አርሶ አደሮች መሬታቸውን ያለካሳ እየተነጠቁ ነው

መራዊ፡- በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ ያለ ፈቃዳችን መሬታቸውን አሳልፈን አንሰጥም ያሉ አርሶ አደሮች እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በመራዊ አካባቢ ሜጫ ወረዳ እናሸንፋለን ቀበሌ መንግስት
የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ እናካሂዳለን በሚል ከ400 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው እንዲለቁ የተደረገውን እርምጃ አርሶ አደሮቹ በመቃወማቸው እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው ከአሁን ቀደም ተመሳሳይ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን የአርሶ አደሮቹ መሬት በአበባ ኢንቨስትመንት ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ተሰጥቶባቸዋል፡፡ 
         ይህም በአሁኑ ወቅት መንግስት ውሃ ለመቆፈር በሚል አርሶ አደሮቹ ከመሬታቸው እንዲለቁ የሚወስደው እርምጃ በተመሳሳይ  ለአበባ እርሻ ሊሰጥባቸው እንደሆነ በማመናቸው ከመሬታቸው አንለቅም ብለዋል፡፡
እስካሁን ለአበባም ሆነ ለሌሎች ተግባራት መንግስት ከአርሶ አደሮቹ መሬት ሲወስድ ያለ ምንም ካሳ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ አሁንም ቢሆን ያለ ካሳና ያለምንም ፈቃድ እየተነጠቁ በመሆኑ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አድርጓዋል፡፡ ከአርሶ አደሮች ባሻገር በከተሞች የሚኖሩ የአርሶ
አደሮቹ ቤተሰቦች ጭምርም ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ምንጮች ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በተለይም ታሳሪዎቹን የሚጠይቁት የአርሶ አደሮቹ ቤተሰቦችና ሌሎች የአካባቢውና በየከተማው የሚኖሩ ግለሰቦችም ለእስር መዳረጋቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን ያለ ፈቃዳቸው አሳልፈው እንደማይሰጡ በመግለጽ ጠንካራ ተቃውሞ ማንሳታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ፖሊስና መከላከያ በብዛት መሰራጨቱን ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡
  Source: ነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog