ግብፅ የህዳሴውን ግድብ በመቃወም ለተመድ አቤት እላለሁ ማለቷን ኢትዮጵያ አጣጣለች

የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በመቃወም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አቤቱታ አቀርባለሁ ማለቱን የኢትዮጵያ መንግሥት አጣጣለው፡፡
ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ግንባታ ማንኛውንም ዓይነት ሕግ የጣሰ አይደለም በማለት መንግሥት የግብፅን አቤቱታ ውድቅ አድርጓል፡፡ 

አል ሞኒተር የተባለ የግብፅ ሚዲያ የተለያዩ የአገሪቱ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ፣ ግብፅ በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ተቃውሞ ዓለም አቀፍ ማድረግ እንደምትፈልግ ዘግቧል፡፡ 
‹‹የህዳሴው ግድብ አሁን ባለው የግንባታ ደረጃ ተገንብቶ ዕውን የሚሆን ከሆነ በግብፅ ላይ
የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን ወደሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መውሰድ እንደሚገባ፣ ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፤›› ያሉት የአገሪቱ የመስኖና ውኃ ሀብት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ካህሊድ ዋሲፍ ናቸው፡፡
‹‹ግብፅ የህዳሴው ግድብ ግንባታን ፈፅሞ አትፈቅድም፡፡ ይህንን ለማሳካትም ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የውጭ ዕርዳታ ለግድቡ እንዳታገኝ ግፊት እናደርጋለን፤›› ሲሉ በይፋ ተናግረዋል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የኢትዮጵያን ግድብ በማውገዝ ከግብፅ ጐን እንዲቆም አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከበረና የተረጋገጠ መብት አላት፡፡ ነገር ግን ይህ የግብፅ መብት በኢትዮጵያ እየተጣሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ሕጋዊ መብት አላት የሚሉት ቃል አቀባዩ፣ ማናቸውም የተፋሰሱ አገሮች ተፋሰሱን በመጠቀም ወደ ልማት መግባት ሲፈልጉ በቅድሚያ ግብፅን የማማከርና ይሁንታ የማግኘት ግዴታ አለባቸው ሲሉ የአገራቸውን አቋም አስታውቀዋል፡፡ 
ኢትዮጵያ ይህንን ግዴታ በመጣስ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ መጀመሯ በራሱ ሕግን የጣሰ መሆኑን፣ ነገር ግን የግብፅ መንግሥት ጉዳዩን በወዳጅነት በመያዝ ሲወያይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ምንም ዓይነት ጉዳት በግብፅ ላይ እንደማያደርስ ኢትዮጵያ ለማረጋገጥ እንቢተኛ በመሆኗ ግብፅ ከውይይቱ ራሷን እንዳገለለች አስረድተዋል፡፡ 
የግብፅ የቀድሞ የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትር ሙሐሙድ ናስር አል ዲን አላም በበኩላቸው፣ ግብፅ ከዚህ በኋላ በህዳሴው ግድብ ላይ ሌላ አማራጭ የላትም ብለዋል፡፡ የቀረውና በፍጥነት ተግባራዊ መሆን የሚገባው አማራጭ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ፣ በዋናነትም ይፋዊ ቅሬታና ተቃውሞ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ማንኛውም የዓባይ ተፋሰስ ተጋሪ አጋር በወንዙ ላይ ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት የግብፅን ይሁንታ ማግኘት አለባት የሚለው ስምምነት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ነው፤›› በማለት የሚከራከሩት የቀድሞው ሚኒስትር ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት በመጣስ ለጀመረችው ግንባታ በተባበሩት መንግሥትት ድርጀት ልትጠየቅ ይገባታል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል አሁን ያለውን አለመግባባት በተመለከተም ዓለም አቀፍ እውነት አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ማጥናት ይኖርበታል በማለት ተከራክረዋል፡፡ 
የግብፅ ባለሥልጣናት እያንፀባረቁት ስላለው አዲስ አቋም የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ውል አይመለከታትም፣ ምክንያቱም አልፈረመችም፤›› ሲሉ የግብፅ ባለሥልጣናት መግለጫን አጣጥለዋል፡፡ የቅኝ ግዛት ውሉ የተፈረመው በግብፅና በእንግሊዝ መካከል መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፈቅ፣ እንግሊዝ ቅኝ የገዛቻቸውን ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ በመወከል ስምምነቱን ፈርማለች፡፡ ይህ ግን ኢትዮጵያን ፈፅሞ አይመለከትም ብለዋል፡፡ 
የግብፅ የቀድሞው የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትር በተደጋጋሚ ይህንን መሳይ ነገር ያነሳሉ በማለት ያስታወሱት አቶ ፈቅ፣ ‹‹ሰውዬው ከሳይንስ ውጭ ነው የሚናገሩት፣ ከእሳቸው የሚጠበቅ አይደለም፤›› ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡ 
‹‹ኢትዮጵያ የጀመረችው የህዳሴው ግድብ ግንባታ የትኛውንም ዓለም አቀፍ ሕግ የጣሰ አይደለም፡፡ ወደፈለጉበት ቢሄዱ የሚመጣ ነገር የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ጉዳዩን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መምራት ሊያተርፍ የሚችለው በሁለቱ አገሮች ያለውን የትብብር መንፈስ ማጥፋት ነው ሲሉ የግብፅ ባለሥልጣናትን የሰሞኑን ዘመቻ አውግዘዋል፡፡ 
Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog