ኢትዮጵያና የግብረ ሶዶማዊያን ዘመቻ!


 ባ
ለፈው ሳምንት በእለተ ቅዳሜ (8/10/2005) ማታ አራት ሰዓት ከሃያ አካባቢ በዛሚ 90.7 በኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም አቅራቢዎች የቀረበው እጅግ አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡ አስደንጋጩ ዜና በአንድ ስሙ ባልተጠቀሰ ትምህርት ቤት ውስጥ የ10 እና የ11 ዓመት ወንድ ሕጻናት መደፈራቸው ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎቹ ደግሞ የትምህርት ቤቱ ስድስት መምህራን ናቸው፡፡ ልጆቹ በጋንዲ እና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደተረጋገጠው በግብረ ሶዶማዊያን ተደፍረዋል፡፡ ተደፍረዋል የሚለው ቃል የነገሩን ክብደት ያቀለዋል፡፡ ከመግደል ሙከራ በላይ ተዶርጎባቸዋል ብል የተሻለ ይመስለኛል፡፡  በተለይ ነፍስ ያላወቁ ሕጻናት መሆናቸው ለሰሚው ከአስደማሚነት ባለፈ የሚያናድድና ፍጹም ነውረኛነት የተሞላበት ነው፡፡ የአንደኛው ሕጻን እናት የልጇን እና የእሷን ነፍስ ለማጥፋት ሙከራ አድርጋለች፡፡ ይህን ነውረኛ ተግባር ፈጸሙት የተባሉት ስድስቱ ተጠርጣሪ መምህራን
ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
መምህርነትን ከሳቴ ብርሃን ተሰማ - የአማርኛ መዝገበ ቃላት “አስተማሪነት፣ መሪነት፣ ካለ ማወቅ ወደ ማወቅ እውቀትን አደራሽነት፣ ገላጭነት” በማለት ይፈክረዋል፡፡ ፡፡ Perceival P. Wren የተባለው የሥነ ትምህርት ባለሙያ ደግሞ “መምህር የእውቀት ማማ (ምንጭ) ብቻ ሳይሆን መሪ፣ ፈላስፋ፣ ጓደኛ፣ ስብዕና ገንቢ፣ አሰልጣኝ እና አዕምሮ አበልጻጊ ነው” በማለት ይገልጸዋል፡፡ መምህር በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን የመምህር ሙያ እና ክብር እንደፊኛ እየሟሸሸ ነው፡፡ መምህርነት የተጠላ ሞያ እየሆነ ነው፡፡ የሆነም ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካላት (መንግስት፣ መምህራን እና  ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች) ተጠያቂ ናቸው፡፡ አሁን በየትምህርት ቤቱ ብትሄዱ መማር የሚፈልግ (ዓላማ ያለው) ተማሪ ማግኜት ይቸግራል፡፡ ሁሉም ቡረቃና ረብሻ ነው የሚወዱት፡፡ መምህራንም ማስተማር ተሰላችተዋል፡፡ ለስሙ አስተማሪ መባል ካልሆነ እና የወር ደሞወዝ ከመቆጠር ያለፈ ለሙያው ፍቅር ያለው መምህር አሁን ማግኜት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰፊና ጥልቅ የሆኑ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚያ ምክንያቶች ተጠንተው መፍትሔ ካልተፈለገላቸው የኢትዮጵያ ትምህርት አደጋ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ የአንድን አገር እጣ ፈንታ ወሳኞች መምህራን መሆናቸውን ሁላችንም ያወቅን አልመሰለኝም፡፡ 
ከላይ ወንድ ሕፃናትን የደፈሩ ተጠርጣሪ መምህራን፣ አንደኛ፣ መምህር ማለት ምን እንደሆነ አልገባቸውም፡፡ መምህር እኮ አባት ነው፡፡ አንዳንዴ ባይጋነን ከአባትም በላይ ነው፡፡ ስለዚህ እንዴት የቀለም ልጁን ይደፍራል? ያውም የ10 እና የ11 ዓመት ወንድ ሕጻናትን? ከልጅነት እስከ ጉርምስና ወቅት አካባቢውን ብሎም ይህችን ዓለም የሚያስተዋውቀው መምህር ነው፡፡ ተማሪዎች ብዙ ጊዜያቸውን የሚሳልፉት ከወላጅ ጋር ሳይሆን ከመምህር ጋር ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ልጅ ከወላጅ የበለጠ የሚቀርጸው መምህሩ ነው፡፡ መምህር ትውልድን ይገድላልም ያድናልም፡፡
ሁለተኛ እነዚህ መምህራን በዘመኑ የሶዶማዊያን እሳት የተገረፉ ይመስሉኛል፡፡ ግብረ ሰዶማዊነትን (Homosexual) ምንም እንኳ በኃይማኖት አስተምህሮ ውስጥ የታወቀ ቢሆንም ብዙዎቻችንን የፈረንጆች ምናምንቴ ወይም ጣጣ ይመስለን ነበር፡፡ አሁን ግን ዓለምን (አፍሪካን ጨምሮ) እየናጣት ያለ ችግር ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መነጋገሪያ ከሆነ አመታት ቢቆጠሩም አሁን አሁን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል፡፡ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ውጉዝ ነበረ፡፡ ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት ኔዘርላንድ የተመሳሳይ ፆታን ጋብቻ ከፈቀደች በኋላ በተለያዩ ሃገሮች የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ህጋዊ ሆኗል፡፡ ከእነዚህ ሃገሮች መካከል፡- ፈረንሳይ፣ ቤልጄም፣ አርጄንቲና፣ አይስላንድ፣ ዴንማርክ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ስፔን፣ ኖርዌይ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ፖርቹጋል እና ስዊድን ይጠቀሳሉ፡፡ በአሜሪካ እና ሜክሲኮ በዛ ባሉ ግዛቶችም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ከተፈቀደ ሰነባብቷል፡፡ ኡራጋይ እና ኒውዝላንድም በቅርቡ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ፊንላንድ፣ አንዶራ፣ ሉክሰምበርግ፣ አየርላንድ፣ ታይዋን፣ ኔፓል፣ ስኮትላንድ እና በተለያዩ የአሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ሜክሲኮ ግዛቶች የተመሳሳይ ፆታ (ግብረ ሶዶማዊያን) ጋብቻን ህጋዊ ለማድረግ  እየተውጠነጠኑ ነው፡፡ ምዕራባዊያንም ያላደጉ ሃራት የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን መፍቀድ እንዳለባቸው በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ይህን የማታከብር ሃገር የሚሰጣት እርዳታ እንደሚጤንባት (እንደሚቀሸብባት ብሎም እንደሚቆምባት) ባደባባይ ዲስኩራቸውን አሰምተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግብረ ሶዶማዊያን ገሃድ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ቢሰራ የበለጠ ማወቅ እንችላለን፡፡ ከዚህ በፊት የተሰራ ካለ ግን አላውቅም፡፡ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን መፍቀድ እና በጉዳዩ መሳተፍ፣ እንደ ስልጣኔ እና በአስተሳሳብ ’ርቆ እንደመሄድ የሚቆጥሩት ብዙ አሉ፡፡ ነገር ግን ግብረ ሰዶማዊነት፣ የሰው ልጅ ወደ ፊት የሚያደርገውን ሕይዎታዊ ጉዘት ሊያቆመው ይችላል ብለው ብዙዎች በመጮኽ ላይ ናቸው፡፡ በቅርቡ እንደምናስታውሰው ፈረንሳይ ውስጥ ግብረ ሶዶማዊነት (ተመሳሳይ የፆታ ጋብቻ) ህግ ሆኖ ሲጸድቅ ብዙ ሰዎች በመቃወም ወደ ጎዳና ወጡ፡፡ ነገር ግን በመፈክራቸው ትውልድ፣ ቤተሰብ (እናት፣ አባት፣ ልጅ፣ እህት፣ ወንድም፣ አክስት፣ አጎት …) ወዘተ ሊጠፋ ነው እያሉ ቢጮኹ፤ ሰሚ ግን አላገኙም፡፡
የግብረ ሶዶማዊያን አብዮት ከአውሮፓና አሜሪካ ወደ አፍሪካ ሰርጎ ከገባ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፍጥነቱ እንደ ሰደድ እሳት ሆኗል፡፡ በቅርብ ጊዜም የአፍሪካ ሃገራት የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን ህጋዊ ለማድረግና ላለማድረግ ፓርላማ ውስጥ እንደሚፋጩ አትጠራጠሩ፡፡ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራትም ይህ ዘመቻ (አብዮት) ተጀምሯል፡፡ ከተጀመረ ደግሞ ከጊዜ በኋላ ህጋዊ መሆኑ እንደማይቀር እሙን ነው፡፡ በተለይ አፍሪካ ዲሞከራሲን ማሽተት ስትጀምር ይህ ጉዳይም ከኋላ እንደ እንግዴ ልጅ የማይቀር ነው፡፡ እኛም አንድ ቀን እንደ ፈረንሳዊያን በመቃወም ሰልፍ እንደምንወጣ እኔ አልጠራጠርም፡፡ ጊዜው ይራቅ እንጂ ይህ የሚከሰት ሃቅ ይመስለኛል፡፡ ይህን ለማለት ነብይ መሆን የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያና በዓለም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአርምሞ መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡ ፍትህ ጋዜጣ ቅጽ 5 ቁጥር 164 ህዳር 23 2004 ዓ.ም ይዛ የወጣችውን ዜና ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ “የግብረ ሰዶማዊያን ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል” የሚል ነበር ዜናው፡፡ ስብሰባው አለም አቀፍ እንደ እንደሆነና በጁፒተር ሆቴል እንደሚደረግ በስፋት ተተንትኖ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዊኪሊክስ ከአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ በተገኜ መረጃ መሰረት፣ ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ በጣም እንደተስፋፋ ገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚኖሩ ግብረ ሰዶማዊያን ድህረ ገፅ ወይም ዌብሳይት ከፍተዋል፣ ለምሳሌ www.EthioLGBT.com ፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይም ዘመቻውን እያጧጧፉት ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱም ሕፃናት በዚህ አስነዋሪ ድርጊት እየተለከፉ ነው፡፡
ሰሞኑን ቤቲ የተባለች ኢትዮጵያዊት በቢግ ብራዘር አፍሪካ ላይ የፈጸመችውን ወሲባዊ ትዕይንት ጋዜጦች እና ራዲዮኖች እንዲህውም አብዛኛው ሰው በተቃውሞ ጮኸባት፡፡ አንዳንዶችም “ቤቲ አዋረደችን፣ አስደበችን” ብለው የጻፉም፣ የተናገሩም አሉ፡፡ ምን አዲስ ነገር አለና ነው እንዲህ የምትጮኹት? ዞር ብላችሁ በከተማችን የሚጸመውን ጉድ ለምን አታዩም? ሃገርስ አንዲት እንስት በፈጸመችው እንዴት ሊዋረድ ይችላል? ብለው የሞገቱም ነበሩ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ሃሳብ ሰጭዎች ላይ ብዙዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
     የሚገርመው ግን ሰው እና መገናኛ ብዙኃኑ የጮኸው ቤቲ ወዳ በፈጸመችው እንጂ በእነዚህ እምቦቀቅላ ሕጻናት ላይ በተፈጸመው አስነዋሪ ወንጀል አይደለም፡፡ ለምን? ለምን ዝምታን መረጥን? የሚገርመው መጮኽ ያለብንና የሌለብንን ጉዳይ የለየን አይመስለኝም፡፡ አዲስ አበባ እኮ የወሲብ እብድ ነች፡፡ ያውም እራቁቷን የምትደንስ፡፡ እብድነቷ ደግሞ በተፈጥሯዊ ወሲብ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከተፈጥሯዊ የፍቅር ስሪያ ባፈነገጡ (በጌዮች እና ሌዝቢያኖች) እየተሞላች ነው፡፡ አንድ ሆቴል ወስጥ የሚሰራ ጓደኛ አለኝ፡፡ ከሚሰራበት ሆቴል የሚገጥሙትና የሚያቸው ነገሮች ግን ይህ ትውልድ ወዴት እያመራ ይሆን ያስብላል፡፡ እጅግም ያስጨንቃል፡፡ እናም ታዛቢው ጓደኛዬ ዛሬ ሌዝቢያኖች መጥተው ነበር፣ ዛሬ ጌዮች መጥተው ነበር፣ ዛሬ አንድ ፈረንጅ አንዲት ሚጥጥዬ ተማሪ ጋር መጥቶ _____፣ ዛሬ አንዲት የምታምር የቤት ልጅ ደላላ ደውሎላት ከአንድ አረብ ጋር አብረው ወደ _____ ሄዱ፣ ይለኛል፡፡ አንድ ቀን “እንዴት ነው ግን ጌዮችን እና ሌዚቢያኖችን የምትለዩአቸው?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ ጓደኛዬ እየሳቀ “ጌዮች እኮ አጓጓዛቸው ብቻ ያሳብቅባቸዋል” አለኝ፡፡ እኔም በግርምት “አጓጓዛቸው ስትል” አልሁት፡፡ አሁንም እየሳቀ “በቃ ሲጓዙ ሸከክ ሸከክ ወይም ሸፈፍ ሸፈፍ ነው የሚሉት” አለኝ፡፡ እኔም እንደመሳቅ ብዬ ሌዝቢያኖችንስ አልሁት፡፡ “እነሱን ማወቅ የምትችለው በሚያደርጉት ድርጊት ነው፡፡ በተለይ ሌዝቢያኖችም ሆኑ ጌዮች ሲጠጡ ማንነታቸው ገሃድ ይወጣል” አለኝ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን አሁን ወደ ጭፈራ ቤቶች የሚሄዱት የወንድና የሴት ጥንድ ሳይሆን የተመሳሳይ ፆታ ጥንዶች እንደሆኑ በተለያዩ ሰዎችና መገናኛ ብዘኃን እየተገለጹም ነው፡፡
      ታዲያ ትውልድን ለማዳን ምን እናድርግ? ለሚለው ኢ-ተገቢነቱን በህግ ብቻ መከልከል ፋይዳ ያለው አይመስለኝም፡፡ አንድ ቀን ይህ ህግ ሊነሳ ይችላል፡፡ ባይነሳም በምስጢር ዘመቻው ከመስፋፋት የሚያግደው የለም፡፡ እናም እንደኔ ብቸኛው መፍትሔ የሚመስለኝ ትውልድን ማንቃት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡


No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog