በቤንሻንጉል አሁንም ዜጎችን ማፈናቀሉ ቀጥሏል!

• ‹‹አማራ ክልል አያገባኝም ብሏል››:: 
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ለዓመታት ከኖሩበት ቦታ እየተፈናቀሉ መሆኑን ተፈናቃዮች አስታወቁ፡፡ ባለፈው ዓመት ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከክልሉ መፈናቀላቸው የሚታወስ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ ማፈናቀሉ በአዲስ መልክ የቀጠለ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ተፈናቃዮቹ በክልሉ ድባጤ ወረዳ አልባሳ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ ከ250 ሰዎች በላይ ከአካባቢው ውጡ ተብለዋል፡፡ ‹‹በአካባቢው ሰፈራ እየተሰጠ ነው፡፡ የተባረሩት ሰዎች ግን 15ና 20 አመት በአካባቢው ኖረዋል፡፡ ቤትና ንብረትም አላቸው፡፡ ከጥቅምትና ታህሳስ ጀምሮ ግን ‹እናንተ በአካባቢው መኖር አትችሉም› ተብለው መስፈር የለባችሁም ተብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኒህ ሰዎች ዛፍ ስር ነው የሚኖሩት፡፡›› ሲሉ ስለ ሁኔታው ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከወራት በፊት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች አሁንም ድረስ ወደቦታቸው እንዳልተመለሱ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ህዝቡ ንብረቱን ተቀምቶ ሲባረር በወኪልነት ፌደራል ድረስ መጥተው ህገ-ወጥ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን በማስረዳት ክስ ያቀረቡና አሁንም የተወሰደባቸው ንብረት እዲመለስ የሚከራከሩት ወኪሎች ወደ ቦታቸው መመለስ አለመቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የተፈናቃኞቹ ተወካይ ሲናገሩ፣
‹‹በከሰስንበት ወቅት የተፈናቀልነው በህገ ወጥ መንገድ መሆኑን የፌደራል እንባ ጠባቂ አረጋግጦ ሀብትና ንብረታችን ተመልሶልን ወደየቦታችን እንድንመለስ ተወስኖ የነበር ቢሆንም የክልሉ ባለስልጣናት እኛን ስትከሱ ኖራችሁ እንደገና አትመለሱም ብለው አስረውናል›› ሲሉ ይልጻሉ፡፡
ተወካዩ አክለውም ‹‹በፌደራል ደረጃ ሲወሰን እኛ መሬታችን፣ እንዲሁም ጥለነው የወጣነው ኃብትና ንብረታችን ካልተመለሰ አንመለስም ብለን ወስነን ነበር፡፡ የቤንሻንጉል ክልል ባለስልጣናት ግን ኃብትና ንብረታቸውን እንመልሳለን፤ መሬትም እንሰጣችኋለን ብለው ቃል በመግባታቸው ተስማማን፡፡ ሆኖም እኔ ወደ ቤቴ ስመለስ ‹ምን ቤት አለህ፡፡ ቤትህ እስር ቤት ነው ብለው ሶስት ቀን ካሰሩኝ በኋላ አባረውኛል›› ይላሉ፡፡
የወኪሎቹ ብቻ ሳይሆን ሀብትና ንብረታችሁ ይመለስላችኋል የተባሉት ተፈናቃዮች ሀብትና ንብረታቸው ስላልተመለሰላቸው በአሁኑ ወቅት በፌደራል ደረጃ እየከሰሱ ይገኛሉ፡፡ ወደ ቤታቸው መመለስ የቻሉት ተፈናቃዮችም ‹‹ለአማራ መሬት አንሰጥም!›› ስለተባሉ የሚያርሱት በኪራይና አበል መሆኑንም ከተፈናቃዮቹ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በሌላ በኩል በተመላሾቹ ላይ እስርና ማንገላታቱ እንዳልቆመም የተፈናቀቃዮቹ ተወካዮች ለነገረ ኢትዮጵያ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ‹ከሳችሁን ነበር› በሚል ተፈናቀዮቹ መሬታቸውን፣ ሀብትና ንብረታቸውን በሚጠይቁበት ወቅትም ከፖሊስ ድብደባና እስር የሚያጋጥማቸው ሲሆን በፖሊስ ድብደባ አንድ ሰው መሞቱን ተወካዮቹ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፖሊስ የተደበደበች ነፍሰ ጡሩ እንዳስወረዳት ይናገራሉ፡፡ የዚች ነፍሰ ጡሩ ባለቤትም በባለቤቱ ላይ የደረሰውን ግፍ ተከትሎ በመክሰሱ ‹‹አንተንስ ብንገልህ ማን አለህ?›› በማለት ሁለት ቀን አስረውና ደብድበው እንደለቀቁት አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተወካዮቹ የተፈናቃዮቹ ሀብትና ንብረት እንዲመለስ እየጠየቁ ሲሆን ‹‹በክልሉ እስርና ወከባው በመቀጠሉ በወንጀል ብንከስ ወደ ቤታቸው የተመለሱትን ይበልጥ ያሰቃዩዋቸዋል በሚል ከመክሰስ ተቆጥበናል›› ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ ተወካዮቹ ለተፈናቃዮቹ ሀብትና ንብረት እንዲመለስ እየጠየቁ ቢሆንም እነሱ ራሳቸው ወደ ክልሉ ቢመለሱ ለህይወታቸው ስለሚያሰጋቸው በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የቀን ስራ እየሰሩ እንደሚከራከሩ ገልጸውልናል፡፡
‹አማራ› ተብለው ከተፈናቀሉና ሲመለሱም ‹‹ለአማራ መሬት አንሰጥም›› የተባሉት ተፈናቃዮቹ በጉዳዩ ለአማራ ክልል ጥያቄ አቅርበው ‹‹እኛ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ሂዳችሁ የምትጠይቁትን ጠይቁ›› መባላቸው እንዳሳዘናቸው አክለው ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከደቡብና ከቢኒሻንጉል ክልሎች የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ በርካታ ዜጎች ‹ከሐገራችን ውጡ› እየተባሉ መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡
 Source: ነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog