ሕመም የትኛውም አካል ላይ ሲከሰት ያሰቃያል። የሕመም ትንሽ የለውም። ይሁንና አንዳንዴ ሕመምን ከሕመም የማበላለጥ ሃሳብ ይሰጣል። «እንደ ጣት ቁስል አትነ ዝንዘኝ» የሚለው የጣት ቁስለትን ጥዝጣዜ ያመለክታል። ይህን የጠቀስኩት ብዙውን ጊዜ ከእግር ጣትና እጅ ላይ የሚከሰተውን ሕመም ምንነት መከላከያና ሕክምና ወዘተ የተመለከቱ መረጃዎችን ለመስጠት አስቤ ነው። – ስለ «ጋንግሪን። ስለ ጋንግሪን ማብራሪያ የሰጡን ዶክተር ሄለን ይፍጠር ይባላሉ።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔ ሻሊስት ሐኪምና በስኳር ሕመም ትምህርትና ጥናት ላይ የሚገኙ ምሁር ናቸው።
ጥያቄ፡- ጋንግሪን ምንድን ነው?
ዶክተር ሄለን፡- ጋንግሪን ወደ አማርኛ ሲመለስ በደም እጥረት የሞተ የሰውነት ክፍል እንደማለት ነው። አንድ የሰውነት ክፍል ደም አጥሮት ምግብና ኦክስጅን አልደርሰው ብሎ ሲጠቁር ሕይወት አልባ ሆኖ ሲሞት ጋንግሪን ተፈጥሯል ማለት ነው።
ጥያቄ፡- የጋንግሪን መነሻ ወይም መከሰቻ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?
ዶክተር ሄለን፡- አንደኛ በተለያዩ አደጋዎችና ምክንያቶች የደም ዝውውር ቢቋረጥ ያ ዝውውሩ የተቋረጠበት የሰውነት ክፍል ጋንግሪን ይፈጥራል። ሁለተኛ የልብ ችግር ያለባቸው ሰዎች ደም ይረጋና ከልብ ወደ ደም ሥሮች ይሄዳል። ትንሽም የረጋች ደም ብትሄድ መተላለፊያ ትዘጋለች። ይህች የረጋች ደም የዘጋችው የደም ሥር ይመግበው የነበረው የአካል ክፍል ጋንግሪን ይፈጥራል። በደም ምግብና አየር እጥረት ምክንያት ይሞታል።ሦስተኛ በደም ሥር ጥበት ጋንግሪን ይፈጠራል። በረጅም ጊዜ የመጣ የስኳር ሕመምተኞች፣ የደም ግፊት ችግር ያለባቸውና የደም ቅባት ከፍ ያለባቸው ሕሙማን የደም ሥራቸው ሊጠብ ይችላል። ደም ሥራቸው ላይ ቅባት እየተጋገረ ጠቦ በመጨረሻ የደም መተላለፊያ ይዘጋል። ደም ከተቋረጠበት አካል በታች ያለው ሰውነት ጋንግሪን ይፈጠርበታል። አራተኛው ምክንያት ኢንፌክሽን ነው። የሰውነት ክፍል ኢንፌክሽን ፈጥሮ ሲያብጥበትና በባክቴሪያ ሲጠቃ በደም ሥር ደም አይደርሰውም። የምግብ ዑደቱ ስለሚቋረጥ ጋንግሪን ይፈጠራል ይሞታል።
ጥያቄ፡-የጋንግሪን ሕመም በዘር ይተላለፋል?
ዶክተር ሄለን።- በተወሰኑ የደም ስር ችግሮች (እንደ ስኳር ባሉ) በዘር የሚመጣ ችግር በጣም አነስተኛ ነው። ነገር ግን ስኳር ሕመም ሳይኖርም በማጨስና በሌላም ምክንያት የደም ዝውውርን መዝጋት ጋንግሪን ሊያመጣ ይችላል። ዋና መነሻዎች የሚባሉት ረዥም ዓመት የቆየ የደም ግፊት፣ የስኳርና የደም ቅባት (ኮሌስትሮል) ችግሮች የደም ሥር ጥበትና መዘጋት ናቸው።
ጥያቄ፡- ጋንግሪን በአገራችን ምን ያህል ችግር እያደረሰ ነው?
ዶክተር ሄለን፡- የጋንግሪን ሕመም የሚከሰትባቸው ሰዎች ከሃምሳ ከመቶ በላይ የስኳር ሕመም ያለባቸውና በስኳር ሕመም መያዛቸውን የማያውቁ ናቸው። የእግር ቁስለት ያጋጠማቸውና በጋንግሪን የታመሙ ሲመረመሩ ስኳር ሕመምተኛ ሆነው ይገኛሉ። የዓይንና የነርቭ ችግር አጋጥሟቸው ሲመረመሩም ስኳር ሕሙማን ሆነው
ይገኛሉ።በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስኳር ሕሙማን ከአሥራ አራት እስከ ሃያ አራት ከመቶ ቢያንስ አንድ ጊዜ የእግር ቁስለት ያጋጥ ማቸዋል። ከእነዚህም ሃያ አምስት ከመቶው በቁስለቱ ምክንያት የእግር መቆረጥ ያጋጥማቸዋል። በአገራችንም ከሕክምና ክትትልና ስኳርን ከመቆጣጠር ባህል እንዲሁም ስኳርንና የእግር ቁስለትንም ሆነ ጋንግሪንን ቀድሞ ከመከላከል ዝቅተኛነት የተነሳ እርግጡን መናገር ባይቻልም ከዓለም አቀፉ ተሞክሮ እንደ ሚበልጥ ይገመ ታል። በጥናት ባይሆንም በየቀኑ የሚታየው ይህ ነው። በአገራችን ምልክት የማያሳየው 2ኛው ዓይነት ከሰላሳና አርባ ዓመት በኋላ የሚከሰተው የስኳር ሕመም እየተስፋፋ ነው። የእግር ቁስለትና የጋንግሪን በሽታም በዚያው መጠን የሕሙማኑን ጉዳት እያባባሰ ነው።
ጥያቄ፡- የጋንግሪን በሽታ መከላከያ ምንድን ነው?
ዶክተር ሄለን፡- ዋናው መከላከያው የስኳርን ሕመም መኖር አለመኖር ቀድሞ ተመርምሮ ማወቅ ነው። 2ኛው ዓይነት የስኳር ሕመም (ከጉልምስና ዕድሜ ጀምሮ የሚከሰት) ምልክት የለውም። በቅድሚያ መመርመር። የደም ግፊት ካለም ቀድሞ መመርመር። የሚያጨሱ የልብ ችግር ያለባቸው ክብደታቸው ከፍ ያለና በዘር የስኳርና የግፊት ችግር ያለባቸው ቀድመው መመርመር አለባቸው። ስኳር ከተገኘ ሕክምናውን በሚገባ መከታተል፣ ግፊትና የደም ቅባትን መቆጣጠር፣ ማጨስን ማቆም፣ ለእግር ጥንቃቄ ማድረግ ጋንገሪንን ቀድሞ መከላከል ነው።
ጥያቄ፡- የጋንግሪን ሕመም ሕክምናው ምንድን ነው?
ዶክተር ሄለን፡- ጋንግሪን የሞተ የአካል ክፍል ላይ የሚከሰት በመሆኑ መወገድ ብቻ ነው ሕክምናው። እጅና እግር ላይ የሞተ አካል ዝም ከተባለ ይስፋፋል። ወደ ሌሎች አካባቢዎች ይሠራጫል። ለከፍተኛ ሕመምና ሞት ይዳርጋል። በምግብና ኦክስጅን እጥረት የሞተ አካል በመሆኑ ማስቀጠል አይቻልም። እንዳይፈጠር መከላከል
እንጂ ጋንግሪን ከተፈጠረ ያ የተፈጠረበት አካል ሕይወት አልባ ስለሆነ የትም አገር ቢኬድ ተቆርጦ ነው የሚወጣው።
ጥያቄ፡- ጋንግሪን በእግርና በእጅ ላይ ብቻ ነው የሚከሰ ተው?
ዶክተር ሄለን፡- ብዙውን ጊዜ በእግርና እጅም ላይ ይከሰታል። እጅና እግር ላይ የሚወጣው ነው «ጋንግሪን» የተባለው። ሆኖም በሌላ የሰውነት አካልም የደም ዝውውር ቢቋረጥ ጋንግሪን ሊፈጠር ይችላል።
ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ በእግር ላይ የሚከሰት ከሆነ ለእግር የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈ ልጋል?
ዶክተር ሄለን፡- አዎ! ለእግር የተለየ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የነርቭ ችግር የደም ሥር ጥበት ከተከሰተና የስኳር ሕመም ካለ በየቀኑ እግርን ማየት በዓመት አንድ ጊዜ እግርን መመርመር ያሻል። « የደም ዝውውሩ ጥሩ ነው አይደለም በእግሩ ላይ ያለ ስሜት ቀንሷል? የእግር ቅርጽ ለውጥ አለ?» የሚሉት ይመረመራሉ። ቁስል የነበረበት ከሆነም መታወቅ አለበት። ከእነዚህ አንዱ ችግር ካለ ለቁስለትና ለመቆረጥ እንዳይ ጋለጥ መከላከል ይገባል። ግለሰቡ በየቀኑ እግሩን ማየት አለበት። በላይ፣ በታች ፣በጣቶቹ መሐል ስሜት መኖሩን ለውጥ መከሰቱን ልብ ማለት አለበት። በየቀኑ ማታ መታጠብ ማድረቅና ደርቆ ተሰነጣጥቆ ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር እንደሎሽን ያሉ ቅባቶችን መቀባት ይመከራል፡፡ ጥፍሩን ሲቆርጥ በምላጭ በሰንጢ ሳይሆን በጥፍር መቁረጫ መሆን አለበት፡፡ አቆራረጡ በቀጥታ (አግድም) ነው፡፡ ጎንና ጎኑን በሞረድ ማስተካከል ይበቃል። ይህ አቆራረጥ ለሁሉም ሰው ጥሩ ነው።
ሌላው ጥንቃቄ የጫማና ካልሲ ነው። ስልሳ ከመቶው የእግር ቁስለት በስኳር ሕሙማን ላይ የሚከሰተው ከጫማ ጋር በተያያዘ ነው። አዲስ ጫማ ይጠባል፤ ብዙ ይኬድበታል፤ እግር ይላጣል ፤ ውሃ ቋጥሮ ችግሩ ይጀምራል። ጫማ ማሠሪያ ያለው፣ ጫፉ ሹል ያልሆነና ብዙ ሙቀት የማይፈጥርና የሚመች መሆን አለበት።
ሴቶች ባለተረከዝ ጫማና ክፍት ጫማ ለአደጋ ስለሚያጋልጣቸው መተው አለባቸው። በቤትና በየትኛውም ቦታ በባዶ እግር መሄድ ክልክል ነው። ካልሲም የጥጥና ጫፉ ተቀዶ ጣትን ለጫማ ፍትጊያ የማያጋልጥ መሆን አለበት።
ጥያቄ፡- ጥፍርን ገባ ብሎ መቁረጥ ለጋንግሪን እንደሚያጋልጥ የሚነገረው እውነት ነውን?
ዶክተር ሄለን፡- ጥፍርን በመቆረጥ ብቻ ጋንግሪን ሊመጣ ይችላል ማለት አይደለም። የእግርና የእጅ መቁሰል ወደ ጋንግሪን የሚሄደው አስቀድሞ የስኳር፣ የደም ስር ጥበትና መሰል የጤና ችግር ነው። በሽታ የመከላከል አቅማቸው ከሌላው ያነሰ ነውና በትንሽ ክፍተት ኢንፌክሽን ይፈጥርና ባክቴሪያ ይይዝና ቶሎና በቀላሉ
የማይድን እብጠት ይፈጠራል። በተለይ የስኳር ሕሙማን ከጥፍሩ ጋር የተያያዘውን ሥጋ ከነኩ በቀላሉ ለችግሩ ይጋለጣሉ።
ጥያቄ፡- የእግር ቁስለት ወደ ጋንግሪን ተቀይሮ ሙት ወይም ሕይወት አልባ የሆነበት ሰው ጣቱ ወይም እግሩ መቆረጥ እንዳለበት ሲነገረው ምን ይመልሳል?
ዶክተር ሄለን፡- ሰውኛ ነው። ማንም ሰው አካሉን ማጣት አይፈልግም። ማንም ሰው ቶሎ አይቀበለውም። በጣም የታመመ ወይም ሕይወቱ አደጋ ላይ የሆነ ካልሆነ በቀር ወዲያው አይስማማም። « የሚሆን ነገር ሞክሩልኝ እንጂ!» ይላል።
ጥያቄ፡- ውሳኔያችሁን አልቀበል ብሎ የሚሄድ አለ?
ዶክተር ሄለን፡- እንቢ ብሎ በጊዜ ሳይስፋፋ ይቆረጥ ተብሎ ጥሎ ሂዶ ብሶበት የሚመጣ አለ። አማራጭ ሲያጣ ነው የሚስማማው። እኛ ግን ቆስሎ ጠቁሮ ከሞተ መመለስ አይቻልም። ሌላ ሕክምና የለውም ብለን እናስረዳለን።
ጥያቄ፡- የአሁኑ መልዕክትዎ ምንድን ነው?
ዶክተር ሄለን፡- ቀድሞ መከላከል። ስኳርን መመርመር፤ ቁስለት ከተከሰተ በባለሙያ መታከም ነው። የደም ስር ጥበትንና የሚሞት አካልን በሌላ ደም ስር ደም እንዲያገኝ የሚያደርጉ አዳዲስ ሕክምናዎች አሉ። ቁስለት ሲኖር በቅባት፤ በሎሚ… ከማለት ቀድሞ መታከም ይገባል። ቁስለቱ ተባብሶ ሆስፒታል እስከሚተኙ መጠበቅ
ችግሩን ያበዛዋል።
ጥያቄ፡- አመሰግናለሁ!
ዶክተር ሄለን ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ዶክተር ሄለን፡- ቀድሞ መከላከል። ስኳርን መመርመር፤ ቁስለት ከተከሰተ በባለሙያ መታከም ነው። የደም ስር ጥበትንና የሚሞት አካልን በሌላ ደም ስር ደም እንዲያገኝ የሚያደርጉ አዳዲስ ሕክምናዎች አሉ። ቁስለት ሲኖር በቅባት፤ በሎሚ… ከማለት ቀድሞ መታከም ይገባል። ቁስለቱ ተባብሶ ሆስፒታል እስከሚተኙ መጠበቅ
ችግሩን ያበዛዋል።
ጥያቄ፡- አመሰግናለሁ!
ዶክተር ሄለን ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
Source: www.tenaadam.com
No comments: