“ዲግሪ ያላቸው በየአስተዳደሩ እንዲገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት፣ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እያካሄደ ያለውን አዲስ
የመተዳደሪያ ደንብ የማፅደቅ ሂደት እና መዋቅራዊ ለውጥ አጥብቀው እንደሚቃወሙ የሃገረ ስብከቱ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ለቅዱስ ፓትሪያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አስታወቁ፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለፅ/ቤቶቹ ባስገቡት ደብዳቤ፤ የሃገረ ስብከቱ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ሳይሳተፉበት በጥቂት አመራሮች
ብቻ የተቀረፀና በውይይት ያልዳበረ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ከነባሩ ህገ ቤተ ክርስቲያንና ከቃለ-አዋዲ ደንብ ጋር የሚጋጭና የሚጣረስ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ደንቡ፤ ነባሩን የቤተክርስቲያኒቱን ሠራተኛ በማፈናቀል በምትኩ ስለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምንም እውቀት የሌላቸውን ግለሠቦች በስመ ድግሪና ዲፕሎማ በመሠግሠግ የቤተክርስቲያኗን ሙሉ አስተዳደራዊ መዋቅር ለመቆጣጠር ያለመ ነው” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
አዲሱን መዋቅር ያዘጋጁት አካላት ማንነታቸው በግልፅ እንደማይታወቅ በደብዳቤያቸው የጠቀሡት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ስልጣን ያለውን ቅዱስ ፓትርያርክ ስልጣንን በመገደብ፣ ቤተክርስቲያኗ የእነዚህ አካላት ሠለባ እንዳትሆን ስጋት አለን ብለዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ ያልጠበቀ ነው ያሉትን አዲሱን መተዳደሪያ ደንብ እንደማይቀበሉትም አስተዳዳሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ለቅሬታው መነሻ የሆነው ደንብ፣ ህግ በማርቀቅና በማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው ገለልተኛ ምሁራንና የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ሊቃውንት እንዲሰናዳ የጠየቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ህጉን አርቅቋል የተባለውን ማንነቱ ማህበር ፓትሪያርኩ እንዲያጣሩ ተጠይቀዋል፡፡ “አዲሱ ደንብ የካህናት ቅነሣ መርሃ ግብርም እንዳካተተ በግልፅ ተረድተናል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ድርጊቱ መንግስት ስራ አጥን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት የሚፃረር ነው” ሲሉ ያጣላሉት ሲሆን ብዙ ሊቃውንትን ከስራ በማፈናቀል ለችግር እና ለእንግልት የሚዳረግ በመሆኑ ህጉ መፅደቅ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የፓትርያርኩ ልዩ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ታምሩ አበራ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ ወደ ፅ/ቤት ሳይገባ በቀጥታ ለፓትርያሪኩ የደረሰ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምላሽም ሆነ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖች በተናጥል ከሚቀርቡ፣ ለቤተክርስቲያኗ ይጠቅማል የሚሉትን ኮሚቴ መርጠው ሃሣባቸውን በማደራጀት ቢያቀርቡ እንደሚሻል የጠቆሙት ሃላፊው፤ የእነሡ ሃሣብ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳ በውይይት ለመተማመን ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
Source: Addis admass
  መገናኛ አካባቢ ወደ ጉርድ ሾላ በሚወስደው መስመር፣ አንድ መንገደኛ ትናንት ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ካልተሳፈርኩ ብሎ ሾፌሩን ወንደሰን ደምሴን በሽጉጥ ገደለ፡፡ “ታክሲው
ውስጥ ካልተሳፈርኩ፣ አትሳፈርም” በሚል በተነሳው ጭቅጭቅ፣ ሾፌሩን ገድሏል የተባለውን ደጀኔ ገመቹ በቁጥጥር ስር እንደዋለ የገለፀው ፖሊስ፤ የአይን ምስክሮችን ቃል በመቀበል ምርመራ እያካሄደ ነው፡፡ ታክሲ እየጠበቁ የነበሩ የአይን ምስክሮች በወቅቱ አቶ ደጀኔ እጁን በማወዛወዝ ሚኒባስ ታክሲውን እንዳስቆመ ተናግረው፣ ከሾፌሩ ጋር ጭቅጭቅ እንደተፈጠረ
ገልፀዋል፡፡ አቶ ደጀኔ በታክሲው ለመሳፈር ሲጠይቅ፣ ሾፌሩ “ቤተሰቤን ነው የጫንኩት፣ ሌላ ሰው አላስገባም” በማለት ምላሽ እንደሰጠው በአካባቢው የነበሩ መንገደኞች ተናግረዋል፡፡ ታክሲ የሚጠባበቁ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ስለነበሩ፣ ጭቅጭቁን ከመነሻው እስከ መጨረሻው የተመለከቱ እማኞች በርካታ ናቸው፡፡ የፖሊስ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የሾፌሩ አባት ታክሲው ውስጥ ነበሩ፡፡ “አትሳፈርም የምትለኝ ንቀት ነው” በሚል ክርክርና “የጫንኩት ቤተሰቦቼን ስለሆነ ሌላ ሰው አልጭንም” በሚል ምላሽ በተባባሰው ጭቅጭቅ፣ አቶ ደጀኔ ሽጉጥ እንዳወጣ እማኞች ተናግረዋል፡፡ ሽጉጡን ሾፌሩ አንገት ስር በመደገን ነው የተኮሰው ብለዋል-ምስክሮች፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ዲቪዥን ክፍል ተወካይ፣ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
Source: Addis Admass
 
ግብፅ የቅኝ ግዛት የውኃ ኮታዋ እንዲከበር አሁንም ጠይቃለች
•ለመስማማት የገባችውን ቃል አፍርሳለች
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በተመለከተ ከግብፅና ከሱዳን መንግሥታት ጋር እያደረገ የሚገኘውን ድርድር ውጤት አስታወቀ፡፡ የግብፅ መንግሥት ያቀረባቸው የግዴታ ሐሳቦች በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኙም፡፡ 

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከግብፅና ከሱዳን አቻ ሚኒስቴሮች ጋር በህዳሴው ግድብ ላይ እያደረጋቸው የሚገኙ ድርድሮችን ማክሰኞ ዕለት ለባለድርሻ አካላትና ለመገናኛ ብዙኃን ሲያሳውቅ፣ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር የተስማማችባቸውንና ያልተስማማችባቸውን ነጥቦች ይፋ አድርጓል፡፡ 
በሚኒስቴሩ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ሚኒስቴሩና ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን ሥልታዊና የተጠና እንቅስቃሴ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጐን እንድትቆም ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ባለፈው ዓመት መጨረሻ
ላይ ያቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ ሪፖርትን ኢትዮጵያና ሱዳን መቀበላቸውን የገለጹት አቶ ፈቅ፣ ይህ ሪፖርት በግብፅ በኩል ተቀባይነትን ያላገኘ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ዓመት መጨረሻ በአዲስ አበባ ተገናኝተው በተስማሙት መሠረት፣ የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተግባራዊነት ላይ ውይይት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ 
በጥቅምት ወር መጨረሻ ሱዳን የተገናኙት የሦስቱ አገሮች ሚኒስትሮች በመፍትሔ ሐሳቡ ተግባራዊነት ላይ በመወያየት የሚያመቻችና የሚከታተል ኮሚቴ ለመመሥረት በሐሳብ ደረጃ መስማማታቸውን፣ ነገር ግን በኮሚቴው አባላት ስብጥር ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ውይይቱ ተቋርጦ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን አስታውሰዋል፡፡ 
የኮሚቴው አባላት ሙሉ በሙሉ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ብቻ መሆን አለባቸው በሚለው የኢትዮጵያ ፍላጎት መኖሩና በግብፅ በኩል የውጭ ባለሙያዎች እንዲካተቱ አቋም መያዙ፣ የልዩነቱ ምክንያቶች እንደነበሩ አቶ ፈቅ ገልጸዋል፡፡ 
ይህንን ልዩነት ለመፍታት ከተያዘው ቀጠሮ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ኮሚሽን ዓመታዊ ጉባዔን ምክንያት በማድረግ ወደ ሱዳን ማቅናቱንና በወቅቱም በሦስቱ አገሮች ድርድር ላይ የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያን አቋም እንዲረዳ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ 
የሱዳን የውኃና የኤሌክትሪሲቲ ሚኒስትር መንግሥታቸው የኢትዮጵያን አቋም ሙሉ በሙሉ ከመቀበል ባለፈ፣ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የማግባባት ሚና እንደሚኖራት በመተማመን ሁለተኛው የሦስቱ አገሮች ድርድር ከመጀመሩ ቀናት በፊት ወደ ግብፅ ማቅናታቸውን ገልጸዋል፡፡ 
የሱዳን ሚኒስትር በካይሮ ቆይታቸው ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳታቸውንና የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያን ሐሳብ እንደሚደግፍ ተገልጾላቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹ግብፅ የህዳሴው ግድብ ከፍታ ዝቅ ይበል የሚል ሐሳቧን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ የገንዘብ ብድር እንዳታገኝ የማደርገውን ሩጫ አቆማለሁ በማለት ለሱዳኑ ሚኒስትር ቃል ገብታ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለተኛው ዙር ድርድር እንዲቀጥል ተደርጓል፤›› ያሉት አቶ ፈቅ፣ በዚህ ድርድር ላይ ግብፅ ይዛ የቀረበችው ሰነድ ከገባችው ቃል የተለየ ነበር ብለዋል፡፡ 
በግብፅ በኩል ለሁለተኛው ዙር ድርድር የቀረበው ሰነድ በሦስቱ አገሮች የሚቋቋመው ኮሚቴ በኢትዮጵያ በኩል የሚገኙ አዳዲስ የጥናት ውጤቶችን እንዲዳስስና የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ኮሚቴው እንዲከታተል ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ማለትም የግብፅና የሱዳን የውኃ ደኅንነትና ፍላጐት ሙሉ በሙሉ መከበር አለበት የሚሉ ነጥቦችን በድጋሚ በሰነዱ አካታ ማቅረቧን ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ይህንን በጭራሽ ኢትዮጵያ የምትቀበለው አይደለም፤›› ያሉት አቶ ፈቅ፣ በዚህና በሌሎች የመወያያ ነጥቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይቱ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደተሞከረ ገልጸዋል፡፡ 
በውይይቱ ላይ ግብፅ ከ20 በላይ ባለሙያዎችን እንዳሳተፈች በኢትዮጵያ በኩል ግን ስድስት ባለሙያዎች እንደተወከሉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በግብፅ በኩል ሆን ተብሎ ውይይቶችን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በማጓተት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን የማዳከም ጥረታቸው ውጤት አልባ እንዲሆን በጥንካሬ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ጥረት በሚመሠረተው ኮሚቴ አባላት ስብጥር ዙሪያ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን አቶ ፈቅ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኮሚቴው በሚቋቋምበት ዓላማና በተወሰኑ የኮሚቴው ተግባርና ኃላፊነቶች ላይ ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው ሐሳቦች ተቀባይነት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
ኮሚቴው ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊነት የመከታተል ዓላማ የሚኖረው በመሆኑ፣ እስካሁን በሦስቱ አገሮች ተቀባይነት ካገኙ የኮሚቴው ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸው ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦችን ማስጠናትና የጥናት ውጤቱን ማፀደቅ ይገኝበታል፡፡ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎቹ ቡድን ባቀረባቸው ሁለት ሐሳቦች በግድቡ ላይ ተጨማሪ የኃይድሮሎጂ፣ የአካባቢያዊና ማኅበራዊ ጥናቶች እንዲደረጉ ጠይቋል፡፡ 
በመሆኑም ኮሚቴው ለሁለቱ ጥናቶች አማካሪ ድርጅቶችን መቅጠርና ማስጠናት፣ የጥናቱን ሪፖርት መገምገም፣ ማስተካከልና ማቅረብ፣ በዚህ የጥናት ሪፖርት ላይ የኮሚቴው አባላት መግባባት ካልቻሉ ጉዳዩ ለሚኒስትሮች ቀርቦ እልባት እንዲያገኝ፣ በዚህ ካልተፈታ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሙያዊ አስተያየት እንዲያቀርቡ የሚረዳ የቅጥርና የሥራ ዝርዝር ኮሚቴው እንዲያዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በቀሩ ጉዳዮች ላይ ለመወያየትም ሦስቱ ሚኒስትሮች በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ በሱዳን ተገናኝተው ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአማካሪ የሚጠኑት ሁለት ጥናቶች ሪፖርት ግምገማ ላይ የኮሚቴ አባላቱም ሆኑ ሚኒስትሮቹ መስማማት ካልቻሉ፣ ሙያዊ አስተያየት የሚሰጥ አማካሪ ለመቅጠር ስምምነት ተደርሷል፡፡ ነገር ግን ሙያዊ አስተያየት የሚሰጠው አማካሪ ቡድን ቅጥር የሚፈጸመው በሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ስምምነት ነው የሚለው ላይ ከስምምነት አልተደረሰም፡፡ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጥ የሚቋቋመው ቡድን በጥናቶቹ የመጨረሻ ሪፖርት ላይ ብቻ አስተያየቱ ይወሰናል በሚለው የኢትዮጵያ አቋም ላይ ያለውን አለመግባባት መቅረፍ ሌላው የውይይቱ አካል ነው፡፡ 
እስካሁን የተደረጉ ድርድሮችን ውጤቶቹን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው ውይይት ላይ የተገኙት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ በእጅጉ አድንቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የትኞቹንም የተፋሰስ አገሮች እንደማይጐዳ ለማሳወቅ ዩኒቨርሲቲው በአገር ውስጥ እያደረገ የሚገኘውን እንቅስቃሴ በማስፋት ወደ ጐረቤት አገሮች እንደሚዘልቅ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በመጪው መጋቢት ወር በሱዳን ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት ከካርቱም ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል፡፡
Source: Reporter

    ከ 4 ዓመት ገደማ በፊት፤ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ አንድ የኔልሰን ማንዴላ ድርጅት ዋና ተመራማሪ፤ ማንዴላን በማሠልጠን ያገዙ በሕይወት የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ ጠይቀው ያሰባሰቡት መረጃ ፣ ማንዴላ ከእሥራኤላውያን ጋር ግንኑነት እንደነበራቸው የሚያረጋግጥ አንዳችም እውነታ አልተገኘበትም። 
     ማንዴላን የጨበጣ ውጊያ ፣ የጦር መሣሪያ፣ አፈታትና አገጣጠም ፤ የቦንብ አጠቃቀምና የመሳሰለውን ያሰለጠኗቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የእሥራኤል የስለላ ድርጅት(ሞሳድ) ሠራተኞች ናቸው ሲል «ሐዓሬትዝ» የተሰኘ በእስራኤል የሚታተም ጋዜጣ አስነብቧል። ይሁን እንጂ የኔልሰን ማንዴላ ድርጅት፤ በሰጠው መግለጫ፤ ከማንዴላ የግል ማኅደርም ሆነ ከሌላ ይህን ዜና የሚያረጋጋጥ አንዳች ፍንጭ እንደሌለ
አስታውቋል። ከ 4 ዓመት ገደማ በፊት፤ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ አንድ የኔልሰን ማንዴላ ድርጅት ዋና ተመራማሪ፤ ማንዴላን በማሠልጠን ያገዙ በሕይወት የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ ጠይቀው ያሰባሰቡት መረጃ ፣ ማንዴላ ከእሥራኤላውያን ጋር ግንኑነት እንደነበራቸው የሚያረጋግጥ አንዳችም እውነታ አልተገኘበትም። ታዲያ «ሐዓሬትዝ» የተሰኘው የእስራኤል ታዋቂ ጋዜጣ ይህንን መረጃ እንዴት ሊያወጣ ቻለ?
Source: www.dw.de
 
ከፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ይልቅ፥ ጠመንጃ ጦርነትን ያደጉ የኖሩበት ሳልቫ ኪር የዲንካን፥ እንደ ፖለቲከኛ-ሻጥርን፥ እንደ ዲፕሎማት ግድምድሞሽ ዘይቤን፥ እንደ ታጋይ የጫካ ዉጊያ አጣምረዉ የያዙት ዶክተር ሪክ ማቼር የኑዌር ጎሳን፥ ከየጎናቸዉ አሰልፈዉ ተፋጠዋል። 
 ዛሬ-ስምት ዓመት በዚሕ ወቅት ግድም የረጅም ጊዜዉ ጦርነት፥ የሚሊዮኖች እልቂት ፍጅት ስደት አበቃለት ተባለ።የዛሬ-ሰወስት ዓመት በዚሕ ወቅት ግድም ሕዝቧ በነፃ ዉሳኔዉ ነፃነትዋን ማስፀደቁ ተነገረ። የዓለም ፖለቲከኞች መሠከሩለትም።ደቡብ ሱዳን።ሐምሌ-ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነፃነቷ ታወጀ።ፌስታ።

ወዲያዉ ግን ግጭት። ደግሞ ጦርነት።ዛሬም ጦርነት ላይ ናት።አዲስ ሐገር፥ ግራ አጋቢ ምድር።እንዴት ለምን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
አምና ነዉ።መስከረም።አዲሲቱን አፍሪቃዊት ሐገር ካሮጌ እልቂት ፎጅቷ ለመድፈቅ፧ አዳዲስ ጄኔራሎቿ የጀመሩት አመፅ፣ የአሮጌ ፖለቲከኞችዋን ነባር ሸኩቻ፤ የነባር ጎሶችዋን አሮጌ ግጭት ባዲስ መልክ አንሮታል።እንደ የበላይ የበታቾቻዉ ሁሉ በዉጊያ፣ አመፅ፣ ሽኩቻ፣ የኖሩት የያኔዉ የሐገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቼር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኒዮርክ የገቡት አዲሱ አመፅ፣ ሽኩቻ ግጭት ከኖሩበትና ከዘወሩት ብዙ ብጤዉ እንደማይከፋ እያሰላሰሉ ነበር።
ማቼር ከጉባኤዉ አዳራሽ ሲደርሱ ካገጠሟቸዉ ጋዜጠኞች ቢያንስ አንዱ የአዲሲቱ ሐገራቸዉን አዲስ ቀዉስ ምናልባትም የራሳቸዉንም ቅሬታ በቅጡ የሚያዉቅ ሳይሆን አይቅርም። «መንግሥትዎን መፈንቅለ መንግሥት ያሰጋዋል ይባላል» ብሎ ጠየቃቸዉ።ጥያቄዉ ያሰቡትን-ወይም ያለሰቡትን የሚያሳስብ ሊሆን፥ ላይሆንም ይችላል።መልሳቸዉ ግን «በፍፁም» የሚል ነበር።
እንዲሕ አይነት እርምጃ «ጅልነት» አሉ-አሉ አንጋፋዉ የነፃነት ታጋይ፥ «አዲሱን መንግሥት በአመፅ መጀመር አንፈልግም።» አከሉ፥-የአዲሲቱ ሐገር የያኔ ትልቅ ሹም።አሁንም አምና ነዉ።ግን ሐምሌ። ኪር እና ማቸር በየልባቸዉ የሚያስቡ፥ የሚያሰላስሉትን ከነሱ በስተቀር በግልፅ የሚያዉቅ-ከነበረ ቢያንስ አስካሁን በግልፅ አይታወቅም።

ሁለቱም ሁለት ዓመት እንደኖሩበት የመጀመሪያዉ እንደ ፕሬዝዳት፥ ሁለተኛዉ እንደ ምክትል ፕሬዝዳት በዓሉን አከበሩ።የነፃነት በዓል-ሁለተኛ ዓመት። ወዲያዉ ግን የመጀመሪያዉ ከሥልጣን አባራሪ፥ ሁለተኛዉ ተባባራሪ ሆኑ።

«አሁን የአንድ ሰዉ አገዛዝ ነዉ ያለን።ያንድ አገዛዝ ምን ማለት ነዉ።አምገነንነት።»
የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ሪክ ማቸር።ከሥልጣን በተባረሩ ማግሥት።ሐምሌ።ደቡብ ሱዳን፥ የሚነገር አይሆንባትም፥ የታቀደ አይፈፀምባትም፥የተነገረ-አይታመንባትም።ወይም የሚነገር፥ የሚባል፥ የሚታቀደዉ ከነባር እዉነቷ፥ከአቅም ማንነቷ ጋር ይጣረሱባታል።ማቼርም አምና መስከረም እንደ ምክትል ፕሬዝዳት ኒዮርክ ላይ የተቃወሙትን፥ባለፈዉ ሳምንት ለዕሁድ አጥቢያ ጁባ ላይ አደረጉት።መፈንቅለ መንግሥት።ከሸፈ።መዘዙ ግን ዛሬም አላባራም።
ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር የመላዉ ሱዳንን የምክትል ፕሬዝዳትነት ሥልጣን ከጆን ጋራግ ከወረሱበት ጊዜ ጀምሮ አደባባይ ሲወጡ አሜሪካኖች «የእረኛ» የሚሉት ሠፊ-ክብ ባርኔጣ ካናታቸዉ ተለይቶ አያዉቅም።ይወዱታል።ባርኔጣዉ በሚዘወተርበት ቴክስሳ ግዛት ያደጉ-የሚኖሩት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ለሳልቫ ኪር የሸለሟቸዉም ይሕኑ ባርኔጣ ነበር።
ዕሁድ ግን ባርኔጣቸዉን አዉልቀዉ፥ ሱፍ ከረባትታቸዉን በጄኔራል ማዕረግ በተንቆጠቆጠ የዉጊያ ልብስ ቀይረዉ ከጦር ሜዳ እንደተመለሰ ጄኔራል እያጉረጠረጡ ከቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ብቅ አሉ።
እርግጥ ነዉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ ከሽፏል።የአዲሲቱ ሐገር እዉነታ ግን ፕሬዝዳንቷ ካሉት ተቃራኒዉ ነዉ።ራሷ ጁባ፥ ቦር፥ ጃንጌሌይ፥ ዩኒቱ ከተሞች እና ግዛቶች ዛሬም በሳምንቱ በዉጊያ ይርዳሉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊሙን ይሕን መሠከሩ።
«እያሽቆለቆለ የመጣዉ የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ሁኔታ በጣም አሳስቦኛል።ሁሉም የፖለቲካ፥ የጦር እና የሚሊሺያ ሐይላት መሪዎች ሰላማዊ ሰዎችን የሚጎዳዉን ጠብ፥ ግጭታቸዉን እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ።»የሰማቸዉ እንጂ ቢያንስ እስካሁን የተቀበላቸዉ የለም።ጥንት በዚያ ግዛት እንዲያ ነበር።ድሮም።የዛሬ ስምንት ዓመትም እንዲሁ።ጥር ዘጠኝ።ሁለት ሺሕ አምስት።ናይሮቢ።
«ወገኖቼ፥ የሐገሬ ወንዶችና ሴቶች ሆይ! እንኳን ደስ አላችሁ።ደስታም በናንተ ላይ ይሁን። ንቅናቄያችሁ SPLM/SPLA እና የብሔራዊ ምክር ቤት መንግሥት አጠቃላይ የሠላም ስምምነት ተፈራርመዉላችኋል።ዛሬ የፈረምነዉና እናንተ ያችሁትን ፍትሐዊ እና የተከበረ የሠላም ዉል አቅርበንላችኋል።በዚሕ የሠላም ዉል መሠረት ከአፍሪቃ ረጅሙን ጦርነት አቁመናል።»
የቀድሞዉ የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጪ ጦርና ንቅናቄ መሪ ዶክተር ጆን ጋራንግ።ጋራንግ እንዳሉት ትልቂቱ አፍሪቃዊት ሐገር በ1956 ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከጥቂት ዓመታት ፋታ በስተቀር ጦርነት ተለይቷት አያዉቅም።ስምንቱ ሚሊዮኖችን የፈጀዉ፥ ከአራት ሚሊዮን በላይ ያሰደደዉን፥ ሰላሳ-ዘጠኝ ዓመታት ያስቆጠረዉን ጦርነት ማስቆሙ እርግጥ ነዉ።ከወጣትነት ዘመናቸዉ ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ያኽል ያን ጦርነት ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ሲዘዉሩ የነበሩት ጆንጋራንግ ያን ስምምነት ሲያበስሩ ዘግናኙ ጦርነት መቆሙን ብቻ ሳይሆን ሌላ ብጤዉ እንደማይከሰትም እርግጠኛ ነበሩ።ወይም ላዳመጣቸዉ መስለዉ ነበር።
«በዚሕ ሥምምነት መሠረት ከእንግዲሕ በየዋሕ ሕፃናትና እናቶች ላይ ከሠማይ የሚወርድ ቦምብ አይኖርም።ከእንግዲሕ ሕፃናት በደስታ የሚቦርቁበት፥ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ደስታቸዉን የተቀሙ እናቶች በእልልታ የሚደሰቱበት ሠላም ይሠፍናል።»«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በርግጥ ከአቅሙ በላይ ተወጥሯል።እዚሕ ያለ ማንም ቢሆን የተለመደዉን ሠብአዊ ርዳታ ለማቀበል ነበር የተዘጋጀዉ።ጁባ ዉስጥም ሆነ በክፍለ ግዛቶች አሁን የተፈጠረዉ ቀዉስ ይፈጠራል ብሎ ማንም ሰዉ አልጠበቀም።»ከኑዌር የሚወለዱት ሪክ ማቼር እንደመሩት በሚታመነዉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ሙከራዉን ባከሸፈዉ በፕሬዝዳት ሲልቫ ኪር ታማኞች መካካል ጁባ ዉስጥ ብቻ በተደረገዉ ዉጊያ ስድስት መቶ ሰዎች ተገድለዋል።በሌሎች ከተሞችና ክፍለ ግዛቶች በተደረገና በሚደረገዉ ዉጊያ የሞተ-የተሰደደ፥ የተፈናቀለዉን በትክክል የቆጠረዉ የለም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ጁባ እና ቦር በሚገኙ ሰወስት ቅጥር ግቢዎቹ ብቻ ከሠላሳ-አምስት ሺሕ በላይ ሕዝብ ተጠልሏል።ምዕራባዉያን ሐገራት ዜጎቻቸዉን ከምስቅልቅሊቱ ሐገር ማሸሹን ነዉ-ያስቀደሙት።ከዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን እስከ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ያሉ መሪዎች ተፋላሚ ሐይላት ከተጨማሪ ጦርነት ታቅበዉ ልዩነታቸዉን በሰላም እንዲፈቱ መጠየቅ-፥ ማሰሰባቸዉ አልቀረም።«የደቡብ ሱዳን መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ ነዉ።የምሥራቅ አፍሪቃ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ለድርድር የሚያስፈልጋቸዉን መረጃ ብቻ ሳይሆን ለጀመሩት ጥረት የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ሙሉ ዉክልናም አግኝተዋል።»
ከኑዌር የሚወለዱት እዉቅ ጄኔራል ፔተር ጋዴት፥በቅርቡ ከዩኒቲ ግዛት አስተዳዳሪነት የተሻሩት ታባን ዴንግ ጋይ፥ ከባሪ የሚወለዱት የቀድሞዉ ሚንስትርና ጄኔራል አልፍሬድ ላዱ ጎር፥የአናሳዉ የመርል ጎሳ አባል የሆኑት ዴቪድ ያዩ፥ እና በርስበርሱ ጦርነት ወቅት «ነጩ ጦር» በመባል የሚታወቀዉ ሚሊሺያ ሐይል ሁሉም እንደ ጋራ ጠላት በሚያዩት በሳልቫ ኪር መንግሥት ላይ ጠመንጃቸዉን አነጣጥረዋል።ይተኩሳሉም።
«ከቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ከዶክተር ሪክ ማቼር እና ከቡድናቸዉ ጋር የሚተባበሩ ወታደሮች ጁባ ዩኒቨርስቲ አጠገብ በሚገኘዉ በSPLA ዋና ፅሕፈት ቤት ላይ ጥቃት ፈፅመዋል።ጥቃቱ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ቀጥሎ ነበር።ይሁንና ለዜጎቼ በሙሉ፥ መንግሥታችሁ ጁባ ያለዉን የፀጥታ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ማሳወቅ እፈልጋለሁ።»

ተናገሩ።አልበሽር (የሰሜን ሱዳን ፕሬዝዳንት) ቦምብ የሚባለዉን ቃል ሲሰሙ ፈገግ አሉ። ጆንግ ጋራንግ የሠላም ስምምነቱን ዉጤት ለማየት፥ የሐራቸዉን ነፃነት ለመመልከት አልታደሉም።ከአርባ ዘመን ጦርነት አምልጠዉ በቅፅበት የሔሊኮብተር አደጋ-ሞቱ።ጋራንግ እንዳሉት እኒያ የሰሜን ሱዳን አዉሮፕላኖች የሚያወርዱት ቦምብ ከሁለት ሺሕ አምስት በኋላ ቆሟል።ደቡብ ሱዳን ግን ሠላም ሆና አለማወቋ እንጂ ቁጭቱ።
የጁባ ነዋሪዎች
በነፃነትዋ ዋዜማ ኮርዶፋን ግዛት ለተደረገዉ ጦርነት ሰሜን ሱዳኖችን መዉቀስ፥ መወነጅሉ፥ ለዛሬዎቹ የጁባ ገዚዎችም፥ ለምዕራባዉያን ደጋፊዎቻቸዉም ቀላል ነበር።አምና መጋቢት ሒጂሊጅ እና አካባቢዉን ያጋየዉን ዉጊያ የቆሰቆሱት ሳል ቫኪር መሆናቸዉ አለጠያየቅም፥ ጦርነቱ የቆመዉ ግን ሐያሉ ዓለም አልበሽርን አዉግዞ አስጠንቅቆ፥ ኪርን ካባበለ በኋላ ነበር።


ደቡብ ሱዳን እስከ ዛሬም ከአስሩ ግዛቶችዋ ዘጠኙ በእርስ በርስ ጦርነት፥በጎሳ ግጭትና ቁርቁስ እንደተመሠቃቀሉ ነዉ።እና ሰሜን ሱዳኖች የሚያወርዱት ቦምብ በርግጥ የለም።የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ግን ዛሬም እንደተገደለ፥ እንደ ቆሰለ፥ እንደተሰደደ፥ እንደተራበ ነዉ።የሳልቫ ኪርን አገዛዝ እና የሳልቫ ኪር ጎሳ የዲንካን የበላይነት በመቃወም በየሥፍራዉ ያመፁት ሰባት የተለያዩ ቡድናት ከመንግሥት ጦር እና እርስር በርስ በሚያደርጉት ዉጊያ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ተገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ተፈናቅሏል።ወይም ተሰዷል።
አሁን ደግሞ መፈንቅለ መንግሥትና መዘዙ ያንመከረኛ ሕዝብ ከዳግም እልቂት፥ ስደት፥ ዶሎታል። አምና መስከረም ጋዜጠኛዉ ማቸርን ሥለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የጠየቀዉ፥ የሐገሪቱን የፖለቲካ ዉጥንቅጥ፥ የጎሳ ጠብ፥ ቁርቁስን ሥላወቀ፥ ወይም ሥለገመተ እንጂ-ነብይነት ቃጥቶት አልነበረም።
በጁባ የዩናይትድ ስቴትስዋ አምባሳደር ሱዛን ፔጅ በቀደም እንዳሉት ግን የሆነዉ እንደሚሆን ማወቅ አይደለም የጋዜጠኛዉን ያሕል እንኳን አልገመቱም ነበር።ማንም አልጠበቀም ይላሉ በጁባ የልዕለ ሐያሊቱ ሐገር ዲፕሎማት።ደቡብ ሱዳን፥ የሚባል አይደረግባትም።ከፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ይልቅ፥ ጠመንጃ ጦርነትን ያደጉ የኖሩበት ሳልቫ ኪር የዲንካን፥ እንደ ፖለቲከኛ-ሻጥርን፥ እንደ ዲፕሎማት ግድምድሞሽ ዘይቤን፥ እንደ ታጋይ የጫካ ዉጊያ አጣምረዉ የያዙት ዶክተር ሪክ ማቼር የኑዌር ጎሳን፥ ከየጎናቸዉ አሰልፈዉ ተፋጠዋል።የዚያች ሐገር አበሳ-በሁለቱ ታዋቂ ፖለቲከኞችዋ ጠብ፥ ግጭት አለማብቃቱ ነዉ ክፋቱ።

የኢትዮጵያን ጨምሮ የአካባቢዉ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ጠብ፥ ግጭት፥ ጦርነቱን በሰላም ለመፍታት ባለፈዉ ሳምንት የጀመሩት የድርድር ጥረት ፍሬማ ዉጤት ማሳየቱን ጠቁመዋል።የደቡብ ሱዳኑ ማስታወቂያ ሚንስትር ሚካኤል ማኩይ በፋንታቸዉ መንግሥታቸዉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታዉቀዋል።

ከምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራት መካካል ዩጋንዳ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯን ብቻ ሳይሆን ጦሯንም ነዉ-ጁባ ያዘመተችዉ።የሠላም፥ ዲፕሎማሲና የዉጊያ ዘመቻ!! «የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚንስትር መንግሥታቸዉ «ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር መዘጋጀቱን ሲገልፁ፥የሐገሪቱ የጦር አዛዦች ባንፃሩ አማፂያኑ የሚቆጣጠሩትን ቦርን መልሶ የሚይዝ ጦር እያዘመቱ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።

አል በሽር አሁንስ ይፈግጉ ይሆን? ደቡብ ሱዳንስ ወዴት፥ እንዴት ትጓዝ ይሆን? ሥለ ማሕደረ ዜና ያላችሁን አስተያየት፥ ማሕደረ ዜና ቢቃኘዉ ጥሩ ነዉ የምትሉትን ጥቆማ በደብዳቤ፥ በስልክ፥ በፌስ ቡክ፥ በኢሜይል፥ በኤስ ኤም ኤስ ላኩልን።እስካሁን አስተያየት ጥቆማ የሰጣችሁኝን አመሰግናለሁ። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ
Source: www.dw.de 

ሊያበቃ ጥቂት ቀናት የቀረው 2013 ዓም በአፍሪቃ በፖለቲካው እና በማህበራዊው ዘርፎች ከታዩት ዓበይት ክንውኖች ጥቂቱ ባጭሩ ይቃኛል። 
እአአ መጋቢት አምስት፣ 2013 ዓም ኬንያ ውስጥ የአጠቃላዩ ምርጫ ቀን ነበር። ብዙ ሕዝብ ነበር ድምፁን ለመስጠት የወጣው። በተፎካካሪዎቹ ኡሁሩ ኬንያታ እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎቹ ጎራ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት ነበር የታየው። በምርጫው ኡሁሩ ኬንያታ አሸናፊ ቢሆኑም፣ ድላቸው አካራካሪ ነበር፣ ምክንያቱም፣ ከአምስት ዓመት በፊት እኢአ በ2007 ዓም የተካሄደው ምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ በተከተሉት ወራት በሀገሪቱ የ 1,200 ሰዎች ሕይወት የጠፋበትን ግጭት ቀስቅሰዋል በሚል ብዙዎች የሚወቅሱዋቸው ኬንያታ እና በምርጫው ዘመቻ ወቅት
ምክትላቸው እንደሚሆኑ ያጩዋቸው ዊልያም ሩቶ በስብዕና አንፃር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ጥርጣሬ ዘ ሄግ በሚገኘው በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት፣ በምሕፃሩ በአይ ሲ ሲ ክስ ተመሥርቶባቸዋል። ሆኖም ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ከተጠናቀቀ ከአራት ቀናት በኋላ ኬንያታ ተፎካካሪያቸውን ራይላ ኦዲንጋን በጠባብ የድምፅ ብልጫ ማሸነፋቸው በይፋ ተረጋገጠላቸው።
« ውድ የሀገሬ ዜጎች፣ ኬንያውያን ዛሬ የዴሞክራሲን ፣ የሰላምን ድል እና የብሔራዊ አንድነትን ድል እናከብራለን። በዓለም ብዙዎች ምርጫውን በትክክለኛ መንገድ ማካሄድ መቻላችንን ተጠራጥረውት ነበር፤ እኛ ግን ከጠበቁት በላይ ከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ብስለት አሳይተናል። » ።

ኬንያታ በአይ ሲ ሲ አንፃር የያዙትን አቋም ካጠናከሩ በኋላ የሀገራቸው ምክር ቤት ኬንያን ከአይ ሲ ሲ ምሥረታ ተፈራራሚ አባል ሀገራት ለማስወጣት ወስኖዋል። ይህ ውሳኔው ግን በኬንያታ እና በሩቶ ላይ በተመሠረተው ክስ ላይ የሚቀይረው ነገር አይኖርም። የኬንያታ ችሎት ያው ቀጠሮ እንደተያዘለት የፊታችን የካቲት በዘ ሄግ ይጀመራል
ግንቦት፣ 2013 በናጀሪያ አክራሪው የሙሥሊሞች ቡድn ቦኮ ሀራም በሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ ጥቃቱን አጠናከረ። የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን ጦራቸውን በቦኮ ሀራም አንፃር ከማሠማራቱ ጎን፣ በሦስት ያካባቢው ግዛቶች ውስጥ እስከተያዘው አውሮጳዊ ዓመት ማብቂያ ድረስ የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አወጁ። የገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይ አብዱላጂ ጃሎየፕሬዚደንቱን አቋም ገልጸዋል።
« ፕሬዚደንቱ ዝግጁ አይደሉም። በፍፁም ዝግጁ አይደሉም። አንድ ስንዝር መሬት እንኳን በጠላት(ቦኮ ሀራም) የሚያዝበትን ሁኔታ በቸልታ አይመለከቱም። » ይሁንና፣ የጦር ኃይሉ ዘመቻ አሁንም አከራካሪ ከመሆኑም ሌላ ያን ያህል ውጤታማ አይደለም። ባለፈው ሀምሌ በፖቲስኩም በአንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት ላይ በተጣለ የቃጠሎ አደጋ ቢያንስ 27 ተማሪዎች እና አንድ መምህር ተገድለዋል። ሌሎች ጥቃቶችም ተከትለዋል። ወደ 500 የሚጠጉ የፅንፈኛው አሸባሪ ቡድን በዚህ ወር መጀመሪያ በማይዱግሪ ከተማ በሚገኘው የአየር ኃይል ሠፈር ላይ በጣሉት ጥቃት አሁንም ጠንካራ መሆኑን ለማሳየት ሞክሮዋል።

ማይዱግሪ ነዋሪ ሙሀመድ ሙሳ የሰዓት እላፊ እያለ ይህን መሳይ ጥቃት በመጣሉ ቅር መሰኘቱን ገልጾዋል። « ጥቃቱ መንግሥት ባካባቢው ላለው የፀጥታ ችግር አንዳችም መፍትሔ እንደሌለው ነው ያሳየው። መንግሥት ስራውን በትክክል እንዲሰራ ነው የምንጠብቀው። ይህ ብቻ ነው ፀጥታ ሊያስገኝ የሚችለው። የአስቸኳይ ጊዜ የሚፈይደው ነገር የለም። »
የዚምባብዌ ላይላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሀምሌ ወር መጀመሪያ ላይ አጠቃላዩ ምርጫ በዚያው በሀምሌ 31፣ እንዲካሄድ ወሰነ። ከአምሥት ዓመት በፊት በሀገሪቱ በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ እንደሚታወሰው የተቃዋሚው ወገን ዕጩ ሞርገን ቻንጊራይ ካለፉት ሦስት አሠርተ ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን በሰፊ የመራጭ ድምፅ ነበር የመሩት። ይሁንና፣ የመለያው ምርጫ ሊደረግ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው እና ሙጋቤ በኃይሉ ተግባር መጠቀም ሲጀምሩ ቻንጊራይ የኃይሉ ተግባር እንዳይባባስ በመስጋት ዕጩነታቸውን ሰረዙ። ይህም ካለ ተፎካካሪ የቀረቡትን ሙጋቤ በሥልጣናቸው እንዲቆዚ አስችሎዋል። በዚህ ዓመቱ አጠቃላይ ምርጫም ወቅት ሙጋቤ በምርጫ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያለ ነገር መሆኑን ነበር ለተፎካካሪዎቻቸው ለማጉላት የሞከሩት።

« አንድ ሰው ራሱን ለአንድ ውድድር ካቀረበ ሁለት አማራጮች ብቻ መኖራቸውን አውቆ መግባት ይኖርበታል። ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ፤፣ ሁለቱን ማግኘት አይቻልም። ወይ ታሸንፋለህ ወይም ትሸነፋለህ። ከተሸነፍክ ሽንፈትህን መቀበል ይኖርብሀል። እና እኛ ይህንን እናደርጋለን፣ ደንቡንም እናከብራለን።
በይፋ በወጡ ውጤቶች መሠረት፣ ፈላጭ ቆራጩ ሙጋቤ በ2013 ዓምም ሥልጣናቸውን እንደገና ለማጠናከር ችለዋል፤ እንዲያውም በምክር ቤት ውስጥ ሕገ መንግሥቱን መቀየር የሚያስችላቸውን ፍፁሙን የመራጭ ድምፅ ነው ያገኙት።

በማሊ የቀድሞው ፕሬዚደንት አማዱ ቱማኒ ቱሬ መጋቢት 2012 ዓም በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሀገሪቱ ቀውስ ላይ ትገኛለች። በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሱት የቱዋሬግ ዓማፅያን እና አክራሪ ሙሥሊሞች ጥቃታቸውን አጠናክረው አካባቢውን በመቆጣጠር ሕዝቡን ማሸበር እና ወደ መዲናይቱ ባማኮም ግሥገሣቸውን በጀመሩበት ጊዜ ፈረንሳይ ማሊን ለመርዳት እና የዓማፅያኑን ሂደት ለማስቆም ባለፈው ጥር 2013 ዓም በጦር ኃይሏ ጣልቃ ገባች። ከፈረንሳይ ድጋፍ ያገኘው የማሊ ጦርም ያማፅያኑን ቱዋሬጎች ግሥገሣ በመግታት የተኩስ አቁም ደንብ እንዲደርሱ ማድረግ ከተሳካለት ብኋላ ባለፈው ሀምሌ ወር ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ተካሂዶ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ አዲሱ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዚደንት ሆነዋል።
«በኢግዚአብሔር እና በማሊ ሕዝብ ፊት በመቆም ማሊን በታማኝነት ለመከላከል እና ሥልጣኔንንም የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደምጠቀምበት ፣ ዴሞክራሲን ለመጠበቅ እና የብሔራዊ አንድነትን እና የሀገሪቱን ነፃነት፣ እንዲሁምየግዛት ሉዓላዊነቱን ዋስትና ለማረጋገጥ እንደምሰራ እምላለሁ። »
በዓመቱ የመጨረሻ ወራት ግን በማሊ በተለይ በሰሜኑ ውጥረቱ እንዳዲስ ተካሮዋል። በቱዋሬግ ዓማፅያን እና በጦር ኃይሉ መካከል በተደጋጋሚ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ዓማፅያኑ ባለፈው ሀምሌ የደረሱትን የተኩስ አቁም አፍርሰዋል። ውጥረቱ ቢካረርም ግን በማሊ የፕሬዝደንት ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ፓርቲ እና ተጓዳኞቻቸው ምክር ቤታዊውን ምርጫ ማሸነፋቸው ተገለጸ። አንድ የመንግሥቱ ባለሥልጣን እንዳስታወቁት፣ በእሁዱ ሁለተኛ ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ ራሱን ለማሊ የተቋቋመ የጋራ ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ፓርቲ እና ሸሪኮቹ 147 መቀመጫዎች ባሉት ምክር ቤት ውስጥ 115ቱን አግኝተዋል።

መስከረም 21፣ 2013 ዓም በኬንያ መዲና ናይሮቢ፤ አሸባሪዎች ዌስትጌት የተባለውን ግዙፍ መደብር አጥቅተው በርካቶችን ገድለዋው ብዙዎችን አቆሰሉ። ለጥቃቱ የሶማልያ አሸባብ ቡድን ኃላፊነቱን ወስዶዋል።« ኬንያውያን አሁን በዌስትጌት የገበያ መደብር የደ,ረሰባቸው ጥቃት የናንተ ጦር ለሚፈፅመው ወንጀል ማካካሻ ነው። »
ኬንያ ጦሯን ወደ ሶማልያ ከላከች ወዲህ ሶማሊያውያን አሸባሪዎች ኬንያ ውስጥ በተደጋጋሚ ጥቃ ጥለዋል። ከጥቃቱ በኋላ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ባሰሙት ንግግር በጥቃቱ ዘመዶቻቸውን እና የዝርቦቻቸውን ላጡት ሀዘናቸውን ገልጸዋል። «በዚህ ጥቃት የቤተሰብ አባላትን ላጡ ወገኖች ሃዘኔን እገልጻለሁ። ምን አይነት የሃዘን ስሜት ዉስጥ እንዳሉ መገመት አይሳነኝም፤ ምክንያቱም እኔም በዚህ ጥቃት በጣም ቅርብ ዘመዶቼን አጥቻለሁ»
ጥቃቱ በተጣለ በአራተኛው ቀን የኬንያ ወታደሮች ወደ መደብሩ በመግባታ አምሥት አጋቾችን ገድለዋል። በጥቃቱን 67 ገደሉ፣ 300 አቆሰሉ፣ ከ 60 በላይ የሚሆኑትም ደብዛቸው እንደጠፋ ነው። ሞዛምቢክ ውስጥ የርስበርሱ ጦርነት ካበቃ ከሁለት አሠርተ ዓመት በኋላ የቀድሞው ያማፅያን ቡድን b ሬናሞ የ16 ዓመቱን የርስ በርስ ጦርነት ያበቃውን እአአ በ1992 ዓም ከገዚው የፍሬሊሞ ፓርቲ ጋ በይፋ የተፈራረመውን ውል ባለፈው ጥቅምት 2013 ዓም ማፍረሱን አስታወቀ። ሬናሞ ይህን ርምጃ የወሰደው የመንግሥቱ ጦር የጦር ሠፈሩን በቦምብ ያጠቃበትንና የያዘበትን ድርጊት በመቃወም ነበር።
ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ መንግሥት የተቃዋሚው ቡድን አባላትን በብዛት ማሰር ከጀመረ ወዲህ ሬናሞ በምላሹ በፀጥታ ኃይላት ላይ ጥቃቱን በማጠናከር ዋነኛውን መተላለፊያ መንገድ ዘጋ፣ ብዙዎች ይህንን ሂደት በሀገሪቱ ከሁለት አሠርተ ዓመታት በፊት ታይቶ የነበረው ዓይነቱ የከፋ ቀውስ ሊነሳ እንደሚችል የሚጠቁም ሆኖ ተመልክተውታል።
« በስጋት መንፈሥ ውስጥ ነው የምንኖረው። እርግጥ፣ በዋናው መተላለፊያ መንገድ መዘጋት በቀጥታ ተጎጂ የሆኑት ሰዎች ርምጃው ያን ያህል እንዳላስጨነቃቸው ገልጸዋል። ይሁንና፣ ከዚሁ አካባቢ ጋ የተጎራበቱት ግዛቶች ሕዝብ ሞዛምቢክ እንደገና እርስ በርሱ ጦርነት ውስጥ ልትወድቅ ትችል ይሆናል በሚል መስጋቱ አልቀረም። »


እአአ ጥቅምት ሦስት፣ 2013 ዓም 500 የሚቆጠሩ ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ አቅራቢያ ሰጠመችበት አደጋ 390 ሞቱ። ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ስትጓዝ በሰጠመችው ጀልባ ከተሳፈሩት ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ ኤርትራውያን እና ሶማልያውያን ነበሩ። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አደጋ በደረሰበት ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ እጅግ ማዘናቸውን አስታውቀዋል።
« በዚህ ዛሬ በላምፔዱዛ እንደገና በደረሰው አሳዛኝ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን ሰለባዎች ማሰብ እፈልጋለሁ። አደጋው መድረሱ አሳፋሪ ነው። »
አደጋው የአውሮጳ ሀገራት በሚከተሉት የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲ ሰፊ ክርክር አስነስቶዋል። ፖለቲካኞች ለጀልባዋ መስመጥ ሕገ ወጦቹን ሰው አሸጋጋሪዎች ተጠያቂ አድርገዋል። በኢጣልያ የሚገኙት ኤርትራዊው ካቶሊካዊው ቄስ አባ ሙሴ ግን በፖለቲከኞቹ አስተሳሰብ አይስማሙም። እንደ እርሳቸው አስተያየት፣ ስደተኞቹ ሕይወታቸውን ለአደጋ ለሚያጋልጡበት ሁኔታ ሕገ ወጦቹ ሰው አሸጋጋሪዎች መንሥዔ አይደሉም። መንሥዔው በየሀገሮቻቸው ያለው ጨቋኝ ሥርዓት እና ምስቅልቅል ሁኔታ ነው ባይ ናቸው። « አውሮጳውያት ሀገራት በሕገ ወጦቹ ሰው አሸጋጋሪዎች አንፃር በርግጥ መታገል ከፈለጉ ብቸኛው አማራጭ ተገን ፈላጊዎቹ ወደ አውሮጳውያቱ ሀገራት በሕጋዊ መንገድ መግባት እንዲችሉ ድንበሮቻቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው። »
በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ በመንግሥቱ ጦር አንፃር የተዋጋው ራሱን «ኤም 23» ብሎ የሚጠራው ያማፅያን ቡድን አባላት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ከፊል ሕዝቡን ሲያሸብሩ ቆይተዋል። በኮንጎ ጦርና በ «ኤም 23» መካከል ውጊያው ተባብሶ ከቀጠለ እና በተለይ ያማፅያኑ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ቢያደርግም፣ በኮንጎ ሰላም አስከባሪዎች ያሠማራው የተመድ በውዝግቡ ጣልቃ መግባት አልቻለም ነበር፤ ምክንያቱም ተልዕኮው ስለማይፈቅድለት። በዚህም የተነሳ፣ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የሕዝቡን ስቃይ ለማብቃት ይቻል ዘንድ አንድ 3000 ወታደሮች የሰለፈ አጥቂ ቡድን ለመላክ ወሰነ። ጀርመናዊው ማርቲን ኮብለር የመሩት ይኸው ቡድን ወዲያው ከኮንጎ መደበኛ ሠራዊት ጎን በመሆን የጥታ ስጋቱን በማስወገዱ ተግባር ላይ ተሠማራ።
« ወደ ኮንጎ የመጣነው ለሕዝቡ ከለላ ለመስጠት ነው፤ ማለትም፣ በተለይ ለጎማ ሲቭል ሕዝብ ከለላ መስጠት ነው ዋናው ተልዕኳችን። በሲቭሉ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት እንዳይደገም ለማድረግ ስንልም ከኮንጎ ጦር ጎን በመሰለፍ በሚቻለን ሁሉ ባማፂው ቡድን አንፃር ወታደራዊው ዘመቻ አካሂደናል። »
በዚሁ የተመድ እና የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፑብሊክ ጦር የጋራ ዘመቻ «ኤም 23» ተሸንፎ እአአ ባለፈው ህዳር አምስት ናይሮቢ ኬንያ ላይ መንግስቱ ጋ የሰላም ስምምነት ተፈርሞዋል። ሁለቱ ወገኖች በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት አማፂዉ ቡድን ተዋጊዎቹን ትጥቅ በማስፈታት ራሱን ወደፖለቲካ ፓርቲነት መለወጥ እና የሰላም ስምምነቱ የ«ኤም 23» አባላት በጦነቱ ለፈጸሙት ጥፋት ምህረትን የሚያገኙበትንም መንገድ መመልከት ይኖርበታል


የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ሕገ ወጥ ያላቸውን የውጭ ዜጎች ከሀገሩ ለማስወጣት ከጀመረች ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ 140,000 የሚጠጉ ዜጎቹን ወደ ሀገር መመልሶዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸዉ ረዳ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸዉ ሳዉዲ ሚገኙት ዜጎች ወደሀገር መመለሱ ተግባር ቅድሚያ ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው የውጭ ዜጎች የሰጠው የሰባት ወር የምሕረት ቀነ ገደብ ባለፈው ህዳር ወር ካበቃ በኋላ ከፖሊስ ጋ በተፈጠረ ግጭት ሦስት ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የፈላስያን ጉዳዮች ተመልካች ድርጅት «አይ ኦ ኤም» በቅርቡ ከሪያድ፣ ከጄዳ እና ከመዲና ተጨማሪ 35,000 ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ብለው ይጠብቃሉ።
የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቀውስ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ባለፈው መጋቢት ፣ 2013 ዓም የሴሌካ ዓማፅያን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የቀድሞ የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ በሀገሪቱ በሚሼል ጆቶጂያ የሚመራ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞዋል። የታጠቁ፣ በብዛት ሙሥሊሞች የሆኑ የቀድሞዎቹ ያማፅያን ቡድኖች ብዙውን የሀገሪቱን ከፊል ተቆጣጥረዋል። እርግጥ፣ ከሽግግሩ መንግሥት ምሥረታ በኋላ የሀገሪቱ መሪ ሚሼል ጆቶጂያ ያማፀያኑን ቡድንኖች በመበተን በብሔራዊው ጦር ውስጥ ቢያዋህዱም፣ ትጥቅ ያልፈቱት በብዛት ሙሥሊሞቹ የቀድሞ ሴሌካ ዓማፅያን በርካታ መንደሮችን እያጠቁ በብዛት ክርስትያኑን ሲቭ ሕዝብ በማሸበር ላይ እንደሚገኙ ተገልጾዋል። ራሳቸውን ከሴሌካ ጥቃት ለመከላከል በተደራጁ የክርስትያን ሚሊሺያዎች እና ዓማፅያኑ መካከል በቀጠለው ግጭት ብዙዎች መገደላቸውን እና መፈናቀላቸው ተሰምቶዋል። ውዝግቡ ወደ ሀይማኖት እና ጎሳ ግጭት ሊቀየር እና በርዋንዳ የታኢ,ውን ዓይነት የጎሣ ጭፍጨፍ እንዳይከሰት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስጠንቅቀዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ባልደረባ የቡድኑን ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን አስጠንቅቋል።

« ሂውማን ራይትስ ዎች የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን በርካታ አስከፊ ወንጀሎችን መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ሰብስቦዋል። በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ በመዲናዋ ባነግዊን ጭምር የሚገኙት እነዚሁ ዓማፅያን ባሁኑ ጊዜ ከቁጥጥር ውጭ ሆነዋል። በመጨረሻ የመዘገብነው አሰከፊ ወንጀል በጋጋ አካባቢ፣ ኦምቤላምቦኮ በተባለ መንደር ሲሆን በዚያ የሴሌካ ዓማፅያን በመንደሩ ላይ ጥቃትበመሰነዘር በነዋሪዎቹ ላይ እጅግ አስከፊ ወንጀል ፈፅመዋል። »
ይህን ተከትሎ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትየቀድሞ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ፍሪቃዊቱ ሀገር ያለውንከ3500 ወደ 6000 ከፍ ይላል የሚባለውን የአፍሪቃ ህብረት ጓድ እንዲጠናክር ያቀረበችው ማመልከቻን አፅድቋል። በዚህም መሠረት በዚያ 600 ወታደሮች ያሉዋተ ፈረንሳይ ተጨማሪ 1000 ልካለች። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የፈረንሳይና የአፍሪቃ ኅብረት ኃይሎች ቢገኙም የሰላማዊ ሰዎች ግድያ አልቆመም።

የቀድሞውን የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት እና እውቁ የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እአአ ታህሳስ አምሥት 2013 ዓም በ95 ዓመታቸው ማረፋቸውን የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ በይፋ አስታወቁ። የነፃነት እና የመቻቻል ተምሳሌት ሆኑትን ለኔልሰን ማንዴላ ሶዌቶ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኝ ስታድዮም በተደረገው ይፋ ስንብት ላይ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የዓለም መሪዎች፤ ቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጆቻቸው እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ከመላው ደቡብ አፍሪቃ የመጣ ህዝብ ተገኝቶ ነበር፣ ከዚያም የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ለሦስት ቀናት በፕሪቶርያ ከተወዳጁ መሪው ስንብት ካደረገ በኋላ ሥርዓተ ቀብራቸው በትውልድ መንደራቸው ኩኑ 4,500 ሰዎች፣ በርካታ መሪዎች ጭምር በተገኙበት ተፈፅሞዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ነፃነቷን ባገኘች ደቡብ ሱዳን ውስጥ በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር ታማኝ ወታደሮች መካከል ካለፈው እሁድ ወዲህ ውጊያው ቀጥሎዋል። በመዲናይቱ ጁባ ብቻ ከ500 የሚበልጥ ሰው መገደሉ እና በርካቶች መቁሰላቸው ተሰምቶዋል። ከ16000 የሚበልጡም መፈናቀላቸው ተገልጾዋል።
ስለመዲናይቱ ጁባ ወቅታዊ ሁኔታ አስተያየት የሰጡት በዚያ ያሉት የተመድ ሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ ቶቢ ላንዛ ሲቭሉ ሕዝብ ለደህንነቱ መስጋቱን ገልጸዋል።
« በአሁኑ ጊዜ ጁባ ውስጥ ሁኔታው ጥቂት ተረጋግቶዋል። 16,000 ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ግን የተመድ ሰላም አስጠባቂዎችን ከለላ ለማግኘት ሲሉ በከተማይቱ ባሉት ሁለት ሠፈሮቻችን ውስጥ ወይም በዚያው አቅራቢያ ይገኛሉ። እንደሚመስለኝ ውኃን የመሳሰሉ መሠረታዊ ርዳታዎች ጭምር ያስፈልጋቸዋል። »
ሳልቫ ኪር ማቻርን ከከሸፈ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ሁከት እንዲባባስ አድርገዋል ሲሉ ይወቅሳል። አሁን ከመዲናይቱ ጁባ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋው ውጊያ ደቡብ ሱዳንን በጎሣ ከፋፍሏታል።
አርያም ተክሌ
ልደት አበበ
Source: www.dw.de

አብዛኞቻችን የመዝገበ ቃላትን አጠቃቀም የተማርንበትንእንግሊዝኛ -አማርኛ መዝገበ ቃላት››
ያዘጋጁት ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ 83 ዓመታቸው ታኅሣሥ 11 ቀን 2006 ዓም ዛሬ ዐረፉ፡፡ ዶክተር አምሳሉ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከሚባልበት ዘመን ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩ መምህር ነበሩ፡፡
Source: http://www.danielkibret.com/
የሰሜን ሱዳን የፖለቲካ ተጽእኖና ፤ የዐረብ ባህል ጫና አንገሽግሾት 22 ዓመታት መሪር ትግል ያካሄደው የደቡብ ሱዳን ህዝብ፤ ነጻነት ባወጀ በ 2 ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ወደ አስከፊ የእርስ በርስ ውጊያ እንዳያመራ አሥግቷል። ባለፈው እሁድ በመዲናይቱ 
በጁባ ያገረሸው ውጊያ ፣ የ 500 ያህል ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ ፤ 34,000 ሰዎች፤ በተባበሩት መንግሥታት ጣቢያዎች መጠለያ እንዲሻ አስገድዷል ። የሥልጣን መቀናቀን ነው የተባለለት ውዝግብ ፣ በጎሣ ልዩነት ተካሮ ባፋጣኝ ወደሌሎች አካባቢዎች መዛመቱ የሚታወስ ነው። ጉዳዩ ያሳሰባቸው የምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት ሚንስትሮች ፤ የአፍሪቃ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች ጁባ ውስጥ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት
ሳልባ ኪር ጋር በዛሬው ዕለት እንደሚወያዩ ይጠበቃል። ስለደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ይዞታ ፣ በፀጥታ ጉዳይ ተቋም፤ (ISS)የምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በማነጋገር የተጠናቀረው ዘገባ የሚከተለው ነው።
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ምክትላቸውን ሪኤክ ማቻርን ከስልጣን ካሰናበቱ ወዲህ ቁርሾው አይሎ፣ የሥልጣን ሽኩቻው ባለፈው እሁድ መፈንዳቱ የሚታወስ ነው። የጎሣ ልዩነትን ብቻ መሠረት ባደረገ በዚያ የተኩስ ልውውጥም ሆነ የኃይል እርምጃ፤ ብዙ ሰዎች ያላበሳቸው የጥይት ራት የሆኑበት ድርጊት የተባበሩትን መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኀላፊ ናቪ ፒላይን እጅግ እንዳሳዘነ ተመልክቷል። ራሳቸው የተ መ ድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፤ በበኩላቸው ፣ ውዝግቡ ባስቸኳይ በፖለቲካ ውይይት መላ እንዲፈለግለት ነው ያስገነዘቡት።
አንዳንድ የ ምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት (IGAD) አባል ሃገራት ውዝግቡን በቀላል ሊፈታ እንደሚችል በተስፋ ይሁን ዲፕሎማሲያዊ ፈሊጥ አድርገው ያን ያህል የሚያሳስብ እንዳልሆን መግለጫ ቢሰጡም፤ ተጨባጩ ይዞታ የሚያረጋጋ ሆኖ አልተገኘም። አንዳንድ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት አኤሮፕላኖች ን በመላክ ላይ ናቸው። አሶኬ ሙከርጂ የተባሉት ህንዳዊ የተባበሩት መንግሥታት ልዑክ፤ 3 ህንዳውያን ሰላም አስከባሪዎች፤ ሆን ተብሎ የጥይት ዓላማዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ዩጋንዳ ዜጎቼን ለመጠበቅ ነው በሚል ሰበብና ከጁባ መንግሥትም ጥሪ ቀርቦልኝ ነው በማለት ፤ በዛሬው ዕለት በደቡብ ሱዳን መዲና ጦር ሠራዊት አሠማርታለች። ትናንት ብርቱ ማስጠንቀቂያ ያሰሙት የዩናይትድ እስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ 45 ወታደሮቻቸው እንዲሠማሩ አድርገዋል። የዚህ ያልተጠበቀ መስሎ የቆየው ውዝግብ ፍንዳታ ዋና መንስዔው ምን ይሆን? ዋና ጽ/ቤቱ በፕሪቶሪያ ፤ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው የፀጥታ ጉዳይ ተቋም ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አንድርውስ አታ አሳሞዋ--
\ «ጉዳዩን ሰፋ አድርገን ካየነው፣ በፕሬዚዳንቱ ክብር ዘብ የተፈጠረ ምሥቅልቅል፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ክፍፍል አሥፍቶታል። የጎሣ ልዩነትም እንዲጎን ነው ያደረገው። ቀስ በቀስምየጎሳ ልዩነትን በማባባስ፣ በፖለቲካው አመራር ለረጅም ጊዜ የቆየውን ክፍፍል በጦር ሠራዊቱና በብሔረሰቦችም ዘንድ ጥርጣሬውን ያባብሰዋል። ይህ ደግሞ፣ አገሪቱ ነጻነት ከማወጇ በፊት አንስቶ ብዙዎች ሲፈሩት የነበረውን ውዝግብ እውን ሊያደርገው በቅቷል።»

ደቡብ ሱዳን እ ጎ አ ከ 1983-2005 ባካሄደችው የ 22 ዓመታት መሪር የትጥቅ ትግል ከ 2 ሚሊዮን በላይ ተወላጆቿን እንዳጣች ነው ታሪኳ የሚያስረዳው። ስለሆነም ሰፊ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ አሁን እርስ በርስ እንዳይፋጅ ያሠጋበት አደጋ ስለመኖሩ በሚነገርበት ወቅት ውዝግቡ በቀላል እንደሚፈታ መገመት ይቻላል?
«ሳልቫ ኪርንና ሪኤክ ማቻርን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ማምጣቱ ከሞላ ጎደል ቀላል ሊሆን ይችላል። ይህ ግን ሁለቱን የፖለቲካ መሪዎች ወይም ተቀናቃኞች የሚመለከት ነው። ግን ፤ ጉዳዩ የዲንካና የኑኤር መቀናቀን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በፖለቲካው መስክ በከፍተኛ አመራር ላይ ባሉት ቅራኔውን እንደምንም ማርገብ ቢቻል እንኳ በሀገሪቱ በመላ ሲብላላ የቆየው ችግር እንደምናስበው በቀላሉ ሊወገድ የሚችል አይደለም።»
የደቡብ ሱዳንን ውዝግብ፣ የካርቱምን መንግሥት በጥሞና ነው የሚመለከተው። በአንድ በኩል ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር የሚወያዩባቸው አንዳንድ ዐበይት የጋራ ጉዳዮች በአንጥልጥል እንዲቀሩ አይሻም። በሌላ በኩል የካርቱም መንግሥት ለአፈንጋጩ ሪኤክ ማቻር ሊያደላም ሆነ ሊደግፍ እንደሚችል የሚናገሩ አሉ። በደቡብ ሱዳን የተፈጠረው ውዝግብ እንዲወገድ ተጽእኖ በማድረግም ሆነ በመሸምገል መፍትኄ ሊያፈላልጉ የሚችሉ አገሮች ን መጥቀስ ያቻላል?

«የአካባቢው አገሮች፤ ዩጋናዳ ኬንያና ኢትዮጵያ ጁባን በሰፊው ማግባባት የሚችሉ ናቸው። ጎረቤቶች ስለሆኑ ብጻቻ አይደለም። ሰሙኑን ሳያገልሉ፣ በጦርነቱ ወቅት የተጫውቱት ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው። ደቡብ ሱዳን ለአነዚህ አገሮች ዐቢይ ከበሬታ ነው ያላት። ብዙዎች ደቡብ ሱዳናውያን፤ ኬንያን በአስተናጋጅነቷ ብቻ ሳይሆን ፤ ብዙ የሚያቀራርቧቸው ጉዳዮች እንዳሉም ይሰማቸዋል። ያም ሆነ ይህ «ኢጋድ» በመሪነት መላ ቢሻ በጣም ጥሩ ነው፤ ይሁንና ዩጋንዳን የመሳሰሉ አገሮችም ለደቡብ ሱዳን መልሶ ሰላም ለማስገኘት በከፍተኛ ደረጃ ተሰሚነት ያላቸው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።»
ተክሌ የኋላ
ሸዋዬ ለገሠ
Source: www.dw.de

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ፕሬዝዳት ኪየር የሚወለዱበት የዲንካ እና ማቼር የሚወለዱበት የኑዌር ጎሳዎች መልክ እና ባሕሪ የያዘዉ ዉጊያ ፈጣን መፍትሔ ካላገኘ አደገኛ ነዉ።ደቡብ ሱዳን፥ ነፃነት ያወጀችበትን ሁለተኛ ዓመት-ከመንፈቅ፥ ከረጅም ጦርነት የተላቀቀችበትን ሥምንተኛ ዓመት፥ እነሆ በጦርነት ልታከብር ዉጊያ ጀምራለች።
የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጦር እና በመንግሥት ላይ ያመፁት ሐይላት ወታደሮች ባለፈዉ ዕሁድ ርዕሠ-ከተማ ጁባ ዉስጥ የጀመሩት ዉጊያ ወደ ሌሎች የሐገሪቱ አካባቢዎች እየተዛመተ ነዉ።የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት የሪክ ማቼር ታማኞች የተባሉት ሐይላት ዛሬ ቦር የተባለችዉን ከተማ ተቆጣጥረዋል።በሌሎች አካባቢዎችም ዉጊያዉ መቀስቀሱ ተዘግቧል።የዉጪ መንግሥታት ዜጎቻቸዉን ከአዲሲቱ ሐገር እያሰወጡ ነዉ።ለግጭቱ ሠላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት የአካባቢዉ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸዉን ወደ ጁባ ልከዋል።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

አዲሲቱ አፍሪቃዊት ሐገር ነፃነትዋን ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ በርግጥ ዉጊያ ጦርነት ተለይቷት አያዉቅም።የእስካሁኑ ጦርነት ዓለም ፈጥኖ-ጣልቃ ለመግባት፥ አለያም ከዋሽግተን፥ ብራስልስ ብዙ ጊዜ እንደሚሰማዉ ካርቱሞችን ደፍሮ ለማዉገዝ የሚጣደፍበት ነበር።ወይም «የጎሳ ግጭት» ብሎ የሚያቃልለዉ ዓይነት።ያሁኑ ከመጀመሪያዉ ይልቅ-ሁለተኛዉን፥ ከሁለተኛዉ ይበልጥ ደግሞ የፖለቲካ ሽኩቻ፥ የሥልጣን ሽሚያ፥ እና የርስ-በርስን ጦርነት መልክ እና ባሕሪ የተላበሰ ነዉ።

እርግጥነዉ የወቅቱን የአፍሪቃ ሕብረት እና የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በእንግሊዝኛ ምሕፃረ-ቃሉ የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዘችዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸዉ ረዳ ግጭቱ በመገናኛ ዘዴዎች እንደሚዘገበዉ አይደለም ይላሉ።
ከጁባ፥ ከካምፓላ፥ ከናይሮቢ የሚወጡ ዘገቦች ግን ተቃራኒዉን ነዉ የሚሉት።ዕሁድ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ተላብሶ ጁባን እስከ ትናንት ባናወጠዉ ዉጊያ በትንሽ ግምት ከስድስት መቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ወደ ሃያ ሺሕ የሚጠጉ አንድም ተሰደዋል፥ አለያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጥር ግቢዎች ሙጥኝ ብሏል።
ዛሬ ርዕሠ-ከተማይቱ ዉጊያዉ ጋብ፥ ቀለል ሲልላት ቦርን ይለብቃት ይዟል።የመንግሥት ጦር ቃል አቀባይ ፊሊፕ አጉዋር ጦራቸዉ ቦር ላይ መሸነፉን ዛሬ ጠዋት አምነዋል።ቃል አቀባዩ እንዳሉት ቦርን የሚቆጣጠረዉ የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት የሪክ ማቻር ታማኞች ናቸዉ።
በ2011 በመንግሥት ላይ አምፀዉ ኋላ ተደራድረዉ የመንግሥት ጦርን ተቀላቅለዉ የነበሩት ሐይለኛ የጦር ጄኔራል ፒተር ጋዴት ማቼርን ደግፈዉ ጆንግሌይ የሠፈረዉን የመንግሥት ጦር ማጥቃት ይዘዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ቶሪት የተባለችዉ ከተማም በዉጊያ እየራደች ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ፥ ብሪታንያ እና ሌሎችም ምዕራባዉያን ሐገራት ተፋላሚዎችን ከመሸምገል በፊት ሁሌም-እንደሚያደርጉትን የዜጎቻቸዉን ሕይወት ለማትረፍ ከዚያ ማስወጣቱን አስቀድመዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ጌታቸዉ ረዳ እንዳሉት መንግሥታቸዉ እንደሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ ዜጎቹን ባያስወጣም የጥንቃቄ እርምጃ እየወሰደ ነዉ።


ፕሬዝዳት ሳላቪ ኪር እና ኪር ከሥልጣን ያስወገዷቸዉ የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ሪክ ማቻር እንደጫሩት የሚታሰበዉን እሳት ለማጥፋት «አንድ ሁለት» ማለት የጀመሩት የኢጋድ አባል ሐገራት ናቸዉ።ኢትዮጵያ፥ ኬንያ፥ ጀቡቲ እና ዩጋንዳ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸዉን ወደ ጁባ ልከዋል።
የሚንስትሮቹ ተልዕኮ ሁኔታዉ «እንዳይባባስ መግታት» ከሚል ጥቅል መግለጫ በስተቀር ዝር ዝር ጉዳዩ አልተነገረበትም።መፈንቅለ መንግሥት በማሴር የተወነጀሉት የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ማቼር ያሉበት ሥፍራ አይታወቅም።በመፈንቅለ መንግሥቱ የተጠረጠሩ አስር የቀድሞ ባለሥልጣናት እና ፖለቲከኞች ታስረዋል።አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ሚንስትሮቹ ምናልባት ተፋላሚዎችን ለማደራደር ይሞክሩ ይሆናል።አቶ ጌታቸዉ ግን ይሕን ማረጋገጥ አልፈለጉም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ፕሬዝዳት ኪየር የሚወለዱበት የዲንካ እና ማቼር የሚወለዱበት የኑዌር ጎሳዎች መልክ እና ባሕሪ የያዘዉ ዉጊያ ፈጣን መፍትሔ ካላገኘ አደገኛ ነዉ።ማም-ምን አለ ምን ደቡብ ሱዳን፥ ነፃነት ያወጀችበትን ሁለተኛ ዓመት-ከመንፈቅ፥ ከረጅም ጦርነት የተላቀቀችበትን ሥምንተኛ ዓመት፥ እነሆ በጦርነት ልታከብር ዉጊያ ጀምራለች።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ
Source: www.dw.de
 
በፓሪስና በኒው ዮርክ የሚገኙት ፣ ድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF) እና ለጋዜጠኞች ህልውናና መብት ተሟጋቹ ፤ (CPJ)፣ በዓለም ዙሪያ የጋዜጠኞችን ፍዳ የሚዘረዝረውን ዓመታዊ መግለጫቸውን ይፋ አደረጉ። ለመገባደድ 2 ሳምንት ገደማ በቀረው 2013 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት
ውስጥ 71 ጋዜጠኞች መገደላቸውናና 178 በእሥራት በመማቀቅ ላይ እንደሚገኙ የወጣው ዘገባ ያስረዳል። ጋዜጠኞችን አሥሮ በማሠቃየት ከተወቁት 10 ሃገራት መካከል፤ ኤርትራ ፣ ኢትዮጵያ፤ግብፅ ፣ ቪየትናም፤ ሶሪያ ፤ አዘርባጃንና ዑዝቤኪስታን ይገኙበታል። በአፍሪቃው ቀንድ የጋዜጠኞችን ይዞታ የሚከታተሉትን ፤ በምሥራቅ አፍሪቃ የ CPJ ን ተጠሪ በማነጋገር ፤ ተከታዩን ዘገባ አቅርበናል።
በሥራ ላይ እንዳሉ ጋዜጠኞች ሕይወታቸውን ያጡባቸው አካባቢዎች ፤ እስያ፤ (24 ናቸው የተገደሉት፤)መካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪቃ (23) ከሰሐራ ምድረ በዳ በስተደቡብ በሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት አምና 21 እንደተገደሉ ሲታወቅ ዘንድሮ ከሞላ ጎደል በግማሽ ቀንሶ (10) ጋዜጠኞች
ናቸው ሕይወታቸውን የገበሩት። ግድያው በአመዛኙ ፍልሚያ በሚካሄድባት ሶማልያ ነው የተፈጸመው። አምና 18 ፤ ዘንድሮ 7!
በአፍሪቃው ቀንድ ፤ በእሥራት የሚማቅቁት ቁጥር ቀላል አይደለም። ስለሆነም CPJ ቢ,ታሠሩ ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ከመጠየቅ አልቦዘነም፣ የአፍሪቃውን ቀንድ፤ በተለይ የኢትዮጵያ ን የኤርትራንና የጂቡቲን ጋዜጠኞች ይዞታ እንዴት እንደሚገመግሙት ፤ የ CPJ ውን ተወካይ ቶም ሮደስን በስልክ ጠይቄአቸው ነበር።
«ሂደቱ ፤ አዝማሚያው ፤ የሚያሳዝን ነው፤ አለመታደል ሆኖ ባለፉት ዓመታት የታዘብነው ነው እንደቀጠለ ያለው። ከሰሐራ በስተደቡብ በሚገኙ አገሮችን አያያዝ፣ በዛ ያሉ ጋዜጠኞች የመታሠራቸው ጉዳይ የአፍሪቃው ቀንድ ይዞታ ፤ የአፍሪቃ ሕብረት አያኢዝ ተምሳሌት ነው።»
CPJ, RSF, እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ AI ,HRW ስለጋዜጠኞችም ሆነ በአጠቃላይ ስለሰብአዊ መብትና የፕረስ ነጻነት እንደሚቆረቆሩ የሚሰማ ጉዳይ ነው። ተሰሚነት ያላቸው እዚህ ላይ አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት ፣ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል ይላሉ?


«ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሣህ፤ ግን ጥሩ መልስ አላገኝልህም። ልክ ነህ፤ CPJ ፤ RSF እና ሌሎች ያለማቋረጥ፤ ብዙዎች ጋዜጠኞች መታሠራቸውን እናወግዛለን። የወረበባቸውንም ክስ አጠያያቂ አድረገን ነው የምንመለከተው። ለምሳሌ የኤርትራውን ብትመለከት፣ በ 22 የክስ አንቀጾች የተከሰሱት ሰዎች ጉዳይ ሲመረመር ፣ አንዳችም ፍርድ ቤት ክስ አልተመሠረተባቸውም። እነዚህን መንግስታት በተቻለ መጠን እንሟገታቸዋለን።
ህጋዊ ምርመራ እንዲካሄድ እንደጠይቃለን፤ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የተደረገው ዓይነት ማለት ነው፤---። ግን ይህ በቂ አይመስለኝም። በመጨረሻ ፍትሕ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅናል። ብዙዎች፤ በሚያሠቅቅ ሁኔታ ነው እሥር ቤት ውስጥ የሚገNUት። ታሣሪዎቹ ጋዜጠኞች፤ ሊፈቱ በሚችሉበት ተስማሚ መፍትኄ ከመንግሥት ጋር ለማግኘት ከዚህ የላቀ ተግባር ማከናወን ይጠበቅብናል።»
ዋና ጽ/ቤቱ በኒውዮርክ የሚገኘው ለጋዜጠኞች ደህንነት የሚታገለው ድርጅት CPJ የአፍሪቃው ቀንድ ጉዳይ ተመልካች ቶም ሮደስ ፤ በደል የፈጸሙ ሰዎች ከመከሰስ ነጻ የሆኑበትን አሠራር እስመልክተው እንዲህ ነበረ ያሉት።


« CPJ ዘመቻ ከሚያካሂድባቸው ጉዳዮች አንዱ በደል ፈጽሞ በቸልታ መታለፍን ነው። እናም መንግሥታት፤ ያወጡትን ሕግ አክብረው መብት እንዲጠበቅ ያደርጉ ዘንድ ነው የምናስገነዝባቸው። እንደሚመስለኝ፤ችላ መባል ነው፤ በአፍሪቃው ቀንድ ዘገባችን እንደሚያመለክተው ብዙ ጋዜጠኞች እንዲታሠሩ ያደረገው።»

ተክሌ የኋላ
ሸዋዬ ለገሰ
Source: www.dw.de
የሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ከእሁዱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ዛሬ መረጋጋትዋ ተዘግቧል ። ነዋሪዎች ዛሬ ከቤታቸው መውጣት ጀምረዋል ። አልፎ አልፎ ተኩስ መሰማቱ ግን አልቆመም ። መንግሥት እንዳስታወቀው ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 10 ሰዎችን አስሯል ። 
ተዘግቶ የቆየው የጁባ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲከፈት መንግሥት ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም አንዳንድ አየር መንገዶች ወደ ጁባ ከመብረራቸው በፊት የፀጥታ ዋስትና ጠይቀዋል ። ዩናይትድ ስቴትስ ዜጎቿን ማስወጣት እንደምትጀምር አስታውቃለች ። በደቡብ ሱዳን የኃይል እርምጃ ማገርሸቱ የሃገሪቱን የዴሞክራሲ ተስፋ እንዳያሰናክል አስግቷል ። በጎሳ የተከፋፈሉ የደቡብ በሱዳን ጦር ሠራዊት አባላት ባለፈው እሁድ ለሊት ጁባ አቅራቢያ ከተታኮሱ በኋላ የተፈጠረውን መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ብሎታል ።
በዚያን ለሊት የሆነው ግን እስካሁን ግልፅ አይደለም ። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እንደ ሁል ጊዜው ጥቁር ሱፍና የተለመደውን ኮፊያቸውን አድርገው ሳይሆን የወታደር ልብስና መለዮ አጥልቀው ከትናንት በስተያ በሰጡት መግለጫ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ባለፈው ሐምሌ ከሥልጣን በተወገዱት የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማሻር ታማኞች መካሄዱን አስታውቀዋል ። ይሁንና ማሻር ዛሬ ታትሞ ለወጣ አንድ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ ክሱን አስተባብለው ይልቁንም ፕሬዝዳንት ኪር ደፈር ብለው የሚናገሯቸውን ለማስወገድ አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው ያሳወቁት ። ፕሬዝዳንንት ኪር በመግለጫቸው ጥቃት የሰነዘሩት ሸሽተው ጦር ኃይሉ እየተከታተላቸው መሆኑንም ተናግረዋል ። ከዚሁ ጋር በተቀናቃኞቻቸው ላይ ፍትህ ድል ያደርጋል ማለታቸው ታዛቢዎቻቸውን አስግቷል ። በደቡብ ሱዳን የኃይል እርምጃ ማገርሸቱ ጀርመናዊቷ የሱዳን ጉዳዮች አጥኚ አኔተ ቬበር እንደሚሉት በሃገሪቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ወደ ወታደራዊ አማራጮች የመሄድ ልምድ መኖሩን ነው የሚያመለክተው ።
« የንቅናቄዎቹ ቅርፅ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ይፈቅዳል ። ይህ የሱዳን ፖለቲከኞች ትውልድ በጦርነትና በግጭት የፈጀው ጊዜ ሲታይ ፣ እንዳለመታደል ሆኖ ይህ የሚያሳየው ሊያደርጉ የሚችሉት ይህ ብቻ መሆኑን ነው ። ይኽውም ግጭቶችን በወታደራዊ መንገዶች መፍታት ነው ።»
እስካሁን የደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በቀድሞው አማፂ ቡድን በሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ በምህፃሩ SPLM የበላይነት ነው የሚመራው ። ከሱዳን ፓርላማ 90 በመቶው በላይ መቀመጫ በነዚሁ ፖለቲከኞች ነው የተያዘው ። ጦር ሠራዊቱ ፖሊሲና ቢሮክራሲውም ቅርበቱ ለዚሁ የፖለቲከኞች ድርጅት ነው ። ምንም እንኳን በይፋ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተዘርግቷል ቢባልም እስካሁን አንዳችም አማራጭ የፖለቲካ መንገድ አልታየም ።
የጁባ መንግስት ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር በተያያዘ 7 የቀድሞ ሚኒስትሮችን ጨምሮ 10 ሰዎችን ማሰሩን አስታውቋል ።የቀድሞውን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪካ ማሻርን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችንም ለጥያቄ እፈልጋቸዋለሁ ብሏል ። ከሥራ የተባረሩት የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ማሻር ሰዎች ባለፈው ታህሳስ መግቢያ ላይ ሳልቫ ኪርን አምባገነን ሆነሃል ብለው ዘልፈው ነበር ። በዚሁ ወቅት አዲስ ምርጫ እንዲጠራም ጠይቀዋል ። ይሁንና ኪርና ደጋፊዎቻቸው ያኔ ጥሬያቸውን ወደ ጎን በመተው ይልቁንም ተቃዋሚዎቹ ሃገሪቱን ካበላሹት ሙሰኞች መካከል ናቸው ሲሉ ወንጅለዋቸዋል ። በአሁኑ
  Salvakarሳልቫ ኪር
የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም ኪር ወዲያውኑ የወነጀሉት እነዚህኑ ሰዎች ነው ። ከመካከላቸው የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ና የSPLM ዋና ፀሃፊን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አሁን ታስረዋል ። የቀድሞው የSPLM መሪ የሟቹ የጆን ጋራንግ ባለቤት ሬቤላ ጋራንግ ንያንዴንግ ከማክሰኞ አንስቶ በቁም እስር ላይ ናቸው ። ከፈረንሳይ ብሔራዊ ሳይንሳዊ የምርምርና ልማት ማዕከል የፖለቲካ ተንታኝ ማርክ ላቬርኝ በSPLM ውስጥ ችግር የፈጠረው የፖለቲካ መቃቃር ብቻ ሳይሆን የጎሳ ልዩነትም ጭምር መሆኑን ያስረዳሉ
« SPLM ውስጥ ትልቁ ለውጥ የተከሰተው በ1991 ነው ። ያኔ ሳልቫ ኪርና ሪክ ማቻር በጠላትነት ነበር የሚተያዩት ። ይህም 100 ሺህ ሰዎችያለቁበትን የርስ በርስ ጦርነት አስከትሏል ። ከፖለቲካው ሽኩቻ በተጨማሪ በአናሳዎቹ በኑዌሮችና በብዙሃኑ በዲንቃዎች መካከል የጎሳ ግጭት አለ ። የሁለቱም ጎሳ የቋንቋና የዘር ሃረግ ናይል ሲሆን ሁለቱም ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ ከብት አርቢዎች ናቸው ። ሁለቱም የሚቀራረቡና በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙ ወነኛ ቡድኖች ናቸው ። »
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመዲናይቱ ከጁባ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ትናንት እንዳስታወቀው ሁለት ሆስፒታሎች በሰሞኑ ግርግር ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን ተመዝግበዋል ። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ዲፕሎማት የቆሰሉት ቁጥር 800 መድረሱን ተናግረዋል ።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ
Source: www.dw.de
:
፩. ምክንያተ ጽሕፈት
ይስማዕከ ወርቁ በቅርብ ጊዜ ባሳተመው ‹ተከርቸም› በሚለው 6ኛ መጽሐፉ ‹እልፍ(፼) ዐሥር ሺህን ሳይኾን አንድ ሺህን ይወክላል› የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡ እኔም በመጽሐፉ ያቀረበውን የእልፍ(፼) ቁጥር አስተያየት ከተመለከትኩ በኋላ መስተካከል ያለበት ጉዳይ መስሎ ስለተሰማኝ ይህንን ጽሑፍ በተወሰነ ደረጃ ሞነጫጭሬ አስቀምጨው ነበር፤ በዕንቁ መጽሔት ተጠይቆ የሰጠውን መልስ ከተመለከትኩ በኋላ ግን መከራከሪያ ነጥቦችን ማቅረብ አስፈላጊ መስሎ ታየኝ፡፡
ምክንያቱም በእኔ ዕይታ የይሰማዕከ የ‹እልፍ አንድ ሺህ ነው› ውሳኔያዊ መጣጥፍና አጠቃቀም ሁለት አንድምታዎች አሰምቶኛል፡፡ አንድኛ ከዚህ በፊት የታተሙት የሊቃውንት መጻሕፍት የግዕዝ ቁጥር አጠቃቀም ስህተት መኾን ይጠቁማል፡፡ ይህ አንድምታም  ‹የሀገራችን ሊቃውንት የግዕዝ ቁጥር ዕውቀት የላቸውም› የሚል ትርጓሜንም ያመጣል፡፡ ይህንን ደግሞ ‹እነዚህ ሕዝቦች እስከ ሺህ ድረስ አልቆጠሩም እንደ?› ያስብለናል እና ‹ቀና ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ› የሚሉት የይስማዕከ አገላለጾቹ ምስክር ናቸው፡፡ ስጋቱ ቢገባኝም ‹ከኛ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው› ዓይነት አቀራረቡ ግን አስተዋይነት ያለው አልመሰለኝም፡፡ ስለዚህ ጥረቱ መልካም ቢኾንም ያላስተዋላቸው ነጥቦች ስላሉ እንዲያጤናቸው እና ሌሎችም ትክክል መስሏቸው የቁጥር አጠቃቀማችን እንዳያዛቡ በሚል አመለካከት ይህንን አስተያየት አቀረብኩ፡፡

፪. በእንተ ይስማዕከ
በመሠረቱ በግሌ ይስማዕከን ከሚያከብሩትና ከሚያደንቁት ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፎቹ የሚያቀርባቸው ሀገራዊ ዕይታዎች ይማርኩኛል፡፡ ለምሳሌ ‹ደርቶጋዳ› የሚለውን መጽሐፉን እንዳነበብኩ ‹ከፍቅር እስከ መቃብር ቀጥሎ 2ኛ ምርጥ የልብ ወለድ መጽሐፍ› ብዬ ለመናገር ደፍሬ ነበር፡፡ ይኸኛው ‹ተከርቸም› የሚለው መጽሐፉም ቢኾን በውስጤ የሚያስቆጨኝን ሐሣብ ይዞ ስለቀረበ ነው መሰል አስደስቶኛል፡፡ እስቲ ለማሳያ እንዲኾነኝ ከዚህኛው መጽሐፍ ልጥቀስ፡-
‹‹ከግድግዳው ጥግ አፉን የከፈተውን ትልቅ ጉድጓድ አይተው፡
‹ስብሐት ለአብ! የምን ጉድጓድ ነው?› አሉ፡፡
‹ለጋን ማስቀመጫ ብዬ ነው፡፡›
‹ታዲያ ይህንን ያህል?›
‹ጋኔ ትልቅ ነው፡፡ ለነገሩ ይህንን ያህል መቆፈር አልፈለኩም ነበር፡፡ ትንሽ ስቆፍረው ተደረመሰና ሰፊ ኾነብኝ፡፡›
‹እንዲያስ ከኾነ በደንብ በቆፈርሽ!›
‹እንዴት?›
‹ብር ወይም ወርቅ ተቀብሮበት ቢኾንስ!›
ኧረ? ማን ሊቀብረው እዚህ ላይ!›
‹አይ ልጄ አባቶቻችን’ኮ ብዙ የቀበሩልን ሀብት ነበር፡፡ ነገ ዛሬ ሲሉ ሳያሳዩን አለቁ እንጂ! ሞት ቀደማቸው! ታሪካችን፣ ሀብታችን ሁሉ እንደ አፅማቸው መሬት ውስጥ ኾነ፡፡ ለማን ይናገሩት? ትውልዱ ሁሉ መና ኾነባቸው፡፡ እኛማ እንኳንስ ለነገ ልንቀብር የዕለት ከርሳችን ከረጢት አልሞላ እያለን ስንዛግጥ እንውላለን፡፡ ስንታክት ኖረን ሳይሳካልን መትነን! ኸረ ወዲያልኝ!› አሉ ጭራቸውን ሽው አድርገው፡፡››
የሚገርመው ታዲያ ቆፋሪዎቹ ጉድጓዱ ያዘጋጁት ሰውየውን (አባ ሰባጋዲስን) ሊቀብሩበት መሆኑ  ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ መለኩሴው ቅርስ አላዘርፍ ስላሏቸው ደብዛቸውን በማጥፋት እና የቅርስ ቤቱን  ቁልፍ ወስደው ቅርሱን በመዝረፍ ለፈረንጆች ለመሸጥ ነው፡፡ በዚህም ይስማዕከ ቅርሶቾቻችንና አባቶቻችን የሚገኙበትን ህልውና ምን እንደሚመስል በሚጥም ምሠላና መቼት ማሳየት ችሏል፡፡ የይስማዕከን ማጠንጠኛ በእውን የሚታይ ክስተት መሆኑን ለማረጋገጥ  የአብነት ትምህርት ቤቶችን ሁኔታ መቃነኘት ብቻ ይበቃል፡፡ አባቶቻችን ያከማቹትን ዕውቀትና በምስጢርነት የያዙትን ሀብት ተረካቢ ሰው በማጣቸው ይዘውት እየተቀበሩ ወይም በዘራፊዎች እየተነጠቁ መሆናቸውን ለመረዳት ያስችላል፡፡ እንዲሁም የታሪካችንን አመጣጥ ዞር ብሎ መዳሰስም በሀጋራችን ዋሻዎችና መሬት ውስጥ ብዙ የተቀበረ ቅርስና ሀብት ሊኖረን እንደሚችል ለመገመት ያስችለናል፡፡ እናም ይህንን ትልቅ ሀገራዊ የታሪክ ቀውስና የቅርስ ዝርፊያ ሁኔታ ነው ይስማዕከ በ‹ተከርቸም› ምጥን አድርጎ የነገረን፡፡ እንደ እኔ ከሆነ የቅርስ ጥበቃ ተቋማት ለማስተማሪያ ቢጠቀሙበትም መልካም ይመስለኛል፡- ይህንን መጽሐፍ!፡፡
 ምንም እንኳን የ‹እልፍ›ን ውሳኔ በሚመለከት ከታች የገለጽኩትን ትችትና ማስተካከያ ባስቀምጥም እንደ ሥራዎቹ ከኾነ ግን ይስማዕከ ‹‹ይበል!› ሊባል የሚገባው ልጅ ነው› የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለእኔ እንዳውም ዐጼ ኃ/ሥላሴን ሳይቀር ‹ልጁን ጥዬ አልሄድም!› እስከማለት ካደረሳቸው  ከወጣቱ የማይጨው ጀግና ‹አብቹ› ጋር ተመሳስሎብኛል፡፡ በእውነት በዚህ በኩል መመስገን ሲያንሰው ነው፡፡ እንደ! የቀሚስ ግልቢያ አቀንቃኝ በበዛበት በዚህ ዘመን እኮ ነው እንቁዎቻችንን (icons) ተጠቅሞ የራሳችንን ማንነት፣ ባህልና ሥልጣኔ እንድንመረመር እየታገለ ያለው፡፡
‹ሰው ማለት ሰው ማለት፣
ሰው ኾኖ ሲገኝ ነው ጀግና በጠፋለት፡፡› ነው የተባለው ልበል?
በጥቅሉ ይህንን ብልም ችግሮች የሉም ማለቴ ግን አይደለም፡- ፍጹም መኾን አይቻልምና፡፡ በተለይ በሥነ ጽሑፍ ሐያሲነት ጎራ የተሰለፉት ብዙ እንደሚያወሩ አውቃለሁ፡፡ በግሌም እንደታዘብኩት የልጅ አውቃለሁ ባይነት የሚንጸባረቅበት ይመስለኛል፡፡ ይህንን ለማለት ያስደፈረኝም ስንት ሊቃውንት የተስማሙበትን የእልፍ ምልክት ዐሥር ሺህ መኾን ስህተት ነው በሚል ላርማችሁ ማለቱ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን ያቀረበው መከራከሪያም አጥጋቢነት ያለው አልመሰለኝም፡፡ ምናልባት ወደፊት የተሻለ ጥናታዊ ማስረጃዎችን የሚያቀርብ ከሆነም (በዕንቁ መጽሔት እንደጠቆመው) በዚያን ጊዜ የሚታይ ይሆናል፡፡ ለጊዜው ግን ከላይ ካነሳሁት አንድምታ አንጻር አስተያየት መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አግንቸዋለሁ፡
፫. የይስማዕከ ክርክር ማጠንጠኛ፡-
ከሁሉም በፊት መታወቅ የሚኖርበት ‹እልፍ(፼) አንድ ሺህ ነው፡፡› በማለት የተጠቀመ ይስማዕከ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ መ.ይትባረክ ገሠሠ መራ የተባሉ አባት የኢትዮጵያ ቁጥር አስመልክተው ባዘጋጁት ‹ሰዋሰወ ቀመር› በሚል ጥናታዊ መጽሐፋቸው ስለ እልፍ ውሳኔ የተወሰኑ ሊቃውንትን ጠይቀዋል፡፡ በጥናታቸው ከጠየቋቸው ሠላሳ አምስት ሊቃውንት መካከልም ሦስቱ ‹አንድ ሺህ› እንደሚሉት አስቀምጠዋል፡፡ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ የተለየ መረጃዎችን በማቅረብ የታወቁት መሪ ራስ አማን በላይ በ2000 ዓ.ም ባሳተሟቸው መጽሐፎች እልፍን እንደ አንድ ሺህ ወስደውት ይገኛል፡፡ ኾኖም ከይስማዕከ በስተቀር ሌሎቹ ‹እልፍ(፼)›ን አንድ ሺህ ያሉበትን ምክንያት አላቀረቡም፡፡ (ምናልባትም ማቅረብ አይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡) ለምሳሌ መሪ ራስ አማን በላይ ‹መጽሐፈ ብሩህ ዣንሸዋ ቀዳማዊ› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 184 እልፍን አንድ ሺህ ካሉ በኋላ እንደ አማራጭ ዐሥር ሺህ ብለው አስቀምጠውታል፡፡ ይህ ደግሞ ግራ ያጋባል፡፡ በዚህ በኩል ‹እልፍን አንድ ሺህ ነው› የሚል መከራከሪያ ያቀረበ ይስማዕከ ብቻ ነው፡፡ የይስማዕከስ መከራከሪያ ምንድን ነው?
‹አንድ ሺህን ዘሎ ለዐሥር ሺህ የ፼(እልፍ) ምልክት (symbol) መስጠት አግባብ አይደለም› የሚለው ሐሣብ ለይስማዕከ ዋና መከራከሪያው ነው፡፡ የእሱን ቃል እንደነበረ ብንጠቀሰው መከራከሪያ ነጥቡ ግልፅ ይኾንልናል፡፡
‹የግዕዝ አቆጣጠር… ለእያንዳንዱ መራሂ ቁጥር (ለምሳሌ ፲፣፳፣፴…፻…) የራሱ ምልክት አለው እንጂ (ከመሠረታዊ ቁጥሮች በቀር) ቁጥሮችን በማገጣጠም አይጠቀምም፡፡ ለመቶ (፻) ምልክት እንዳለው ሁሉ ለሺህም ምልክት ያበጃል እንጂ ዐሥር(፲) እና መቶ(፻) አጣምሮ ምልክት አያበጅም፡፡ ለሺህ ምልክት ሳያበጅ ለዐሥር ሺህ ምልክት ያበጃል ብሎ ማመንም አጉል ነው፡፡ እንደዚያ ከኾነማ ለሃያ ሺህም ቀጥሎ ላሉትም ምልክት ሊያስፈልግ ነው፡፡ ሺህን ዘሎ ለዐሥር ሺህ ፼(እልፍ) የሚባል ምልክት (symbol) ያበጃል ብዬ ማመንም በግሌ ይቸግረኛል፡፡ የሚያሳምነኝም አጥቼ ትቸዋለሁ፡፡› በማለት የራሱን ማሰማኛ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡
በተለይም፡-
1)  ‹በመጽሐፍ ቅዱስ ‹እልፍ› የሚለው ቁጥር አንድ ሺህም ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ እብራይስጥ፣ ዐረብና ትግሬም እልፍ ብለው የሚጠሩት አንድ ሺህን ነው፡፡› የሚለውን የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ሐሣብ እና
2)  ›እልፍን ዐሥር ሺህ እየተባለ መጠቀም የመጣው የጥንታዊ ትምህርታችን እየተዘነጋ፤ የተዘበራረቀ አጠቃቀም ተለምዶ ነው፡፡› የሚሉ ነጥቦችን መከራከሪያዎቹ አድርጓቸዋል፡፡
፬. ባቀረባው መከራከሪያ ላይ የሚኖረኝ ትችት
‹የግዕዝ አቆጣጠር ለሺህ ምልክት ሳይሰይም ለዐሥር ሺህ እልፍ(፼) ምልክት ማበጀቱ ትክክከል ነው ወይስ አይደለም?› የሚለውን መከራከሪያ ከታች አሳማኝ ማረጋገጫዎችን የማቀርብበት ስለኾነ ላቆየውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላነሳቸው የመከራከሪያ ጥቅሶች ማስተካከያ ነጥቦች ላቅርብ፡፡
  1. መጀመሪያ መታወቅ የሚኖርበት እልፍ አንድ ጊዜ አንድ ሺህ ሌላ ጊዜ ዐሥር ሺህ ተብሎ መጠቀሱ ግልፅ የኾነ አጠቃቀስ አለመኖሩን ያመለክታል እንጂ ‹አንድ ሺህ› ለመሆኑ ማስረጃ አይኾንም፡፡ ይህም ትክክለኛውን መርምረን ለማወቅ እንድንጥር ይጋብዘናል:: ለክርክሩ ከኾነ ግን አእላፍንም ‹አንድ ሺህ ነው› ብሎ መሟገት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ይስማዕከ እንዳስቀመጠው ከኾነ  በ‹ዘጸአት ፳፬፥፯ ‹ወይገብር ምሕረተ ላዕለ አእላፍ› (ምህረቱን እስከ ሺህ ትውልድ የሚጠብቅ…) ስለሚል አንድ ሺህ አእላፍ ተብሎ ተገልጽዋልና፡፡ እንዲሁም መ. ይትባረክ ባደረጉት ጥናት ውስጥም እልፍን መቶ ሺህ(ሰዋሰወ ቀመር ገጽ 31) ነው በማለት ያስቀመጡ አባት አሉ፡፡  ስለዚህ የእልፍ በተለያየ መልክ መጠቀስ የአበውን የቁጥር አጠቃቀም ስልት እንዲንመረምር ይጋብዘናል እንጂ ‹እልፍ አንድ ሺህ ነው› ብለን ለመወሰን በቂ ምክንያት አይኾንም፡፡ እና አበው ለምን አንድ ሺህን እልፍ እያሉ ይጠሩታል?
  1. እልፍ፣ አእላፍ… የመሳሰሉት አሐዞች ብዙን ጊዜ ብዛትን አመልካች ኾነው ይቀርባሉ፡፡ ለዚህም በትንቢተ ዳንኤል ፮፥፲ ‹ወየአውድዎ እልፍ ወትእልፍተ አእላፋት› ማለትም ‹ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፡፡ አእላፈ አእላፋትም በፊቱ ይቆሙ ነበር፡፡› በሚል የተገጸው የብዙህነት ማሳያ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ እንዲሁም አለቃ ክዳነወልድ ክፍሌ ለ‹እልፍ› አማራጭ ትርጉም ሲሰጡ ‹ብዙ፣ እጅግ፣ ዐያሌ› ማለት ነው በማለት እንደማሳያ በዘዳግም ፯፥፲ ‹ወእገብር ምሕረተ እስከ እልፍ ትውልድ ለእለ ያፈቅሩኒ› ማለት ‹ለሚወዱኝም… ምሕረቴን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የምጠብቅ…› የሚለውንና ሌሎች ጥቅሶችንም በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ በተለይ ‹እልፍ›ን ብዙ ለማለት ‹የአንድ ስንደና የገብስ ዛላም ከፍሬው ብዛት የተነሣ እያንዳንዱ ራስ እልፍ ይባላል፡፡› በማለት ‹የስንደ ዛላ እፍኝ ይሞላ፡፡› የሚለውን ተረት ተርተዋል፡፡ በመሆኑም ‹እልፍ› ኾነ ‹አእላፍ› የሚለው ብዛትን ለማመልከት አንድ ሺህን ሊወክል ይችላል፡፡
  1. በግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እልፍ አንድ ሺህን ወክሎ የተገኘበት ምክንያት ምናልባት በመጻሕፍት ትርጓሜ ጊዜ የእብራስጥ ወይም የዐረብ ቋንቋ ተጽዕኖ መኖሩን ማሳያ ኾኖ የቀረ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የተተረጎመበትን ቋንቋ በመጠቀም የመጻሕፍት አተረጓጎም ምሥጢርን ለመጠበቅ የሚደረግ ስልት ነው፡፡ ይህንንም በመዝሙረ ዳዊት ፻፲፱(119) የተቀመጡትን የአምላክ መጠሪያ ስሞች (በእብራይስጥ) በቀጥታ ተወስደው (በቁም) መተርጎማቸውን እንደ ምሳሌ ወስዶ በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ ከተተረጎበት ቋንቋ ተጽዕኖም አንጻር ይታያል፡፡
  1. ድፍረት ባይኾንብኝ ይስማዕከ አውቆም ይሁን ሣያውቅ (በታይብ ስህተት የተነሣም ሊኾን ይችላል) ትክክለኛውን ትርጉም ወይም አገላለጽ  በአግባቡ ያልላስቀመጠባቸው አገላለጾችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
v  በአግባቡ የተተረጎሙትን እንደተሳሳቱ በመቁጠር፡- ‹ነገሥት ካልዕ ፲፱፥፴፭ ‹ወቀተለ፡ እምተዓይኒሆሙ ለአሦር ዐሥርተ ወስምንተ እልፈ  ወሃምሣ ምዕተ፡፡› (ሰረዝ የተጨመረ) የሚለው በአሐዝ ሲጻፍ ፲ወ፰፼ወ፶፻ ይሆናል፡፡ የአማርኛው ትርጉሙም ይስማዕከ እንዳስቀመጠው ‹ከአሦራዊያን ወገን መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፡፡› ማለት ነው፡፡ እና በዚህ ‹እልፍ› ዐሥር ሺህ ነው ወይስ አንድ ሺህ? በግልፅ ዐሥር ሺህን ወክሎ ነው የተጻፈው፡፡ ይስማዕከ ግን አንድ ሺህን እንደሚገልጽ አድርጎ ነው ያብራራው፡፡ ምንም እንኳን ምሳሌውን ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወሰድኩት ቢልም ትክክል አይደለም፤ አለቃ እንደማስረጃ የወሰዱት ሌላ ነው፡፡ እንዲህ ይላል አለቃ የጠቀሱት (እልፍ አንድ ሺህ ተብሎ የተጠቀሰበት) ማስረጃ ‹‹ከዐረብ ቋንቋ የተቀዳው መጽሐፈ ቄርሎስ በመዠመሪያው ክፍል ‹ምእተ ወሰማንያ ወኀምስት እልፈ› ይላል፡፡›› (ሰረዝ የተጨመረ)፡፡ ትርጉሙም ከላይ ከተጠቀሰው ጋር ተመሳሳይ ነው፡- መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ፡፡  የሁለቱን አገላለጽ ልዩነት ግን ልብ ይሏል፡፡ በሁለተኛው ጥቅስ ትርጉሙ ላይም የዐረብኛ ተፅእኖ መኖሩን መረዳት ይቻላል፡፡
v  አግባባዊ ያልኾነ ጥቅስ አጠቃቀም፡- በራዕይ ዮሐ. ፯፥፭ ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፡፡ የሚለውን በግዕዙ ‹እም ውስተ ሕዝበ ይሁዳ ፪፼ ወ፳፻› ይላል በማለት አስቀምጦታል፡፡ እኔ የአገኘሁት የግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ‹እለ እምውስተ ሕዝበ ይሁዳ ፼ወ፳፻…› ብሎ ይገልጸዋል፡፡ ይህ አሐዝም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን ለሁሉም ነገደ እሥራኤል ዐሥራ ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ እስከ ቁጥር ፰ ድረስ ተጠቅሷል፡፡ የቁጥሩ የአማርኛ ትርጉምም ‹አሥራ ሁለት ሺህ› ማለት ነው፡፡ የዚህን ምሥጢር ደግሞ አስረስ የኔ ሰው ‹የካም መታሰቢያ› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 11 ፈታተው አሳይተውታል፡፡  ስለዚህ ይስማዕከ የተሳሳተ የግዕዝ ቁጥር ተጠቅሟል ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባትም እሱ ወደሚፈልገው እየጎተተው ነው እንዴ? ለማለት ሁሉ ዳድቶኛል፡፡ ምናልባት ትክክል ነው የሚል ከኾነ ከየትኛው የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ እንደጠቀሰው ቢጠቁመን ስህተቱ ከምን እንደኾነ ለመመርመር ያስችለናል፡፡ የታይፕ ስህተት ከኾነ ግን ይቅርታ! ማስተካከል ግን ይገባል፡፡
  1. ይስማዕከ ያቀረባቸው የመከራከሪያ ጥቅሶች አብዛኞቹ ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍል ‹መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ› መጽሐፍ (ገጽ ፪፻፳፬) የተወሰዱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ደግሞ እልፍ(፼) ዐሥር ሺህ መሆኑን በማብራራት የጻፉ ናቸው፡፡ በእብራይስጥና በዐረብም ‹እልፍ አንድ ሺህ ነው› ያሉት የእነዚህ ቋንቋዎች ሊቅ ስለነበሩ አነጻጽረው ለማስረዳት ነው፡፡ ስለዚህ ይስማዕከም ይህንን በአግባቡ ቢመለከተው መልካም ይመስለኛል፡፡
፭. እልፍ(፼) ዐሥር ሺህ ስለመሆኑ ማሳመኛዎች፡-
በትክክልም ይስማዕከ እንደጠቀሰው እልፍ(፼) ‹አንድ ሺህ ነው› ወይስ ‹ዐሥር ሺህ› የሚለው አከራካሪ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን የተወሰኑ ግራ መጋባቶች ቢኖሩም በግልፅ የምናያቸው መረጃዎችና የግዕዝ ቁጥር አፈጣጠር ግን በትክክል የሚያስረዱት የእልፍን ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡ ለዚህም ከዚህ በታች የተጠቀሱት ማሳያዎች ማረጋገጫ ይኾኑናል፡፡
  1. የግዕዝ አሐዝ ዕድገት የራሱ የኾነ አመክንዮአዊ አካሔድ አለው፡፡ እልፍም ይህን አሐዛዊ አመክንዮ ተከትሎ መጠሪያውን ያገኘ ነው፡፡ ሺህ የተባለው የቁጥር ስያሜ ግን ከዐረበኛው (ከሌሎች) የቁጥር አጠቃቀም ጋር ለማጣጣም ተብሎ ኋላ የተሰየመ ይመስላል እንጂ የግዕዝ ቃል አይደለም፡፡ ለዚህም ‹ሸ› የሚባል የፊደል ‹ሆሄ› በግእዝ የፊደል ገበታ ውስጥ አለመኖሩ ምስክር ይሆናል፡፡
የግዕዝ አቆጣጠር አካሔድ ማሳያ ሰንጠረዥ
አኀዝበግዕዝ ሲነበብበአማርኛ ትርጉሙአመክንዮአዊ አካሔዱ
አሐድ (አሐዱ)አንድ1
ክልኤትሁለት2
ሠለስትሦስት3
አርባዕትአራት4
ኀምስትአምስት5
ስድስትስድስት6
ሰብዐትሰባት7
ሰመንትስምንት8
ተስዐትዘጠኝ9
የአንድ ቤት ጨረሰ፡፡ በኢትዮጵያ ዜሮ (አልቦ) የሌለ ነገርን ስለሚወክል ተቆጣሪ ኾኖ ውክልና አልተሰጠውም ማለት ይቻላል፡፡
ዐሥርትዐሥር1X10
ዕሥራሃያ2×10
ሠላሳሠላሳ3×10
አርብዓአርባ4×10
ኀምሳሐምሳ5×10
ስሳስልሳ= ስድሳ6×10
ሰብዓሰባ7×10
ሰማንያሰማንያ8×10
ተስዓዘጠና9×10
ምእትመቶ10×10=100
እዚህ ላይ ዐሥር እጥፍ በመሆኑ የአንድ ቤትን በዐሥር ቤት ማብዛት ዝርዝርነቱን ጨርሷል፡፡ ስለዚህ ዝርዝር የኾነውን የአንድን ቤት በውስጠ ታዋቂ ይዘን የዐሥር ቤት እስከሚያልቅ (እጥፍ እስከሚኾን) ቀጥለን እንይ፡፡
፲፻ዐሥርቱ ምእትዐሥር መቶ= ሺህ10×100
፳፻ዕሥራ ምእትሃያ መቶ=2ሺህ20×100
፴፻ሠላሳ ምእትሠላሳ መቶ=3 ሺህ30×100
፵፻አርብዓ ምእትአርባ መቶ=4ሺህ40×100
፶፻ኀምሳ ምእትአምሳ መቶ=5ሺህ50×100
፷፻ስሳ ምእትስልሳ መቶ=6ሺህ60×100
፸፻ሰብዓ ምእትሰባ መቶ=7ሺህ70×100
፹፻ሰማንያ ምእትሰማንያ መቶ=8ሺህ80×100
፺፻ተሰዓ ምእትዘጠኝ መቶ=9ሺህ90×100
፻፻=፼እልፍመቶ መቶ=10ሺህ100×100=10000
እዚህም ላይ መቶ እጥፍ መኾን መቻሉን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ የተነሣ አዲስ ስያሜ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚያም ነው ዐሥር ሺህ  ‹እልፍ› የተባለው፡፡ ከዚያ በፊት ባሉት (ለምሳሌ በሺህ) ስያሜ (ምልክት) መስጠት አያስፈልግም፤ እጥፍ መኾን አልቻለምና፤ ዐሥርቱ ምእት(፲፻) የሚለውም መወከል ችሏልና፡፡
ከሰንጠረዡ አመክንዮአዊ የመራሔ ቁጥር አሰያየምና የቁጥር ዕድገት ስልት መረዳት የምንችለውም እልፍ የዐሥር ሺህ ምልክት መኾኑን ነው፡፡ የግዕዝ አቆጣጠር ከእልፍ በላይ ባሉት ቁጥሮች አጨቃጫቂነት ይታይበታል፡፡ አስተማማኝ ጥናትም ስለሚጠይቅ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቢያለሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ተነሣሁበት ነጥብ በመመለስ እልፍ ዐሥር ሺህ መሆኑን ወደሚያረጋግጥ ተጨማሪ ነጥብ ልለፍ፡፡
  1. በግዕዝ ቁጥር ውስጥ ትልቁ ነፃ (ነጠላ) ምልክት ያለው ቁጥር መቶ(፻) ነው፡፡ የእልፍ ምልክት(፼) የሁለት መቶዎች (ምእታት) ብዜት እንጂ ራሱን የቻለ ነጠላ ምልክት አይደለም፡፡ ከሌሎቹ ተጣማሪ ምልክቶች የሚለየው በአንድነት መታሠሩ (፻፻=፼) እና መጠሪያው ነው፡፡ ከሌሎች በተለየ የተጣመረበት ምክንያት ምናልባት በጥንት ጊዜ አጻጻፍ በተከታታይነት ከሚቀመጡ ሁለት የመቶ አሐዞች ጋር እንዳያምታታ በሚል ጥቅም ላይ የዋለ ይመስላል፡፡ ለዚህም የኢዛና ሐውልት የአሃዝ ጽሑፎችን (ለምሳሌ፡ Ö፼â፻፻á=25140) ማየት ማረጋገጫ ይሆነናል፡፡ ስለሆነም እልፍ የሚለው የሁለት መቶ አሐዞች ጥምረት መቶ ጊዜ መቶ መሆኑን በግልጽ ይመሰክራል፡፡ ምናልባትም የይስማዕከም ስህተት እልፍ የሁለት መቶዎች ጥምረት መሆኑን ያለመገንዘብ ችግር ይመስለኛል፡፡ እንደ እኔ ግንዛቤ ይህንን የተረዳ ሰው የእልፍ ምልክት አንድ ሺህን ይወክላል ብሎ ለመከራከር አይደፍርም፡፡ ስለዚህ እልፍ ዐሥር ሺህ መኾኑን በዚህ ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
  1. የተደረገ ጥናትም የሚያረጋግጠው የእልፍ(፼)ን ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡ በመ.ይትባረክ ገሠሠ መራ የተዘጋጀው ‹ሰዋሰወ ቀመር› በሚለው የጥናት መጽሐፍ የተጠየቁት መምህራን ይህንን አረጋግጠዋል፡፡ ስለዚህ የእልፍ ዐሥር ሺህ መኾንን በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የመጻሕፍት፣ የቅኔና የቁጥር መምህራን የተስማሙበት ነው፡፡ የጥናት ውጤቱንም በጥቅል መልክ በሰንጠረዥ ስናስቀምጠው የሚከተለውን ይመስላል፡፡ (መጽሐፉን ያገኘ ከገጽ 21-44 ያለውን ይመልከት)
የሊቃውንት የእልፍ ውሳኔ ማሳያ ሰንጠረዥ
ተ.ቁጥናቱ የተካሔደበት ሥፍራብዛትእልፍ ላይ ያለው ውሳኔ
አንድ ሺህዐሥር ሺህ
1አክሱም321
2ተምቤን101
3መቀሌ101
4ደሴ202
5ሐዋሳ202
6ሐረር202
7ድሬደዋ303
8ደብረ ማርቆስ101
9ባህር ዳር201 (አንዱ መቶ ሺህ ነው ብለዋል፡፡)
10ዲማ2?1
11ጨጎደ፣ አዳማ101
12ጎንደር513 (አንዱ አባት ውሳኔያቸውን ሳያሳውቁ ሞተዋል)
13አዲስ አበባ707
14ቤተ ክህነት303
ድምር35329
ያልተወሰነ3
ከዚህ በላይ ባለው ሰንጠረዥ መረዳት እንደሚቻለው ከተወሰኑት (9%) በስተቀር አብዛኝቹ መምህራን(83%) ‹እልፍ ዐሥር ሺህ ነው› የሚለውን የሚደግፉ ናቸው፡፡ በእውነት የራሳችንን ምኞት እንከተል ካላልን በስተቀር ከእነዚህ የቅኔ፣ የመጻሕፍትና የቁጥር ሊቃውንት የበለጠ ስለ ግዕዝ ቁጥር አመጣጥና ስለ እልፍ አሰያየም ዐውቀን ለማረም የምንችል አይመስለኝም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እነ አስረስ የኔሰው፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበጊዮርጊስ እና መሰል የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ሊቃውንት በየመጻሕፍታቸው የእልፍን ዐሥር ሺህነት መሰከሩ እንጂ አንድ ሺህ ነው በማለት አልጻፉም፤ አልተከራከሩም፡፡ ለምሳሌ አስረስ ኔሰው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ‹የጥንት ፊደላችን በአልፋ ቤት (አ) ይጀምር ነበር› ብለው መጻፋቸውን ነቅፈው በሀሌታ ‹ሀ› መጀመሩን ለማሳየት መጽሐፍ ጽፈዋል፡- ‹የካም መታሰቢያ› እና ‹ትቤ አክሱም መኑ አንተ?› የሚሉ፡፡ በእልፍ ጉዳይ ላይ ግን የነበራቸው አቋም ተመሳሳይ ነው፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ደግሞ እንደ ተራ ምሁር የሚታዩም አይደሉም፡- የዕውቀት ውቅያኖሶች እንጂ፡፡ ስለዚህ በእልፍ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም የነበራቸው ከጥንት ጀምሮ የእልፍ ምልክት(፼) ዐሥር ሺህን መወከሉ የተረጋገጠ ስለነበር ነው፡፡
  1. የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አጻጻፍም የሚነገረን የእልፍ(፼)ን ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡  የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ዓመተ ዓለምን እስከ ስምንት ሺህ ዓመተ ምህረትን ደግሞ እስከ ሁለት ሺህ ድረስ አድርሶታል፡፡ በእኒህ የዓመታት አጠቃቀስም ሺህን እልፍ በማለት ያስቀመጠ የለም ማለት ይቻላል፤ ይልቁንም በምእት(በመቶ) ቤት (ለምሳሌ ፲፻፣ ፳፻፣ ፴፻…) ነው የሚገለጸው፡፡ በተለያዩ መዛግብት የሚገኙ መረጃዎች በእልፍ የተገለጸ የዓመታት አጻጻፍ አይታይባቸውም፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ በቀላሉ እንኳን በዐጼ ቴዎድሮስ (የእነ አለቃ ዘነብን)፣ በአጼ ምኒሊክ (በአማርኛ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ሰዋሰው፣ የአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስን ጦቢያ…)፣ በንግሥት ዘውድቱ (መንፈሳዊ መጻሕፍት) የንግሥና ዘመናት እንዲሁም በቀ/ን/ነ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያዎቹ የንግሥና ዓመታት የታተሙ መንፈሳዊና ዓለማዊ መጻሕፍትን የኅትመት ጊዜ አጻጻፍ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ እልፍ አንድ ሺህ ቢኾን ኖሮ ፲፰፻፣ ፲፱፻… እያሉ ከመጻፍ ይልቅ ፼፰፻፣ ፼፱፻… እያደረጉ መጻፍ በተለመደ ነበር፡፡ ልብ ይበሉ እልፍ(፼) ለዓመታት መጻፊያ ኾኖ ያልተጠቀሰው ከስምንት ሺህ በላይ በመውጣት በዐሥር ሺህ የሚጻፍ ዓመት ስለሌን ነው፡- በመንፈሳዊ አቆጣጠር፡፡ ደግሞስ ዓመተ ምሕረትን ብቻ እንኳን በሺህ መጻፍ ከጀመርን ከሺህ ዓመት በላይ ኾኖን ሳለ ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ እልፍን አንድ ሺህ አድርገን ካልጻፍን ብለን እንዴት እንዳአዲስ ልንሟገት እንችላለን?
  1. ከዓመታት አጻጻፍ ሌላ ከዐሥር ሺህ በላይ የኾኑትን አብዛኞቹን ቁጥሮች ግን በእልፍ ተጽፈው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌም ዮሐ.ራዕይ ፯፥፬ ‹ወሰማዕኩ ኁልቆሙ ለእለ ተኀትሙ ፲ወ፬፼ወ፵፻›፡- ትርጉሙ ‹ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።›፤ ዘዳግም፲፪፥፴፯ ‹ወግዕዙ ደቂቀ እሥራኤል እምራምሴ ውስተ ሰኮታ ፷፼›፡- የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ።፤ ራዕይ ዮሐንስ ፯፥፬-፰ ያሉ ቁጥሮች…የመሳሰሉት ጥቅሶች  ዐሥር ሺህን በእልፍ ምልክት መግለፅ የተለመደ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
  1. ከኹሉም በላይ በአፄ ኢዛና የድል ሐውልት ላይ ተጽፈው የሚገኙ የግዕዝ ቁጥሮች የእልፍን ዐሥር ሺህ መኾን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌም ‹…ለስድስቱ ነገሥት ፪፼፶፻፻፵ ለህመ› ይላል፤ ይህንንም ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ‹…ለስድስቱ ነገሥታት 25140 ሠንጋ ሠጠን፡፡› ብለው ተርጉመውታል፡፡ እንዲሁም ሌላ ‹…ምህርካ ፫፼፲፻፱፻፶፯ ለህም…› የሚል አሐዝ አለ፤ ይህም ቁጥር ‹30957›ን የሚወክል መኾኑን መረዳት ይቻላል፡፡  በሐውልቱ ላይ ሌሎች የግዕዝ ቁጥሮች ስላሉ የበለጠ በመመርመር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ኾኖም ከላይ በተ.ቁ. 2 እንደተጠቀሰው ከአሁኑ አጻጻፍ ጋር ልዩነት መኖሩንም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ከላይ የጠቀስናቸው የሐውልት ቁጥሮች በአሁን ጊዜ አጠቃቀም የተጻፉ ቢኾኑ ኖሮ የመጀመሪያው ፪፼፶፩፻፵፣ የሁለተኛው ደግሞ ፫፼፲፱፻፶፯ ዓይነት አጻጻፍ ይኖራቸው ነበር፡፡ ስለዚህ የእልፍ(፼) ቁጥርን ዐሥር ሺህ መኾን ታሪካዊ ማስረጃዎች ሁሉ ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡
በእኔ በኩል ከዚህ በላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች እልፍ ዐሥር ሺህ ለመሆኑ አሳማኝ መከራከሪያዎችን ያቀረብኩ ይመስለኛል፡፡ አሳማኝ መከራከሪያ እንኳን ማቅረብ ባልችል እልፍን አንድ ሺህ አድርጎ ለመጠቀም ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ውድቅ የሚያደርግ ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ ያለበለዚያ የእኛን የቁጥር አካሔድ በውጭዎች ስልት እየመዘንን መለዋወጡ አግባብ አይመስለኝም፡፡
  ፮.ማሣረጊያ
እኔ እንደማምነው ከኾነ ምንም እንኳን አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም የባህላዊ አስተምህሯችን በትውፊት ተያይዞ እኛ ጋር ደርሷል፤ የእልፍ  ትክክለኛ ስያሜ ምልክትም እንደዚሁ፡፡ አሁን ያለው የሀገራችን የአስተምህሮ ችግር ከዐጼ ምኒልክ በኋላ የዘመናዊ ትምህርት አስተምህሮ ውጫዊ (የአውሮፓን አስተምህሮ መሠረት ያደረገና ሀገር በቀል የሆኑ ትምህርቶችን ያቃለለ) መኾን ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ ይህ ግን በዘመናዊ አስተምህሮ አካባቢ ያለውን አካሔድ የሚመለከት እንጂ የአብነት ትምህርት ቤቶችን የበረዘ (ተጽዕኖው ቢኖርም) አይመስለኝም፡፡ የእኛ የጥንታዊ አስተምህሮ ደግሞ ያለው በእነዚህ ተቋማት (በአብነት ት/ቤቶች) ነው፡፡ እንዲሁም  የተለያዩ የቆዩ የብራና መጽሐፎች በውጭም ኾነ በሀገር ውስጥ መኖራቸው የጥንታዊ የቁጥር ስያሜ በአግባቡ ተመዝግበው ስለመገኘታቸው ማረጋገጫ መኾን ይችላሉ፡፡ የእልፍ አሐዝ ስያሜም ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም የእልፍን ስያሜ ድንገት ዛሬ ተነስተን የፈጠርነው አለመሆኑን መረዳት አለብን፡፡
ይስማዕከም በጥቅሉ እልፍ አንድ ሺህ ነው በማለት የመከራከሪያ ነጥብ ማንሳቱ መልካምና የሚደገፍ ቢኾንም ጥናት ላይ ሳይመሠረት በራሱ ውሳኔ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ግን ትክክል አይመስልም፡፡ ምክንያቱም የእልፍን አንድ ሺህነት የሚያመለክቱ የመጻሕፍት የኅትመት መግለጫዎች የሉም፡፡ የቆዩ የብራና መጻሕፍትም ዓመተ ዓለምንና ዓመተ ምህረትን በእልፍ (አንድ ሺህ አድርገው) የገለጹ አይመስለኝም፡፡ የጥንት የብራና መጻሕፍትም እልፍን አንድ ሺህ በማድረግ ቢያስቀምጡ ኖሮ ቢያንስ ዐጼ ኃ/ሥላሴ እያስተረጎሙ እንዲታተሙ ባደረጓቸው የአንድምታ መጽሐፎች ውስጥ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ መጽሐፎቹ የሚመሰክሩት የእልፍን(፼) ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡ ስለዚህ የ‹እልፍ› ምልክት(፼) ዐሥር ሺህን መወከል የታመነባትና አግባብነት ያለው ነው፡፡ ለማንኛውም ይሰማዕከ ይህንን ጉዳይ በማንሳቱና እኔም እንድጽፍ ምክንያት ስለኾነኝ እግዜር ይስጠው፡፡
Source: kassahunalemu.wordpress.com
ፍልስጤም-እስራኤሎች፥ ዋሽንግተን፥ ሞስኮዎች፥ ዋሽንግተን፥ ቤጂንግ፥ ዋሽንግተን ቴሕራኖች፥ ዋሽንግተን ሐቫናዎች፥ አስመራ-አዲስ አበቦች፥ ኢሕአዲግ ተቃዋሚዎች፥ ሶማሌዎች፥ ሶሪያዎች፥ ብዙ ናቸዉ። ቁጥራቸዉን መዘርዘሩ ያታክታልም። ከማንዴላ ምግባር ጥቁቱን፥ ከዴክላክ ድፍረት ትንሹን እንኳን ገቢር አለማድረጋቸዉ በርግጥ ያጠያይቃል 
ማንዴላ ተቀበሩ። ታላቁ የነፃነት፣ የእኩልነት አርበኛ ከሞቱበት እስከ ተቀበሩበት ድፍን ዓለም አዘነ፥ ወይም ማዘኑን ገለፀ። ከቄሱ እስከ ሼኩ፥ ከዘማሪዉ እስከ ዘፋኙ፥ ከተዋኙ እስከ ስፖርተኛዉ ለዚያ ታላቅ-ክቡር ሠዉ ታላቅ አድናቆት፥ አክብሮቱን ሲያንቆረቁር ሰነበተ። ከፕሬዝዳት ዙማ-እስከ ፕሬዝደንት ኦቦባ፥ ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም እስከ ጠቅላይ ሚንስትር ካሜሩን የትንሽ ትልቁ ሀገር መሪ የማንዴላን አብነት ለመከተል፥ ዓላማ፥ ራዕይ አስተምሕሯቸዉን ገቢር ለማድረግ ቃል ገባ። ካንጀት-ይሆን ካንገት ማረጋገጪያዉ-በያኙ በርግጥ ምግባር እና ጊዜ ነዉ። ማንዴላ
ፈጥራ በማንዴላ የተፈጠረችዉ ራስዋ-ደቡብ አፍሪቃ ግን በማንዴላነቷ መቀጠሏ ካሁኑ አያነጋገረ ነዉ። ብልጭ ያሉ፥ እዉነት፥ አስተያየቶቾን እያጠቃቀስን ላፍታ አብረን እንቆዝም።

ባለፈዉ ማክሰኞ፥ ለማንዴላ የሐዘን ስንብት ድግሥ በታደመዉ ሕዝብ መሐል፥ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ የኩባ አቻቸዉን ራዑል ካስትሮን መጨበጣቸዉ ማንዴላ ሞተዉም ጠላቶችን ያጨባበጡ፥ ጉደኛ ሰዉ አሰኝቶ ነበር። እያሰኘም ነዉ። ይሁንና ኦባማ-ከፖለቲካ መርሕ አብነታቸዉ ከክሊንተን፥ ራዑል ከትግል ጓድ፥ ከስልጣን ርዕዮተ-ዓለም፥ አዉራሻቸዉ፥ ከሁሉም በላይ ከታላቅ ወንድማቸዉ ከፊደል የተለየ ነገር አላደረጉም።

መስከረም 8 ሁለት ሺሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የያኔዎቹ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ቢል ክሊንተን እና ፊደል ካስትሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ተጨባብጠዉ ነበር። ያኔም እንዳሁኑ በርግጥ ጉድ ተብሎ ነበር። እና አሁን ጉድ ካሰኘ-ጉድ ማሰኘት የነበረ-ያለበት፥ የሚኖርበትም የዓለም አቻ የለሽ ግዙፍ፥ ኃያል፥ ሀብታም ሀገር ከትንሽ፥ ደሀ፥ ደካማይቱ ደሴት ጎረቤቷ ጋር ለስልሳ ዘመናት በጠላትነት መፈላለጓ በሆነ ነበር።

ጉድ ካሰኛ የትልቂቱ ሀገር የመጀመሪያ የጥቁር-ነጭ ክልስ መሪ የማንዴላን አብነት ገቢር ማድረግ እንደማይችሉ ባደባባይ ማመናቸዉ ጉድ ባሰኘ ነበር።


«ኔልሰን ማንዴላን ብጤ ከእንግዲሕ ብጨራሽ አናገኝም። ይሁንና ለአፍሪቃ እና ለመላዉ ዓለም ወጣቶች የሚከተለዉን ልናገር፥-የማንዴላን የሕይወት ምግባር የራሳችሁ ማድረግ ትችላላችሁ። ከሠላሳ ዓመት በፊት ገና ተማሪ እያለሁ ስለማንዴላ እና እዚች ሀገር ስለሚደረገዉ ትግል ተምሬያለሁ። ይሕ በዉስጤ የሆነ ነገር አጭሯል። ለሌሎች እና ለራሴ ኃላፊነት እንዳለብኝ ቀስቅሶኛል። እና ዛሬ ከዚሕ ካደረሰኝ አስቸጋሪ ጉዞ ዶሎኛል። የማዲባን አብነታዊ ምሳሌ ገቢር ለማድረግ ቢያቅተኝም የተሻለ ሠዉ ለመሆን እንድጥር አድርጎኛል።»

ማንዴላ ተወንጅለዉ፥ ታስረዉ፥ የጠላቶቻቸዉን ቋንቋ ተምረዉ፥ ተፈተዉ፥ ለጠላቶቻቸዉ ይቅር ብለዉ ደቡብ አፍሪቃን ዴሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃን ፈጥረዉ፣ መርተዉ፣ ኖረዉ ሞቱ። የዓለም ፖለቲከኞች እንዳሉና እንደሚሉት የዓለም የትንሹም የትልቁም አብነት ናቸዉ። በተለይ ለአፍሪቃ -የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እና የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ እንዳሉት የወደፊት ተስፋዋም አብነት ናቸዉ።

«እንደ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት እዉነተኛ መሪ እና ልዩ ሰብዕናቸዉ ሁሉ፥ የማንዴላ ሕይወት የክፍለ-አሐጉሪቱን የወደፊት (ተስፋ) የሚወክልም ነዉ።»

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ከአዲስ አበባ ወደ ቁኑ ከመብረራቸዉ በፊት-አርብ፥ ከዚያዉ ከአዲስ አበባ ይሕን ሰምተን ነበር።

ፍልስጤም-እስራኤሎች፥ ዋሽንግተን፥ ሞስኮዎች፥ ዋሽንግተን፥ ቤጂንግ፥ ዋሽንግተን ቴሕራኖች፥ ዋሽንግተን ሐቫናዎች፥ አስመራ-አዲስ አበቦች፥ ኢሕአዲግ ተቃዋሚዎች፥ ሶማሌዎች፥ ሶሪያዎች፥ ብዙ ናቸዉ። ቁጥራቸዉን መዘርዘሩ ያታክታልም። ከማንዴላ ምግባር ጥቁቱን፥ ከዴክላክ ድፍረት ትንሹን እንኳን ገቢር አለማድረጋቸዉ በርግጥ ያጠያይቃል። አጠያየቀም አላጠያየቀ ኦባማ እንዳሉት ማለትና-ማድረግ ለየቅል፥ አንዳንዴም ተቃራኒ ናቸዉ።

«ስለዚሕ እኛም ለፍትሕ (ሥርፀት)፥ ለሰላም (ፅናት) እርምጃ መዉሰድ አለብን። የማዲባን በዘር መካካል እርቅ የማዉረድ ዉርስ-ቅርስን በደስታ የሚቀበሉ፥ ግን በተቃራኒዉ ሥር የሠደደ ድሕነትን፥የኑሮ ተባለጥ ለመቋቋም፥ መጠነኛ ለዉጥ ማድረግን እንኳን ከልባቸዉ የሚቃወሙ በርካታ ሰዎች አሉ።»

ማንዴላ እራሳቸዉ ደጋግመዉ እንዳሉት ተዓምረኛም፥ ቅዱስም አይደሉም። ብዙዎች እንደመሠከሩት ግን አንድ ሰዉ ሊያደርገዉ ከሚገባዉ በላይ አድርገዉ፥ ዴሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃን ፈጥረዉ እንደ አንድ ሰዉ አረፉ፥ አለፉ። የማንዴላ ደቀመዛሙርት፥ የርዕዮተ-ዓለም፥ የሥልጣን ወራሾች እንደተቀረዉ ዓለም መሪዎች ሁሉ የማንዴላን ጅምር ለመቀጠል፥ ራዕይ-አስተምህሯቸዉን ገቢር ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

«(ማዲባ) በህይወታችን ከአንድ መሪ የምንፈልገዉና ሊኖረን የሚገባዉ መሪ ሆነህ በአስቸጋሪ ወቅት በመገኘትህ እናመሰግናለን። ለነፃነት የተደረገዉ ረጅም አካላዊ ጉዞ ቢያበቃም፥ የኛ የራሳችን ጉዞ ግን ይቀጥላል። አበክረሕ የጣርክለትን ዓይነት ማሕበረሰብ ለመመሥረት በጀመርከዉ መቀጠል አለብን። ጅምርህን ወደፊት ማራመድ አለብን። ከበለፀገዉ ልዩ ምግባርህና ከሕይወት ልምድህ መማራችንን እንቀጥላለን።»

ፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማ። ዕሁድ። የማንዴላዋ ዴሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃ በ1994 ስትመሠረት በምጣኔ ሀብት ዕድገት የነበራትን ሥፍራ ዛሬም አለቀቀችም። ከአፍሪቃ አንደኛ ናት። ከአፍሪቃ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ሃያ-አራት በመቶዉን ትይዛለች። ማንዴላ ሲፈጥሯት ትንሽ የነበረዉ ሙስና ግን ዛሬ ሰንጎ ይዟታል።

የማንዴላን ፅናት፥ ሥልት፥ የአስተዳደር አመራር ብልሐትን ለመቀጠል ቃል የገቡት ፕሬዝደንት ዙማ ራሳቸዉ በመንግሥት ገንዘብ በሃያ-ሁለት ሚሊዮን ዶላር መኖሪያ ቤት ማስገንባታቸዉ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ። ዙማ ቤቱን ከቤተሰባቸዉ በተሰጣቸዉ ገንዘብ ማስገንባታቸዉን መናገራቸዉ አልቀረም። ያመናቸዉ ግን የለም።

ማንዴላ ሁሉንም ዘር ያሳተፈ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመሠረቱበት ወቅት የደቡብ አፍሪቃዊዉ ሥራ አጥ ቁጥር አስራ-ስድስት በመቶ ነበር። ዘንድሮ ግን ከአንድ አራተኛ የሚበልጠዉ ደቡብ አፍሪቃዊ ሥራ የለዉም። ሃያ-አምስት ከመቶ። በዚሕ ቁጥር ላይ ሥራ መፈለግ ያቆመዉ ሁለት ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ሲጨመርበት የሥራ-አጡ ቁጥር ሠላሳ ሰባት ከመቶ ሊደርስ ይችላል።


የሠራተኞች ተደጋጋሚ የሥራ ማቆም አድማ፥ የባለሥልጣናት ሙስና፥ የግልፅ የምጣኔ ሀብት መርሕ ችግር ከዓለም የምጣኔ ሀብት ክስረት ጋር ተዳምሮ የአፍሪቃዋ የምጣኔ ሀብት ቋት ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በእጅጉ እያዘገመ ነዉ። የአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ምጣኔ ሀብት ከአምስት-እስከ ሰባት ከመቶ በሚያድግበት በዚሕ ዘመን የደቡብ አፍሪቃ አማካይ የምጣኔ ሀብት ዕድገት 3.5 ከመቶ ላይ ያጣጥራል።

ከማንዴላ በፊት የሠላም ኖቤልን የተሸለሙት ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ የማንዴላ ጅምር ዳር እንደሚዘልቅ፥ የሐገራቸዉ የወደፊት ጉዞ እንደሚሰምርም ይናገራሉ።

«አባታችን ሞተ፥ ከእንግዲህ ምን ይገጥመናል? ሞቱ የምፅዓት ቀንን እና ጥፋትን ያስከትልብን ይሆን? አንዳንዶች እሱ አሁን እንዳለፈዉ ካለፈ በኋላ ሀገራችን ትነዳለች ይላሉ። ይሕ እንደሚመስለኝ እኛን ደቡብ አፍሪቃዉያንን አሳንሶ መመልከት ነዉ። የእሱን ቅርስ ማሳነስ ነዉ። ጀምበሯ ነገም ተወጣለች፥ ከነገወዲያ፥ በሚቀጥለዉ ቀንም። እንደ ትናንቱ ደማቅ አትሆን ይሆናል፥ ሕይወት ግን ይቀጥላል።»

እንደመንፈሳዊ አባት መጪዉን ዘመን በበጎ ተስፋ ከመቃኘት፥ ጥሩ ጥሩዉን ከመስበክ ሌላ-ሌላ ማለት በርግጥ የቄስ ምግባር አይደለም። ቱቱ እንዳሉት ሕይወት ደብዛዛም ቢሆን ይቀጥላል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች ስልሳ ሁለት በመቶ ለሚሆኑት የነዙማ መንግሥት ፈጣን መፍትሔ ካለመጣላቸዉ ሕይወታቸዉ የሚቀጥለዉ ከድሕነት ጠገግ በታች እየማቀቁ ነዉ።

ፖለቲካዉም ከኤኮኖሚዉ የተለየ አይደለም። ከ1994 ጀምሮ ደቡብ አፍሪቃ ያለ ብዙ ተቀናቃኝ የሚመራዉ የደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ኤ.ኤን.ሲ) በመሪዎቹ ሽኩቻ፥ መጠላለፍና ሙስና ግራ ቀኝ እየተላጋ ነዉ። ANC በሁለት ሺሕ አራት በተደረገዉ ምርጫ ሰባ ከመቶ ያህል ድምፅ አግኝቶ ነበር። ከአምስት አመት በሕዋላ በተደረገዉ ምርጫ ግን ANC ያገኘዉ ድምፅ ስልሳ፥ ስድስት ከመቶ እንኳን አይሞላም።

በመጪዉ ዓመትም ምርጫ አለ።2014 እርግጥ ነዉ የዙማ እና የኢምቤኪ (የቀድሞዉ ፕሬዝዳት) ደጋፊ በሚል በሁለት የተከፈሉት የፓርቲዉ አባላት ንትርክ ቀዝቀዝ ያለ መስሏል። ይሁንና ምርጫዉ የሚደረገዉ አድማ በመቱ የማዕድን ቆፋሪዎች ላይ በተፈፀመዉ ግድያ ሰበብ እስካሁን ለኤ.ኤን ሲ ያላሰለሰ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩት የሠራተኞች ማሕበራት መሪዎች ከፓርቲዉ መሪዎች ጋር በሚወዛገቡበት ወቅት ነዉ።

የቀድሞዋ የፀረ-አፓርታይድ እዉቅ ታጋይ ዶክተር ማምፌሌ ራምፌሌ ለረጅም ጊዜ ከሚደግፉት ከኤ.ኤን ሲ አፈንግጠዉ ባለፈዉ የካቲት የራሳቸዉን ፓርቲ መስርተዋል። የኤ.ኤ.ን ሲን የወጣቶች ክንፍ ይመሩ የነበሩት ጁሊየስ ማሌማም ከፓርቲዉ ከተባረሩ በኋላ ባለፈዉ ጥቅምት አዲስ ፓርቲ መስርተዋል።

የአንጋፋዉ ፓርቲ መሰነጣጠቅ ነጮች ለሚበዙበት ለዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ለዴሞክራቲክ ሕብረት ጥሩ አጋጣሚ ነዉ። እየተራበ፥ እየተቸገረ፥ መሪዎቹ በስሙ በያዙት ሥልጣን እንደሚቀማጠሉ እያወቀ የማንዴላ ሥም፥ ግርማ ሞገስ፥ የገድል-ድላቸዉ ዝና ብቻ ትዕግስት ሆኖት የቆየዉ ሕዝብ እስካሁን በታገሰበት መንገድ መታገሱ አጠራጣሪ ነዉ። እሳቸዉ ደግሞ ይሰጋሉ።ነጭ ናቸዉ።ደቡብ አፍሪቃዊት።

«ያሰጋኛል። ምክንያቱም፥ እንደሚመስለኝ ይህ የአንድ ዘመን ፍፃሜ ነዉ። ነጮች እና ጥቁሮች አብረን የኖርንበት ዘመን ፍፃሜ እንዳይሆን እፈራለሁ። ብዙ መጥፎ ሰዎች እሳቸዉን (ማንዴላን) ስለሚያከብሩ ብቻ መጥፎ ነገር ከማድረግ የታቀቡ ይመስለኛል። እነዚሕ ሰዎች ይህቺን ሀገር ምናልባት ወደ ሌላ አቅጣጫ ይነዷታል ብዬ እሰጋለሁ።»

ሰዉዬዉ፥ በ1962 ከደቡብ አፍሪቃን በሕገ-ወጥ መንገድ በመዉጣት እና የሥራ ማቆም አድማን በማነሳሳት በተከሰሱ ወቅት፥ ከሳሹ አቃቤ ሕግ ፒ.ጄ ቡሽ ይባሉ ነበር። አቃቤ ሕጉ ነጭ እና የነጭ ዘረኞቹ መንግሥት አቀንቃኝ ናቸዉ። ማንዴላ ላይ ሊፈረድ ሲል «አንዴ ለብቻዉ ላነጋግረዉ እፈልጋለሁ» ይላሉ አቃቤ-ሕጉ። ተፈቀደላቸዉ። ማንዴላን ጨበጧቸዉ አሏቸዉም «መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ።» ለሳቸዉ የሰላም እረፍት፥ ለናንተ መልካም ጊዜ ልመኝ። እና እንደተለመደዉ ስለ ማሕደረ ዜና አስተያየታችሁን፥ በደብዳቤ፥ በስልክ፥ በኢሜይል፥ በፌስ ቡኩም እንድትሰጡ ጠይቄ ልሰናበት። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ
Source: www.dw.de
 

በደቡብ ሱዳን ትላንት የተሞከረው የመንግስት ግልበጣ መክሸፉን የኣገርቱ መንግስት ኣስታወቀ። በቀድሞው ም/ፕሬዝደንት ማቻር የተመራው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የከሸፈው ለፕሬዝደንት ሳልቫኪር ታማኝ የሆኑ ወታደሮች የበላይነትን በማግኘታቸው ነው ተብሏል። 
የቀድሞው የኣገሪቱ ም/ፕሬዝደንት ከስልጣን የተባረሩት ባለፈው ሀምሌ ወር ሲሆን ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚሉት ከዚያ ወዲህ በመንግስትም ሆነ በገዚው የSPLM ግንባር መካከል ክፍፍል ተፈጥሯል።
ከእሁድ ቀትር በኃላ ጀምሮ እስከ ዛሬ ማለዳ የዘለቀው የተኩስ ልውውጥ ኣሁን መቆሙን እና በከተማይቱ ጁባ ኣንጻራዊ መረጋጋት መስፈኑን የኣይን እማኞች ይናገራሉ።
በቀድሞው ም/ፕሬዝደንት የሚመሩ ያኮረፉ ወታደሮች እና ፖለቲከኞች በመንግስት ኃይሎች በተለይም በቤተመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የከፈሩት ድንገተኛ ተኩስ ከየኣቅጣጫው
እያስተጋባ ትላንት ምሽት እና ለሊቱን በሙሉ በከተማይቱ ጁባ የዘለቀ ሲሆን የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን የጠቀሱ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ውጊያው ዛሬ ጧትም በመጠኑ ቀጥሏል። ዓለማውም በዓለማችን የመጨረሻው ዓዲስ መንግስት የሆነውን የደቡብ ሱዳን መንግስት ለመገልበጥ ነው ተብሏል። በኣገሪቱ ጦር ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የሰራዊቱ ዓባላትም በዋና ከተማይቱ ጁባ የሚገኘውን የመሳሪያ ግ/ቤት ወረው ለመዝረፍ ሞክረው ነበር። የደቡብ ሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን ለአሶሺዬትድ ፕሬስ እንደነገሩት ከሆነ ግን ወረራውን በመመከት የመሳሪያ ግ/ቤቱን ለመታደግ ተችሏል። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ኣንዳንድ ፖለቲከኞችም ተይዟል። የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን የመሩት የቀድሞው ም/ፕሬዝደንት ሬክ ማቻር ስለመያዛቸው ግን ማረጋገጥ ኣልቻሉም። የደ/ሱዳን የመ/ሚኒስቴር ቃ/ኣቀባይ ኮ/ል ፊሊፕ ኣጉዬር ዛሬ ረፋዱ ላይ ለዜና ሰዎች እንዳስረዱት ለፕ/ት ሳልቫኪር ታማኝ የሆኑ ወታደሮች በኣሁኑ ሳዓት የጁባ ከተማን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጣራሉ።
በቅጡ የታጠቁ እና መትረየስ በተገጠመባቸው ተሽከርካሪዎች የታገዙ በርካታ ወታደሮች በጁባ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ለቁጥጥር ተሰማርተው እንደሚንቀሳቀሱ የገለጹት የዓይን እማኞችም ከወታደሮች በስተቀር ዛሬ ጎዳናዎች ላይ የሚታይ ሰላማዊ ሰው ኣለመኖሩን ለዜና ሰዎች ኣስረድቷል። የግብጽ አየር መንግድም የጁባ ኣውሮፕላን ማረፊያ በመዘጋቱ ዛሬ ወደዚያው ያደርገው የነበረውን በረራ ለመሰረዝ መገደዱን ኣስታውቐል። በዚያ የሚገኘው የተመድ ሰላም ኣስከባሪ ጦር በበኩሉ በከተማይቱ በተጋጋለው የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ የተነሳ በተጠንቀቅ መሆኑን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችም ወደ ካምፓቸው እየሸሹ መሆናቸውን ኣስታውቐል። በኣዲሲቷ የዓለማችን ኣገር ደ/ሱዳን መንግስት ውስጥ ልዩነት እና ፍጥጫ የነገሰው ፕ/ት ሳልቫኪር ባለፈው ሀምሌ ወር ምክትላቸውን ማቻርን ከስልጣን ማባረራቸውን ተከትሎ ነው። ከሁለት ዓመታት በኃላ በ2015 በዚያች ኣገር በሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የሳልቫኪር ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የቀድሞው ም/ፕ/ት ማቻር ከስልጣን እንደተባረሩ በሰጡት መግለጫ ኣገሪቱ ኣንድ ሆና እንድትቀጥል ከተፈለገ የኣንድ ሰው ኣገዛዝ ማክተም ኣለበት። ኣንባገነናዊ ኣገዛዝን መታገስ የለብንም ብለውም ነበር። የማቻር መባረር ከመንግስት ም/ቤትም ኣልፎ በገዢው ፓርቲ ውስጥም ክፍፍል መፍጠሩን የተረዱት የUS አሜሪካ እና የኣውሮፓ ህብረት ዲፕሎማቶች ውጥረቱ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳያመራ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።
ሳልቫኪር የቀድሞው ሸማቂ እና የኣሁኑ ገዢ ፓርቲ SPLM የወታደራዊ ክንፍ መሪ በነበሩበት ወቅት ማቻርን ጨምሮ ኣሁን ከእሳቸው ጋር የተባረሩት የግንባሩ አባላት ለአስርተ ዓመታት ከሱዳን መንግስት ጋር በተካሄደው ውጊያ ወቅት በከፍተኛ የዓመራር እርከን ላይ የነበሩ ናቸው። ዘ ሱዳን ትሪብዩት የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ግጭቱ የተጀመረው፣ ትላንት እሁድ መሆኑ ነው፣ ከፕ/ት ሳልቫኪር የዲንካ ጎሳ የሆኑ ወታደሮችን ለማጥቃት በተንቀሳቀሱ ከኑዌር ጎሳ የሆኑ የማቻር ታማኝ ኃይሎች መካከል ነበር። ጁባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲም ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኣሳስቧል። የተመድ የደ/ሱዳን ልዩ መልዕክተኛም ውጥረቱ ኣሁንም ድረስ ኣለመቀረፉን ጠቅሰው ሁለቱም ወገኖች በኣስቸኩዋይ ተኩስ ኣቁመው ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያፈለልጉ ጥሪ ኣድርገዋል።
ጃፈር ዓሊ
ሸዋዬ ለገሰ
Source: www.dw.de


| Copyright © 2013 Lomiy Blog