ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር በሚያደርገው ቀጣይ ትግል ህብረተሰቡ ከጎኑ እንዲቆምም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

የፓርቲው አመራሮች “‹‹ነጻነት በሌለባት ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አስተዳደር መትከል ዘበት ነው!›› በሚል ርእስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በምርጫው ሂደት በመቆየታቸው የኢህአዴግን አውሬነት ማሳየታቸውን በመጥቀስ፤
‹‹በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስት በህዝብ ተቀባይነት የለውም››ብለዋል።
‹‹ምርጫው ከዚህ ቀደም ከተካሔዱት ምርጫዎች ጋር እንኳ ሊወዳደር የማይችል እጅግ ኢ-ፍትኃዊ፣ ወገንተኛና ተዓማኒነት የሌለው በመሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ሂደቱንም ሆነ ውጤቱን አይቀበለውም፡፡›› ብለዋል-የፓርቲው አመራሮች።
ፓርቲው በ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት እንደሌሉና ገዥው ፓርቲም እውነተኛ ምርጫ እንደማይፈቅድ እያወቀ መሆኑን የገለፀሱት አመራሮቹ፤ ፓርቲው በሂደቱ የተሳተፈው የስርዓቱን
ችግሮች ለማጋለጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹በሂደቱ ውስጥ በመቆየታችን እጩዎቻችን በህገ ወጥ መንገድ ሲታገዱ፣ ታዛቢዎች ሲከለከሉና ሲታሰሩ አሳይተናል፡፡ በሂደቱ በመቆየታችን የኢህአዴግን አውሬነት አሳይተናል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮም
ሆነ በምርጫው ወቅት የነበረውን ማጭበርበር ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም አጋልጠንበታል፡፡›› ብለዋል፡፡
የፓርቲው ም/ሊቀመንበር እና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስለሽ ፈይሳ በበኩላቸው ምርጫው መትረየስ ተጠምዶ፣ ብረት ለበስ በየመንገዱ ቆሞ፣ የአጋዚ ጦር አባላት ከተማ ውስጥ ተሰማርተው ከመካሄዱም ባሻገር ከፍተኛ የድምጽ ማጭበርበር
የነበረበት ነው ብለዋል፡፡ የምርጫው ብቸኛ የውጭ ታዛቢ የሆነውን የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድንም ራሱንም ሌላም ማዳን የማይችል ‹‹የእንጨት ድምጽ ነው!›› ሲሉም ተችተዋል፡፡
ምርጫው በህገ ወጥ አሰራሮች የታጀበ፣ በማንኛውም መመዘኛ ፍትሃዊ፣ ነፃና ተአማኒ ሊሆን እንደማይችል ሒደቱ በግልፅ አመላካች ነበር ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹በውጤቱም በሐገራችን የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖርን ወደ
መቃብር የከተተና ኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ ስርዓት ሐገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው፡፡”ነው ብሏል።
ፓርቲው አያይዞም በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስትም በሕዝብ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጾአል፡፡
“የዜጎች ነፃነት ሳይከበር ነጻና ፍትኃዊ ምርጫ ሊደረግ አይችልም” ያለውሰማያዊ ፓርቲ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን እስከሚከበሩ ድረስ ፓርቲው በሚያካሂደው የነጻነት ትግል ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አድርጓል፡፡

ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በሃመር ወረዳ በዲመካ ከተማ እና አካባቢዋ የሚኖሩ አርብቶአደሮች ” እኛ ድምጽ ሳንሰጥ” እንዴት ኢህአዴግ አሸነፈ ይባላል በሚል ካለፈው
ሰኞ ጀምሮ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ሲታኮሱ መቆየታቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አንድ ሻለቃ ጦር እና የፌደራል አባላት ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ በወሰዱት እርምጃ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር በመቶዎች ያደርሱታል።
የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት አርብቶ አደሮች 5 የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ያቆሰሉ ሲሆን፣ ቁስለኞችም በሄሊኮፕተር ተወስደዋል። በአርብቶ አደሮች በኩል የተገደሉትን ሰዎች በትክክል ለማወቅ እንደማይቻል የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች
አስከሬን በየቦታው ወደቆ እንደሚታይ እየገለጹ ነው።
በዞኑ የሚኖሩ አንድ ታዋቂ ግለሰብ እንደተናገሩት ደግሞ ትናንት አርብቶ አደሮች ዲመካን በሌሊት ለመያዝ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት የመንግስት ወታደሮች ከባድ መሳሪያ በመተኮስ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች
እንደተገደሉ መረጃው እንደደረሳቸው ገልጸዋል። በሶስት ፒካፕ መኪኖች የተጫኑ ቁስለኛ ወታደሮች ጂንካ ሆስፒታል መግባታቸውንም አክለው ገልጸዋል። ሁለቱም ወገኖች ለወራት የጦርነት ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ፣
የችግሩ ምንጭ ከምርጫ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመሬት ጋር የተያያዘ መሆኑም ይገልጻሉ።
ሌላ የአካባቢው ነዋሪም እንዲሁ በተወሰደው እርምጃ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል ። የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በርጤ ዢላ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢሳት በሁለቱም ወገን የሞቱትን ሰዎች ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት ያደረገው መኩራ አልተሳካለትም።
ኢሳት ከሶስት ቀናት በፊት አርብቶአደሮች 3 ፖሊሶች ማቁሳለቸውን ዘግቦ የነበረ ሲሆን፣ ሆቴል ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሁንም ድረስ እንደተዘጉ ነው።
ለወራት የዘለቀው ውጥረት ምርጫውን ሰበብ አድርጎ መጀመሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ሰመጉ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው ልዩ መግለጫ ከጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተ ግጭት 7 ሰዎች መገደላቸውንና 9 ሰዎች መቁሳለቸውን
በጥናት አረጋግጦ ይፋ አድርጓል።
ሰመጉ በሪፖርቱ ህዳር 7 ቀን 2007 ዓም አቶ ዑልዴ ሃይሳ በሐመር ወረዳ ሸንቆ ወልፎ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የነበረ አርብቶ አደር ሲሆን፣ በድንገት በተነሣ አለመግባባት ምክንያት ባሌ ኢልዴ በተባለ የፖሊስ አባል ኩላሊቱ ላይ በከባድ
እርግጫ በመመታቱ የአቶ ዑልዴ ህይወት በእለቱ ህዳር 7 አልፏል። የሐመር ብሔረሰብ አባላት አቶ ዑልዴን የገደለው የፖሊስ አባል ሕግ ፊት ቀርቦ ባለመጠየቁ ከፍተኛ ቅሬታ አድሮባቸውና የመበደል ስሜት ውስጥ ገብተው እንደነበር
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ አስታውቃል።
ማንጐ ተብሎ በሚጠራው ፓርክ ጎሽ የገደሉ የሐመር ብሔረሰብ አባላትን ለመያዝ ከደቡብ ኦሞ ዞን ፓሊስና ልዩ ኃይል የተውጣጡ አባላት ጥር 7/ 2007 ሥፍራው ሲደርሱ ለሽምግልና የተቀመጡ የአካባቢውን ሽማግሌዎች ጎሽ ገዳዮችን እንዲያወጡ በጠየቁዋቸው ጊዜ “በቅርቡ የተፈጸመውን የአቶ ዑልዴን ግድያ ሳታጣሩና ገዳዩን ይዛችሁ ለፍርድ ሳታቀርቡ፣ ከረዥም ጊዜ በፊት ጎሽ ገደለ የምትሉትን ሰው ለመያዝ እንዴት መጣችሁ?” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ይሁን እንጅ ” የፖሊስና ልዩ ኃይል አባላቱ በወቅቱ የተሰጣቸው ግዳጅ ጎሽ የገደለን ሰው መያዝ ብቻ መሆኑን በመግለጽ፣ ፖሊስ የተላክሁበትን ግዳጅ እፈጽማለሁ በማለቱ የሐመር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰቡ አባላት ደግሞ የአቶ ዑልዴ ሃይሳን ገዳይ ሳትይዙ
የጎሽ ገዳይ ልትይዙ አትችሉም በሚል አለመግባባት መፈጠሩን ሪፖርቱ ያስረዳል።
አለመግባባቱ እየተካረረ ሄዶ በዚያው ቀን ጥር 7 ቀን 2007 በሐመር ማኅበረሰብ አባላትና በፖሊሶች መካከል ተኩስ ተጀምሮ፣ ሰፋ ወዳለ ግጭት ያመራ ሲሆን በግጭቱም 7 ሰዎች ሲሞቱ 9 ሰዎች መቁሰላቸውን ማረጋገጡን የሰመጉ 134ኛ
ሪፖርት ያስረዳል።
ሰመጉ ባወጣው የሟቾች ስም ዝርዝር አብዛኞቹ የሞቱትና የቆሰሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስና የልዩ ሃይል አባላት ናቸው።
ሰመጉ በግጭቱ ተሳታፊ ከነበሩት የሐመር ብሔረሰብ አባላት በኩል ምን ያህል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰ ለማወቅ አለመቻሉን በመግለጫው አስታውቋል።
በሃመር ወረዳ ከ45 ሺ በላይ ነዋሪዎች ይኖራሉ። ዲመካ የወረዳው ዋና ከተማ ናት።

ግንቦት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ የግንቦት15ቱን ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፉ ከተገለጸ በሁዋላ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ከሁለት ተከፍለዋል። ምንጮች እንደገለጹት በርካታ ፊደል ቀመስ አባሎቹ ኢህአዴግ አሸነፍኩ
ያለበትን የድምጽ ልዩነት አልተቀበሉትም። ውጤቱን የሚቃወሙ የግንባሩ አባላት ” ህዝቡ ከእንግዲህ በሰላም መንግስት እቀይራለሁ የሚለው እምነቱ ተሟጦ የሃይል አማራጭን ብቻ እንዲመለከት ከማድረጉም በላይ፣ የሃይል አማራጭን
የሚከተሉ ሃይሎች በህዝቡም ሆነ በአለማቀፉ ማህበረሰብም የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል” በማለት ለድርጅቱ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ተገኘ የተባለውን ውጤት ከመደገፍ አልፈው፣ ህዝቡ እንዴት ለተቃዋሚዎች ይህን ያክል ድምጽ ሊሰጥ ቻለ በማለት በቁጭት አስተያየት የሚሰጡ ደጋፊዎች መኖራቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።
ኢህአዴግ እያሰባሰበ ባለው መረጃ ላይ እንደተገለጸው፣ አንዳንዶች ” ይህ ህዝብ ምን አይነት ልቡ የማይታወቅ ከሃዲ ህዝብ ነው! እንዴት ይሄን ሁሉ ልማት እያዬ ለተቃዋሚ ድምጹን ሊሰጥ ቻለ?” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫ ቦርድ ራሱ ባወጣው ሰሌዳ መሰረት የምርጫውን ውጤት መግለጽ የነበረበት ግንቦት21 ቢሆንም፣ የግንቦት20 በአልን ለማድመቅ እንዲረዳ በሚል ከእቅዱ በፊት እንዲገለጽ መደረጉን ምንጮችን ዋቢ በማድረግ
ዘጋቢያችን ገልጿል።
ኢህአዴግ በየክልሉ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የፌሽታ በዓላትን አዘጋጅቷል። ትናንት የገዢው ፓርቲ ደጋፊ አርቲስቶች ያዘጋጁት የኪነጥበብ ምሽት በብሔራዉ ቲያትር ተካሂዷል፡፡፡ በርካታ የፌዴራል የመንግስት መ/ቤቶች በተለያዩ ሆቴሎች
በዓሉን ለማክበር ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምርጫ ቦርድ የኢህአዴግን አሸናፊነት ቢያውጅም መድረክ የተባለው የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የምርጫውን ውጤት አልተቀበለውም። ድርጅቱ ምርጫው አነስተኛ የሚባሉ መስፈርቶችን እንኳ ያላሟላ በማለት አጣጥሎታል። መድረክ
በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ገለልተኛ የሚባሉ ሰዎች ተመርጠው መምርራ እንዲያካሂዱ ጠይቋል።
ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫውን በተመለከተ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ያለው ነገር የለም። መንግስት የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎችን እያዋከበ በማሰር ላይ መሆኑ፣ ፓርቲውን አጣብቂኝ ውስጥ ሳይከተው አልቀረም። ሰማያዊ የምርጫውን
ውጤት ይቀበለዋል ተብሎ አይጠበቅም።
የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን በተመለከተ በርካታ እጸጾችን አውጥተው ቢገልጹም፣ ከኢህአዴግ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደማያቋርጡ አስታውቀዋል። የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ ዲፕሎማቶች
በምርጫ ታዛቢነት እንዳይሰታፉ መከልከላቸው፣ ምርጫው አሳታፊ አለመሆኑንና የተለያዩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች መታሰራቸውን በመግለጫቸው አመልክተዋል።
በምርጫው ሂደት ያጋጠሙ በርካታ አስገራሚ ክስተቶች ለኢሳት እየደረሱ ነው። ግንቦት12 ቀን 2007 ዓም በአዲስ አበባ ልዩ ቦታው ላንቻ ወይም ጠመንጃ ያዥ ነዋሪ የሆነ አንድ የ12 ዓመት ህፃን የኢህአዴግን የምርጫ መልዕክት ያየዘ
ፖስተር ከተለጠፈበት ግድግዳ ላይ ቀደሃል በሚል 6 ወር ተፈርዶበታል።
በአዲስ አበባ ችሎት በሚባል ቦታ አርብ ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም ሁለት ማየት የተሳናቸው ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። ወጣቶቹ የተያዙት አንደኛው ሙሉ ሰማያዊ ልብስ ለብሶ በመውጣቱ በተፈጠረው አተካራ ነው። የአካባቢው
ሴት ካድሬ አንደኛውን ማየት የተሳነው ወጣት “ለምን ሰማያዊ ልብስ ለበስክ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነሆይ?” በማለት ጥያቄ ስታቀርበለት፣ ጓደኛው “ምን አገባሽ ምንስ ብለብስ!” የሚል መልስ መስጠቱን ተከትሎ፣ ግለሰቧ በብስጪት
ለደህንነቶች ባስተላለፈችው ጥቆማ መሰረት ሁለቱም ወጣቶች በድንገት ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን እስከዛሬ ድረስ ታስረው ይገኛሉ።
መነን መሰናዶና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም ፀሃይ ጮራ ት/ቤት ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው 20 መምህራንና 30 ተማሪዎች የሰማያዊና የአንድነት ፓርቲ አባላት ናቸው በሚል ዝርዝራቸው ለጸጥታ አካላት ተልዕኮ በልዩ ሁኔታ ክትትል እንዲደረግባቸው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከምርጫ በፊት ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ሚያዝያ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ገዢው ፓርቲ ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ ህዝቡን አስተባብረው ህዝባዊ አመጽ ያስነሱ ይሆናል በሚል የሚጠረጥራቸውን ወጣቶች ሁሉ እያፈሰ ከማሰር አልፎ ፣ አንዳንዶች እየተገደሉ ሌሎች ደግሞ አሰቃቂ ድብደባ እየተፈጸመባቸው ነው።
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ የሚማር አንድ የመድረክ አባል እንደሆነ የሚታወቅ የ3ኛ አመት ተማሪ ግቢው ውስጥ ወድቆ ከተገኘ በሁዋላ የተሻለ ህክምና ለማግኘት ባለመቻሉ ህይወቱ አልፎአል።
በቴክስታይል የትምህርት ክፍል የኢንጀሪንግ 3ኛ አመት ተማሪ የነበረው ያዕቆብ ቡዴ ከደቡብ ህዝቦች ክልል የመጣ ሲሆን ሰኞ ግንቦት 10/2007 ዓ.ም ከምሽቱ በ5 ሰዓት በግቢው ውስጥ ወድቆ በመገኘቱ በአካባቢው ሲዘዋወሩ የነበሩ ተማሪዎች አግኝተውት ፣ በዩኒቨርስቲው ክሊኒክ እንዲረዳ ቢያደርጉትም ወደ ተሻለ ህክምና ሊወሰድ ባለመቻሉ ህይወቱ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ማለፉን የዩኒቨርስቲው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ተማሪ ያዕቆብ ቡዴ የመድረክ ፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ ሆኖ እንደሚንቀሳቀስ በቅርብ የሚያውቁት ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡ የገዢው መንግስት ካድሬዎች በየጊዜው ይዝቱበት እንደነበር የሚናገሩት የልጁ ጓደኞች በዩኒቨርስቲ ቆይታው አንድም ቀን ታሞ እንደማያውቅ ያክላሉ። ወጣቱ በልብ ህመም እንደሞተ ተደርጎ የሚሰጠው መግለጫ ትክክል አለመሆኑን የሟቹ ጓደኞች ገልጸዋል።
የባህርዳሩ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል በሚገኝበት ከተማ እና በርካታ አምቡላንስና የዩኒቨርስቲው መኪኖች እያሉ ወደ ህክምና ማድረስ ሲቻል በዩኒቨርስቲው አነስተኛ ክሊኒክ በቂ እርዳታ ሳደረግለት ህይወቱ በማለፉ ከፍተኛ ንዴት ውስጥ የሚገኙት የሟች ጓደኞችና የትምህርት ክፍል አጋሮቹ ፣ ጓደኛችን ሆን ተብሎ እንዲሞት ተደርጓል በማለት ብስጫታቸውን እየገለጹ ነው።
የሟች አስክሬን ከሌሊቱ በ10 ሰዓት በዩኒቨርስቲው መኪና ተጭኖ በድብቅ ወደ ትውልድ ሀገሩ ሸኖ ከተማ መላኩን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከአሁን በፊት በዩኒቨርስቲው ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በህመምም ሆነ በተለያዩ ምክንቶች ሲያርፉ ተማሪውና የዩንቨርስቲው ማህበረሰብ በነቂስ ወጥቶ በዲፓርትመንቱ የአበባ ጉንጉን ተዘጋጅቶ እንደሚሸኝ የሚገልጹት ተማሪዎች፣ የተማሪው አስከሬን በድብቅ አንዲሄድ መደረጉ ከአሟሟቱ ጋር በተያያዘ ሌሎች ችግሮች እንዳይነሱ በመስጋት ነው ይላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው አቤል ኤፍሬም በደረሠበት ድብደባ ኩላሊቱ ተጎድቶ ምንሊክ ሆስፒታል መግባቱ ታውቋል።
ወጣት አቤል በደህንነቶች ተይዞ ወደማዕከላዊ መወሰዱን የገለጹት የቅርብ ጓደኞቹ፤ ማዕከላዊ እስር ቤት ከቀኑ 5 ሠዓት ጀምሮ እስከ እኩለ-ሌሊት በተፈፀመበት ከፍተኛ ድብደባ ኩላሊቱ በመጎዳቱ ሌሊት 11 ሠዓት ላይ ወደምኒልክ ሆስፒታል እንደተወሰደ ተናግረዋል።
እንደ ትግል ጓደኞቹ ገለጻ አቤል ከመያዙ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በማስተማር ላይ የሚገኙ 13 መምህራን በፖሊስ ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፤ አቤል ማዕከላዊ በገባበት ቀን ፦” በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኙ መምህራንን በህቡዕ እንደምታደራጅ ደርሰንበታል” የሚል ክስ ቀርቦበታል።
ለመርማሪዎቹ ስለጉዳዩ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ የገለፀው ወጣት አቤል፤ ብሔሩን ሲጠየቅ “ብሔሬ ኢትዮጵያዊ ነው” ማለቱ ያናደዳቸው የደህንነት ኃይሎች መታወቂያውን በመቀበል ብሔሩን ለማጣራት ሲሞክሩ ብሔር የሚለው ስፍራ ላይ ምንም ብሄር አለመጠቀሱን ተመልክተዋል።
“ተያዥ” በሚለው ስፍራ ላይ ታማኝ በየነ የሚል ፅሁፍ በማገኘቱ፤ በብስጭትና በእልህ እየተፈራረቁ ክፉኛ እንደደበደቡት ጓደኞቹ ይገልጻሉ።
ሌሊቱን በሙሉ ምግብ እና ውሃ ሳይቀምስ ክፉኛ ሲደበድቡት ያደሩት የደህንነት ሀይሎች ፤ ሌሊት ላይ የአቤልን መድከም ሲረዱ ምኒልክ ሆስፒታል እንደወሰዱት ገልጸዋል።
በምኒልክ ሆስፒታል የነበሩ የ ዐይን ምስክሮች አቤል ሆስፒታል ሲደርስ በድብደባ ብዛት ኩላሊቲ እንዳበጠ እና የለበሰው ልብስ ከጥቅም ውጪ እንደሆነ መናገራቸውን ጓደኞቹ ተናግረዋል።
ነገረ ኢትዮጵያ ባወጣው ዘገባ ደግሞ ቤተሰቦቹ ምኒልክ ሆስፒታል ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት ዶክተሮቹ አቤልን መጠየቅ እንደማይቻል ገልጸውላቸዋል።
አቤል ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበትና ማንንም ማናገር እንደማይችል ሆስፒታሉ ውስጥ ከሚሰሩ ሰዎች መረጃ ማግኘታቸውን ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አቤል ሰማያዊ በጠራው አንድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድቦ ራሱን ስቶ ከሞት መትረፉ በወቅቱ መዘገቡ ይታወቃል። አቤል ኤፍሬም ታህሳስ ወር ላይ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ አንድ ሃይለ ሃለፎም የሚባል ፖሊስ ብሄርህ የት ነው ብሎ ሲጠይቀው ኢትዮጵያዊ ብሎ መመለሱን፣ ከዚያም ጥያቄ ሲበዛበት አባቴ የተወለደው አድዋ ነው ብሎመናገሩን፣ ፖሊሱም ” እና አንተ ደግሞ ምን ጎድሎብህ ነው የምትታገለው” ብሎ ከመለሰለት በሁዋላ ስርአቱን አምርሮ እንዲታገለው እንዳደረገው” ገልጾ ነበር ።
በአዲስ አበባ የ22 ማዞሪያ ሰፈር ነዋሪ የኾነው የ25 ዓመቱ ወጣት ሢሳይ ተሾመ በእስር ቤት ውስጥ በደረሰበት አስከፊና ተደጋጋሚ ድብደባ ከጥቂት ቀናት በፊት ለህልፈተ ህይወት እንደተዳረገ መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀዳሚ ገፅ ጋዜጣ ሥራ አስኪያጅና አምደኛ እንዲሁም የሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ ሪፖርተር የነበረው ሀብታሙ ምናለ ዛሬ ከረፋዱ 5፡30 ላይ ቦሌ ሩዋንዳ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በፖሊሶች ተይዞ በአካባቢው ወደ ሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱ ታውቋል።
እስካሁን በሚደርሱን መረጃዎች በአለፉት 2 ወራት ከ4 ሺ በላይ ወጣቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተይዘው ታስረዋል። ከ3 ሺ ያላነሱ ወጣቶች አዋሽ አርባ አካባቢ ከሚገኝ የገጠር እስር ቤት ውስጥ ሲገኙ፣ ንቁ የተቃዋሚ አባላት ናቸው የተባሉት ደግሞ በአዲስ አበባና በክልሎች ታስረው ይገኛሉ።
ገዢው ፓርቲ በክልሎችና በአዲስ አበባ ያለውን ደህንነቱን እያጠናከረ ሲሆን፣ በአንዳንድ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ወታደሮች በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እያሳደሩ ነው።

ሚያዝያ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው ግንቦት 12/2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት በሃያዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም
ተስፋው ፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ ናቸው።
ተከሳሾች “ኤርትራ ውስጥ መቀመጫውን ባደረገውና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ግንቦት ሰባት ስር አባል ሆነው የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ወስነው ከድርጅቱ ጋር ለመቀላቀል የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር አቋርጠው ሊሻገሩ ሲሉ
በቁጥጥር ስር መዋላቸውን” በዚህም የተነሳ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በአባልነት በመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ እንደሚያመለክት ጋዜጣው ዘግቧል።
ተከሳሾቹ ጠበቃ ማቆምን በተመለከተ ከፍርድ ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሁሉም ተከሳሾች፣ ‹‹ከተያዝን ጊዜ ጀምሮ በደል እየደረሰብን ነው፤ ይህ የብቀላ ስራ ነው ብለን ስለምናምን እና በዚህ ሁኔታ ተከራክረን ፍትህ እናገኛለን ብለን ስለማናምን
የግልም ሆነ የመንግስት ጠበቃ አንፈልግም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው አቤቱታ ‹‹የተከሰስኩበት ወንጀል በክሱ ላይ የተመለከተው ሆኖ እያለ በግድ ቀድሞ እሰራበት በነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ጓደኞቼ ላይ በተለይም በፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እና በህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የግንቦት ሰባት አባል እንደሆኑ ተደርጎ መስክር እየተባልኩ ስቃይ እየደረሰብኝ ነው›› ብሎአል።
“ማንነትን መሰረት ያደረገ ስድብ እንደሚሰደብ፣ ጨለማ ቤት እንደሚታሰር እንዲሁም የተጠየቀውን ካልፈጸመ ወደማዕከላዊ ሊመልሱት እንደሚችሉ እንደሚዝቱበት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱ ወጣት ብርሃኑ አለኝ ያለውን አቤቱታ በጽሑፍ እንዲያቀርብ በማሳሰብ፣ ተከሳሾች በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለመቀበል ለግንቦት 28/2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሶስቱ የሰማያዊ ፓርቲ ተከሳሾች ከዚህ ቀድም በተለያዩ ሰበቦች እየታሰሩ ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስባቸው ቆይቷል።
የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ሃለፊ የነበረው ወጣት ተስፋሁን አለምነው በቅርቡ በትጥቅ ትግል የሚታገሉ ሃይሎችን መቀላቀሉ መዘገቡ ይታወሳል።
በአገር ውስጥ እየደረሰ ያለውን አፈና በመሸሽና ስርአቱን በሃይል ለመታገል በርካታ ወጣቶች የትጥቅ ትግል የሚያራምዱ ሃይሎችን እየተቀላቀሉ ነው።
የወጣቱ መፍለስ ያስደነገጠው የሚመስለው ገዢው ፓርቲ በድንበሮች አካባቢ ክትትሉን ቢያጠናክርም፣ ወጣቶቹ መንገዱን እያጠኑ በመቀላቀል ላይ መሆናቸውን የተቃዋሚ መሪዎች ይናገራሉ።
ዘ-ሐበሻ) የቢትዮጵያ ትያትር እና ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ያበረከተው አንጋፋው አርቲስት ሠይፈ አረአያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ:: 
የዘ-ሐበሻ የአዲስ አበባ ዘጋቢዎች እንዳሉት ዝነኛው አርቲስት ለረጅም ጊዜ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በመጨረሻም ይህችን ምድር ተሰናብቷታል::
በብሄራዊ ትያትር እና በሌሎችም ትያትር ቤቶች በማገልገል በርከታ የመድረክ ሥራዎችን ያቀረበው ሰይፈ አረአያ በተለያዩ የአማርኛ ፊልሞችም ላይም ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል::
ዘ-ሐበሻ በአርቲስቱ ሕልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸች ለቤተሰቦቹ እና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን::
Source: Zehabesha


ሚያዝያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ በተለይ በሰሜን
የአገሪቱ ክፍል አብዛኛው ህዝብ ረብሻ ይነሳል ብሎ ያምናል። በዚህም የተነሳ ቀድም ብለው ገንዘባቸውን ባንክ ያስቀመጡ ሰዎች ገንዘባቸውን እያወጡ ለምግብ የሚውሉ የእህል ዘሮችን፣ ጨውና ሌሎችንም እቃዎች እየገዙ ነው። ወፍጮ ቤቶች ሰሞኑን ተጨናንቀው ታይተዋል። አቅም ያለው ቤተሰብ ለሶስት ወር የሚበቃ እህል ሲያስፈጭ፣ ድሃው ደግሞ አቅሙ በፈቀደ መጠን ለማጠራቀም እየተሯሯጠ ነው።
“በየከተሞች የሚታየው የሰራዊት እንቅስቃሴና ጥበቃ በህዝቡ ውስጥ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እያደረገ ነው” የሚለው ዘጋቢያችን፣ ” ህዝቡ መንግስት በከፍተኛ ሁከት እና ብጠብጥ ይወገዳል” የሚል ግምት ማሳደሩ አሁን ለሚታየው አለመረጋጋት ምክንያት ሳይሆን አልቀረም ይላል።
የኖርዌይ፣ ስዊድንና አሜሪካ ኢምባሲዎች ያወጡዋቸው መግለጫዎች ለአለመረጋጋቱ ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸውን ይጠቅሳል።
በህዝቡ ብቻ ሳይሆን የመንግስት ባለስልጣናትም ተወጥረዋል። በየአካባቢው ሌሊቱን በውጠራ በተጠንቀቅ የሚያሳልፉ ወታደሮችን ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል።
በባህርዳር ከተማ የመከላከያን ዩኒፎርም የለበሱ ወታደሮች የመገናኛ ሬዲዮ፣ ከባድ መሳሪያና ሌሎችም ቁሳቁሶች በመያዝ በየቀኑ ከ11 ሰአት በሁዋላ በከተማይቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች ይዞራሉ። ህዝቡ ማንኛውንም አመጽ በመሳሪያ እንቆጣጠራለን የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ፈልገው ነው በማለት አስተያየት ይሰጣል።
በባህርዳር የመሰናዶ ተማሪዎች ለቅስቀሳ በተላከው የኢህአዴግ ቡድን ላይ ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን፣ ኢህአዴግ ይወረድ የሚል መፈክሮችን አሰምተዋል።
ባህርዳር፣ ጎንደር፣ አዋሳ፣ አዳማ፣ አምቦና አዲስ አበባ አመጽ ሊነሳባቸው ይችላል ተብሎ ከተለዩት ከተሞች መካከል ናቸው።
ገዢው ፓርቲ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን በስራና ስልጠና በመደለል እንዲሁም በረብሻ ስም እያፈሰ አዋሽ አርባ አካባቢ በሚገኝ በረሃማ ቦታ ወስዶ አስሮአቸዋል። በርካታ ወጣቶች ከእስር ቤት ሲያመልጡ መንገድ ላይ በአውሬ መበላታቸውን እንዲሁም በምግብና ውሃ ጥም መሞታቸውን የሚደረሱን ተከታታይ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በቅርቡ ከማእከሉ ጠፍተው ጎንደር የደረሱ 5 ወጣቶች በእስር ቤቱ ያለው አስከፊ ሁኔታ እንዲጠፉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። ብዙ ወጣቶች መንገድ ላይ ወድቀው ማየታቸውንም ተናግረዋል።
ከምርጫ ዜና ሳንወጣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የንብ ምልክት ያለበትን ፖስተር በየሰዎች ቤት ግድግዳ ላይ የሚለጥፉ ሲሆን፣ ፖስተሩ ተቀዶ ከተገኘ የቤቱ ባለቤት ተጠያቂ እየሆነ ነው። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አባት፣ “ንቧን እንዳይቀዷት ቁጭ ብየ ስጠብቅ አድራለሁ ” በማለት ያጋጠማቸውን ፈተና ተናግረዋል።

ሚያዝያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የብአዴን ማእከላዊ የዞን ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች ውይይት በቀጣይ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን መመሪያ ለአባላቱ ባስተላለፈው የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት፣ ድርጅቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የድርጅቱ
ልዩ ልዩ አመራሮች ተናግረዋል፡፡
የብአዴን ማእከላዊ ዞን ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ሲናገሩ የብአዴን አመራሮች በ1990 ዓ.ም ከታየው የጥገኝነት ዝቅጠት አንስቶ በርካታ ፈተናዎችን ለማለፍ እንደተገደዱ ገልጸው፤ ጥገኝነት የስርአቱ አደጋ መሆኑን አምነው ተናግረዋል፡፡
ሃላፊው ‹‹ የክራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አልተተካም፡፡የክራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት መሰረት አልተናጋም ” ያሉ ሲሆን፣ በርካታ ፈተናዎች አሉብን፡፡አርሶ አደሩን እናደርሳለን ብለን ባሰብነው የምርታማነት ደረጃ ላይ አለማድረሳችን ትልቅ ፈተና ” ሆኖብናል ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ ዝቅተኛ እሴት ፈጣሪ መስኮች ብቻ የመሰማራት አዝማሚያ እንጅ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገውን እንቅስቃሴ መዋቅራዊ ለውጥ ሊያግዙና ሊያሳድጉ የሚችሉ ትልልቅ እሴት ፈጣሪ እንቅስቃሴዎች አለመደረጋቸውንም ገልጸዋል።
የክልሉ ቴክኒክ ሞያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዘላለም ንጉሴ በበኩላቸው ስርዓቱን ያጋጠሙት በርካታ ፈተናዎች እንዳሉ ገልጸው፤በተለይ ክራይ ሰብሳቢነት ትልቁ አደጋ በመሆን በከተሞች አካባቢ ገዝፏል ብለዋል፡፡
በገዢው ፓርቲ አመራሮች መካከል የትግል መቀዛቀዝ ፣በጽንሰ ሃሳብም ሆነ በክህሎት አቅምን የማጎልበት የተዳከመ ነገር መታየቱንም ተናግረዋል፡፡
ያመጣነውን ለውጥ እየተፈታተነው ያለው በኋላ ቀርነትና በክራይ ሰብሳቢነት በተግባር እየተከሰተ ያለው ሁኔታ መሆኑ የገለጹት የቀድሞው የባህርዳር ከንቲባና የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ያየህ አዲስ ሰራተኛው በሚፈጽማቸው ስራዎች በኩል ያለው ስልቹነት መታየቱ ስርአቱ በፈለገው ደረጃ ህዝብን ይዞ መጓዝ እንዳላስቻለው ተናግረዋል፡፡የገዢው መንግስት ህዝብን በሚፈጽማቸው ስራዎች አለማሳተፍና የአስገዳጅነት ባህሪ ማሳየቱ ጸረ ዲሞክራሲዊ አካሄድ የስርአቱ አደጋዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
በመግለጫው የተሳተፈፉት አመራሮች ኢህአዴግ በ24 ዓመታት አገዛዙ ችግሮችን መቅረፍ እንዳልቻለ ተናግረው፤ በየጊዜው የሚቀርቡትን ችግሮች በቀጣይ አሻሽላለሁ በማለት መናገሩ ልማዱ ነው ሲሉ ያክላሉ።

ሚያዝያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ቴሬንሴ ሊዮንስ በዋሽንግተን ፖስት ላይ “ነጻና ፍትሀዊ ምርጫን ከኢትዮጵያ ጋር ምን
አገናኘው?”በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሁፍ በመጪው ግንቦት 16 በ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ የመርሀግብር ማሟያ እንጂ ትርጉም ያለው እንዳልኾነ ገልጸዋል።  
ሂደቱ ከቅድመ-ምርጫ ጀምሮ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ እንዳልነበር በስፋት ያብራሩት ጸሃፊው ”ዜጎች አዲስ መንግስት የማይመርጡበት ትርጉም የለሽ ምርጫ”ሲል አጣጥለውታል። የአሜሪካ ምክትል የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ወንዲ ሸርማን ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ሀገር ማለታቸውና በመጪው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውንም ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ብለው ማሞካሸታቸውን ተችተዋል።
ጸሃፊው እንደሚሉት ምርጫው ለውጭ አገር ህጋዊ ተቀባይነት ማስገኛ ተብሎ በየጊዜው ከሚደረግ ይልቅ፣ በአገር ውስጥ ያለውን ህዝብ ለመቆጣጠርና አፈና ጉልበትን ለማሳየት ተብሎ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል። በጆርጅ ማሶን ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፀጻፊው ፣ ገዢው ፓርቲ በ2002 ምርጫ ካገኘው ውጤት ያልተናነሰ እንደሚያገኝም ገልጸዋል።


በገዢው የኢህአዴግ መንግስት ላይ የትጥቅ ትግልን እያካሄዱ የሚገኙ የተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ ጥምረት እና ውህደት የሚወስዳቸውን ውይይት መጀመራቸውን ባለፈዉ አርብ ይፋ አደረጉ ።


የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፥ የጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፥ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ፥ የአማራ ዴሞክራሲ ሀይል ነቅናቄ፥ እና የአርበኞች ግንቦት ፯ ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ የጥምረት ብሎም የውህደት ዉይይቶችን መጀመራቸውን አስታወቁ ።

“ሀገርን እና ህዝብን ለማዳን የጋራ ግብ አድርጎ ለመስራት” በሚል መርህ የተዘጋጀውን ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑን ንቅናቄዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል ።

በቅርቡ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኘው አርበኞች ግንባር፥ ከግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ጋር ውህደት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን አምስቱ ንቅናቄዎች በማካሄድ ላይ ያሉትን ውይይት አስመልክቶ ውጤቱን በቀጣይ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከድርጅቶቹ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ንቅናቄዎቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ከመቼውም ግዜ በላይ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይና መከራ ተባብሶ መቀጠሉን የገለጹት ድርጅቶቹ፥ አንድነትን በማጠናከር ሀገርንና ህዝብን ነጻ ማውጣት የሚገባበት ወቅት አሁን ነው ሲሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ አክለው አስታቀዋል።
የማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊ የነበረው አቶ አለነ ማህፀንቱ በትናንትና ዕለት ያለፍርድ ቤት ማዘዣ በደህንነት ኃይሎች ታፍኖ የተወሰደ ሲሆን፤ በኃይልና በድብደባ የኢሜል አድራሻውንና ፓስዎርድን ከወሰዱ በኋላ ጉለሌ ፖሊስ ጣቢያ አምጥተው እንዲታሰር አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የአንድነት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ በላይ ፍቃዱ እና ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ተክሌ በቀለ በተመሳሳይ ዕለት በደህንነት ኃይሎች ሲዋከቡ የዋሉ ሲሆን ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ተስጥቷቸወዋል።


እንግዲህ አንድነትን አፍርሰው፤ በህገወጥ መንገድ ለተላላኪዎቻቸው ካስረከቡ በኋላ፤ እንዲህ በሀገራችን እንኳ በሰላም መኖር እንዳንችል በወከባና በክትትል፤ በእስርና በማስፈራሪያ መከራችን የሚያሳዩን ምን ፍጠሩ እንደሚሉን ግልፅ አይደለም፤ ሰርተን መኖር አልቻልም፤ ወይ ይሰሩን ወይም በግልፅ ሀገሩን ልቀቁልን ይበሉንና ሀገር አልባ ሆነን እግራችን ወደ አመራው እንሂድላቸው፤ ቀድሞውስ መቼ ሀገር ነበረን፤ ሀገር ቢኖረንማ እንዲህ ሁሉም ነገር ባዕድ ሆኖብን ባልኖርን ነበር።

እኔ በሀገሬ ተስፋ ቆርቼ አላውቅም፤ እነዚህ ሰዎች ምን አድርጉ እንደሚሉን ግን አይገባኝም፤ በሆነ ባልሆነ ነገር በባነነ ቁጥጥር እኛን ማሰርና ማስፈራራት መፍትሄ ያደረጉት ነው የሚመስለው፤ ሰው እንዴት በሀገሩ በሰላም መኖር ይከለከላል፤ አሁን እኛ ምን እንዳናደርግ ነው የሚፈልጉት፤ በቃ በኃይል ፓርቲያችንን ሰርፈውን የለ ከዚህ በላይ ምን ይፈልጋሉ፤ የግል ንብረታችንን እንኳ ማውጣት እኮ አልቻልም፤ ለምሳሌ የእኔ አንድ አዲስ ኮት እዚያ ቀርቷል፤ ቢሮዬ ውስጥ ለምሳ እንደወጣሁ ነበር ፖሊሶች መጥተው ጽ/ቤቱን የወረሩት፤ እኔም ምናልባት ያመጧቸው ሰዎች ኮት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ዝም አልኩ፤ መቼስ የእኔ ኮት ከአንድነት አይበልጥ!
በትግርኛ አንድ ተረት አለ፤ “ወይ እንዳሉህ ሁን ወይም ሀገራቸውን ልቀቅላቸው” የሚል፤ ጎበዞቹ ይህን ተረት በተግባር እያዋሉት ይመስላሉ፤ ልዩነቱ ሀገሩ የእኛም መሆኑ ላይ ነው! ሀገራችን ለቀን ወዴት እንሂድ እኔማ በእንዲህ ዓይነት ስርዓት ስር መኖር እንዴት እንደመረረኝ… መግለፅ ከምችለው በላይ ነው! ሀገር እንዲህ ያስጠላል፤ እንዲህ ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል!
አሰግድ ታመነ
ከየመን የተመለሱ ስደተኛ ኢትዮጲያውያን ከቦሌ አየር ማረፊያ ተይዘው በመአከላዊ እስር ቤት ታስረዋል በየመን በቀተስተው ግጭት የተነሳ ከየመን ወደ ስአውዲ ሊሻገሩ ሲሞክሩ በስአውዲ ፖሊስ ለቀናት ከታስሩ በህዋላ አምስት የሚሆኑ ኢትዮጲያውያን ከ4 ቀናት በፊት ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም በቦሌ አየረ ማረፊያ በፖሊሶች ተይዘው ወደ መአከላዊ ውስር ቤት መወስዳችውን የBBN ምንጮች አረጋግጠዋል ። እስረኞቹን ቤተስቦች እስረኞቹን ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ ባይሳካም በመአላዊ ደጃፍ ላይ ከደቡብ አፍሪካ የተመለሱ እስረኞችም እንዳሉ ከጠያቂዎች መግንዘብ ችለዋል ።

አሰግድ ታመን
ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ በቀረው አምስተኛው አገርአቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ተወዳዳሪ ከሆኑ ፓርቲዎች መካከል ሰማያዊ ፓርቲ እና በመድረክ ስር ያለው ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ “በአባሎቻችን እና እጩዎቻችን ላይ እንግልት፣ እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው ነው” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስታወቁ።

የዓረናፓርቲሊቀመንበርአቶብርሃኑበርሄ “በቅድመ ምርጫ ዝግጅት ያገጠመን ችግር ከባድና ውስብስብ ነው። ከጥላቻ ፍረጃ እሰከ ጥብቅ ክትትልና ማሰፈራራት፣ ወከባ፣ ድብደባና እስር ተደጋግሞ ያጋጠሙን ችግሮች መሆናቸውን በጊዜው ሲገለፅ ቆይቷል። ቢሆንም የተወሰኑ አብነቶች ለመግለፅ በምእራባዊ ትግራይ ዞን ለህዝብ የሚታደሉ ፅሑፎች ከመቀማት እስከ ከባድ ድብደባ ተፈፅሞብናል” ብለዋል።

ሊቀመንበሩ አያይዘውም በአፅቢ የምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደር፣ በቆላ ተምቤን ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደር፣ ባታሕታይ ማይጨው /አክሱም አካባቢ/ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደር እጩ ተወዳዳሪ መሆናቸው እየታወቀ የምርጫ ህጉ ያረጋገጠላቸውን ያለመከሰስ መብት በመጣስ ታስረው ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደርጎ በስንት አቤቱታ አሁን የተፈቱ ቢሆንም የመቀስቀስ መብታቸው ተገድቦ ቆይቷል” ብለዋል።

ዓረና ትግራይ ፓርቲን ወክለው በመቐለ ከተማ የሚወዳደሩት የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው “ካለፉት ምርጫዎች በበለጠ በዚህ ምርጫ ምህዳሩ የጠበበ ነው” በማለት ተናግረዋል። አቶ ገብሩ አያይዘውም “የምርጫ ታዛቢዎች የተመረጡት የፓርቲያችን ውክልና እና እውቅና ሳይኖረው ነው። ብዙዎቹ የምርጫ ታዛቢዎች በግልጽ የገዥው ፓርቲ አባላት መሆናቸው ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በመራጮች ምዝገባ የመራጭነት ካርድ ገዥው ፓርቲ ለሚፈልጋቸው ሰዎች በየቤታቸው እያንኳኳ ሲያድል ለማይፈልጓቸው ደግሞ ሊመዘገቡ እንኳ ሲሄዱ ካርድ ጨርሰናል በማለት መልሰዋል። ለእዚህ አንዱ ምሳሌ እኔ ነኝ። እኔ ተዋዳዳሪ ብሆንም የመራጭነት ካርድ የለኝም” ብለዋል።

የዘንድሮውን ምርጫ “ከአፍሪካ ህብረት ውጭ ሌላ የውጭ አገር ታዛቢ የሌለበት ምርጫ ነው” ያሉት አቶ ገብሩ በእጩዎቻቸው ላይ እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑንም ተናግረዋል። “በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚወዳደሩ እጩዎቻችን እየተንገላቱ ነው። በአጽብሂ የሚወዳደረው እጯችን ታስረው ቆይተው በቅርቡ ነው የተለቀቁት። ይህንን ሁሉ ስታይ የፖለቲካ ምህዳሩ ካለፉት ዓመታት ምርጫዎች በበለጠ የጠበበ መሆኑን ነው” በማለት ተናግረዋል። ዓረና ትግራይ ፓርቲ በትግራይ ክልል ከሚገኙ 38 ምርጫ ክልሎች በ29 የምርጫ ክልሎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በ28 ምርጫ ክልሎች ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ዕጩዎችን አቅርቦ እንደሚወዳደር ሊቀመንበሩ አቶ ብርሃኑ በርሄ ተናግረዋል። አቶ ገብሩ አስራት ዓረና ትግራይን ወክለው፣ ህወሓት/ኢህአዴግን ወክለው ከሚወዳደሩት አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ ጋር በመቐለ ይወዳደራሉ። አቶ ብርሃኑ በርሄ በመቀሌ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ሲሆን የቀድሞዋ ታጋይ አረጋሽ አዳነ ደግሞ በዚያው መቀሌ ምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወዳደሩ ከፓርቲው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ ዜና ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት ለምርጫ ቅስቀሳ የለጠፍኩት ፖስተርና ባነር እየተቀደደብኝ ነው፤ እኔ የለጠፈኩትን ፖስተር እየገነጠለ በተከለከሉ ቦታዎች የሚለጥፍ ኃይል አለ፤ በፓርቲያችን ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል ሲል አስታውቋል። የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሰንደቅ ጋዜጣ “ለምርጫ ቅስቀሳ በምንወጣበት ጊዜ የምርጫ መቀስቀሻ ወረቀቶችን የመንግስት ካድሬዎች ቀምተው ተሰውረዋል” ሲሉ ተናግረዋል። እንዲሁም በጋምጎፋ ዞን በአንድ ቀን የምርጫ ቅስቀሳ ብቻ 17 የፓርቲው አባላት መታሰራቸውንና እስከትናንት ማክሰኞ ድረስ እንዳልተፈቱ ገልጸዋል።

አቶ ዮናታን ጨምረው ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ተጠርቶ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተከሰተው ሁከትና ረብሻ ምክንያት ተጨማሪ ሶስት የፓርቲው አባላት መታሰራቸውን ተናግረዋል። የታሰሩት የፓርቲው አባላት ናትናኤል የዓለምዘውድ፣ ሜሮን አለማየሁና ደብሬ አሸናፊ ናቸው። የፓርቲው አባላት የታሰሩት ከቤታቸው ተወስደው መሆኑን የገለፁት አቶ ዮናታን ሰላማዊ ሰልፉ ተካሂዶ በነበረበት እለት ከታሰሩት አምስት የፓርቲው አባላት በተጨማሪ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤ እና ማቲያስ መኩሪያ የሚባሉ አባሎች በድጋሚ ተይዘው መታሰራቸውን ተናግረዋል። በቁጥጥር ስር ከሚገኙት 11 የፓርቲው አባላት መካከል አራቱ እስከ ግንቦት 24 ድረስ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የተፈረደባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ስለታሰሩት የፓርቲው አባላት በመንግስት በኩል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ እውነቱ ብላታ ስልክ ስንደውል ስብሰባ ላይ መሆናቸውንና ስለጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸውልናል።

ቀደም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት ዘጠኝ ቀን በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም በእለቱ ለመራጩ ህዝብ የምርጫ ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን በመሆኑ ምንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ የተከለከለ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል። የቦርዱን ውሳኔ ተከትሎ ፓርቲው የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪውን ሰርዟል ወይስ ለሌላ ጊዜ አራዝሟል? ተብለው የተጠየቁት አቶ ዮናታን “ወደ ፊት የምናሳውቅ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

በይርጋአበበ
ምንጭ፦ ሰንደቅ
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ከውህደቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አርበኛ ታጋዮች ከትናንት በፊት እሁድ ግንቦት 2 2007 ዓ.ም ደማቅና ታሪካዊ በሆነ ስነ-ስርዓት አስመረቀ፡፡
እነዚህ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመጀመሪያ ዙር ተመራቂ አርበኛ ታጋዮች ለሦስት ተከታታይ ወራት የተሰጣቸውን የፖለቲካ፣ የወታደራዊ እና እንዲሁም የመረጃና ደህንነት ስፋትና ጥልቀት ያላቸውን ትምህርቶች በመውሰድ በብቃት የተወጡና በተግባር የተፈተኑ መሆናቸውን የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አርበኛ ታጋይ ተስፋሁን ተገኘ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል፡፡
አርበኛ ታጋዮች በተመረቁበት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የሌሎች ደርጅቶች አመራሮችና ልዩ ልዩ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር አርበኛ ታጋይ ማዕዛው ጌጡ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ታጋዮች ከውህደቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመመረቃቸው ታሪካዊና ልዩ እንደሆኑና ነባሩን ሰራዊት ሲቀላቀሉ ተረክበው በረሃ የወረዱበትን ታላቅ የህዝብ አደራ በማናቸውም የነፃነት ትግል ሜዳ ላይ ሙሉ በሙሉ መወጣት ስለመቻላቸው ታላቅ ዕምነት እንዳላቸውና እንዲሁም የህወሓት አገዛዝ ግብአተ መሬት መቃረቡንም ጭምር ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ወታደራዊ መምሪያ ዋና ኃላፊ አርበኛ ታጋይ ኮማንደር አሰፋ ማሩም በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ የህወሓት አገዛዝ ህዝባዊነትና ወታደራዊ አቅም እየተሸመደመደ በእጅጉ እየተዳከመ ባለበት ሁኔታ በተቃራኒው አርበኞች ግንቦት 7 ሰፊ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ ወታደራዊ ጡንቻውም እየፈረጠመ የመጣ መሆኑን፤ የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ አንገቱን የደፋው ህዝብ አለንላችሁ ተብሎ ቀና እንዲል የሚደረግበት ጊዜ መድረሱን እና ከእንግዲህ ወዲህ ማናቸውም ምድራዊ ኃይል አርበኞች ግንቦት ሰባትን ፋጽሞ ሊያቆመው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
04 09 2007 ዓ.ም
Source: የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ

በዋሽንግተን ዲሲ ማንደሪን ኦሪየንታል ሆቴል ድንገት የተገኙት የወያኔው መንግስት መከላከያ ሚኒስተር ጄነራል ሳሞራ የኑስ በኢትዮጵያዊያኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸው ውርደትን መከናነባቸውን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመለከተ::
በአንድ ለሊት አዳር 12 ሺህ 700 ብር በሚከፈልበት በማንደሪን ኦሪየንታል ሆቴል ያረፉት ጀነራል ሳሞራ የኑስ ከዋሽንግተን ዲሲ ግብረሃይል ወጣቶች ጋር ፍጥጫ ገጥመው ከፍተኛ የሆነ ግብግብ ተፈጥሯል:: አካባቢው በዲሲ ፖሊሶች የታጠረ ሲሆን ሳሞራም ካረፈበት ከዚህ ሆቴል ሊወጣ እንዳልቻለ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ጠቁመዋል::
ኢትዮጵያውያኑ “ኢትዮጵያውያንን የሚያሰቃይ ወንጀለኛ ለፍርድ ይቅረብ” በሚል ሳሞራ ላይ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ናቸው::
በሽንግተን ዲሲ መጥተው በኢትዮጵያውያኑ ውርደትን ከተናነቡ የወያኔ ተላላኪ ባለስልጣናት ውስጥ ስብሃት ነጋ; ሬድዋን ሁሴን; ሶፊያን አህመድና ሌሎችም ይገኙበታል::
ግብግቡ አሁንም የቀጠለ ሲሆን የደረስንበትን መረጃ እናሳውቃችኋለን::
“ወያኔን በሰላማዊ ትግል አይወድቅም ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ በትጥቅ ትግል መታገል ነው” ወጣት ተስፋሁን አለምነህ
የቀድሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው ወጣት ተስፋሁን አለምነህ በአገር ቤት የወያኔን አገዛዝ በሰላማዊ ትግል ታግሎ መጣል አይቻልም ብሎ በመወሰን እሱና ሌላው የመኢአድ አባል ደሳለኝ ሲሳይ ከበርካታ ወጣቶች ጋር ኤርትራ የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ሰሞኑን መግባታቸውን ለህብር ሬዲዮ ከስፍራው በሰጠው አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ገለጸ።
<<በአስቸጋሪ ሁኔታ አልፈን የቀድሞው መኢአድ ግማሹ ክንፍ ኤርትራ ገብተናል>> በሚል አርዕስት ለህብር የላከውን ማስታወሻ እውነተኛነት ለማጣራት ባቀረብነው ጥያቄ የኤርትራ ስልኩን ልኮልን እሱም ሆነ ሌሎቹ በትጥቅ ትግል ስርዓቱን ለመጣል ኤርትራ የገቡ ወጣቶች መኖራቸውንና  ገልጿል ።
በአገር ቤት በሰላማዊ ትግዩ አምንን በተደጋጋሚ ስንታሰርና መከራ ሲደርስብን ነበር ያለው ተስፋሁን ሰላማዊ ትግሉ መሪያችን ፕሮፌሰር አስራትን ጨምሮ ብዙዎችን ከማስበላት ያለፈ ስርዓቱን ለማዳከም ባለመቻሉ የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ኤርትራ መግባታቸውን አረጋግጦልናል ።
<<ወያኔን በሰላማዊ ትግል አይወድቅም ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ በትጥቅ ትግል መታገል ነው>> ያለው ወጣት ተስፋሁን አለምነህ ስርኣቱን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ታግሎ መጣል አለመቻሉን ጠቅሷል።
ከወጣት ተስፋሁን አለምንህ ጋር ያደረግነውን አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ዘግይተን እናቀርባለን።
(ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችንና ከዘ-ሐበሻ በተጨማሪ ዘወትር በ7124328451 ማዳመጥ ይቻላል)
ምንጭ – ህብር ሬዲዮ
ኢሳት ዜና :- ጠ/ሚኒስትሩ ሚኒስትሮችንና የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናትን በሙሉ ሲያስገመግሙ ከከረሙ በሁዋላ በመጨረሻ ራሳቸው 15 ሰአታት በፈጀ ግምገማ ተገምግመዋል። አብዛኞቹ በአቶ ሃይለማርያም የስራ ችሎታና አመራር ላይ ዘለፋ ቀረሽ ሂስ አቅርበውባቸዋል። አቶ ሃይለማሪያም የቀረበባቸውን ሂስ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸው ግምገማው ረጅም ጊዜ እንዲወስድ አድርጓል። ግምገማው ከምርጫው በሁዋላ የሚቀጥሉና የማይቀጥሉ ባለስልጣናትን ለመለየት እና ግድፈታቸውን አርመው ሰርተው እንዲጠብቁ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተነግሯል።
አቶ ሃይለማርያም ከህወሃቶቹ ከአቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ስብሃት ነጋና አስመላሽ ወልደስላሴ የሰላ ትችት ሲቀርብባቸው፣ ከራሳቸው የደህዴን አባላት ከሆኑት ከአቶ ሬድዋን ሁሴንና ሙፈሪያት ከሚልም ዘለፋ ቀረሽ ትችት አስተናግደዋል። አብዛኞቹ ብአዴኖች፣ አቶ በረከት ሳይቀሩ የአቶ ሃይለማርያምን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ አስገብተዋል። በመጠኑም ቢሆን የራሩላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ብቻ ናቸው።
አቶ ሃይለማርያም እንቅስቃሴያቸውንና የሌሎችን ሰዎች እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠሩ የስለላ ካሜራዎች እንዳይተከሉ፣ በጽህፈት ቤታቸው ያለውም እንዲነሳ ማድረጋቸው ከደህንነት ሃይሉ ጋር አጋጭቷቸው እንደቆየና ውዝግቡ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ መሆኑ ተወስቷል።
አቶ ሃይለማርያም አንዳንድ መልሶችን ሲሰጡ እንባ ይተናናቃቸው ነበር። በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ደግሞ በእልህና በወኔ ተሟግተዋል። አቶ ስብሃት ነጋ በአቶ ሃይለማርያም ላይ ለሰነዘሩት ትችት፣ አቶ ሃይለማርያም ” ስብሃት በጣም ይጮሃል፣ እንዳሞራ ሁሉ ይዞረኛል፣ እዚህ ሳወያይም ይጮሃል፣ አለቃ መሆን ችግር ነው ብየ ዝም አልኩ። ንግግር ከመልክ ያምራል ይባላልና ያሳሳትኩት ነገር ካለ አርማለሁ። በአባባል ክፍተት ካለ ይቅርታ” በማለት መልሰዋል።
የግምገማውን ዝርዝር ሪፖርት በነገው ዘገባ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እናወዳለን።



አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ውህደት አድርጎ አንድ ከሆነ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ አርበኛ ታጋዮችን ማስመረቁ ተሰማ::
አርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮቹን በኤርትራ ያስመረቀው ያለፈው እሁድ ግንቦት 2 ነው:: ከኤርትራ ለዘ-ሐበሻ የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ኤርትራ በመግባት አርበኞች ግንቦት 7ን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ:: የምርቃቱን ፎቶዎች ይመልከቱ::
Source: Zehabesha
ሰሞኑን በህውሓት/ኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ባሉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰማያዊ ፓርቲ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘመተ ያለውን የስም ማጥፋት ፕሮፓጋንዳ በአትኩሮት ሲከታተለው ቆይቷል፡፡ በዚህም የህዝብ ንብረት የሆኑ ሚዲያዎች፤ ለህዝብ አገልግሎትና በህዝብ ግብር በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚተዳደሩ የማህበረሰቡ የአገልግሎት ተቋማት ጭልጥ ብለው የሰማያዊ ፓርቲ ስም በማጉደፍ እና በማብጠልጠል ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን በትዝብት ተመልክተናል፡፡
Semayawi party to welcome Andinet members
ሰማያዊ ከተቋቋመ ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ በደሎችን በሀገርም ሆኖ በውጪ ሲፈፀም ዝም ብሎ የመመልከት ትዕግስት ኖሮት አያውቅም፡፡ ይህ በዋነኝነት ፓርቲው የተቋቋመለት መርህ ነው፡፡ በግራዚያኒ ስም ለሚሰራ ሃውልት ተቃውሞ ለማሰማት አስፈላጊውን የህግ መስፈርት አሟልተን ባለበት ሁኔታ በገዢው ፓርቲ ትእዛዝ አባላቶቻችን ተደበደቡ፡፡ በሳውዲ አረቢያ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው ኢሰብአዊ በደል ሰቆቃቸውን ለማሰማት በጠራነው ሰልፍ እንደገና በመንግስት ትእዛዝ አባላቶቻችን ላይ ድብደባና እስር ተፈጸመባቸው፡፡ በቅርብ በሊቢያ፣ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በየመን በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ የደረሰውን እጅግ ሰቅጣጭ እና በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ብሔራዊ ውርደት ሰማያዊ ፓርቲ አስቆጭቶታል፡፡ በዚህም የተነሣ እነዚህ በደሎች መድረሳቸው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በንቃት እየተከታተለ መረጃው ለህዝብ እንዲደርስ እያደረገ ጎን ለጎን መንግስት ለወገኖቻችን የድረሱልኝ ጥሪ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ፓርቲያችን ሲያሳስብ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ይኸንን ዘግናኝ እና አረመኔያዊ ድርጊት ማውገዛችን እና መቃወማችን ከዛም አልፎ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመ ተግባር መከታተላችን ፓርቲው ሊያስመሰግነው ሲገባ ይልቁንም ገዥው ፓርቲ በተለያዩ የመንግሰት ሚዲያዎች የሰማያዊ ፓርቲ ስም ለማጠልሸት ሲሯሯጡ ማየት ትዝብት ውስጥ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በህግም የሚያስጠይቅ ጭምር ነው፡፡ መንግስት ሃላፊነቱን እና ተግባሩን በመመርመር በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ብሔራዊ ውርደት ዳግመኛ እንዳይፈጸም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ገዢው ፓርቲ ከሃገር ብሄራዊ ጥቅም ይልቅ የድርጅቱ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ በልጦበት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
ከዛም አልፎ ተርፎ ዜጎች በሀገራቸው በሚደርስባቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች ዙሪያ ተነጋግሮ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እየተሳናቸው በየበረሃው ሲሰደዱ የሚደርስባቸው ስቃይ አልበቃ ብሎ አይኤስ አይኤስ በሚባል አሸባሪ ቡድን የደረሰባቸውን ዘግናኝ በደል ሃዘኑ ገና ከልባችን ሳይጠፋ በሃገር ውስጥ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚንቀሳቀስ ሰማያዊ ፓርቲን ከእንደዚህ አይነት ነውረኛ እና ሰይጣናዊ ተግባር ከሚፈጽመው ድርጅት ጋር ህብረት እንዳለን ለማሣየት መሞከሩ እጅግ ጸያፍና ለዜጎቹ ያለውን ንቀት ማሳያ ጭምር ነው፡፡
ሰማያዊ በዜጎቻችን ላይ ከ1ዓመት ከ6 ወር በፊት በሳውዲ አረቢያ እንዲሁም በተለያዩ አገራት አገራቸውን በመንግስት የአስተዳዳር ደካማነት በተፈጠረው ችግር ምክንያት ጥለው በመሰደዳቸው፤ ለተለያየ ችግር እና ብሔራዊ ውርደት የሚዳረጉ ወገኖቻችንን ችግር ለመፍታት ጥሪ ለመንግስት አድርገን የአንድ ሠሞን ጫጫታ ከመሆን አልፎ ለዘለቄታው ችግሩን ለመፍታት ባለመቻሉ ለዳግመኛ ዘግናኝና አረመኔያዊ ስቃይ ዜጎቻችንን መዳረጉ በገሀድ የሚታይ እውነታ ሆኗል፡፡
ስለዚህ መንግስት ሰማያዊን በመውቀስ ፋንታ ለድርጊቱ ቀጥተኛ ተጠያቂ የሆነውን የድርጊቱ ፈፃሚ አይኤስ አይኤስ ተጨባጭ አፀፋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አቅም እንደሌለው ጭምር አስመስክሯል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው የሚደርስባቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንዲሰደዱ የዳረጋቸው የተሣሣተ አመራር የያዘው ህወሓት/ኢህአዴግ መሆኑን ተረድቶ ነገ ከታሪክ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል ሰማያዊ ፓርቲ ያስገነዝባል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በአዋጅ የተሰጠውና ስልጣን ወደጎን በመተው ሰማያዊ ፓርቲ የስራ እንቅስቃሴውን ለመተለም የሚያደርገውን ተግባር በህወሓት/ኢህአዴግ እና በሌሎች የሚደረግበት ጣልቃ ገብነትን በዝምታ ማለፉ ፓርቲያችንን እጅግ ያስቆጣ ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕጋዊነት እውቅና የሰጠውን ተቋም ህወሓት/ኢህአዴግ እና ደጋፊዎች በአሸባሪነት ሲፈርጁ ምንም ለማለት አለመፈለጉ ሰማያዊ ፓርቲ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነቱ ላይ ለሚያነሳው ጥያቄ ዋንኛ ማሳያ ነው፡፡
ሰማያዊ በአገራችን ጠንካራ አማራጭ ፓርቲ እንደሆነ አምነው ከጎኑ የቁሙትን በሙሉ እያመሰገነ፤ ፓርቲው የህዝብ አማራጭነቱን ለማጥፋት በከፍተኛ ጥረት የተሰማራው ህወሓት/ኢህአዴግ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ እያስጠነቀቀ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ እየፈፀመበት ያለው የስም ማጥፋት ውንጀላ ሰማያዊ ፓርቲ ከጀመረው ትግል ፈፅሞ እንደማይገታው በፅኑ ያሳውቃል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበ
በጋሞጎፋ ዞን በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እየታደኑ እየታሰሩ መሆኑን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከትናንት ሚያዝያ 30/2007 ዓ.ም ጀምሮ ጋሞ ጎፋ ዞን ጎፋ ወረዳ ሳውላ ከተማው ውስጥ በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸውን የጋሞ ጎፋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በትናንትናው ዕለት በጋሞጎፋ ዞን ዳራማሎ ወረዳ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ 17 የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ታስረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጋሞጎፋ ዞን ቦንኬ ወረዳ ለፖሊስ ‹‹ለሰማያዊ ፓርቲ የሚቀሰቅስ ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ውሰዱ›› የሚል ትዕዛዝ መተላለፉን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡
| Copyright © 2013 Lomiy Blog