የአፍሪቃ መሪዎች እና ICC

በዘር ማጥፋት፥በሰብአዊ ፍጡር ላይ በተፈፀመ ወንጀል እና በጦር ወንጀል የሚጠረጠሩ ፖለቲከኞችን እንዲመረርምር፥ በተረጋገጠባቸዉ ላይ እንዲፈርድ የተቋቋመዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ግን እስካሁን ክስ የመሠረተዉ በስምት የወንጀል ጭብጦች ነዉ።በስምንቱም ጉዳዮች የከሰሳቸዉ፥ ወይም የፈረደባቸዉ ፖለቲከኞች በሙሉ ግን አፍሪቃዉያን ናቸዉ።
በ1919 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያን አቆጣጠር ነዉ) የጦር ወንጀለኞችን የሚቀጣ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ሐሳቡ ሲነሳ፣ ሲወድቅ፣ በ1948 ዳግም ሲነሳ፣ ደንቡ ሲረቀቅ፣ ረቂቁ ሲወድቅም አብዛኞቹ አፍሪቃዉያን ከአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች ነፃ ለመዉጣት ገና እየገደሉ ይሞቱ ነበር።1975 በደራዉ ክርክር ዉስጥም አፍሪቃዉያን አልነበሩበትም።በ1998 የመመሥረቻ ዉሉን ለመፈረም፣ በ2002 ለማፅደቅ ግን አፍሪቃ ይንጋጋ ገባ።ለፍርድ ቤቱ በርካታ አባላትን በማሰለፍ አፍሪቃ አንደኛ ናት።ፍርድ ቤቱ ከአፍሪቃዊ ዉጪ በአንድም የሌላ አሐጉር ወንጀለኛ ላይ
አልበየነም።አንድም የሌላ አሐጉር ተጠርጣሪ አልተከሰሰም። ከአፍሪቃዉያን ሌላ አንድም ሐገር ፍርድ ቤቱን አልተቃወመም። ድንቅ መስተጋብር።እንበል ይሆን?

የአፍሪቃ መሪዎች የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (ICC) አባል ለመሆን ሲሽቀዳደሙ ከዚያ በፊትና በሕዋላም-ዩጋንዳ አንድ መሪ ነበሯት።አሏትምም።ፕሬዝዳት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ።ፍርድ ቤቱ የሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አልበሽር በተገኙበት እንዲያዙ የእስራት ዋራንት ሲቆርጥባቸዉም ሙሴቬኒ በነበሩ-ባሉበትም ሥልጣን ላይ ነበሩ።ምናልባት የረጅም ጊዜ ተቀናቃኛቸዉ በመዋረድ፥ መከሰሳቸዉ ተደስተዉ ይሆን-ይሆናል።በይፋ ያሉት ግን አልነበረም።

የሙሴቪንን መንግሥት በሐይል አስወግዶ ዩጋንዳን በመፅፍ ቅዱሱ አስርቱ ትዕዛዛት መሠረት ለመግዛት የሚፋለመዉ የሐሪቱ አማፂ ቡድን መሪዎች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲዳኙ የጠየቁትም ራሳቸዉ ሙሴቬኒ ነበሩ።የኬንያ ፖለቲከኞች በምርጫ ዉጤት ሰበብ ጎሳን ከጎሳ አጋጭተዋል፥ ሰዉ አስገድለዋል በሚል ጥርጣሬ ሲከሰሱም የዩጋንዳ መሪ በይፋ ያሉት አልነበረም።


ተከሳሾቹ የኬንያን የፕሬዝዳትነትና የምክትል ፕሬዝዳትነት ሥልጣን ከያዙ በኋላ ግን አንጋፋዉ ፕሬዝዳንት የደገፉትን፥ ሐገራቸዉን አባል ያደረጉበትን፥ ተቃዋሚዎቻቸዉ እንዲከሰሱ የጠየቁትን፥ ፍርድ ቤት ይተቹ፥ በዘረኝነት ይወቅሱ ገቡ።

«(የኬንያዉ ግጭት) ሕጋዊ ጉዳይ አይደለም።ርዕዮተ-ዓለማዊ ነዉ።መያዝ ያለበትም በዚሕ መሠረት ነዉ።እነዚሕ የICC ሰዎች ግልብ ናቸዉ።»ሌላ ጊዜም ቀጠሉ።ጠንከር፥ ከረርም አሉ።«እኒያ ሥለ ጎሳ እና ሐራጥቃ የሚያወሩ የአፍሪቃ ጠላቶች ናቸዉ።በግል ደግሞ የኔ፥ የእናንተም ጠላቶች ናቸዉ።»

የተከበሩት የዩጋንዳ መሪ አይነቱ አቋም በጎቲንገን-ጀርመን ዩኒቨርስቲ የወንጀለኝ ጉዳይ የሕግ-ባለሙያ ካይ አምቦስ እርስ በርሱ የሚቃረን ይሉታል።«ICC የዩጋንዳ አማፂያንን እንዲከስ ጉዳዩን ለፍርድ ቤቱ የመሩት የዩጋንዳዉ ፕሬዝዳት ራሳቸዉ ናቸዉ።እና አሁን የሚሰነዘረዉ ትችት በጣም (ከድርጊቱ) የሚቃረን ነዉ።አሁን የአፍሪቃ ሕብረት ዉስጥ የሚደረገዉ ICC የመቃወም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነዉ።በተለይ በግልፅ የሚታየዉ ጉዳዩ ከነካቸዉ (ከተከሠሱት) መንግሥታት።»


በሴራሊዮኑ የርስ በርስ ጦርነት የተደረሰዉን ግፍ የሚመረምረዉ የሴራሊዮን ጉዳይ ፍርድ ቤት የቀድሞዉን የላይቤሪያ ፕሬዝዳት ቻርልስ ቴለርን የከሰሰ፥ ያሰረዉም፥ የቀድሞዉ የየኮትዲቯር ፕሬዝዳት ሎራ ባግቦም ከሥልጣን የተወገዱ፥ የተከሰሱ የታሰሩትም በአፍሪቃዉያን መሪዎች ትብብር ነበር።በዚሕም ሰበብ ያኔ ፍርድ ቤቱን የወቀሰ፥ የተቸም አልነበረም።

የሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አልበሽር ዳርፉር ዉስጥ ተፈፅሟል በተባለዉ ወንጀል ጥርጣሬ ሲከሰሱ፥ በተገኙበት እንዲያዙ ፍርድ ቤቱ ሲያዝ ግን አንዳድ የአፍሪቃ መሪዎች ማንገራገር ጀመሩ።አፍሪቃ ዉስጥ በሥልጣን ላይ ያለዉን መንግሥት በጠመንጃ ዉጊያ አለያም በፖለቲካዊ አመፅ፥ ወይም በምርጫ ለማስወገድ የተደራጀ ሐይል የሌለበት ሐገር ጥቂት ነዉ።

አል-በሽር የዳርፉር አማፂዎችን ለመቅጣት በወሰዱት እርምጃ ከተከሰሱ ጠላት ወይም ተቃዋሚዎቹን ለማጥፋት የሚታገለዉ አፍሪቃዊ መሪ ነግ በኔ ማለቱ አይቀርም።የነቻርልስ ቴለርን ጉዳይ ችላ ያሉት ብዙዎቹ የአፍሪቃ መሪዎች ክሱ አልበሽር ላይ ሲደርስ የማንገራገራቸዉ ትክክለኛ ምክንያት ነግ በኔ የማለት ሥጋት ሊሆን ይችላል።በይፋ የተሰጠዉ ሰበብ ግን ISS በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ዶክተር ሰለሞን ደርሶ እንደሚሉት የዳርፉርን የሠላም ሒደት ያደናቅፈዋል የሚል ነበር።

የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች ብሪታንያ፥ ፈረንሳይና ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች ሠላሳ ሁለት ወዳጆቻቸዉን አስከትለዉ ዓለም የጦር ወንጀለኞች የሚዳኙበት የጋራ ፍርድ ቤት እንዲኖራት በ1919 ሲመክሩ አብዛኞቹ አፍሪቃዉን በአዉሮጳዉያን ቅኝ ገዢዎች ይረገጡ ነበር።ፍርድ ቤት ይቋቋም የሚለዉን ሐሳብ ቀድመዉ ያነሱት የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ነበሩ።የፍርድ ቤቱ ማቋቋሚያ ጥናት ሲቀርብ ግን አሜሪካኖች ተቃዋሚ ሆኑ።ሐሳቡም፥ በሐሳብ ቀረ።

ሐሳቡ በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ዳግም ተነስቶ የፍርድ ቤቱ ማቋቋሚያ ደንብ እስከ መረቀቅ ደርሶ ነበር።ረቂቁ በሁለተኛ ዓመቱ ሲጠናቀቅ ግን ዓለም በቀዝቃዛዉ ጦርነት በምትናጥበት በዚሕ ወቅት የጋራ ፍርድ ቤት ማቋቋም አይቻልም ተብሎ ቀረ።
 
በ1975 እንደገና ሐሳቡ ተነሳ፥ እንደገና ተዳፈነ።የኮሚንስቱ ጎራ ከተፈረካከሰ በሕዋላ ግን ፍርድ ቤቱን የማቋቋሚያዉ ዉል በ1998 ተፈረመ።በሁለት ሺሕ ሁለት ፍርድ ቤቱ ተቋቋመ።የፍርድ ቤቱን መቋቋም የተቃወሙት ሰባት ሐገራት ብቻ ነበሩ።ቻይና፥ ኢራቅ፥ እስራኤል፥ ሊቢያ፥ ቀጠር፥ ዩናይትድ ስቴትስ እና የመን።ሐሳቡን ስታነሳ-ስትጥል፥ ሥታስረቀቅ-ስታግድ የነበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ የፍርድ ቤቱን መቋቋም ስትቃወም አብዛኞቹ አፍሪቃዉያን ግን መስራቾች ሆኑ።

የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሑዩማን ራይትስ ወች ባልደረባ ኤልዛቤት ኤቬንሰን እንደሚሉት አፍሪቃዉያን ከፍርድ ቤቱ አባል ሐገራት መካከል ከፍተኛዉን ቁጥር የያዙ ናቸዉ።

«የአፍሪቃ ሐገራት ከመሥራቾቹ ሐገራት መሐል ናቸዉ።እነሱ (ICC) ለመቋቋሙ መንገድ ጠርገዋል።ከፍተኛ ቡድንም ናቸዉ።»

እርግጥ ነዉ፥ የዩጎዝላቪያ፥ የሩዋንዳ፥ የሴራሊዮን ወዘተ እየተባሉ የተቋቋሙት ፍርድ ቤቶች በየሐገራቱ የተፈፀሙ ወንጀሎችን መርምረዉ ብይን ሰጥተዋል።ይሰጣሉም።በዘር ማጥፋት፥በሰብአዊ ፍጡር ላይ በተፈፀመ ወንጀል እና በጦር ወንጀል የሚጠረጠሩ ፖለቲከኞችን እንዲመረርምር፥ በተረጋገጠባቸዉ ላይ እንዲፈርድ የተቋቋመዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ግን እስካሁን ክስ የመሠረተዉ በስምት የወንጀል ጭብጦች ነዉ።

የከሰሳቸዉ፥ ወይም የፈረደባቸዉ ፖለቲከኞች በሙሉ ግን አፍሪቃዉያን ናቸዉ።ክስና ብይኑ በተለይ የኬንያ ፕሬዝዳት ኡሁሩ ኬንያታንና ምክትላቸዉን ዊሊያም ሩቶን መንካቱ ያስቆጣቸዉ የአፍሪቃ መሪዎች ፍርድ ቤቱን በዘረኝነት ለመወቅስ ሰበብ-ምክንያታቸዉም ይኸዉ ነዉ።የአፍሪቃ ሕብረትን ተዘዋዋሪ የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዘችዉ የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቴዎድሮስ አድሐኖም ፍርድ ቤቱን የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል እስከማለት ደርሰዋልም።


የኬንያ ምክር ቤት ሐገሪቱ ከፍርድ ቤቱ አባልነቷ እንድትወጣ በቅርቡ ወስኗል።ሌሎቹ የፍርድ ቤቱ አባላት የሆኑት ሠላሳ ሰወስቱ የአፍሪቃ ሐገራትም የኬንያን ፈለግ ይከተላሉ የሚል ሥጋት ነበር። አፍሪቃ ከፍርድ ቤቱ ጋር ሥለሚኖራት ግንኘት ለመነጋገር ባለፈዉ ቅዳሜ ተሰይሞ የነበረዉ የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ግን አባል ሐገራት ከፍርድ ቤቱ አባልነት እንዲወጡ አልወሰነም።
ይሁንና ጉባኤዉ በስልጣን ላይ ያሉ አፍሪቃዉያን መሪዎች እንዳይከሰሱ ጠይቋል።ጥያቄዉን ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ባንድ ወይም በሌላ መልኩ በበላይነት ለሚመራዉ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የሚያቀርቡ መልዕክተኞችም ወደ ኒዮርክ እንዲሔዱ ጉባኤዉ ወስነዋል።ዶክተር ሰለሞን ደርሶ እንደሚሉት የአፍሪቃ መሪዎች የቅዳሜ ዉሳኔ በጎም-መጥፎም ነዉ።

«ከፍርድ ቤቱ አባልነት በጅምላ መዉጣት የለም።ይሕ ቀና ነገር ነዉ።ይሁንና ከቀረበዉ ጥያቄ አኳያ ማለት በሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎች እንዳይከሰሱ መጠየቁ ሲታይ፥ የአፍሪቃ ሕብረት ወይም አባላቱ ከICC ጋር የፈጠሩትን የልዩነት ክፍተት ለመድፈን በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል።»

የሕግ ባለሙያ ሐርሜን ፋን ዴር ቪልት እንደሚሉት ደግሞ በወንጀል የሚጠረጠርን ሰዉ ሥልጣን እሰከሚለቅ መከሰስ የለበትም ማለት ተገቢ አይደለም።ሥልጣን የወንጀለኞች ወይም የተጠርታሪዎች መሸሸጊያ መሆን የለበትምና።

«ሥልጣን ላይ እስካለሕ ድረስ ሥልጣንሕ በወንጀል ከመከሰስ መከታ ሊሆን አይገባም።እንደሚመስለኝ የአፍሪቃ ሕብረት ዓላማ ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ከተገቢዉ ተልዕኮዉ ማሳት ነዉ።»

አሳተም-አላሳተ የአፍሪቃ መሪዎች ጉዳዩን ሥራዬ ብለዉ መያዛቸዉ እርግጥ ነዉ።መሪዎቹ ለቅዳሜዉ ጉባኤና ዉሳኔ የደረሱትም ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በተለይ በኬንያ መሪዎች ላይ የመሠረተዉን ክስና የሚያደርገዉን ምርመራ ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነዉ።
አሁን ማስጠንቀቂያ አዘል ጥያቄያቸዉን የሚያቀርቡት ለፍርድ ቤቱ አይደለም።ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ነዉ።በምክር ቤቱ ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ካላቸዉ ከአምስቱ ሐያላን በጣም ሐይለኞቹ፥ ቻይና፥ ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ የፍርድ ቤቱ አባላት አይደሉም።
ይሁንና የአፍሪቃዉያኑ ጥያቄ ለድምፅ ከቀረበ ሐርሜን ፋን ዴር ቪልት እንደሚሉት ጥያቄዉን ዉድቅ ለማድረግ ፍርድ ቤቱን ከሚደግፉት ከፈረንሳይና ከብሪታንያ ያንዳቸዉ ተቃዉሞ በቂ ነዉ።
«ብሪታንያና ፈረንሳይ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ደጋፊዎች ናቸዉ።ዉሳኔዉን ሊሽሩት ይችላሉ።»

የአፍሪቃ መሪዎች አምባገነን ሊሆኑ ይችላሉ።ያሁን ጥያቄያቸዉ ከቀድሞ አቋማቸዉ መቃራኑም አያነጋግርም።ጥያቄቸዉን ለመስማት ወይም ላለስማት፥ ለመቀበልም-ሆነ ላለመቀበል በፍትሑም፥ በዓለም ማሕበሩም መድረክ ዛሬም ወሳኞቹ አፍሪቃን ለዘመናት በቅኝ ገዢነት ሲረግጡ የነበሩት የለንደን እና የፓርስ መንግሥታት መሆናቸዉ በርግጥ ያስተዛዝባል።ግን ለዛሬ ይብቃን።ከዛሬ ጀምሮ ሥለ ዝግጅታችን ያላችሁን አስተያት፥ እንጠብቃለን።ማሕደረ ዜና ቢያስተናገደዉ ጥሩ ነዉ ብላችሁ የምታስቡትን ጉዳይም ጠቁሙን።የሥልክ፥ የደብዳቤና የኤስ ኤም ኤስ አድራሽችን የተለመደዉ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
 Source: http://www.dw.de

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog