አገሬ ታማለች!

አገሬ ታማለች!


(በካሣሁን ዓለሙ)
እማማ ታማለች፣
አገሬ ታማለች፣
ሆስፒታል ተኝታ
እ!እ!…ህእ!ም!…ህም!!! ትለኛለች፤
ከህቅታዋም ውስጥ ጣሯ ይሰማኛል፣
ህመሟን ስቃዩዋን፣
ዝም ብዬ እየሰማሁ፣
እማዬ! እላታለሁ፤
ህመሟ ያመኛል፣
ጧሯ ይነዝረኛል፣
አዎ! እማማ ታማለች፣
ይኸው በሆስፒታል
እ!!…ህ!!!.. እህ!!!… ትለኛለች፤

በዚህ በሽታዋም፡
የሩቁ ሰው ዐይቶ ምራቁን ይመጣል፣
የተጠጋውም ሰው መርዶውን ይነግራል፤
‹እሷማ አትተርፍም› ብሎ ያሟርታል፤
በደንብ የሚያውቃትም እንባውን ይዘራል፣
በ‹እንዲህ ሆነች በቃ!› ተስፋዬን ይገድላል፤
እማማ! ታማለች፣
ሆስፒታል አልጋ ላይ
‹እ!ህ!… እ!..ም!!!› ትለኛለች፤
ሐኪሙም ብቅ ብሎ ጉዴን ይነግረኛል፣
‹ከእንግዲህ እወቀው በሽታዋ! ከፍቷል፣
የተበከለው ደም በውስጥ ተሠራጭቷል፤
የመቋቋም አቅሟም ከእንግዲህ አብቅቷል፤
ዝውውሩም ሊቆም የቀረው ትንሽ ነው፣
የተበከለው ደም በሙሉ ሲሠራጭ አበቃ ማለት ነው፤›
ብሎ ጉዴን ይነግረኛል፤
አዎ! በጠና ታማለች፣
ሆስፒታል ተኝታ
‹እ!ህ!!… እ!..እ!!!› ትለኛለች፤
ሐኪሙም በሐዘን ሁኔታየን ዐይቶ፣
ልቦናዬን በልቶ
‹ምናልባት ከቻልከው፣
ደሟን አስጠርገህ በጤነኛ አስተካው፣
ወይ ካንሠሩን ክፍል ቆርጠን እንጣለው፣
ይህነን የማድረግ ምርጫው የራስህ ነው፤›
ብሎ ይመክረኛል፤
ግና እንዴት ተደርጎ፣
‹እናቴን ላደርጋት አካለ ‹ጎደሎ›?
ይሁን እንኳ ቢባል የገንዘብ ክፍያው ከየት ተፈልጎ?
ደግሞስ የትኛው ነው ከእሷ የሚቆረጥ፣
አንጀቷ ነው፣ ልቧ ወይስ እግር እጇ
በሐኪም የሚፈለጥ?
ይህንን ተደርጎስ የመዳን እድሏ፣
ብትድንስ እንኳ ጤናው መመለሱ
የቀረው አከሏ፤›
ዋስትናው ምንድን ነው?
በእናቴ አካላት ላይ የምደራደረው?›
እያለ ውስጤ ይወቅሰኛል፤
ያም አለ ያም አለ!
እናቴ ታማለች፣
ሆስፒታል ውስጥ ነች፣
በሚያንቋርር ድምፅዋ ‹እ!ህ!…እ!!!…› ትለኛለች፡፡
እኔም ዝም ብዬ ዐይን ዐይኗን ዐያለሁ፤
በታሪክ ሰምጬ የእናቴን ማንነት፣
የባህል ዕንቁነት፣ የጠባይ ኩሩነት፣
አብሰለስላለሁ፣
የ‹ህእ!!..›ታ ድምፅዋን በውስጤ እያዳመጥኩ፣
የልቧን ት..ር..ታ በእጄ እየደባበስኩ፤
እጠባበቃለሁ፤
ዐይኔ እንዲህ እያየ እናቴ ልትሞት ነው?
ይህንን እያሰብኩ፣
ሳትሞት እየገደልኩ
መብሰልሰል መብሰልሰል ሥራዬ መራድ ነው፤
ግና እንደዚያም ሆና!
ዐይኗ ትክ አድርጎ ዐይን ዐይኔን ያየኛል፣
ስሜቷ እየጮኸ ፍቅሯን ይነግረኛል፤
የፍቅሯ ቃጠሎ ውስጤን ይነዝረዋል፤
እንዴት እየሞተ ሰው ፍቅር ያወራል?
እንዳው ዝም ብዬ በሙጣጭ ተስፋ ውስጥ
እኔም ዐያታለሁ፣
እንዳው ዝም ብዬ
በልብ ትርታዋ ሕይወት እለካለሁ፤
አዎ! እማዬ ታማለች፣
‹እ!..ህ!!…› ብቻ ትላለች፤
በህቅታዋም ውስጥ
የእናትነት ፍቅሯን እያመላለሰ፣
ውስጤ እያስታወሰ፣
ልዩ እናት መሆኗን እየመሰከረ፣
ከአንጀት እስከ ጀርባ እየደረደረ
‹እሷ እኮ! ናት! አንተ! አልጋ ላይ የዋለች!
እሷ! እኮ! ናት! አንተ! እየጣረች ያለች!›
በማለት ውስጤን ያቆስለዋል፣
ከህመሟ ብሶም ይለበልበኛል፤
ብጨነቅ ብጠበብ አልቻልኩም ላድናት፣
ሆስፒታል ውስጥ ናት፤
ብቻ ‹እ!.ህ!!..እ!..ም!!..እ!..ህ!…› ትለኛለች፣
በእውነት! በእውነት! አገሬ-እማማ! ታማለች፡፡
ኧረ! ሐኪም!ኧረ ሐኪም!
ኧረ! ሐኪም! ኧረ! ሐኪም!…
አካሏን ጠባቂ እግዜር የሚፈራ፣
ብክለት የሚያጠራ፣
እናቴን የሚያድን! እናቴን የሚያክም!!!
ኧረ! ሐኪም! ኧረ! ሐኪም!…
(ግንቦት 1፣ 2006 ዓ.ም.)

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog