የብአዴን አመራሮች ድርጅታቸው የገጠመውን ፈተና ተናገሩ


ሚያዝያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የብአዴን ማእከላዊ የዞን ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች ውይይት በቀጣይ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን መመሪያ ለአባላቱ ባስተላለፈው የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት፣ ድርጅቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የድርጅቱ
ልዩ ልዩ አመራሮች ተናግረዋል፡፡
የብአዴን ማእከላዊ ዞን ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ሲናገሩ የብአዴን አመራሮች በ1990 ዓ.ም ከታየው የጥገኝነት ዝቅጠት አንስቶ በርካታ ፈተናዎችን ለማለፍ እንደተገደዱ ገልጸው፤ ጥገኝነት የስርአቱ አደጋ መሆኑን አምነው ተናግረዋል፡፡
ሃላፊው ‹‹ የክራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አልተተካም፡፡የክራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት መሰረት አልተናጋም ” ያሉ ሲሆን፣ በርካታ ፈተናዎች አሉብን፡፡አርሶ አደሩን እናደርሳለን ብለን ባሰብነው የምርታማነት ደረጃ ላይ አለማድረሳችን ትልቅ ፈተና ” ሆኖብናል ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ ዝቅተኛ እሴት ፈጣሪ መስኮች ብቻ የመሰማራት አዝማሚያ እንጅ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገውን እንቅስቃሴ መዋቅራዊ ለውጥ ሊያግዙና ሊያሳድጉ የሚችሉ ትልልቅ እሴት ፈጣሪ እንቅስቃሴዎች አለመደረጋቸውንም ገልጸዋል።
የክልሉ ቴክኒክ ሞያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዘላለም ንጉሴ በበኩላቸው ስርዓቱን ያጋጠሙት በርካታ ፈተናዎች እንዳሉ ገልጸው፤በተለይ ክራይ ሰብሳቢነት ትልቁ አደጋ በመሆን በከተሞች አካባቢ ገዝፏል ብለዋል፡፡
በገዢው ፓርቲ አመራሮች መካከል የትግል መቀዛቀዝ ፣በጽንሰ ሃሳብም ሆነ በክህሎት አቅምን የማጎልበት የተዳከመ ነገር መታየቱንም ተናግረዋል፡፡
ያመጣነውን ለውጥ እየተፈታተነው ያለው በኋላ ቀርነትና በክራይ ሰብሳቢነት በተግባር እየተከሰተ ያለው ሁኔታ መሆኑ የገለጹት የቀድሞው የባህርዳር ከንቲባና የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ያየህ አዲስ ሰራተኛው በሚፈጽማቸው ስራዎች በኩል ያለው ስልቹነት መታየቱ ስርአቱ በፈለገው ደረጃ ህዝብን ይዞ መጓዝ እንዳላስቻለው ተናግረዋል፡፡የገዢው መንግስት ህዝብን በሚፈጽማቸው ስራዎች አለማሳተፍና የአስገዳጅነት ባህሪ ማሳየቱ ጸረ ዲሞክራሲዊ አካሄድ የስርአቱ አደጋዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
በመግለጫው የተሳተፈፉት አመራሮች ኢህአዴግ በ24 ዓመታት አገዛዙ ችግሮችን መቅረፍ እንዳልቻለ ተናግረው፤ በየጊዜው የሚቀርቡትን ችግሮች በቀጣይ አሻሽላለሁ በማለት መናገሩ ልማዱ ነው ሲሉ ያክላሉ።

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog