አስራት አብርሃም
የሳውዲ መንግስት በወገኖቻችን ላይ እየፈፀመ ባለው ግድያ እና ግፍ ምክንያት በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራው ሰልፍ በመንግስት በእኩል ይሁንታ እንዳላገኘ ብንሰማም የሆነው ይሁን እነርሱ በሰው ሀገር መከራና ስቃይ እየተቀበሉ አይደለ በሚል ነው ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር ወደ ሰልፉ ለመሄድ የቆረጥነው። ችግር ሊኖር እንደሚችል ገምተናል።
የሳውዲ መንግስት በወገኖቻችን ላይ እየፈፀመ ባለው ግድያ እና ግፍ ምክንያት በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራው ሰልፍ በመንግስት በእኩል ይሁንታ እንዳላገኘ ብንሰማም የሆነው ይሁን እነርሱ በሰው ሀገር መከራና ስቃይ እየተቀበሉ አይደለ በሚል ነው ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር ወደ ሰልፉ ለመሄድ የቆረጥነው። ችግር ሊኖር እንደሚችል ገምተናል።
ከሰማያዊ ፓርቲ ብርሀኑ ተክለያሬድ ጋር የት ደረሳችሁ እየተባባልን እየተደዋወልን ነበርና በመሀሉ ስልኩ ጠፋኝ። መጨረሻው ግን አራት ኪሎ እንደታገቱ ሰማንና እኔና ሌሎች ሶስት ጓደኞቼ ሆነን ወደ ሰልፉ ቦታ መሄድ ጀመርን። ከኋላችን ብዙ ሰው ቀስ እያለ እየመጣ ነበር። ወደ ሰልፉ እየተጠጋን ስንመጣ ብዙ ሰው ወደእኛ አከባቢ እየሸሸ ሲመጣ ተመለከትን። የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወጣት ሴት ልጆች እያለቀሱ ወደ እኛ እየመጡ ነው። በዚህ ጊዜ እነ ዳዊት ከበደ፣ ኤልያሰ ገብሩ እና እስክንድር ፍሬው አግኝተናቸው ስለሁኔታው
ስንጠይቃቸው ፌደራል ፖሊሶች ሰልፉን በኃይል እየበተኑት መሆኑ፣ ብዙ ሰውም ክፉኛ እየተደበደበ መሆኑንና ሰውም እያፈሱ እንደሆነ ነገሩን። ፌደራል ፖሊስ ያገኘውን ሰው ሁሉ እየመታ እንደሆነና ወደኋላ መመለሱ እንደሚሻልም ነገሩን።
ስንጠይቃቸው ፌደራል ፖሊሶች ሰልፉን በኃይል እየበተኑት መሆኑ፣ ብዙ ሰውም ክፉኛ እየተደበደበ መሆኑንና ሰውም እያፈሱ እንደሆነ ነገሩን። ፌደራል ፖሊስ ያገኘውን ሰው ሁሉ እየመታ እንደሆነና ወደኋላ መመለሱ እንደሚሻልም ነገሩን።
እስኪ ትንሽ ወደፊት ገፍተን የሚሆነውን እንይ ብለን ወደፊት ትንሽ እንደሄድን በፖሊስ የተያዙ የምናውቃቸው ልጆች አገኘንና ሰላም እንዳልናቸው እኛም በዚያው በቁጥጥር ስር ዋልንና ወደ አንድ ግቢ ውስጥ አስገቡን። እዚያ ትንሽ ካቆዩን በኋላ የፖሊስ መኪና አስመጥተው እያዳፉ እና እየተሳደቡ ጫኑን። አልጫንም ብሎ ያስቸገረ ሰው የለ! በዚያ ሰዓት ለምን እንደሚማቱና እንደሚሳደቡ ባስብ ባስብ ሊመጣልኝ አልቻለም። ለማንኛውም ዱላው እንዳረፈብን ፈጠን ፈጠን ብለን ተሳፈርን። ከኋላው በክፍቱ ነው የተጫንነው፤ ሶስት ፖሊሶችም ከእኛ ጋር ተጭነዋል፤ የተወሰኑ ደግሞ ከጋቤናና ከውስጥ ገቡ። ከዚያ በኋላ መኪናዋ ዋናውን መንገድ ትታ በመንደር ውስጥ ለውስጥ በፍጥነት እየበረረች ከፊት ያገኙት ሰው ሁሉ “ዞር! በል ዞር በል!” እያሉ አጣደፉት። በመንገድ ላይ የነበረው ሰዉ ሁሉ በድንጋጤ ወደ ጉድጓድም ወደ ገደልም እየዘለለ ገባ። አንዱ ግን ፈጠን ብሎ መሸሽ ባለመቻሉ ፖሊሰቹ እያዳፉ ከእኛ ጋር ቀላቀሉት።
ከእኛ ጋር ከተጫኑት ሶስት ፖሊሶች ውስጥ አንዱ አዛዥ ነው መሰል ሽጉጥ ታጥቋል። በጣም ተናዷልም። “አሁን በዚህ ቀዳዳ ተጠቅማችሁ መንግስት ልትጥሉ ነው አይደለ የፈለጋችሁት! የኢትዮጵያ ሰራዊት አንድ ባንድ ሞቶ ሁሉም ሳይልቅ ይሄ መንግስት አይወድቅም! ይሄ ህገ መንግስት እንዴት እንደመጣ ታውቃላችሁ?! አታውቁም! ስለማታውቁ ነው! ልብ ካላችሁ ጫካ አትገቡም! ፈሳም ሁላ!” ብዙ ብዙ እዚህ ለመግለፅ የሚከብዱኝ ስድቦች ሁሉ ይሳደባል። ከእርሱ ጋር የነበሩት ሌሎች ሁለት ፖሊሶች ደግሞ እርሱን ተከትለው ይሳደባሉ፤ እርሱ ሲማታም ተከትለው እንደሚማቱ ያወቀኩት ትንሽ ቆይቼ ነው። ቢያንስ አንድ ሰው ለመማታት ወይም ለመሳደብ ጊዜ እንኳ በራሴ ጊዜ አያስብም እንዴ! ስድቡ መቆሚያ አልነበረውም። በእውነቱ እኔ ይህ ሰው የህግ ሰው ነው ብዬ ለማሰብ ከበደኝ። ፍፁም በንዴትና በጥላቻ አቅሉን ስቷል።
በዚህ ጊዜ እኔ ያረጋገሁ መስሎኝ “አንተ ፖሊስ ነህ ቢያንስ የለበስከውን ልብስ እንኳ ማክበር አለብህ እኛ ሰልፍ ነው የወጣነው የፈፀምነው ወንጀል የለም። አሁን ደግሞ በህግ ቁጥጥር ውለን በሰላም እየሄድን ነው፤ ስድቡና ዱላው ለምን አስፈለገ? ይሄ እኮ ትርፍ ነገር ነው” ብዬ ተናግሬ ሳልጨርስ “ምን አባትህ ታመጣለህ?” ብሎ ሊማታ እጁን ሰነዘረ። እነዚያ ፖሊሶችም እርሱን ተከትለው እጃቸውን ሰነዘሩ። ፖሊሱ የሚችለውን ስድብ ሁሉ አወረደብኝ። ሁኔታው ስላልፈቀደለት እንጂ እንደ ደርግ ጊዜው አሰልፎ ቢረሽነን የሚጠላ አይመስልም። በትግራይ እንዲህ ዓይነቱ ሰው “ደርጊ” የሚል መጠርያ ነው የሚሰጠው። በእውነቱ እነም ይሄ ሰው “ደርጊ” ከሚል ቃል ሌላ የሚመጥነው ስም አላገኘሁለትም። በኋላ ከሌሎች ፖሊስ ጠይቄ እንደተረዳሁት ከሆነ ረዳት ሳጂን ክንፈ ነው የሚባለው፤ የአባቱን ስም ለማግኘት አልቻልኩም። የላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ፖሊስ ነው። በግዕዝ ክንፈ ማለት ራሱን የቻለ ቃል አይደለም ሙሉ ለመሆን የሆነ ቅጥያ ያስፈልጋል። ብዙውን ጊዜ የመላዕክት ስም ነው የሚከተለው። ለምሳሌ ክንፈ ሚካኤል፣ ክንፈ ገብርኤል ወዘተ እየተባለ እንደሚጠራው ማለት ነው። የዚህ ሰው ስም ግን ከተግባሩ ተነስቼ ስገምት ክንፈ ሳጥናኤል መሆኑን አለበት። አሁን ይሄ ሰው ለምን እንደዚያ ያደርገዋል? ከፈለጋችሁ ጫካ ግቡ የሚለን የጫካ መንገድ ጠፍቶን እኮ አይደለም እዚያ የተገኘነው፤ የወገኖቻችን ሰቆቃና መከራ ሰምተን ዝም ብሎ መቀመጥ ስላለቻልን ቢያንስ እዚህ ካለው የሳውዲ ኤምባሲ ላይ ተገኝተን ድምፃችንን በማሰማትና አጋርነታችን ለማሳየት ነው እንጂ መንግስት ለመገልበጥ አይደለም ሰልፍ የወጣነው። ለመሆኑ የጫካው መንገድ ካለኢህአዴግ ሌላ የሚያቅው የለም እንዴ። ጫካ ቢገባ ያው የድሃ ልጅ ነው የሚሞተው፤ የድሃ እናት ናት የምታለቅሰው ብለን ነው እንጂ የጫከ መንገድ ጠፍቶኝ አይደለም። በኃይል የሚሆን ነገር የሰው ህይወት እና የንብረት ውድመት ስለሚያስከትል ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ዘላቂ ሰላም ስለማያስገኝ እንጂ መንገዱማ በጣም ቀላል ነው።
ደራሲ አስራት አብርሃም
አንዱ ፖሊስም “አሁን ተስልፋችሁ ምን አመጣችሁ?” ብሎናል ተደበደባሁ እንጂ የሚል ቅላፄ አለው ከአነጋገሩ። የሰልፉ አላማ እኮ መንግስት ለመገልበጥ አልነበረም። እንዲያውም ሰልፉማ ከታለመው በላይ ተሳክቷል። አንደኛ ለሳውዲ መንግስት ቁጣችን ለመግለፅ ነበር የፈለግነው እነርሱን ሆኖ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሲፋለምላቸው በቪድዮ ሁሉ ሲቀርፁ ነበር። ስለዚህ ፈደራል ፖሊስ ባይኖር ብለው ማሰባቸውና መስጋቸው አይቀርም። ስለዚህ ህዝቡ በሳወዲ ድርጊት ምን ያህል እንደተቆጣ መገንዘባቸው አይቀርም። ሁለተኛ ኢትዮጵያውያን ለሀገሩ የሚቆረቆር መንግስት እንደሌለን በድንብ ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ህዝብ በሰው ሀገርም በሀገሩም በፖሊስ የሚደበደብ የሚታሰርና የሚዋረድ መሆኑ ታይቷል። መንግስት የለንም ቢባል እንዴት ማጋነን ሊሆን ይችላል። መንግስት ቢኖረን ኖሮማ ቢያንስ እንደዚህ ሊሆን አይችልም ነበር።
እንዲያ እያዋገቡና እየሰደቡ ላንቻ በሚባለው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ አስገቡን። እዚያ ቀድሞውን እዚያ ከደረሱ ሌሎች ሰልፈኞች ጋር ቀላቀሉን። ኢዮብ አራጋው የተባለ ልጅ መሬት ላይ ያጣጥራል። “ኧረ እባካችሁ አስቸኳይ ህክምና ያስፈልገዋልና ወደ ህክምና ውሰዱት” እያለ እዚያ የነበረ ሰው ሁሉ ይጨሀል። የሚገርመው ነገር አንዱ ፖሊስ “በመጀመርያ ቃሉ ይሰጥና ከዚያ በኋላ ወደ ህክምና ይሄዳል” አለ። በዚህ ጊዜ እንኳን ቃሉን ሊሰጥ በአጋባቡ እንኳ መተንፈስ አይችልም ነበር። በኋላ ከተወሰነ ቆይታ ልጁ ወደ ህክምና ተወሰደ። አንዴት የሰባ ዓመት እናት ከመንገድ ላይ አፍሰው እኛ ጋር አምጥተው ቀላቀሏቸው። ከዚያም አንዲት ልጅ “እማማ ምን ሆነው ነው?” አለቻቸው። “የሆንኩትንማ እናንተው ንገሩኝ እንጂ” ብለው በዚያ ጭንቅ ሰዓት ላይ አሳቁን። እናቷ ሞታባት ጥቁር የለብሰች ሁሉ ከመንገድ ታፍሳ መጥታለች። ወይዘሮ አዜብ መንስፍን እንኳን ያን ቀን በዚያ አላለፉ፤ ከእኛ ጋር ታሳሪ ይሁኑ ነበር፤ ቢያንስ ማንነታቸው እስኪጣራ ድረስ!
አንዴ በክፍለ ከተማ፣ ሌላ ጊዜ በፆታ እየከፋፈሉ ከቆጠሩን በኋላ አስራ አምስት የምንሆን ሰዎች ብቻ መርጠው ለብቻችን አውጥተው መርማሪዎች ቃል ወደ ሚቀበሉበት ክፍል በረንዳ ላይ ወስደው አስቀመጡን። እዚያ ቁጭ ብዬ ዙርያውን ቃኘሁት። ከፊት ለፊታች ካለው መስኮት ላይ በVECOD የተዘጋጀ “ጭጭ በል!” የሚል ርዕስ ያለው ፖስተር ተመለከትኩ፤ አባት ልጁን ሲገርፍ የሚያሳይ ስዕልም ከጎን ይታያል። ከዚያ ትንሽ ወረድ ብሎ ደግሞ “ቅጣት የበዛበትና በደሉን የማያሰማ ልጅ ነፃነቱን የሚያስከብር ዜጋ ሊሆን ይችላል?” የሚል ፅሁፍ ይነበባል። እርግጠኛ ነኝ ረዳት ሳጂን ክንፈ “ጭጭ በል!” ከሚለው ርዕስ በታች ያለውን ፅሁፍ ያየው ወይም ያነበበው አይመስለኝም። ሲያዩት በጣም ችኩል ሰው ይመስላል። ስለዚህ ይህን ለማንበብ የሚያስችለው ሰከን ያለ ቀልብ ስለሌለው ነው ሊያነበው የማይችለው። ትዕግስቱን እንዲሰጠው ብንፀልይለትስ! አሁን እንዲህ ያለ ሰው ከራሱ በስተቀር ማንን ሊወክል ይችላል! ግፋ ቢል ስርዓቱን ሊወክል ይችል ይሆናል፤ ለዚህም እርግጠኛ አይደለሁም፤ ምክንያቱም እዚያ በጣም ብዙ ፖሊሶች ነበሩ የእርሱ ግን ከሁሉም በጣም የተለየ ነው። በሆነ ጥላቻ በሆነ ስሜት ውስጥ ገብተዋል። ከራሱ ጋር ጠብ ከሌለው በስተቀር አንድ ሰው እንደዚያ ሊሆን አይችልም። በአብዛኞቹ ታሳሪዎች ዘንድ ግን ለእርሱ ስድብ ብዙም ቦታ የሰጠው ሰው አልነበረም። እንዳያያቸው ብቻ አጎንብሰው የሚስቁ ሁሉ ነበሩ፤ እኔ ነኝ እንጂ አዲስ የሆነብኝ እነርሱ ሁሌም ሲታሰሩ የሚባሉት ነገር መሆኑ በኋላ ላይ ነገሩኝ።
ወደሌላኛው ግድግዳ ስመለከት ደግሞ “ብልሁና ቁርጠኛው መሪያችን ቢለዩንም የተጀመሩትን የልማት ስራዎች በቁርጠኝነት እናስቀጥላለን” ይላል፤ ልማት የሚሉት ዜጎችን ማስርና ማንገላታት የሆን ብዬ እያሰብኩ ወደ ሌላኛው ግድግዳ ሳማትር ወደ አንዱ ከፍል መግቢያ ላይ “ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪካ ኩራትና የቁርጥ ልጅ ናቸው” የሚል አገኘሁ። ነገሩን በደንብ ያልገባው አንባቢ “ይሄ ፅሁፍ ስለየትኛው ጠቅላይ ሚንስትር ነው የሚያወራው?” ብሎ መጠየቁ አይቀርም። “ንጉሱ እንዲህ አሉ ወይም እንዲህ አደረጉ” ሲባል ኃይለስላሌ መሆኑ በጣም ግልፅ ነው። ምክንያቱም ከእርሳቸው በኋላ ሌላ ሰው ስላልነገሰ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲል ግን ትንሽ ግር ይላል፤ ምክንያቱም አሁንም ጠቅላይ ሚንስተር አለ ተብሎ ነው ኃይለማርያም እያስተዳደሩ ያሉት። ወይስ የጠቅላይ ሚንስትርነት መዓርግ ለአቶ መለስ ብቻ ነው የተሰጠው። ለምሳሌ እኔ አንዱን ፖሊስ ጠርቼ “ይሄ ፅሁፍ ኃይለማርያም ደሳለኝ ማለቱ ነው?” ብለው “አይደለም” እንደሚለኝ በጣም እርግጠኛ ነኝ፤ ቀጥዬ “አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራትና የቁርጥ ልጅ አይደሉም ማለት ነው” ብለው ግን መልስ የሚኖረው አይስለኝም፤ ምናልባት ረዳት ሳጂን ክንፈ ከሆነ የተጠየቀው፣ የስድብና የዱላ መልስ ይኖረው ይሆናል!
በመጨረሻ ኮንዶም መስጫ ሳጥን ከሚል የቆርቆሮ ሳጥን ላይ ዓይኔ አረፈ፤ ይሄ ጥሩ ነው ቢያንስ ለህይወታቸው ዋጋ ይሰጣሉ ማለት ነው አልኩ፤ በዚያም የሌላውን ህይወት ዋጋ መስጠት ቢማሩ እንዴት ጥሩ ነበር!
እዚህ ፖሊስ ጣቢያ እጅግ በጣም ካሰለቸን ነገር እያንዳንዱ ፖሊስ እየመጣ ስማቸን፣ አድራሻችን፣ የምንሰራበት ቦታ፣ ኃይማኖታችን ሁሉ ይጠይቁናል፤ ፆታችንም ያልጠየቁን እነርሱ ሆነው ነው! ከአስር በላይ ጊዜ ቃላችን ሰጥተናል። እኔማ ለመናገር ሁሉ እየደከመኝ መታወቀያዬን እየሰጠሁ ከዚያ እየገለበጡ የተወሰነውን ጥያቄ እንዲቀንስልኝ አድርጌያለሁ።
ከዚያ ወደ ከሰዓት አከባቢ መርማሪዎች ተከፋፍለው ጥያቄ ይቀበሉን ጀመር። ከዚያ በፊት ግን መስክር ተብለው በእኛ ላይ እንዲመሰክሩ ስለተዘጋጁ ፖሊሶች ትንሽ ልበል፤ “ምስክሮቹ የት አሉ?” ሲል መርማሪው ሰምቼ ገርሞኝ ውጭ ውጪ አያለሁ “ምስክር ደግሞ ከየት ሊያመጡ ነው” ብዬ። ነገሩ ለካ ሌላ ኖሯል፤ እዚያ የነበሩን ፖሊሶች ተከፋፈሉን አንዱ ተነሳና በእርሱ ላይ እኔ
እመሰክራለሁ ብሎ በጣቱ እየጠቆመ ያሳያል፤ ይህ ሰው እኔ ስያዝ እንዳልነበረ በፍፅም እርግጠኛ ነበርኩ። በቦታው አልነበረም፤ ነገር ግን የሆነ የሆነ ነገር ሲያደርግ አይቻዋለሁ ብሎ ምስክርነቱን ሰጠ። ከዚያ እኔ ራሴ ቀርቤ ክሱን ተነበበልኝ። “አረቦች ከሀገራችን ይውጡ” ብለሃል “በአርበኛ የተፃፈ ፅሁፍ ይዘህ ስትጮህ ነበር” “የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በዜጎቻችን ጉዳይ እያደረገ ያለ ነገር አንቋሽሸሃል፣ ድንጋይ ወርርሃል” ብዙ ብዙ ማለቂያ የሌለው ክስ አነበበልኝ እና “የምትለው ነገር አለ?” አለኝ፤ “እኔ ሰልፍ መውጣቴ እርግጥ ነው የምትለው ነገር ግን አልፈፀምኩም” አልኩት። በዚህ መሀል መርማሪው ፖሊስ “ቤተሰብ አለህ? ማለቴ ትዳር አለህ?” አለኝ። “አዎ” አልኩኝ በትህትና! “ታዲያ ምን ልታደርግ እዚህ መጣህ?” አለኝ በማስከተል፤ በዚህ ጊዜ በጥያቄው ተገርሜ “ሰልፉ የላጤዎች መሆኑ አላወቁም ነበር” አልኩት። ቱግ ብሎ “እየቀለድክ ነው!” አለኝ። “እየቀልድክ ያለውስ አንተ” ልለው ፈልጌ ቁጣው አይቼ ተውኩት። በጥፊ ቢያላጋኝስ ማን አዛዥ አለው። ቃሌን ሰጥቼ እንደወጣሁ ያ እኔ ላይ የመሰከረው ፖሊስ “አንተ ለመሆኑ እኔ የተያዝኩት የቱ ጋር ነው? የት ላይ ነው ያየኸኝ?” ስለው እየሳቀ “በኢትቪ” ብሎ አላገጠብኝ።
አንዱ ታሳሪ ደግሞ ለመርማሪው ቃሉን እየሰጠ ነው፤ እናም “ብሄር” በሚለው ጉዳይ ላይ ሊግባቡ አልቻሉም ከመርማሪው ጋር። “ብሄርህ ምንድነው?” ይለዋል። ልጁ “ኢትዮጵያዊ” አለ።
“ኢትዮጵያዊ ብሎ ብሄር የለም ትናገር እንደሆነ ተናገር” ይለዋል ፖሊሱ። ልጅ በዚያ አቋሙ ፀና። መርማሪው ደግሞ ይሄ በፀጋ ሊቀበለው አልፈለገም። በዚህ ተነሳ ሌሎች ፖሊሶችም ተደርበው ልጁን ያወክቡት ያዙ “ብሄርህ ተናገር” እያሉ።
እኔ እስከማውቀው ድረስ “ብሔር” ማለት ሀገር ማለት ነው በግዕዝ። ለምሳሌ “አይተ ብሄርከ?” ካለ “ሀገርህ የትነው?” ማለቱ ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲባል ሀገራዊ ቡድን ለማለት ነው። “ምን ታደርጌዋለሽ!” አለ ጥላሁን! የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መፅሐፍ ብሄርን ምን ብሎ እንደሚተረጎመው አላውቅም።
መርማሪው ትንሽ ካሰበ በኋላ መላ የዘየደ መስሎት “እሺ የትነው የተወለድከው?” አለው። ልጁም ከእርሱ የባሰ እልሀኛ ኖሯል “ደቡብ” አለው። ከስልሳ በላይ ብሄረሰቦች ወደሚኖርበት ክልል ወስዶ ዶለው!
“ደቡብ የት?”
“አርባ ምንጭ።”
በዚህ ጊዜ ምን ብሎ እንደሚፈርጀው ግራ ገባው። “ደብረማርቆስ” ብሎት ቢሆን ኖሮ እዳው ገብስ ይሆንለት ነበር። አንድ ከአሁን በፊት የሰማሁት ቀልድ ነበር ሰውየው መታወቂያ ሊያወጣ ወደ ቀበሌ ይሄዳል “ብሄር?” ይለዋል። ኢትዮጵያዊ አለው። “አውቄብሃለሁ አማራ ነህ ማለት ነው” ብሎ በመታወቂያው ላይ ሞላለት እየተባለ ይነገር ነበር። እናም መርማሪው ልጁን “ብሄር የለኝም በል እንጂ ኢትዮጵያዊ የሚባለ ብሄር የለም” ብሎ ግግም አለበት። ሌሎቹም በቃ ብሄር የለውም ብለህ ሙላው ሲሉት ጊዜ ብሄር የለውም ተብሎ ተሞላለት። በነገራችን ላይ የታሰርነው ከሁሉም ብሄረሰብ ነበር ማለት ይቻላል። አንዱም አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ነውና ብሄሩን ለመናገር ብዙ ካገራገረ በኋላ መጨረሻ ላይ “ጉራጌ” አለ!
በዚህ ጊዜ “የአዲስ አበባ ልጅ በቦታ እንጂ በብሄር መጠራት አይወድም” የሚባለውን አስታውሼ ፈገግ ማለቴ አልቀረም። የጨርቆስ ልጅ፣ የቦሌ ልጅ፣ የፒያሳ ልጅ ማለትን ነው የሚቀናው። ለአዲስ አባባ ልጆች ብሄር በሚለው ቦታ ላይ ኢትዮጵያዊ ተብሎ ቢሞላላቸው እኔም ደስ ይለኝ ነበር። ምክንያቱም የብሄር መለኪያ በዚህ ሀገር በጣም ግልፅ አይደለም። በቋንቋ ነው እንዳትለው ቋንቋ የሚለመድ ነገር ነው፤ ለምሳሌ ደርግ በሰፈራ ወደ ወለጋ ያመጣቸው የትግራይ ሰዎች አሁን ልጆቻቸው ኦሮምኛን ልክ የአከባቢው ሰዎች ያህል ነው የሚናገሩት። በኦሮሚኛ ችሎታቸው እነ ፕሮፌሰር መራራ ጉዳና ሳይቀር ሊያስንቁ ይችላሉ፤ ነገር ግን ኢህአደግ ኦሮሞ ናቸው የሚላቸው አይመስለኝም። አቶ ገብሩ አስራት አባቱ ሙሉ አማራ ናቸው፤ ነገር ግን ትግራዋይ ቁጠር ብባል ከአቶ ገብሩ አስራት አንድ ብዬ ልጀምር እችላለሁ። አቶ መለስም ከኤርትራ እስከ ጎጃም ድረስ ይወለዳሉ። እንዲህ በዘመቻና በንግድ ምክንያት ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀስ እየተዋለደ የኖረን ህዝብ እንዴት አድርገህ ነው የምትለየው!
(ቀሪውን ሳምንት ይቀጥላል)
Source: Fact Magazine
Source: Fact Magazine
No comments: