ካልተሳፈርኩ” ብሎ የታክሲ ሹፌሩን በሽጉጥ ገደለ

  መገናኛ አካባቢ ወደ ጉርድ ሾላ በሚወስደው መስመር፣ አንድ መንገደኛ ትናንት ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ካልተሳፈርኩ ብሎ ሾፌሩን ወንደሰን ደምሴን በሽጉጥ ገደለ፡፡ “ታክሲው
ውስጥ ካልተሳፈርኩ፣ አትሳፈርም” በሚል በተነሳው ጭቅጭቅ፣ ሾፌሩን ገድሏል የተባለውን ደጀኔ ገመቹ በቁጥጥር ስር እንደዋለ የገለፀው ፖሊስ፤ የአይን ምስክሮችን ቃል በመቀበል ምርመራ እያካሄደ ነው፡፡ ታክሲ እየጠበቁ የነበሩ የአይን ምስክሮች በወቅቱ አቶ ደጀኔ እጁን በማወዛወዝ ሚኒባስ ታክሲውን እንዳስቆመ ተናግረው፣ ከሾፌሩ ጋር ጭቅጭቅ እንደተፈጠረ
ገልፀዋል፡፡ አቶ ደጀኔ በታክሲው ለመሳፈር ሲጠይቅ፣ ሾፌሩ “ቤተሰቤን ነው የጫንኩት፣ ሌላ ሰው አላስገባም” በማለት ምላሽ እንደሰጠው በአካባቢው የነበሩ መንገደኞች ተናግረዋል፡፡ ታክሲ የሚጠባበቁ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ስለነበሩ፣ ጭቅጭቁን ከመነሻው እስከ መጨረሻው የተመለከቱ እማኞች በርካታ ናቸው፡፡ የፖሊስ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የሾፌሩ አባት ታክሲው ውስጥ ነበሩ፡፡ “አትሳፈርም የምትለኝ ንቀት ነው” በሚል ክርክርና “የጫንኩት ቤተሰቦቼን ስለሆነ ሌላ ሰው አልጭንም” በሚል ምላሽ በተባባሰው ጭቅጭቅ፣ አቶ ደጀኔ ሽጉጥ እንዳወጣ እማኞች ተናግረዋል፡፡ ሽጉጡን ሾፌሩ አንገት ስር በመደገን ነው የተኮሰው ብለዋል-ምስክሮች፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ዲቪዥን ክፍል ተወካይ፣ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
Source: Addis Admass
 

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog