በሚኒስትሯ የትዊተር ገጽ ላይ የሰፈረው መልዕክት አነጋጋሪ ሆኗል!

-መንግሥት አካውንታቸው ተጠልፏል እያለ ነው::
የሴቶች፣ የሕፃናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በትዊተር ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ፣ ‹‹በተወዳጇ አፍሪካዬ ውስጥ ጥላቻና መገለል ቦታ የላቸውም፡፡
የአለባበስ ሥርዓት ወይም የፀረ ግብረ ሰዶማዊ ሕጐችን ማውጣት የመንግሥታት ሥራ አይደለም፤›› በሚል የወጣው መልዕክት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ መንግሥት ግን የሚኒስትሯ የትዊተር አካውንት መጠለፉን ገልጾ፣ ይህ መልዕክት የሚኒስትሯንም ሆነ የመንግሥትን አቋም አይወክልም ሲል አስተባብሏል፡፡ 

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በኡጋንዳ የፀደቀውን ፀረ ግብረ ሰዶማዊያን ሕግ በመቃወም በሚኒስትሯ የትዊተር ገጽ ላይ የተጻፈው ይህ መልዕክት፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ የግብረሰዶማዊ መብቶች አቀንቃኞች አድናቆት ተችሮታል፡፡ ሆኖም ግን የሴቶች፣ የሕፃናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ዓብይ ኤፍሬም፣ ‹‹መልዕክቱ በማይታወቁ ሰዎች የተጻፈ ሲሆን፣ የእሳቸውንም ሆነ የመንግሥትን አቋም የማይገልጽ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
አቶ ዓብይ አክለው፣ ‹‹ሚኒስትሯ ይህን የማኅበረሰብ ሚዲያ የሚጠቀሙት ሕዝቡ በቀጥታ ሊያገኛቸው የሚገቡ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ አዋጭ ሚዲያ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የትዊተር ገጻቸውን የሚያንቀሳቅሱት ራሳቸው ወይዘሮ ዘነቡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዓብይ፣ በገጻቸው ላይ በጠላፊዎች በተላለፈው መልዕክት ሚኒስትሯ ማዘናቸውን አስረድተዋል፡፡ 
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል የሚኒስትሯ የትዊተር አካውንት መጠለፉን አረጋግጠው፣ ‹‹የሚኒስትሯን አካውንት ጠልፈው በመግባት የእሳቸውንና የመንግሥትን አቋም የማይገልጽ
መልዕክት ያስተላለፉት ግለሰቦች ጉዳይ ከተጣራ በኋላ፣ አስፈላጊው ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ብለዋል፡፡
የሚኒስትሯ የትዊተር አካውንት መቼ እንደተጠለፈ በውል ባይታወቅም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ግብረ ሰዶማዊያን እኩል መብት ይኑራቸው የሚል መልዕክታቸው፣ ጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በአካውንታቸው በድጋሚ ትዊት ተደርጓል፡፡ ሚኒስትሯ በዚህ የትዊተር ገጻቸው የተላለፉት መልዕክቶች በእሳቸው እንዳልተጻፉ ገልጸዋል፡፡ 
በአገሪቱ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ ከአንቀጽ 629 እስከ 631 ድረስ በሰፈረው መሠረት የግብረ ሰዶም ወንጀል አሥራ አምስት ዓመት ድረስ በእስራት ያስቀጣል፡፡   
ሚኒስትሯን በትዊተር ገጽ ላይ የሚከተሏቸው 1,600 ሰዎች የነበሩ ሲሆን፣ ማክሰኞ ምሽት ላይ ይህ ቁጥር 1,837 ደርሶ ነበር፡፡ እሳቸው ደግሞ የሚከተሏቸው 99 አካውንቶች ሲኖሩ፣ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ 672 የትዊተር መልዕክቶችን በገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ 
 Source: Reporter
በዩጋንዳ ትናንት ጀምሮ ግብረ ሰዶማዊነት የሚቃወም ህግ ተደንግጓል ። የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የዩጋንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግብረ ሰዶማዊነትን በመቃወም ባለፈው ታህሳስ ያሳለፈውን ህግ ትናንት በፊርማቸው አፅደድቀዋል ። ህጉ የፀደቀው በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ግብረሰዶማዊነትን በሚቃወሙ ወገኖች መካከል ለዓመታት ከተካሄደ ትግል በኋላ ነው ። በአዲሱ ህግ የሰዶማዊነት ተግባር በእድሜ ልክ እሥራት ያስቀጣል ። አዲሱ ህግ ከመፅደቁ በፊት ብዙ ጊዜ ወስዷል ።
እጎአ በ2009 ነበር ግብረ ሰዶማዊነትን የሚቃወም ረቂቅ ህግ ለዩጋንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ። የያኔው ረቂቅ ህግ በተደጋጋሚ የግብረ ሰዶም ተግባር ሲፈፅም በተገኘ ሰው ላይ እስከ ሞት ቅጣት የሚደርስ ብይን እንዲተላለፍ የሚደነግግ ነበር ። ይህም በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ ። በመጨረሻም መቀመጫውን ካምፓላ ያደረገው የሃገሪቱ ፓርላማ ባለፈው ታህሳስ ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት ዝቅ ያደረገውን ህግ አሳለፈ ። ዩጋንዳ በብሪታኒያ
ቅኝ አገዛዝ ሥር ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ በወንጀለኛ መቅጫ ደንብ ግብረ ሰዶማዊነትን የሚያስቀጣ አንቀፅ ሰፍሮ ይገኛል ። የአሁኑ ህግ ግን ከዚያም በላይ የጠነከረ ነው ። የግብረ ሰዶማውያንን ጥቅሞች የሚያስጠብቁ ወይም ግብረ ሰዶማዊ ባህርይ ያላቸውን ሰዎች የማያጋልጡም በእስራት ሊቀጡ ይችላሉ ። የስደተኞች ህግ ፕሮጀክት የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ ለሆኑት ለሲራንዳ ጀራልድ ብላክስ ይህ አስደንጋጭ መልዕክት ነው ።
«ይህ ረቂቅ እጆችን በሙሉ የሚያስር ነው ። ህጉ ሁላችንንም ችግር ውስጥ ይከታል ። ከግብረ ሰዶማውያን የሚሠሩ ወይም የሚኖሩ ቤት አከራይም ይሁኑ አለያም ሃኪሞች ብቻ እነዚህን ሰዎች የሚያውቁ ለፖሊስ የማመልከት ግዴታ አለባቸው ። ያን ካላደረግን ልንታሰር እንችላለን ። »
ሙሴቬኒ ህጉን ወዲያውኑ አላፀደቁም ከዚያ በፊት ሳይንሳዊ ምክር እንደሚፈልጉ አሳወቁ ። አጋጣሚውን በመጠቀም የዩጋንዳ የህግ ባለሞያዎችና የመበት ተሟጋቾች ረቂቅ ህጉ አድሎአዊና ኢህገመንግሥታዊ ነው ሲሉ ስጋታቸው ለፕሬዝዳንቱ ገለፁ ። ዓለም ዓቀፍ ሃኪሞች ችግሩን በማሳወቅ ለፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ ሲፅፉ ከ60 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችም ህጉ የሚያስከትላቸውን መዘዞች በመዘርዘር አሳወቁ ።እነዚህ ወገኖች ከሁሉ በላይ ግብረ ሰዶማውያን ህክምና ከተነፈጋቸው HIV ኤድስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ ተፅእኖ ያሳድራል የሚል ስጋት አላቸው ። በዚህ ኦመት መጀመሪያ ላይ የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ጉዳድላክ ጆናታን ሰዶማዊነትን የሚቃወም ህግ በፊርማቸው ካፀደቁ ወዲህ ሙሴቬኒ በዚህ የተደፋፈሩ አስመስሏቸዋል ። የጠበቀ የክርስትና እምነት ያላቸው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ራሳቸው ከሳይንቲስቶች ከሃኪሞችና ከፖለቲከኞች የመለመሏቸው 11 ሰዎች የሚገኙበት ኮሚሽን የግብረ ሰዶማዊውያንን ተፈጥሮ አጥንቶ የሚያቀርበውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ ናቸው ። በመሃሉ ግን የካቲት 3 ቀን 2006 ሃላፊነት ያለበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውጤቱን በማቅረብ ሳይንሳዊ የተባለ አቋም ወስዷል ። በዚህ ውጤት መሠረት ግብረሰዶማዊነት ተጨባጭ በሆነ ዘረ መል የሚከሰት በሽታ እንዳልሆነ ገልጿል ። አሁንም ቢሆን ተጨማሪ ምርምር ያስፈልጋል ። ኮሚሽኑ ግን እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨባጭ የሆነ ምክር አልሰጠም ። ይሄ ዜና የደረሰው የሙሴቬኒ ፓርቲ አብይ ጉባኤ ላይ ነበር ። በዚያኑ እለትም የ69 ዓመቱ ሙሴቬኒ ለ2016 ምርጫ ራሳቸውን በእጩ ተወዳዳሪነት አቅርበዋል ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የደረሰበትን ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ ተቀብለው ሆኖም ግብረሰዶማዊነት በተፈጥሮ የሚወረስ ሳይሆን ከመጥፎ ማህበራዊ መስተጋብር የሚመጣ ነው የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰዋል ። ታዛቢዎች የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ሥልጣን ለመቆየት የተጠቀሙበት ስልት ነው ሲሉ ተችተዋል ። ከጀርመን የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት አንድሪያ ኬምፕፍ
«ይህን ናይጀሪያን በመሳሰሉ ሌሎች አገራትም የምንታዘበው ነው ። ከልምድ እንደምገነዘበው ይህ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ነው ። እጎአ በ2009 ህጉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ በ2011 ምርጫው ተካሄደ ።»
ሙሴቬኒ በግብረ ሰዶማውያን ላይ የወሰዱት እርምጃ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በኩል ጠንካራ ትችት አስከትሏል ። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እርምጃው ዩጋንዳ ለሚገኙ ግብረ ሰዶማውያን አደጋ መሆኑን ለኡጋንዳውያንም ወደ ኃላ እንደመጓዝ የሚታይ እንደሆነ ተናግረዋል ። የጀርመን መንግሥት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ክሪስቶፍ ሽትራሰር ደግሞ ውሳኔው እንዳስደነገጣቸው አስታውቀዋል ። ከ54 ቱ የአፍሪቃ ሃገራት በ38 ቱ ግብረሰዶማዊነትን በህግ ያስቀጣል ። ከመካከላቸው በሞሪቴንያ በሱዳንና ሶማሊያ በሞት የሚያስቀጣ ድርጊት ነው ።
 Source: www.dw.de

በቦሌ ዋናው መንገድ ከሚሊኒየም አዳራሸ ማዶ በሚገኘው የሕብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ቅርንጫፍ በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት፣ ‹‹ኑሮ መሮኛል›› በማለት እየተናገረ ለጥበቃ በያዘው ጠመንጃ የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ራሱን አጠፋ፡፡
ወጣቱ የጥበቃ ሠራተኛ በሱፈቃድ በጋሻው በኪሱ ውስጥ ከተገኙት የተለያዩ መታወቂያዎች መረዳት እንደተቻለው፣ አጋር የጥበቃ ሠራተኞች ማሠልጠኛ ተቋም ተቀጣሪ ነው፡፡ በተጨማሪም የኮሌጅ ተማሪ መሆኑን በሚገልጸው መታወቂያ ላይ እንደሠፈረው ከሆነ፣ በ1982 ዓ.ም. የተወለደና የ24 ዓመት ወጣት ነው፡፡ በምን ምክንያት ከፖሊስ ባልደረባነት እንደለቀቀ ባይታወቅም፣ የ13ኛ ኮርስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባል እንደነበር በቅርብ ከሚያውቁት ወዳጆቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በባንኩ አሠራር አንድ የጥበቃ አባል 24 ሰዓት ሠርቶ 24 ሰዓታት የሚያርፍ በመሆኑ፣ ሟች በሱፈቃድም የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት አዳሪ ጓደኛውን ከቀየረ በኋላ፣ ባንኩን ለመጠበቅ የቻለው ለ24 ሰዓታት ሳይሆን ለሰባት ሰዓታት ብቻ ነው፡፡ ወጣቱ ‹‹ኑሮ መሮኛል›› በማለት እያማረረ እያለ በመሀል የያዘውን ጠመንጃ ቃታ በመሳብ አንድ ጊዜ ወደ ላይ ሲተኩስ፣ አብረውት የነበሩ ሴት ፈታሽና ሌሎች የባንኩ ተጠቃሚዎች በመደናገጥ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ ሽሽት ይጀምራሉ፡፡ ሁለተኛውን ጥይት በመተኮስ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ በኩል በፍጥነት መራመድ መቀጠሉን በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ 
ሦስተኛውን ጥይት ወደ ላይ ከተኮሰ በኋላ አራተኛውን አንገቱ
ሥር በመደገን ተኩሶ፣ ራሱን ማጥፋቱን የዓይን እማኞቹ አስረድተዋል፡፡
ሟች በሱፈቃድ ተወልዶ ያደገው በጉለሌ አካባቢ እንደሆነ፣ አሁንም ከቤተሰቡ ጋር እየኖረ እንደሚገኝ፣ ጊዜውን ባይጠቅሰውም በተወለደበት አካባቢ ነዳጅ የጫነ ተሳቢ ፍሬን ተበጥሶ ከሞት ማምለጡን፣ መሞት ካለበት ደግሞ ራሱን በራሱ ማጥፋት እንዳለበት መወሰኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎ በኪሱ መገኘቱም ተሰምቷል፡፡
Source: Reporter
 
-ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነካቢኔያቸው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ
የግብፅ መንግሥት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የጀመረውን ዘመቻ ዓለም አቀፍ ገጽታ ለማላበስ አዲስ እንቅስቃሴ ሊጀምር ነው፡፡
ከወደ ግብፅ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የግብፅ የውኃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይህንን አዲስ እንቅስቃሴ ያስተባብራሉ፡፡ 
ከዚህ ቀደም ግድቡን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ለማቅረብ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተገትቶ፣ አዲሱ ዘመቻ ፊቱን ወደ ጣሊያንና ኖርዌይ አዙሯል፡፡ ከዚያም ወደተለያዩ አገሮች ይቀጥላል፡፡ 
ባለፈው ሳምንት የውኃ ሚኒስትሩ መሐመድ አብዱል ሙታሊብና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነቢል ፋህሚ ወደ ጣሊያን ጉዞ አድርገዋል፡፡ የግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ዋነኛ ሸሪክና የግድቡ ግንባታ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ባሉዋት ጣሊያን የተደረገው ጉብኝት ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡ 
   የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የግድቡን ጥናትና ግንባታ የሚያካሂድ በመሆኑ፣ ጣሊያን የግብፆች የአዲሱ ዘመቻ ዓላማ መሆኗ እየተነገረ ነው፡፡ የውኃ ሚኒስትሩ ሙታሊብ ለግብፅ ሚዲያዎች እንደገለጹት፣
የጣሊያን ጉብኝት ግቡን በመምታቱ ወደ ሌሎች አገሮችም ጉዞው ይቀጥላል፡፡ ምንም እንኳ የተገኘው ስኬት ምን እንደሆነ ባይብራራም፣ ሙታሊብ ለጣሊያን መንግሥት ባለሥልጣናት በግድቡ ምክንያት ግብፅ ሊደርስባት የሚችለውን የውኃ ችግር ማስረዳታቸውን፣ የጣሊያን ባሥልጣናትም ችግሩን አሁን ገና መስማታቸውን መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የሚቀጥለው ጉዞም ለህዳሴው ግድብ የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች ባሉዋት ኖርዌይ እንደሚሆን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኖርዌይ ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ መቼና የት እንደሰጠች ግን አላብራሩም፡፡ ግብፆች ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች መካከል አንዷ ኖርዌይ ናት በማለት ሌሎችም አገሮች ዕርዳታ ይሰጣሉ የሚል አንድምታ ያለው አስተያየት መሰንዘራቸው ተሰምቷል፡፡  
የግብፅ መንግሥት የሚቀጥለው ዕርምጃ በተለያዩ አገሮች የሚደረግ ጉዞ ሲሆን፣ በየአገሮቹም የግብፅን አቋም በሰፊው ማስተዋወቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የዚህ ጉዞ ዓላማ ለግብፅ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ማስገኘት መሆኑ ተወስቷል፡፡ ከእነዚህ ጉዞዎች ለግብፅ ድጋፍ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ማሳጣትም ነው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡ ግብፅን አይጐዳም እያለች ባለችበት ወቅት፣ ግብፆች ግን ይህ ግድብ በግብፅ ህልውና ላይ አደጋ የጋረጠ ነው በማለት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ መዘጋጀታው ተሰምቷል፡፡ 
ለተመድና ለአፍሪካ ኅብረት የሚቀርበው አቤቱታ ከፕሬዚዳንታዊው ምርጫ በኋላ የሚመሠረተው መንግሥት ተግባር እንዲሆን ወደጐን ተገፍቶ፣ አሁን የተያዘው በተለይ በአውሮፓ አገሮች ውስጥ ሰፊ ዘመቻ መጀመር እንደሆነ ሾልከው የወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ በግድቡ ላይ ጥያቄ ለማስነሳት ሌላ ዘመቻ መታቀዱም ይሰማል፡፡ ሰሞኑን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋህሚ ነቢል በታንዛኒያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ጉብኝቱንም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዊቴ ማንም አገር ግድብ ሲገነባ የተፋሰስ አገሮችን ማማከር አለበት ማለታቸው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡      
የግብፅ የውኃ ሚኒስትር ሙታሊብ መንግሥታቸው በርካታ አማራጮችን በመያዝ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ስምምነት መድረሱን በይፋ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት በበርካታ አገሮች ግድቡ ግብፅን እንዴት እንደሚጐዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል፡፡ የግብፅን ተለዋዋጭ አቋምና ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ወገኖች ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአፀፋው ተዘጋጅቷል ወይ በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡ ከራሷ አልፎ ለአካባቢው አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጐት መሟላት ወሳኝ መሆኑንና የግድቡን የጥራት ደረጃ በሚገባ ማሳየት አለባት ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ እውነታውን ይዛ በግብፅ ፕሮፓጋንዳ መበለጥ የለባትም በማለት ያስረዳሉ፡፡   
ይህ በዚህ እንዳለ የግብፅ ጊዜያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐዚም አል ቤብላዊና የሚመሩት ካቢኔ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአገሪቱ ሊካሄድ የሁለት ወራት ዕድሜ ሲቀረው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ 
ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ እስኪከናወን ድረስ አገሪቱን እንዲያስተዳድር የተመረጠው የግብፅ ጊዜያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትርና የሚመሩት ካቢኔ ባለፈው ሰኞ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ማስገባታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ያስገቡበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ፣ እሳቸውና ካቢኔያቸው የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሊ መንሱር እንዳስገቡ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያውን ለምን እንዳስገቡ ባይገልጹም፣ ከካቢኔያቸው ጋር የ15 ደቂቃ ውይይት አድርገው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በግብፅ መንግሥት ውስጥ ብቻ ለውጥ ማምጣት ትርጉም የለውም፡፡ የግብፅ ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚመኘውን ለመሆን በራሱ መጣር አለበት፤›› ሲሉ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትር አል ቤብላዊ፣ ‹‹ግብፅ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆነች ሁሉ ሊጨበጡ የሚገባቸው ትልልቅ ዕድሎች እየተበላሹባት ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜው ለአገራችን ስንል መስዋዕትነት የምንከፍልበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
በሙያቸው ኢኮኖሚስት የሆኑት ቤብላዊ የግብፅ ሕዝብ አገሬ ምን አደረገችልኝ ከማለት ባለፈ፣ ለአገሬ ምን አደረግኩ ብሎ መጠየቅ እንዳለበት ገልጸው፣ የአጭር ደቂቃ መግለጫቸውን አጠናቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚመሩት ካቢኔ በአጠቃላይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ትችት ሲጐርፍባቸው ነበር በማለት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ይገልጻሉ፡፡ በበርካታ መገናኛ ብዙኃን ትችቶችም ሲወርዱባቸው ነበር፡፡  
የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲን አሸባሪ ብሎ ለመፈረጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረጅም ጊዜ አጥፍተዋል፡፡ በቅርቡ በፀደቀው የደመወዝ ስኬል የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች እንዳይካተቱ ማድረጋቸው፣ በአገሪቱ ውጥረትና የሽብር ጥቃቶች እንዲንሰራፉ አድርገዋል በማለት ይተቿቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪና የጨርቃ ጨርቅ ሠራተኞች፣ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው የፖሊስ አባላት፣ የፖስታ ቤት ሠራተኞች፣ እንዲሁም የሕክምና ዶክተሮች በተቃውሞ ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው ያቀረቡትን መልቀቂያ የአገሪቱ ጊዜያዊ መንግሥት ተቀብሎት፣ በአል ቤብላዊ መንግሥት የቤቶች ሚኒስትር ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ኢብራሂም መህሊብ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሾም ካቢኔያቸውን እንዲመሠርቱ ማክሰኞ ዕለት ተነግሯቸዋል፡፡ 
የአገሪቱን ትልቁን የኮንስትራክሽን ኩባንያ ከአሥር ዓመታት በላይ ሲመሩ የነበሩት መህሊብ፣ የአዲሱ ካቢኔያቸው አባላት ‹‹የቅዱስ ጦርነት ተዋጊዎች›› ይሆናሉ ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፀጥታ በማስከበር ሽብርተኝነትን እንዋጋለን፤›› ያሉት መህሊብ፣ ካቢኔያቸውን በሦስት ቀን ውስጥ እንደሚያዋቅሩ ገልጸዋል፡፡  
በሆስኒ ሙባረክ ዘመን የገዥው ፓርቲ (ናሽናል ዲሞክራቲክ ፓርቲ) አባል የነበሩት መህሊብ ካቢኔውን ሲመሠርቱ፣ አብዛኞቹን ሚኒስትሮች በነበሩበት ቦታ ላይ ይመድባሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚታወቁት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት በግብፅ እንደገና አመፅ ሊቀሰቀስ ይችላል እየተባለ ነው፡፡       
 Source: Reporter

ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በእያንዳንዱ የሕወሓት የልደት በዓል ማለትም የካቲት 11 በዋነኝነት ከሚከበርበት የትግራይ ርዕሰ ከተማ መቐለ ተገኝተው በሚያደርጉት ንግግር በዓሉን ሁሌም ድምቀት ይሰጡት ነበር፡፡
ሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ ዋነኛ መሥራች የሆነውን ሕወሓት የረጅም ጊዜ ጠንካራ ሊቀመንበሩን ያጣው ባለፈው ዓመት በዓሉን ከማክበሩ ስድስት ወራት በፊት ነበር፡፡
አቶ መለስ ለመጀመርያ ጊዜ ያልተገኙበት 38ኛው በዓል ግን እሳቸውን በመዘከር በሐዘን ድባብ ነበር ያለፈው፡፡ ተተኪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በወቅቱ በበዓሉ ላይ ቢገኙም፣ በአቶ መለስ መሪነት እዚህ ደርሷል ያሉት ሥርዓት ከፍተኛውን መስዋዕትነት ከፍሎበታል ካሉት ከትግራይ ሕዝብ ጋር እጅና ጓንት በመሆን እንደሚሠሩ፣ ‹‹የማፅናኛ›› ንግግር አድርገው ነበር የተመለሱት፡፡ 
ዘንድሮ የተከበረው 39ኛው የሕወሓት በዓል ግን ባለፈው ዓመት በሐዘን ድባብ ያለፈውን በዓል ያካካሰ በሚመስል ሁኔታ እጅግ ደማቅ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ላለፉት 22 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ ዋነኛ አካል የሆነው ሕወሓት፣ በሚቀጥለው አርባኛ የልደት ዓመቱ በበለጠ በደመቀ ሁኔታ ያከብራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የዘንድሮው ግን ከተገመተው በላይ ደማቅ ሆኖ ተከብሯል፡፡ 
የሕወሓት በዓል እጅግ እንዲደምቅ ምክንያት የሆነው ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለየ የሠራው ነገር ኖሮ አይመስልም፡፡ እንዲያውም ድርጅቱ ጠንካራ መሪውን በሞት ካጣ በኋላ መረጋጋት ተስኖት በውስጥ መከፋፈልና እርስ በርስ በመወነጃጀል ማሳለፉ ይነገራል፡፡ የድርጅቱ ሌሎች አንጋፋ መሪዎችም ያላግባብ ከአመራር መሸኘቱ ከፍተኛ ትችት ያስተናገደበት ዓመት ነበር፡፡ በሌሎች ዓመታት እንደተለመደው
የድርጅቱን የትጥቅ ትግል ታሪክ በሚያወሱ ዘጋቢ ፊልሞች፣ የጦር ውሎዎችና ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ያስመዘገበው ልማት በመንግሥት ሚዲያ ታጅቦ ነው በዓሉ የተከበረው፡፡ 
ይህ ጽሑፍ ዋና ዓላማው የሕወሓትን የልደት በዓል ወይም የድርጅቱን የትጥቅ ትግልና መስዋዕትነት ለመተረክ አይደለም፡፡ የዘንድሮው የድርጅቱ የልደት በዓል እንዲደምቅ ምክንያት የሆነው የተለየ አንድ ውጫዊ የሆነን አጋጣሚ መነሻ በማድረግ አገራዊ አንድምታውን መዳሰስ ነው፡፡ 
‹‹ሴሲና›› ታሪካዊው አውሮፕላን 
ወጣት ተስፋሁን አምባቸው በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ካፌ ውስጥ ሻይ ቡና እያለ በኢቲቪ በቀጥታ ሲተላለፍ የዋለውን የድርጅቱን በዓል ሲመለከት ነበር፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርም ሆኑ ሌሎች አመራሮች ያደረጓቸው ንግግሮች ምን እንደሚሉ ቀድሞ እንደሚያውቅ ሰው ለመስማት እምብዛም የጓጓ አልነበረም፡፡ የተስፋሁንን ቀልብ መሳብ የጀመረው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር መኖራቸውን ሲመለከት ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የቅርብ ወዳጅ እንደበሩ የሚነገርላቸው ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ በዚህ የሕወሓት በዓል መገኘታቸው ብቻ አይደለም የተስፋሁንን ቀልብ የሳበው፡፡ 
የተስፋሁንና የጓደኞቹ ወሬ የሚያጠነጥነው በሕወሓት የልደት በዓል ላይ አልነበረም፡፡ ፕሬዚዳንት አል በሽር ኢትዮጵያ መጥተው በሕወሓት በዓል ላይ ሲገኙ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ የግሉ ሚዲያ እምብዛም ትኩረት የሰጠው ባይመስልም፣ የመንግሥትን ሚዲያ ለተከታተሉ አብዛኛዎቹ ሰዎች አነጋጋሪ የሆነው የእነተስፋሁን ጓደኞችንም ቀልብ የሳበው የፕሬዚዳንቱ መገኘት ነው፡፡ የብዙ ኢትዮጵያውያን ዜጐችን ቀልብ የሳበው ግን የፕሬዚዳንቱ መገኘት ብቻ በራሱ አይመስልም፡፡ በግንቦት 1983 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና አቶ ሥዩም መስፍን፣ አቶ ተፈራ ዋልዋና ሌሎች የሕወሓት ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ድርጅቱ ባካሄደው ጦርነት ደርግን አሸንፎ ወደ አራት ኪሎ ታላቁ ቤተ መንግሥት ሲገባ በአንድ አውሮፕላን ነበር የመጡት፡፡ ከሱዳን ካርቱም ወደ አዲስ አበባ የመጡበት አውሮፕላን አብራሪ የነበሩት ቀድሞ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ጄኔራል አልፋታህ በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በወቅቱ በጉዞ ላይ እያሉ የዚህ ታሪካዊ አውሮፕላን አንደኛው ሞተር ከሥራ ውጪ በመሆኑ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ሆነው በወቅቱ ታጋይ ሥዩም መስፍን ከአብራሪውና ከድርጅቱ ሊቀመንበር ታጋይ መለስ ዜናዊ የተለዋወጡዋቸው ‹‹ኑዛዜ›› የሚመስሉ ምልልሶች ነበሩ፡፡ በተለይ አቶ ሥዩም፣ ‹‹ይኼ ሕዝብ ዕድለኛ አይደለም ማለት ነው፣ እኔ ነኝ ጉድ ያደረጉኩህ፡፡ ጓዶች በመኪና እንድንመጣ አስጠንቅቀውን ሳለ በፕሌን እንድንመጣ በማድረጌ አዝናለሁ፤›› ሲሉ፣ ታጋይ መለስ በበኩላቸው በፈገግታ፣ ‹‹አንተ ባስክብንኮ›› ማለታቸውን አቶ ሥዩም አውስተዋል፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር የነበሩት አብራሪው ጄኔራል አልፋታህም ከታጋዮች ጋር የቅርብ ወዳጅ የነበሩ በመሆናቸው ትውስታቸውን እንዲህ በማለት ነበር የገለጹት፡፡
‹‹አንድ የማስታውሰው ነገር ቢኖር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፣ አል በሽርና እኔ ተቀምጠን እየተወያየን ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜያት የሕወሓት የትግሉ አካል መሆኔን ተመልክቶ አምባሳደር እንድሆን ሲጠይቀኝ እኔም አምባሳደር ሆንኩኝ፡፡ እኔ የአውሮፕላን አብራሪ ብቻ ሳልሆን ደርግንም የምታገል አካል ነበርኩ፡፡ የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል መሆኔ እጅግ ያስደስታል፤›› ነበር ያሉት፡፡ 
‹‹ሴሲና›› በመባል የሚታወቀውና ከአስፈሪው አደጋ ያመለጠው ይህ ታሪካዊ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ በስጦታ የተበረከተ ሲሆን፣ በመቐለው የሰማዕታት ሙዚየም ውስጥ እንዲቀመጥ ተወስኗል፡፡
የፕሬዚዳንት ሐሰን አል በሽር ንግግርም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ሕወሓት ጋር የነበራቸው የቀረበ ወዳጅነት፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በተመለከተ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለታዳሚዎቻቸው ከፍ ባለ ድምፀት ያለው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጠንሳሽነት የተመሠረተው ድርጅት ራዕይ ተግባራዊ መሆኑን ነበር የተናገሩት፡፡ ‹‹የሰማዕታት ደም ሊካስ የሚችለው ሰማዕታት የወደቁባቸው ተራሮች፣ ሜዳውና ሸንተረሩ በልማት ሲሸፈኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር አቶ ዓባይ ወልዱም ንግግር አድርገዋል፡፡ 
ከጉርብትናም በላይ ወዳጅነት 
የፕሬዚዳንት አል በሽርና በኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር ጄኔራል አልፋታህ በዚሁ የሕወሓት በዓል መገኘታቸው ትልቅ ቀልብ የሳበበት ምክንያት የሁለቱ አገሮች መልካም ጉርብትና ብቻም አይደለም፡፡ 
በቅርቡ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያንን እያጨቃጨቀ ያለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጉብኝቱ ጀርባ ያለ ይመስላል፡፡ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የተነሳውን አለመግባባት ለመፍታት ሱዳንን ጨምሮ ላለፈው አንድ ዓመት የተካሄደው የሦስትዮሽ ውይይት ትልቅ ሥፍራ የተሰጠው ነበር፡፡ በሦስተኛው ውይይት ሒደቱ ያለውጤት ቢበተንም፣ የግብፅ ታሪካዊ ወዳጅ የሆነችው ሱዳን በድርድር ሒደት ውስጥ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ማዞሯ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስጦታ ነበር፡፡ 
ቀደም ሲል ግብፅና ሱዳን በዓባይ ላይ የተዋዋሉዋቸው አግላይ ስምምነቶች (1929 እና 1959) የውኃውን ክፍፍል ለሁለቱም አገሮች ማድረጋቸውና ሁሌም የሱዳን አቋም ከግብፅ ጋር የተገናኘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁለቱም አገሮች ከተፋሰስ አባል አገሮች በስድስቱ የተፈረመውን የአሥር ዓመት የውይይት ውጤት በሆነው የዓባይ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ማዕቀፍ (CFA) በእንቢተኝነት ፀንተው ነበር፡፡ ከዚያም በተጨማሪ አንዳንድ የአሜሪካ የስለላ መረጃዎች እንዳጋለጡት፣ በግብፅና በሱዳን ባለሥልጣናት መካከል በተደረጉ ሚስጥራዊ ግንኙነቶች፣ ግብፅ ግድቡን ለማውደም የሱዳንን ግዛት ለመጠቀም ዕቅድ ነበራት፡፡ የአሁኑ የሱዳን አቋም መለወጥ ግን በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የነበረው የኃይልና የዲፕሎማሲ ሚዛን እንዲቀለበስ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ 
በአሁኑ ወቅት የግብፅና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አንዳንድ የተካረሩ ቃላት እየተለዋወጡ ሲሆን፣ ከፕሬዚዳንት አል በሽር ጋር በጋራ በመቐለ በሕወሓት በዓል ታዳሚ የነበሩት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግብፅን አካሄድ በመቃወም ግልጽ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሊ ካርቲ ለሱዳን ትልቁ ሚዲያ ሱዳን ትሪቢዩን እንደተናገሩት፣ የግብፅ ባለሥልጣናት በሚዲያ እየሰጡዋቸው ያሉት ተንኳሽ መግለጫዎች ሁኔታውን የሚያባብሱ ናቸው፡፡ ‹‹የሱዳን አቋም ግልጽ ነው፡፡ በግብፅ ባለሥልጣናት በቀውሱ ላይ ሱዳን በምትጫወተው አወንታዊ ሚና እንዲጠቀሙ ነግረናቸዋል፡፡ የቀድሞ ገዥዎቻቸው ግትርነት አላሠራ ብሏቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ራሳቸው ፕሬዚዳንት አል በሽርም ቀደም ሲል በግልጽ ቋንቋ የታላቁን ዓባይ ግድብ መገንባት እንደሚደግፉ ተናግረው ነበር፡፡
ሱዳን የአቋም ለውጥ ለምን አደረገች?
የዓባይን ውዝግብ በተመለከተ ቀደም ሲል በሱዳንና በግብፅ መካከል የነበረው ግንኙነት መዳሰስ የዛሬውን ለመገንዘብ ይረዳል፡፡ በተለይ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙትን ሁለቱን ስምምነቶች መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1929 በታላቋ ብሪታንያና በግብፅ መካከል የተደረገ ነው፡፡ ለሱዳን የተሰጠ የውኃ መጠን አራት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲሆን፣ የተቀረው 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ደግሞ ለግብፅ ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት ግብፅ በፈለገችው ጊዜ በወንዙ ላይ ግድብ የመሥራትና የመጠቀም ሥልጣን ያላት በመሆኑ፣ ሱዳን ይህንን ለማድረግ የግብፅን ፈቃድ እንደትጠይቅ ትገደዳለች፡፡ 
ሁለተኛው ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. በ1959 የተፈጸመ ነው፡፡ ይህ በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገ ስምምነት ነበር፡፡ በቀድሞው የውኃ ስምምነት ያልታወቀ የውኃ መጠን በመገኘቱ በዚህ ስምምነት የሱዳንን ድርሻ ወደ 18.5 መቶኛ ኪዩቢክ ሜትር ከፍ እንዲል የተደረገ ቢሆንም፣ ሱዳኖች ውኃውን የመጠቀም መብታቸው በግብፅ በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ መረዌ የተባለው ግድብ ከአራት ዓመታት በፊት ተገንብቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ በውኃ ለመሙላት እስካሁን ሱዳኖች ፈቃድ አላገኙም፡፡ ሮዜሬስ የተባለውን ግድብ የውኃ መጠኑን ከፍ ለማድረግ ጠይቀውም እስካሁን አልተፈቀደላቸውም፡፡ 
የውኃው ዋነኛ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ያገለሉ እነዚህ ስምምነቶች ውኃውን በግብፅና በሱዳን መካከል የሚከፋፍሉ ቢሆንም፣ ሱዳን በስምምነቱ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ትገነዘባለች፡፡ ግብፆች በሱዳኖች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ዛሬ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በሚኒስትሮች ደረጃ ሳይቀር እጃቸው ረዘም ያለ እንደነበረ ቢታወቅም፣ በአሁኑ ወቅት ጫናው እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ 
በመስኖና የውኃ ሚኒስትር የወሰንና የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሱዳኖች በዓባይ ውኃ ጥቅማቸው የሚጠበቅላቸው ከግብፆች ጋር በማበራቸው ሳይሆን ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር በመተባበራው መሆኑን በተግባር ታዝበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተከዜ ግድብ በመገደቡ ምክንያት ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ገበሬዎች በመስኖ ከፍተኛ ልማት እያከናወኑ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ቀደም ሲል በጎርፍ ይጥለቀለቁ እንደነበር፣ አሁን ከዚህ ችግር መገላገላቸውና በደለል ይሞላ የነበረው ወንዛቸው አሁን ከዚህ ችግር ወጥቶ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሲሰጥ ማየታቸው ለሱዳኖች አቋም መለወጥ ዋና ምክንየት መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ 
ዶ/ር ያሲር መሐመድ በሱዳን የውኃ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በኔዘርላንድስ ደግሞ የዩኔስኮ የውኃ ትምህርት ተቋም የውኃ ሀብት ተጋባዥ መምህር ናቸው፡፡ ከሦስት ወራት በፊት በመቐለ በተካሄደው አንድ የውኃ ኤክስፖርቶች ቴክኒካዊ ምክክር ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በአጋጣሚ አግኝተናቸው ስለጉዳዩ አጭር ቆይታ አድርገን ነበር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የግብፅ ሥጋት ኢትዮጵያ በምትገነባው ግድብ የውኃው መጠን እንዳይቀንስ አይደለም፡፡ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች በወንዙ ሊለማ የሚችል መሬት ተደምሮ አንድ ላይ የሱዳንን ያህል አይሆንም፡፡ እስካሁን ግን ሱዳን በከፍተኛ ደረጃ የመስኖ ልማት እምብዛም ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ የወደፊት ዕቅዷ ግን ይኼንን ውኃ ጥቅም ላይ በማዋል ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን መሳብ ነው፡፡ እንደሳቸው እምነት፣ ግብፅ የምትጎዳው እዚህ ላይ ነው፡፡ የውኃውም መጠን የሚቀንሰው ሱዳን ውኃውን ለመስኖ መጠቀም የጀመረች ቀን ነው፡፡ 
ዶ/ር ያሲር መሐመድ እንደሚሉት፣ ግብፆች ግልጽ ባያወጡትም በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳዩት ተቃውሞ በተዘዋዋሪ  በዋናነት በሱዳን ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ‹‹የውክልና ጦርነት ነው፡፡ እውነተኛ ችግራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከሱዳን ጋር ነው፡፡ ውዝግቡን ግን ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሆን ይመርጣሉ፤›› ብለዋል፡፡ 
የታላቁ የዓባይ ግድብ መገንባትን የሚደግፉት የውኃ ተመራማሪው እንደሚሉት፣ የሱዳን መንግሥት ሰፊ ለም መሬቱን ተጠቅሞ በመስኖ ማልማት የሚችለው ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ግድቦችን ከሠራች ብቻ ነው፡፡ ‹‹ግብፆችም ሱዳኖችም ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን የሚገነዘቡ አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ስትራቴጂካዊ የሆነ ትብብር ማድረግ አለባቸው፡፡
የሱዳኑ የውኃ ምሁር አስተያየት ማረጋገጫ የሚመስል አንድ መረጃ ተገኝቷል፡፡ የተከዜ ግድብ ከተሠራ በኋላ የደለል መሙላት በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፣ የሱዳኑ አትባራ ወንዝ የውኃ መጠን በአሥር እጥፍ መጨመሩ የሱዳን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ 
ሱዳኖች ያሳዩት የአቋም ለውጥ ከራሳቸው ተጨባጭ ጥቅም በመነሳት መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት በበዓሉ ላይ መገኘት ጥልቅ የሆነ ወዳጅነት መመሥረቱ አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ‹‹መምጣታቸውም ለአገራችንና ለሕዝባችን ያላቸውን ጥልቅ ድጋፍና ከበሬታ የሚያሳይ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የሁለቱም አገሮች ወዳጅነት ምን ደረጃ እንደደረሰ አመላካች መሆኑን በማስረዳት፡፡
ሱዳንና ኢትዮጵያ ትናንትና
የሱዳንና ኢትዮጵያ ግንኙነት ታሪክ ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተለየ አይመስልም፡፡ አንዱ የሌላውን አማፂ ቡድን የመደገፍ አዝማሚያዎች ያሳዩ ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ ኢትዮጵያ በቅርቡ ነፃነታቸውን ላገኙት የደቡብ ሱዳን ኃይሎች (SPLM) እና በተቀረው የሰሜን ሱዳን አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አማፂዎችን ትደግፍ ነበር፡፡ ሱዳን በበኩሏ፣ አሁን ሥልጣን ላይ ላለው ሕወሓት፣ ለኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅትና በሕወሓት አሸናፊነት ለተበታተነው ለኢዲዩ ከፍተኛ ወታደራዊና የትጥቅ ድጋፍ ታደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 
የሁለቱም አገሮች ጐርባጣ ግንኙነት የተቀየረው ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ነበር፡፡ ባለፉት ቅርብ ዓመታትከ ኢትዮጵያ ጋር ያላት መልካም ጉርብትና በቀዳሚነት የሚነሳ ነው፡፡ የሱዳን ገዢ ፓርቲ ብሔራዊ እስላማዊ ግንባር (National Islamic Front - NIF) እና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አል በሽር ከኤርትራ እስላማዊ ኃይሎችና ከኤርትራ መንግሥት በተለይ ደግሞ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያላቸው አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚለው ግንኙነት፣ የኢትዮ ሱዳን ትብብር ዘላቂነትን ሁሌም ጥርጣሬ ላይ የሚጥለው ነበር፡፡
በሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የጋራ የድንበር ኮሚሽን አማካይነት በቅርቡ የድንበር መካለል ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት ትችቶችን ባይቀበልም፣ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን እየተሰጠ ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ሲሰማ ሰንብቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ሁለቱም አገሮች በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሠረተ ግንኙነት አላቸው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ በሁለቱም ሱዳኖች መካከል በተከሰተው የድንበር ጦርነት ዋና ገለልተኛ ሸምጋይ ሆና የተገኘች ሲሆን፣ በተመድ ጥላ ሥርም ቢሆን አቢዬ ላይ ከሠፈረው ሰላም አስከባሪ ኃይል አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ የተውጣጡ ወታደሮች ይገኙበታል፡፡ 
ደቡብ ሱዳኖች ነፃነታቸውን በሕዝበ ውሳኔ ከማግኘታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ፣ በዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት የክስ ዋራንት ተቆርጦባቸው የነበረው ፕሬዚዳንት አል በሽር የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ድጋፍ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ በወቅቱ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነታቸው ከፍ ብሎ የነበረው አቶ መለስ፣ ፕሬዚዳንት አል በሽርን ከዚህ ክስ ነፃ እንዲሆኑ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ያደረጉት የተሳካ ጥረት ለሱዳን ፕሬዚዳንትና መንግሥት ትልቅ እፎይታ የሰጠ ነበር፡፡
Source: Reporter

ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንበኞች ቀንን በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባከበረበት ወቅት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአየር መንገዱ ደንበኞች አየር መንገዱ ስለደረሰበት የዕድገት ደረጃ ዝርዝር ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር፡፡
የአገር ባህል ልብስ ለብሰው ፈገግታ ሳይለያቸው የአየር መንገዱን ስኬት ሲያስረዱ ‹‹ዋካ ዋካ›› በሚለው በሻኪራ ተወዳጅ ዜማ ታጅበው ነበር፡፡ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት አብዱሰላም አቡበከር፣ ታዋቂ ባለሀብቶችና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በዚህ ደማቅ ሥነ ሥርዓት ላይ አቶ ተወልደ የአየር መንገዱን ስኬት በኩራት አስረድተዋል፡፡

በእርግጥም አየር መንገዱ ባለፉት አምስት ዓመታት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ የዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ቁጥር 79 አድርሷል፡፡ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ደግሞ ወደ 63 አሳድጓል፡፡ እጅግ ዘመናዊ የሚባለውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን እጁ በማስገባት ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም ሦስተኛው አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል፡፡ ገቢውን በሰባት እጥፍ በማሳደግ 2.1 ቢሊዮን ዶላር አድርሷል፡፡
የዚያን ዕለት በአየር መንገዱ ስኬት ሲፍነከነኩ የነበሩትን አቶ ተወልደን ለተመለከታቸው ሰው፣ ከአንድ ቀን በኋላ አስደንጋጭ ዜና ይነገራቸዋል ብሎ በፍፁም ሊያስብ አይችልም ነበር፡፡ የሆነው ግን እንደዚያ ነው፡፡
እሑድ የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ሌሊት ለሰኞ አጥቢያ 202 መንገደኞችንና የአውሮፕላኑን ሠራተኞች አሳፍሮ ከአዲስ አበባ
ወደ ሮም ይጓዝ የነበረው ቦይንግ 767-300 አውሮፕላን፣ ከአንድ ሰዓት በረራ በኋላ የሱዳን አየር ክልል ውስጥ እንደገባ በረዳት አብራሪው ኃይለመድኅን አበራ ተገኝ ተጠልፎ ወደ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ እንዲጓዝ ተደረገ፡፡ ዋና አብራሪው ጣሊያናዊው ካፒቴን ፓትሪዚዮ ባርቤሪ ወደ መፀዳጃ ቤት ሲሄዱ ጠብቆ የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍሉን በር ከውስጥ ቆልፎ አውሮፕላኑን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገው ኃይለመድኅን (ቤተሰቦቹ ታዴ ብለው ነው የሚጠሩት) አውሮፕላኑን በጄኔቭ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም አሳርፎ እጁን ለስዊዘርላንድ ፖሊስ ሰጥቷል፡፡
ኃይለመድኅን በአገሩ የመኖር ዋስትና እንዳጣ በመግለጽ የስዊዘርላንድ መንግሥት ጥገኝነት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፖሊስ በኃይለመድኅን ላይ ምርመራ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ የስዊዘርላንድ መንግሥት ጠበቃ አቁሞለታል፡፡ ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁሌም የአውሮፕላን ጠለፋ በውጭ ሰው የሚከናወን በመሆኑ የኃይለመድኅን የበረራ ቁጥር ‹‹ET 702›› በረዳት አብራሪው መጠለፉ አስገራሚ አድርጐታል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ በመላው ዓለም የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ድርጊቱ የጤና ነው ወይ የሚል ጥያቄም አስነስቷል፡፡ በረዳት አብራሪው የአዕምሮ ጤንነት ላይ ጥያቄ መሰንዘር ተጀምሯል፡፡ 
የኃይለመድኅን ታናሽ እህት ትንሳኤ አበራ በፌስቡክ ገጿ ላይ ባስነበበችው ጽሑፍ ወንድሟ መጠነኛ የሆነ የአዕምሮ መታወክ ገጥሞት እንደነበር ይፋ አድርጋለች፡፡ ከቤተሰብና ጓደኞቹ ራሱን ማግለል፣ ሊያጠቁት የፈለጉ ማንነታቸው የማይታወቅ ሰዎች እንደሚከታተሉት በማሰብ በሥጋት መኖር፣ ወንድሟ ካሳያቸው የተለዩ ባህሪያት መካከል ይገኙበታል፡፡ ኃይለመድኅን እርሱ በሌለበት ቤቱ እንደሚበረበር በማሰብ በቤቱ ውስጥ የቅኝት ካሜራ እስከመስቀል እንደደረሰ ትንሳኤ ተርካለች፡፡ ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምምልስ ያደረጉት ታላቅ ወንድማቸው ዶ/ር እንዳላማው አበራ ወንድማቸው የአዕምሮ ጤንነት ችግር ገጥሞታል ብለው እንደሚጠረጥሩና እህቶቹ ኃይለመድኅን የሥነ አዕምሮ ሐኪም ዘንድ እንዲሄድ እንደመከሩት ተናግረዋል፡፡
የኃይለመድኅን ጐረቤቶች በበኩላቸው ዘወትር ብቻውን የሚታይ፣ ዝምተኛና ሰላምተኛ ሰው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ኃይለመድኅን የሚኖረው ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ሳሚ ሕንፃ ጀርባ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ብሎክ ሰባት በመጀመሪያ ፎቅ ከሚገኝ ባለ አንድ መኝታ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ጠለፋው ከተፈጸመ በኋላ ቤቱ በፖሊስ የተፈተሸ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ በፌዴራል ፖሊስ አባላት የሚጠበቅ በመሆኑ ማንም ወደ ቤቱ ውስጥ መግባት አይፈቀድለትም፡፡ ከመርማሪ ፖሊሶች በስተቀር፡፡
የኮንዶሚኒየሙ አንድ የጥበቃ አባል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኃይለመድኅን በግቢው ውስጥ ለአምስት ዓመታት ተከራይቶ ኖሯል፡፡ ኃይለመድኅን ወደ ቤቱ ሲገባና ሲወጣ ከሰው ጋር አይታይም፡፡ ጓደኛም ይዞ አይመጣም፡፡ ‹‹ሲገባና ሲወጣ ሰላምታ ይሰጠናል፡፡ ከዚያ ውጪ ከሰው ጋር ክፉም ሆነ ደግ ሲነጋገር አይተነው አናውቅም፤›› ያሉት የጥበቃ አባል፣ ኃይለመድኅንን መጨረሻ ያዩት እሑድ የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹እንደተለመደው ቲሸርትና ቁምጣውን አድርጐ በግቢው ደጃፍ ከሚገኘው አነስተኛ የገበያ አዳራሽ (Mini Market) ዕቃ ገዝቶ የተለመደውን ሰላምታ ሰጥቶን አልፏል፡፡ ከዚያ በኋላ አላየሁትም፤›› ያሉት ጥበቃው በወቅቱ የተለየ ነገር እንዳላዩበት ተናግረዋል፡፡ 
በሳሚ ሕንፃ ወደ ውስጥ በተነጠፈው ኮብልስቶን መንገድ በስተግራ በኩል ባለው የኮንዶሚኒየም ግቢ ደጃፍ ምግብ ቤት፣ ኢንተርኔት ቤት፣ ግሮሰሪና አነስተኛ የገበያ አዳራሽ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ንግድ ቤቶች አንዱ በሆነው ተክሌ ግሮሰሪ ውስጥ ተቀጥራ የምትሠራው ወጣት መቅደስ፣ ኃይለመድኅንን ለአራት ዓመት ያህል ታውቀዋለች፡፡ ‹‹ስሙ ኃይለመድኅን መሆኑን ያወቅነው ከሚዲያ ነው እንጂ እኛ ታዴ በሚል ስም ነው የምናውቀው፤›› ያለችው መቅደስ፣ ኃይለመድኅን ብዙ ጊዜ ቁርስ ለመመገብ ወደ ተክሌ ግሮሰሪ እንደሚመጣ ተናግራለች፡፡ እንቁላል ፍርፍር ወይም እንቁላላ በሥጋ አዘውትሮ ለቁርስ እንደሚመርጥ የምትናገረው መቅደስ፣ ኃይለመድኅን ዝምተኛና ብቸኛ ሰው እንደሆነ ታስረዳለች፡፡
ወደ ግሮሰሪው የሚመጣው ብቻውን እንደሆነና መጠጥ ሲጠጣ አይታው እንደማታውቅ ገልጻለች፡፡ ‹‹በጣም ሰላማዊ ሰው ነው፡፡ ምን ዓይነት ነገር እዚህ ውስጥ እንደከተተው እግዚአብሔር ይወቅ፤›› ብላ፣ ዓርብ ዕለት የወሰደውን የአንድ ጠርሙስ ጉደርና እሑድ ዕለት የወሰደውን ሁለት ጠርሙስ ማልታ (አልኮል የሌለው የሜታ ምርት) ሒሳብ እሑድ ከሰዓት በኋላ ሰጥቷት እንደሄደ በትካዜ ታስታውሳለች፡፡
በተክሌ ግሮሰሪ በአስተናጋጅነት ለሦስት ዓመት ያህል የሠራው ጐሳዬ የተባለው ወጣት፣ የኃይለመድኅን ሽርክ እንደሆነ በሠፈሩ ይነገራል፡፡ ጐሳዬ ኃይለመድኅንን የሚያውቀው በተክሌ ግሮሰሪ ተቀጥሮ ሲሠራ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ኃይለመድኅን ዕረፍት በሆነባቸው ቀናት በስልክ የሚፈልገውን ምግብ፣ ለስላሳ መጠጦች፣ የሞባይል ካርድ የመሳሰሉትን እንዲያመጣለት እንደሚያዘውና የጠየቀውን በፍጥነት እንደሚወስድለት ተናግሯል፡፡ 
‹‹ፀባዩ ይመቸኛል፡፡ በጣም ዝምተኛ ነው፡፡ ሲበዛ ጥሩ ሰው ነው፡፡ ከአፉ ክፉ ነገር አይወጣም፡፡ ከስንቱ ጋር በሒሳብ ስጨቃጨቅ እርሱ ግን አንድም ቀን ተከራክሮኝ አያውቅም፡፡ ያዘዘኝን እወስድለታለሁ ሒሳቡን አስቦ ከነጉርሻው ይሰጠኛል፡፡ አጋጣሚ ሳይከፍለኝ ወደ ሥራ ከሄደ ከበረራ ሲመለስ ራሱ ደውሎ ናና ሒሳብህን ውሰድ ይለኛል፤›› ያለው ጐሳዬ፣ ኃይለመድኅን ቤት ውስጥ ገብቶ እንደማያውቅ፣ የጠየቀውን ዕቃና ገንዘብ የሚለዋወጡት ቤቱ በር ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ኃይለመድኅንን ባገለገለገባቸው ሦስት ዓመታት አንድም ጊዜ ከሰው ጋር አይቶት እንደማያውቅ ጐሳዬ አስረድቷል፡፡
‹‹ዕረፍት ከሆነ ከቤቱ አይወጣም፡፡ ያዘዘኝን ላደርስ ቤቱ ስሄድ ፊልም ሲመለከት ነው የማገኘው፡፡ እቤቱ ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ  አይቼ አላውቅም፤›› ብሏል፡፡ ኃይለመድኅንን በፀባዩ በጣም እንደሚወደውና በገጠመው ነገር በጣም ማዘኑን የሚናገረው ጐሳዬ፣ በቅርቡ ነጭ መኪና መግዛቱን ተናግሯል፡፡ 
የኃይለመድኅን ጐረቤቶች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሰላምታ ያለፈ ከእነርሱ ጋር ቅርርብ የለውም፡፡ ይልቁንም ኃይለመድኅን በዕረፍቱ ቀናት (በረራ ሳይኖረው) ረዥም ጊዜ የሚያሳልፈው መሲ ቢዝነስ ሴንተር በተባለው ቤት ኢንተርኔት በመጠቀም እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
መሲ ቢዝነስ ሴንተር የሚገኘው በኮንዶሚኒየሙ ግቢ በውጪ በኩል ጥግ ላይ ነው፡፡ የቢዝነስ ሴንተሩ ባለቤት ወ/ሮ መሠረት ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡ መሠረት ኢንተርኔት ቤቱን ከከፈተች ሰባት ወር እንደሆናት፣ በዚህም ጊዜ ኃይለመድኅን ዋና ደንበኛዋ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ ‹‹ዕረፍት ከሆነ እኛ ጋር ይመጣል፡፡ ለረዥም ሰዓት ይቀመጣል፡፡ በኢንተርኔት የሚከታተለው የውጭ ፊልም አለ፡፡ አስቂኝ ፊልም ሳይሆን አይቀርም ፊልሙን እያየ ይስቃል፤›› ብላለች መሠረት፡፡ 
‹‹የሚመለከተው ነገር ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያለው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የሚቀመጥበት ቦታ ማንም ሰው ከኋላው ወይም በረንዳው ላይ እንኳ ሆኖ ሊመለከተው ይችላል፤›› የምትለው መሠረት፣ ኃይለመድኅን ዝምተኛና መልካም ፀባይ ያለው ሰው እንደሆነ ትመሰክራለች፡፡ 
ሳሚ ሕንፃ ፊት ለፊት ጫማ ከሚጠርጉት ሊስትሮዎች መካከል አንዱ የሆነው አሸናፊ በቀለ ኃይለመድኅን ደንበኛው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የ15 ዓመት ታዳጊ የሆነው አሸናፊ የኃይለመድኅን ጫማን ቀለም በቀባ ቁጥር ስድስት እስከ አሥር ብር እንደሚሰጠው ይናገራል፡፡ ክሬም ጫማ ለመቀባት የሚያስከፍለው ስድስት ብር ቢሆንም ኃይለመድኅን አሥር ብር እንደሚሰጠው በፈገግታ ያስታውሳል፡፡
የአካባቢው ሰዎች ኃይለመድኅንን የሚገልጹት በተመሳሳይ ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ ዝምተኛ፣ ብቸኛና ሰላማዊ ሰው ነው በማለት፡፡ ኃይለመድኅን የአዕምሮ ጤንነቱ እንደታወከ በሥነ አዕምሮ ሐኪሞች ማረጋገጥ ከተቻለ ከፍርድ ነፃ ሊወጣ እንደሚችል ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉ ድርጊቶችን በትክክል በአዕምሮ ጤና መታወክ የተፈጸሙ መሆኑን ፍርድ ቤትን ማሳመን የሕግ ባለሙያዎችን የሚፈትን ከባድ ሥራ እንደሆነ የሕግ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡ 
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በአውሮፕላን ጠለፋው ዙሪያ ባለፈው ማክሰኞ ከሰጡት መግለጫ ውጪ የምጨምረው የለም ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዝምታን መርጧል፡፡ 
አቶ ሬድዋን የረዳት አብራሪውን የአዕምሮ ጤንነት በተመለከተ ተጠይቀው አየር መንገዱ እስከሚያውቀው ድረስ ግለሰቡ ጤነኛ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አብራሪዎች በየጊዜው ሙሉ የጤና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ገልጸው፣ የምሥለ በረራ ሥልጠና በሚወስዱ ጊዜ ጭንቀትን (Stress) የመቋቋም ብቃታቸው ይታያል ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ የምናውቀው አቶ ኃይለመድኅን ብቁ (Qualified) አብራሪ መሆኑን ነው፤›› ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ባለበት ወቅት በተፈጠረ አንድ ክስተት ምክንያት የገነባው መልካም ስምና ዝና ሊናድ አይገባም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 8,000 ሠራተኞች ሲኖሩት፣ 651 አብራሪዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል 100 ያህሉ የውጭ ዜጐች ናቸው፡፡ ‹‹ስምንት ሺሕ ሠራተኞች ባሉበት ኩባንያ ውስጥ አንድ ሰው ባደረገው ድርጊት ሁሉም ነገር በዜሮ ሊባዛ አይችልም፣ አይሆንምም፤›› ብለዋል፡፡
Source: Reporter
 
በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ በሚገኘው 28 ተከሳሾች ላይ ለቀረበ የአቃቤ ህግ የቪዲዮ ማስረጃ አስተርጓሚ እንዲመድብ የታዘዘው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ ተግባራዊ ባለማድረጉ ዋና ዳይሬክተሩ ፍ/ቤት ታስረው እንዲቀርቡ ታዘዘ፡፡
በእነ አማን አሠፋ መዝገብ በሚገኙ የሽብር ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ህግ የሰው ምስክሮችንና በሺዎች የሚቆጠሩ የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍ/ቤቱ አቅርቦ ያጠናቀቀ ሲሆን በአረብኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች ለቀረቡት የቪድዮ ማስረጃዎች ኢሬቴድ አስተርጓሚ እንዲመድብ ከፍ/ቤቱ የተላለፈውን ትዕዛዝ ተግባራዊ አላደረገም ተብሏል፡፡ በዚህም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ ኪዳነማርያም ታስረው ፍ/ቤት እንዲቀርቡ ታዟል፡፡
ቀደም ሲል እነዚህን የሽብር ተጠርጣሪዎች አስመልክቶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ጅሃዳዊ ሃረካት” የሚል ዶክመንተሪ ፊልም ተዘጋጅቶ መሰራጨቱ የሚታወስ ሲሆን አቃቤ ህግም በክስ ማመልከቻው፣ ተጠርጣሪዎች የአልቃይዳ ህዋስ ሆነው በአለማቀፍ የሽብር መዋቅር ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ማመልከቱ ይታወሳል፡፡
Source: Addis Admass
 
“የተሳፋሪው ፍላጎት የሆነ መሬት ላይ ማረፍ ብቻ  ነበር”
በሃዋሳ ከተማ በተለምዶ ኬሮ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተወልዶ ያደገው ወጣት ምህረቱ ገብሬ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀድሞው ሀዋሳ ኮምቦኒ የመጀመርያ ደረጃ ት/ቤት ነው የተከታተለው። የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያና የመሰናዶ ትምህርቱንም በቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ት/ቤት አጠናቋል። ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2001 ዓ.ም በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላም፤ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት አገልግሏል፡፡ በመቀጠልም ነጻ የትምህርት ዕድል በማግኘት፣ ወደ ጣሊያን አምርቶ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡

በቅርቡ ለእረፍት ወደ አገሩ የመጣውና በሃዋሳ ቆይቶ ወደ ጣሊያን ለመመለስ አውሮፕላን የተሳፈረው ምህረቱ፣ ባለፈው ሰኞ በረዳት አብራሪው ተጠልፎ ጄኔቭ እንዲያርፍ በተደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩት 200 ገደማ ተሳፋሪዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በጣሊያን የሚገኘው ምህረቱ፣ የጠለፋውን አጋጣሚ በተመለከተ ጋዜጠኛ አንተነህ  ይግዛው በኢ-ሜይል ለላከለት ጥያቄዎች የሰጠውን ምላሽ  እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል፡፡

የጉዞው አጀማመር ምን ይመስል ነበር?
አርፍዶ ወደ አውሮፕላን ጣቢያ መምጣት የሚያደርሰውን ጣጣ ስለማውቀው፣ አውሮፕላኑ ከሚነሳበት 50 ደቂቃ ያህል ቀድሜ ነበር የተገኘሁት፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ማለት ነው፡፡ ያው ጉዞው ሲጀመር እንደሌላው ጊዜ ሁሉ ስርአቱን የጠበቀና ሰላማዊ ነበር።  አውሮፕላኑ ከበራራ ሰዓቱ ሰባት ደቂቃ ያህል ዘግይቶ ነበር የተነሳው።
አውሮፕላኑ ውስጥ አቀማመጥህ እንዴት ነበር? የት አካባቢ ነው የተቀመጥከው?
የመቀመጫዬ ቁጥር 27F ነበር። የተሳፈርንበት ቦይንግ 767 በርዝመቱ ትይዩ 7 የመቀመጫ መደዳዎች አሉት። ሁለት ሁለት መደዳዎች በሁለቱም ጥጎች እና ሶስት መደዳዎች መሃል ላይ። እኔ የተቀመጥኩት ከመሃል ሶስቱ መደዳዎች የመሃለኛዋ ወንበር ላይ ነበር። ከበስተግራዬ ያለችው ወንበር ላይ የተቀመጡት ሪካርዶ የተባሉ የ85 አመት የዕድሜ ባለጸጋ ጣሊያናዊ ነበሩ፡፡ በቀኜ በኩል እንዲሁ በግምት በስድሳዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌላ ጣሊያናዊ ተቀምጠው ነበር፡፡ ተዋውቀን ነበር፣ አሁን ግን ዘንግቼዋለሁ። ኢትዮጵያን ተዟዙረው እንደጎበኟት እያጫወቱኝ ነው ጉዞውን የጀመርነው፡፡
ጉዞውስ  እንዴት ነበር?
እንደማስታውሰው ጉዞው ሲጀመር ሰላማዊ ነበር። ከፓይለቱ ጋርም ግንኙነት (ኮሙኒኬሽን)  ነበረን፡፡ እኔ ድካም ስለተሰማኝ ወዲያው አሸለብኩ፡፡ በረራው ከተጀመረ በግምት ከ1 ሰዓት በኋላ የሱዳን አየር ክልል ውስጥ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ. . . መብራት ሲበራ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ የምግብ ሰዓት መድረሱ ገብቶኛል። ወደ ፊት አሻግሬ ሳይ ሆስተሶቹ እያስተናገዱ ከእኔ ፊት 4ኛ ይሁን 5ኛ ረድፍ ደርሰዋል። ሁሉም ተዘገጃጅቶ እየተጠባበቀ ነበር። በዚህ መሃል የፕሌኑ ፍጥነት ሲጨምር ይታወቀኛል፡፡ ከፍታዉም ሲጨምር በጆሮዬ ላይ በሚሰማኝ ስሜት አስተዋልኩ። በተሳፋሪዎች ፊት ላይ የመረበሽ ስሜት ሲፈጠር አየሁ። እኛ  ኢኮኖሚ ክላስ ስለነበርን ከፊት ምን እየተካሄደ እንደነበር አላየንም። በኋላ ስሰማ ከፊት የነበሩትም የቢዝነስ ክላስ ተሳፋሪዎች ምንም መረጃ አልነበራቸውም፡፡
ከዚያም በድምጽ ማጉያው የሆነ ድምጽ ተሰማ፡፡ የረዳት አብራሪው ድምጽ ነበር።
“ተሳፋሪዎች ከ 12 ደቂቃዎች በኋላ ሚላን እናርፋለን” አለ ረዳት አብራሪው፡፡ ጥቂት ቆይቶም፣ “ስለተፈጠሩ አንዳንድ መጉላላቶች ይቅርታ እንጠይቃለን” ሲል አከለ-በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ። የረዳት አብራሪውን ንግግር ተከትሎ የተወሰኑ ተሳፋሪዎች ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ አንዳንዶችም ጮክ ብለው ሲያወሩ ይሰሙ ነበር፡፡ ከኔ በስተግራ በኩል ሶስት አራት መደዳዎችን አልፎ ከፊቴ ተቀምጦ የነበረ አንድ ወፍራም ሰው፣ በጣሊያንኛ ቆጣ ብሎ እየጮኸ ተናገረ - “መጀመሪያ ሚላን ሳይሆን ሮም ነው ማረፍ ያለብን ፣ ወደ ሮም ውሰዱን!” በማለት። ሌሎችም የሰውየውን ሃሳብ ደገፉ፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ተሳፋሪ ወደ ሮም ነበር የሚጓዘው። ረዳት አብራሪው ሚላን ላይ እንደምናርፍ መናገሩ ብዙዎችን አበሳጭቶ ነበር፡፡
እውነቱን ለመናገር፣ እኔ ግን ሚላን እንደምናርፍ ስሰማ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔ ሚላን ወራጅ ነኝ፡፡ ረዳት አብራሪው የነገረን አስራ ሁለቱ ደቂቃዎች እየተገባደዱ መሆናቸው ሲገባኝ፣ ከአውሮፕላኑ ለመውረድ መዘገጃጀትና ጓዜን መሸካከፍ ሁሉ ጀመርኩ። ሆኖም  አስራ ሁለቱ ደቂቃዎች አልፈውም አውሮፕላኑ አላረፈም፡፡ ካሁን አሁን ሚላን አውሮፕላን ማረፊያ ደረስን እያልን ስንጠባበቅ፣ ሌላ አስራ ሁለት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ አሁንም ሌላ አስራ ሁለት ደቂቃዎች---
ተሳፋሪው ሁሉ ግራ በመጋባት ሰዓቱን ደጋግሞ መመልከትና እርስ በርስ በጥርጣሬ መተያየት ጀመረ። ከአስራ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሚላን ላይ ያርፋል የተባለው አውሮፕላን፣ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በአየር ላይ ቆየ፡፡ የሚገርመው ያን ያህል ጊዜ አየር ላይ መቆየቱ ብቻ አይደለም፡፡ አበራረሩ የተለየ ነበር፡፡ አንዴ ፍጥነቱን ጨምሮ ይከንፋል፣ ከዚያ ደግሞ ፍጥነቱን ይቀንስና ተረጋግቶ ይበራል፡፡ እንደገና ይፈጥናል፣ እንደገና ይረጋጋል፡፡ ግራ ገብቶን እያለን፣ ከመቅጽበት አውሮፕላኑ ማረፊያው ላይ ደርሶ ማኮብኮብ ጀመረ፡፡ ያንን ያህል ግዙፍ አውሮፕላን፣ በዚያች ጠባብ ቦታ ላይ ያለችግር ማሳረፍ መቻሉ፣ የረዳት አብራሪውን ብቃት ያሳያል፡፡ ለማንኛውም አውሮፕላኑ በሰላም አረፈና እኛም እፎይ አልን፡፡
አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ የተሳፋሪዎች ስሜት ምን ይመስል ነበር?
የሚገርመው ነገር፣ አውሮፕላኑ እንዳረፈ በተሳፋሪው ፊት ላይ ከታየው ደስታና እፎይታ በተጨማሪ፣ ተሳፋሪው ለረዳት አብራሪው የሰጠው አድናቆት ነበር፡፡ አብዛኛው ተሳፋሪ ስለረዳት አብራሪው ችሎታ ነበር ተደንቆ የሚያወራው፡፡ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተውጠው፣ ለረዳት አብራሪው ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባና በፉጨት የገለፁም ነበሩ፡፡ እኔም በደመነፍስ ሳጨበጭብ ነበር፡፡ ሚላን ምድር ላይ በሰላም እንዲያሳርፈኝ ለፈጣሪዬ ያደረስኩትን ጸሎት የማውቀው እኔ ነኝ፡፡
ሚላን እንዳረፋችሁ ነበር የምታውቁት ማለት ነው?
የሚገርመው እኮ እሱ ነው!... አውሮፕላኑ መሬት ከነካ በኋላ ሁሉ፣ ተሳፋሪው በሙሉ ጣሊያን ሚላን እንዳረፈ ነበር የሚያውቀው፡፡ ሚላን እንደምናርፍ ነው ረዳት አብራሪው የነገረን፡፡ ትኬት ከፍለን የተሳፈርነውም ወደ ጣሊያን እንጂ ወደ ስዊዘርላንድ ለመሄድ አልነበረም። በዚህ ቅጽበት ጄኔቭ የምትባል ከተማ በምን ተአምር እንሄዳለን ብለን እናስብ?
ጄኔቭ መሆናችሁን ያወቃችሁት እንዴት ነው?
አውሮፕላኑ በሰላም ካረፈ በኋላ ተሳፋሪው ከጭንቀቱ ተገላግሎ መረጋጋት ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ሞባይል ስልኮቻቸውን አውጥተው መነካካት ያዙ። በሞባይላቸው የኢንተርኔት መስመር በመጠቀም ጎግል ማፕ የተሰኘውን የአገራትና የከተሞች ካርታ የሚያሳይ ድረገጽ፣ ጂ ፒ ኤስ ከሚባለው አቅጣጫ ጠቋሚ ቴክኖሎጂ ጋር አያይዘው ሲመለከቱ፣ ፊታቸው ላይ ድንገተኛ መደናገር ሲፈጠር አየሁ፡፡ አንዱ ተሳፋሪ ሞባይሉ ላይ ያየውን መረጃ በመጠራጠር፣ የሌላኛውን ሞባይል ማየት ጀመረ፡፡ “የት ነው ያለነው?” ለሚለው ጥያቄ እርግጠኛ የሆነ መልስ የሚሰጥ ጠፋ፡፡ ግማሹ “ ኦስትሪያ ነን!” ሲል፣ ገሚሱ “የለም ፈረንሳይ ነን!” ብሎ ይመልሳል፡፡ አንዳንዱ “ጀርመን ውስጥ ነው የምንገኘው!” ይላል፡፡ ሌላው “ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ነው ያረፍነው!” እያለ ይናገራል፡፡ ጭንቀትና ውጥረት የፈጠረው መደናገር ሊሆን እንደሚችል ያሰብኩት በኋላ ነው፡፡
 ጄኔቭ ማረፋችሁንና አውሮፕላኑ መጠለፉን ያወቃችሁት እንዴት ነበር?
እያንዳንዱ ተሳፋሪ አውሮፕላኑ ያረፈበትን አገርና ከተማ በተመለከተ የየራሱን መላምት እየሰነዘረ ግራ ተጋብቶ ጥቂት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ በዚህ መሃል ነው፣ ድንገት የአውሮፕላኑን ዋና አብራሪ ድምጽ የሰማነው። በረራው ከተጀመረ አንስቶ የዋና አብራሪውን ድምጽ ስንሰማ ለመጀመሪያ ጊዜያችን ነበር፡፡ ዋና አብራሪው በጣሊያንኛ ቋንቋ ነበር የሚያወሩት፡፡ በጣሊያን ቆይታዬ የቀሰምኳት ቋንቋ ብዙም የምታወላዳ አልነበረችምና፣ ደቂቃዎችን ከፈጀው የአብራሪው ንግግር የተወሰነችዋን ተረድቼ፣ ቀሪውን ከጎኔ ከተቀመጡት ጣሊያናውያን ጠይቄ ለመረዳት ሞከርኩ፡፡
አብራሪው  ወደመጸዳጃ ቤት ሲወጡ ረዳት አብራሪው በር እንደዘጋባቸው፤ አውሮፕላኑን ለሰዓታት ሲያበር የቆየው ረዳት አብራሪው እንደነበር፤ አውሮፕላኑ ያረፈው ጄኔቭ መሆኑን፤ በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን መግለጻቸውን እንዲሁም እያንዳንዱ ተሳፋሪ የስዊዘርላንድ ፖሊሶች ለሚያደርጉት ምርመራ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ነገሩኝ፡፡ ተሳፋሪው ስለ ጠለፋው ያወቀው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
ተጠልፋችሁ ያላሰባችሁት ቦታ እንዳረፋችሁ ስታውቁ ምን ተሰማችሁ?
እውነቱን ለመናገር በወቅቱ የሁሉም ተሳፋሪ ጸሎትና ምኞት በረራው በሰላም መጠናቀቁና አውሮፕላኑ አደጋ ሳያጋጥመው ማረፉ ብቻ ነበር፡፡ የተሳፋሪው ፍላጎት የትም ይሁን የት፣ ብቻ የሆነ መሬት ላይ ማረፍና ከጭንቀት መገላገል ነበር፡፡ አስበው እስኪ… ከአብራሪውም ሆነ ከሆስተሶቹ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት በሌለበት አደናጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ለሰዓታት የበረርነው፡፡ ከዚያ ደግሞ… ሮም የማረፍ ዕቅዱ ተሰርዞ፣ ከ12 ደቂቃዎች በኋላ ሚላን እንደምናርፍ ድንገት ተነገረን፡፡ ይሁን ብለን ተቀብለን፣ አስራ ሁለቱን ደቂቃ በጉጉት ስንጠባበቅ ደግሞ፣ ለተጨማሪ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜ በረራው ቀጠለ፡፡ በዚያ ላይ በረራው ጤነኛ አልነበረም፡፡ አንዴ የሚፈጥን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚረጋጋ ምቾት የማይሰጥ በረራ ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ተሳፋሪ፣ የትም ቢሆን ማረፍን እንጂ፣ማረፊያ ቦታውን አይመርጥም፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ተሳፋሪዎች ጉዳዩን ያወቅነው፣ ጠለፋው ከተጠናቀቀና አውሮፕላኑ ጄኔቭ ውስጥ በሰላም ካረፈ በኋላ ዋና አብራሪው ሲነግሩን በመሆኑ እምብዛም አልተደናገጥንም፡፡
ከአውሮፕላኑ ስትወርዱ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አውሮፕላኑ ጄኔቭ ካረፈ በኋላ በግምት ለአንድ ሰአት ያህል በሩ ሳይከፈት ቆሞ ቆየ፡፡ ዋና አብራሪው ሁሉንም ነገር በግልጽ ከነገሩን በኋላ፣ ከእግር ጣታቸው እስከ ራስ ጸጉራቸው የብረት ጭንብል የለበሱ ሰዎች፣ በሩን በርግደው በፍጥነት ወደ ውስጥ ገቡ። አገባባቸውና መላ ሁኔታቸው አክሽን ፊልም የሚሰሩ ነበር የሚመስሉት፡፡ ሁኔታው እጅግ ያስጨንቅ ነበር፡፡ በመካከል አንደኛው ፖሊስ በእጁ በያዛት አነስተኛ የድምጽ ማጉያ ፈረንሳይኛ በሚመስል እንግሊዝኛ መናገር ጀመረ።
“ዚስ ኢዝ ኤ ፖሊስ ኦፔሬሾን። ዶንት ሙቭ!... ፑት ዩር ሃንድስ ኦን ዩር ሄድ!... ዶንት ሜክ ሙቪ ባይ ሞባይል (በሞባይል አትቅረጹ ማለቱ ነው)” ሲል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ሁሉም እጆቹን አናቱ ላይ ጭኖ ድምጹንም አጥፍቶ አቀረቀረ፡፡ ተሳፋሪው በፖሊሶቹ መሪነት አንድ በአንድ ከአውሮፕላኑ እየወረደ፣ ሁለት ሁለት ጊዜ ተበርብሮ ተፈተሸ፡፡
ፍተሻው እንደተጠናቀቀም በትላልቅ ሽንጣም አውቶብሶች እየጫኑ ወደ ተርሚናሉ ወሰዱን፡፡ ተርሚናሉ ላይ ስንደርስ የሚገርም አቀባበል ተደረገልን፡፡ የምንበላው ቁርስና ሻይ ቡና እንዲሁም ለብርዱ ብርድልብስ ተዘጋጅቶ ጠበቀን፡፡ የህክምና ባለሙያዎችና የስነልቦና ባለሙያዎች እርዳታ ሊሰጡን እየተጠባበቁ ነበር፡፡ አስገራሚ አቀባበል ነው የተደረገልን።
ኢትዮጵያውያንስ አላገኛችሁም?
ተርሚናሉ ዉስጥ ገብተን ትንሽ እንደቆየን አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ እኛ ሲመጣ ተመለከትን፡፡ ለጊዜው ስሙ ትዝ አይለኝም። ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደመጣ ነገረንና ስለሁኔታው ጠየቀን። “አይዟችሁ!... ደርሰንላችኋል!...” የሚል መንፈስ ያለው ማበረታቻ ሰጠን፡፡ ከዚያም የግል ሞባይሉን ከኪሱ አውጥቶ አገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቻችን ጋ ደውለን ደህንነታችንን እንድናረጋግጥ ራሱ እየደወለ ያገናኘን ጀመር፡፡ 
በዚህ ጊዜ ነው፣ በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የመጡት፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበርን ኢትዮጵያውያንን አነጋግረው አረጋጉን፡፡ በስተመጨረሻም ከተርሚናሉ እንዲወጡ ስለታዘዙ የማስታወሻ ፎቶግራፍ አብረውን ተነሱና ጉዳያችንን በቅርብ እንደሚከታተሉ ነግረውን አበረታቱንና ሄዱ፡፡ ሌሎች ሁለት የኤምባሲው ባልደረቦችም፣የሚፈቀድላቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ እየተገኙ ድጋፍ በማድረግ እስከመጨረሻው አብረዉን ነበሩ።
በእለቱ ስለተከሰተው ሁኔታ ምን ትላለህ?
እናቴ እንደነገረችኝ፣ በህፃንነቴ የወራት ዕድሜ ላይ እያለሁ፣ የሆነ ቀን ከታላቅ ወንድሜ መላኩ ገብሬ ጋር ከጎማ ላስቲክ የተሰራ አልጋ ላይ ተኝቼ ነበር። ቡና ስታፈላ ምንጊዜም ዕጣን ማጨስ እማትዘነጋው እናታችን፣ ያጨሰችዉን እጣን እኛ የተኛንበት አልጋ አጠገብ አስቀምጣው ኖሮ፣ እሷ ጎረቤት ደርሳ ስትመለስ ቤቱ በጭስ ተሸፍኖ ጨልሞ ጠበቃት። ጩኸቷን ለቀቀችው። ጩኸት ሰምቶ የመጣ ጎረቤት ነው አሉ ፈልጎ አግኝቶኝ በመስኮት ወደ ውጭ የወረወረኝ። ምህረቱ የተባልኩትም በዚያ ምክንያት ነው። እንዳጋጣሚ እሳቱ ቀድሞ የተያያዘው ወንድሜ በተኛበት በኩል ስለነበር እሱን ማትረፍ አልተቻለም።
የፈጣሪ ምህረት ዛሬም አልተለየኝም፡፡ በአውሮፕላኑ ላይ ሊደርስ ከሚችለው አሰቃቂ አደጋ አትርፎኛል። እንደትላንትናው ሁሉ ነገዬም በፈጣሪ እጅ እንደሆነች አምናለሁ። እርሱ ይሁን ያለው ሁሉ መልካም ነው። ቸርነቱ አይለየኝና ፍቃዱ ሆኖ ለነገ ካበቃኝ ለልጆቼ የምነግረው ተጨማሪ ታሪክ አግኝቻለሁ።
ደህና ነኝ እንኳን ብላት የማታምነኝ እናቴ ብርሃነማርያም ኪአን፣ እጮኛዬ ዮዲት ቦርሳሞን፣ ወንድሞቼን፣ ብቸኛዋን እህቴን፣ አክስቶቼን ከነቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቼን፣ስለደህንነቴ የሚጨነቁልኝን ሁሉ ደህና መሆኔን ንገርልኝ። ከሁሉ አስቀድሞ ስለሆነውም ስለሚሆነዉም ክብር ሁሉ የእርሱ ነውና ፈጣሪ የሚገባዉን ክብር እና ምስጋና ይውሰድ።
Source: Addis Admass
 
ኢትዮጵያ ዉስጥ የመሬትና ዉሃ ቅርምት ማኅበረሰቡን እየጎዳ እንደሚገኝ ዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች ሂዉማን ራይትስ ዎች አመለከተ። ድርጅቱ ይህን አመልክቶ ባወጣዉ ዘገባ በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያና ኬንያ ዉስጥ 500,000 አርብቶ አደሮች ለችግር መጋለጣቸዉን ገልጿል። 
ሂዉማን ራይትስ ዎች፤ ኢትዮጵያ፤ የመሬትና ዉሃ ቅርምት ማኅበረሰቦችን ጎዳ በሚል ዛሬ ባወጣዉ ዘገባ፤ አዳዲስ ከሳተላይት የተገኙ ምስሎች በታችኛዉ ኦሞ ሸለቆ አካባቢ ነባር ማኅበረሰቦች ይጠቀሙበት የነበረዉን መሬት ለስኳር ልማት በስፋት መመንጠሩን ማሳየታቸዉን አመልክቷል። ላለፉት አምስት ወራትም 7,000 የሚሆኑ የቦዲ ጎሳ አባላት ጋ በቂ ምክክር ሳይደረግ ተግባሩ መከናወኑን ዘርዝሯል። የድርጅቱ የአፍሪቃ ጉዳይ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮ፤ ድርጅታቸዉ በUNESCO በዓለም ቅርስነት
በተመዘገበዉ አካባቢ ለበርካታ ዓመታት የሚከናወነዉን እንደሚከታተል በማመልከት፤
«የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ግድቦችን በኦሞ ወንዝ አካባቢ በመገንባት ላይ ይገኛል። የወንዙ ዉሃም ለስኳር ተክሉ ወደግድቦች ለመስኖ ተቀልሷል። እናም ባጠቃላይ እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች በኦሞ ሸለቆ በሚገኙ ነባር ኗሪዎች ህይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አስከትለዋል። እዚያ ወደሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ይኖራሉ። አብዛኞቹም እዚያ መሬታቸዉ ሲመነጠር አይተዋል፤ ወደሌላ ስፍራ አንዳንዴም ወደመንደሮች ተወስደዉ በግዳጅ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። እናም የኑሯቸዉ ሁኔታ እጅግ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነዉ።» 
ዘገባዉ እንደሚለዉ የመሬት ምንጠራዉ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሞ ሸለቆ ያቀደዉ ሰፊ የልማት ተግባር አካል ነዉ። የግድብ ግንባታዉን ጨምሮ፣ የስኳር ተክል ልማቱም ሆነ ለገበያ የሚዉል የእርሻ ምርት ማምረቻዉ በኦሞ ወንዝ የሚገኘዉን አብዛኛዉን ዉሃ ይጠቀማል የሚል ስጋትም አለዉ። ይህም በአካባቢዉ በኢትዮጵያም ሆነ በጎረቤት ኬንያ የሚገኙና ዉሃዉን ለኑሯቸዉ የሚጠቀሙ ወገኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚጎዳ አመልክቷል። ዘገባዉ የኢትዮጵያ መንግስት መሬቱንና የተፈጥሮ ሃብቱን ማልማት እንደሚችል ያ ግን በአካባቢዉ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን መብት በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ያስገነዝባል። እንዲህ ያሉ የልማት ተግባራት ሲከናወኑ የሚከተል የጎንዮሽ ችግር አይጠፋም እና ይህ እንዴት ይታያል ለሚለዉ፤ ሌቭኮቭ ችግሩ የሚከናወንበት መንገድ ነዉ፤ ነዉ የሚሉት፤
«እርግጥ ነዉ የኢትዮጵያ መንግስት እንደማንኛዉ መንግስት ለኤኮኖሚ እድገት ዉሃዉንም ሆነ የተፈጥሮ ሃብቱን ማልማት ይችላል። ችግሩ የሚከወንበት መንገድ ነዉ። በኦሞ ሸለቆ የሚገኙ አብዛኞቹ ማኅበረሰቦችም በአካባቢዉ እንደሚገኝ ነባርና ይህን መሬት ለበርካታ መቶ ዓመታት ሲጠቀም እንደኖረ ዜጋ መብት አላቸዉ። የሚያሳዝነዉ ነገር በመከናወን ላይ ያለዉ ሂደት የእነሱን መብት ከግምት ያላስገባ መሆኑ ነዉ። አብዛኞቹ ሰዎች አልተጠየቁም፤ ካሳ አላገኙም፤ የኗኗራቸዉ ሁኔታ ዳግም በማይመለስ መልኩ በፍጥነት ሲለወጥ ነዉ የሚያስተዉሉት።»
ከዚህም ሌላ ይኸዉ ምክንያት ጎረቤት ኬንያ ዉስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦችንም ህይወት እየጎዳ እንደሚገኝም አመልክተዋል። የኦሞ ወንዝ የቱርካና ሃይቅ ዋነኛ ምንጭ መሆኑን በመግለፅም ወደ300,000 የሚሆኑ እና ኑሯቸዉ በቱርካና ሃይቅ ላይ የተመሠረተ ወገኖች መጎዳታቸዉን ዘርዝረዋል። ሂዉማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይህን ጉዳይ ደጋግመዉ ማንሳታቸዉና ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ይታያል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ዘገባዎቹ ከእዉነት የራቁና የተዛቡ መሆናቸዉን ነዉ የሚገልፀዉ። የልማት ተግባራቱን የሚያከናዉነዉ የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል መሆኑንም ይናገራል። ሌስሊ ለፍኮዉ ማኅበረሰቡም እንዲህ ባሉ ተግባራት ሃሳቡን የመስጠት መብቱ መከበር አለበት ባይ ናቸዉ፤
«ችግሩ እንዲህ ባሉ ልማቶች ማኅበረሰቡም የራሱን ሃሳብ የመስጠት መብት አለዉ፤ መንግስት የእነዚህ በሁኔታዉ በጣም የሚነኩ እና የሚጎዱ ወገኖችን አስተያየት፣ ሃሳብና ግብዓት ሙሉ በሙሉ ይህን ችላ ብሏል፤ ይህ ደግሞ ከባድ ችግር ነዉ። ሰዎች መሬታቸዉ ሲነጠቅ፤ ሌላ አዲስ ስፍራ ለመስፈር ሲገደዱ እንዴት ህይወታቸዉን ማቆየት እንደሚችሉ ይቸገራሉ። ምክንያቱም በአኗኗራቸዉ ላይ ፍፁም ለዉጥ ነዉ። ለዚህ ደግሞ አልተዘጋጁም።» 
እናም ሁኔታዉ በከፍተኛ ግፊት በአካባቢዉ በሚኖሩ ወገኞች ላይ መጫኑንም አያይዘዉ ጠቅሰዋል። አንዳንድ ዘገባዎች ኢትዮጵያ አፍሪቃ ዉስጥ ከሚገኙ የዓለማችን 10 ድሃ ሃገራት አንዷ መሆኗን ይጠቅሳሉ። መንግስት የሚያከናዉናቸዉ የልማት እንቅስቃሴዎች ሀገሪቱን ወደመካከለኛ ገቢ ወዳላቸዉ ሃገራት ተርታ ያደርሳሉ ባይ ነዉ። እንዲህ ያሉት ተግባራት የጎንዮሽ ችግር ማስከተላቸዉ እየታየ ከሆነ ድርጅቱ የሚያቀርበዉን ዘገባ መንግስት ከግምት እንዲያስገባ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? ሌስሊ ሌፍኮዉ፤
«ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ማለቴ በዘገባችን ምን ለማቅረብ እንደፈለግን የተሻለ ግንዛቤ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ልማትንም ለማከናወን የተሻለ መንገድ መኖሩን ይገነዘባሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በመንግስት አስተዳደር ዉስጥ የሚገኙ ሰዎችም ዘገባዎቹን በጥንቃቄ በመመልከትና በማንበብ ለሁሉም የሚጠቅም ልማትን ለማከናወን አቅጣጫቸዉን ይለዉጣሉ ብዬ በጣም ተስፋ አደርጋለሁ። በተለይ በፕሮጀክቱ ኑሯቸዉ በቀጥታ ተፅዕኖ የሚያርፍበትን ወገኖች።» 
Source: DW
 

February 18, 2014 (KHARTOUM) –Sudanese foreign minister Ali Karti has criticised Egypt for its handling of a dispute involving the construction of a massive dam project in Ethiopia, which it has vehemently opposed over concerns it could disrupt water flows from the Nile river.
Karti said Egypt was further inflaming the situation by making critical comments in the media, adding that Sudan would continue its efforts to bridge the gap between the two countries.
“The position of Sudan is clear and we have already called on Egyptian officials to take advantage of the central role that Sudan could play regarding the crisis, but the arrogance
of the previous government did not allow them to accept this idea,” he said.
“If there is a room for a role that Sudan can play then the atmosphere must be clear away from the tensions and the cries over the media that do more harm than good,” he added.
Karti and Sudanese president Omer Hassan al-Bashir returned home from Ethiopia on Tuesday from Ethiopia, where they were participating in celebrations marking the 39th anniversary of the establishment of the Tigrayan People’s Liberation Front (TPLF). Sudan played a key role in supporting the Ethiopian rebel group, who managed to bring down the regime of Mengistu Haile Mariam in 1991.
Bashir also held talks with Ethiopia’s prime minister Haile-Mariam Desalegn on the sidelines of the events, which Karti said addressed ways to strengthen bilateral trade to serve their countries’ interests.
Speaking to reporters at Khartoum airport following his return, Karti said Ethiopia and Sudan had agreed to open border crossings and activate existing economic and trade committees between the two countries.
He denied that Sudan is taking sides in the dispute over the Ethiopian Grand Renaissance Dam (EGRD) because of it has joint interests in both nations.
Egypt fears that the $4.6 billion hydropower plant will diminish its share of the river’s water flows, arguing its historic water rights must be maintained.
Ethiopia is the source of about 85% of the Nile’s water, mainly through rainfall in its highlands, with over 90% of Egyptians relying on water from the Nile’s flows.
In June, a panel of international experts tasked with studying the impacts of the Ethiopian dam on lower riparian countries, including Sudan and Egypt, found that the dam project will not cause significant harm to either country.
Cairo remains unconvinced and has sought further studies and consultation with Khartoum and Addis Ababa.
Sudan angered its Egyptian neighbour to the north by accepting the final findings and offering to send experts and technicians to help in the dam’s construction, a move welcomed by Ethiopia.
The Sudanese foreign minister is expected to travel to Cairo in the coming days, local media have reported.
 Source: ST

-  መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጠው ይፈልጋል:
ባለፈው እሑድ ሌሊት 6፡30 ሰዓት ከአዲስ አበባ ወደ ሮም መብረር የጀመረውን የበረራ ቁጥሩ ‹‹ET 702›› የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን የጠለፈው ረዳት አብራሪው ኃይለመድኅን አበራ ተገኝ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ጠለፋውን ፈጸመ የተባለው ረዳት አብራሪ ቤተሰቦች መሆናቸውን የሚናገሩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኃይለመድኅን ላይ ያልተለመዱ ባህሪዎችን መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡
ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ደግሞ ግለሰቡ በተለያዩ ጊዜያት የዲስፒሊን ችግሮች ቢኖሩበትም፣ ብቃት ያለው አብራሪ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ባለፈው ሰኞ ከቀትር በኋላ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚነስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ግለሰቡ ጠለፋውን ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው እንቆቅልሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንድ ሰው በጠለፋ ወንጀል ከተሰማራ ቢያንስ 20 ዓመት ነው የሚፈረድበት፡፡ ከ20 ዓመት በኋላ ምን እንደሚያትርፍ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ምን ዓይነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደገፉት ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን የ31 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ በአየር መንገዱ ለአምስት ዓመታት ያገለገለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሬድዋን፣ በግለሰቡ የግል ሕይወት ዙሪያ በምርመራ የተደረሰበት መረጃ በአሁኑ ወቅት እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የረዳት አብራሪውን የግል ሕይወት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ ለጤንነት የማያሰጋ ሁኔታ ነበር ወይ የሚል መረጃም የለም፤›› ብለዋል፡፡
በበረራ ኢንዱስትሪ ውስጥ የበረራ ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አየር መንገዶች የበረራ ሠራተኞቻቸውን ጤንነት በየጊዜው እንደሚከታተሉ ለበረራ ኢንዱስትሪው ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ፡፡ ሙሉና ጥልቅ የሆነ የጤና ምርምራ በየስድስት ወራት በበረራ ሠሪተኞች ላይ እንደሚደረግ፣ ድንገተኛ የጤነንት ምርመራ ደግሞ በማንኛውም የበረራ ሠራተኛ ላይ በድንገት ሊደረግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አውሮፕላኑን ጠለፈ በተባለው ረዳት አብራሪ ላይ የተደረገ የቅርብ ጊዜ የጤንነት ምርመራ ውጤት መረጃዎች ምን እንደሚሉ የተጠየቁት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹አየር መንገዱ እስከሚያውቀው ድረስ የተሟላ ጤንነት እንደነበረው ነው፤›› ብለዋል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ ያነጋገራቸው የረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን አጐት መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አለሙ አስማማው የተባሉ ግለሰብ፣ ‹‹ኃይለመድኅን ከቅርብ ወራት ወዲህ በሌላ አንድ አጐቱ ድንገተኛ ሞት ምክንያት ጭንቀት ውስጥ እንደገባ አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ኃይለመድኅን ዓለም አቀፍ በረራዎች ባሉበት ጊዜያት ሁሉ ጉዞ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ለቅርብ ቤተሰቦቹ ይደውል ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መደወል ከማቆሙም በላይ፣ ከቤተሰቦቹም ራሱን እያራቀና አያገለለ መጥቷል፤›› ሲሉ አቶ አለሙ አስረድተዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብሮት መማሩን ለሪፖርተር የገለጸ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ አንድ ሰው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባህር ዳር ጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማሩንና በ1992 ዓ.ም. ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
በትምህርቱ ጥሩ ውጤት በማምጣትም አዲስ አበባ አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ እንደነበር የሚያስታውሰው ይህ ግለሰብ፣ የሥነ ሕንፃ ትምህርት መማር መጀመሩን ነገር ግን ስለማጠናቀቁ እርግጠኛ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓይለትነት ትምህርት እየወሰደ በነበረበት ወቅት ከመምህሩ ትዕዛዝ ውጪ የመለማመጃ አውሮፕላን በማብረሩ የዲሲፕሊን ዕርምጃ ተወስዶበት ነበር፤›› ሲል አስታውሷል፡፡ ኃይለመድኅን የተወለደው ባህር ዳር ሲሆን፣ አባትና እናቱ እዚያ እንደሚኖሩ አስረድቷል፡፡
ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርበት ያላቸው በበኩላቸው ኃይለመድኅን ‹‹በጣም ጐበዝና ተስፋ የሚጣልበት ረዳት አብሪራ ነው፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡
ጣሊያናዊ ዜግነት ያላቸው ዋና አብራሪና ረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን ባለፈው እሑድ ሌሊት የበረራ ቁጥሩ ‹‹ET 702›› የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ቦይንግ 767 አውሮፕላን በማብረር ከ200 በላይ የተለያዩ አገር መንገደኞችን ሮም የማድረስ ኃላፊነትን ከአየር መንገዱ ተረክበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ አብራሪዎች በበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል (ኮክፒት) ውስጥ የጋራ ቆይታ ያደረጉት የሚያበሩት አውሮፕላን የሱዳን አየር ክልል ውስጥ እስከገባበት ጊዜ ድረስ ብቻ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡
አውሮፕላኑ የሱዳን አየር ክልል ውስጥ በገባበት ወቅት ዋናው አብራሪው መፀጻጃ ቤት ለመሄድ ከበረራ ክፍሉ መውጣታቸውን፣ በዚሁ ወቀትም ረዳት አብራሪው የበረራ ክፍሉን ከውስጥ በመዝጋት ጠለፋውን እንደፈጸመ መዘገቡ እንዲሁ ይታወሳል፡፡
ወደ ሮም ማምራት የነበረበትን አውሮፕላን መስመር በመለወጥ ወደ ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ማብረር የቀጠለው ረዳት አብራሪው ኃይለመድኅን፣ የሱዳን አየር ክልል ውስጥ አውሮፕላኑን እንደጠለፈ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ምልክት መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጄነቭ አውሮፕላን ማረፊያ ክልል ውሰጥ ደርሶ ለሰዓታት በአየር ላይ መቆየቱን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ሁለት የጣሊያንና አንድ የፈረንሳይ ተዋጊ ጄቶች የተጠለፈውን አውሮፕላን አስገድደው ለማሳረፍ ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን የውጭ ሚዲያዎች ዘገባ ያመለክታል፡፡
ኃይለመድኅን አውሮፕላኑን ተቆጠጥሮ ወደ ጄኔቭ በሚያመራበት ወቅት ስለተፈጠረው ችግር የሚያውቁ መንገደኞች ጥቂት እንደነበሩ፣ አንዳንዶች ግን ዋና አብራሪው ወደ በሪራ ክፍሉ ለመመለስ የበረራ ክፍሉን በር እየደበደቡ እንዲከፈትላቸው ሲጠይቁት እንደነበር መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህ ጊዜም ረዳት አብራሪው ዋና አብራሪው በሩን መደብደብ ካላቆሙ  አውሮፕላኑን እንደሚከሰከስ በቁጣ መናገሩንና የአደጋ ጊዜ የአየር መሳቢያ ጭንብሎች ከሳጥኖቻቸው ተዘርግፈው ወደ ተሳፊሪዎች እንዲደርሱ እንዳደረገ አንዳንድ ተሳፋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ሊነጋጋ ሲል የደረሰው  አውሮፕላን በጠላፊው አማካይነት በሰላም ማረፍ የቻለው ከስዊዘርላንድ መንግሥት ባገኘው ፈቃድ መሆኑን አቶ ሬድዋን አረጋግጠው፣ የስዊዘርላንድ መንግሥት ለሰጠው ፈቃድ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ግለሰቡ የፖለቲካ ጥገኝነት በስዊዘርላንድ እንዲሰጠው ወይም ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፈው እንዳይሰጡት መጠየቁን ከሚዲያዎች አንደሰሙ አቶ ሬድዋን ተናግረዋል፡፡
‹‹ጥገኝነት መጠየቁን በተመለከተ ከስዊዘርላንድ መንግሥት መረጃ አልደረሰንም፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የምርመራው ውጤት ሲደርሰን እናሳውቃለን፤›› ሲሉ አቶ ሬድዋን ገልጸዋል፡፡
ጠላፋውን የፈጸመው ረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን አበራ የትም አገር መሄድ የሚያስችለው የሙያ ባለቤት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ካልተመቸው አውሮፕላን መጥለፍ ሳያስፈልገው መሄድ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
‹‹አውሮፕላን መጥለፍ እዚህ ያለውን አለመመቸት አያካክስም፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ውሰጥ ሳይገባ ተከብሮ በሥራው ላይ መቀጠል ይችላል፤›› ያሉት አቶ ሬድዋን ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወንጀለኞችን አሳልፎ ስለመስጠት የሚደነግገውን የጄኔቭ ኮንቬንሽን ኢትዮጵያም ሆነ ስዊዘርላንድ ፈርመዋል፣ በመሆኑም ኃይለመድኅን ተላልፎ እንዲሰጥ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡
ረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን በአሁኑ ጊዜ በስዊዘርላንድ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን፣ የስዊዘርላንድ ፖሊስ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ቶቆጥቧል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡
Source:  Reporter

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ሲካሄድ የቆየው የሦስትዮሽ ውይይት ከተቋረጠ ከሳምንታት በኋላ፣ ሰሞኑን ሦስት የግብፅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግድቡ ግንባታ እንዲቋረጥ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡
‘ዲሞክራቲክ ፒፕል ፓርቲ’፣ ‘ኢጂፕቲያን ዓረብ ሶሻሊስት ፓርቲ’ እና ‘ሶሻል ጀስቲስ ፓርቲ’ የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ዘ ሄግ ለሚገኘው ዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድታቆም የሚጠይቅ ማመልከቻ አስገብተዋል፡፡ 
ግብፅ በየዓመቱ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ከዓባይ ተፋሰስ እንደምትጠብቅ የተናገሩት የዲሞክራቲክ ፒፕል ፓርቲ ሊቀመንበር ፉአድ ሃፌዝ፣ ባለፈው መስከረም ወር የወንዙ ፍሰት በ20 ቢሊዮን ኪዩቡክ ሜትር ቅናሽ ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡
የፍርድ ቤቱን አንቀጽ 40 እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን አንቀጽ 96 በመጥቀስ አቤቱታ ማቅረብ መብታቸው መሆኑን የተናገሩት የፓርቲዎቹ መሪዎች፣ ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ምንም ዓይነት ግድብ እንዳትገነባ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በመስኖ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና የወሰን ተሻጋሪ
ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ፍርድ ቤቱ በፓርቲዎች የሚቀርቡ ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን የለውም ብለዋል፡፡
አቶ ፈቅአህመድ እንዳሉት፣ ግብፅ ወደ የትኛውም ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ብትወስደው ኢትዮጵያ የሚያስፈራት ነገር የለም ብለው፣ አቤቱታው የቀረበለት ፍርድ ቤት ጉዳዩን መመልከት የሚችለው በሁለት ሉዓላዊ አገሮች መልካም ፈቃድ የቀረበ እንደሆነ ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 
በሌላ በኩል ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐዜም አል ቤብላዊ፣ ‹‹የዓባይ ውኃ የሚወክለው የግብፅን ህልውና ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህንን ይበሉ እንጂ ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ የመጠቀም መብት እንዳላት አምነዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግድብ መገንባት እንደምትችል፣ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በሦስቱ አገሮች መካከል ተጀምሮ የተቋረጠው ውይይት መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት መጀመሩ ሦስቱንም አገሮች ቢጠቅም እንጂ ፈጽሞ አይጐዳም የሚል እምነታቸውን ያንፀባረቁ ቢሆንም፣ የውይይቱ አጀንዳ እንዲሆን የሚፈልጉት ግን ኢትዮጵያ በማትቀበለው የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ተሳትፎ ላይ ነው፡፡ 
Source: Reporter

GENEVA (AP) -- An Ethiopian Airlines co-pilot locked his colleague out of the cockpit, hijacked a Rome-bound plane and landed Monday in Geneva, all in an attempt to seek asylum in Switzerland, officials said.
The Boeing 767-300 plane with 202 passengers and crew had taken off from the Ethiopian capital of Addis Ababa and landed in the Swiss city at about 6 a.m. (0500 GMT). Officials said no one on the flight was injured and the hijacker was taken into custody after surrendering to police.
It wasn't immediately clear why the co-pilot, an Ethiopian man born in 1983 whose name wasn't released, wanted asylum. However, Ethiopian Airlines is owned by Ethiopia's government, which has faced persistent
criticism over its rights record and alleged intolerance of political dissent.
The plane first sent a distress message while flying over Sudan's airspace on its way to Rome, Ethiopia's communications minister said.
"From Sudan all the way to Switzerland, the co-pilot took control of the plane," said the minister, Redwan Hussein. He didn't elaborate but added that the pilot was Italian.
Passengers on the plane were unaware at the time that it had been hijacked, officials said. Even local authorities at first thought the Ethiopian plane just wanted to land in Geneva for an emergency refueling before realizing it was hijacked, Geneva police spokesman Eric Grandjean said.
Two Italian fighter jets were scrambled to accompany the plane, Geneva airport chief executive Robert Deillon told reporters.
The co-pilot took control of the plane when the pilot ventured outside the cockpit, Deillon said.
"The pilot went to the toilet and he (the co-pilot) locked himself in the cockpit," Deillon said. "(He) wanted asylum in Switzerland."
A few minutes after landing in Geneva, the co-pilot left the cockpit using a rope, then went to the police forces close to the aircraft and "announced that he was himself the hijacker," Grandjean said.
Police escorted the plane's passengers out one by one, their hands over their heads, from the taxied plane to waiting vehicles. Geneva airport was closed to other flights for about two hours after the hijacked plane landed.
Geneva prosecutor Olivier Jornot said the co-pilot will be charged with taking hostages, a crime punishable by up to 20 years in prison. The Swiss federal prosecutor's office will take over the investigation.
Jornot said the man's chances of winning asylum were slim.
"Technically there is no connection between asylum and the fact he committed a crime to come here," he said. "But I think his chances are not very high."
The leader of Ethiopia's opposition Blue party, Yilikal Getnet, said he believes the hijacker was trying to make a statement about the political situation in Ethiopia, where the party of the late strongman Meles Zenawi has dominated politics since the 1990s.
"I think he took the measure to convey a message that the ... government is not in line with the public and people are not impressed by what the government says," he said.
Human Rights Watch says Ethiopia's human rights record "has sharply deteriorated" over the years. The rights group says authorities severely restrict basic rights of freedom of expression, association and assembly and the government has been accused of targeting journalists, opposition members and minority Muslims.
There have been numerous hijackings by Ethiopians, mostly fleeing unrest in the East African nation or avoiding returning home - and some have involved the national carrier.
In 1994, Ethiopian Airlines suffered two hijackings at the hands of passengers who demanded to be flown to Europe, according to the Aviation Safety Network, which tracks aviation hijackings.
The following year, five armed men seized an Ethiopian Airlines jetliner and demanded the plane be flown to Greece and then Sweden. It was instead diverted to Al Obeid, 300 miles (480 kilometers) west of Khartoum, Sudan.
Source: Associated Press

ቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ውስጥ መምህራንና ተማሪዎች በመማር ማስተማሩ ሒደት ለመምከር ተሰባስበዋል፡፡
የ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› 2013/14 ሪፖርት ይፋ መሆንን ተከትሉ ውይይቱን ለማድረግ ለተወከሉት ተማሪዎች ሴራሊዮናዊው አወያይ ቼርኖር ባህ ‹‹መምህር መሆን የሚፈልግ አለ?›› ሲል ጥያቄውን ሰነዘረ››፡፡ ከደቂቃዎች ዝምታ በኋላ አንድ ተማሪ ‹‹እኔ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ጥያቄ ለመምህራኑ እንድጠይቅ ግን ፍቀድልኝ›› አለች፡፡ ሚስተር ባህ መድረኩን ሰጣት፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከማላዊና ከፓኪስታን ለተወከሉት መምህራን ‹‹ከእናንተ ውስጥ ልጁ መምህር እንዲሆን የሚፈልግ አለ?›› ስትል ጠየቀች፡፡ አንድም መምህር አዎ ሲል አልተደመጠም፡፡ 

ቤተሰብ በልጁ ላይ ከሚፈጥረው የ‹‹መምህር አትሆንም›› ተፅዕኖ በተቃራኒ ልጁ መምህር እንዲሆንለት የሚፈልግ እንዲሁም በፍላጐት ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ አሉ፡፡ ሆኖም ዛሬ ዓለም እያስተናገደች ያለችው ከፍተኛ የመምህራን እጥረትና ፍልሰትን ነው፡፡ በየትምህርት
ቤቶችም ውስጥ ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑንና አገሮች እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጓቸውን መምህራን እንኳን ሊያሟሉ እንደማይችሉ የ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› 2013/14 ሪፖርት ያሳያል፡፡ አገሮች መምህራንን በብሔራዊ ደረጃ እያሠለጠኑ ቢሆንም መምህራኑ በዘርፍ የማይቀጥሉበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ አዲሰ አበባም የችግሩ ተቋዳሽ ሆናለች፡፡

ቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት በአገሪቱ ካሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማሩ ሒደት ባስመዘገበው ጥሩ ደረጃ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ሽፋን አግኝቷል፡፡ በ2005 ዓ.ም. በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናም ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከአዲስ አበባ 1ኛ፣ በብሔራዊ ደረጃ 2ኛ ወጥቷል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ በመምህራን ፍልሰት ከሚቸገሩ የከተማዋ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የለቀቁ መምህራን እስኪተኩ ድረስ በቀሩት መምህራን ትብብር ክፍት ክፍለ ጊዜዎችን እየሸፈነ ለውጤት ቢበቃም የመምህራኑ ፍልሰት ለአስተዳደሩም ሆነ ለመምህራን ፈተና ሆኗል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ዳንኤል መኰንን እንደሚሉት፣ ከመስከረም 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከ20 በላይ መምህራን ለቀዋል፡፡ መምህራን እንደለቀቁ ወዲያው ምትክ ማግኘቱም ቀላል አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቱ ለክፍለ ከተማው አሳውቆ ክፍለ ከተማው መምህር እስኪመድብ በሚኖረው የሳምንትና የሁለት ሳምንት ክፍተት ሌሎች መምህራን በሳምንት ከሚያስተምሩት የትምህርት ክፍለ ጊዜ በላይ ተጨማሪ ይሰጣቸዋል፡፡ መምህራኑ በእሺታ ክፍተቱን ለመሙላት የሚሠሩ ቢሆንም በመሰናዶ ትምህርት ደረጃ መምህሩ ላይ ጫና መፍጠር የትምህርት ጥራቱን ያስጠብቃል ወይ? የሚለው ለመምህራኑም በጥያቄ የሚቀመጥ ነው፡፡ ሆኖም ተማሪዎቹ እንዳይጐዱና ከሌሎች ተማሪዎች ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ያግዛል በሚል ቀሪ መምህራን ደርበው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ደረጃ የመምህራን ፍልሰቱ የሚፈጥረውን ክፍተት ለመሙላት ቢጥሩም ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን ግን አቶ ዳንኤል ይናገራሉ፡፡ 
በከተማዋ ከሚገኙ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ባንዱ በርእሰ መምህርነት የሚያገለግሉትና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ መምህር፣ መምህሩ የተሻለ ገቢ ፍለጋ ከሥራው የሚለቅበትን ምክንያት ያስቀመጡት የሳቸውን ደመወዝ ዋቢ በማድረግ ነው፡፡ ከ25 ዓመት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ደመወዛቸው ከታክስ በፊት 2,800 ነው፡፡ 300 ብር ለቤት ኪራይና 100 ብር ለወንበር አላቸው፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ ከሁለት አሠርት በላይ ቢያስተምሩም፤ ከሚወጡት ኃላፊነት አንፃር የሚያገኙት ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዓመት በፊት ለቤት ኪራይ 1,800 ብር ይከፍሉ እንደነበር የሚያስታውሱት መምህር የባለቤታቸው 1,400 ብር ደመወዝ ተጨምሮም ‹‹ለኪሴ›› የሚሉት ገንዘብ ተርፏቸው እንደማያውቅ፣ ሙያውን ስለሚወዱት ግን እስካሁንም እንደሚያገለግሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹መምህርነት ጊዜያዊ መጠለያ የሆነበት ዋናው ምክንያት ተመጣጣኝ ደመወዝ ስለማይከፈል ነው›› ይላሉ፡፡ 
እንደ እሳቸው ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለመምህሩ የሚከፈለው ደመወዝ አግባብ ቢመስልም መምህሩ በሚያገኘው ገቢ ደስተኛ አለመሆኑን ሥራውን በመልቀቅ እያሳየ ነው፡፡ አብዛኞቹ መምህራን ወደ ሌላ ሥራ ሊያሰማራቸው በሚችል የትምህርት ዓይነት በየዩኒቨርሲቲዎች በማታው ክፍለ ጊዜ ይማራሉ፡፡ እንደተመረቁ ሥራቸውን ይቀይራሉ፡፡ ሥራ መቀየር ምርጫ ቢሆንም መምህርነት፣ በመምህርነት ሥልጠና ለመግባት ያለውን የቅበላ መስፈርት ከፍተኛ ከማድረግ ጀምሮ ደመወዙና የሚያገኘው ጥቅማ ጥቅም ተወዳዳሪ ቢሆን መምህርነት በፍላጐት የሚመጣበት ዘርፍ ይሆን ነበር ይላሉ፡፡ የቅበላ መስፈርቱንም ‹‹ሞራል የሚነካ›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ 
የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው የወቅቱ የመሰናዶ መግቢያ 2.4 ቢሆን በ2.00 እና በ2.4 መካከል ያመጡ ተማሪዎች በመምህርነት በዲፕሎማና ሠርተፊኬት መሠልጠን ይችላሉ፡፡ በተቃራኒው በሕክምናና በምሕንድስና የመሳሰሉና በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ በተሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች ለመግባት ለመሰናዶ የሚያበቃ ውጤት ከማምጣት ባለፈም የ12ኛ ክፍልን ብሔራዊ ፈተና በከፍተኛ ውጤት ማለፍ ግድ ነው፡፡ ይህም ትውልድ ለሚቀርጸው የመምህርነት ሙያ የተሰጠውን ዝቅተኛ ግምት ያሳያል፡፡ ዘርፉ ‹‹የማይፈለግ›› ወይም ‹‹ትኩረት የተነፈገው›› መሆኑ የሚጀምረውም ከቅበላ መስፈርቱ ነው ይላሉ፡፡
አንድ ዓመት ያህል በመንግሥት ትምህርት ቤት አገልግለው መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የተቀጠሩት አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ ከመምህርነታቸው የለቀቁት በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አንደኛው በመምህሩና ተማሪው መካከል ያለው ግንኙነት መስመር የለቀቀና ተማሪው ለመምህሩና ለሥነ ሥርዓት የማይገዛ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ደመወዙ ነው፡፡ በሌላ በኩል መምህርነትን ሥራ ለማግኘት እንጂ መርጠውት ስላልገቡ በዘርፉ ሊቆዩ አልቻሉም፡፡ ‹‹እኔ እስከማውቀው ጓደኞቼ ሁሉ መምህርነትን ፈልገውት አልገቡም፡፡ ከገቡም በኋላ እየለቀቁ በተለያየ ሙያ ተሰማርተዋል፤›› ይላሉ፡፡ 
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ትውልድን የሚቀርፀውን መምህር በሥራው ለማቆየትና ፍልሰትን ለመቀነስ ዘርፉ በከፍተኛ ውድድር የሚገባበት፣ ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈልበት መሆን ይገባዋል፡፡ እሳቸው በተማሩባቸው በ1980ዎቹ እንኳን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደመምህርነት ዘርፍ የሚመድባቸው ተማሪዎች መጀመርያ ዓመት ላይ ከመባረር የተረፉ ግን ዝቅተኛ ውጤት ያላቸውን ነው፡፡ ይህ ልማድ ዛሬም በቅበላ ላይ ይታያል፡፡ ‹‹ክብር ባልተሰጠው ሙያ ማንስ መቆየት ይፈልጋል?፡፡ በፍላጐቱና በጥሩ ውጤት ለገባው መምህርም ቢሆን ክብር ያሳጣል፡፡››
ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መምህራን የሚያሠለጥነው ኮተቤ መምህራን ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነው፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ ተፈሪ በለው የመምህራን ቅበላ መስፈርት በመምህራን ፍልሰት ላይ ያለው ተፅዕኖ በጥናት ባይረጋገጥም እንዲሻሻል ሁሌም የሚያነሱት ጥያቄ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ወደዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በዲፕሎማ ደረጃ የሚገቡ ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ መምህር የሚሆኑ ሲሆን በዲግሪ ደረጃ ከሚሠለጥኑት ደግሞ መምህር መሆን የሚፈልጉት ብቻ ተጨማሪ አንድ ዓመት ሠልጥነው ወደሙያው እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ 
በዲግሪ ደረጃ ያለው ፖሊሲ ፍላጐትን ያማከለ ነው፡፡ በዲፕሎማ ደረጃ የሚሠለጥኑት መምህራን ግን ሥራ ከያዙ በኋላ በሌላ የትምህርት ዘርፍ የማታ እየተማሩ ሥራ ሊቀይሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ሆኖም በዲፕሎማ ደረጃ አዲስ አበባ ላይ የመምህራን ችግር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ 
አቶ ተፈሪ እንደሚሉት ለመምህራን ፍልሰት እንደምክንያት የሚነሳውን የደመወዝ ማነስ አገሪቱ ካለችበት ደረጃና ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ሲነፃፀር ደህና የሚባል ነው፡፡ ሆኖም ከተሸከመው ኃላፊነት ጋር ሲነፃፀር አይሄድም፡፡ 
በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታየውን የመምህራን ፍልሰት በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዋና የሥራ ሒደት አቶ አማኑኤል ኤሮሞ ‹‹የመምህራን ፍልሰት ጉዳይ የሁላችንም ጭንቀት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ተማሪ ትምህርት ቤት አስገብተን ያለ መምህር ዋጋ የለውም›› በማለት የመምህራን ፍልሰት አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ከ2006 ዓ.ም. መስከረም ወዲህ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 50፣ በነፋስ ስልክ ላፍቶ 57 መምህራን መልቀቃቸውን አውስተዋል፡፡  
የመምህራን ፍልሰት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካም መሆኑን የሚገልጹት አቶ አማኑኤል፣ ለመምህራን ፍልሰት ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆኑም ሚዛን በሚደፉት በደመወዝ ጭማሪ ጥያቄና በሙያው ፍላጐት ዙርያ በአዲስ አበባ ደረጃ ጥናት ሊደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
እንደ መፍትሔም በትምህርት ቤት መልካም አስተዳደርና ምቹ አገልግሎት እንዲኖር እንዲሁም ከደመወዝ ጭማሪ አኳያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተወያዩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
Source: Reporter

| Copyright © 2013 Lomiy Blog