መነሻቸውና መድረሻቸው ከየትና ወዴት እንደሆነ ያልተገለጸው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ የመን ሰንዓ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በየመን የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው መታሰራቸው ተሰማ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በየመን የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ታስረዋል የተባለው ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሰንዓ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከመያዛቸው ውጪ ከየት ተነስተው ወዴት እንደሚሄዱ አልታወቀም፡፡
በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጁት አልቃይዳ፣ አልሸባብ፣ ኦነግና ኦብነግ ጋር በአሸባሪነት የተፈረጀው ግንቦት 7 ዋና ጸሐፊውን በሚመለከት ያወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው፣ አቶ አንዳርጋቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ካወቀ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ለማስለቀቅ ውስጥ ለውስጥ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከአስመራ በየመኒያ አየር መንገድ ተሳፍረው፣ በየመን ሰንዓ ትራንዚት በማድረግ ወደ ኳታር ዶሃ ለመጓዝ ሲሞክሩ ሳይሆን እንደማይቀር የተለያዩ ድረ ገጾች ዘግበዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ደርግ የንጉሡን ሥርዓት በኃይል ከተቆጣጠረበት ሁለት ዓመታት በኋላ በ1969 ዓ.ም. ይከታተሉት የነበረውን የምህንድስና ትምህርት አቋርጠው ወደ ትግል መግባታቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓ) በመቀላቀል ትግል የጀመሩት አቶ አንዳርጋቸው፣ የበረሃ ትግላቸውንም ከተወሰኑ ጊዜያት በላይ እንዳልገፉበት የሚናገሩት ጓደኞቻቸው፣ ከኢሕአፓ አመራሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ወደ እንግሊዝ አገር መሄዳቸውንም ይናገራሉ፡፡ በእንግሊዝ የስደት ዘመናቸው የደርግ መንግሥትን ይታገሉ ለነበሩት የኢሕአዴግ ታጋዮች የተለያዩ ዕርዳታዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተጠቁሟል፡፡ ኢሕአዴግ የደርግ ሥርዓትን አስወግዶ ሥልጣን ሲይዝ በተደረገላቸው ጥሪ በ1983 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ አንዳርጋቸው፣ ከኢሕአዴግ ጋር የነበራቸው ቆይታ ከሁለት ዓመታት በላይ አልዘለቀም፡፡
በሽግግሩ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ጸሐፊ በመሆን የሠሩት አቶ አንዳርጋቸው፣ በ1985 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ መልቀቂያ አስገብተው የተመደቡበትን ኃላፊነትና የኢሕአዴግ አባልነታቸውን በመተው በስደት ወደኖሩበት እንግሊዝ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በድጋሜ ወደ አገር ቤት የተመለሱት በ1997 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን፣ ወዲያውኑ የቅንጅት አባል በመሆን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ለመሆንም ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በ1997 ዓ.ም. የነበረውን አገራዊ ምርጫን ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው የኢሕአዴግና የቅንጅት አለመግባባት የቅንጅት አመራሮችና የተወሰኑ አባላት ሲታሰሩ እሳቸው ባይታሰሩም፣ ቀደም ብሎ በተለያዩ ምክንያቶች ታስረው እንደነበርም ይታወሳል፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው የግንቦት 7 ድርጅት አመራር አባል የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው፣ አገር ውስጥ በህቡዕ ተደራጅተው መንግሥትንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመገርሰስ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ክስ ተመሥርቶባቸው ከነበሩት እነብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና አቶ አሳምነው ጽጌ (ማዕረጋቸው ተገፎ ነው)፣ እንዲሁም የግንቦት 7 ድርጅት አመራር ከሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር መከሰሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እነጄኔራል ተፈራ ማሞ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ሲወስን፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሞት እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያና የመን ባደረጉት እስረኛን አሳልፎ የመሰጣጠት ስምምነት መሠረት የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው፣ አንዳንድ በጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም አንድ ነጋዴ ከባንኮች ብድር ወስደው ካገር ከወጡ በኋላ የመን በመያዛቸው፣ የየመን መንግሥት አሳልፎ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የአቶ አንዳርጋቸውን በየመን ቁጥጥር ሥር መዋል አስመልክቶ ለሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡
Source: Reporter
No comments: