ሚያዝያ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው ግንቦት 12/2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት በሃያዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም
ተስፋው ፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ ናቸው።
ተከሳሾች “ኤርትራ ውስጥ መቀመጫውን ባደረገውና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ግንቦት ሰባት ስር አባል ሆነው የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ወስነው ከድርጅቱ ጋር ለመቀላቀል የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር አቋርጠው ሊሻገሩ ሲሉ
በቁጥጥር ስር መዋላቸውን” በዚህም የተነሳ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በአባልነት በመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ እንደሚያመለክት ጋዜጣው ዘግቧል።
ተከሳሾቹ ጠበቃ ማቆምን በተመለከተ ከፍርድ ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሁሉም ተከሳሾች፣ ‹‹ከተያዝን ጊዜ ጀምሮ በደል እየደረሰብን ነው፤ ይህ የብቀላ ስራ ነው ብለን ስለምናምን እና በዚህ ሁኔታ ተከራክረን ፍትህ እናገኛለን ብለን ስለማናምን
የግልም ሆነ የመንግስት ጠበቃ አንፈልግም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው አቤቱታ ‹‹የተከሰስኩበት ወንጀል በክሱ ላይ የተመለከተው ሆኖ እያለ በግድ ቀድሞ እሰራበት በነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ጓደኞቼ ላይ በተለይም በፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እና በህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የግንቦት ሰባት አባል እንደሆኑ ተደርጎ መስክር እየተባልኩ ስቃይ እየደረሰብኝ ነው›› ብሎአል።
“ማንነትን መሰረት ያደረገ ስድብ እንደሚሰደብ፣ ጨለማ ቤት እንደሚታሰር እንዲሁም የተጠየቀውን ካልፈጸመ ወደማዕከላዊ ሊመልሱት እንደሚችሉ እንደሚዝቱበት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱ ወጣት ብርሃኑ አለኝ ያለውን አቤቱታ በጽሑፍ እንዲያቀርብ በማሳሰብ፣ ተከሳሾች በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለመቀበል ለግንቦት 28/2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሶስቱ የሰማያዊ ፓርቲ ተከሳሾች ከዚህ ቀድም በተለያዩ ሰበቦች እየታሰሩ ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስባቸው ቆይቷል።
የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ሃለፊ የነበረው ወጣት ተስፋሁን አለምነው በቅርቡ በትጥቅ ትግል የሚታገሉ ሃይሎችን መቀላቀሉ መዘገቡ ይታወሳል።
በአገር ውስጥ እየደረሰ ያለውን አፈና በመሸሽና ስርአቱን በሃይል ለመታገል በርካታ ወጣቶች የትጥቅ ትግል የሚያራምዱ ሃይሎችን እየተቀላቀሉ ነው።
የወጣቱ መፍለስ ያስደነገጠው የሚመስለው ገዢው ፓርቲ በድንበሮች አካባቢ ክትትሉን ቢያጠናክርም፣ ወጣቶቹ መንገዱን እያጠኑ በመቀላቀል ላይ መሆናቸውን የተቃዋሚ መሪዎች ይናገራሉ።
No comments: