(ተመስገን ደሳለኝ):
ባለፈው ሳምንት የምስራቅ ኢትዮጵያ ፖለቲካን ተጨባጭ እውነታዎችን ቃኝቼ ተከታዩን ክፍል በይደር አቆይቼው እንደነበረ ይታወሳል፤ እነሆም ዛሬ እንዲህ እቀጥላለሁ፡-
ሐረር እንደ ማሳያ
(መቼም ኢህአዴግ በብቸኝነት የሚኩራራበት የፖለቲካ ‹ስኬት›፣ ለዘመናት አንድ ሆኖ የኖረ ሕዝብን ‹ብሔር ብሔረሰቦች› በሚል ከፋፋይ የ‹ክርስትና ስም› እጥምቆ በአደባባይ ማስጨፈር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ርግጥ ነው በአንድ ወቅት በፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መጨፈር›› በሚል ርዕስ የታተመ መጣጥፍን ተከትሎ ‹ፀረ-ብሔር ብሔረሰቦች› ተደርጌ በተመሰረተብኝ ክስ ፍርድ ቤት መመላለሴ ዛሬም ድረስ መቋጫ አላገኘም፤ ርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቼ በስታዲዮሞች እየተሰባሰቡ የራስ ፀጉራቸው ላይ ላባ ሰክተው፣ ቆዳ አገልድመው እየዘለሉ ትርኢት ከማሳየት ባለፈ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ መብቶቻቸው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡ …እውነታው ይህ ቢሆንም ወደ አጀንዳችን /የከሸፈው ፌደራሊዝምን/ ወደ መፈተሹ በአዲስ መስመር እንመለስ፡፡
ቋንቋን መሰረት ያደረገው ኢህአዴግ ሰራሹ ‹ፌደራሊዝም› አወቃቀር የሀገሪቱ መፃኢ ዕድል የተቋጠረበት ‹የሰዓት ቦንብ› መሆኑን ለመረዳት
የምስራቅ ኢትዮጵያዋን ሐረር እንደ መሳያ መውሰዱን ግድ የሚያደርጉ በርካታ ገፊ ምክንያቶች አሉ፡፡ እንደሚታወቀው የሐረር ከተማ አመሰራረት ብዙሃኑ ህዝብ ከሚኖርበት ‹ጀጎል› ከተሰኘው በግንብ የተከለለ ቅፅር ጋር ይያያዛል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ራሳቸውን ከብሔር ወረራ ለመከላከል በአካባቢው ነዋሪዎች እንደታነፀ በርካታ ድርሳናቶች የሚናገሩለት ጥንታዊውና ታሪካዊው የጀጎል ግንብ በአምስት (ሐረር፣ ኤረር፣ ሠንጋ፣ ቡዳ እና በርበሬ በር በሚባሉ) በሮች የተከፋፈለ ነው፡፡
ጀጎል ከ40ሺ ለማያንሱ የክልሉ ነዋሪዎች መጠለያ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ከዘጠኝ ሺህ በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የሐረሪ ተወላጆች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ሆኖ መስከረም 30 ቀን 1997 ዓ.ም. ‹‹የሐረሪ ሕዝብ ክልል መንግስት ሕገ-መንግስት›› በሚል ርዕስ ተሻሽሎ የፀደቀው አዋጅ፣ ስርዓቱ በአደባባይ ከሚመፃደቅበት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ‹ፌደራሊዝም› የሚቃረኑ እና ከዴሞክራሲ ባህሪያት ጋር የሚጋጩ በርካታ አንቀፆች የታጨቁበት መሆኑ ለጠቀስኩት ሀገራዊ ስጋት መነሻ ነው፡፡ ለማሳያም ያህል የክልሉ ምክር ቤት ይቋቋምበታል ተብሎ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የተካተተውን የምርጫ ሕግ መመልከት የሚችል ይመስለኛል፡፡ ይህ ሕገ-መንግስት ተሻሽሎ ከመፅደቁ ሶስት ዓመት ቀደም ብሎ በስታስቲክ ባለሥልጣን ይፋ የተደረገው መረጃ የክልሉ ነዋሪ ህዝብ ብዛት በጥቅሉ 131,139 እንደሆነ ይገልፅና በየብሔሩ ሲከፋፈል ደግሞ ኦሮሞ 41%፣ አማራ 22.77%፣ ሐረሪ 8.65%፣ ጉራጌ 4.34% ሶማሌ 3.87%፣ ትግራይ 1.53%፣ አርጎባ 1.26% መሆኑን ይዘረዝራል፤ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎችም ኦሮምኛ 56%፣ አማርኛ 27.53%፣ ሐረሪ 7.33%፣ ሶማሊኛ 3.70%፣ ጉራጌኛ 2.91%... ነው ይለናል፡፡
በመሬት ያለው እውነታ ይህ ቢሆንም የክልሉ ሕገ-መንግስት ደግሞ በአንቀፅ 49 ‹‹የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት›› በሁለት ጉባዔዎች እንደሚመሰረት ከገለፀ በኋላ፣ እነርሱም ‹‹የህዝብ ተወካዮች ጉባኤ›› እና ‹‹የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ›› እንደሆኑ ይነግረናል፤ ይኸው አንቀፅ በቁጥር 2 እና 3 ላይ ‹የሕዝብ ተወካዮች› ሃያ ሁለት፣ የሐረሪው በብሔሩ ተወላጆች ብቻ የሚወከሉ 14 አባላት ይኖሩታል ይላል፡፡ ይህ ሁኔታ በምርጫ ወቅት እንዴት እንደሚተገበር ደግሞ በአንቀፅ 50 ላይ ‹‹የጉባዔዎች አከፋፈል፣ አወካከልና አመራረጥ›› በሚል ርዕስ ስር እንደሚከተለው ተብራርቷል ‹የሕዝብ ተወካዮች› ለተሰኘው ጉባኤ ከጀጎል ነዋሪዎች አራት፣ ከጀጎል ውጪ ከሚገኙ የከተማና የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበራት 18 አባላት ይመረጡበታል፡፡ ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ደግሞ በክልሉና ከክልሉ ውጪ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ውስጥ 14 አባላት ይመረጡበታል፡፡ ይሁንና ሕጉ ብዙሃኑን የአካባቢው ነዋሪዎች የፖለቲካ ውክልና ከመንፈጉ በተጨማሪ ከክልሉ ተቋማትም ሆነ መብቶች እንዲገለሉ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይም በራሱ በመንግስት መረጃ ሳይቀር በተወላጅነትም ሆነ ቋንቋውን በመናገር ከኦሮሞ ብሔር ቀጥሎ በሁለተኛነት የሚገኙት፣ እንዲሁም አብላጫውን የፖለቲካ ስልጣን ከያዘው ከሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ከእጥፍ በላይ ቁጥር እንዳላቸው የተረጋገጠው አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በዞን ደረጃ እንኳ እንዲዋቀሩ አለመደረጉ ‹ፌደራሊዝሙ› ከአፋዊነት አለማለፉን ያመላክታል (በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በዞን ደረጃ እንዲዋቀሩ የተደረጉ ጥቂት የማይባሉ ብሔሮች እንዳሉ ልብ ይሏል) እንዲህ አይነቱ አደረጃጀት ሌላው ቢቀር እንኳ በዚህ ዘመን ፋሽን ከሆነው ‹‹ውጡ፣ ክልላችሁ አይደለም!›› ከሚለው ነውረኛ ፖለቲካ የመታደግ ጉልበት ሊኖረው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ሁናቴ ዛሬም ድረስ መፅናቱ ‹ብሔረሰቡን እወክላለሁ› የሚለው የእነ አዲሱ ለገሰ ብአዴን ከተላላኪነት ያለፈ ሚና እንደሌለው የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
የሆነው ሆኖ የሙግቱ ዋነኛ መግፍኤ የጀጎል ነዋሪ ከሆኑት ውስጥ ከሶስት እጅ ለሚልቁት አራት፣ ለተቀሩት ጥቂት ሐረሪዎች ደግሞ አስራ አራት የምክር ቤት ወንበር ከመስጠቱ ጋር ይያያዛል፡፡ በዚህ ሕግ መሰረት በጀጎል የምርጫ ክልል ከአራቱ ወንበሮች ውጪ ሐረሪ ያልሆነ የትኛውም ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ለውድድር መቅረብ እንደማይችል በግልፅ ተደንግጓል፡፡ እንዲህ አይነቱ አናሳዎችን በብዙሃኑ ላይ የሚሾም ኢ-ፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍል አብዛኛውን የክልሉ ነዋሪ በገሃድ እየተንፀባረቀ ላለው ባይተዋር አገዛዝ ከማጋለጡም በላይ፣ ከመልካም አስተዳደር ጋር በአዋጅ የተፋታ እስኪመስል ድረስ በሙስናና በአድሎአዊነት ለተተበተበ ስርዓት ዳርጎታል፤ ይህ ሁኔታም በህዝቦች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠርና በጥላቻ ምሽግ ውስጥ እንዲያደፍጡ ማስገደዱ አይቀርም፡፡
በጥቅሉ የብዙዎችን መብት ጨፍልቆና አንዱን ነጥሎ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ማንበር የማታ ማታ ጊዜውን ጠብቆ ከሚፈነዳ አደጋ ጋር ማላተሙና የብሔር ግጭት የመቀስቀስ መዘዝ ማስከተሉን አስቀድሞ ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠበቅም፤ የኢህአዴግ ‹‹እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትበታተናለች›› ፉከራም ይህን መሰል ተንኮል ከገመደው የክልል አወቃቀር ቀመር ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ወደ እንዲህ አይነቱ ድምዳሜ የሚገፋን የሃሳቡ አመንጪዎችም ሆኑ መበታተናችን አይቀሬ እንደሆነ የሚያረዱን ራሳቸው የኢህአዴግ መስራቾች መሆናቸው ነው፡፡ በተቀረ ‹የምንከተለው የፌደራል ስርዓት ቋንቋን መስፈርት ያደረገ ነው› እስከተባለ ድረስ በሐረሪ ያለው አስተዳደር በራሱ በኢህአዴግ አጋፋሪነት በፀደቀው ህገ-መንግስትም ጭምር ተቀባይነት እንደሌለው ከገዥዎቻችን የተሰወረ አለመሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ከፈለገ በክልሉ ምክር ቤት ሰላሳ ስድስቱም ወንበሮች ላይ የመወዳደር መብት ተሰጥቶታል፡፡ በግልባጩ ኦህዴድን ጨምሮ በሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ያልተመሰረተ ማንኛውም የተቃዋሚ ፓርቲ ከሃያ ሁለቱ ወንበር ውጭ በአስራ አራቱ ላይ እጩ ማቅረብ እንደማይችል በሕግ ታውጇል፤ የስራ ቋንቋንም በተመለከተ በክልሉ ነዋሪዎች ከአማርኛ ቋንቋ በሁለት እጅ ያነሰ ተናጋሪ ያለው ሐረሪ እና በስፋት የሚነገረው ኦሮምኛ ብቻ እንዲሆኑ መደረጉም ራሱ አገዛዙ ከሚያቀነቅንለት የቋንቋ ‹ፌደራሊዝም› ጋር ይጣረሳል፡፡ በርግጥም የስርዓቱ ‹ኤጲስ ቆጶሳት› ደጋግመው ‹ለአስራ ሰባት ዓመታት የታገልነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአፍ መፍጫ ቋንቋው እንዲማር፣ እንዲዳኝ፣ እንዲተዳደር… ነው› የሚሉት ሀቲት ማደናገሪያ መሆኑን ለመረዳት ከዚህ የበለጠ ክስተት ሊኖር አይችልም፡፡
በአናቱም የክልሉ ፕሬዝዳንት እና ም/አፈ ጉባዔ ከሐረሪ ብቻ የሚመረጡ ሲሆን፣ ዋናውን አፈ-ጉባዔ ደግሞ በጋራ ሁለቱ ጉባኤዎች እንደሚመርጧቸው በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በፌደራሉ ህገ-መንግስት ላይ የተካተተውና አጨቃጫቂው ‹‹የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት›› የተሰጠው በተናጠል ለሐረሪ ብሔረሰብ ብቻ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ልዩ ችሎታም ሆነ ከላይ የተጠቀሰው ልጓም አልባ ሥልጣን በሌሎች ክልሎች በተመሳሳይ መልኩ ለሚገኙ ብሔሮች አልተሰጠም፤ ለምሳሌ በደቡብ ሲዳማ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ…፤ በአማራ ክልልም የአገው ብሔረሰብ ከሐረሪ የበለጠ ቁጥር ቢኖራቸውም በዞን ደረጃ እንዲዋቀሩ ከመፍቀድ ያለፈ ያገኙት ልዩ መብት የለም፡፡ በነገራችን ላይ ሐረሪ እንዲህ ለሀገር አንድነት አስጊ በሆነ መልኩ እንዲደራጅ የተደረገው በተወላጆቹ ፍላጎት እና ጥያቄ ነው የሚል እምነት የለኝም፤ ምክንያቱም የብሔረሰቡ አባላት እንደማንኛውም ዜጋ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የሚኮሩ መሆናቸውን ከታሪክ መረዳቱ አያዳግትም፡፡ እናም በግሌ የዚህ ሁሉ መግፍኤ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ኤርትራን እና አሰብን የመሰለ የሀገር ጉሮሮ (ወደብ) ኃላፊነት በማይሰማው መልኩ አሳልፎ የሰጠው ኢህአዴግ እንደ መጠባበቂያ አስልቶ ያጠነጠነው የተንኮል ድር ይመስለኛል፡፡ የክልሉ ህገ-መንግስትም ሆን ተብሎ ወደ አንድ ወገን እንዲያጋድል መደረጉ (በአንዳች ክፉ ቀን ሊመዘዝ የሚችል አደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ማቀፉ) ከላይ የጠቀስኳቸውን ማሳያዎች ያስረግጥልናል፡፡
የኃይማኖት መቻቻል…
የሐረሪ ክልል ሌላኛው ችግር የኃይማኖት ልዩነት ያነበረው ውጥረት ለነዋሪው ሕዝብ ተጨማሪ ስጋት መፍጠሩ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን አልቃይዳ እንዳቀነባበረው የታመነውን የቦንብ አደጋ አድርሷል ተብሎ ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ዘግይቶ በነፃ የተለቀቀው ሐምዲ ኢስሐቅ የሐረሪ ተወላጅና የጀጎል ልጅ መሆኑ ክልሉ በማዕከላዊ መንግስቱ በአይነ ቁራኛ እንዲታይ አድርጎት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ሐምዲ በአደጋው ተጠርጥሮ ጣሊያን ሮም ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለዜናው ከፍተኛ ሽፋን መስጠታቸውን ተከትሎ፣ በወቅቱ አንድ ጊዜ ብቻ ታትማ የጠፋችው ‹‹መዝናኛ›› መፅሔት ባቀረበችው ሰፊ ዘገባ እንዲህ በማለት ማስነበቧ አይዘነጋም፡- ‹‹በሐረር ጥብቅ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ስር እየሰደደ ነው፡፡ አንዳንድ ሃይማኖተኞች እስከ ፓኪስታንና አፍጋኒስታን በመዝለቅ የእስላማዊ ትምህርትና ትግል ስልጠናን በመቅሰም እንደሚመለሱ ተረድቻለሁ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በቁጣና በቁጭት የሚመለከቱት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ‹እውነት ከእኛ መካከል የተፈጠረው ሐምዲ ይህንን ሰርቶ ከሆነ አደንቀዋለሁ› ብሎኛል አንድ ወጣት፡፡››
በ2004 ዓ.ም. አፈንዲ ሙተቂ በተባለ ፀሐፊ ተዘጋጅቶ፣ የቅጂ መብቱን በመጋራት የሐረሪ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ወጪውን በመሸፈን ‹‹ሐረር ጌይ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ላይም ሐረር ‹‹እስላማዊ ከተማ ናት›› ተብሎ መገለፁ በራሱ የሚያመለክተው ጉዳይ አለ፤ መቼም ዓለማዊቷን ከተማ ‹‹እስላማዊት›› እያለ የሚጠራን መጽሐፍ መንግስታዊው ተቋም አሳትሞ ማሰራጨቱ፣ ሃይማኖትና መንግስት የተነጣጠሉ ናቸው ብሎ በአዋጅ ለሚለፍፈው ኢህአዴግ መራሹ ስርዓት ምፀት ይመስለኛል፡፡ በርግጥም ‹‹ኢትዮጵያ
የክርስቲያን ደሴት ናት›› የሚሉትንም ሆነ፣ ሐረርን እስላማዊ ለማድረግ የሚያሴሩትን እንዲህ አቅፎና ደግፎ ‹በኃይማኖታችን መንግስት ጣልቃ አይግባ› ያሉ መዕምናን ተወካዮችን (መንፈሳዊ መሪዎችን) ሰብስቦ ማሰሩ አገዛዙ የመጨረሻው አፈና ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው፤ የፖለቲካ ተንታኞችም ‹መንግስታዊ ሽብርተኝነት› የሚሉት ይህ አይነቱን ተግባር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ድሬዳዋ
ሌላኛው የምስራቅ ኢትዮጵያ ውጥንቅጥ የፖለቲካ መገለጫ የድሬዳዋ አስተዳደር ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታትና በቀድሞዎቹ ስርዓታት ድሬ በሀገሪቱ ግንባር ቀደም የንግድ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው ጥቂት ከተሞች አንዷ እንደነበረች ነዋሪዎቿ ዛሬም ድረስ በትዝታ ያስታውሳሉ፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ጁቡቲ ድረስ ተዘርግቶ የነበረው የባቡር መስመር ነው፡፡ ይሁንና ኢህአዴግ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ያሰሙበት ከነበሩ የሀገሪቷ ከተሞች ድሬዳዋ አንዷ መሆኗ ቂም እንዲይዝባት ከመግፋቱም በላይ ‹የነፍጠኛ መከማቻ› ተብላ በ‹ጥቁሩ› መዝገብ መስፈሯ ባለፉት ሃያ ሁለት የስልጣን ዓመታት ባለችበት ትረግጥ ዘንድ በማይታየው የስርዓቱ ‹ክፉ እጅ› ለመዳመጥ ዳርጓታል፡፡
የሆነው ሆኖ ድሬ በተጧጧፈ የንግድ ሂደት ደምቃ የምትታይበት ያ የመኸር ዘመኗ እንደ ጉም በንኖ፣ ለአስከፊ ድህነትና ሥራ እጥነት እጅ መስጠቷን ለማስተዋል ከተማዋን ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ተዟዙሮ መቃኘቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ ርግጥ ነው የኢኮኖሚዋ ዋልታ ከምድር ባቡርና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪክ (ኮተን) በተጨማሪ ሕጋዊም ባይሆን የኮንትሮባንድ ንግድ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ዛሬ ከሞላ ጎደል ሶስቱም የሥራ ዘርፎች በጥልቅ እንቅልፍ የተወሰዱ መስለዋል (ምንም እንኳ ከታማኝ ምንጭ ባላረጋግጥም ኮንትሮባንዱ ‹ፖለቲካዊ ቡራኬ› ማግኘት በቻሉ የስርዓቱ የጥቅም ተጋሪዎች በድብቅ እንደሚሰራ ይነገራል) ምድር ባቡርን በተመለከተ ግን በህይወት ለመኖሩ ደፍሮ የሚከራክር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በርግጥ ለድርጅቱ መፍዘዝ ብሎም መክሰም እንደምክንያት የሚቀርበው ‹ኪሳራ› ቢሆንም ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ፣ የተቋሙ የሒሳብ ሠራተኛ የነበሩ አንድ የድሬዳዋ ነዋሪ በዚህ አይስማሙም፤ እንደእርሳቸው አገላለፅ መስሪያ ቤቱ ለኪሳራ የተዳረገው የህወሓት ሰዎች ከጀርባ ባሴሩበት ደባ ነው፤ ‹‹በኤፈርት ስር ከተቋቋሙ ድርጅቶች አንዱ የሆነው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ላይ የተሰማራው ‹ትራንስ› ከጅቡቲ የሚጫኑ እንደ የዕርዳታ ስንዴና ማዳበሪያ መሰል ምርቶችን በጨረታ እንዲያሸንፍ ይደረግና በጣም እርካሽ በሆነ ዋጋ ለምደር ባቡር የኮንትራት-ኮንትራት ይሰጠዋል፤ ይህ ሁኔታም እየተደጋገመ ሲሄድ ድርጅቱን ለኪሳራ ዳረገው፤ በዚህ ላይ ማነጅመንቱ በተቋሙ ንብረትና ጥቅም ላይ ሙስና ሲፈፅም፣ የስርዓቱ መሪዎች አይተው እንዳላየ ያልፉ ነበር፤ ሠራተኛ ማህበሩ ሳይቀር በግልፅ ለፀረ-ሙስና ሪፖርት ያቀረበባቸው፣ ነገር ግን በሕግ ያልተጠየቁ የአስተዳደር ኃላፊዎች አሉ›› ሲሉ ገደል አፋፍ ስለቆመው የቀድሞ የድሬ ‹ደም-ስር› ምድር ባቡር በቁጭት ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ንብረት በሙሉ በመከላከያ ቴክኖሎጂ (መቴክ) ለሚመራው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ከሰራተኞቹም አብላጫው ተባርረው አምስት መቶ ለሚሆኑት ኢንዱስትሪው ከጥቅምት 30 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝ እየከፋላቸው እንደሚገኝና ከነበሩት 19 ሞተሮች (ባቡር) መካከልም አገልግሎት የሚሰጡት አራት ብቻ እንደሆኑ የድርጅቱ ቅርብ ሰው አረጋግጠውልኛል፡፡ ከአዲስ አበባ-መተሀራ እና ከካሳራት-ኤረር በጠቅላላ 114 ኪ.ሜ. ለሚሸፍን የድልድይ (ሀዲድ) ዕድሳት ይውል ዘንድ የአውሮፓ ህብረት የለገሰውን 60 ሚሊዮን ዩሮንም (ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ የወሰደው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የረባ ስራ ሳይሰራ ‹‹ቄሱም ዝም…›› መሆኑ ብዙዎችን ግራ ከማጋባቱም በላይ በሀገሪቷ ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ያለመኖሩ ማሳያ ነው፡፡
በአናቱም መንግስት ሕገ-ወጡን የኮንትሮባንድ ንግድ በኃይል ሲያስቀር፣ ካለበት ኃላፊነት አኳያ አማራጭ የስራ ዘርፎችን አለመፍጠሩ ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ይቀርባል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ባለስልጣናት አንደበት ሳይቀር የ‹ደረቅ ወደብ› አገልግሎት መስጫ በድሬዳዋ እንደሚመሰረትና ለአካባቢው ነዋሪ አማራጭ የሥራ ዕድል እንደሚሆን ተደጋግሞ ከተነገረ በኋላ፣ ሃሳብ ተቀይሮ ሞጆ ላይ እንዲመሰረት መደረጉ ከተማዋ ‹አልቦ ተቆርቋሪ› መሆኗን እንደሚያሳይ በአንድ ወቅት የመስተዳደሩ ምክር ቤት አባል የነበሩ ግለሰብ ይናገራሉ፡፡ የግለሰቡ መከራከሪያ ‹‹ድሬዳዋ ለጁቡቲ ካላት ቅርበት አኳያ የከባድ መኪናዎችን ምልልስ ያፈጥነዋል፤ ይህ ደግሞ በወደብ ላይ ለሚከማቹ ጭነቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል›› የሚል ነው፡፡ በርግጥም ከአዲስ አበባ እምብዛም ከማትርቀው ሞጆ ይልቅ፣ ለእንዲህ አይነቱ አገልግሎት ድሬዳዋ የተሻለች መሆኗን ለመረዳት ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡
የድሬ ፖለቲካ…
የድሬዳዋ ነዋሪዎችን በተመለከተ በ1998 ዓ.ም (በፈረንጆች 2007 ዓ.ም) በስታስቲክ ባለስልጣን የተደረገው ቆጠራ እንደሚያሳየው አጠቃላይ የሕዝብ ብዛቷ 341 ሺህ 834 ሲሆን፤ ኦሮሞ 45%፣ ሶማሌ 24.3%፣ አማራ 20.7%፣ ጉራጌ 4.5%፣ ትግራይ 1.2%፣ ሐረሪ 1.01% ቁጥር አላቸው፡፡ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎች ደግሞ ኦሮምኛ 46.1%፣ አማርኛ 33.2%፣ ሶማሊኛ 13.4%... መሆናቸውን ይዘረዝራል፡፡ ይሁንና ድሬ በተፃፈው ሕግ እንደ ሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በፌደራል መንግስት ስር መዋቀሯ ቢደነገግም፣ በገሃድ ያለው እውነታ የሚያሳየው (በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ) ኦህዴድና ሶሕዴፓ (የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ባልተፃፈ ሕግ በሚፈራረቁበት አድሎአዊና ብልሹ መስተዳደር ውላ-ማደሯን ነው፤ በርግጥም ዛሬ በሥልጣን ላይ ካለው የኦህዴዱ አሳድ ዚያድ በፊት፣
የከንቲባነትና የምክትሉን ወንበር አንድ የምርጫ ዘመንን ዕኩል በመክፈል ሁለቱ ድርጅቶች በየሁለት ዓመት ተመንፈቁ ሲቀያየሩበት መቆየታቸው የሚያመላክተው ዓብይ ጉዳይ ፌደራሊዝሙ በሕይወት ለመኖሩ በ‹ሳይንስ›ም ቢሆን ሊረጋገጥ አለመቻሉን ነው፡፡
በድሬዳዋ የሚታየው ሌላኛው ‹ፌደራሊዝማዊ› ፌዝ፣ ከነዋሪው ሕዝብ ቁጥር ኦሮምኛ ተናጋሪው 46.1% ሆኖ ሳለ የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ ነው፤ ማንነትን በ‹ቋንቋ› የሚወስነው ኢህአዴግ ድሬዳዋ ላይ ተመሳሳይ መንገድ አለመከተሉ (…መቀነቱ ማደናቀፉ) በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚደረገውን ተቋማዊ ጫና የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡ መቼም ሌላው ቢቀር እንኳ ቢያንስ ራሱ የቀረፀው ‹ፌደራሊዝም› ሁለቱንም የሥራ ቋንቋ ማድረግ የሚቻልበት በቂ መፍትሄ እንደማያጣ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ኩነት ኦህዴድም ልክ እንደ ብአዴን ከተላላኪነትና ቱርጁማንነት ያለፈ የፖለቲካ ቁመና የለውም ወደሚል ጠርዝ ይገፋል (በነገራችን ላይ የአጀንዳው ተጠየቅ በዚህ መልኩ የቀረበው ከራሱ ከኢህአዴግ ርዕዮተ-ዓለም አንፃር እውነታውን ለመፈተሽ ሲባል ነው እንጂ በግሌ የብሔር ፖለቲካ ለኢትዮጵያችን ይበጃታል ብዬ ስለማምን አይደለም)
እንደ መውጫ
ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝሙ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ እንደ አዲስ ሀገር ማዋቀሪያ አማርጭ ፖሊሲ ተደርጎ ሲጠነሰስ የፌደራሊዝሙ ቅርፅ አገሪቱን ይበታትናል ከሚለው ድምፅ ባላነሰ፣ ደርዝ ያለው ሙግት ሆኖ ቀርቦ የነበረው በሀገሪቱ የረዥም ጊዜ የሕዝብ ለሕዝብ ፖለቲካዊ ግንኙነት በአንድ ቋንቋ ብቻ የሚወሰን ማህበረሰባዊ ቡድን (ብሔር) ካለመገኘቱ ባለፈ፣ ያንን የተወሰነ ቋንቋ የሚናገረው ስብስብ በአንድ በተወሰነ መልክዐ-ምድራዊ ቅፅር ውስጥ አይገኝም የሚል ነበር፡፡ ይህንን ክርክር ከዚህ ፅሁፍ አውድ አንፃር ተጨባጭ የሚያደርገው የጠቀስኳቸው ሁለቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በሁለቱም ክልል ውስጥ ከኦሮሞ እስከ ትግሬ፣ ከአማራ እስከ ሶማሌ… ከጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀትና የየራስ ወጥ መለዮ ጋር መገኘታቸው መልክዐ-ምድራዊውን የፌደራሊዝም ቅርፅ ትክክለኛ አማራጭነት ለማስረገጥ በቂ ማሳያዎች ይመስሉኛል፡፡
ከዚህ ባሻገር የኢህአዴግ ‹ፌደራሊዝም› እንኳን ድርጅቱ ሥልጣን ላይ ባለበት ወቅት ቀርቶ፣ በሕዝባዊ ማዕበል በሚወድቅበት ጊዜም ቢሆን በአንድ ጀንበር መቀየር እንደማይቻል ቢታወቅም ሂደታዊ የእርምት አካሄድ ብቸኛው ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ይህ ፌደራሊዝም የብሔር ግጭትን ከመከላከል በላይ ተራምዶ፣ ሰሞኑን እንዲያ ‹አሸሼ-ገዳሜ› የሚባልለትን በሕዝቦች መካከል አንድነት ሊያጠብቅ ቀርቶ በአግባቡ ባለመተግበሩ (ለምሳሌ በሐረሪና ድሬዳዋ የሚገኙ፣ ነገር ግን በክልሎቹ ስልጣን ውስጥ ያልተወከሉ ብሄሮች) የተፈጠሩት ኩነቶች ወደሰዓት ቦንብነት እየተቀየሩ የመጡትን የተለያዩ ቋንቋ ተናገሪዎች የእርስ በእርስ ትንቅንቆች መግራት ከማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ይህ ኩነት “ደግሞ የእዚህች አገር ህልውናን ለመፈታተን ጥቂት ጊዜያቶችን ብቻ መጠበቅ የማይቀር ዕጣ ፈንታ ያደረገው ይመስለኛል፡፡

No comments: