ጥንታዊ ስልጣኔን ለታሪክ ትተን ከድህነት ወለል በታች ከሚፈረጁት የዓለማችን ኣገራት ተርታ ተሰልፋ የምትገኘው ኢትዮጵያ ግን ደግሞ ይህ ነው የማይባል የተፈጥሮ ሀብትም እንዳላት ይታወቃል።
ከተፈጥሮ ሀብቷ መካከልም ኣንደኛው የውኃ ኃብቷ ሲሆን ወንዞቿ ደግሞ ድንበር ዘለልም ጭምር ናቸው። ከዚሁ የተነሳ የምስራቅ ኣፍሪካ የውኃ ምንጭ በመባልም ትታወቃለች። ኣንዱና ዋናው ደግሞ ጥቁር ዓባይ ወይንም በውጪው ኣጠራር ብሉ ናይል ነው። 75 በመቶ የሚሆነው የናይል ውኃም የሚመጣው
ከዚሁ ከብሉ ናይል ወይንም ከኢትዮጵያው ጥቁር ዓባይ ነው። በኣንጻሩ ግን እስከዛሬ ግብጽና ሱዳን እንጂ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ኣልነበረችም። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የኢትዮጵያ መንግስት በዓባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብ ሲል የሚጠራውን እጅግ ግዙፍ የሆነ የኃይል ማመንጫ ግድብ መጀመሩ ይታወቃል። ፕሮጀክቱ ደግሞ የታችኛው ተፋሰስ ኣገሮችን በተለይም ግብጾችን ማሳሰብ የጀመረው ገና ከጅምሩ ነበር ማለት ይቻላል።
ከዚሁ ከብሉ ናይል ወይንም ከኢትዮጵያው ጥቁር ዓባይ ነው። በኣንጻሩ ግን እስከዛሬ ግብጽና ሱዳን እንጂ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ኣልነበረችም። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የኢትዮጵያ መንግስት በዓባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብ ሲል የሚጠራውን እጅግ ግዙፍ የሆነ የኃይል ማመንጫ ግድብ መጀመሩ ይታወቃል። ፕሮጀክቱ ደግሞ የታችኛው ተፋሰስ ኣገሮችን በተለይም ግብጾችን ማሳሰብ የጀመረው ገና ከጅምሩ ነበር ማለት ይቻላል።
ከአዲስ ኣበባ በስተ ምዕራብ 620 ኪ ሜ ያህል ርቆ እና ከሱዳን ድንበር ደግሞ 20 ኪ ሜ ገደማ ብቻ ገባ ብሎ በቤኒሻንጌል ጉሙዝ ክልል እየተገነባ ያለውን ታላቁን የዓባይ ግድብ ባለስልጣናቱ የህዳሴ ግድብ የሚል ስያሜ ተሰተውታል። የሚሊኒየም ግድብ እያሉም ይጠሩታል። እኣኣ በታህሳስ ወር 2011 ሳሊኒ ከተባለ የኢጣሊያ ተቐራጭ ኩባኒያ ጋር በተፈረመ ውል መሰረት ግንባታው እስከኣሁን 26 በመቶ መድረሱ ተነግሯል። ከ5 ዓመታት በኃላ በ2018 ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል። እንደ ውጥኑ ከተጠናቀቀ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በኣፍሪካ ደረጃም ትልቁ ግድብ መሆኑ ነው።
ከ60 እስከ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሚይዝ የሚነገርለት የህዳሴ ግድብ 6000 ሜጋ ዋት የዓኬትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረውም ይገመታል። የሚፈጀው ወጪም በመንግስት ስሌት 4,8 ቢሊየን ዶላር ሲተመን ኣንዳንድ ባለሙያዎች ደግሞ የኢሌትሪክ መስመር ዝርጋታን ጨምሮ የፕሮጀክቱን ወጪ ከ6 እስከ 7 ቢሊ,ን ዶላር ያደርሱታል።
ኣንደኛው ጥያቄ የዓለም ባንክም ሆነ ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቐም ብድር በነፈጉበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ዓቅም እንዴት ይዘለቃል የሚለው ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ግን በህዝባችን ትብብር በሚል በድፍረት ይዞታል። ግንባታው በኣንድ ወይንም በሌላ መልኩ ከተጠናቀቀ ባኃላም ቢሆን ለዚህን ያህል ከፍተኛ የኤሌትሪክ ኃይል የውጪ ገበያ የማግኘቱ ጉዳይም ሌላው ተዛማጅ ጥያቄ ነው። ምክኒያቱ ደግሞ እንደ ዋና ገበያ የሚታሰቡት ግብጽ እና ሱዳን የታችኛው ተፋሰስ ኣገሮች በመሆናቸው ፕሮጀክቱ ገና ከውጥኑ ስጋት ሆኖባቿልና። የውኃውን ፍሰት ይቀንስብናል በሚል። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በUS አሜሪካ የዊስካንሲን ዩኒቨርሲቲው የስነ ውኃ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፓውል ጄ ብሎክ እንደሚሉት የግብጾች ስጋት ተደጋግሞ እንደሚሰማው የግድቡ ግንባታ የውኃውን ፍሰት ይቀንስብናል የሚል ሲሆን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በበኩላቸው የግድቡ ዓላማ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ብቻ በመሆኑ እና ወደ ግድቡ የገባው ውኃ የኃይል ማመንጫውን ካንቀሳቀሰ በኃላ ተመልሶ ወደ ወንዙ ስለሚለቀቅ በፍሰቱ መጠን ላይ የተለየ ተጽዕኖ ኣይኖረውም ሲሉ ይከራከራሉ። ሌላው ቀርቶ ግብጾች ይህን የመሰለ ግዙፍ ግድብ እስኪሞላ ድረስ ባሉት ዓመታትም ቢሆን ስለሚኖረው የውኃ ውስንነት ስጋት ኣላቸው። በኢትዮጵያ መንግስት መግለጫዎች መሰረት ግን የሙሌቱ ሂደት በየዓመቱ አነስተኛ የውኃ መጠን ብቻ ወደ ግድቡ በማስገባት የሚከናወን ሲሆን ጠቀም ያለ ውኃ በመያዝ በአጭር ጊዜ ለመሙላት ቢፈለግም እንኩዋን የግብጹ የአስዋን ግድብ የኣገሪቱን ኣጠቃላይ የውኃ ፍጆታ ለ 3 ዓመታት ያህል የሚሸፍን የመጠባበቂያ ክምችት ስላለው በእነዚያ ጊዜያት ሊጠቀሙበት ይችላሉ ሲሉ ባለስልጣናቱ ኣማራጭ መከራከሪያም ያቀርባሉ። ባለሙያው ፕሮፌሰር ፓውል ግን ኣስታራቂው ሀሳብ ዓለም ዓቀፍ የሆነው የሙሌት ፖሊሲ ነው ይላሉ።
የሙሌት ደምቡ ፕሮፌሰር ፓውል እንደሚሉት ሁለት መልክ ኣለው። ኣንደኛው በየወሩ ወይንም በየዓመቱ በጣም አነስተኛ የውኃ መጠን ብቻ ወደ ግድቡ በማስገባት በረጅም ጊዜ እስኪሞላ መጠበቅ ሲሆን ይህ ግን ባለ በሌለ ኣቅሟ እያስገነባች ላለችው ኢትዮጵያ ኣዋጪ ኣይመስልም። ጠቀም ያለ ውኃ ተይዞ በኣጭር ጊዜ ለመሙላት ቢሞከር ደግሞ የታችኞቹን የተፋሰሱን ኣገሮች ስለሚጎዳ በሙሌት ደምቡ መሰረት ሊያስማማ ባይችል ሊያቀራርብ የሚችሉ ኣማራጮችን መፈለጉ የግድ ይሆናል ይላሉ ፕሮፌሰር ፓውል ጄ ብሎክ።
እናም ይላሉ ተመራማሪው ከዚህ የተለየ የሙሌት ደምብ ኣማራጮችን መፈተሹ የግድ ይሆናል። ለምሳሌም ያህል ይላሉ ፕሮፌሰር ፓውል፣
የዚህ ኣይነቱ የሙሌት ደምብም ቢሆን ኢትዮጵያን የሚጎዳበት ኣጋጣሚ እንደሚኖረው የጠቀሱት ፕሮፌሰር ፓውል ምክንያቱ ደግሞ የአየሩ ጸባይ ከዓመት ወደ ዓመት ተለዋዋጭ በመሆኑ ዝናብ ኣጠር በሆኑ ዓመታት ኢትዮጵያ ኣጠቃላዩን ውኃ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ኣገራት ለመልቀቅ ያስገድዳታል ይላሉ። የሆነ ሆኖ የሙሌት ፖሊሲው ሌሎች የተለያዩ ኣማራጮችም እንዳሉት የጠቀሱት ፕሮፌሰር ፓውል ወሳኙ ነገር የሶስቱ ኣገሮች በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንደሆነ ይመክራሉ።
ባለፈው ወር የኢትዮጵያ የግብጽ እና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች ካርቱም ላይ ተገናኝተው ኣንድ የጋራ ቴክኒካዊ ኮሚቴ ለማቐቐም መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን በኮሚቴው አባላት ኣሰያየም ላይ ግን ግብጽ እና ኢትዮጵያ በልዩነት መለያየታቸው ኣይዘነጋም። ኢትዮጵያ ኮሚቴው ከሶስቱ ኣገሮች በተወከሉ ባለሙያዎች ብቻ እንዲዋቀር ትፈልጋለች። ግብጽ ደግሞ ገለልተኛ የሆኑ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ተወካዮችም እንዲካተቱ ትሻለች።
ሌላው ተዛማጅ ጥያቄ በመግቢያችን ላይ እንደተጠቀሰው የግድቡ ወጪ በኢትዮጵያ አቅም ብቻ መሸፈን ስለመቻሉ ሲሆን ኣሁን ባለው ሁኔታ ለዚህ ፕሮጀክት ብድር የማግኘቱ ዕድል የመነመነ ቢሆንም ባለፈው ጥቅምት ወር ጠ/ሚ ኃ/ደሳለኝ መንግስታቸው ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር በሽርክና ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው ነበር። ይህንኑ ተከትሎ የግብጽ ባለስልጣናትም እየተለሳለሱ መምጣታቸው ይሰማል። እናም ይህ ከሆነ ተንታኞች እንደሚሉት ለኢትዮጵያ ይህን ከፍተኛ የግንባታ ወጪ ለመሸፈን ከማገዙም ባሻገር ኣገሪቱ ከግድቡ ለምታመነጨው የኤሌትሪክ ኃይል የውጪ ገበያ ያስገኝላታል። ለግብጽ እና ለሱዳንም ቢሆን የሚፈልጉትን የኤሌክትሪክ ኃይል በቅናሽ ዋጋ እንዲገዙ ያስችላቿል። ከሁሉም በላይ የወንዙን ውኃ በጋራ እያለሙ በጋራ እንዲጠቀሙ እድል ይፈጥርላቿል ተብሎ ይታመናል። በተለይም ግብጽ እና ኢትዮጵያ ይህንን ካደረጉ ፕሮፌሰር ፓውል ጄ ብሎክ እንደሚሉት ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቐማትም ፕሮጀክቱን ሊደግፉ ይችላሉ።
እንዲያውም ይላሉ ፕሮፌሰር ፓውል የግብጽ እና የሱዳን ግድቦች በየዓመቱ ከፍተኛ የውኃ መጠን በትነት መልክ ያባክናሉ። የህዳሴ ግድብ ግን የትነት መጠኑ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ሶስቱ ኣገሮች ከተስማሙ በዚህ ብቻም ሳይወሰኑ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ተቸማሪ ግድቦችን በጋራ እያስገነቡ እና እያስተዳደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆንም ይችላሉ። ይህም በክረምት ወራት ከፍተኛ የሆነ የውኃ መጠን ኢትዮጵያ ላይ በመያዝ በበጋ የናይል ወንዝ በሚመነምንበት ወቅት ተጨማሪ ውኃ ይዞ ይዞ ወደ ሱዳን እና ግብጽ በረኃዎች እንዲዘልቅ ማድረግም ይቻላል ይላሉ ፕሮፌሰር ፓውል።
በተያያዘ ዘገባ የቻይና መንግስትም ከግድቡ ኣንስቶ እስከ አዲስ ኣበባ ከተማ ድረስ ያለውን የ619 ኪ ሜ የኤሌትሪክ መስመር ዝርጋታ ወጪ ለመሸፈን የ1 ቢሊየን ዶላር ብድር መፍቀዱ ታውቐል። ግብጽም ብትሆን ምንጮች እንደሚጠቁሙት ከ20 እስከ50 በመቶ የሽርክና ድርሻ ለመግዛት እያሰበች መሆኑ ተሰምቷል። ይህ ግን የሚሆነው በኢትዮጵያ መልካም ፈቃደኝነት ነው ተብሏል።
ግብጽ የናይል ወንዝን በተመለከተ እኣኣ በ 1891 እና 1959 ዓ ም የተፈረሙ ዓለም ዓቀፍ ውሎችን መነሻ በማድረግ ልዩ የባለቤትነት መብት ኣለኝ ስትል ቆይታለች። ኢትዮጵያ በበኩልዋ ከሱዳን በስተቀር ሌሎች የተፋሰሱ ኣገሮች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተፈራረሙት የጋራ ስምምነት መሰረት አሮጌው የግብጽ የተናጠል ውል ዋጋ እንደማይኖረው ትከራከራለች።
ጃፈር ዓሊ
ሒሩት መለሰ
Source: www.dw.de
No comments: