የሀያኛውን ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቀየሩ አነስተኛ ሰነዶች

(አፈንዲ ሙተቂ):-
ይህንን አነስተኛ መጣጥፍ ከዚህ በፊት (በታህሳስ ወር 2006) ለጥፌው ነበር፡፡ ነገር ግን በርካታ ወዳጆቼ ከፌስቡክ ግድግዳህ ላይ ልናገኘው አልቻልንም” ስላሉኝ እንደገና መድገሙ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለፍለጋ ቀለል የሚለው ብሎግ ስለሆነ በኔ ብሎግ ላይም እለጥፈዋለሁ፡፡
እነዚህ ሰነዶች በ20ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳርፈዋል በማለት በዝርዝሩ ውስጥ የያዝኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ዝርዝሩ በሌሎች ምሁራንም ሆነ የጥናት ተቋማት እውቅና አልተሰጠውም፡፡ ማንም ሰው የክፍለ ዘመኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ ገምግሞ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድረዋል ያላቸውን ሰነዶች ሊጠቁም ይችላል፡፡ እኔም ይህንኑ ነው ያደረግኩት፡፡

ሰነዶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. አዕምሮ ጋዜጣ- 1904
2. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ህገ-መንግሥት- 1923
3. የኤርትራ ፌዴሬሽን ህገ-መንግሥት 1944
4. የተሻሻለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ህገ-መንግሥት- 1948
5. የጀብሃ ቻርተር- 1954
6. የሜጫና ቱለማ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ-1955
7. የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ (በዋለልኝ መኮንን የተጻፈ ጽሑፍ)-1961
8. “ንህናን ዓላማናን”(እኛና ዓላማችን)- ሻዕቢያ ከጀብሃ የተገነጠለበት አነስተኛ ጥራዝ-1964
9. ደርግ ስልጣን የያዘበት አዋጅ- መስከረም 2/1967
10. የገጠር መሬትን ለህዝብ ያደረገው አዋጅ- የካቲት 25/1967
11. ዲሞክራሲያ ጋዜጣ (የኢህአፓ መመስረት ይፋ የሆነበት የፓርቲው ህቡዕ ጋዜጣ)- ነሐሴ 27/1967
12. የተሓሕት/ህወሐት ማኒፌስቶ- የካቲት 1968
13. የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አዋጅ- ታህሳስ 1968
14. የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት የተመሰረተበት አዋጅ- ሚያዚያ 1968
15. የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም- ሰኔ 1968
16. ኢሰፓአኮ የተቋቋመበት አዋጅ-ሰኔ 1971
17. ኢሰፓ የተመሰረተበት አዋጅ- መስከረም 1977
18. የኢህዲሪ ህገ-መንግሥት-ጳጉሜ 1979
19. የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ቻርተር- ሀምሌ 1983
20. የፕሬስ አዋጅ- የካቲት 1984
21. የክልሎች ማቋቋሚያ አዋጅ- ጥቅምት 1985
22. ኢትዮጵያ ለኤርትራ ነጻነት እውቅና የሰጠችበት ደብዳቤ (በአቶ መለስ ዜናዊ የተጻፈ)-ሚያዚያ 1985
23. የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት- ህዳር 29/1987
24. የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያበቃበት የአልጀርስ ስምምነት -ታህሣስ 1993
25. አብዮታዊ ዲሞክራሲና ቦናፓርቲስታዊ የመበስበስ አደጋዎች (በአቶ መለስ ዜናዊ የተጻፈ ጥራዝ)- ጥር 1993
26. የቅንጅት ማኒፌስቶ-1997
ከላይ የተዘረዘሩት ሰነዶች በኔ እይታ በ100 ዓመት (ከ1900-2000 በነበረው) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አድርሰዋል፡፡ እያንዳንዱን ሰነድ ልብ ብላችሁ ካያችሁት የፖለቲካ ሚናው ከፍተኛ እንደነበረ በቀላሉ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ ለምሳሌ አቶ መለስ “ቦናፓርቲዝም” በሚል ርዕስ የጻፉት ጽሑፍ በ1993-95 የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በከፍተኛ ጡዘት ውስጥ የጨመረ ነው፡፡ እነ ስዬ አብርሃን ከማባረር ጀምሮ የክልሎችን አስተዳደራዊ መዋቅር እስከመቀየር እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለመሳሰሉት ፐሮግራሞች ትግበራ ጥርጊያ ጎዳና ያመቻቸ ነው (የጸረ-ሙስና ኮሚሽንም የርሱ ውልድ ነው)፡፡ የህዝብ ድርጅት ጽ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅም “ቀበሌ” የሚለውን የአስተዳደር አከፋፈል ከማስተዋወቅ ጀምሮ በቀይ ሽብር ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን የጥበቃ ጓዶች እስከ ማስታጠቅ ድረስ ላሉት ታላላቅ ክስተቶች መፈጠር እንደ እርሾ ሆኖ አገልግሏል፡፡
በናንተ በኩል በዚህ ዝርዝር ውስጥ መካተት አለባቸው የምትሏቸው ሰነዶች የትኞቹ ናቸው? በናንተ ሚዛን ፖለቲካዊ ሚናቸው ሀይለኛ የሆኑትን መጠቆምና በኔ ያቀረብኩትን ዝርዝር መተቸት ትችላላችሁ (የኤርትራ ሰነዶች በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተጽእኖ ስለነበራቸው ነው)፡፡
ሰላም
———————–
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 4/2000
Source: Zehabesha.com
 

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog