የሱዳን ወዳጅነት ከጉርብትናም በላይ?

ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በእያንዳንዱ የሕወሓት የልደት በዓል ማለትም የካቲት 11 በዋነኝነት ከሚከበርበት የትግራይ ርዕሰ ከተማ መቐለ ተገኝተው በሚያደርጉት ንግግር በዓሉን ሁሌም ድምቀት ይሰጡት ነበር፡፡
ሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ ዋነኛ መሥራች የሆነውን ሕወሓት የረጅም ጊዜ ጠንካራ ሊቀመንበሩን ያጣው ባለፈው ዓመት በዓሉን ከማክበሩ ስድስት ወራት በፊት ነበር፡፡
አቶ መለስ ለመጀመርያ ጊዜ ያልተገኙበት 38ኛው በዓል ግን እሳቸውን በመዘከር በሐዘን ድባብ ነበር ያለፈው፡፡ ተተኪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በወቅቱ በበዓሉ ላይ ቢገኙም፣ በአቶ መለስ መሪነት እዚህ ደርሷል ያሉት ሥርዓት ከፍተኛውን መስዋዕትነት ከፍሎበታል ካሉት ከትግራይ ሕዝብ ጋር እጅና ጓንት በመሆን እንደሚሠሩ፣ ‹‹የማፅናኛ›› ንግግር አድርገው ነበር የተመለሱት፡፡ 
ዘንድሮ የተከበረው 39ኛው የሕወሓት በዓል ግን ባለፈው ዓመት በሐዘን ድባብ ያለፈውን በዓል ያካካሰ በሚመስል ሁኔታ እጅግ ደማቅ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ላለፉት 22 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ ዋነኛ አካል የሆነው ሕወሓት፣ በሚቀጥለው አርባኛ የልደት ዓመቱ በበለጠ በደመቀ ሁኔታ ያከብራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የዘንድሮው ግን ከተገመተው በላይ ደማቅ ሆኖ ተከብሯል፡፡ 
የሕወሓት በዓል እጅግ እንዲደምቅ ምክንያት የሆነው ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለየ የሠራው ነገር ኖሮ አይመስልም፡፡ እንዲያውም ድርጅቱ ጠንካራ መሪውን በሞት ካጣ በኋላ መረጋጋት ተስኖት በውስጥ መከፋፈልና እርስ በርስ በመወነጃጀል ማሳለፉ ይነገራል፡፡ የድርጅቱ ሌሎች አንጋፋ መሪዎችም ያላግባብ ከአመራር መሸኘቱ ከፍተኛ ትችት ያስተናገደበት ዓመት ነበር፡፡ በሌሎች ዓመታት እንደተለመደው
የድርጅቱን የትጥቅ ትግል ታሪክ በሚያወሱ ዘጋቢ ፊልሞች፣ የጦር ውሎዎችና ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ያስመዘገበው ልማት በመንግሥት ሚዲያ ታጅቦ ነው በዓሉ የተከበረው፡፡ 
ይህ ጽሑፍ ዋና ዓላማው የሕወሓትን የልደት በዓል ወይም የድርጅቱን የትጥቅ ትግልና መስዋዕትነት ለመተረክ አይደለም፡፡ የዘንድሮው የድርጅቱ የልደት በዓል እንዲደምቅ ምክንያት የሆነው የተለየ አንድ ውጫዊ የሆነን አጋጣሚ መነሻ በማድረግ አገራዊ አንድምታውን መዳሰስ ነው፡፡ 
‹‹ሴሲና›› ታሪካዊው አውሮፕላን 
ወጣት ተስፋሁን አምባቸው በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ካፌ ውስጥ ሻይ ቡና እያለ በኢቲቪ በቀጥታ ሲተላለፍ የዋለውን የድርጅቱን በዓል ሲመለከት ነበር፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርም ሆኑ ሌሎች አመራሮች ያደረጓቸው ንግግሮች ምን እንደሚሉ ቀድሞ እንደሚያውቅ ሰው ለመስማት እምብዛም የጓጓ አልነበረም፡፡ የተስፋሁንን ቀልብ መሳብ የጀመረው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር መኖራቸውን ሲመለከት ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የቅርብ ወዳጅ እንደበሩ የሚነገርላቸው ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ በዚህ የሕወሓት በዓል መገኘታቸው ብቻ አይደለም የተስፋሁንን ቀልብ የሳበው፡፡ 
የተስፋሁንና የጓደኞቹ ወሬ የሚያጠነጥነው በሕወሓት የልደት በዓል ላይ አልነበረም፡፡ ፕሬዚዳንት አል በሽር ኢትዮጵያ መጥተው በሕወሓት በዓል ላይ ሲገኙ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ የግሉ ሚዲያ እምብዛም ትኩረት የሰጠው ባይመስልም፣ የመንግሥትን ሚዲያ ለተከታተሉ አብዛኛዎቹ ሰዎች አነጋጋሪ የሆነው የእነተስፋሁን ጓደኞችንም ቀልብ የሳበው የፕሬዚዳንቱ መገኘት ነው፡፡ የብዙ ኢትዮጵያውያን ዜጐችን ቀልብ የሳበው ግን የፕሬዚዳንቱ መገኘት ብቻ በራሱ አይመስልም፡፡ በግንቦት 1983 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና አቶ ሥዩም መስፍን፣ አቶ ተፈራ ዋልዋና ሌሎች የሕወሓት ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ድርጅቱ ባካሄደው ጦርነት ደርግን አሸንፎ ወደ አራት ኪሎ ታላቁ ቤተ መንግሥት ሲገባ በአንድ አውሮፕላን ነበር የመጡት፡፡ ከሱዳን ካርቱም ወደ አዲስ አበባ የመጡበት አውሮፕላን አብራሪ የነበሩት ቀድሞ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ጄኔራል አልፋታህ በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በወቅቱ በጉዞ ላይ እያሉ የዚህ ታሪካዊ አውሮፕላን አንደኛው ሞተር ከሥራ ውጪ በመሆኑ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ሆነው በወቅቱ ታጋይ ሥዩም መስፍን ከአብራሪውና ከድርጅቱ ሊቀመንበር ታጋይ መለስ ዜናዊ የተለዋወጡዋቸው ‹‹ኑዛዜ›› የሚመስሉ ምልልሶች ነበሩ፡፡ በተለይ አቶ ሥዩም፣ ‹‹ይኼ ሕዝብ ዕድለኛ አይደለም ማለት ነው፣ እኔ ነኝ ጉድ ያደረጉኩህ፡፡ ጓዶች በመኪና እንድንመጣ አስጠንቅቀውን ሳለ በፕሌን እንድንመጣ በማድረጌ አዝናለሁ፤›› ሲሉ፣ ታጋይ መለስ በበኩላቸው በፈገግታ፣ ‹‹አንተ ባስክብንኮ›› ማለታቸውን አቶ ሥዩም አውስተዋል፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር የነበሩት አብራሪው ጄኔራል አልፋታህም ከታጋዮች ጋር የቅርብ ወዳጅ የነበሩ በመሆናቸው ትውስታቸውን እንዲህ በማለት ነበር የገለጹት፡፡
‹‹አንድ የማስታውሰው ነገር ቢኖር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፣ አል በሽርና እኔ ተቀምጠን እየተወያየን ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜያት የሕወሓት የትግሉ አካል መሆኔን ተመልክቶ አምባሳደር እንድሆን ሲጠይቀኝ እኔም አምባሳደር ሆንኩኝ፡፡ እኔ የአውሮፕላን አብራሪ ብቻ ሳልሆን ደርግንም የምታገል አካል ነበርኩ፡፡ የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል መሆኔ እጅግ ያስደስታል፤›› ነበር ያሉት፡፡ 
‹‹ሴሲና›› በመባል የሚታወቀውና ከአስፈሪው አደጋ ያመለጠው ይህ ታሪካዊ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ በስጦታ የተበረከተ ሲሆን፣ በመቐለው የሰማዕታት ሙዚየም ውስጥ እንዲቀመጥ ተወስኗል፡፡
የፕሬዚዳንት ሐሰን አል በሽር ንግግርም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ሕወሓት ጋር የነበራቸው የቀረበ ወዳጅነት፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በተመለከተ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለታዳሚዎቻቸው ከፍ ባለ ድምፀት ያለው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጠንሳሽነት የተመሠረተው ድርጅት ራዕይ ተግባራዊ መሆኑን ነበር የተናገሩት፡፡ ‹‹የሰማዕታት ደም ሊካስ የሚችለው ሰማዕታት የወደቁባቸው ተራሮች፣ ሜዳውና ሸንተረሩ በልማት ሲሸፈኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር አቶ ዓባይ ወልዱም ንግግር አድርገዋል፡፡ 
ከጉርብትናም በላይ ወዳጅነት 
የፕሬዚዳንት አል በሽርና በኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር ጄኔራል አልፋታህ በዚሁ የሕወሓት በዓል መገኘታቸው ትልቅ ቀልብ የሳበበት ምክንያት የሁለቱ አገሮች መልካም ጉርብትና ብቻም አይደለም፡፡ 
በቅርቡ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያንን እያጨቃጨቀ ያለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጉብኝቱ ጀርባ ያለ ይመስላል፡፡ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የተነሳውን አለመግባባት ለመፍታት ሱዳንን ጨምሮ ላለፈው አንድ ዓመት የተካሄደው የሦስትዮሽ ውይይት ትልቅ ሥፍራ የተሰጠው ነበር፡፡ በሦስተኛው ውይይት ሒደቱ ያለውጤት ቢበተንም፣ የግብፅ ታሪካዊ ወዳጅ የሆነችው ሱዳን በድርድር ሒደት ውስጥ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ማዞሯ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስጦታ ነበር፡፡ 
ቀደም ሲል ግብፅና ሱዳን በዓባይ ላይ የተዋዋሉዋቸው አግላይ ስምምነቶች (1929 እና 1959) የውኃውን ክፍፍል ለሁለቱም አገሮች ማድረጋቸውና ሁሌም የሱዳን አቋም ከግብፅ ጋር የተገናኘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁለቱም አገሮች ከተፋሰስ አባል አገሮች በስድስቱ የተፈረመውን የአሥር ዓመት የውይይት ውጤት በሆነው የዓባይ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ማዕቀፍ (CFA) በእንቢተኝነት ፀንተው ነበር፡፡ ከዚያም በተጨማሪ አንዳንድ የአሜሪካ የስለላ መረጃዎች እንዳጋለጡት፣ በግብፅና በሱዳን ባለሥልጣናት መካከል በተደረጉ ሚስጥራዊ ግንኙነቶች፣ ግብፅ ግድቡን ለማውደም የሱዳንን ግዛት ለመጠቀም ዕቅድ ነበራት፡፡ የአሁኑ የሱዳን አቋም መለወጥ ግን በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የነበረው የኃይልና የዲፕሎማሲ ሚዛን እንዲቀለበስ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ 
በአሁኑ ወቅት የግብፅና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አንዳንድ የተካረሩ ቃላት እየተለዋወጡ ሲሆን፣ ከፕሬዚዳንት አል በሽር ጋር በጋራ በመቐለ በሕወሓት በዓል ታዳሚ የነበሩት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግብፅን አካሄድ በመቃወም ግልጽ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሊ ካርቲ ለሱዳን ትልቁ ሚዲያ ሱዳን ትሪቢዩን እንደተናገሩት፣ የግብፅ ባለሥልጣናት በሚዲያ እየሰጡዋቸው ያሉት ተንኳሽ መግለጫዎች ሁኔታውን የሚያባብሱ ናቸው፡፡ ‹‹የሱዳን አቋም ግልጽ ነው፡፡ በግብፅ ባለሥልጣናት በቀውሱ ላይ ሱዳን በምትጫወተው አወንታዊ ሚና እንዲጠቀሙ ነግረናቸዋል፡፡ የቀድሞ ገዥዎቻቸው ግትርነት አላሠራ ብሏቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ራሳቸው ፕሬዚዳንት አል በሽርም ቀደም ሲል በግልጽ ቋንቋ የታላቁን ዓባይ ግድብ መገንባት እንደሚደግፉ ተናግረው ነበር፡፡
ሱዳን የአቋም ለውጥ ለምን አደረገች?
የዓባይን ውዝግብ በተመለከተ ቀደም ሲል በሱዳንና በግብፅ መካከል የነበረው ግንኙነት መዳሰስ የዛሬውን ለመገንዘብ ይረዳል፡፡ በተለይ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙትን ሁለቱን ስምምነቶች መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1929 በታላቋ ብሪታንያና በግብፅ መካከል የተደረገ ነው፡፡ ለሱዳን የተሰጠ የውኃ መጠን አራት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲሆን፣ የተቀረው 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ደግሞ ለግብፅ ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት ግብፅ በፈለገችው ጊዜ በወንዙ ላይ ግድብ የመሥራትና የመጠቀም ሥልጣን ያላት በመሆኑ፣ ሱዳን ይህንን ለማድረግ የግብፅን ፈቃድ እንደትጠይቅ ትገደዳለች፡፡ 
ሁለተኛው ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. በ1959 የተፈጸመ ነው፡፡ ይህ በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገ ስምምነት ነበር፡፡ በቀድሞው የውኃ ስምምነት ያልታወቀ የውኃ መጠን በመገኘቱ በዚህ ስምምነት የሱዳንን ድርሻ ወደ 18.5 መቶኛ ኪዩቢክ ሜትር ከፍ እንዲል የተደረገ ቢሆንም፣ ሱዳኖች ውኃውን የመጠቀም መብታቸው በግብፅ በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ መረዌ የተባለው ግድብ ከአራት ዓመታት በፊት ተገንብቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ በውኃ ለመሙላት እስካሁን ሱዳኖች ፈቃድ አላገኙም፡፡ ሮዜሬስ የተባለውን ግድብ የውኃ መጠኑን ከፍ ለማድረግ ጠይቀውም እስካሁን አልተፈቀደላቸውም፡፡ 
የውኃው ዋነኛ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ያገለሉ እነዚህ ስምምነቶች ውኃውን በግብፅና በሱዳን መካከል የሚከፋፍሉ ቢሆንም፣ ሱዳን በስምምነቱ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ትገነዘባለች፡፡ ግብፆች በሱዳኖች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ዛሬ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በሚኒስትሮች ደረጃ ሳይቀር እጃቸው ረዘም ያለ እንደነበረ ቢታወቅም፣ በአሁኑ ወቅት ጫናው እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ 
በመስኖና የውኃ ሚኒስትር የወሰንና የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሱዳኖች በዓባይ ውኃ ጥቅማቸው የሚጠበቅላቸው ከግብፆች ጋር በማበራቸው ሳይሆን ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር በመተባበራው መሆኑን በተግባር ታዝበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተከዜ ግድብ በመገደቡ ምክንያት ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ገበሬዎች በመስኖ ከፍተኛ ልማት እያከናወኑ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ቀደም ሲል በጎርፍ ይጥለቀለቁ እንደነበር፣ አሁን ከዚህ ችግር መገላገላቸውና በደለል ይሞላ የነበረው ወንዛቸው አሁን ከዚህ ችግር ወጥቶ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሲሰጥ ማየታቸው ለሱዳኖች አቋም መለወጥ ዋና ምክንየት መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ 
ዶ/ር ያሲር መሐመድ በሱዳን የውኃ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በኔዘርላንድስ ደግሞ የዩኔስኮ የውኃ ትምህርት ተቋም የውኃ ሀብት ተጋባዥ መምህር ናቸው፡፡ ከሦስት ወራት በፊት በመቐለ በተካሄደው አንድ የውኃ ኤክስፖርቶች ቴክኒካዊ ምክክር ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በአጋጣሚ አግኝተናቸው ስለጉዳዩ አጭር ቆይታ አድርገን ነበር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የግብፅ ሥጋት ኢትዮጵያ በምትገነባው ግድብ የውኃው መጠን እንዳይቀንስ አይደለም፡፡ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች በወንዙ ሊለማ የሚችል መሬት ተደምሮ አንድ ላይ የሱዳንን ያህል አይሆንም፡፡ እስካሁን ግን ሱዳን በከፍተኛ ደረጃ የመስኖ ልማት እምብዛም ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ የወደፊት ዕቅዷ ግን ይኼንን ውኃ ጥቅም ላይ በማዋል ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን መሳብ ነው፡፡ እንደሳቸው እምነት፣ ግብፅ የምትጎዳው እዚህ ላይ ነው፡፡ የውኃውም መጠን የሚቀንሰው ሱዳን ውኃውን ለመስኖ መጠቀም የጀመረች ቀን ነው፡፡ 
ዶ/ር ያሲር መሐመድ እንደሚሉት፣ ግብፆች ግልጽ ባያወጡትም በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳዩት ተቃውሞ በተዘዋዋሪ  በዋናነት በሱዳን ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ‹‹የውክልና ጦርነት ነው፡፡ እውነተኛ ችግራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከሱዳን ጋር ነው፡፡ ውዝግቡን ግን ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሆን ይመርጣሉ፤›› ብለዋል፡፡ 
የታላቁ የዓባይ ግድብ መገንባትን የሚደግፉት የውኃ ተመራማሪው እንደሚሉት፣ የሱዳን መንግሥት ሰፊ ለም መሬቱን ተጠቅሞ በመስኖ ማልማት የሚችለው ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ግድቦችን ከሠራች ብቻ ነው፡፡ ‹‹ግብፆችም ሱዳኖችም ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን የሚገነዘቡ አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ስትራቴጂካዊ የሆነ ትብብር ማድረግ አለባቸው፡፡
የሱዳኑ የውኃ ምሁር አስተያየት ማረጋገጫ የሚመስል አንድ መረጃ ተገኝቷል፡፡ የተከዜ ግድብ ከተሠራ በኋላ የደለል መሙላት በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፣ የሱዳኑ አትባራ ወንዝ የውኃ መጠን በአሥር እጥፍ መጨመሩ የሱዳን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ 
ሱዳኖች ያሳዩት የአቋም ለውጥ ከራሳቸው ተጨባጭ ጥቅም በመነሳት መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት በበዓሉ ላይ መገኘት ጥልቅ የሆነ ወዳጅነት መመሥረቱ አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ‹‹መምጣታቸውም ለአገራችንና ለሕዝባችን ያላቸውን ጥልቅ ድጋፍና ከበሬታ የሚያሳይ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የሁለቱም አገሮች ወዳጅነት ምን ደረጃ እንደደረሰ አመላካች መሆኑን በማስረዳት፡፡
ሱዳንና ኢትዮጵያ ትናንትና
የሱዳንና ኢትዮጵያ ግንኙነት ታሪክ ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተለየ አይመስልም፡፡ አንዱ የሌላውን አማፂ ቡድን የመደገፍ አዝማሚያዎች ያሳዩ ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ ኢትዮጵያ በቅርቡ ነፃነታቸውን ላገኙት የደቡብ ሱዳን ኃይሎች (SPLM) እና በተቀረው የሰሜን ሱዳን አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አማፂዎችን ትደግፍ ነበር፡፡ ሱዳን በበኩሏ፣ አሁን ሥልጣን ላይ ላለው ሕወሓት፣ ለኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅትና በሕወሓት አሸናፊነት ለተበታተነው ለኢዲዩ ከፍተኛ ወታደራዊና የትጥቅ ድጋፍ ታደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 
የሁለቱም አገሮች ጐርባጣ ግንኙነት የተቀየረው ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ነበር፡፡ ባለፉት ቅርብ ዓመታትከ ኢትዮጵያ ጋር ያላት መልካም ጉርብትና በቀዳሚነት የሚነሳ ነው፡፡ የሱዳን ገዢ ፓርቲ ብሔራዊ እስላማዊ ግንባር (National Islamic Front - NIF) እና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አል በሽር ከኤርትራ እስላማዊ ኃይሎችና ከኤርትራ መንግሥት በተለይ ደግሞ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያላቸው አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚለው ግንኙነት፣ የኢትዮ ሱዳን ትብብር ዘላቂነትን ሁሌም ጥርጣሬ ላይ የሚጥለው ነበር፡፡
በሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የጋራ የድንበር ኮሚሽን አማካይነት በቅርቡ የድንበር መካለል ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት ትችቶችን ባይቀበልም፣ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን እየተሰጠ ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ሲሰማ ሰንብቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ሁለቱም አገሮች በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሠረተ ግንኙነት አላቸው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ በሁለቱም ሱዳኖች መካከል በተከሰተው የድንበር ጦርነት ዋና ገለልተኛ ሸምጋይ ሆና የተገኘች ሲሆን፣ በተመድ ጥላ ሥርም ቢሆን አቢዬ ላይ ከሠፈረው ሰላም አስከባሪ ኃይል አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ የተውጣጡ ወታደሮች ይገኙበታል፡፡ 
ደቡብ ሱዳኖች ነፃነታቸውን በሕዝበ ውሳኔ ከማግኘታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ፣ በዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት የክስ ዋራንት ተቆርጦባቸው የነበረው ፕሬዚዳንት አል በሽር የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ድጋፍ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ በወቅቱ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነታቸው ከፍ ብሎ የነበረው አቶ መለስ፣ ፕሬዚዳንት አል በሽርን ከዚህ ክስ ነፃ እንዲሆኑ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ያደረጉት የተሳካ ጥረት ለሱዳን ፕሬዚዳንትና መንግሥት ትልቅ እፎይታ የሰጠ ነበር፡፡
Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog