እኩልነት ወይስ የበላይነት? ኢትዮጵያን ለመምታት በማጭበርበር የተገኘ ተራድኦ

ጌታቸው ኃይሌ :-

መግቢያ፤ 

የዛሬው ድርሰቴ ለመግለጥ የሚሞክረው የዘወትር ድምፃቸው "ተበድለናል" የሚለው፥ የሌላው በደል ግን ደንታቸው 
ያልሆነ፥ የኦሮሞስላሞች አክራሪዎችን ድብቅ ዓላማ ነው። የፈለገ እስላሞሮሞች አክራሪዎች ሊላቸው ይችላል። ዋናው ቁም 
ነገር (1) ኦሮሞ መሆናቸው፥ (2) እስላሞች መሆናቸው፥ (3) አክራሪዎች መሆናቸው፥ (4) የሌላው ነገድ እስላም አክራሪዎች 
የሚደግፏቸው መሆኑ፥ (5) የሚፈልጉት የበላይነት መሆኑ፥ ያ ካልሆነ ኢትዮጵያን ማውደም መሆኑ ለአገር ወዳዱ ሕዝብ 
ግልጽ እንዲሆን ነው። እነሱ ግን "ኦሮሞ" መባልን ይመርጣሉ። ለብልሃታቸው ነው፤ ምክንያቱም፥ ኦሮሞስላሞች ወይም 
እስላሞሮሞች ብቻ መባሉ እውነትነት ቢኖረውም፥ በነጠላው "ኦሮሞ" መባሉ ክርስቲያን ኦሮሞዎችንና እናት አገራቸውን 
የሚወዱ እስላም ኦሮሞዎችን ስለማያካትት፥ የድምፃቸውን ቊጥርና ጉላት በሰሚያቸው ዘንድ ይቀንስባቸዋል። 

የጽሑፌ ርእስና ይዞቱ የሚያመለክተው ይኸንኑ ለማብራራት ነው። ለምሳሌ፥(1) ጨርጨር ውስጥ ባለው በጥንቱ የአሰቦት 
ገዳም ውስጥ በሚኖሩ መነኮሳት ላይ የፈጸሙትን ግድያ የኦሮሞዎች ሁሉ ወንጀል ለማድረግ፥(2) በኦሮሞ ስም ቤተ 

ክርስቲያን ለማቃጠል፥ (3) በኦሮሞ ስም ካህናት ከነነፍሳቸው ገደል ለመስደድ፥ ለዚህ ሁሉ የዛሬው ታሪካችን ለመዘገበው 
ጥፋት "አል-ኢቲሐድ አል-ኢስላሚያ"፥ ወይም "አል-ሸባብ አል-ኦሮሚያ"፥ ወይም "የእስላም ነፃ አውጪ ግምባር" ከመባል 
ይልቅ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ተቆርቋሪ መስሎ መቅረብ ብዙ ጥቅም አለው፤ አንደኛ፥ የእስላም አክራሪዎች ንቅናቄ በዓለም 
ስለተጠላ፥ ስሙ ባይነሣ ይሻላል፤ ሁለተኛ፥ የጎሳዎችን መጨቆን ማንም ስለማይወደው ለጭቁን ኦሮሞዎች የተጨነቁ መስሎ 
መታየት አይዟችሁ ባይ ሊያስገኝ ይችላል። በእነዚያ ላይ እንደ አቶ ተስፋየ ገብረአብ አማርኛቸው የኔ ብጤውን ሳይቀር 
የሚደልሉ የቱልቱላ ጸሐፊዎች አሉላቸው። ባጭሩ፥ የሚያሳዩት ገጽታቸው ኢትዮጵያን ለመምታት የተጭበረበረ ተራድኦ 
ለማግኘት የቀረጹት ነው። 

ግን ትንተናዬን ለመቃወም፥ ከዚህም፥ ከዚያም፥ ብቅ ብቅ ሲሉ፥ ማንነታቸውን መግለጣቸው መሆኑን ልብ ሳይሉት 
ቀርተዋል። ለምሳሌ፥ ትናንት በክርስቲያኖቹ ላይ ያ ሁሉ ወንጀል ሲፈጸም ዝም ብለው፥ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበብ 
ያስከለከሉት የአባ ባሕርይ ድርሰቶች በነፃ ሲለቀቅ ሲያዩ እሪ አሉ። [በነገራችን ላይ፥ መጽሐፉን የሚፈልግ ethiopiawi.net 
ላይ ያገኘዋል።] መጽሐፍ እንዳይነበብ ከማድረግ የበለጠ ኋላ ቀርነት የለም። ኢትዮጵያን አገራችን ብለው ለዲሞክራሲ 
የሚታገሉ እስላሞችና ሌሎች ኦሮሞዎችም እንደማይታለሉላቸው በተግባር አስመስክረዋል፤ ለዲሞክራሲ በመቆማቸው 
የቃሊቲን እስር ቤት ሞልተውታል። የቀራቸው እነዚህን የኦሮሞ ልብስ የለበሱ ውስጣቸው ግን ተናካሽ ተኵላዎችን በይፋ 
ማውገዝና በስማቸው እንዳይጠቀሙ መከልከ ነው። 

እነዚህ ተኲላዎች ዓላማቸውን ለመምታት ተቃራኒ ሐሳቦችን በማጭበርበር ለማስማማት ሞክረዋል፤ ይኸውም፥ ኢትዮጵያ 
ውስጥ "ከጥንት ጀምሮ ነበርን" ማለትንና "አልነበርንም፤ የኢትዮጵያ ታሪክም ታሪካችን አይደለም" ማለትን ነው። ይህ 
እንኳን "የሌሊት ወፍ አቋም" ስለሆነ፥ እንደኔ እንደኔ ቢተዉት ይሻላል። ከ"አለን" እና ከ"የለንም" አንዱን ይያዙ። 
እንደማውቀው ከሆነ ግን፥ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ከቦታ ወደቦታ ፈለሱ እንጂ፥ ሁል ጊዜም የኢትዮጵያ ንጉሥ 
በሚያስገብረው ሀገር ላይ ነበሩ። ታዲያ በኢትዮጵያ እየኖሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ ሲሠራ፥ የግዕዝም ሆነ የአማርኛ ሥነ 
ጽሑፍ ሲዳብር፥ ተሳታፊዎችና አስተዋፅኦ አድራጊዎች እንጂ፥ ቁጭ ብለው ተመልካቾች አልነበሩም። 

የአክራሪዎቹ ስሕተት፡ (ሀ) የሀገራችን ስም፤ 

ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች እንዳይታለሉ፥ ታሪክ እንዲያነቡ ልጋብዛቸው። በነፃ ለማግኘት በሚቻለው በየአባ ባሕርይ 
ድርሰቶች መጀመር ይችላሉ። ሌሎቹ የታሪክ መጻሕፍት እዚህ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ተዘርዝረዋል። ኦሮሞዎች 
የተሳተፉባቸውን አንዳንድ ድርጊቶች ለናሙና ያህል እዚህም እጠቁማለሁ። ግን የእስላሞሮሞ አክራሪዎችን አቋም ሆን ብዬ 
ያበላሸሁት እንዳይመስልብኝ፥ መጀመሪያ የሚሉትን እንደተረዳሁት ላቅርበውና መሳሳታቸውን ላሳይ። እንዳነበብኩትና 
እንደሰማሁት፥ እነሱ የሚሉት እንዲህ ነው፤ 

ዛሬ የምናውቃት ኢትዮጵያ ግዛቷ የተወሰነው በአፄ ምኒልክ መሬት ማስፋፋት ጊዜ ነው። ያም እሳቸው 
ያስፋፉት ግዛት ኢትዮጵያ የሚል ስም የወጣለት አሁን በኛ ዘመን እንጂ፥ እኛን የማያካትተው ከአፄ ምኒልክ 
መሬት ማስፋፋት በፊት የነበረው ግዛትማ ስሙ አቢሲኒያ ነበር። 2 


ይኸንን ነው የሚሉት። የዚህ ሐሰት ምንጭ Bonnie K. Holcom እና Sisai Ibsa The Invention of Ethiopia በሚል 
ርእስ የጻፉት መጽሐፍ ነው። ሐሰቶቹን በማስረጃ ልዘርዝራቸው፤ 

ኢትዮጵያውያን "ዓለም ሳይፈጠር፥ ዘመን ሳይቈጠር" መንግሥት ካቋቋሙ ጀምሮ ሀገራቸውን የሚጠሯት "ኢትዮጵያ" እያሉ 
ነው። ይኸንን ከየትኛውም ዘመን ታሪካችን ምንጭ እየጠቀስኩ ልረታ እችላለሁ። ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን ሲጽፉ 
ሀገራቸውን (ሰፈራቸውን ማለቴ አይደለም) "ኢትዮጵያ" ከማለት ይልቅ አንድ ጊዜ እንኳን "አቢሲኒያ" ሲሉ ከተገኙ 
"የስፖርት ፈጣን መኪና እሰጥ" ብዬ እሟገታለሁ። (ገና ለገና የሚረታኝ አይኖርም ብዬ ላገኘው በማልችል "በሰጋር በቅሎ" 
አልሟገትም።) 

እስላሞሮሞ አክራሪዎችንና ጸሐፊዎቻቸውን ያሳሳቷቸው እነማን እንደሆኑ ግን አውቃለሁ፤ ፈረንጆች በየቋንቋቸው ሀገራችንን 
አንድ ጊዜ Ethiopia አንድ ጊዜ Abyssinia ይሏት ነበር። የፈረንጅ ጸሐፊዎች ሀገራችንን በፈለጉት ስም ቢጠሯት 
የመቆጣጠር ሥልጣን አልነበረንም። ሆኖም፥ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፥ ያውም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ፥ "ተዉ 
አታወላውሉ፤ ሀገራችንን Ethiopia በማለት ብቻ ጽኑ" የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ስለተሰጠ፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተጻፉ 
የታሪክ መጻሕፍትና መዛግብት ሁሉ ኢትዮጵያን Ethiopia ነው የሚሏት። እስላሞሮሞ አክራሪዎች፥ ሀገሪቱ "ኢትዮጵያ 
የሚል ስም የወጣላት አሁን በኛ ዘመን ነው" የሚሉት ይኸን ይዘው ነው። አሁን እንግዴህ ፈረንጆቹ "Abyssinia" 
ማለታቸውን ከተዉ በኋላ ወደኋላ ሄዶ "አቢሲኒያ" እንበላት ማለት ኦሮሞዎችን ወደኋላ ሄዶ "ጋላ" እንበላቸው እንደማለት 
ነው። ይኸ አንዱ ስሕተት ነው። 

የአክራሪዎች ስሕተት፡ (ለ) የኢትዮጵያ ምድርና ሕዝቧ፤ 

ሁለተኛው ስሕተት ፈረንጆች "አቢሲኒያ" የሚሉት መሬት ስለሚያካትተውና ስለሚኖርበት ሕዝብ የተጻፈው ነው። ለዚህ 
ሁለት ዓይነት ምንጮች አሏቸው፤ (1) የአውሮፓ ቅኝ አገዛዝ ኢትዮጵያን ከመክበቡ በፊት "አቢሲኒያ" የሚሉት ከቀይ ባሕር 
እስከ ነጭ ዓባይ ድረስ ያለውን ምድር ነበር። ለምሳሌ ያህል በሳሙኤል ጎባት መጽሐፍ (Samuel Gobat, Journal of 
Three Years' Residence in Abyssinia, 1851) ውስጥ የተጻፈውን መቅድም ማንበብ ይበቃል። (2) በኋላ ግን "አሞራን 
ለመብላት የፈለገ ጅግራ ይለዋል" እንደሚባለው፥ አገራችንን ሊቆርሱላት ሲያስቡ፥ "አቢሲኒያ ትግሬዎችና አማሮች 
ከሰፈሩበት ምድር አያልፍም" ማለት አመጡ። አንድ ዋይልደር የሚባል የእንግሊዝ ሰላይማ ከመቀሌ ተነሥቶ ወደ አዲስ 
አበባ ያደረገውን ጉዞ ሲገልጥ (Augustus B. Wylde, Modern Abyssinia, 1901) "ከአቢሲኒያ ተነሥቼ ሸዋ ገባሁ" ብሎ 
ጽፏል። ሸዋንም ከአቢሲኒያ አስወጧት ማለት ነው። 

አገራችንን እኛ "ኢትዮጵያ" ብንላትም፥ ወይም ሌሎች "አቢሲኒያ" ቢሏት፥ በድምበሯ ወሰን ከተስማማን፥ የስሟ ጉዳይ 
የስልቻና የቀንቀሎ ነገር ነው። እስላሞሮሞ አክራሪዎች ግን "አቢሲኒያ" የሚለውን ስም የሙጥኝ ብለው የያዙት፥ የቅኝ 
ገዢዎች አገር በሚሻሙበት ጊዜ የጻፉትን ይዘው ነው--"አቢሲኒያ እኛን በደቡብ በኩል ያለነውን አይጨምርም" ለማለት 
ነው። በእምቢታው ካልገፉበት፥ ታሪክ አይደግፋቸውም። የኢትዮጵያ ቆዳዋ ተቀንሶለት እንደሆነ ነው እንጂ፥ አፄ ምኒልክ 
በጥንቷ ኢትዮጵያ ላይ አንዳች ስንዝር መሬት አልጨመሩላትም። "ጥንቷ ኢትዮጵያ" የሚለው አነጋገር እንዳያሳስት፥ 
የቅርቡን ጊዜ፥ ማለት፥ የዘመነ መሳፍንት ዋዜማ ኢትዮጵያን ማለቴ ነው። 

"አፄ ምኒልክን አንዳንዶች መሬት አስፋፉ ይሏቸዋል፤ አንዳንዶች የጥንቷን ኢትዮጵያ መልሰው አቋቋሙ ይሏቸዋል፤ ይህ 
ያስተያየት ጉዳይ ነው" የሚል ፈሊጥ እሰማለሁ። ይህ የታሪክ ጉዳይ እንጂ፥ ያስተያየት ጉዳይ አይደለም። ለምሳሌ፥ "ያበሻ 
ልብስ ያምራል፤ አያምርም" ቢባል፥ ያስተያየት ጉዳይ ነው። ልብሱ "ያበሻ ልብስ" መሆኑ ግን "ያስተያየት ጉዳይ" ሊባል 
አይገባም። አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ወይ የሰው አገር ነጥቀው አስፋፍተዋታል፤ ወይ ያመፁትን መሳፍንት አስገብረዋል። 
የሆነው ግን፥ አፄ ቴዎድሮስ የጀመሩትን አመፀኞችን ማስገበር፥ አፄ ዮሐንስ፥ አፄ ምኒልክ፥ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቀጥለውበታል። 

ስለዚህ፥ አፄ ምኒልክ ሲነግሡ፥ ሥልጣናቸው የሞቱ ጊዜ ከደረሰበት አይደርስም ነበር። በኦሮሞዎች ወደ ሰሜን ፍልሰትና 
ወረራ ምክንያት፥ የጎንደር ማእከላዊ መንግሥት የብዙዎቹን ክፍላተ ሀገር መሳፍንት ማስገበርና መቈጣጠር አልቻለም ነበር። 
ትግራይን፥ ወሎን፣ ሸዋን፥ ባሌን፥ ጉራጌን፥ ሳይቀር የሚገዟቸው ለንጉሥ የማይገብሩ አፈንጋጭ መሳፍንት ነበሩ። ደቡቡማ 
ወራሪዎቹ ነባር መሳፍንቱን አሸንፈው አዳዲስ መሳፍንት ነግሠውበት ነበር። ዘመኑ ዘመነ መሳፍንት የተባለውም ስለዚህ 
ነበር። ከዘመነ መሳፍንት አስቀድሞ እስከ አፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ(1674-1698) ድረስ የገዙ ነገሥታት ግን፥ ሥልጣናቸውን 
በኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር ዘርግተዋል--ኦሮሞዎች በሰፈሩበት በብዙው ቦታ ሁሉ ማለት ነው። "ነገሥታቱ አቢሲኒያን 
አስፋፉ" ማለት በግድ የገበሩትን ትግራይን፥ ወሎን፣ ሸዋን፥ ባሌን፥ ጉራጌን፥ እናርያን (ወለጋን) ሁሉ የኢትዮጵያ ክፍል 
አልነበሩም ማለት ይሆናል። 3 

ተረቱን እንተወውና፥ እነዚህ የጎንደር ቅድመ ዘመነ መሳፍንት ነገሥታት ኢትዮጵያን የገዙትም ከኦሮሞቹ፥ ከአማራዎቹ፥ 
ከቡሻዎቹ፥ ከጉራጌዎቹ፥ እንዲያው በጠቅላላው ከግዛታቸው ሕዝብ ጋር ሆነው ነበር። ለምሳሌ፥ ከ1555 እስከ 1589 ዓ. ም. 
የገዛው አፄ ሠርፀ ድንግል ቱርክን ዛሬ ኢሳይያስ አፈወርቂ ከሚገዛው ሀገር ያባረረው በኦሮሞ ወታደሮቹ ፊታውራሪነት ነበር፤ 
ይህ ታሪክ በዘመኑ ተመዝግቧል። በዚያን ጊዜ ኦሮሞዎች የመንግሥት ወታደሮች የሆኑት እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ 
ወታደር ያገራቸው ንጉሥ ምልምሎች ሆነው ነው እንጂ፥ ከሌላ አገር በገንዘብ ተገዝተው የመጡ ወታደሮች (mercenaries) 
አልነበሩም። ከ1674 እስከ 1698 የገዛው አፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ሥልጣኑ በደቡብ እስከ ጊቤ፥ በሰሜን ምሥራቅ እስከ 
ምጽዋ ድረስ እንደተዘረጋ በጊዜው በተጻፈው የታሪክ መዝገብ ተመዝግቧል። 
የዚህ የአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ሥልጣን ተካፋዮች ኦሮሞዎቹ እነአዛዥ ሀከኮ ነበሩ። አዛዥ ሀከኮን ታሪክ ጸሐፊው 
ሲያደንቀው፥ "ዓቢይ ጋላ ወማእምረ ኵሉ ነገር" (የነገርን ሁሉ ስልት የሚያውቅ ታላቅ ኦሮሞ) ይለዋል። ሌሎቹ 
ባለሥልጣኖች ጸሐፌ ላሕም ቱሉ፥ ብላቴን ጌታ ባስልዮስ ይባላሉ። ታሪክ መዝጋቢው ቱሉን ሲያደንቀው "ይሉ አይሉ፥ 
የታለ ቱሉ" ይባልለት እንደነበረ ይነግረናል፤ "የነገር ሁሉ መደምደሚያ የቱሉ ቃል ነው" ሲለን ነው። ብላቴን ጌታ ባስልዮስን 
ደግሞ፥ "ጠቢብ ወማዕምር ወለባዌ ፍትሕ ወክቡረ ዘመድ ወነገድ እምነገደ ጋላ ወአድያ፥ ወልደ ቡናያ ወወልደ እኅቱ 
ለደጃዝማች ሎሬንስ" (ከኦሮሞ ነገድና ከሀድያ የሆነው፥ ጥበበኛውና ዐዋቂው፥ ፍርድ አስተካካዩ፥ ባለክቡራን ዘመዶች 
የሆነው የቡንያና የደጃዝማች ሎሬንስ እኅት ልጅ) ይለዋል። የጋብቻውንና የዝምድናውንም ነገር እግረመንገዳችንን ልብ 
እንበለው። "ብላቴን ጌታ" ከቢትወደድ ቀጥሎ የሚመጣ ከፍተኛ ማዕርግ ነበር። በመጨረሻም፥ ንጉሡ ከአማራና ከኦሮሞ 
ሴቶች ከወለዳቸው ከሦስቱ ልጆቹ፥ ከአቤቶ ዓፅቁ፥ ከአቤቶ ኃይሉ፡ ከአቤቶ ዋዩ መርጦ አልጋውን ያወረሰው ለአቤቶ ዋዩ 
ነው። አቤቶ ዋዩ ማን ነበረ? 
ኢትዮጵያዊ ሆይ፥ ስምህ ማነው? 
አቤቶ ዋዩ የተባለው ልዑል የወሎ አሚጦ ኦሮሞ ልጅ፥ የሉባውና የዱላው እኅት ከሆነችው ከእመቤት ወቢ የተወለደውና 
ሲነግሥ ኢዮአስ የተባለው ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ስም በመውሰዱ ኦሮሞነቱ ቀርቶበታል ከተባለ፥ አንድ ኢትዮጵያዊ 
በእስላምነቱ የቁራን ስም ከወሰደ ኢትዮጵያዊነቱ ይቀርበታል ማለት ይሆናል። በስም አንፍረድ፤ ይፈረድብናል። አንድን 
ኦሮሞ ኦሮሞ የሚያደርገው የኦሮሞ ስም ሲይዝ ወይም እስላም ሲሆን ብቻ መሆን የለበትም። 
በስማቸው ምክንያት፥ ኦሮሞነታቸው ሳይታወቅ የኢትዮጵያን ታሪክ ያገነኑ ኦሮሞዎችን ቍጥር ማን ያውቀዋል? ታሪክ 
ጸሐፊው ባይነግረን ኖሮ፥ ከላይ ስሙን ያነሣሁት ብላቴን ጌታ ባስልዮስ ኦሮሞ መሆኑን፥ አፄ ኢዮአስ የኦሮሞይቷ ልጅ 
መሆኑን አናውቅም ነበር። "የወፍ ወንዱ፥ የሰው ግንዱ አይታወቅም" የሚባለው ለዚህ ነው። ኢትዮጵያ የሚያኮራ ታሪክ 
እንዳላት፥ ሕዝቧም እንደዚህ ድብልቅ እንደሆነ ለልጆቿና ለዓለም ላስታወቀው "ላልታወቀው ደብተራ" መታሰቢያ ሐውልት 
በማቆም ባለውለታ መሆኗን፥ ማሳየት ይኖርባታል። ያልታወቀው ደብተራ "በቀለ ገብረ መድኅን" ወይም "በቀለ ዋቅጂራ" 
ወይም "በቀለ ኦርፊቾ" ወይም "በቀለ ዓሊ" . . . ሊሆን ይችላል። 

በዘመነ መሳፍንት፥ ማእከላዊው መንግሥት በየጁ ኦሮሞዎች እጅ ነበረ። ስማቸው የኦሮሞ፥ የአማራ፥ የቁርኣን ነበረ። ታዲያ፥ 
ባለማወቅ ካልሆነ፥ "በጥንቷ ኢትዮጵያ አስተዳደር ውስጥ የለንበትም፤ ለሌላው የተሰጠው ክብርና ብልጽግና ለኛም 
አልደረሰንም" የሚሉት፥ ከዚህ የበለጠ ኢትዮጵያዊነትና ባለ ሥልጣን መሆን፥ መከበርም፥ ለማን ተሰጥቷል? በገበሬነትና 
በገባርነትም ቢሆን ሰፊው የአማራ ሕዝብ ከኦሮሞዎች የተሻለ ሕይወት አልኖረም። "ለምን በሸሪዓ የሚተዳደር መንግሥት 
አልተቋቋመም ፤ ለምን እስልምና የበላይነት አያገኝም" ማለት ከሆነ፥ የሱን መልስ የሚያውቅ እኔ ሳልሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ 
ነው። 

የአፄ ምኒልክ ግዛትና አስተዳደር፤ 

አለበቂ ምክንያት ወደሚወቀሰው ወደቅርቡ ዘመን ስንመጣ፥ የአፄ ምኒልክ አስተዳደርም ገጽታው ይኸንኑ የቀድሞዎቹን 
የወረሰ ነበር። አማራው፥ ጉራጌው፥ ኦሮሞው፥ ወላሞው፥ ትግሬው፥ ሐማሴኔው፥ ጎንደሬው፥ ጎጃሜው፥ ሸዌው . . . 
የሠለጠነበት አስተዳደር ነበር። የአድዋን ድል እነማን እንዳስገኙልን የማያውቅ ካለ፥ ሐዘንተኞች ነን። አለማወቅን ለማረም፥ 
ሌላው ቢቀር G.F.-H. Berkeley, The Campaign of Adowa and the Rise of Menelik (1902) እና Wikipedea 
("Battle of Adwa") መነሻ ይሆናሉ። ያልገበሩ መሳፍንትን ለማስገበርም በኩል ሁሉም እኩል ሕይወቱን የሰጠበት ዘመን 
ነበር። ለማወቅ ለሚፈልግ፥ በዘመናቸው የተዘመቱ ዘመቻዎች የአመፀውን ከማሳመን እንዳላለፈ የሚያሳዩ ተጨባጭ 
ምልክቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ በጉራጌ ዘመቻ ዝዋይ ውስጥ የተገኙት የጥንት መጻሕፍት፥ የአርሲ እረኛ የጅራፍ እጀታ 
አድርጎት የተገኘ የእጅ መስቀል፥ አይኬ ሀበርላንድ የጻፈው የደቡብ ኢትዮጵያ የጥንት የክርስቲያን ታሪክ (Eike Haberland, 
"Altes Christentum in Süd-Äthiopien") ይገኙበታል። የጥንቱ መጻሕፍት አሁንም እዚያው እዝዋይ ደሴት ውስጥ 4 

በምትገኘው በደብረ ጽዮን ገዳም አሉ። የኦሮሞዎችን ወታደራዊ ሥርዓት (ገዳ) ያጠኑልን አባ ባሕርይም የጋሞ መነኲሴ 
ነበሩ። የአፄ ምኒልክ አስተዳደርም ከቀድሞዎቹ የሚለየው፥ የጎጃሙ ጸሐፊና ሠዓሊ ደብተራ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ 
እንደጻፉት፥ የዜጋቸውን ልብ በርኅሩኅነት መማረካቸው ነው። በምኒልክ ዘመን ወታደር የገበሬ ሚስት መድፈሩ ቀረ፤ 
ማስፈራሪያ ጠመንጃው እንደ አገዳ ታየ ይሉናል። 

አፄ ምኒልክ የአባቶቻቸውን ግዛት ልክ ለአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች በሁለት ሰነዶች ገልጸውላቸዋል፤ መጀመሪያው 
ያባቶቻቸውን ኢትዮጵያ የሚያሳይ ካርታ ሲሆን፥ ሁለተኛው የአባቶቼን ርስት ልትቆርሱ ከመጣችሁ፥ ዝም ብየ 
አላስቆርሳችሁም የሚል ደብዳቤ ነው። ግን ሦስቱን ቀመኞች (እንግሊዞችን፥ ፈረንሳዮችን፥ ኢጣልያኖችን) አልቻሏቸውም፤ 
ሆኖ የአባታቸው ቤት ሲዘረፍ የተቻላቸውን ያህል፥ በማባበልም በጦርነትም አብረው ዘርፈዋል። የአፄ ምኒልክን የማስገበር 
ዘመቻ ከቅኝ ገዢዎች አፍሪካን መቀራመት ጋር የሚያመሳስሉ ካሉ፥ የኢትዮጵያን ታሪክ የማያውቁ ናቸው። የኛ ዘመቻ 
(ልዩነታችንን በሰላም ማስተናገድ ባለመቻላችን) ከጥንት ጀምሮ አብሮን ያለ ነው። ቅኝ ገዢዎች የመጡት ግን በቅርብ ጊዜ 
ነው። 

በጦርነት ደግሞ ከሁለቱም ወገን ሰው እንደሚጎዳ የታወቀ ነው። ጉራጌ የዘመተው ጦር አንድ ሦስተኛው እዚያው ወድቆ 
ቀርቷል። አፄ ቴዎድሮስ ሸዋን ለማስገበር የዘመቱ ጊዜ የሆነውን ለመግለጽ አልቃሽ፥ "ባላልቦ አደረጉት ያንን ሁሉ ሴት" 
ያለቻቸውን አንርሳ። 

የሀገሪቷን አንድነትና የኛ ንብረትነቷን ከተቀበልን ዘንዳ፥ የሚያዋጣን ኢትዮጵያን ላቆዩልንና ላወረሱን ሁሉ ነፍሳቸውን 
ይማር እያልን፥ ቊስላችንን እየጠገንን ወደፊት መገሥገሥ ነው። የፈሰሰ ደም አይታፈስም። ቤተ ክርስቲያን ማቃጠል 
የክርስቲያኖችን ቊስል ያመረቅዛል እንጂ፥ የእስላሞችን ቍስል አያድንም። እንተማመን፤ እንተሳሰብ። አንዱ ወገን ለሌላው 
ወገን (ወንዱ ለሴቱ፥ እስላሙ ለክርስቲያኑ፥ ኦሮሞው ለወላይታው፥. . . ) ካላሰበ፥ ሲያስብ ደግሞ የሚያምነው ከሌለ፥ 
ዕድላችን እንደ ሀገር ልጆች ተቃቅፎ ከመጓዝ ይልቅ፥ እንደ ኮርማ በሬዎች ተቆላልፎ መቅረት ይሆናል። 

ለፈገግታ ያህል፤ 

"አበሻ" እና "አቢሲኒያ" አንድ ናቸው ወይ? እንዴት አርጎ አንድ ይሆናሉ! አንድ አይደሉም። እኛ ስናወራ "አበሻ" የምንለው 
ሰዉን፥ "የሐበሻ" የምንለው ባህሉን (ለምሳሌ፥ ልብሱን፥ ምግቡን፥ ዘፈኑን፥ እስክስታውን) ነው። አገራችንን ግን ስናወራም 
ሆነ ስንጽፍ "አበሻ" አንላትም። ቃሉም የዓረቦች እንጂ፥ በመሠረቱ የኛ አይደለም። (አትገረሙ፥ ከዓረቦች ብዙ ነገር 
ወስደናል።) ፈረንጆች ግን "አቢሲኒያ" ይሉ የነበረው ሀገሪቱን (ኢትዮጵያን)ነው። 

ታሪኬን መልሱ፤ ብዕሬን በወርቅ ቀለም አብሱ። 

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog