በአሜሪካ ስለላ ድፍን አውሮፓ ተናውጧል!
የመከላከያና የደህንነትን ነገረ ስራ ጉዳዬ ብለው የሚከታተሉ ባለሙያዎች፤ ሰላይና ተሰላይ በአንድ ጣራ ስር አድፍጠው የየፊናቸውን ጉዳይ የሚከውኑበት መስሪያ ቤቶች ቢኖሩ የስለላ ድርጅቶች ብቻ ናቸው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ሁሌም የሚጠቀሙበት አንድ አሪፍ አባባል አላቸው፡- “በሬ ካራጁ ይውላል” ይላሉ፡፡
የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ይህ አባባል በረጅም የአገልግሎት ዘመኑ ለበርካታ ጊዜ ተጠቅሶበታል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ሌሎችን ለመሰለል የቀጠራቸው ሰላዮቹ፣ ራሱን መልሰው በመሰለል የመከዳትን መራራ ጽዋ ወዶ እስኪጠላ ድረስ ሲግቱት ኖረዋል፡፡
ኤንኤስኤ በሚለው አጭር ስያሜው ይበልጥ የሚታወቀው ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት አሜሪካ ካሏት የተለያዩ የመረጃና የደህንነት ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የዚህ ድርጅት የምሰረታ ታሪክ ልብወለድ ይመስላል፡፡
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ የመገናኛና የኤሌክትሮኒክ ባለሙያዎች፤ የጀርመንንና የጃፓን ከፍተኛ ወታደራዊ ሚስጥሮችን ኮድ በመስበር በአሜሪካ ይመራ ለነበረው
የተባበረው የጦር ሃይል መሪዎች ያስተላልፉ ነበር፡፡ በተለይ የጀርመንን የ“U - Boat” ከፍተኛ ወታደራዊ ሚስጥር ኮድ በመስበር ያቀበሉት መረጃ፣ የተባበረው የጦር ሀይል በሰሜን አትላንቲክና በፓስፊክ አውደግንባሮች ከፍተኛና ወሳኝ ድሎችን እንዲቀዳጅ አስችሎታል፡፡
ይህንን ሁኔታ በትኩረት ይከታተሉ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሀሪ ትሩማን፤ የባለሙያዎችን የሚስጥር ኮዶችን እየሰበሩ የጠላትን ጓዳ ጐድጓዳ የመበርበር ተግባር፣ ከጦርነቱ በኋላም በሚገባ ለመጠቀም ስለሚቻልበት ሁኔታ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግ አዘዙ፡፡ በትዕዛዛቸው መሠረትም ጥናቱ ተካሂዶ ውጤቱ ቀረበላቸው፡፡
ፕሬዚዳንት ትሩማን የቀረበላቸውን የጥናት ውጤት ከአማካሪዎቻቸው ጋር ከገመገሙ በኋላ፣ ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት በሚል ስያሜ በዋናነት “የጠላትን” የግንኙነት መረቦች በመጥለፍ፣ የምስጥር ኮዶችን በመስበር፣ በተለይም በጠላትነት የተፈረጁ ሀገራትን መሪዎች፣ ከፍተኛ የሲቪልና የጦር ሃይል አዛዦችን ማናቸውም አይነት የኤሌክትሮኒክ ግንኙነቶች በመጥለፍ መረጃ እንዲሰበስብ ስልጣንና ሃላፊነት በመስጠት ህዳር 4 ቀን 1952 ዓ.ም እንዲቋቋም አደረጉ፡፡
ድርጅቱ የተቋቋመው ከጦር ሃይሉ፣ ከስለላ ተቋማት፣ ከቴክኖሎጂ የምርምር ተቋማትና ከሌሎች ምሁራን የተውጣጡ ምርጥና ብቁ ባለሙያዎችን በመያዝ ነበር፡፡ ይህ ጠንካራ የሰው ሀይሉ በተለይ በበርካታ አሜሪካውያን ዘንድ እንኳን ሰው ይቅርና ነፋስም በውስጡ አስርጐ የማያስገባ፣ ሁለመናው ድፍንና ለምንም አይነት አደጋ ያልተጋለጠ፣ እጅግ ጠንካራ የስለላ ድርጅት ተደርጐ እንዲቆጠር ምክንያት ሆኖት ቆይቷል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ የድርጅቱ ስዕል የውሸት ነበር፡፡ እንደ ሲአይኤ ሁሉ ይሄውም ድርጅት ከአራጁ ጋር የሚውል በሬ ነበር፡፡
ወጣቱና መልከ መልካሙ ኤድዋርድ ስኖውደን በኮምፒውተር እውቀቱ፣ በመረጃ አያያዝና ትንተና ችሎታው እኔ ነኝ ያለ ድንቅ ባለሙያ ነው፡፡ ለስራውና ለሚሰራበት ድርጅት የነበረው ጥብቅ ታማኝነትም በተለያዩ መስሪያ ቤቶች አብረውት በሰሩ አለቆቹና ባልደረቦቹ ተመስክሮለታል፡፡
ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት እምነት ጥሎበት ቁልፍ በሆነ የመረጃ ምስጢራዊ የስራ ቦታ ላይ በከፍተኛ ደመወዝ የቀጠረውም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ በኤድዋርድ ስኖውደን አዕምሮ ውስጥ ግን የተመሠከረለት ታማኝነት ሳይሆን በሬውን የማረድ ሃሳብ ይመላለስ ነበር፡፡ ስኖውደን በሬውን ለማረድ የሚጠቀምበት ካራ፣ በእውቀትና፣ በችሎታ የተካኑት ጣቶቹ ነበሩ፡፡
እናም ከጥቂት ወራት በፊት እጅግ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ከፍተኛ የአሜሪካ ምስጢራዊ መረጃዎች በረቀቀ ስልት ለህዝብ ይፋ በማውጣት፣ የበሬውን አንገት ክፉኛ ካረደ በኋላ ተሰዶ ሞስኮ ገባ።
ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ ለብሔራዊ የደህንነት ድርጅቱ እስከወዲያኛው ድረስ አይመልሰው የሚያሰኝ ነው፡፡ ኤድዋርድ ስኖውደን ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ በበተናቸው እጅግ በርካታ ሚስጥራዊ መረጃዎች የተነሳ አሜሪካ ፈፅሞ አይታው በማታውቀው የዲፕሎማሲ ቅሌት ውስጥ እስከ አፍንጫዋ ተዘፈቀች፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የብሔራዊ ደህንነት ድርጅት፤ የመሪዎቿን፣ ከፍተኛ የሲቪልና ወታደራዊ መሪዎቿን የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነቶች በመጥለፍ ለረጅም ጊዜ ስትሰልላት እንደነበር ያወቀችው ብራዚል፤ አሜሪካንን በማውገዝና ለአለም በማጋለጥ አገር ይያዝልኝ አለች። ከብራዚል ቀጥላ የቤቷን ጉድ ያወቀችው ሜክሲኮም “የመልካም ጉርብትናና የክፉ ቀን አጋርነት ውለታዬ ይሄ ሆነ ወይ” በማለት አሜሪካ ላይ የእርግማን መአት በማውረድ፣ እሪ እምቧ አለችባት፡፡ ሌሎች የደቡብ አሜሪካ ሀገራትም ለብራዚልና ሜክሲኮ ያላቸውን ወዳጅነት ለመግለጽ አሜሪካን “ደረቅ አይናውጣ!”፣ “ይሉኝታ ቢስ ወራዳ!” በማለት ተጨማሪ ውግዘት አወረዱባት፡፡
ይህን ጊዜ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የብሔራዊ የደህንነት ድርጅቱን መሪዎች አስጠሩና “እንዴት ነው ጐበዝ! ይህ ሁሉ የውግዘትና የእርግማን መአት የወረደብን? ለመሆኑ ምኑን ከምን ብታደርጉት ነው? እንዲያው ስራችሁ ግን ምንድን ነው?” በማለት የአለቅነታቸውን ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የብሔራዊ ደህንነት ድርጅት መሪዎችም፤ በአዋጅ በተሰጠን ስልጣንና ሃላፊነት መሠረት እንዲህ ያሉና እንዲህ የመሰሉ ስራዎችን እንሰራለን፡፡
ከእነዚህ ስራዎቻችን አንዱና ምናልባትም ዋነኛው “Head of state collection” ይባላል በማለት መልስ ሰጡ፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ከቀረበላቸው መልስ “Head of state collection ከሚለው በስተቀር ሌላው ግልጽ ሆኖላቸው ነበር፡፡
ይሄኛውን ግን “ለመሆኑ ምን ማለት ነው” እያሉ ለራሳቸው ሲያሰላስሉ ከቆዩ በኋላ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ሳይጠይቁ እነሱም ሳይሰጧቸው በዚሁ ተለያዩ፡፡
የዚያኑ ቀን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከባለቤታቸውና ከሁለት ሴት ልጆቻቸው ጋር የባለቤታቸው እናት ያዘጋጁላቸውን ሰላጣና አሳ ተመግበው ሲያበቁ፣ ከመተኛታቸው በፊት አምላክ እርግማኑንና ውግዘቱን በብራዚልና በሜክሲኮ በቃህ እንዲላቸው ፀሎታቸውን አቅርበው ነበር፡፡
ከሶስት ቀን በኋላ የተከሰተው ነገር፣ የፕሬዚዳንት ኦባማ ፀሎት እንዳልተሠማ ይልቁንም ኢትዮጵያውያን “የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል” የሚሉት አባባል እንደደረሰባቸው አረጋገጠ፡፡
መዘዘኛው ኤድዋርድ ስኖውደን፤ ለህዝብ ይፋ ያደረገው ምስጢራዊ መረጃ አሜሪካ ፈረንሳይን ለአመታት ስትሰልላት እንደነበር አጋለጠ፡፡ ፈረንሳውያን በተቃውሞ “አገር ይያዝልን!” አሉ። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንድም እሳት ለብሰው፣ እሳት ጐርሰው ለፕሬዚዳንት ኦባማ ስልክ በመደወል ተቃውሟቸውንና ስሞታቸውን ካቀረቡ በኋላ፣ ስለጉዳዩ ይፋ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ይሁን እንጂ ከአሜሪካ ዘንድ ያገኙት መልስ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ የኤሊዜ ቤተመንግስት መግለጫ አመለከተ፡፡
ፈረንሳይ ያስነሳችው አቧራ ጭሱ ገና እንኳ ገለል ሳይል፣ አሜሪካ ስልሳ ሚሊዮን የሚሆኑትን ስፔናውያን የስልክ ንግግራቸውንና የመልዕክት ልውውጣቸውን እየጠለፈች ስትሰልላቸው እንደነበር ኤልሙንዶ የተሰኘው ጋዜጣ አጋለጠ። አሜሪካና ፕሬዚዳንቷ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በቅሌት ላይ ቅሌት ተደራረበባቸው፡፡
የሆኖ ሆኖ ነገሩ ወይም የቅሌቱ ማዕበል በዚህ ቢያበቃ ኖሮ፣ አሜሪካና ፕሬዚዳንት ኦባማ እፎይ ባሉና በተገላገሉ ነበር፡፡ የስፔናውያን የተቃውሞ ጩኸት ገና ተግ ሳይል የጀርመኑ ጉድ ፈነዳ፡፡ አሜሪካ Head of state በተሰኘው የብሔራዊ የደህንነት ድርጅት የስለላ መርሀ ግብር አማካኝነት ጀርመንን በተለይም ደግሞ የቻንስለር አንጌላ መርከልን ተንቀሳቃሽ ስልክ በመጥለፍ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ስትሰልል እንደቆየች መረጃው በይፋ ተጋለጠ፡፡
ይህን ጊዜ ድፍን አውሮፓ ከዳር ዳር ተናወጠ፡፡ የአውሮፓ ህብረት ይህን የአሜሪካ ነውረኛ ድርጊት ከዋነኛ አጀንዳዎቹ አንዱ አድርጐ የሚነጋገር ዘጠኝ አባላት ያሉት የልዑካን ቡድኑ መሪ የሆኑትን ቪቪያን ሪዲንግ፤ “ጓደኛሞችና አጋሮች እርስበርሳቸው አይሳለሉም፤ ይህ ቀላል መርህ ነው፡፡ አሁን የተፈጠረው የመተማመን ቀውስ ነው፡፡ የእርስ በርስ መተማመን ሳይኖር የጋራ አጀንዳ የሆነውን የንግድ ስምምነት እንዴት መገንባት እንችላለን” በማለት የሁኔታውን ከባድነትና አስቸጋሪነት ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል፤ የአሜሪካ አጋር፣ በተለይ ደግሞ የፕሬዚዳንት ኦባማ የቅርብ ወዳጅ በመሆናቸው “አሜሪካ ትሰልለኛለች” ብለው እንዳያስቡ አድርጓቸው ነበር፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በ2009 ዓ.ም እሳቸውና 5250 የሚሆኑ የጀርመን ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለስልጣናት ተንቀሳቃሽ ስልካቸው እንዳይጠለፍ የሚከላከል መሳሪያ ተገጥሞላቸው ነበር፡፡
የአሜሪካው “ፎርብስ” መጽሔት በያዝነው አመት ከአለማችን አስር እጅግ ጠንካራና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ውስጥ በአምስተኛ ደረጃ ያስቀመጣቸው ቻንስለር አንጌላ መርከል፤ ከዚህ ጥንካሬአቸው ባሻገር በቀንደኛ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚነትም በድፍን አውሮፓ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ይህን ነገረ ስራቸውን ያዩ የሀገራቸው ሰዎች “ዳይ ሀንዲ ካንዝለሪን” ወይም “ባለ ተንቀሳቃሽ ስልኳ መሪ” በሚል የቅጽል ስም ያሽሞነሙኗቸዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ቻንስለር አንጌላ መርከል፤ ያለ ተንቀሳቃሽ ስልክ የማይሆንላቸው ሴት ናቸው። ከባለቤታቸው፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከካቢኔና ፓርቲ አባሎቻቸው እንዲሁም ፕሬዚዳንት ኦባማን ከመሳሰሉ የአለም መሪዎች ጋር በዋናነት የሚገናኙት ቢሮዋቸው ውስጥ ባለው ስልክ ሳይሆን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ነው፡፡ በሀገራቸውም ሆነ ከሀገራቸው ውጪ አሰልቺ ወይም ደባሪ ስብሰባ ሲያጋጥማቸው መሠልቸታቸውንና ድብርታቸውን የሚያስወግዱት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ጌም በመጫወት አሊያም መልዕክት በመላላክ ነው፡፡ የአሜሪካው ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት ደግሞ ይሄንን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በርሊን የሚገኘው አዲሱ የአሜሪካ ኤምባሲም አሪፍ የስራ ቦታ ሆኖለታል፡፡ በዚህ ቢሮ ውስጥም እጅግ የተራቀቁ የስለላ መሳሪያዎችን በመትከል፣ የቻንስለር አንጌላ መርከልን የስልክ ንግግርና መልዕክት መጥለፍ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷን እንቅስቃሴያቸውን ሁሉ በጥብቅ ይከታተል ነበር፡፡
በ2008 ዓ.ም ከፍ ባለ ስነሥርዓት አዲሱን የአሜሪካ ኤምባሲ መርቀው ሲከፍቱ፣ ከአሜሪካ ውጪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መንጋ የአሜሪካ ሰላይ የሚርመሰመስበት ዋነኛ ጣቢያ ይሆናል ብለው ያልገመቱት ቻንስለር አንጌላ መርከል ብቻ ነበሩ። የማታ ማታ የቅሌቱን ዜና የነገሯቸው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸው ነበሩ፡፡ ጉዳቸውን ከሀ እስከ ፐ ሰምተው ከጨረሱ በኋላ፣ በከፍተኛ የቁጣ ስሜት “አሀ! እንደ ምስራቅ ጀርመን ጊዜ መሆኑ ነው” አሉ፡፡ አንጌላ መርከል ተወልደው ያደጉት ምስራቅ ጀርመን ውስጥ ስለነበር የኮሙኒስት ፓርቲውን የስልክ ጠለፋ የስለላ ዘዴ በሚገባ ያውቁታል፡፡ ለስርአቱ የነበራቸው ጥላቻ ዛሬም ድረስ አልበረደላቸውም፡፡
ቃል አቀባያቸው ስቴፈን ሲይበርት እንደመሠከሩት፤ አንጌላ መርክል ለፕሬዚዳንት ኦባማ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ደወሉና አይናቸው ላይ በግልጽ የሚታየውን ከፍተኛ የቁጣ ስሜት እንደምንም ተቆጣጥረው “አንተ! ተንቀሳቃሽ ስልኬን ጠልፈህ ስትሠልለኝ ኖረሃል ለካ! ስማ እንዲህ ያለው ወራዳ ድርጊት በመካከላችን ያለውን መተማመን ጨርሶ እንደሚያጠፋው አታውቅም” አሏቸው፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ አስሬ እየማሉና እየተገዘቱ ጉዳዩን አላውቅም አሉ፡፡ የስራ ባልደረቦቻቸውም፤ እርግጥ ነው አንጌላ መርክል ይሰለሉ እንደነበረ ፕሬዚዳንት ኦባማ አያውቁም ነበር አሉላቸው። በመሀሉ ግን የብሔራዊ ደህንነት ድርጅቱን ሃላፊዎች ጠርተው ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ከጠየቁ በኋላ ፕሮግራሙ እንዲገደብ አዘዙ፡፡
የዚህ የስለላ ነገር በአለም አቀፍ ደረጃ ያስነሳው አቧራ፣ የድርጅቱን ሃላፊ ጀነራል ኪዝ አሌክሳንደርን በጣም አብሽቋቸው ነበር፡፡ ኮንግረሱና ሴኔቱ፣ የፖለቲካ ተንታኝ ነን የሚሉት ሁሉ ድርጅቱን የሚከሰቱና ክፉኛ የሚወቅሱት ስለተሰላዮቹ መሪዎች ማወቅ ያለበትን ያህል ማወቅ አልቻለም እያሉ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ትችቱ እንዴት የአጋር አገር መሪዎችን እየሰለለ ሀገሪቱን ቅሌት ያከናንባል ወደሚል ተቀይሯል፡፡ ጀነራል ኪዝ አሌክሳንደር ግን ብሽቀታቸውን ዋጥ አድርገው በመያዝ፣ ለጠየቃቸው አካል ሁሉ በአዋጅ ከተሰጣቸው ተግባርና ሃላፊነት ውጪ አንዳችም ህገወጥ ተግባር እንዳልፈፀሙ፣ መሪዎችን መሠለል ደግሞ ዋነኛው ስራና ሀላፊነታቸው መሆኑን ወዲያና ወዲህ ሳያወላዱ ፈርጠም ብለው አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻ ጽሑፌን የምቋጨው በአንድ ሁነኛ ጥያቄ ነው፡፡ “ለመሆኑ ሌሎችን በመሰል የታወቀው የብሔራዊ የደህንነት ድርጅት የራሱን ምስጢር በወጉ ሸክፎ መያዝ እንዴት አቃተው?”

Source: Addis Admass
No comments: