የእግር ኳሱን አንኳር ችግር መንካት የተሳነው ግምገማ

ክስተቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጥሩም በመጥፎም እያነጋገረ ሰንብቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት አንዳንዶች ‹‹በአጋጣሚ›› አንዳንዶች ደግሞ ‹‹በጥረት›› በሚሉት መንገድ ወደ አፍሪካ ዋንጫ፣
እንዲያም ሲል ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከአሥር የአፍሪካ ምርጦች አንዱ ሆኖ የመጣው የዋሊያዎቹ ቡድን፣ እንደ አመጣጡ መጓዝ ተስኖት የተሰናበተ የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ትዝብት ውስጥ ጥሎታል፡፡

አንድም ጐል ሳያስቆጥር በሁሉም ግጥሚያዎች ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ መሆኑ ብዙ አስነቅፎታል፡፡ ከሕዝቡ የተሰነዘረበት ትችት የበረታ መሆኑን ተከትሎ ተጨዋቾቹ፣ አሰልጣኙና ሌሎችም በቡድኑ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው አካላት ቅሬታቸውን ሲያሰሙ
ቆይተዋል፡፡
ተጫዋቾቹ በተለይ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በሚዲያ የሰነበተው ትችት ለውጤቱ መበላሸት አስተዋጽኦ ማድረጉን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ከዚሁ በመቀጠል ብሔራዊ ቡድኑን በሚመለከት ግምገማም ተደርጓል፡፡ ግምገማው ላይ ከሞላ ጐደል የእግር ኳሱ ችግሮች ቢቃኙበትም፣ ነገር ግን ደግሞ በስፖርቱ ዘርፍ ሁሉም ባለድርሻና የሚመለከታቸው ሁሉ ተሳትፈዋል ማለት ግን ይከብዳል፡፡
ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በሽልማት የተበረከተበት የዋሊያዎቹ ቡድን፣ በበቂ ተተኪ ተጨዋቾች አለመደራጀቱ፣ ለሽንፈቱና ለደካማ ተወዳዳሪነቱ ከተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ በዋናነት ጐልተው የወጡ ነበሩ፡፡
እንደሚታወቀው 2004/05 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለዓመታት ሲቆዝምበት ከኖረው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች ከታሪክ ነጋሪነት ተላቆ በመጠኑም ቢሆን አንድ ዕርምጃ ወደፊት የሔደበት ዓመት ነበር ቢባል የሚያከራክር እንዳልሆነ የብዙዎች እምነት ሆኖ ቆይቷል፡፡
በአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) የዋሊያዎቹ ተሳትፎና ውጤቱ ግን ጐምዛዛ ሆኖ የቀደመውን ሁሉ ጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በዚሁ መነሻነት ይመስላል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የብሔራዊ ቡድኑን የቻን ተሳትፎ አስገምግሟል፡፡
በግምገማው የተጠበቀውና የሆነው
በአገሪቱ እግር ኳስም ሆነ በሌሎች ስፖርቶች ዜጐች ችግሮች ሰፍተው ትልቅ ጥፋት ከማስከተላቸው በፊት ከጅምሩ እርምት እንዲደረግባቸው ጥቆማዎቻቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማሰማት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ ሰሞኑንም ካለፉት ሁለት ዓመት ወዲህ መጠነኛ መነሳሳት የታየበት እግር ኳስ በቻን ላይ ያሳየውን ተሳትፎ ተከትሎ የችግሩን መንስኤና መፍትሔውን ጭምር እያመላከቱ ናቸው፡፡ 
ቅሬታውንና ጥቆውን ሲያዳምጥ የሰነበተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ቅዳሜ ባዘጋጀው መድረክ፣ የብሔራዊ ቡድኑ የቻን ተሳትፎ በሙያተኞች እንዲገመገም አድርጓል፡፡ የግምገማው አካሔድ በተጠባባቂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ይግዛው ብዙአየሁ አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ መኰንን ኩሩ በቁጥር የተደገፉ ቴክኒካዊ ጉዳዮችና እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ የቡድኑን የሜዳ ላይ ተግባራት የተመለከተ በዋና አሰልጣኙ አቶ ሰውነት ቢሻው አማካይነት በፕሮጀክተር የታገዙ ማብራሪያዎች ቀርበው ነበር፡፡ 
አስተዳደራዊ ተብለው ከቀረቡት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሶማሊያ አቻው ጋር ካደረገው የማጣርያ ማጣሪያ ጨዋታ ጀምሮ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደተደረገለትና 14 ሚሊዮን 878 ሺሕ ብር የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተለት ተሰምሮበታል፡፡ ቀጥሎም እንደ ድክመት በአመራሮችና ቡድን መሪዎች ቸልተኝነት የተጠቀሰው በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ወቅት በፊፋ የተላለፈው የሦስት ነጥብ ቅጣት ውሳኔ ነው፡፡ ያጋጠሙ ችግሮች ተብሎ ከቀረቡት ደግሞ ለቡድኑ አልባሳት የሚውሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ትጥቆች ጥራትና መጠን በገበያ ላይ አለመገኘት የሚሉት ናቸው፡፡ 
ቴክኒክን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሜዳ ውስጥ ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች በቁጥር በማስደገፍ ከመግለጽ ባለፈ፣ የቡድኑን ጥንካሬና ድክመት የሚያመላክቱና ጥልቀት ያላቸው ቴክኒካዊ ማብራሪያዎች የቀረቡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ከግምገማው ተሳታፊዎች አንዳንዶቹ ‹‹ሪፖርቱ በጨዋታ ወቅት ከሁለት ተጋጣሚ ቡድኖች የትኛው የተሻለ የኳስ ቁጥጥርና የግብ ሙከራ አደረገ የሚለውን ለመለየት ከሚቀርበው ስታስቲክስ የተወሰደ›› በማለት ሲተቹት ተደምጠዋል፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት በበኩላቸው፣ እሳቸው ለሚመረጡት አጨዋወት ይመጥናሉ ያሉዋቸውን ተጨዋቾች እንደመረጡ፣ ውጤቱን በተመለከተም ተጠያቂነቱን እንደሚወስዱ ከተናገሩ በኋላ ሁሉም የሚናገረውና የሚተቸው እውነት ለለውጥ ከሆነ ለእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ የሕይወት አቅጣጫቸው ሲሉ እንደሚቀበሉትና ከእነዚሁ አካላት ጋር አብረው ለመሥራት ቃል እንዳሚገቡ ጭምር ያስረዱት ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ሦስቱም ተናጋሪዎች አንዱ የሌላውን ጥንካሬና ድክመት ለማሳየት የሞከሩበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ 
ከሦስቱ ሰዎች ማብራሪያ በኋላ ለግምገማው የመጡትን ሙያተኞች በቡድን በመከፋፈል የቀረበውን ማብራሪያ መሠረት አድርገው እንዲወያዩ፣ ከዚያም ከመካከላቸው አንድ ሰው በመምረጥ ቡድኑ የደረሰበትን ጭብጥ ገለጻ እንዲያደርግ ነበር የተደረገው፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹የኮሚቴው አቋም ነው›› ተብሎ አልፎ አልፎ እውነተኛ የእግር ኳሱን ችግሮች ለማሳየት ከተሞከረው ውጪ በአብዛኛው የ‹‹እከክልኝ ልከክልህ›› ዓይነት ሆኖ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ 
የመድረኩ ሰብሳቢና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ገለጻ ባደረጉት ሙያተኞች ላይ ‹‹ተጨማሪ አስተያየትና ጥቆማ አለኝ›› የሚል ካለ ዕድሉን ቢሰጡም፣ ቀድሞውንም ጥሪውና የቡድን ስብጥሩ በ‹‹ኔትዎርክ›› የተጠላለፈ ነበርና አንዱ አንዱን ከመተያየት ባለፈ ደፍሮ የቀረበው ገለጻ የ‹‹እኔ ሐሳብ አይደለም›› ብሎ ለመናገር የሞከረ አልነበረም፡፡
ግምገማውን አስመልክቶ በዕረፍት ሰዓት ያነጋገርናቸው አንዳንድ የግምገማው ተሳታፊዎች፣ ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሙያተኞች በአገሪቱ የእግር ኳስ ችግሮችና መንስዔዎች ላይ ተወያይተው የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማሳየት ፍላጐት ቢኖረው ግምገማውን በቡድን ከፋፍሎ እንዲከናወን ከማድረግ ይልቅ በተናጠል መድረኩ ላይ እንዲደረግ ነፃ ማድረግ ነበረበት፡፡ ከዚያም በላይ ለግምገማው የሚመጥኑ ትክክለኞቹ የሙያው ሰዎች ጥሪ አልተደረገላቸውም፡፡ ጥሪው እውቂያና ቅርበትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ማግስት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የዚህ ተመሳሳይ የግምገማ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ዛሬ ያነሳናቸው ችግሮች በዚያን ወቅትም ተነስተው የተለወጠ አንዳች ነገር የለም፡፡ ከዓመት በኋላ መልሶ ያንኑ በመድገም ቂምና ጥላቻ ለማትረፍ ካልሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ሌላው ግምገማው ለእግር ኳሱ መፍትሔ ለመሻት ከሆነ፣ የአንድ ብሔራዊ ቡድን ቴክኒካዊ ግምገማ የቡድኑን መሠረታዊ የሆኑ ቴክኒካዊ ግምገማዎች፣ ማለትም ቡድኑ በዝግጅት ወቅት፣ ቡድኑ በጨዋታ ወቅትና ከዚያም አልፎ የተጋጣሚ ቡድኖች ከጨዋታ በፊት የነበራቸውን ጠንካራ ደካማ ጐን ምን እንደሚመስል የተመለከተበትን ዕይታ፣ ከዋና አሰልጣኙ ጋር በመነጋገር የደረሰበት ጭብጥና በዚያ መሠረት አሰልጣኙ ተግባራዊ ያደረጋቸውን፣ ያላደረጋቸው ብሎ ለቀጣይ እርምት ማድረግ ይቻል ዘንድ በጥልቀት ማሳየት ሲገባው፣ በቁጥር የተደገፈ የጨዋታ ስታትስቲክስ በቀረበበት የግምገማ ሪፖርት ለማን ነው የምናወራው? የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የዲሲፕሊን ሁኔታና ትርጉም በሌለው አስተዳደራዊ መዋቅር የሚዳክር ጽሕፈት ቤት ባለበት፣ ለተጨዋቾች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሸልሜያለሁ፣ ችግሬ ስታንዳርዱን የጠበቀ ምርት ነው በሚል የውይይት ሪፖርት ላይ ምን ማለት ይቻላል›› ብለው፣ ብንናገርም የምናተርፈው ‹‹ቂምና ጥላቻ እንጂ ለውጥ አይደለም›› ሲሉ ግምገማው ግምገማ የሚለውን መስፈርት እንደማያሟላ ተናግረዋል፡፡ 
ግምገማውን ግምገማ ያስመሰለው
በግምገማው ማጠቃለያ አስተያየታቸውን የሰጡት የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አምበሳው እንየው ናቸው፡፡ እሳቸው በሰጡት አስተያየትም በእግር ኳሱ ዙሪያ እየቀረበ ያለውን ግምገማ አስፈላጊነቱን አጽንዖት በመስጠት ቀጣዩን ትዝብታቸውን አቅርበዋል፡፡ ‹‹እግር ኳሱ የአገሪቱ የስፖርት ቤተሰብ ከጫፍ ጫፍ በጉጉትና በፍቅር የሚከታተለው ነው፡፡ ሰዎች አንሳሳት ትናንት ዛሬ አይደለም፡፡ አደረጃጀታችንና አሠራራችንን የግድ ከወቅቱና ከጊዜው ጋር በማቀናጀት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ አስተዳደሩ ከቴክኒክ ክፍሉ፣ አስተዳደሩ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፣ ቴክኒክ ክፍሉ ከብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው እንዲሁም ንኡሳን ኮሚቴው ከአስተዳደሩ ያላቸው አሠራርና አደረጃጀት የተደበላለቀ ነው፡፡ ያላቸው ኃላፊነትና የተጠያቂነት ወሰን አይታወቅም፡፡ እየተሠራ ያለው በስማ በለው ነው፡፡ ይኼ ችግር ነጥሮ ካልወጣ በስተቀር ችግሩ የሚቀጥል ነው የሚሆነው፤›› ብለው፣ ‹‹ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አለው፡፡ ዳይሬክተሩ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የብሔራዊ ቡድኑ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ዝግጅት ዕቅድ አውጥቶ የተከታተለበትና የገመገመበት ሁኔታ አለ? የሚቀመጠው ሙያተኛስ ምን ያህል በሙያው ያለፈ ነው ተብሎስ ታይቷል? የፌዴሬሽኑ ቅጥር ሙያን መሠረት ያደረገ ነው ወይስ በእውቂያ መለየት መቻል ይኖርበታል፡፡ የቴክኒክ ዳይሬክተርና የቴክኒክ ኮሚቴ ኃላፊነትና ድርሻ ተለይቶ መቀመጥ መቻል ይኖርበታል፡፡ ዳይሬክተር ብለን ካስቀመጥን ክፍሉ ከብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት አልፎ፣ የክለቦችን ሥልጠናና ዝግጅት የሚከታተልበትና የሚገመግምበት አሠራር ሊኖረው ይገባል፡፡ ክፍሉ ክለቦች ተተኪዎች ላይ እንዲሠሩ ምን ያህል የሙያ እገዛ እያደረገላቸው ነው? የቴክኒክ ሰው ምን ዓይነት ዕውቀትና አቅም ሊኖረው እንደሚገባ ገብቶን ነው የምንመድበው ወይስ በግምትና በእውቂያ? የጠራ አደረጃጀት መያዝ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህንና ተመሳሳይ የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጥ ማምጣት እስካልቻልን ድረስ ኅብረተሰቡም ሆነ ተቋሙ የሚፈልጉት ለውጥ አይመጣም፤›› ብለዋል፡፡
Source: Reporter
 

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog