የማንዴላ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

የነፃነት እና የፀረ-ዘረኝነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ስርዓተ ቀብር እሁድ ታኅሣሥ 6 ቀን 2006 ዓም ደቡብ አፍሪቃ ኩኑ በተባለችው የትውልድ መንደራቸው ተካሄደ። ለማንዴላ ክብር በቀብር ስርዓቱ 21 ጊዜ መድፍ የተተኮሰ ሲሆን፤ የጦር ጀቶች ከዕድምተኛው በላይ ሲያንዣብቡም ታይተዋል።
  ከእንስሳት ቆዳ የተሰፉ ባሕላዊ ልብሶችን የለበሱ ሀዘንተኞች ለማንዴላ ውዳሴ አሰምተዋል። የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ ስርዓት ከተገረሰሰ በኋላ የሀገሪቱ የመጀመሪያው በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ኔልሰን ማንዴላ ግብዓተ መሬት የተፈፀመው በምሥራቃዊ ደቡብ አፍሪቃ በምትገኘው ኩኑ በተሰኘችው ገጠራማ መንደር ውስጥ ነው። በቀብር ስርኦቱ ላይ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገኙ የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ቀደም ብሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በማንዴላ ቅፅር
ውስጥ በተዘጋጀው ሰፊ ድንኳን በመገኘት ለነፃነት ታጋዩ ውዳሴ በማሰማት የጭፈራ ትርዒት አሳይተዋል። ኔልሰን ማንዴላ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ሐሙስ፣ ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓም ማረፋቸው ይታወሳል።
ገና ከማለዳው ነበር መላ የኩኑ ነዋሪዎች ማለት በሚቻል ሁኔታ ሕዝቡ በአጠቃላይ ወደ አደባባይ የወጣው። የመጀመሪያዎቹ ወደ 5000 የሚጠጉት የቀብር ታዳሚዎች የማንዴላ ስርዓተ-ቀብር ላይ ለመሳተፍ ተሰባስበዋል። ሞተረኛ ፖሊሶችም የውጭ ሃገራት መሪዎችን በማጀብ አውራ ጎዳናዎቹ ላይ በመመላለስ ተጠምደዋል። በማንዴላ የትውልድ መንደር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎችም ከጎዳናዎቹ ራቅ እንዲሉ ፖሊሶች ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ለዓለም ማኅበረሰብ ስርዓቱን ለመዘገብ በቀብር ስርዓቱ ላይ ወደ 2000 የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችም መታደማቸው ታውቋል። የቀብር ስርዓቱ ለበርካታ ታዳሚዎች እጅግ ስሜታዊ እንደነበረም ተዘግቧል። የቀብር ስርዓቱ ወደ አራት ሠዓት ገደማ መዝለቁም ተጠቅሷል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ልደት አበበ
Source: www.dw.de


No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog