የግብፅ እጅ መንሻ?

በተጠናቀቀው ሳምንት የግብፅ ወጣት የዲፕሎማሲ ሠልጣኞች ቡድን በአዲስ አበባ የአንድ ሳምንት ቆይታ አድርጓል፡፡ ሪፖርተርን ጨምሮ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችም ጥሪ ተደርጐላቸው ከግብፅ ልዑካን ቡድን ጋር ለመነጋገርና ለመወያየት ተጋብዘዋል፡፡ 
በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሐመድ እድሪስ ስለ ቡድኑ መምጣት፣ ዓላማና ግብ እንዲሁም የቡድኑ አባላት ማንን እንዳነጋገሩ፣ የት የት እንደሄዱ ገልጸው፣ በየዓመቱ የግብፅ መንግሥት ሠልጣኝ ዲፕሎማቶቹን ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች አፍሪካ አገሮች ልምድ እንዲቀስሙ እንዲህ ዓይነት ጉዞ እንደሚያዘጋጅላቸውና ይህም እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞው ብቻ እንደ አንድ ልማድ ተደርጐ እየተወሰደ መሆኑን በኤምባሲው ለተገኙ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ገለጻ አድርገዋል፡፡ 

የግብፅ አምባሳደር መሐመድ እድሪስ፣ ‹‹ሠልጣኞቹ በወሬ ከሚሰሙትና በቃል ከሚያወሩት እዚህ በአካል መጥተው ኢትዮጵያን መመልከታቸው እጅግ አስደስቷቸዋል፤ እናም ራሳቸው ሠልጣኞቹ
የተሰማቸውን ይገልጹላችኋል፤›› ካሉ በኋላ ሁሌም በተገኘው አጋጣሚ ደጋግመው የሚገልጹትና እንደ ልማድ የሚመስል ንግግራቸውን ጣል አድርገዋል፡፡ ንግግራቸው የብዙ ሰዎችን ቀልብም የሚስብ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያና ግብፅ ጥንታዊያን ናቸው፡፡ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤትም ናቸው፡፡ ሁለቱም እህት አገሮች፣ በሺዎች የሚቆጠር ዘመን የከፍታ የሥልጣኔ ምንጭ አንድ ነው፡፡ እሱም የዓባይ ወንዝ ነው፡፡ ሁለቱም ትላልቅ ሕዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት ከአንድ ወንዝ የተቀዳ ሥልጣኔ ስላላቸው ብቻም አይደለም፡፡ አንድ ዓይነት ባህልና ታሪክ ተጋርተዋል፡፡ የሚያስተሳስራቸው ረዥሙ የዓባይ ወንዝ ብቻም ሳይሆን ይኼው ሥልጣኔም ጭምር ነው፤›› የሚል ነበር፡፡
ግብዣ የተደረገላቸው ተወካዮችም አጭር ገለጻና ንግግር አድርገዋል፡፡ ሠልጣኝ ዲፕሎማቶቹ እዚህ መምጣታቸው በጣም እንዳስደሰታቸው፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር ገንቢ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ 
በመቀጠልም በሥፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች ለሠልጣኝ ዲፕሎማቶቹ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል ተሰጠ፡፡ ወጣት ዲፕሎማቶቹ በአገራቸው (በግብፅ) ያሉ ትላልቅ ሚዲያዎች ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን አለመግባባት እንዴት እንደሚዘግቡትና በዚህ ረገድ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያካፍሉ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጥያቄ ተሰንዝሮላቸዋል፡፡ ከወጣት ዲፕሎማቶቹ አንዱ ጥያቄውን የመለሰ ሲሆን፣ ምላሹም አጭርና እንዲህ የሚል ነበር፡፡ ‹‹የዓባይን ወንዝ ኢትዮጵያውያንም ግብፆችም ይፈልጉታል፡፡ ለኢትዮጵያ የህልውናዋ ጥያቄ ነው፡፡ ዕድገቷና ልማቷም እዚህ ወንዝ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለግብፅም እንዲሁ፡፡ የግብፆች ሕይወት ከዓባይ ወንዝ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ አጠቃቀሙን በተመለከተ በትብብርና በምክክር ሁለቱንም አገሮች በማይጐዳ መንገድ መጠቀም አለባቸው፡፡ ሚዲያዎችም አዎንታዊ ሚና መጫወት አለባቸው፤›› ብሏል፡፡
በመቶ ሺዎች የሚታተመው የግብፅ አል አህራም ጋዜጣን ጨምሮ ሌሎች በዓባይ ወንዝና በታላቁ የዓባይ ግድብ ላይ ለዓለም የሚያሠራጩት ዘገባ ግን እጅግ የተዛባና ሚዛን የሳተ እንደሆነ የብዙ ኢትዮጵያውያን እምነት ነው፡፡ ወጣት ዲፕሎማቶቹ አስተያየት እንዲሰጡ የተፈለገው በግብፅ ሚዲያ የዓባይ ፖለቲካ አያያዝ ላይ ቢሆንም የጥያቄውን ጭብጥ አድበስብሰው አልፈውታል፡፡
‹‹ጥቃት ፈጸምክብን››? 
አርባ አምስት አባላት የያዘው ይኼው የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ወንድም ሕዝቦች ለመማርና ፍላጐታቸውን ለመስማት መምጣቱን አንድ የቡድኑ አባል አብራርቷል፡፡ መንፈሱም ይህንን ይመስላል፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች የዲፕሎማሲ ሰዎች ንግግርን ማመን ይቸገራሉ፡፡ ምክንያቱም ዲፕሎማቶች ፖለቲከኞች እንደመሆናቸው ለጥቅማቸው ሲሉ ያጣላሉ፣ ያስታርቃሉ የሚል እምነት በመኖሩ ነው፡፡ የቡድኑ መሪ በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዲፕሎማሲ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር አምባሳደር ዓሊ አልሃዲዴና አምባሳደር መሐመድ እድሪስ፣ ወጣት ዲፕሎማቶችና ወጣት ጋዜጠኞች ሁለቱ አገሮች መልካም ግንኙነት እንዲፈጥሩ ትልቅ ድልድይ ሊሆኑ እንደሚገባቸው በመግለጽ፣ ወጣት ዲፕሎማቶቹ ለቀረበላቸው የሚዲያ አዘጋገብ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ አጠናክረዋል፡፡
ሆኖም የአምባሳደሩንና የዳይሬክተሩን ንግግር ሳይለዝዝ፣ ይኼው ተቃራኒ የሚመስል ድርጊት ሲፈጸም ተስተውሏል፡፡ በርካታ ጥያቄዎችንም አስነስቷል፡፡ 
በቅርቡ በኤምባሲው ተገኝተው በግብፅ ወቅታዊ ሁኔታና በግድቡ ዙርያ አስተያየት የሰጡት ግብፃውያን በተመለከተ የተሠራ ዘገባ የተቃርኖ ምንጭ ሆኗል፡፡  
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ለአንድ ዓመት ጥናት ያደረገው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ሪፖርቱን ለሦስቱ አገሮች ቢያቀርብም፣ ለመገናኛ ተቋማት ሚስጥር እንዲሆን ግን ስምምነት ነበረ፡፡ ይሁን እንጂ የባለሙያዎች ቡድንም ሆነ የሦስቱ አገሮች መንግሥታት በሚስጥር የያዙት መረጃ ብሉምበርግ በተባለ የመገናኛ ተቋም ይፋ ሆኗል፡፡ መረጃው በሚዲያ እንዲወጣ ያደረገው የግብፅ መንግሥት መሆኑን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሪፖርቱን ዋና ድምዳሜ አሉታዊ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተሠራ እንደሆነ ያምናል፡፡ በጋዜጣውም የተጻፈው ይኼው ነው፡፡ በኤምባሲው ከሚገኙ ዲሎማቶች አንዱ ግን ይህንን ዘገባ በሥፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች ለማስነበብ ይጣደፋል፡፡   
ይህ ዲፕሎማት በሥፍራው ከተገኙ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ከአንዱ ጋር ተቃርኖ ያለው ይመስላል፡፡ ጋዜጠኛውን ተመልሶ ማናገር እንደሚፈልግ በዓይኑ እየጠቆመ ‹‹አንተ በጥባጭ›› በማለት እየተጣደፈ ሄደ፡፡ በጥድፊያ መሄዱን ተከትሎ ሌላው የኤምባሲ ቪዛ ክፍል ኃላፊ ወጣና ጋዜጠኛውን ወደ አንድ የእንግዳ መቀበያ ጥግ ወስዶ አነጋግሮታል፡፡ ‹‹ሦስት ጊዜ ጥቃት ፈጸምክብን›› በሚል መነሻ ንግግሩ ቀጠለ፡፡ ጋዜጠኛው ያልተባለ ነገር ሪፖርት ተደርጐ ከሆነ፣ ኤምባሲው ለሚዲያ ተቋሙ ቅሬታውን መግለጽ እንደሚችል ገለጸ፡፡ የቪዛ ክፍል ኃላፊው ቁጣ ቁጣ እያለው፤ ‹‹በጣም ነው የሚያሳዝነው፤ እኛ በግብፅ ነፃ ትምህርትና ሥልጠና የምታገኝበትን ዕድል እየፈለግን እንዴት እንዲህ ዓይነት ነገር ትጽፋለህ?…›› በሚል ንግግሩን ቀጠለ፡፡ ቀደም ሲል በነገር ሸንቆጥ አድርጐት የሄደው ሠራተኛም መጣና ነገሩን አከለበት፡፡ በሁኔታው ማዘኑን የገለጸው ጋዜጠኛውም፣ እንዲህ ዓይነት ጥቅማ ጥቅም እንደማይፈልግ አስረዳ፡፡ መጠነኛው ጭቅጭቅ ቀጠለ፡፡   
ሁኔታውን ከሩቅ ሆነው ሲመለከቱ የነበሩት ነገሩ ያልጣማቸው የሚመስሉት አምባሳደር መሐመድ እድሪስ ጠጋ ብለው አስታራቂ ንግግር ሲጀምሩ፣ የሚዲያ ሚናን በተመለከተ የተጀመረው ንግግር ወደ ጥያቄና መልስ ተቀየረ፡፡ ሌሎች የመንግሥትና የግል ጋዜጠኞችም ተቀላቀሉና አጋጣሚው ወደ መግለጫ ተቀየረ፡፡ 
በአጋጣሚው ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ግብፅ በቅርቡ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ውዝግብ ወደ የተባሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማቅረቧ መዘገቡን አስመልክቶ ‹‹እውነት ነው ወይ?›› የሚል ነበር፡፡ አምባሳደሩ በሰጡት ምላሽ በቅርቡ የተቋረጠው ውይይትና ድርድር መቀጠል እንዳለበት፣ አገሮቹ በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ቢያቅታቸው እንኳ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ድርድራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ ‹‹ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ተመድ መውሰዷ የተገለጸ ነገር የለም፣ አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡
ታሪካዊ አንድምታው 
የተለያዩ መዛግብት እንደሚያሳዩት ከጥንት ጀምሮ ግብፃውያን የዓባይን ምንጭ የመቆጣጠር ፍላጐት ነበራቸው፡፡ ለበርካታ ጊዜያት በሃይማኖት ስም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠራቸው የሚነገር ሲሆን፣ አንዱ ቡድን በሌላው ላይ እንዲያምፅ በመደገፍ፣ አንዳንዴም በቀጥታ ጦርነት በመክፈት በርካታ ሙከራዎች ማድረጋቸው ሰፍሯል፡፡ 
በአብዛኛው ያደረጉዋቸው ሙከራዎች ያልተሳኩ ቢሆንም፣ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ነገሥታት ወንዙን ጨርሶ ለመዝጋት በማስፈራራታቸው ምክንያት ከፍ ያሉ ስጦታዎች መቀበላቸው ይነገራል፡፡ በአገር ደረጃ ይኼ ነው የሚባል ክህደት የፈጸመ ንጉሥ ወይም መሪ ግን ነበር ለማለት የሚያስችል ምንም መረጃ የለም፡፡
በ1876 ዓ.ም. በጉንደት ከግብፆች ጋር በተደረገው ከፍተኛ ጦርነት ግብፆች ያለወሬ ነጋሪ የተሸነፉ ሲሆን፣ ምናልባትም ተመሳሳይ ሙከራ እንዳያደርጉ ትልቅ ትምህርት የሰጣቸው ይመስላል፡፡ ታላቁ የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ይፋ መሆኑን ተከትሎ፣ ከካይሮ ለተሰነዘሩ ዛቻዎችም ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው ምላሽ ይኼው ነበር፡፡ ‹‹ከታሪክ የማይማሩ ብቻ ከሆኑ ኢትዮጵያን ይወራሉ፤›› የሚል፡፡ 
በዚሁ ታሪካዊ የጉንደት ጦርነት ግን አሁንም መነሳት ያለበት አንድ ክስተት አለ፡፡ በአንዳንድ መዛግብት እንደተገኘው ጦርነቱን በድል ያጠናቀቁት አፄ ዮሐንስ አራተኛ፣ በኢትዮጵያ ጦር ከተማረኩት መካከል በርከት ያሉ ሐበሾችን ይመለከታሉ፡፡ ‹‹እናንተ የአገሬ ሰዎች አይደላችሁም? ምን ነካችሁ ከግብፆች ጋር ሆናችሁ አገራችሁን የምትወጉ?›› በማለትም ይጠይቋቸዋል፡፡ 
አብዛኞቹ ከአገር በፊት ሃይማኖታችንን እናስቀድማለን የሚል ምላሽ ሲሰጡ፣ ሌሎች ደግሞ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደተሰጣቸው ሳይደብቁ ገልጸውላቸዋል፡፡ ንጉሡና ጄኔራላቸው ራስ አሉላ አባ ነጋ ድርጊቱ እጅግ ቢያበሳጫቸውም ሰዎችን በምክር ገስፀው ምሕረት አድርገውላቸዋል ይባላል፡፡ 
በተለያዩ ሙከራዎች የዓባይን ምንጭ መቆጣጠር ያቃታቸው ግብፆች፣ ኢትዮጵያን ለማዳከም የተለያዩ ሥልቶች እንደሚጠቀሙ በርካታ የታሪክ ምሁራን ጽፈዋል፡፡ 
በአምባሳደርነት ግብፅን ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት አሕመድ አል ራሺድና ሃምዲ ሐሰን “The Nile River and Egyptian Foreign Policy Interests” በሚል በቅርቡ ያሳተሙት ጽሑፍ፣ የግብፅ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በአብዛኛው በዓባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ሲያስረዱ፣ በወንዙ ተጋሪ አገሮች ውስጥ ምንም ዓይነት የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይኖር፣ ቢኖርም አንዱ በሌላው ላይ አለመደገፍ መርህ እንደሚከተል ያስረዳሉ፡፡ ይህንን መርህ በሱዳንና በኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆናቸውንም ጽፈዋል፡፡ 
ኤርትራን ለማስገንጠል በረሃ የወጡት የጅብሐ መሥራቾች የመጀመርያ ሥልጠና ያገኙት ግን ካይሮ ውስጥ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኦነግና ኦብነግም ከግብፅ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያገኙ እንዲሁ ይገለጻል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው ግንቦት ሰባት መሥራቾችም ግብፅ በታላቁ የዓባይ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም መደገፋቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ፣ ከግብፅ ገንዘብ ተቀብለዋል ከሚል ውንጀላ ጀምሮ የተለያዩ ወቀሳዎች ይሰማሉ፡፡ በአሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ እንዲታወጅ የሚሰብኩ አንድ ግብፃዊ ሼክም፣ በበርካታ መሰሎቻቸው ድጋፍ ሲቸራቸው በቪዲዮ ታይቷል፡፡ 
ግብፆች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ግድብ እንዳይሠራ፣ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በመሰግሰግ ብድርና ዕርዳታ ለማስከልከል ተሳክቶላቸዋል፡፡ በቅርቡም እነዚህ የገንዘብ ተቋማትም ሆኑ ኃያላን አገሮች ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ካላቋረጠች ለሌላም ዘርፍ የሚውል ዕርዳታና ብድር እንዳይሰጡ እየተማፀኑ መሆኑን መንግሥት አሳውቋል፡፡ 
የግድቡ ግንባታ እንደማይቋረጥ የተገነዘቡ ግብፃውያን የሚይዙት የሚጨብጡት የጠፋባቸው ይመስላል፡፡ የዓባይን ወንዝ መጠቀም የሚከለክል አንቀጽ በሕገ መንግሥታቸው ማካተትን ጨምሮ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እስከ መውሰድ መዘጋጀታቸው ይነገራል፡፡   
ይህንን የግብፅ ስትራቴጂ የሚገነዘቡት መንግሥትን፣ ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ፣ በማናቸውም መንገድ ግድቡ መደናቀፍ እንደሌለበት ለሪፖርተር እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ዓይነት መደለያዎችና ማባበያዎች የሚታለሉ ኢትዮጵያውያን ወይም የመንግሥት አካላት እንዳይኖሩ ግን መንግሥት ብርቱ ክትትል እንዲያደርግ ይጠይቃሉ፡፡        
Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog