ያሬድ ጥበቡ በትግል ስማቸው ጌታቸው ጀቤሳ ይህን ጽሁፍ ያሰፈሩት በፌስቡክ ገጻቸው ነበር:: ለግንዛቤ ይረዳል ብለን በማሰብ አካፍለናችኋል::
ይህ ፎቶ ከተነሳ 30 አመት ሆነው ። የካርቱምን የአራዊት መናኸሪያ (ዙ)፣ ስንጎበኝ የተነሳነው ነው ። ከግራ ወደቀኝ ህላዌ ዮሴፍ፣ ታምራት ላይኔ፣ ዳዊት፣ ሙሉአለም አበበና እኔ ነን ። ህላዌ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሲሆን፣ እኔ ታምራትና ዳዊት በአሜሪካ ስደተኞች ነን ። ሙሉአለም የኢህአዴግ የአዲስ አበበሰ ከንቲባ ሆኖ ካገለገለ በሁዋላ፣ አጨቃጫቂ ነበረ ከተባለ የብአዴን ስብሰባ መልስ፣ ባህርዳር ቤተመንግስት አልጋው ላይ ተንጋሎ ሳለ፣ መስኮቱ ክፍት ስለነበር ከውጪ በተወረወረ የእጅ ቦምብ መገደሉን ሰምቻለሁ ።
ዳዊት የወያኔ ባታሊየን ኮማንደር የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተሰዶ መጥቶ 22ኛ ና ፒ ስትሪት መገናኛ ላይ የቤንዚን ማደያ ተቀጣሪ ሆኖ ሲሰራ አየሁት ። እናም አዘንኩ ። በስንት ጦር ሜዳ ጀግንነቱን ያስመሰከረ የጦር መሪ ዝቅ ብሎ ለእለት ጉርሱ ሲማስን ማየት ልብ ደሰብራል ። ዝም ብሎ የወያኔ ጄኔራል በመሆን የፎቆች ባለቤት እንደማይኮንና፣ የፖለቲካ ሰልፍን ካላሰመሩ ትግሬነትም ሆነ ጀግንነት ብቻውን ፋይዳ እንደሌለው ዳዊት ጥሩ ምስክር ይመስለኛል ።
ታምራት ከእስር እንደተለቀቀ በስልክ የተገናኘን ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ የጴንጤዎች ስብሰባ ላይ ሲያለቃቅስ በዩቱብ ከማየት ውጪ ሰምቼውም አግኝቼውም አላውቅም ። ወደ ሃይማኖት ፊቱን ማዞሩን አልጠላሁትም ነበር ። እኔ ራሴም ፊቴን ወደመንፈሳዊ ጥናቶች መልሼ እነ ኤካርት ቶሌን ማጥናት ጀምሬ ስለነበር፣ ታምራት “ከእንግዲህ ስለ ፍቅር አስተምራለሁ” ማለቱን ወድጄው ነበር ። በብቸኛው የስልክ ወሬያችንም ያንን የገለፅኩለት ይመስለኛል ። ሆኖም አሜሪካ ሲመጣ መገናኘት አልፈለገም ። የመጨረሻዎቹ የበረሃ አመታት ላይ አርሱ ከነመለስ ወግኖ የቆመ ቢሆንም፣ አግኝቼ ላወራው ግን ይናፍቀኛል ። የሆነው ሁሉ እንዴት እንደሆነ የርሱን ግንዛቤና አስተያየት ለማወቅ ሁሌም እፈልጋለሁ።
ከኢህአፓና ኢህዴን የበረሃ ህይወታችን በኋላ ከህላዌ ጋር የተገናኘነው ሁለት ጊዜ ነው ። አንዱ ከምርጫ 97 ሁለት ወራትበፊት አዲስ አበባ በሄድኩበት ወቅት፣ ምክትል ከንቲባ ሳለ አርከበ ቢሮ ውስጥ ያደረግነው አጭር ውይይት ነው ። ሌላ ጊዜ የተገናኘነው ከበረከት ጋር ዋሽንግተን መጥተው፣ አምባሳደር ብርሀኔ በቤቱ የራት ግብዣ አድርጎላቸው ሳለ ነው ። አመሻሽ ላይ ውጪ እናውራ ተባበለን በረንዳው ላይ ቁጭ ብለን ሳለ፣ ቃል አቀባይ ሶሎሜ ታደሰ መጣችና “ደህነታችሁን ለማረጋገጥ ነው” ብላ ቀለደች ። ህላዌም ሲመልስ “ነገ አንቺ ከሰልፈኛው ጎን ቆመሽ ይሰቀሉ እያልሽ ስትፈክሪ ሰለ ንፅህናችን የሚመሰክርልን ጀቤሳ ነው” ብሎ መለሰና ተሳሳቅን ። በቅርቡ ሶሎሜ ነፃ እጩ የፓርላማ ተወዳዳሪ ሆና ስትቀርብ በሎተሪ መጣሏን ስሰማ ይህችን ምሽት አስታወስኩ ።
የዚህ ፎቶና መጣጥፍም መልእክት ይሄው ይመስለኛል ። ትናንት የት ነበርን፣ ዛሬ የት ነን? የሚል ። ፖለቲካ ውስጥ መፋታትና መለያየት ተፈጥሯዊ መሆኑን ። ሆኖም መቃቃርና ጠላትነት ቦታ ሊኖረው እንደማይገባ። መለያየትም እስከመጨረሻው መሆን እንደሌለበተ ። እኔና ታምራት ከድርጅታችን ከተለየን ያካበትነውን የእውቀት፣ የመንፈሳዊነት ሀይል ይዘን ብንመለስ ኢህአዴግን እንዴት አድርገን ከገባበት አረንቋ ልናወጣው እንደምንችል ሳስበው “ወይ አለመታደል” እላለሁ ። እኔ እንደዚህ በአግራሞት ብዋጥም፣ ዛሬ ጠዋት ባህርዳር የሚገኘው የሰማእታት ሃውልት አስጎብኚ፣ ግድግዳው ላይ ከተሰቀለው ፎቶዬ ሥር ቆማ “ይህ ደግሞ ጌታቸው ጀቤሳ ይባል የነበረው የአመራር አባላችን ነው ። በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የግንቦት ሰበት መሥራች ሆኖ፣ ዴሞክራሲያችንን በመፈታተን ላይ ይገኛል” እንዳለች ጉብኝት ላይ ከሚገኝ የሥራ ባልደረባዬ የቫይበር መልእክት ደረሰኝ ። አይገርምም የሰው ነገር? የአስቴር አወቀን “ለሰው ሞት አነሰው ትላለች ቀበሮ” ን እያዳመጣችሁ እስቲ አላምጡት ይህን ነገር ።
No comments: