ሰሞኑን በህውሓት/ኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ባሉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰማያዊ ፓርቲ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘመተ ያለውን የስም ማጥፋት ፕሮፓጋንዳ በአትኩሮት ሲከታተለው ቆይቷል፡፡ በዚህም የህዝብ ንብረት የሆኑ ሚዲያዎች፤ ለህዝብ አገልግሎትና በህዝብ ግብር በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚተዳደሩ የማህበረሰቡ የአገልግሎት ተቋማት ጭልጥ ብለው የሰማያዊ ፓርቲ ስም በማጉደፍ እና በማብጠልጠል ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን በትዝብት ተመልክተናል፡፡
ሰማያዊ ከተቋቋመ ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ በደሎችን በሀገርም ሆኖ በውጪ ሲፈፀም ዝም ብሎ የመመልከት ትዕግስት ኖሮት አያውቅም፡፡ ይህ በዋነኝነት ፓርቲው የተቋቋመለት መርህ ነው፡፡ በግራዚያኒ ስም ለሚሰራ ሃውልት ተቃውሞ ለማሰማት አስፈላጊውን የህግ መስፈርት አሟልተን ባለበት ሁኔታ በገዢው ፓርቲ ትእዛዝ አባላቶቻችን ተደበደቡ፡፡ በሳውዲ አረቢያ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው ኢሰብአዊ በደል ሰቆቃቸውን ለማሰማት በጠራነው ሰልፍ እንደገና በመንግስት ትእዛዝ አባላቶቻችን ላይ ድብደባና እስር ተፈጸመባቸው፡፡ በቅርብ በሊቢያ፣ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በየመን በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ የደረሰውን እጅግ ሰቅጣጭ እና በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ብሔራዊ ውርደት ሰማያዊ ፓርቲ አስቆጭቶታል፡፡ በዚህም የተነሣ እነዚህ በደሎች መድረሳቸው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በንቃት እየተከታተለ መረጃው ለህዝብ እንዲደርስ እያደረገ ጎን ለጎን መንግስት ለወገኖቻችን የድረሱልኝ ጥሪ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ፓርቲያችን ሲያሳስብ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ይኸንን ዘግናኝ እና አረመኔያዊ ድርጊት ማውገዛችን እና መቃወማችን ከዛም አልፎ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመ ተግባር መከታተላችን ፓርቲው ሊያስመሰግነው ሲገባ ይልቁንም ገዥው ፓርቲ በተለያዩ የመንግሰት ሚዲያዎች የሰማያዊ ፓርቲ ስም ለማጠልሸት ሲሯሯጡ ማየት ትዝብት ውስጥ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በህግም የሚያስጠይቅ ጭምር ነው፡፡ መንግስት ሃላፊነቱን እና ተግባሩን በመመርመር በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ብሔራዊ ውርደት ዳግመኛ እንዳይፈጸም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ገዢው ፓርቲ ከሃገር ብሄራዊ ጥቅም ይልቅ የድርጅቱ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ በልጦበት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
ከዛም አልፎ ተርፎ ዜጎች በሀገራቸው በሚደርስባቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች ዙሪያ ተነጋግሮ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እየተሳናቸው በየበረሃው ሲሰደዱ የሚደርስባቸው ስቃይ አልበቃ ብሎ አይኤስ አይኤስ በሚባል አሸባሪ ቡድን የደረሰባቸውን ዘግናኝ በደል ሃዘኑ ገና ከልባችን ሳይጠፋ በሃገር ውስጥ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚንቀሳቀስ ሰማያዊ ፓርቲን ከእንደዚህ አይነት ነውረኛ እና ሰይጣናዊ ተግባር ከሚፈጽመው ድርጅት ጋር ህብረት እንዳለን ለማሣየት መሞከሩ እጅግ ጸያፍና ለዜጎቹ ያለውን ንቀት ማሳያ ጭምር ነው፡፡
ሰማያዊ በዜጎቻችን ላይ ከ1ዓመት ከ6 ወር በፊት በሳውዲ አረቢያ እንዲሁም በተለያዩ አገራት አገራቸውን በመንግስት የአስተዳዳር ደካማነት በተፈጠረው ችግር ምክንያት ጥለው በመሰደዳቸው፤ ለተለያየ ችግር እና ብሔራዊ ውርደት የሚዳረጉ ወገኖቻችንን ችግር ለመፍታት ጥሪ ለመንግስት አድርገን የአንድ ሠሞን ጫጫታ ከመሆን አልፎ ለዘለቄታው ችግሩን ለመፍታት ባለመቻሉ ለዳግመኛ ዘግናኝና አረመኔያዊ ስቃይ ዜጎቻችንን መዳረጉ በገሀድ የሚታይ እውነታ ሆኗል፡፡
ስለዚህ መንግስት ሰማያዊን በመውቀስ ፋንታ ለድርጊቱ ቀጥተኛ ተጠያቂ የሆነውን የድርጊቱ ፈፃሚ አይኤስ አይኤስ ተጨባጭ አፀፋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አቅም እንደሌለው ጭምር አስመስክሯል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው የሚደርስባቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንዲሰደዱ የዳረጋቸው የተሣሣተ አመራር የያዘው ህወሓት/ኢህአዴግ መሆኑን ተረድቶ ነገ ከታሪክ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል ሰማያዊ ፓርቲ ያስገነዝባል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በአዋጅ የተሰጠውና ስልጣን ወደጎን በመተው ሰማያዊ ፓርቲ የስራ እንቅስቃሴውን ለመተለም የሚያደርገውን ተግባር በህወሓት/ኢህአዴግ እና በሌሎች የሚደረግበት ጣልቃ ገብነትን በዝምታ ማለፉ ፓርቲያችንን እጅግ ያስቆጣ ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕጋዊነት እውቅና የሰጠውን ተቋም ህወሓት/ኢህአዴግ እና ደጋፊዎች በአሸባሪነት ሲፈርጁ ምንም ለማለት አለመፈለጉ ሰማያዊ ፓርቲ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነቱ ላይ ለሚያነሳው ጥያቄ ዋንኛ ማሳያ ነው፡፡
ሰማያዊ በአገራችን ጠንካራ አማራጭ ፓርቲ እንደሆነ አምነው ከጎኑ የቁሙትን በሙሉ እያመሰገነ፤ ፓርቲው የህዝብ አማራጭነቱን ለማጥፋት በከፍተኛ ጥረት የተሰማራው ህወሓት/ኢህአዴግ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ እያስጠነቀቀ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ እየፈፀመበት ያለው የስም ማጥፋት ውንጀላ ሰማያዊ ፓርቲ ከጀመረው ትግል ፈፅሞ እንደማይገታው በፅኑ ያሳውቃል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments: