረ፣
ተብረክርኮ ቀረ!› አለ አድናቂዋ!
‹ጥበብ ምንድን ናት?› መቼም ፈተና ላይ የተቀመጠ ተማሪ መልሱ ቢጠፋበትም ይሞክራል እንጂ ዝም ብሎ አይተወው፤ እኔም የጥበብን ምንነት ማወቅ ከቻልኩ ብዬም መጻሕፍትን ዘረጋሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ቃኘሁ፤ የፈላሶፎችን አስተያየት ተመለከትክ፤ የት/ቤት ደብተሮችን (ፋይሎችን) አገላበጥኩ፡፡ ጥበብን እንደተሸበበች በቅሎ በአንድ በአንድ አቅጣጫ ብቻ መመልከት ሙሉ አይመስለኝም፤ እንደ ኢትዮጵያዊያን የአንድምታ ትርጓሜ በተለያየ አቅጣጫና ደረጃ ገጽታዋ ሊታይና ሊነገር ይገባዋል፡፡ ለእኔ በጥቅል የተረዳሁት የመሰለኝ የጥበብ ምንነት ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ› የሚል ነው፤ አንድም በኢትዮጵያውኛ እንግለጻት ካልን ‹ጥበብ ማለት ቅኔ ናት› (ግጥም አላልኩም)፤ ካሠራር ብልሃት አንጻር ካየናትም ‹ጥበብ ማለት ፊደል ናት›፤ አንድም ከመንፈሳዊ ዕይታ ከተመለከትናት ጥበብ እግዚአብሔርን (ሥላሴ) ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥርነት ፈክራ ታመሠጥራለች›፡፡ እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ከሆነ ‹ጥበብ ሰባት አዕማዳት ያሏት ቤት› ነች፡፡ ስለዚህ ጥበብን በተለያየ ዕይታና አተረጓገም መቃኘት ይገባል፤ ግን መሠረታዊ ትርጓሜዋን መልቀቅ የለባትም፤ ያንኑ ማምጠቅ ወይም መወሰን ነው ልዩነቱን የሚፈጥረው፤ አንድም የትርጓሜው ልዩነቱ የሚፈጠረው ከምትታይበት የአንግል መለያየት የተነሣ ይሆናል፤ ለማንኛው እነዚህን አንድማታዊ ትርጓሜዎች አንቃኛቸው፡፡
የመጀመሪያ የጥበብ መሠረታዊ ትርጓሜ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ (ቅኔ) ናት› ያልነው ነው፡፡ ጥበብን ልዩ ተወዳጅ ያደረጋትም የእነዚህን ነገሮች ተዋህዶ የያዘች መሆኗ ነው፡፡ ከእነሱም እውነት መሠረት፣ ዕውቀት ግድግዳና ጣሪያ፣ መልካምነት ደግሞ ልስንና ክዳን በመሆን የተዋበችውን የጥበብ ቤት ሠርተዋታል፡፡ ይህች ቤት ናት እንግዲህ ስንቶችን በፍቅር እያከነፈች ስባ ካስገባች በኋላ ነፍሳቸውን አሳልፈው እንዲሰጧት የምታደርገው፤ ከመሠረት አሠራሯ፣ ድዛይኗ እስከ አመራረግ፣ አለሣሰን፣ አከዳደንና አቀባብ ውበቷ እየተደነቁ በፍቅር ከንፈው የቀሩላት፣ መኖሪያ እሥር በታቸው ያደረጓት ለዚያ ነው፡- እንዴት ብለው ይልቀቋት ትንሽ የምትመስል የዓለምን ምንነት ማወቂያና መገምገሚያ መነጽር ያላት አስደናቂ ቤት ሆና!፡፡ ከእነዚህ ከሦስት አስፈላጊ ነገሮች አንዷ ከተለየች ሦስቱም አይነሩም፤ አንዱ ያለ ሌላው ህልውና የላቸውም ምክንያቱም ጥበብን ወይም የጥበብ ቤትን ማስገኘት የቻሉት በመያያዝ ስለሆነ አይነጣጠሉም፡፡ ይህም ማለት እውነት ያለ ዕውቀት መታወቅ አይችልም፤ እውነትነት የሌለው ዕውቀትም ትርጉም የለውም፤ ያለ ዕውቀትና እውነት መልካምነትም አይገለፅም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሦስት የጥበብ መሠሪያዎች አንድም ሦስትም በመሆን በተዋህዶ ጥበብን ያከበሩ ናቸው፡፡
ጥበብ ደግሞ የምትሠራው በብልሃት ነው፤ የብልሆችም መዋያና ማደሪያም ትሆናለች፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ በተፈጥሯዊ ባህርዩ ብልሃትን የታደለ ፍጡር ስለሆነ ሁሉም ሰው ጠቢብ (ፈላስፋ) ነው ይባላል፡፡ አነጋገሩ እውነታነት አለው፤ ግን ጥንቃቄንም ይጠይቃል ምክንያቱም ኮከብ እምኮከብ ይኼይስ ክብሩ፡- ከአንዱ ኮከብ ክብር የአንዱ ኮከብ ክብር ይበልጣል› እንዳለው ቅ.ጳውሎስ፤ አንድ ጣት ከሌላው ጣት ሲነጻጸር እንደሚበላለጠው፤ የጠቢባኑም ደረጃና ብልሃት ተነጻጽሮ የበለጠው ጥበብ የበለጠ ሳቢነትንና ተደናቂነት ያገኛል፡፡ እንዲሁም የጥበብ ቤት የምትሠራው በዘመን ሂደት በጠቢባኑ ቅብብሎሽና ትብብር፣ ወይም መናበብ ነው፡- የጥበብ ቤት የስንት አብሰልስሎት ሥራ ናት፡፡ ስለዚህ በሚገኙበት የዘመን ማዕዘንና ዕይታ ድንጋዩን፣ ዕንጨቱን፣ ሣሩን፣ ማገሩን፣ ጭቃውን፣ ቀለሙንና የመሳሰሉት በማቀበልና በማስተካከል ባደረጉት አስተዋፅኦ፣ መተራረምና ማስተካከል ነው ጥበብ በቤትነት የተሠራችው፡፡ ስለዚህ አሁን የምትገኘው ጥበብ የብዙ ዘመናት ጠቢባን እውነት፣ ዕውቀትና መልካምነት ግንባታ ውጤት ናት ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል የጠቢባነ-ጠቢባኑ እየተመካከሩና እየተራረሙ የእውነት ዓለትን አጥብቀው (አንጠርው) በመመሥረት፣ በዕውቀት መሣሪያነት አስልተውና አስተካክለው በመሥራት በመልካምነት እሴት አስውበውና አክብረው እኛ አለንበት ዘመን ጋር አድርሰዋታል፡፡ ለዚያም ነው
‹የሚጥሩ ሰዎች ለዕውቀት የታጠቁ፣
በጣም ክቡር ናቸው እንደ አልመዝ እንደ ዕንቁ›የተባለላቸው፡፡
አንድም ‹ጥበብ ማለት የተዋህዶ ቅኔ ነች›፡፡ ጥበብ ማለት አእምሯችን መጥቆ ውስብስቡን፣ የማይታየውንና ረቂቃዊን ዓለም በሚታየው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸርና በማዋሃድ እየለየ የሚፈታባት የሁለት ኑባሬያት ተዋህዶ የሆነች ቅኔ ወይም የሰምና የወርቅ ምሥጢራዊ የተራቆ ትርጉምን ያቀፈች ድንቅ ነገር ነች፡፡፡ በዚህም አዕምሯችን የማይታየውንና መልስ ያልተገኘነትን ስውርና ውስብስብ ክስተት መልስ ባለውና ግልፅ ሆኖ በሚታወቀው እያነጻጸረና የሚታወቀውን ተጠቅሞ ውስብስቡን እየፈታ፤ ያልተገለጠውን ደግሞ ‹ምንድን? ለምን? እንዴት?› በሚሉ ጥያቄዎች እያበጠረ የሚለይባት ማጉሊያ መሣሪያው ናት፡- ጥበብ፡፡ በዚህ የተነሣ የዓለምን ጠቢባን በተዋህዶዋ ዕንቆቅልሽ፣ በቅኔዋ የምሥጢር አፈታት ለሁለት በቡድን ተለያይተው እንዲደባደቡ አድርጋቸዋለች፡- ሐሳባዊያንና ቁሳዊያን በሚል፡፡ ይሁንና እነሱ ተለያይተው በቡድንና በውገና ሲሟገቱ ቢኖሩም እሷ በተዋህዷዊ ቅኔዋ እየሳቀችባቸው የየትኛቸውን ክስ ሳትጠየፍ፣ የየትኛቸውንም ፉከራ ሳታጸድቅ በተዋህዶዊ ተቀኝቶዋ አለች፤ እንዳለች፡፡ በዚህ ተዋህዷዊ ቅኔዋም ዓለምን ተቆጣጥራ፣ ያለም ጠቢባን ዕንቆቅልሽ ሆና፣ ፍቅረኛቸውም እንደሆነች አለች፤ እንዳለች፡፡ ለዚየም ነው ከበደ ሚካኤል፡-
‹ሰዎች የፈጸሙት የተግባር ሃተታ፣
ክብደቱ ግምቱ ሲሰፈር በጾታ፣
መዓረግ ተሰጥቶትም ሲደለደል ቦታ፣
ቅኔ ተቀመጠች አክሊል ተቀዳጅታ፡፡› ያሉት
ጠቢቡ ሰለሞን ‹ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ ሰባት አዕማዳትንም አቆመች› (ምሳሌ 9፣1) ይላል፡፡ ጠቢቡ በእውነትም ታላቅ ጠቢብ ነበር ማለት ይቻላል፤ አባባሉንም ዝም ብሎ አልተናገረም፤ የሚያስገርም ምሥጢርን አምቆና አዋህዶ ገልጾበታል እንጂ! ስለሆነም መመርመር ያስፈልገዋል፤ የጥበብን ቤት ምንነትንና የሰባት አዕማዳቷን ምሥጢር ተንትኖ አንድምታውን ለመረዳት መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ሰለሞን ጥበብን ለምን በቤት መመሰል፣ በሰባት አዕማዳት መቆሟን መግለጽ አስፈለገው? አዕማዳቱስ ምን ምንድን ናቸው? እንመልከታቸው፡፡
ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ (በተለይም ሰለሞን በተናገረበት የዕብራውያን ልማድ) ሰባት ቁጥር የፍጽምና፣ የምሉዕነትና የመደምደሚያነት ምልክት ነው፡፡ ይህም ዝም ተብሎ ሳይሆን የተፈጥሮ አሠራርንና የጊዜ ዑደትን በማስተዋል፤ ሌሎችንም የመንፈሳዊ ትርጓሜያትን በማመሥጠር የተነገረ የጥበብ ፍች ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አስተምህሮ ሰማያት ሰባት ናቸው፤ ፍጥረታት የተፈጠሩባቸው ቀናትም በሰባት ዕለታት ነው ተከፍለው የጊዜ ዑደትን የሚያከናውኑት፤የመጨረሻው ፍጡር ሰውም ቢሆን ፍጽምናን ያገኘ ድንቅ ፍጥረት የሆነው ሰባት ባሕርያትን ስላሟላ ነው፡፡ ስለዚህ ጠቢቡ ሰለሞን የጥበብ ቤት ያለው አጠቃላይ የፍጥረታት መኖሪያ የሆነውን ዓለመ-ፍጥረቱን ነው፤ ይህም በሰባት ሰማያትን ተደልድሏል፤ ‹ሰማይ› ማለት ራሱ ሰባት በውሃ የተከፈለ ሥፍራ (ሰ-ማይ) ማለት ነውና፤ አንድም ፍጥረታት በሙሉ በሰባቱ ሰማያት ተሠራጭተው በሰባቱ ዕለታት ውስጥ ተፈጥረው ተፈጽመዋልና፤ የጊዜያት ቀመርም የተመሠረተው በዚህ ነው፡፡ በሌላ በኩል የፍጥረታት ሁሉ ምሥጢር የተጻፈበት አስደናቂው ፍጡር ሰው ነው፤ የሰው ልጅ የተሟላ የጥበብ ቤት፣ የዓለምና የፍጥረታት ዕንቆቅልሽ መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ ይህንንም በሰባት ባሕሪያቱ አምቆና አትሞ ይዟል፡፡ የሰው ልጅ ሰባት ባሕርያት የተባሉትም ክቡድነት (መሬትነት)፣ እርጥብነት (ውሃነት)፣ ሞቃትነት (እሳትነት)፣ ተንቀሳቃሽነት (ነፋስነት)፣ ለባዊነት (አመንጭነት)፣ ነባቢነት (ተናጋሪነት) እና ሕያውነት (በሕይወት መኖር) ናቸው፡፡ የትኛውም ፍጡር ከእነዚህ ባሕርያት ሊወጣ አይችልም፤ የዓለማት የፍጥረታት ምሥጢር ሁሉ በሰው ልጅ ላይ ተጽፎ ይገኛልና፡፡ ስለዚህ ሰለሞንም ከሰማይ በታች ምንም ዐዲስ ነገር የለም ሲል ምን ያህል የተፈጥሮን ምሥጢር ጠልቆ መረዳቱን ያሳያል፡፡
አንድም ጥበብስ ፊደል ናት፤ ምሰሶዎቿም ሰባቱ ሆህያት ናቸው፡፡ አበው ፊደልን ሲሠሩ የታሪካቸው መዝገብ፣ የፍልስፍናቸው አመሥጥሮ፣ የፍጥረታት ሥዕላዊ ወካይ ምልክት፣ የሃይማኖታቸው መንፈሳዊ የምሥጢር ትርጓሜ፣ ወዘተ ማስተማሪያና ማስተላለፊያ መሣሪያ አድርገው ነው፡፡ ለዚያም ነው፡-
‹ሊቆች በአንጎላቸው ዕውቀት ያረገዙ፣
ጥበብን ፊደልን (ትምሀርትን) ወልደዋል በብዙ፡፡› የተባለላቸው፡፡
እያንዳንዱ የፊደል ሆሄም ከፍጥረታት ምንነት፣ ከጊዜያት ዑደት፣ ከሰው ልጅ ባሕርያት፣ ከሌሎች መንፈሳዊ ትርጉሜያት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የፊደል ፍልስፍና ማጠንጠኛም በእውነተኛ የተፈጥሮ ክስተት ላይ የተመሠረት፣ በዕውቀትና በብልሃት የተሠራ መልካምነት የተዋሃዱበት ጥበብን ማሟላት ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለም ከዚህ ከፊደል ጥበብ የበለጠ አስደናቂና የብልህ ጥበበኛ ሰው ሥራ የሆነ ጥበብ የለም፤ ስለዚህ ጥበብ ማለትስ ፊደል ነው፡፡
የዚች የጥበብ ጉዳይ በጣም ጥልቅ ነው፤ ከላይ የሚታይ ፍች ብቻ ሳይሆን ምሥጢራዊና መንፈሳዊ ትርጓሜም አላት፡- ‹ጥበብ ቅኔ ናት› የተባለውም ለዚያ ነው፡፡ ዓለማችን የሚታይ የሚዳሰስ ጥበብ ብቻ አይደለም ያለት፤ ብዙ አስደናቂና ሥውር ጥበባትንም አምቃ ይዛለች፤ የሃይማኖትና የመንፈሳዊ ጥበባትም ባለቤት ነች፡- የሚያስተውልላት እየጠፋ ነው እንጂ! በተለይ ከክርስትና ሃይማኖት አንጻር ስናጮልቅ ጥበብ ክርስቶስን ትወክላለች፡፡ እንዴት ሆኖ ማለት? መልካም ጥያቄ ነው፡፡ በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል፤ አንድም ከጥበብ ቅኔነት አንጻር፤ ሌላም ከጥበብ ፍጽምናን ናፋቂነት አኳያ!
‹ጥበብ ቅኔ ናት› ብለናል፤ ቅኔ ደግሞ በተዋህዶ የከበረ ምሥጢርን ያቀፈች ጥበብ ነች፡፡ ይህ ዓለም ደግሞ በሁለት ነገሮች ተዋህዶ የሚኖር ክስተት ነው፤ ለምሳሌ በሐሳብና በአዕምሮ፣ በመንፈሳዊ ነገርና በዓለማዊ ክስተት፣ ወዘተ፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ተዋህደው በአንድነት የሚኖሩ መሆናቸው ድንቀትን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ የሐሳብና የአዕምሮ ግንኙነት በፍልስፍናው ዓለም ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ፣ የፍልስፍና አሳቢዎች የተባሉትን በሁለት ጎራ አስለይቶ የሚያጠዛጥዝ ነጥብ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በአሁኑ ጊዜ የፍልስፍና መምህራኑን ይዘታዊ (Continental) እና ቅርጻዊ(Analytical) በሚሉ ጎራዎች አከፋፍሎ የሚያዋጋቸው የዚህ የሐሳብና የአዕምሮ ዕንቆቅልሽ የፈጠረው ቡድናዊነት ነው፡- ምንም እንኳን አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ቢሆንም፡፡ ያም አለ ያ ምሥጢሩ ያለው የሚታወቀውና ቁስ የሆነው አዕምሮ እና የማይታይ፣ የማይዳሰስና መንፈሳዊ የሆነው ሐሳብ በተዋህዶ ተዋህደው ሰው የሚለውን ፍጡር ያስገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ረቂቅ. ምጡቅ፣ ስፉህና ምሉዕ የሆነው መለኮት ግዙፍ፣ ውስን፣ ተዳሳሽና የሚታይ የሆነውን ሰውን በተዋህዶ ገንዘብ አድርጎ መገለጹን ለማጠየቅ ነው፤ የጥበብ ቅኔነትም እዚህ ላይ ነው፤ በተዋህዶ መክበር (መገኘት)፡፡ ‹ጥበብሰ ክርስቶስ ውእቱ፡- ጥበብ ማለት ክርስቶስ ነው› እንዳሉ አበው፤ ቅዱስ ጳውሎስም የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው› (1ኛ ቆሮንቶስ 1፣ 24) ብሎ ጨርሶታል፡፡ የበለጠ ሲያብራራም
በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችንዓለም ገዦች ጥበብን አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር› ብሎ ነው የገለፀው፡፡ (1ኛ ቆሮንቶስ 2፣ 6-8)
በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ ናት› ብለናል፡፡ እነዚህን መሠረታተ-አሚን በምሉዕነት ወይም በፍጽምና አማልቶ የተገኘ ደግሞ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ‹እውነትና ሕይወት እኔ ነኝ› ብሏል፤ በዕውቀቱም ዓለም ሳይፈጠር የነበረውን ሁኔታ ሳይቀር ተናግሯል፤ በመልካምነትም ቢሆን ‹የላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት፤ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የበዛባት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት፡፡› በማለት ነው ሐዋሪያው ያዕቆብ የገለጸው (ያዕቆብ፤ 3፣ 17)፡፡ በመሠረቱ ከላይ እንደተገለጸው ሦስቱ ጽንሣተ-ሐሳብ በተዋህዶ አይነጣጠሉም አንድ ይሆናሉ እንጂ!
በሌላ በኩል ‹ጥበብ አንድም ሦስትም የሆነው የእግዚአብሔር ምሳሌ ናት›፡፡ ለእዚያም ነው ‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው› የተባለው (ምሳ.1፣7)፡፡ አንዱ ፈላስፋም ‹የዕውቀት ሥር መሠረቷ ሃይማኖት፣ እግዚአብሔርን መፍራት፣ ለሰው ሁሉ ባሕርየ-መልካም መሆንና ከወንድም ከጓደኛም ጋር መፋቀር ነው፡፡› ብሏል (አንጋረ-ፈላስፋ፣ ገጽ-34)፡፡ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ የሆነው ወልደ-ሕይወትም
ፀሐይ የብርሃን መሠረት እንደ ሆነ እንዲሁ እግዚአብሔርም የጥበብ መሠረት ነው፡፡ መንፈስ የሕይወት ምንጭ እንደ ሆነ እንዲሁ እግዚአብሔርም የእውነት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ … መመርመር ወደ ጥበብ የምንገባበት በር ነው፡፡ ዕውቀትም ይህን በር ከፍተን ወደ አዳራሹ ምሥጢር ገብተን ከጥበቡ መዝገብ የምንካፈልበት እግዚአብሔር የሰጠን ቁልፍ ነው፡፡ ((የኢትዮጵያ ፍሎሶፊዎች፡ ሐተታ ዘርአ-ያዕቁብ ወወልደ-ሕይወት፣ ገጽ፣46-47) በማለት ነው ጥበብ የእግዚአብሔርን መሠረት እንደምታደርግ የገለጸው፡፡
‹ስለዚህ ጥበብ ሥላሴ ናት›፤ ለዚያ ነው አበውም ‹ጥበበ ሥላሴ› የሚል ስም የሚያወጡት፡፡ ከዚህ በፊት ጥበብ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ (ቅኔ) ናት› ብለናል፤ መንፈሳዊ ትርጓሜዋ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ‹እግዚአብሔር› የሚለው ቃልም አንድም ሦስትም የሆነውን የአምላክ ስም በተዋህዶነት የሚገልፅ ነው፡፡ ምክንያትም እግዚአብሔር ማለት ‹እግዚእ-ጌታ፣ አብ-አባት፣ ሔር-ቸር› በማለት ተዘርዝሮ ይፈታል፤ ይህም ‹አብ ወልድ መንፈስ-ቅዱስ› ማለትን ይገልጻል፡፡ በዚህም አብ በመሠረትነት (በእውነትን)፣ ወልድ በሠሪነትን (በዕውቀትነት)፣ መንፈስ-ቅዱስ ደግሞ ሕይወት በመሥጠት (በመልካምነት) የሚገለጹ ናቸው፡፡ የጥበብ ተዋህዶነትም እዚህ ላይ ትመሠጠራለች፤ እውነት ያለ ዕውቀት አትገለጽም፤ ያለ መልካምነትም እውነትነቷ አይቆምም፤ ያለ እውነትም ዕውቀት አትኖርም፤ ያለ መልካም እሴትም ዕውቀት ትርጉም አይኖራትም፡፡ ስለዚህ ጥበብ አንድም ሦስትም ናት፤ ሥላሴ ማለት ናት፡፡
ለነገሩ የጥበብን ጥልቅነትና እግዚአብሔርነት አለቃ ዘነብ ኢትዮጵያዊ መጥነውና ተጠበው ገልጸውታል፤ እንዲህ በማለት፡
እግዚአብሔር አብ ጣት ነው፣ እግዚአብሔር ወልድ ብዕር ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ቀለም ነው፤ ሰማይና ምድር ወረቀት ናቸው፤ ፊደሉም ፍጥረት ነው፤ እግዚአብሔር አብም በቃሉ ሰማይንና መሬትን ፈጠረ፤ ያለባቸውን ፍጥረት ሁሉ ፈጠረ፤ በመንፈሱም አጠናቸው… የዚህን ዓለም ሥሩን አገኛለሁ ብዬ ቆፈርሁት፤ ጽኑም ድንጋይ ሆነብኝ ድጅኖ አሳቤም ሁሉ አለቀ፤ እንዲያው ባየው ባስተውለው ሥሩ እግዚአብሔር ነው፡፡› (መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ፣ ገጽ 14-15)፡፡
ለእኔ ድንቅ ገለጻ! የጥበብ ምሥጢር ያስተዋለ አነጋገር ማለት ይህ ነው፡፡ ለዚህ ነው አበው በምናኔና በብህትውና ጥበብን እያውጠነጠኑና በእሷ ተደንቀው እየተመሠጡ ቤት ንብረታቸውን ትተው የሚጠፉት፡፡ ‹ፍልስፍና ማለት ጥበብን ማፍቀር ነው› ማለትስ ይኸ አይደለም ወይ? ሰዎች በእሷ ራሳቸውን ቢጥሉ እሷን እሷን የሚያሳስበውን፣ ቀልብ የሚያስት መስተፋቅሯን አስነክታቸው አይደለም ወይ? እኛ የጥበብ ጾመኞች ስለሆንን ብቻ እነሱን መኮንን አለብን እንዴ?
ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ዓለም ተመሰቃቅሏል፤ እልቃቂቱ ዓለመ-ፍጥረት ላይ የተጠነጠነው የፍጥረት ማግ ውሉ ጠፍቶበት የሚዛቁነውና አእምሮውን ያበላሸው ሁሉ ፈላስፋ እየተባለ፤ የተነገሩና የተጻፉ አባባሎችን በፋይልነት እያጎረ የሚያስተምረው ‹በከመ ይቤ› አስተማሪም ሊቀ-ፋላስፎች እየሆነ፤ በጎነትን በመጥፎ ወስጥ አስገብቶና አደባልቆ የሚደነፋ ‹አጭቤ› ‹የዘመኑ-ምሁር› ተብሎ እየነገሠ፤ በማስመሰል የሚተውነው ‹አርቲስት›ና በተሰጥኦው የሚዘፍነው ዘፋኝ የጠቢብነትን ካባ በተከናነቡበት እንዴት ትክክለኛዋ፣ ጥልቋና በዘመን ሂደት የዳበረችው ጥበብ ትታወቅ? እውነታው ግን ወዲህ ነው ምንም እንኳን የተዘነጋች ብትመስልም ጥበብ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የማልካምነት ተዋህዶ- የሦስትነትና የአንድነት ተዋህዶ› መሆኗን መቼም አትቀይርም? በዚህ መልክ ያልተረዳትም ‹የጥበብ አፍቃሪ› ወይም ‹ፈላስፋ ነኝ› ቢል ስህተት ነው፤ ይልቁንስ መባል ያለበት ‹ሐሳዊ ጠቢብ› ወይም ‹ስሁት ፈላስፋ› ነው፡፡ ለማንኛው ይህንን በዚህ እንግታና ተጨማሪ ጥያቄ እናንሳ እስቲ!
‹ፍልስፍና ምንድን ናት?› ለሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ፍችዋ ‹ጥበብን ማፍቀር› ነው በሚለው ተስማምተናል፤ ጥበብ ደግሞ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ ናት› ካልን፤ የፍልስፍናም ምንነት በእነዚህ በእውነት (Metaphysics)፣ በዕውቀት (Epistemology) እና በመልካምነት (Axiology) ዙሪያ ይሽከረከራል ማለት ነው፡፡ በዚህ የምንስማማ ከሆነ ‹እውነት፣ ዕውቀትና መልካምነትስ ምንድን ናቸው? ፍልስፍና የምትጠናውስ (የምትመረመረው) እንዴት ነው?
‹በጥበብ ግብዣ ላይ ተሳተፍ ትውልዱ፣
ያጠግባል ያረካል የቅኔ ማዕዱ፡፡› ብለው መክረዋል አበው፡፡
አቦ! ጥበቡን ለብዎዉን ይሣልብን፤ ይስጠን፤ የመመርመር ተሰጥኦን አድሎ ከጥበብ ማዕድ ያውለን፤ አሜን፡፡
(ይቆየን፤ ያቆየን)
| Copyright © 2013 Lomiy Blog