ለቀጣይ ህክምና 60ሺህ ብር ተጠይቋል
ጋዜጠኞች ገንዘብ ለማሰባሰብ መክረዋል
ከተመሰረት ጥቂት ወራትን ያስቆጠረው የ “ኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጣ ስራ አስኪያጅ ሚሊዮን ደግነው፣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ እና አዘጋጁ ኤፍሬም በየነ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ወደ ሀዋሳ የተጓዙት ለሽርሽር አልነበረም። በነጋታው ረቡዕ የፍ/ቤት ቀጠሮ ስለነበራቸው ነው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት “ኢትዮ-ምህዳር”፤ ከሙስና ጋር በተያያዘ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዙሪያ በዘገበው ዜና ምክንያት፣ ዩኒቨርስቲው በጋዜጠኞች ላይ የ300ሺ ብር ክስ እንደመሰረተባቸው ይታወሳል። ጋዜጠኛ ኤፍሬም አብሯቸው የተጓዘው አንድም ዜናውን የሰራው እርሱ በመሆኑ፣ ተከራከሩ ቢባል ለፍ/ቤቱ በደንብ እንዲያስረዳ፣ ሁለትም የተከሳሽ ባልደረቦቹን የፍርድ ቤት ውሎ በአካል ተገኝቶ ለመዘገብ እንደነበር ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ተናግሯል፡፡
“ማክሰኞ ማታ ራሱ ኤፍሬም አልጋ ፈላልጎ ያዘልን፤ ምክንያቱም የሀዋሳ ልጅ በመሆኑ ከተማዋን በደንብ ያውቃታል” ያለው ጋዜጠኛ ጌታቸው፤ ምሽቱም ሌሊቱም በጥሩ ሁኔታ እንዳለፈ ገልፆ፤ ረቡዕ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ በቀጠሯቸው መሰረት ሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት መቅረባቸውን ይናገራል፡፡ ሆኖም በዘጠኝ ሰዓት ተመልሳችሁ ኑ ተባልን ይላል። “እኛ በፌደራል ደረጃ ተመዝግበን የምንሰራ በመሆናችን ጉዳያችንም በፌደራል ፍ/ቤቶች ይታይልን፤ እንደገና ዘጠኝ ሰዓት ለመምጣት አንችልም፤ ወደ አዲስ አበባ መመለስ አለብን” ብንልም የግድ ዘጠኝ ሰዓት እንድንመለስ ታዘዝን ብሏል ዋና አዘጋጁ፡፡ ጋዜጠኞች ገንዘብ ለማሰባሰብ መክረዋል
ከተመሰረት ጥቂት ወራትን ያስቆጠረው የ “ኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጣ ስራ አስኪያጅ ሚሊዮን ደግነው፣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ እና አዘጋጁ ኤፍሬም በየነ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ወደ ሀዋሳ የተጓዙት ለሽርሽር አልነበረም። በነጋታው ረቡዕ የፍ/ቤት ቀጠሮ ስለነበራቸው ነው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት “ኢትዮ-ምህዳር”፤ ከሙስና ጋር በተያያዘ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዙሪያ በዘገበው ዜና ምክንያት፣ ዩኒቨርስቲው በጋዜጠኞች ላይ የ300ሺ ብር ክስ እንደመሰረተባቸው ይታወሳል። ጋዜጠኛ ኤፍሬም አብሯቸው የተጓዘው አንድም ዜናውን የሰራው እርሱ በመሆኑ፣ ተከራከሩ ቢባል ለፍ/ቤቱ በደንብ እንዲያስረዳ፣ ሁለትም የተከሳሽ ባልደረቦቹን የፍርድ ቤት ውሎ በአካል ተገኝቶ ለመዘገብ እንደነበር ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ተናግሯል፡፡
ከፍ/ቤት ወጥተው በእግራቸው ወደ መነሀሪያ ከተጓዙ በኋላ ሻይ የሚጠጡበት ቦታ ፈልገው አጭር የኤዲቶርያል ስብሰባ እንዳደረጉ የጠቆመው ጌታቸው፤ “በስብሰባችን የተነጋገርነው የጋዜጣው አብዛኛው አዘጋጆች እዚህ በመሆናችን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ባለው ጊዜ ዞር ዞር ብለን ስራ እንስራ፤ ከተሳካልን ከከተማዋ ባለስልጣናት አንዱን የጋዜጣችን እንግዳ እናድርግ” በሚል ተስማማን ይላል ጌታቸው፡፡ ከዚያም የሀዋሳ ጋዜጠኛ ወደሆነ አንድ ጓደኛቸው ይደውላሉ፤ ማንን ብናናግር ይሻላል በሚል እንዲያማክራቸው፡፡ ጋዜጠኛ ጓደኛቸው ግን “ልጄ ታሞብኝ ፒያሳ አካባቢ መድሀኒት እየገዛሁ በመሆኑ፣ ባጃጅ ተሳፍራችሁ ፒያሳ ድረስ ከመጣችሁ እጠብቃችኋለሁ” ይላቸዋል፡፡ ዋና አዘጋጁና ስራ አስኪያጁ በቀጠሮው ሲስማሙ፣ ጋዜጠኛ ኤፍሬም ግን ደስተኛ እንዳልነበር ጌታቸው ተናግሯል፡፡ “ለምን እዚሁ አንጠብቀውም? የእኛ ወደ ፒያሳ መሄድ አልታየኝም” ብሎም ነበር፤ እንደ ጌታቸው ገለፃ፡፡
“ባክህ እንሂድ ጊዜ አናባክን ብየው፣ ፒያሳ ለመጫን ከተደረደሩት ባጃጆች ውስጥ በዥዋዥዌ መልክ ይንቀሳቀስ የነበረ ባጃጅ ላይ ቀድሜ ገባሁ ያለው ጌታቸው፤ ኤፍሬምም ደስ ሳይለው አብሮ ባጃጅ ውስጥ መግባቱን ይናገራል፡፡ “ባጃጁ በጣም ይበራል፤ ትንሽ እንደሄድን ኤፍሬም አሁንም “በቃ” እዚህ እንውረድና ማኪያቶ እየጠጣን እንጠብቀው” ቢልም ጆሮ አልሰጠነውም ነበር ብሏል ጌታቸው በፀፀት፡፡ እየበረረ የነበረው ባጃጅ የበለጠ ፍጥነቱን ሲጨምር “አንተ ቀስ በል! ቀስ በል! ሞተር መጣ፤” እያለው ሞተሩ የተሳፈሩበትን ባጃጅ በሀይል ገጨው፡፡
አደጋው የተከሰተው በግምት ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ እንደሆነ ጌታቸው ተናግሯል፡፡
“ከዚያ በኋላ እኔ ራሴን እንደመሳት አድርጎኝ ስለነበር፣ ብዙም የሆነውን አላውቅም፤ ሰዎች ሊያነሱኝ ሲሞክሩ ግን አመናጭቃቸው ነበር” ሲል በወቅቱ የተፈጠረውን አሰቃቂ አደጋ ገልጿል፡፡ ሰዎች በሌላ ባጃጅ አሳፍረው አዳሬ ወደተባለ ሆስፒታል ሲወስዷቸው፣ አንድ እጁ መጎዳቱን ልብ እንዳለ የሚናገረው ጌታቸው፤ ስራ አስኪያጁ ሚሊዮን ደግሞ ደረቱ ላይ እንደተጐዳ አወቀ፤ የኤፍሬም ጉዳት ግን እጅግ ዘግናኝ ነበር ብሏል፡፡
“ኤፍሬም በደረሰበት አደጋ ከወገቡ በታች ሰውነቱን ማዘዝ አይችልም፤ የማጅራቱ ሰባተኛው አከርካሪ አጥንት ተሰብሯል” መባሉን ስሰማ ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ” በማለት አስረድቷል፡፡
ከአዳሬ ሆስፒታል ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ለጌታቸውና ለሚሊዮን የመጀመሪያ እርዳታ ሲደረግላቸው፣ በኤፍሬም መጎዳት የተደናገጡት የሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ዶክተሮች፤ ልጁ በአስቸኳይ አዲስ አበባ መሄድና ኮሪያ ሆስፒታል መግባት እንዳለበት ገልፀው፤ አንገቱ እንዳይነቃነቅ በጀሶ ካሰሩት በኋላ፣ በሆስፒታሉ አምቡላንስ ወደ አዲስ አበባ ኮሪያ ሆስፒታል ልከውታል፡፡
“አሁን ጥፋተኝነትና ፀፀት የሚሰማኝ የኤፍሬምን ስድስተኛ የስሜት ህዋስ መረዳትና ማንበብ ባለመቻሌ ነው” የሚለው ጌታቸው፤ “ከአንድም ሁለቴና ሶስቴ ወደ ፒያሳ የምናደርገውን ጉዞ ለመሰረዝና እኛን ለማሳመን ጥረት አድርጎ ነበር” ብሏል፡፡
ረቡዕ አመሻሽ ላይ ኮሪያ ሆስፒታል የገባው ጋዜጠኛ ኤፍሬም፤ ከወገቡ በታች ሰውነቱን ማዘዝም ሆነ ሽንቱን መቆጣጠር አይችልም ነበር፡፡ ከትላንት በስቲያ የቀዶ ህክም የተደረገለት ሲሆን፤ ከሌላ የሰውነቱ አካል አጥንት ተወስዶ አከርካሪው ላይ በተሰበረው አጥንት ምትክ ቢገባለትም ሰውነቱን የማዘዝም ሆነ ከዚህ በኋላ ቆሞ የመሄድ ተስፋ እንደሌለው ሀኪሞቹ ተናግረው የነበረ ቢሆንም እንደገና ሰፋ ያለ ቀዶ ህክምና ካደረገ በኋላ ከወገቡ በታችና እግሩ አካባቢ መስማት ጀምሯል፡፡ ለቀጣይ ህክምና 60ሺህ ብር መጠየቁንም ጋዜጠኛ ጌታቸው ገልጿል፡፡
ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን ጋዜጠኛ ለማትረፍ ሆስፒታሉ እንዲያሲዙ የጠየቃቸውን ብር በአፋጣኝ ለማግኘት ፈተና እንደነበር የሚናገረው ጌታቸው፤ “ኢትዮ-ምህዳር” አዲስ ጋዜጣ በመሆኑና ብዙ ስላልተቋቋምን ተቸግሬ ነበር ብሏል - ጋዜጠኛ ጌታቸው ሀሙስ 11 ሰዓት ላይ ከበርካታ ጋዜጠኞች ጋር ባደረገው ውይይት፡፡ “ጋዜጠኞች ህይወታችን ለአደጋ የተጋለጠ ነው፤ ራሳችንን ከጥቃት ለመከላከል፣ በአደጋ ጊዜ ለመረዳዳትም ሆነ ለመሰል ጉዳዮች የሚያገናኘን አንድም መድረክ የለም” ሲል ለሙያ አጋሮቹ ንግግር ያደረገው ጋዜጠኛው፤ በሌሎቻችን ላይ አደጋ ላለማድረሱ ዋስትና ስለሌለን በቀጣይ ምን ብናደርግ ይሻላል ሲል ጠይቋል፡፡
በቅርቡ ከስደት የተመለሰውን ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ከጉዳቱ እንዲያገገም ለመመኘት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡ ስብሰባውን ያስተባበሩት የ “ነጋድራስ” ጋዜጣ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት አንጋፋው ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ ናቸው፡፡
የ27 አመቱ ጋዜጠኛ ኤፍሬም፤ ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ በ1999 ዓ.ም በጆርናሊዝምና ኮሙዩኒኬሽን ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ሥራ የጀመረው በነጋድራስ ጋዜጣ ላይ ነበር፡፡ ከጋዜጠኛ ጌታቸው ንግግር በኋላ ጋዜጠኞች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡
“በአሁኑ ሰዓት ቅድሚያ ሰጥተን መረባረብ ያለብን ጋዜጠኛ ኤፍሬም ላይ ነው” ያሉት ጋዜጠኞቹ፤ ውጭ አገር ሄዶ መታከም ካለበት፣ባለበትም ሆኖ የሚታከምበትና የሚድንበት መንገድ ካለ ሁላችንም በየፊናችን ገንዘብ በማሰባሰብና ስፖንሰር በማፈላለግ መትጋት አለብን” በማለት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
በአደጋው መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁና ማሊዮን ደግነው በፍ/ቤቱ ቀጠሮ መሰረት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ፤ ያቀረቡትን አምስት የክስ መቃወሚያዎች ውድቅ በማድረግ ተከራከሩ በሚል ለህዳር 10 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አደጋውን ያደረሱት የባጃጅና የሞተር ሳይክል ሹፌሮች ዘለው እንደወረዱና ተይዘው ፖሊስ ጣቢያ ገብተው እንደነበረ የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት ጉዳዩን ወደያዙት የከተማዋ ትራፊክ ፖሊሶች ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
Source: Addis Admass
No comments: