እኛ ተርፈናል፤ እዛ ላሉት ድረሱላቸው
ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተገደው እየተደፈሩ ነው !
እስር ቤት አንዲት ነፍሰ ጡር ሞታብናለች - የስደት ተመላሾች
ሳኡዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ወደ አገሯ የገቡ ስደተኞችን በሃይል ማስወጣት
ከጀመረች ሁለተኛ ሳምንቷን ያስቆጠረች ሲሆን ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደአገራቸው የመመለስ ዘመቻው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ዜጐችን ከሳኡዲ ለማምጣት ባለፈው ሳምንት በቀን ሰባት በረራዎች ይደረጉ እንደነበር ያስታወሱት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በዚህኛው ሳምንት በቀን 12 በረራዎች እየተደረጉ ዜጐችን ማምጣቱ እንደቀጠለና እስከትላንት ድረስ ከ19ሺ በላይ ዜጐች መመለሳቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተገደው እየተደፈሩ ነው !
እስር ቤት አንዲት ነፍሰ ጡር ሞታብናለች - የስደት ተመላሾች
ሳኡዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ወደ አገሯ የገቡ ስደተኞችን በሃይል ማስወጣት
የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በቦሌ አየር ማረፍያ ተገኝተው ተመላሾቹን ያነጋገሩ ሲሆን፤ ስደተኞቹን ለማቋቋም ከክልል መንግስታት ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ሁለት ሌሎች ቦታዎች ለስደተኞቹ በጊዜያዊ መጠለያነት እያገለገሉ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ከሶስት የሳኡዲ ተመላሾቹ ጋር ባደረገችው ቆይታ የስደት መከራቸውን እንደሚከተለው ነግረዋታል፡፡
“ኤምባሲያችን አይሰማም እንጂ ደጋግመን ነግረናል”
ራውዳ ጀማል ትባላለች፡፡ የሃያ ዓመት ወጣት ናት፡፡ ስለራስዋም ሆነ በሳኡዲ ስላሉ ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ሁኔታ ስታወራ እያለቀሰችና እየተወራጨች ነው፡፡ ለማነጋገር ስቀርባት “ወንድ ከሆናችሁ ጋዜጠኞች ነን፣ የህዝብ አፍ ነን ካላችሁ፤ እዚህ ተቀምጣችሁ፣ “ሁለት ሰው ሞተ” እያላችሁ ከምታቅራሩ ሳኡዲ ሂዱና በየቀኑ ሁለት ሶስት ሰው የሚሞትበትን እልቂት ተመልከቱ፣ “ሰዎቹን ምን እየሰራችሁ ነው?” ብላችሁም ጠይቁልን” አለችኝ። መቅረፀ ድምፄን ሶስት አራት ጊዜ ያስጠፋችኝ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ ሆነችልኝ፡፡
ስንት ዓመት ቆይተሽ መምጣትሽ ነው?
ከሁለት ዓመት በኋላ ነው የመጣሁት፡፡ እስከ አስረኛ ክፍል የተማርኩት አዲስ አበባ ቢሆንም፤ የኮምቦልቻ ልጅ ነኝ፡፡
እንዴት ነበር የሄድሽው?
በፓስፖርት… በኮንትራት ነበር የሄድኩት … ካላስ! የሰውየው ልጆች ግን “የማይሆን” ፊልም ተመልከቺ እያሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ሲመረኝ ጠፍቼ ወጣሁ፡፡ ከዚያም ከጓደኞቼ ጋር በነፃነት ቤት ተከራይተን እየኖርን፣ በ1800 ሪያል ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ቤተሰቤንም ገንዘብ እየላኩ እረዳ ነበር፡፡
ወደ አገርሽ እንዴት ተመለስሽ?
ውጡ ሲባል… ረብሻ ሲነሳ.. ጓደኞቻችን ሲሞቱ.. ሲደፈሩብን.. ‘ድሮም ስደተኛ ክብር የለውም’ ብዬ ተመልሼ መጣሁ..ከሚገሉኝ ከሚያበለሻሹኝ ብዬ እጄን ሰጠሁ፡፡ ብዙ ኢትዮጵውያኖች ችግር ላይ ናቸው.. እባካችሁ ድረሱላቸው፡፡ ብርዱም ፀሃዩም ሲፈራረቅባቸው.. ያሳዝናሉ፡፡ ብዙ ያልመጡ አሉ፤ መምጣት እየፈለጉ፡፡ ስቃይ ላይ ናቸው፡፡ እኔ አሁን አስራ ሶስት ቀን ታስሬ ነው የመጣሁት፡፡
እስቲ ስለ እስሩ ንገሪኝ …
ሁለት ቀን ያለ ምግብ ያለ ውሃ ነው የታሰርነው። ከዛ በኋላ ግን ጥሩ ምግብ ሰጥተውናል፣ ጥሩ መኝታም አግኝተናል፡፡ ብዙዎቹ ግን ከእኛ የባሰ ችግር ላይ ናቸው፡፡ መጠለያ ያላገኙ አሉ…ኤምባሲያችንም አይሰማም እንጂ ስንት ጊዜ ደውለን ተናግረናል መሰለሽ፡፡ ግን የሚሰማ የለም፡፡
ከአገራችን ውጡ ካሉ በኋላ ትዕግስት ያጡና መልሰው ይዩዙናል፡፡ በዛን ጊዜ አበሻው፣ ሻንዛ/ጩቤ ይመዛል፡፡ ፖሊስ ራሱን ለማዳን ይተኩሳል። እኔ እንደውም ደህና ነኝ፤ እዛ ላሉት ድረሱላቸው። በምድረ ዱርዬ እየተደፈሩ ነው ያሉት /ለቅሶ/ ስንት ህፃናት አሉ የሚሞቱ፣ የሚታመሙ፡፡ ስንመጣ ደሞ፤ ሻንጣ አትያዙ ተብለን ተመናጭቀን…በጥፊ ተመትተን..መከራችንን በልተናል፡፡
ወንዶችና ሴቶች ለብቻ ነበር የተቀመጣችሁት?
የተቀመጣችሁት አትበይ! የታሰራችሁት በይ፡፡ … የሴት እስር ቤት ለብቻው ነው በሴቶችና በህፃናት ለቅሶ የተሞላ ነው፡፡ እኔ ራሴ ስድስት ያበዱ ሴቶችን ይዤ መጥቻለሁ…/ለቅሶ/
አሁን ቤተሰብ እየጠበቅሽ ነው?
ነበረ ግን ሻንጣዬ ጠፋብኝ፡፡ በርግጥ ጤነኛ ሆኖ መምጣትም ቀላል አይደለም፡፡ እዛ ያሉትን ጥለናቸው ስንመጣ እያለቀስን ነው፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ አንድ እርጉዝ ሞታብናለች፡፡ እዛው እስር ቤት እያለን ምጥዋ መጣ፤ ግን የህክምና እርዳታ ባለማግኘትዋ ሞተች፡፡
እስር ቤት ያሉት ምን ያህል ይሆናሉ?
ሰማኒያ ክፍል አለ..በየክፍሉ ስልሳ አምስት ስልሳ አምስት ሰው ነው ያለው፡፡ መካሲመሺ እስር ቤት ይባላል፡፡ የወንድና የሴት እስር ቤት የተራራቀ ነው፡፡ በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ በመኪና እንጂ በእግር አይሞከርም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማው ያለው እስር ቤት ሞልቶ የመዝናኛና የስብሰባ አዳራሹን ሁሉ እስር ቤት አድርገውታል፡፡ የተደፈሩት የሞቱት..ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዷን እርጉዝ ለሶስት ሲደፍሯት ሞታለች፡፡
የሌሎች አገር ስደተኞችም እየወጡ ነው ተብሏል…
አዎ፡፡ ኢትዮጵያዊው ከበደሉ ብዛት የተነሳ እየተናነቀው እኮ ነው ግጭቱ የሚከረው፡፡ ሚስቱንኧ እህቱን ከእጁ መንትፈው ሊወስዱበት ሲሉ ነው ጦርነት የሚነሳው፡፡ አበሻ ወንድ እየሞተ ያለው ‹‹ሴቶቻችንን አትንኩብን..›› ስለሚል እኮ ነው፡፡ ኤምባሲው ሊደርስላቸው ይገባል፡፡
“የሁለት ሰው መርዶ ይዤ መጥቻለሁ”
ስምሽ ማን ነው?
ፀጋ ኪዳኔ ገብረኪዳን
ምን እየጠበቅሽ ነው?
ዘመድ አለችኝ አዲስ አበባ የምትኖር፤ እስዋ እስክትመጣ እየጠበቅሁ ነው፡፡
ሳኡዲ ምን ያህል ጊዜ ቆየሽ?
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ነው ከሪያድ/ሞንፋ የመጣሁት፡፡ ከኢትዮጵያ ስሄድ በኮንትራት ቢሆንም በባህር ከሄዱት ስደተኞች የተለየ ክብር አላገኘሁም፡፡ ጭቅጭቅ፣ ስድብና ድብደባ ሲበዛብኝ ከተቀጠርኩበት ቤት በስምንተኛ ወሬ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ የሄድኩት ለአንድ ስራ ብቻ ተዋውዬ ነበር። የምተኛው ግን ከሁለት ሰዓት አይበልጥም ነበር፡፡ ሥራ ብቻ ነው 24 ሰዓት!
እስቲ ስለደረሰብሽ ችግር በዝርዝር ንገሪኝ..
በ700 ሪያድ ተቀጥሬ ነበር ከዚህ የሄድኩት፡፡ አሰሪዬ ቤት አራት ትላልቅ ወንድ ልጆች አሉዋት። የእህትዋ ልጆችም እዚያው ነው የሚኖሩት፡፡ ‹‹ወሲብ ካልፈፀምን..›› ብለው ያስቸግራሉ፡፡ በጣም ተሰቃየሁ፡፡ ከአቅሜ በላይ … ለህይወቴ በጣም አስፈሪ….ሲሆንብኝ ወጣሁ፡፡
ከአቅሜ በላይ ስትይ …
ልጆቹ ወሲብ ካልፈፀምን ብለው አሻፈረኝ ስላቸው፣ “በቢላ እናርድሻለን” እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ እምነቴን እንድቀይር ሁሉ ይፈልጋሉ። አፈር ድሜ በላሁ፡፡ ሰርቼ ለፍቼ … በዚያ ላይ ነፃነት አልነበረኝም፡፡ ወገቤ፣ ዓይኔ ታመመ፡፡ እነሱ እኮ ሃያ አራት ሰዓት እየበሉ እየጠጡ ነው፡፡ በዚያ ላይ በእጅሽ ላይ ስልክ ማየት አይፈልጉም፡፡ ሁሉ ነገር ሲያንገፈግፈኝ ሁለት ወር የሰራሁበትን ገንዘብ ጥዬ ወጣሁ፡፡ ከዛ ኤጀንሲው ለሌላ ሰው ሸጠኝ፤ በአስር ሺህ ሪያድ፡፡ እዚያም ግን አልተመቸኝም። ስራው ሃያ አራት ሰዓት ነበር፡፡ አምስት ሰው እንኳን የማይችለው ስራ ነበር፡፡ አንድ ኩንታል ሊጥ አብኩቼ፣ ለሱቅ የሚሸጡት ብስኩት ጠብሼ፣ ሰባት መቶ ሪያል ነበር የሚከፈለኝ፡፡ ሁለት ወር ሙሉ እንደምንም ድምጼን አጥፍቼ ሰራሁ… በእንቅልፍ እጦት ልወድቅ እየተንገታገትኩ፡፡ እፊታቸው ላይ ግን ደስተኛ እመስል ነበር፡፡ ሰውነቴ እየመነመነ መጣ፡፡ ይሄኔ ድጋሚ ለመጥፋት ተዘጋጀሁ፡፡
“ለሌላ ሰው ሸጠኝ” ያልሽው … ኢትዮጵያዊ ነው?
/እንባዋ እየፈሰሰ/አረብ ነው፡፡ ወደ ሳኡዲ ከላከኝ ኤጄንሲ ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ የረመዳን ጊዜ ደግሞ ሱቃቸው ወሰዱኝ፤ የአንድ ሰዓት መንገድ ተጉዞ ሌላ ቤት አላቸው፡፡ እዛ ይዘውኝ ሲሄዱ ስራ ይቀልልኛል ብዬ ነበር፡፡ … ግን የባሰ ሆነብኝ፡፡ ለካ ጓደኞቻችን ወደው አይደለም ራሳቸውን የሚያጠፉት፤ አብደው ጨርቃቸውን ጥለው በየጎዳውና የወጡትና መንገዱ የወደቁት ... የወገብና የአእምሮ በሽተኞች የሆኑት? “ምነው እናቴ ስትወልጅኝ በመሃፀንሽ ውስጥ ደም ሆኜ በቀረሁ? እናቴ እባክሽ መልሰሽ ዋጪኝ” አልኩኝ፡፡ ራሴንና ቤተሰቤን ልረዳ ስንገታገት ከፊታቸው ድፍት ብል እኮ … እንደሰው ከቆጠሩኝ ... ሬሳዬን ለእናቴ ይልኩላት ይሆናል፡፡ ያለዚያ ግን የሀገራቸው መንግስት አውጥቶ ይቀብረኛል፡፡
ከዚያ ሁሉ በፊት ጠፍቼ መውጣት እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ አንድ ቀን ረመዳን ካፈጠሩ በኋላ ቤተሰቡ ተሰብስቦ ሊዝናኑ ወጡ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ቶሎ ብዬ የሴትየዋን ሙሉ ልብስ ለብሼ፣ ሽፍንፍን ብዬ ወጣሁ፡፡
ሻንጣ ምናምን ሳትይዢ?
ባዶ እጄን ነው የወጣሁት፡፡ የሰራሁበት ገንዘብ እንኳን በእጄ የለም፡፡ በቃ ዝም ብዬ ወጣሁ፡፡ ፓኪስታናዊ የታክሲ ሾፌር አገኘሁ፡፡ ‹‹ምን ሆንሽ?›› ብሎ ሲጠይቀኝ በዝርዝር ነገርኩት፤ አዘነ፡፡ ‹‹ሪያድ የሀበሻ ሃገር ነው፤ ብዙ ኢትዮጵያዊ አለ›› ብሎ እዛ (በነፃ) ወሰደኝ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን አገኘሁ፡፡
እዚያ መኖር ጀመርሽ ማለት ነው?
ሳያቸው በጣም ነው ያለቀስኩት፡፡ አገሬ የገባሁ ይመስል..መሬት ሁሉ ስሚያለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ በባህር (በህገወጥ መንገድ) የመጡ ሴቶች ነበሩ። ከእነሱ ጋር አንድ ቤት በስድስት መቶ ሪያድ ለስድስት ወር ተከራይተን አብረን እየኖርን እንሰራ ጀመር፡፡
ቤቱን ለስንት ተከራያችሁ?
አስር ነበርን፡፡ ሁለት ወር እንደሰራሁ ግን በአካባቢው ግጭት ተነሳ፡፡ እግሬ አውጪኝ ብለን በየፊናችን ተበታተንን፡፡
ምን ዓይነት ግጭት?
መንግስት የሌለበት አገር ይመስል ጐረምሶች በር እያንኳኩ በሽጉጥ፣ በካራ፣ ሰው መግደል ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ‹‹እጃችንን እንስጥ›› ብለን ተማከርን፡፡ ሌላው ችግር ፖሊስ፤ ትዳር መስርተው የሚኖሩትን የአበሻ ወንዶች እየወሰደ፣ ሴቶችን ለብቻቸው ይተዋቸው ነበር፡፡ በቤቱ ወንድ አለመኖሩን የተገነዘበ የአገሩ ዱርዬዎች (እንኳን ለአበሻው ለመንግስትም ልባቸው ያበጠ ነው) ሴትዋን ለአራትና ለአምስት እየሆኑ መድፈር ያዙ፡፡ ከእኛ ጎን የነበሩትን ሲያሰቃይዋቸው አይተናል፡፡ ወንዶቹን ፖሊስ ሲወስዳቸው ጎረምሶቹ ተከትለው ይገቡና ሴቶቹን መጫወቻ ያደርጓቸዋል/ለቅሶ/፡፡ አንድ ያየሁትን ልንገርሽ../ረጅም ትንፋሽ/እነዚህ ጐረምሶች…ሶስት ሴቶች ያሉበት ክፍል ውስጥ ገብተው ለሰባት ደፈሯቸው፡፡ /ማውራት አልቻለችም፤ ሳግና እንባዋ እያቋረጣት/..ከሶስቱ አንዷ የሰባት ወር ነፍሰጡር ነበረች፤ ሲገናኝዋት ሞተች፡፡ አንዷን ደግሞ ለሰባት ደፈሯትና ገድለው ጥለዋት ሊወጡ ሲሉ ሽርጣ/ፖሊስ መጣ፡፡ ከፖሊስ ጋር ተኩስ ገጥመው እርስ በርስ ተገዳደሉ፡፡ የሀበሻ ወንድ ከእህቱ ወይንም ከሚስቱ ሊለዩት ሲመጡ አልለይም ይልና ይገደላል፤ ይደበደባል … በቃ እልቂት ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ ብለሽ ካራ ቆሬ እንደምትይው..ሪያድ ብለሽ ሞንፋ የሚባል አካባቢ በርካታ አበሾች ይኖራሉ፡፡ እኔ እንኳን የማውቀው … ከአምስት በላይ ሴቶች እንደተገደሉ ነው፡፡ መላ አካላቸውን ቆራርጠው ነው የጣሏቸው፡፡ ግን ይሄ ሁሉ መከራ ምን አድርገን ነው?
አንቺ እንዴት መጣሽ ወደ አገርሽ?
እጄን ሰጠኋ፡፡ አሰሪዬ ‹‹የት ልትሄጂ ነው?›› ብላ ስትጠይቀኝ፡፡ ‹‹አንድ ጓደኛዬ ልትወልድ ነውና ልጠይቃት ..›› ብዬ የሰራሁበትንም ሳልቀበል ወጣሁ፡፡ ምክንያቱም ብትገለኝስ ብዬ ፈራሁ፡፡ አብዛኛው አበሻ ከስራ ወደቤቱ ሲሄድ እየተያዘ ነው የሚመጣው፡፡ የሰራበትን የለፋበትን ሳይዝ ባዶ እጁን፡፡ እና እኛም ነገሩ ስላስፈራን እጃችንን ሰጠን። በቃ እኔም ወደ እዚህ መጣሁ፡፡
ዛሬ ላይ ሆነሽ ስታስቢው ወደዛ በመሄድሽ ምን ይሰማሻል?
መጀመሪያ ከዚህ ስሄድ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፤ የራሴንና የቤተሰቤን ህይወት ላሻሽል እንደሆነ ተስፋ በማድረግ፡፡ ከዛ በኋላ ግን ከስራው ብዛት የተነሳ ከጥቅም ውጪ ልሆን ነው ብዬ እጅግ አምርሬ አለቅስ ነበር፡፡ በጣም ስጋት ያዘኝ፡፡ ግን ከሞት ተርፌ ወደዚህ ስመጣ አምላኬን አመሰገንኩ፡፡
ቤተሰብሽ መምጣትሽን አውቀዋል?
አላወቁም፡፡ ምን እያሰቡ ይሆን? ይሄን ሁሉ ነገር እየሰሙ፡፡ እናቴ መንገድ መንገድ እያየች ይሆናል፡፡ ደሞ ከእኛ አካባቢ ልጆች ብዙ የሞቱ አሉ፡፡..አሁን እኔ ራሴ የሁለት ሰው መርዶ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ እናቴም ሰው ሲመጣ ‹‹ልጄን አይታችኋል?›› ትል ይሆናል፡፡ እኔስ መጣሁ..በረሃ ላይ ተደፍተው ለመምጣት ወረፋ እየተጠባበቁ ያሉ ህጻናትና ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ እዚህ የመጣነው እኮ ግማሽ አንሞላም፡፡ በሳኡዲ የኢትዮጵያውያን እንባ ያሳዝንሻል፡፡ ብዙዎቹ በሃዘን ላይ ናቸው፤ ድረሱላቸው፡፡
“ሰባት ያበዱ ሴቶችን አይቻለሁ”
ስምሽን ንገሪኝ..?
ሀያት አህመድ
እስቲ አካሄድሽን ንገሪኝ …
ከደሴ ነው በኤጀንሲ የሄድኩት፡፡ የምሰራው በጠለብ/በህጋዊ መንገድ ነበር፡፡ ሰዎቹ ሳይመቹኝ ሲቀሩ..ብዙ ጓደኞቻችን ችግር ሲደርስባቸው ሳይ፣ ስልካችንን ቀምተው ቤተሰቦቻችን በሃሳብ ሲያልቁ፣ እኔም ነገሩ ስላልተመቸኝ ጥዬ ጠፋሁ፡፡ ከዛም በሃጂና ኡምራ የሄድኩ አስመስዬ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡
በጠለብ ስንት ጊዜ ሰራሽ?
ሶስት ወር ነው የሰራሁት፡፡
አሰሪዎችስ ቤት የሚደርስብሽ ችግር ምን ነበር?
በቤት ውስጥ ያሉ ወንዶች ያስቸግሩኝ ነበር፤ አስገድዶ ለመድፈር ይተናነቁኛል፡፡ አሰሪዬ በስራዬ አትደሰትም፣ ያጠብኩትን ነገር እንደገና እጠቢ ትለኛለች፡፡
“የኢትዮጵያ ሰራተኞች ሞያ የላቸውም፣ “ሞዴስ እንኳን በአግባቡ መጠቀም አይችሉም፣ በዚያ ላይ ወንዶቻችንን ያባልጋሉ” የሚል ክስ ከሳኡዲ ሴቶች ይሰማል፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?
በጭራሽ! እኛ ደልቶን ይሄን ልናስብ? አንገታችንን ቀና አድርገን እንኳን ለመሄድ እንቸገራለን እኮ፡፡ እዛ ቦታ ላይ እኛን ብታይ ኢትዮጵያዊነት ያስጠላሻል፡፡ አለባበሳችን ምንድን ነው፣ ሁኔታችንስ፣ ኑሮዋችንስ..እኛ የእነሱን ባል የምናባልግ ምን አምሮብን፣ እንዴት ሆነን ነው? እኛን እኮ ይጠየፉናል፡፡ በምን አንገታችን ቀና ብለን ነው የእነሱን ወንዶች የምናባልገው? እኛ እኮ ለህይወታችን እየሰጋን ነው… እያንዳንዷን ቀን የምናሳልፈው፡፡ በርግጥ የገጠር ልጆችም ይሄዳሉ። እንግዲህ በንፅህና የሚታሙት እነሱ ናቸው፡፡ ግን ስንቱን አእምሮውን አሳጡት…. ወይኔ!!..አሁን ስንመጣ እንኳን ጅዳ ኤርፖርት ውስጥ ሰባት ያበዱ ልጆችን አይቻለሁ፡፡ ‹‹ይዛችኋቸው ሂዱ›› ሲሉን ነበር፤ እንዴት አድርገን እንይዛቸዋለን? ጥለናቸው ነው የመጣን፡፡ አይ ዜጎቻችን! እየቀወሱ፣ እየተደፈሩ፣ እየተደበደቡ፣ እየተጣሉ ነው ሜዳ ላይ ….ተመልካች አጥተው፡፡
ጣትሽ ላይ የጋብቻ ቀለበት አያለሁ … ባለትዳር ነሽ?
ፈትቻለሁ፡፡ የአስር ዓመትና የስምንት ዓመት ልጆች አሉኝ፡፡ እነሱን ላሳድግ ብዬ ነው በሰው አገር የተንገላታሁት፡፡ ገንዘብ እልክ ነበር፡፡ ሆኖም እኔም አልተለወጥኩም፤ ለልጆቼም አልሞላልኝም፡፡ አንድ ጊዜ ሆድ ብሶኝ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር፡፡ ታውቂያለሽ… ልጆቼ በዓይን በዓይኔ መጡብኝና … ከድርጊቴ ታቀብኩ፡፡
አይኔ እንቅልፍ ካጣ ስንት ጊዜው ሆነ መሰለሽ… አይኔ ስር ጥቁር ብሎ የምታይው፣ የበለዘ የሚመስለው እኮ በእንቅልፍ እጦት የተፈጠረብኝ ነው፡፡ ጀርባዬን ያመኛል፡፡ ብዙ ሰዓት የምቆምበት እግሬንም እጅግ ታምሚያለሁ፡፡ አሁን ለትንሽ ጊዜ ማገገም አለብኝ፡፡
ጂዳ ኤርፖርት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚጠባበቁ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ ይባላል…?
በጣም ብዙ እንጂ! ‘ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገር ነቅሎ ነው እንዴ የወጣው ብዬ ተደንቄያለሁ፡፡ በጣም ያዘንኩት ግን ወደዚህ ስመጣ ኤርፖርት ሰባት ያበዱ ልጆች ስመለከት ነው፡፡ እዛ ያለው ኤምባሲያችን እንዴት ወደ አገራቸው አይመልሳቸውም? ‹‹እህ›› ብሎ ችግራቸውን የሚያደምጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ እስቲ አስቢው…ሰባት ሴቶች አብደው አይቻለሁ፤ በአይኔ በብረቱ፡፡ አንዷ ልጅዋ ሞታባት (በረሃብ ነው) የቀወሰችው፡፡ ስድስቱ ደግሞ በስራ ቦታቸው ቀውሰው፣ አሰሪዎቻቸው ናቸው አምጥተው የጣልዋቸው፡፡ የምናየው ነገር ሁሉ ለዓይን ይዘገንናል፡፡
ከዕረፍት በኋላ ምን ልትሰሪ አቀድሽ…?
አሁን ጤንነት አይሰማኝም፤ ካገገምኩ በኋላ እንግዲህ … እንጃ ምን እንደምሰራ፡፡ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ተቀምጬ ነው የመጣሁት፡፡ ከአስርና አስራ አምስት ዓመት በላይ የኖሩትም ‹‹ምንድነው የምንሰራው..›› የሚል ነው ጥያቄያቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ኖረው ቢመጡም ምንም የያዙት ነገር የላቸውም፡፡ በጣም ያሳሰበኝ እሱ ነው፡፡
ከአሁን በኋላ ወደ ሳኡዲ የመመለስ ሃሳብ አለሽ?
አላህ ያውቃል፡፡
Source: Addis Admass
No comments: