የ2013 የአፍሪቃ ዓበይት ክንውኖች

ሊያበቃ ጥቂት ቀናት የቀረው 2013 ዓም በአፍሪቃ በፖለቲካው እና በማህበራዊው ዘርፎች ከታዩት ዓበይት ክንውኖች ጥቂቱ ባጭሩ ይቃኛል። 
እአአ መጋቢት አምስት፣ 2013 ዓም ኬንያ ውስጥ የአጠቃላዩ ምርጫ ቀን ነበር። ብዙ ሕዝብ ነበር ድምፁን ለመስጠት የወጣው። በተፎካካሪዎቹ ኡሁሩ ኬንያታ እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎቹ ጎራ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት ነበር የታየው። በምርጫው ኡሁሩ ኬንያታ አሸናፊ ቢሆኑም፣ ድላቸው አካራካሪ ነበር፣ ምክንያቱም፣ ከአምስት ዓመት በፊት እኢአ በ2007 ዓም የተካሄደው ምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ በተከተሉት ወራት በሀገሪቱ የ 1,200 ሰዎች ሕይወት የጠፋበትን ግጭት ቀስቅሰዋል በሚል ብዙዎች የሚወቅሱዋቸው ኬንያታ እና በምርጫው ዘመቻ ወቅት
ምክትላቸው እንደሚሆኑ ያጩዋቸው ዊልያም ሩቶ በስብዕና አንፃር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ጥርጣሬ ዘ ሄግ በሚገኘው በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት፣ በምሕፃሩ በአይ ሲ ሲ ክስ ተመሥርቶባቸዋል። ሆኖም ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ከተጠናቀቀ ከአራት ቀናት በኋላ ኬንያታ ተፎካካሪያቸውን ራይላ ኦዲንጋን በጠባብ የድምፅ ብልጫ ማሸነፋቸው በይፋ ተረጋገጠላቸው።
« ውድ የሀገሬ ዜጎች፣ ኬንያውያን ዛሬ የዴሞክራሲን ፣ የሰላምን ድል እና የብሔራዊ አንድነትን ድል እናከብራለን። በዓለም ብዙዎች ምርጫውን በትክክለኛ መንገድ ማካሄድ መቻላችንን ተጠራጥረውት ነበር፤ እኛ ግን ከጠበቁት በላይ ከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ብስለት አሳይተናል። » ።

ኬንያታ በአይ ሲ ሲ አንፃር የያዙትን አቋም ካጠናከሩ በኋላ የሀገራቸው ምክር ቤት ኬንያን ከአይ ሲ ሲ ምሥረታ ተፈራራሚ አባል ሀገራት ለማስወጣት ወስኖዋል። ይህ ውሳኔው ግን በኬንያታ እና በሩቶ ላይ በተመሠረተው ክስ ላይ የሚቀይረው ነገር አይኖርም። የኬንያታ ችሎት ያው ቀጠሮ እንደተያዘለት የፊታችን የካቲት በዘ ሄግ ይጀመራል
ግንቦት፣ 2013 በናጀሪያ አክራሪው የሙሥሊሞች ቡድn ቦኮ ሀራም በሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ ጥቃቱን አጠናከረ። የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን ጦራቸውን በቦኮ ሀራም አንፃር ከማሠማራቱ ጎን፣ በሦስት ያካባቢው ግዛቶች ውስጥ እስከተያዘው አውሮጳዊ ዓመት ማብቂያ ድረስ የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አወጁ። የገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይ አብዱላጂ ጃሎየፕሬዚደንቱን አቋም ገልጸዋል።
« ፕሬዚደንቱ ዝግጁ አይደሉም። በፍፁም ዝግጁ አይደሉም። አንድ ስንዝር መሬት እንኳን በጠላት(ቦኮ ሀራም) የሚያዝበትን ሁኔታ በቸልታ አይመለከቱም። » ይሁንና፣ የጦር ኃይሉ ዘመቻ አሁንም አከራካሪ ከመሆኑም ሌላ ያን ያህል ውጤታማ አይደለም። ባለፈው ሀምሌ በፖቲስኩም በአንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት ላይ በተጣለ የቃጠሎ አደጋ ቢያንስ 27 ተማሪዎች እና አንድ መምህር ተገድለዋል። ሌሎች ጥቃቶችም ተከትለዋል። ወደ 500 የሚጠጉ የፅንፈኛው አሸባሪ ቡድን በዚህ ወር መጀመሪያ በማይዱግሪ ከተማ በሚገኘው የአየር ኃይል ሠፈር ላይ በጣሉት ጥቃት አሁንም ጠንካራ መሆኑን ለማሳየት ሞክሮዋል።

ማይዱግሪ ነዋሪ ሙሀመድ ሙሳ የሰዓት እላፊ እያለ ይህን መሳይ ጥቃት በመጣሉ ቅር መሰኘቱን ገልጾዋል። « ጥቃቱ መንግሥት ባካባቢው ላለው የፀጥታ ችግር አንዳችም መፍትሔ እንደሌለው ነው ያሳየው። መንግሥት ስራውን በትክክል እንዲሰራ ነው የምንጠብቀው። ይህ ብቻ ነው ፀጥታ ሊያስገኝ የሚችለው። የአስቸኳይ ጊዜ የሚፈይደው ነገር የለም። »
የዚምባብዌ ላይላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሀምሌ ወር መጀመሪያ ላይ አጠቃላዩ ምርጫ በዚያው በሀምሌ 31፣ እንዲካሄድ ወሰነ። ከአምሥት ዓመት በፊት በሀገሪቱ በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ እንደሚታወሰው የተቃዋሚው ወገን ዕጩ ሞርገን ቻንጊራይ ካለፉት ሦስት አሠርተ ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን በሰፊ የመራጭ ድምፅ ነበር የመሩት። ይሁንና፣ የመለያው ምርጫ ሊደረግ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው እና ሙጋቤ በኃይሉ ተግባር መጠቀም ሲጀምሩ ቻንጊራይ የኃይሉ ተግባር እንዳይባባስ በመስጋት ዕጩነታቸውን ሰረዙ። ይህም ካለ ተፎካካሪ የቀረቡትን ሙጋቤ በሥልጣናቸው እንዲቆዚ አስችሎዋል። በዚህ ዓመቱ አጠቃላይ ምርጫም ወቅት ሙጋቤ በምርጫ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያለ ነገር መሆኑን ነበር ለተፎካካሪዎቻቸው ለማጉላት የሞከሩት።

« አንድ ሰው ራሱን ለአንድ ውድድር ካቀረበ ሁለት አማራጮች ብቻ መኖራቸውን አውቆ መግባት ይኖርበታል። ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ፤፣ ሁለቱን ማግኘት አይቻልም። ወይ ታሸንፋለህ ወይም ትሸነፋለህ። ከተሸነፍክ ሽንፈትህን መቀበል ይኖርብሀል። እና እኛ ይህንን እናደርጋለን፣ ደንቡንም እናከብራለን።
በይፋ በወጡ ውጤቶች መሠረት፣ ፈላጭ ቆራጩ ሙጋቤ በ2013 ዓምም ሥልጣናቸውን እንደገና ለማጠናከር ችለዋል፤ እንዲያውም በምክር ቤት ውስጥ ሕገ መንግሥቱን መቀየር የሚያስችላቸውን ፍፁሙን የመራጭ ድምፅ ነው ያገኙት።

በማሊ የቀድሞው ፕሬዚደንት አማዱ ቱማኒ ቱሬ መጋቢት 2012 ዓም በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሀገሪቱ ቀውስ ላይ ትገኛለች። በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሱት የቱዋሬግ ዓማፅያን እና አክራሪ ሙሥሊሞች ጥቃታቸውን አጠናክረው አካባቢውን በመቆጣጠር ሕዝቡን ማሸበር እና ወደ መዲናይቱ ባማኮም ግሥገሣቸውን በጀመሩበት ጊዜ ፈረንሳይ ማሊን ለመርዳት እና የዓማፅያኑን ሂደት ለማስቆም ባለፈው ጥር 2013 ዓም በጦር ኃይሏ ጣልቃ ገባች። ከፈረንሳይ ድጋፍ ያገኘው የማሊ ጦርም ያማፅያኑን ቱዋሬጎች ግሥገሣ በመግታት የተኩስ አቁም ደንብ እንዲደርሱ ማድረግ ከተሳካለት ብኋላ ባለፈው ሀምሌ ወር ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ተካሂዶ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ አዲሱ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዚደንት ሆነዋል።
«በኢግዚአብሔር እና በማሊ ሕዝብ ፊት በመቆም ማሊን በታማኝነት ለመከላከል እና ሥልጣኔንንም የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደምጠቀምበት ፣ ዴሞክራሲን ለመጠበቅ እና የብሔራዊ አንድነትን እና የሀገሪቱን ነፃነት፣ እንዲሁምየግዛት ሉዓላዊነቱን ዋስትና ለማረጋገጥ እንደምሰራ እምላለሁ። »
በዓመቱ የመጨረሻ ወራት ግን በማሊ በተለይ በሰሜኑ ውጥረቱ እንዳዲስ ተካሮዋል። በቱዋሬግ ዓማፅያን እና በጦር ኃይሉ መካከል በተደጋጋሚ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ዓማፅያኑ ባለፈው ሀምሌ የደረሱትን የተኩስ አቁም አፍርሰዋል። ውጥረቱ ቢካረርም ግን በማሊ የፕሬዝደንት ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ፓርቲ እና ተጓዳኞቻቸው ምክር ቤታዊውን ምርጫ ማሸነፋቸው ተገለጸ። አንድ የመንግሥቱ ባለሥልጣን እንዳስታወቁት፣ በእሁዱ ሁለተኛ ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ ራሱን ለማሊ የተቋቋመ የጋራ ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ፓርቲ እና ሸሪኮቹ 147 መቀመጫዎች ባሉት ምክር ቤት ውስጥ 115ቱን አግኝተዋል።

መስከረም 21፣ 2013 ዓም በኬንያ መዲና ናይሮቢ፤ አሸባሪዎች ዌስትጌት የተባለውን ግዙፍ መደብር አጥቅተው በርካቶችን ገድለዋው ብዙዎችን አቆሰሉ። ለጥቃቱ የሶማልያ አሸባብ ቡድን ኃላፊነቱን ወስዶዋል።« ኬንያውያን አሁን በዌስትጌት የገበያ መደብር የደ,ረሰባቸው ጥቃት የናንተ ጦር ለሚፈፅመው ወንጀል ማካካሻ ነው። »
ኬንያ ጦሯን ወደ ሶማልያ ከላከች ወዲህ ሶማሊያውያን አሸባሪዎች ኬንያ ውስጥ በተደጋጋሚ ጥቃ ጥለዋል። ከጥቃቱ በኋላ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ባሰሙት ንግግር በጥቃቱ ዘመዶቻቸውን እና የዝርቦቻቸውን ላጡት ሀዘናቸውን ገልጸዋል። «በዚህ ጥቃት የቤተሰብ አባላትን ላጡ ወገኖች ሃዘኔን እገልጻለሁ። ምን አይነት የሃዘን ስሜት ዉስጥ እንዳሉ መገመት አይሳነኝም፤ ምክንያቱም እኔም በዚህ ጥቃት በጣም ቅርብ ዘመዶቼን አጥቻለሁ»
ጥቃቱ በተጣለ በአራተኛው ቀን የኬንያ ወታደሮች ወደ መደብሩ በመግባታ አምሥት አጋቾችን ገድለዋል። በጥቃቱን 67 ገደሉ፣ 300 አቆሰሉ፣ ከ 60 በላይ የሚሆኑትም ደብዛቸው እንደጠፋ ነው። ሞዛምቢክ ውስጥ የርስበርሱ ጦርነት ካበቃ ከሁለት አሠርተ ዓመት በኋላ የቀድሞው ያማፅያን ቡድን b ሬናሞ የ16 ዓመቱን የርስ በርስ ጦርነት ያበቃውን እአአ በ1992 ዓም ከገዚው የፍሬሊሞ ፓርቲ ጋ በይፋ የተፈራረመውን ውል ባለፈው ጥቅምት 2013 ዓም ማፍረሱን አስታወቀ። ሬናሞ ይህን ርምጃ የወሰደው የመንግሥቱ ጦር የጦር ሠፈሩን በቦምብ ያጠቃበትንና የያዘበትን ድርጊት በመቃወም ነበር።
ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ መንግሥት የተቃዋሚው ቡድን አባላትን በብዛት ማሰር ከጀመረ ወዲህ ሬናሞ በምላሹ በፀጥታ ኃይላት ላይ ጥቃቱን በማጠናከር ዋነኛውን መተላለፊያ መንገድ ዘጋ፣ ብዙዎች ይህንን ሂደት በሀገሪቱ ከሁለት አሠርተ ዓመታት በፊት ታይቶ የነበረው ዓይነቱ የከፋ ቀውስ ሊነሳ እንደሚችል የሚጠቁም ሆኖ ተመልክተውታል።
« በስጋት መንፈሥ ውስጥ ነው የምንኖረው። እርግጥ፣ በዋናው መተላለፊያ መንገድ መዘጋት በቀጥታ ተጎጂ የሆኑት ሰዎች ርምጃው ያን ያህል እንዳላስጨነቃቸው ገልጸዋል። ይሁንና፣ ከዚሁ አካባቢ ጋ የተጎራበቱት ግዛቶች ሕዝብ ሞዛምቢክ እንደገና እርስ በርሱ ጦርነት ውስጥ ልትወድቅ ትችል ይሆናል በሚል መስጋቱ አልቀረም። »


እአአ ጥቅምት ሦስት፣ 2013 ዓም 500 የሚቆጠሩ ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ አቅራቢያ ሰጠመችበት አደጋ 390 ሞቱ። ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ስትጓዝ በሰጠመችው ጀልባ ከተሳፈሩት ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ ኤርትራውያን እና ሶማልያውያን ነበሩ። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አደጋ በደረሰበት ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ እጅግ ማዘናቸውን አስታውቀዋል።
« በዚህ ዛሬ በላምፔዱዛ እንደገና በደረሰው አሳዛኝ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን ሰለባዎች ማሰብ እፈልጋለሁ። አደጋው መድረሱ አሳፋሪ ነው። »
አደጋው የአውሮጳ ሀገራት በሚከተሉት የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲ ሰፊ ክርክር አስነስቶዋል። ፖለቲካኞች ለጀልባዋ መስመጥ ሕገ ወጦቹን ሰው አሸጋጋሪዎች ተጠያቂ አድርገዋል። በኢጣልያ የሚገኙት ኤርትራዊው ካቶሊካዊው ቄስ አባ ሙሴ ግን በፖለቲከኞቹ አስተሳሰብ አይስማሙም። እንደ እርሳቸው አስተያየት፣ ስደተኞቹ ሕይወታቸውን ለአደጋ ለሚያጋልጡበት ሁኔታ ሕገ ወጦቹ ሰው አሸጋጋሪዎች መንሥዔ አይደሉም። መንሥዔው በየሀገሮቻቸው ያለው ጨቋኝ ሥርዓት እና ምስቅልቅል ሁኔታ ነው ባይ ናቸው። « አውሮጳውያት ሀገራት በሕገ ወጦቹ ሰው አሸጋጋሪዎች አንፃር በርግጥ መታገል ከፈለጉ ብቸኛው አማራጭ ተገን ፈላጊዎቹ ወደ አውሮጳውያቱ ሀገራት በሕጋዊ መንገድ መግባት እንዲችሉ ድንበሮቻቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው። »
በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ በመንግሥቱ ጦር አንፃር የተዋጋው ራሱን «ኤም 23» ብሎ የሚጠራው ያማፅያን ቡድን አባላት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ከፊል ሕዝቡን ሲያሸብሩ ቆይተዋል። በኮንጎ ጦርና በ «ኤም 23» መካከል ውጊያው ተባብሶ ከቀጠለ እና በተለይ ያማፅያኑ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ቢያደርግም፣ በኮንጎ ሰላም አስከባሪዎች ያሠማራው የተመድ በውዝግቡ ጣልቃ መግባት አልቻለም ነበር፤ ምክንያቱም ተልዕኮው ስለማይፈቅድለት። በዚህም የተነሳ፣ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የሕዝቡን ስቃይ ለማብቃት ይቻል ዘንድ አንድ 3000 ወታደሮች የሰለፈ አጥቂ ቡድን ለመላክ ወሰነ። ጀርመናዊው ማርቲን ኮብለር የመሩት ይኸው ቡድን ወዲያው ከኮንጎ መደበኛ ሠራዊት ጎን በመሆን የጥታ ስጋቱን በማስወገዱ ተግባር ላይ ተሠማራ።
« ወደ ኮንጎ የመጣነው ለሕዝቡ ከለላ ለመስጠት ነው፤ ማለትም፣ በተለይ ለጎማ ሲቭል ሕዝብ ከለላ መስጠት ነው ዋናው ተልዕኳችን። በሲቭሉ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት እንዳይደገም ለማድረግ ስንልም ከኮንጎ ጦር ጎን በመሰለፍ በሚቻለን ሁሉ ባማፂው ቡድን አንፃር ወታደራዊው ዘመቻ አካሂደናል። »
በዚሁ የተመድ እና የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፑብሊክ ጦር የጋራ ዘመቻ «ኤም 23» ተሸንፎ እአአ ባለፈው ህዳር አምስት ናይሮቢ ኬንያ ላይ መንግስቱ ጋ የሰላም ስምምነት ተፈርሞዋል። ሁለቱ ወገኖች በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት አማፂዉ ቡድን ተዋጊዎቹን ትጥቅ በማስፈታት ራሱን ወደፖለቲካ ፓርቲነት መለወጥ እና የሰላም ስምምነቱ የ«ኤም 23» አባላት በጦነቱ ለፈጸሙት ጥፋት ምህረትን የሚያገኙበትንም መንገድ መመልከት ይኖርበታል


የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ሕገ ወጥ ያላቸውን የውጭ ዜጎች ከሀገሩ ለማስወጣት ከጀመረች ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ 140,000 የሚጠጉ ዜጎቹን ወደ ሀገር መመልሶዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸዉ ረዳ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸዉ ሳዉዲ ሚገኙት ዜጎች ወደሀገር መመለሱ ተግባር ቅድሚያ ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው የውጭ ዜጎች የሰጠው የሰባት ወር የምሕረት ቀነ ገደብ ባለፈው ህዳር ወር ካበቃ በኋላ ከፖሊስ ጋ በተፈጠረ ግጭት ሦስት ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የፈላስያን ጉዳዮች ተመልካች ድርጅት «አይ ኦ ኤም» በቅርቡ ከሪያድ፣ ከጄዳ እና ከመዲና ተጨማሪ 35,000 ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ብለው ይጠብቃሉ።
የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቀውስ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ባለፈው መጋቢት ፣ 2013 ዓም የሴሌካ ዓማፅያን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የቀድሞ የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ በሀገሪቱ በሚሼል ጆቶጂያ የሚመራ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞዋል። የታጠቁ፣ በብዛት ሙሥሊሞች የሆኑ የቀድሞዎቹ ያማፅያን ቡድኖች ብዙውን የሀገሪቱን ከፊል ተቆጣጥረዋል። እርግጥ፣ ከሽግግሩ መንግሥት ምሥረታ በኋላ የሀገሪቱ መሪ ሚሼል ጆቶጂያ ያማፀያኑን ቡድንኖች በመበተን በብሔራዊው ጦር ውስጥ ቢያዋህዱም፣ ትጥቅ ያልፈቱት በብዛት ሙሥሊሞቹ የቀድሞ ሴሌካ ዓማፅያን በርካታ መንደሮችን እያጠቁ በብዛት ክርስትያኑን ሲቭ ሕዝብ በማሸበር ላይ እንደሚገኙ ተገልጾዋል። ራሳቸውን ከሴሌካ ጥቃት ለመከላከል በተደራጁ የክርስትያን ሚሊሺያዎች እና ዓማፅያኑ መካከል በቀጠለው ግጭት ብዙዎች መገደላቸውን እና መፈናቀላቸው ተሰምቶዋል። ውዝግቡ ወደ ሀይማኖት እና ጎሳ ግጭት ሊቀየር እና በርዋንዳ የታኢ,ውን ዓይነት የጎሣ ጭፍጨፍ እንዳይከሰት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስጠንቅቀዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ባልደረባ የቡድኑን ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን አስጠንቅቋል።

« ሂውማን ራይትስ ዎች የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን በርካታ አስከፊ ወንጀሎችን መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ሰብስቦዋል። በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ በመዲናዋ ባነግዊን ጭምር የሚገኙት እነዚሁ ዓማፅያን ባሁኑ ጊዜ ከቁጥጥር ውጭ ሆነዋል። በመጨረሻ የመዘገብነው አሰከፊ ወንጀል በጋጋ አካባቢ፣ ኦምቤላምቦኮ በተባለ መንደር ሲሆን በዚያ የሴሌካ ዓማፅያን በመንደሩ ላይ ጥቃትበመሰነዘር በነዋሪዎቹ ላይ እጅግ አስከፊ ወንጀል ፈፅመዋል። »
ይህን ተከትሎ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትየቀድሞ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ፍሪቃዊቱ ሀገር ያለውንከ3500 ወደ 6000 ከፍ ይላል የሚባለውን የአፍሪቃ ህብረት ጓድ እንዲጠናክር ያቀረበችው ማመልከቻን አፅድቋል። በዚህም መሠረት በዚያ 600 ወታደሮች ያሉዋተ ፈረንሳይ ተጨማሪ 1000 ልካለች። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የፈረንሳይና የአፍሪቃ ኅብረት ኃይሎች ቢገኙም የሰላማዊ ሰዎች ግድያ አልቆመም።

የቀድሞውን የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት እና እውቁ የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እአአ ታህሳስ አምሥት 2013 ዓም በ95 ዓመታቸው ማረፋቸውን የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ በይፋ አስታወቁ። የነፃነት እና የመቻቻል ተምሳሌት ሆኑትን ለኔልሰን ማንዴላ ሶዌቶ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኝ ስታድዮም በተደረገው ይፋ ስንብት ላይ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የዓለም መሪዎች፤ ቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጆቻቸው እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ከመላው ደቡብ አፍሪቃ የመጣ ህዝብ ተገኝቶ ነበር፣ ከዚያም የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ለሦስት ቀናት በፕሪቶርያ ከተወዳጁ መሪው ስንብት ካደረገ በኋላ ሥርዓተ ቀብራቸው በትውልድ መንደራቸው ኩኑ 4,500 ሰዎች፣ በርካታ መሪዎች ጭምር በተገኙበት ተፈፅሞዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ነፃነቷን ባገኘች ደቡብ ሱዳን ውስጥ በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር ታማኝ ወታደሮች መካከል ካለፈው እሁድ ወዲህ ውጊያው ቀጥሎዋል። በመዲናይቱ ጁባ ብቻ ከ500 የሚበልጥ ሰው መገደሉ እና በርካቶች መቁሰላቸው ተሰምቶዋል። ከ16000 የሚበልጡም መፈናቀላቸው ተገልጾዋል።
ስለመዲናይቱ ጁባ ወቅታዊ ሁኔታ አስተያየት የሰጡት በዚያ ያሉት የተመድ ሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ ቶቢ ላንዛ ሲቭሉ ሕዝብ ለደህንነቱ መስጋቱን ገልጸዋል።
« በአሁኑ ጊዜ ጁባ ውስጥ ሁኔታው ጥቂት ተረጋግቶዋል። 16,000 ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ግን የተመድ ሰላም አስጠባቂዎችን ከለላ ለማግኘት ሲሉ በከተማይቱ ባሉት ሁለት ሠፈሮቻችን ውስጥ ወይም በዚያው አቅራቢያ ይገኛሉ። እንደሚመስለኝ ውኃን የመሳሰሉ መሠረታዊ ርዳታዎች ጭምር ያስፈልጋቸዋል። »
ሳልቫ ኪር ማቻርን ከከሸፈ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ሁከት እንዲባባስ አድርገዋል ሲሉ ይወቅሳል። አሁን ከመዲናይቱ ጁባ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋው ውጊያ ደቡብ ሱዳንን በጎሣ ከፋፍሏታል።
አርያም ተክሌ
ልደት አበበ
Source: www.dw.de

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog