ኢህአዴግ ስለምን ይጮኻል?

(ተመስገን ደሳለኝ)
በረዥሙ የኢትዮጵያ ዘመነ መንግስት ታሪክ፣ በአስተዳደሩ ተመስግኖ በክብር የተሸኘ ገዥ ስለመኖሩ የሚያወሳ አንድም ድርሳን ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሁሉም መንግስታት የተወገዱት በአመፅ አሊያም በተፈጥሮ ሞት ነውና፡፡ በ1983 ዓ.ም ወርሃ ግንቦት በጠብ-መንጃ ኃይል ሥልጣን የተቆናጠጠው ኢህአዴግ-መራሹ መንግስትም ቢሆን፣ በቀድሞዎቹ ገዥዎች ‹የብረት ጫማ› ውስጥ ተከልሎና ተደላድሎ ዕለተ-ስንብቱን በመጠባበቅ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ዕ
ለተ-ስንብቱ መቃረቡን የሚጠቁመው ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልክ እንደ ደርግ የመጨረሻዎቹ ወራት ሁሉ፣ ግንባሩና አጋር ፓርቲዎቹ ለየት ባለ መልኩ በራሳቸውና በሹማምንቶቻቸው ላይ በአደባባይ የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት መጀመራቸው ነው፡፡ የዚህ ፅሁፍ ተጠየቅም ይህ ነውና ተጨባጭ እውነታውን ለማብራራት በቂ የሆኑ አስረጂዎችን በአዲስ መስመር በዝርዝር ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡

አስረጅ አንድ
በ2005 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ዓመታዊ ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ባቀረበበት ወቅት ከአገዛዙ የተለየ ድምፅ የተሰማው እንደ ወትሮው ሁሉ፣ በም/ቤቱ ተቃዋሚ ፓርቲን ከወከለው ‹አንድ ለእናቱ› አቶ ግርማ ሰይፉ ብቻ አይደለም፤ ኢህአዴግ በአምሳሉ ከፈጠራቸው አጋር ፓርቲዎችም ጭምር እንጂ፡፡
በዕለቱ ሚንስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በመንግስት በመገንባት ላይ ያለውን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን አስመልክቶ ‹አክራሪ› ካላቸው መነኮሳትና ‹ጥቂት› መዕምናን ‹ግርግር የመፍጠር ሙከራ› ባለፈ የተከሰተ የጎላ ችግር አለመኖሩን በሪፖርቱ መጥቀሱን ተከትሎ የአፋር ክልል ተወካዩ በአጋርነት ያነበረውን ስርዓት እንዲህ ሲል ነበር የተቸው፡-
‹‹ለፋብሪካው ግንባታ ተብሎ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንዲሰፍሩ የተደረገበት ቦታ ውሃና መብራት ያሌለው ነው፤ ይህ ለምን ሆነ? ብለን ስንጠይቅ ‹ድሮም የነበሩበት ቦታ መብራትና ውሃ የለውም› በማለት ይመልሱልናል፡፡ በአጠቃላይ በአፋርና አካባቢው በሪፖርቱ ያልተካተቱ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡››
የሶማሌ ክልል ተወካይም በበኩሉ በዚሁ ዕለት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ‹የሰብዓዊ መብት አያያዝ›ን በተመለከተ አድበስብሶ ማለፉን የተቃወመው በሚከተለው አኳኋን ነበር፡-
‹‹በእኛ አካባቢ የሰብዓዊ መብት አይከበርም፤ ሰዎች ይገደላሉ፤ ይታሰራሉ፤ ይደበደባሉ፡፡›› (በርግጥ በመልከዓ ምድር ለአካባቢው ከማንም በላይ የሚቀርበው የሀረሪው ተወካይ ብዙውን ጊዜ በምክር ቤቱ ስለማይገኝ በዕለቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ቅሬታ ይኑረው ድጋፍ ማወቅ አልተቻለም)
አስረጅ ሁለት
ጥቅምት 22 ቀን 2006 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቦይ ስብሃት ነጋ፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለውጭ፣ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የዓመቱን በጀት ለማፀደቅ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ጋር ተግባብተው መስራት አለመቻላቸውን በግልፅ ተናግረዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የተመሰረተበት አቢይ ዓላማ ‹‹የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሚያስገኘው ውጤት ዙሪያ ጥልቅ ጥናት ለማካሄድ›› መሆኑ ቢታወቅም፣ ውጭ ጉዳይ ‹‹ይህንን አጥኑልን›› ብሎም ሆነ አቅጣጫ አሳይቶ እንደማያውቅ ከረር ባለ ድምፅ አስረድተዋል፡፡
መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠር ዓመታዊ በጀት የበጀተለትን ይህንን ተቋም በኃላፊነት እንዲያስተዳድሩ በዶ/ር ክንፈ አብርሃ ህልፈት ማግስት የተሾሙት አቦይ ስብሃት፣ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ፡- ‹‹ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ የተቀመጠለትን ዓላማ ከማስፈፀም አኳያ ቀደም ሲልም አልነበረም፤ አሁንም የለም›› ማለታቸው የሚያመላክተው የስርዓቱን ዝቅጠት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በአንድ ፓርቲና በተመሳሳይ ርዕዮተ-ዓለም የሚመሩት መንግስታዊ ተቋማትም እንኳ እርስ በእርስ ተግባብተው መስራት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም ጭምር ነው፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
አቦይ ስብሃት በመደምደሚያቸው ላይ ለችግሩ ተጠያቂ አድርገው ያቀረቡት (ምንም እንኳ ምክንያቱን ዘርዝረው ባያብራሩትም) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በራሱ በኢንስቲትዩቱ መካከል ሰፊ ክፍተት መፈጠሩን ነው፡፡ ኢህአዴግ ተቋሙን አዛዥ-ናዛዥ እንዲሆኑበት ለእሳቸው አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት፣ በጀቱ የሚሸፈነው በዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እንደነበረ ይታወሳል (በነገራችን ላይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሓኖም ከሌሎች አክራሪ የህወሓት ታጋዮች የሚለይበት መልካም ጎኖች ቢኖሩትም፣ በ‹ቲውተር ገፁ› የተሰማውን ሃሳብ የማንፀባረቅ ድፍረት ቢኖረውም፣ ከሙስና ጋር ገና እንዳልተላመደ ቢነገርለትም፣ ከሴራ ፖለቲካ የፀዳ፣ ከዘረኝነትም የነፃ ቢሆንም፣ ከ2007ቱ ምርጫ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን ቢወራለትም… ከቁምነገር ይልቅ ወደማፌዙ ያመዘነ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ በመካከለኛው ምስራቅ ምድራዊ ፍዳን እየተቀበሉ ያሉ እህት ወንድሞቻችንን ይታደግልናል ብለን ስንጠብቅ፣ ሰራተኞችን ሰብስቦ ‹ዛሬ… ልዩ… ልዩ… ቀን ነው…፣ ልዩ…› እያለ ሲዘፍን ይውላል፤ ብሔራዊ ዕርቅ ለመፍጠር ብርሃኑ ነጋንና ኦባንግ ሚቶን ይጠራል ብለን ስንጠብቅም አንገብጋቢ ባልሆነው ጉዳይ ገብቶ ኳስ ተጨዋች ሲጠራ ታይቷል)
አስረጅ ሶስት
መቼም አርብ ጥቅምት 22 ቀን 2006 ዓ.ም የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የበጀት ዓመት ዕቅዱን ባቀረበበት ወቅት፣ ተጠባበቂ ዳይሬክተሩ አቶ ኃ/ማርያም አለምሰገድ በባለስልጣናቱ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ማቅረባቸውን ያደመጠ ሰው፣ ሀገሪቱ በገሃድ ከለየላቸው ‹ማፍዎች›ም በከፉ ስግብግብ ሹማምንት መዳፍ ስር መውደቋን ለመረዳት አይቸግረውም፡፡
‹‹አንዳንዱ ባለሥልጣን አስፓልት ይሰራልኝ ይላል፤ ይህንን በቃል ቢሆንም ለጠ/ሚኒስቴር ጽ/ቤት ነግረናል፤ ግማሹ እምነ-በረዱን አንሳልኝ ይላል፤ መፀዳጃ ቤቱ እንዲህ መሆን የለበትም የሚልም አይጠፋም፡፡ የኪራይ ቤቶች ቤት የተሰራው ከሰባ ዓመት በፊት ነው፤ ነገር ግን ዱባይ እንዳዩት አዲስ አይነት ባኞ ቤት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ በግዥ እንጨናነቃለን፤ ይህ ካልተደረገ ያለውን የስልክ ጩኸት ለመግለፅ ይከብዳል፡፡››
ዳይሬክተሩ ከዚሁ ጋር አያይዞ እንደገለፀው ባለስልጣናቱ አንድ ነገር ሲበላሽ ስልክ ደውለው እንደሚያስፈራሩ፣ ቤቱን ለመንግስት እንዲያስረክቡ በሚጠየቁበትም ጊዜ የጦር መሳሪያ ታጥቀው ኤጀንሲው ቢሮ ድረስ በመምጣት በዛቻ እየፎከሩና እየሸለሉ ከህግ በላይ መሆናቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ እጅግ በርካታ መሆኑን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ከዚህ ስርዓት መቼም ቢሆን ታማኝ የሕዝብ አገልጋይ ተቋም ማግኘት እንደማይቻል አስበን በተስፋ መቁረጥ እንድንሞላ የሚያደርገን አሳዛኙ ነገር ደግሞ፣ ኤጀንሲው ይህ አይነቱ ወሮበላነት ከሙስና ጋር ይያዛል በሚል ለኮሚሽኑ ኃላፊዎች ባሳወቀበት ጊዜ የተሰጠውን ምላሽ ስንሰማ ነው፡-
‹‹ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋርም በጋራ ጠንካራ ሥራ ለመስራት እንፈልጋለን፤ ነገር ግን እነርሱንም ስናማክራቸው የራሳቸው የቤት ፍላጎት አላቸው፤ እናም ቤት ይሰጠን፣ ቤቱን በስማችን አድርጉልን እና ሌሎችም ጥያቄዎች እያቀረቡ ነው፡፡ ስለዚህም መጀመሪያ እነርሱም መስመራቸውን ሊያጠሩት ይገባል፡፡››
ጉዳዩን በሕግም ለመፍታት እንዳልተቻለ በሪፖርቱ ላይ የተገለፀው፡- ‹‹ፍርድ ቤትም ቤቱን አንለቅም ከሚሉት ሰዎች በላይ ለእነርሱ እየተከራከረ ነው›› በማለት ነው፡፡
አስረጅ አራት
ብዙ የተወራለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋና አካል ሆኖ በ2002 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመው ‹‹የብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ልማት ኢንስቲትዩት››ንም በተመለከተ ጥቅምት 22 ቀን 2006 ዓ.ም ዳይሬክተሩ አቶ ደሳለኝ ወርቅነህ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ባቀረበበት ወቅት፣ ስራዎቹ ከተጠበቀው በታች ከመሆኑም በላይ የማስፈፀም ብቃት ማነስና የአመራሩ አቅም አስተማማኝ አለመሆኑ እንደ ዋነኛ ችግር ተገልጿል፡፡
ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት ላይም የቀረበው መደምደሚያ ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ እንዲሁም ጥቅምት 27 የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ መንግስት ‹‹ልዩ ድጋፍ አደርግላቸዋለሁ›› ከሚላቸው አፋር፣ ቤንሻንጉል-ጉምዝ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና ሀረሪ ክልሎች ጋር ባደረገው ውይይት፣ በርካታ ችግሮችና ድክመቶች የተጠቀሱበት ከመሆኑም በላይ ኃላፊነቱን መወጣት አለመቻሉ የማያስተባብለው ጥፋት ሆኖ ቀርቦበታል፡፡
ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም የሩብ ዓመት አፈፃፀሞቻቸውን ያቀረቡት ‹‹የህዝብ እንባ ጠባቂ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን››፣ ‹‹የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት››ም በተመሳሳይ መልኩ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ተውስቷል፡፡ በተለይ ማሪታየም ‹‹የስትራቴጂክ ዕቅድ የሌለው፣ የተገልጋይ ቅሬታን የማያስተናግድ፣ የትራንስፖርት ክፍያዎችን በወቅቱ የማይከፍል፣ ክፍት የስራ ቦታዎችን የማይሞላ፣ ዕቃዎችን ከወደብና ተርሚናል በጊዜ እንዲነሱ የማይጥር…›› እና የመሳሰሉት ችግሮች የተጠቀሱበት ሲሆን፤ መስሪያ ቤቱ ያቀረበው ሪፖርትም አሉታዊ ጎኑ እንደሚያመዝን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገምግመዋል፡፡
የሆነው ሆኖ በዕለቱ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በሪፖርታቸው ላይ፡- ‹‹በ2007ቱ ምርጫ ዘመናዊና ልዩ የድምፅ አሰጣጥ ዘዴን በመተግበር ሁሉም ለምርጫ የደረሱ የአገሪቱ ዜጎች ተሳታፊ እንዲሆኑ አደርጋለሁ›› ያሉት በግልፅ ተብራርቶ የቀረበ ባለመሆኑ ምን ለማለት እንደተፈለገ ለመረዳት ያዳግታል (መቼም ‹ኢህአዴግ ጌታ ነው› ከሚሉ አማኝ ሹማምንት አንዱ የሆኑት እኚህ ፕሮፌሰር የሚመሩት ምርጫ ቦርድና ገዥው ፓርቲ ‹ሰምና ወርቅ› ሆነው ከዚህ ቀደም የ‹ድምፅ ካርድ›ን ከኮሮጆ የሚመነትፉበትን አስማታዊ ጥበብ፣ በሚቀጥለው ምርጫ ከመራጭ ኪስ ወደመስረቅ ለማሳደግ እየተጋን ነው ቢሉም አይደንቅም)
አስረጅ አምስት
ጥቅምት 28 ቀን 2006 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ‹‹ሀገራዊ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ማቀጣጠያ መድረክ›› በሚል ርዕስ በተካሄደ ውይይት ላይ ፍትህ፣ ንግድ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ እና የከተማ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መ/ቤቶች-በሚኒስትሮቻቸው፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በዳይሬክተሩ አማካኝነት ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡
በዚህ መድረክ በተለይም በራሱ በፍትህ ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዩ አንደበት የተገለፀው ችግር ‹በሀገሪቱ መንግስት የለም› ወደሚል ጠርዝ ይገፋል፡፡ እነበረከት ስምዖንና አባይ ፀሀዬ መርጠው የሾሙት ሚንስትር ‹‹የፍትህ ስርዓቱ አድሎኛ፣ የማይታመን፣ ቅንነት የጎደለው፣ በትውውቅ የሚሰራ፣ በብሔር የሚያደላ፣ በሙስና የተተበተበ…›› መሆኑን (ያውም እነርሱም ከፊት ወንበር በተኮለኮሉበት አዳራሽ) በግልፅ እየመሰከረ ባለበት ሁኔታ ‹ሀገር እያስተዳደርን ነው› ሊሉ አይችሉም፤ ባይሆን በሀገሪቱ ሀብት ‹ቤተሰቦቻችንንና ዘመድ አዝማዶቻችንን እያስተዳደርንበት ነው› ቢሉን፣ ቢያንስ ለግልፅነታቸው ፅዋችንን ከፍ እናደርግላቸው ነበር፡፡
የፍትህ ሚኒስትሩ በየቦታው በአሰቃቂ ሁኔታ ስለታጎሩ እስረኞች የተናገረውም፣ እንኳንስ የወገኖቹ ሰቆቃ የሚያሳምመውን ተቆርቋሪ ዜጋ ቀርቶ፣ ልበ-ደንዳናውንም ቢሆን በስቃይ ‹መስቀል› የሚቸነክር መራራ እውነታ ነው፡-
‹‹በሕግ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ተጠርጣሪዎች ላይ፣ በአንዳንድ ፖሊሶችና መርማሪዎች አማካኝነት መረጃ ለማግኘት በሚል ድብደባ ይፈፀምባቸዋል፤ ታሳሪዎች ንፁህ የማረፊያ ቦታ፣ ህክምናና ጥሩ ምግብ አያገኙም፤ በአንዳንድ ቦታዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትም አለ፡፡››
በርግጥ ሚኒስትሩ እንዲህ በግልፅ ከማመኑ ከዓመታት በፊት እኛ ኢትዮጵያውያን ቀርቶ፣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ደጋግሞ ብሎ፣ ብሎ የሰለቸው ጉዳይ ነው፤ ይህ በርካታ ተጨባጭ ማስረጃዎች ማቅረብ የሚቻልበት ትልቁ የመንግስት ጥፋትም ይመስለኛል፤ የእስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ ከቤተሰብ ውጪ ሌላ ጠያቂ መከልከል፣ የርዕዮት አለሙ የህክምና እርዳታ መነፈግ፣ የአቡበከር መሀመድና ውብሸት ታዬ በመርማሪ ፖሊሶች መደብደብ፣ በበቀለ ገርባና ኦልባና ሌሊሳ ላይ የተፈፀመውን ሥቅየት (ቶርቸር) መጥቀሱ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡
ሌላው ድንጋጤ ውስጥ የሚከተው በወንጀል ምርመራ፣ በክስ አዘገጃጀትና በችሎት ክርክር ላይ የሚሳተፉ መርማሪዎችና ዓቃቢያን ሕጎች ያለባቸው የዕውቀት ማነስ፣ የአመለካከትና የሥነ-ምግባር ችግር መጠቀሱ ነው (መቼም በሽብርተኝነት በተፈረጁ ድርጅቶች ስም እያመኻኙ በሀሰተኛ ክስ እልፍ አእላፍ ንፁሀን ዝነኛውን የቃሊቲ ወህኒ ቤት ጨምሮ በተለያዩ ማጎሪያዎች እንዲማቅቁ ከመደረግ የበለጠ ሌላ ዓይነተኛ ማረጋገጫ መፈለግ ያለብን አይመስለኝም) በአናቱም ሕዝብን በአገልጋይነት ስሜት በክብር አለማስተናገድ፣ ውሳኔን በፅሁፍ አለመግለፅ እና ሌሎች መሰል ችግሮች በሀገሪቱ መንሰራፋታቸው የፓርቲው ጉምቱ መሪዎች በተሰበሰቡበት ተዘርዝሮ ቀርቧል፡፡
የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚንስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑም ያቀረባቸውን ችግሮች በጥሞና ላስተዋለ፣ ስርዓቱ ለመጪዎቹም 40 እና 50 ዓመታት እንኳ በስልጣኑ ቢቀጥል መፍትሄ የሚያገኝላቸው አይደሉም (እዚህች ጋ ፈገግታን የሚያጭር አንድ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፤ ይኸውም አቶ አለማየሁ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኙ የሀገሪቱ ቀበሌዎችን መጥቀሱን ተከትሎ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን
ገ/ሚካኤል፡- ‹‹አገልግሎት ያላገኙት ቀበሌዎች ሶስት ሺህ ናቸው ያልኩት ለማጠጋጋት ነው እንጂ ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ናቸው›› የሚል ምላሽ መስጠቱ ነው፡፡ በርግጥ ኃ/ማርያም ደሳለኝም በጉዳዩ ላይ ያቀረበው መከራከሪያ እንዲሁ ተጨማሪ ሳቅ የሚፈጥር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡- ‹‹ከማንኛውም የአፍሪካ ሀገር በበለጠ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረብን ነው!››
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ ደግሞ፣ መላኩ ፈንቴና ገብረሃዋድን ጨምሮ ዛሬም በሞቀ አልጋቸው ላይ ሚስቶቻቸውን አቅፈው በነፃነት የሚምነሸነሹ ባለሥልጣናት መጫወቻ የሆነውን የገቢዎች መስሪያ ቤትን አስመልክቶ በዋናነት ከዘረዘራቸው ጉድለቶች መሀል ‹‹አድርባይነት፣ ችግሮችን እያወቁ ከመፍታት ይልቅ በቸልተኝነት መተው፣ ቅን ያለመሆን፣ ግብር ከፋይን ማስበርገግ፣ ጫና ማድረግ፣ ማስፈራራት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት…›› ይጠቀሳሉ፡፡
አስረጅ ስድስት
እዚህ ጋ የማነሰው ጥቅምት 2006 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ከታተመው መንግስታዊው ‹‹ዘመን›› መፅሄት ጋር ቃለ-መጠይቅ ያደረጉ ባለሥልጣናትን ምስክርነት ነው፡፡
የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ የተጋነነውን የዋጋ ንረት ተከትሎ የተፈጠረውን የኑሮ ወድነትና የመንግስት ሰራተኛ ደመውዝ እንደማይጨመር መገለፁን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ‹‹ሁሉም ዜጋ ችግሩን ተቋቁሞ ነገ የሚመጣውንና አሁንም እየመጣ ያለውን የተሻለ ሁኔታ እንዲያይ ነው የሚፈለገው›› ሲል ከቀለደ በኋላ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ረገድ በርካታ ችግሮችና ድክመቶች መኖራቸውን፣ በአዲስ አበባ ከተማም የትራንስፖርት ችግር መኖሩን አልሸሸገም፤ አያይዞም፡-
‹‹በከተሞች አካባቢ ሰፊ የሥራ አጥነት ችግር አለ፤ መረጃው የሚያሳየንም እንደዚያ ነው፡፡ ከ17 በመቶ በላይ (ቁጥሩን ሆነ ብሎ አሳንሶታል) መስራት የሚፈልግ የከተማ ነዋሪ የሥራ ዕድል አላገኘም፡፡ በጣም ብዙ ኃይል ነው ይሄ›› ማለቱ ለስርዓቱ ፖሊሲዎችና ዕቅዶች መክሸፍ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም የትውልድ ቦታው በሆነው ወለጋ የተንሰራፋውን ድህነት የገለፀው እንደሚከተለው ነበር፡-
‹‹…በሰብል በተለይ ገብስና ጥራጥሬ ከፍተኛ ምርት ሊሰጥ የሚችል አካባቢ ነው፡፡ የሰዉ የኑሮ ሁኔታ ግን የምጠብቀውን ያህል የሚያመረቃ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡››
የመፅሄቱ ሌላኛዋ እንግዳ የማዕከላዊ ስታስቲክና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያም በበኩሏ ‹‹እውነት እውነት የሚመስለኝ ሥራ ይሄ ነው›› ያለችበት አውድ፣ መንግስት ዛሬም ድረስ ለሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ራሱን የቻለ ምፀት ይመስለኛል፡፡
የመውጫው በር
ስርዓቱ ከሚመራው ህዝብም ሆነ ከምሁራን ዘንድ የሚሰነዘርበትን ድክመትና ችግሮች ለዓመታት ሲያጣጥል የቆየ ቢሆንም፣ እነሆ አሁን ግን በዚህ መልኩ በራሱ ሰዎች አንደበት አምኖ መቀበሉን ይፋ አድርጓል (በርግጥ ‹ተሳስቼአለሁ› ማለቱ ለለውጥ ተዘጋጅቶ ወይስ አንዳች ሊያስቀይስ ያሰበው ጉዳይ ስላለ? የሚለውን በሌላ ዕትም በስፋት እንፈትሸዋለን) አሁን ግን በብልሹ አስተዳደር ሳቢያ የተፈጠሩት እነዚህንና እነዚህን መሰል ችግሮችና ድክመቶች እስከ መቼ ነው የሚቀጥሉት? መፍትሄውስ ምንድር ነው? የሚለውን ጥያቄ በደምሳሳው ለመመለስ በቅድሚያ ከሀገራችን ታሪክ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡-
በ1910 ዓ.ም በንግስት ዘውዲቱና በልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ዘመን ‹ሚኒስትሮቹ በሀገሪቱ ላይ በደል እያደረሱ ነው› በሚል ህዝቡ በጃንሜዳ ተሰብስቦ ምክክር ካደረገ በኋላ ለአልጋ ወራሹ እንዲህ የሚል ደብዳቤ መፃፉን በ‹‹ዝክረ ነገር›› መፅሀፍ ውስጥ ተገልጿል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ ሆይ፡-
እኛ ባሮችዎ የኢትዮጵያ ህዝብ በንግሥታችን በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ በእርሶም በልዑል አልጋ ወራሻችን በኩል ተበድለናል፣ ተጎድተናል የምንለው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ታላቁ ንጉሥ ዳግማዊ ምኒሊክ ሕዝቤን ይጠብቁልኛል፣ የዠመርኩትን ሥራዬን
ይፈፅሙልኛል ሲሉ የሾሟቸው ሚኒስትሮች ራሳቸው ሕዝብ መበተን፣ አገራችንን ማጥፋት፣ አገርንና ገንዘብን ለራሳቸው መካፈልና ዕውቀትን ማጥፋት፣ ትምህርት መድፈን ሆነ እንጂ ለመንግስታችን የረዱት የጠቀሙት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ከመበደልና ከመገፋት፣ ከውርደትና ከመበሳጨት፣ ድኻው ከመዘረፉ መንግስታችን ካለመጠቀሙ የተነሳ ለንግሥታችንና ላልጋ ወራሻችን እናመለክታለን፡፡››
ልዑል ተፈሪ መኮንንም ሕዝቡ ላቀረበው ጥያቄ አርኪ መልስ ሰጡ፡-
‹‹…እንድጋ የሕዝቡ መሰብሰብ ምን ያኽል የሚያጎድል ይመስላችኋል? እንደዚሁ ባለ ምክንያት መስኮብን ያኽል ታላቅ መንግስት… ከተማው ባንድ ቀን ጠላቶች ገቡበት፤ ሰዋቸውም ተከፋፍሎ ርስ በርሱ ተላለቀ፤ አሁን እናንተ ሚኒስትሮች ይሻሩልን ማለታችሁ የተሾሙት ሰዎች ይሻሩልን ብላችሁ ነው እንጂ የተነሳችሁት፤ የበደላችሁ ሥራው አይደለም፡፡
‹‹…የመንግስት ኃይልና የሕዝብ ኃይል ትክክል ነው፡፡ አሁንም ለሹም ሽሩና ለሌላው ሥራ እኛም ብንጨርሰው፣ ሰው ከእኛም መካር አግኝተን ብንጨምር እንደ ሚያስፈልግ እያየን እናደርገዋለን፤ አሁን ያሉትን ሚኒስትሮች ግን ሽረንላችኋል፤ ይህነንም በዝግታ ብታሳውቁን እንደሚሆን አድርገን ሕዝቡም ተሰበሰበ ሳይባል እንጨርስላችሁ ነበር፡፡
መጋቢት ፲፮ ቀን ፲፱፻፲ ዓ.ም ተጻፈ፤ አዲስ አበበ ከተማ››
የልዑሉ ተፈሪ ምላሽ ሙሉ በሙሉ ለህዝብ መገዛትን ያሳያል፤ እንደሚታወሰው በወቅቱ ሕዝቡ ፈቅዶም ይሁን ተገዶ የንጉሠ ነገሥቱ ሹመት ‹ሠማያዊ ነው› የሚል እምነት ነበረው፤ ልዑሉም ‹የመንግስት ኃይል› ሲሉ የገለፁት ንጉሡንና ወራሾቹን እንደሆነ የሚሳት ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህም እነርሱ ይሻራሉ ተብሎ አይጠበቅም፤ በግልባጩ ሚኒስትሮቹ የተሾሙት በንጉሠ ነገሥቱ በመሆኑ ሕዝባዊ ተቃውሞ በቀረበባቸው ጊዜ ‹የሕዝብ ኃይል ትክክል ነው› ብለው በሚሸነግሉ ነገሥታት እስከመሻር ይደርሳሉ፡፡
እነሆም ከመቶ ዓመታት በኋላም ይህ ጥያቄ መቅረቡ አልቀረም፤ በርግጥ ዛሬ ‹ሠማያዊ ሹመት› የተበላበት ማጭበርበሪያ ካርታ በመሆኑ፣ ‹መረጥከኝ› ለሚለው ዘመናዊ የ‹ዲሞክራሲ› ስርዓት ቦታውን ለቋል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ምድር ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የሚያካሄደው ምርጫ ጊዜ ያለፈበት የማጭበርበሪያ ‹ካርታ› ለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል፤ ምክንያቱም ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉ እንደልጅነት ዘመን ‹‹ዳቦ ተቆረሰ፣ ጨዋታው ፈረሰ›› አይነት ስለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎች ቀርቦበት በመላ ዓለም ዘንድ የታመነበት የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ቆይቷልና፡፡
በአናቱም የሚኒስትሮቹ ‹አለቃ› ኃይለማርያም ደሳለኝ ሕዝብ የተቃወማቸውን ቀርቶ፣ ራሳቸውም እንዲህ በአደባባይ ሥራው እንዳቃታቸው የተናገሩ ባለሥልጣናትን፣ የልዑል ተፈሪን ያህል ሥልጣን ኖሮት ‹ሽሬአቸዋለሁ› ሊል አይችልም፤ እነርሱም ቢሆኑ እንደሰለጠነው ዓለም መንግስት ሕዝብን ‹ይቅርታ› ጠይቀው ራሳቸውን ከኃላፊነት ያነሳሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እንዲያውም ሁሉም አይናቸውን በጨው አጥበው ለሚቀጥለው ምርጫ ሽር-ጉድ እያሉ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደቀደሙት ምርጫዎች ሁሉ ኢህአዴግ በዝረራ ማሸነፉን ሊያበስሩን (ሊሚያሳምኑን) ያሰፈሰፉ ‹ልማታዊ ጋዜጠኞች› እንኳ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው እንዲጠብቁ ከታዘዙ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ለህዝብ ብሶትና ጩኸት ጆሮ የሚሰጥ አንድ እንኳ አልተገኘም፡፡
እናም ቀሪው የመፍትሄ መንገድ አንድና አንድ ይመስለኛል፤ የኢትዮጵያን ‹ታህሪር› አደባባይ ፈልጎ ከሰማይ ከፍታ በላይ ጩኸትን በማስተጋባት ተራሮችን ማንቀጥቀጥ፣ ምድሪቷን ማራድ!

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog