“የአሲምባ ፍቅር” ደራሲ በአፍታ ቆይታ

የታጋይ ቤተሰቦች አዳዲስ መረጃዎች አግኝተዋል:: 
የመፅሀፉ ፋይዳ
መፅሀፉ የታሪክ ማስታወሻ ነው፡፡ በትግሉ ለተሰዉት ሀውልታቸው ነው፡፡ በህይወት ላለነው ደግሞ ምን ጠንካራ ጎኖችና ጉድለቶች እንደነበሩን በማሳየት፣ አዲሱ ትውልድ ከኛ ጥንካሬ እንዲማር፤ ስህተታችንንም እንዳይደግም ያደርገዋል፡፡ ባለታሪኮቹ ከሞትን
በኋላ ሌሎች በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርተው ከሚፅፉት በህይወት ያለን ሰዎች ምስክርነታችንን ብንሰጥ ጠቃሚ ይሆናል። from the horse’s mouth (ከባለቤቱ አፍ) እንደሚባለው፡፡
ስለ መጽሐፉ ምን ተባለ? 
መፅሀፉ ከወጣ በኋላ እዚህ ላይ ይህንን ረስተሃል፣ እዚህ ጋ እንዲህ ነበር፤ በዚህ በኩል አልፈናል፣ በዚያ ወጥተን ወርደናል… የሚሉ የተለያዩ አስተያየቶች ደርሰውኛል፡፡ ይህ የሚጠበቅ ነው፡፡ እኔ የፃፍኩት ራሴ በአይኔ ያየሁትንና የሰማሁትን ብቻ ነው፡፡ ከኔ መንገድ ውጪ ግራና ቀኝ አልሄድኩም፡፡ 
የታጋይ ቤተሰቦች ምን አሉ?
የጓድ ግርማ በልሁ እህት መፅሀፉ ከወጣ በኋላ ኢሜይል አደረገችልኝ፡፡ ጓድ ግርማ አየር ወለድ ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ስለሱ የሚያውቁት በ1966 ለስራ ተመድቦ አስመራ እንደሄደ ብቻ ነው፡፡ እህቱ ስትነግረኝ፤ አልፎ አልፎ እንግሊዝ ሄዷል ከሚል ተባራሪ ወሬ ውጪ የኢህአፓ ሰራዊትን ተቀላቅሎ አሲምባ እንደነበር ያወቁት መፅሃፉን ሲያነቡ ነው፡፡ መፅሀፉ ላይ እንደተጠቀሰው፤ ኢህአፓን ከተቀላቀሉ የአየር ወለድ አባላት አንዱ ነበር፡፡ ማስታወሻ እንዲሆናት ብዬ ስለሱ የማውቀውን ባህርይ በሙሉ ነገርኳት፡፡ ወደ ቤጌምድር በለሳ ስንሄድ አንድ ጋንታ ነበርን፡፡ እናም የማውቃቸውን ባህርያቱን ስነግራት እጅግ በጣም ተደሰተች፡፡ የአየር ወለድ አባላት ለነበሩትና ኢህአሰን ከተቀላቀሉት ውስጥ እነ ጓድ ቢኒያምን ስለ ጉዳዩ ስለነገርኳቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እንደሚያገኟት ቃል ገብተዋል፡፡
የግደይ እህትም በተመሳሳይ በስልክ አገኘችኝ፡፡ ወንድሟ ወደ ራሺያ ሲሄድ በጣም ትንሽ ስለነበረች፣ እሷም ሌሎች እህቶቹም ብዙም አያውቁትም፡፡ ስለሱ የሚያውቁት ወሎ ላይ ተይዞ አራተኛ ክፍለ ጦር መታሰሩን ብቻ ነው፡፡ እሱ ከራሺያ ሲመለስ ወደ አሲምባ ነበር የመጣው፡፡ ይህ ለነሱ አዲስ መረጃ ነው፡፡ ስለወንድማቸው ባህርይና ቁመና የማውቀውን በስልክ ብዙ ነገርኳቸው፤ እነሱም በጣም ደስ አላቸው፡፡ 
የፀጋዬ ገብረመድህን ወይም ደብተራው ቤተሰቦችም አግኝተውኛል፡፡ ወንድሙ በእንባ እየታጠበ  “ስለሱ ምንም አናውቅም ነበር፤ የአሲምባ ፍቅር መፅሀፍ ላይ የሁላችሁም መካሪ እንደነበር፤ እንዲሁም በተባይ እንዳትሰቃዩ የሚያደርገውን እንክብካቤ ስናነብ፣ ወንድማችን በህይወት የተመለሰ እስኪመስለን ድረስ የደስታ ስሜት ፈጠረልን” ብሎኛል፡፡ 
መድፈሪያሽ በላይ ወይም ጀሚላ የመጀመሪያዋ ወደ በረሀ የመጣች ሴት የኢህአሰ ታጋይ ናት። ቤተሰቦቿ ስለሷ የሚያስታውሱት ወደ በረሀ ከመውጣቷ በፊት በነበራት ፎቶግራፉ ብቻ ነበር።  ወንድሞቿ መፅሀፉን ካነበቡ በኋላ ደውለው አናግረውኛል፡፡ ስለሷ በማወቃቸው  ደስታቸው ወደር እንደሌለው ገልፀውልኛል፡፡
የድላይ እህት በጣም የሚያሳዝን ደብዳቤ ፃፈችልኝ። “ለዘመናት ውስጤ የነበረው ቁስል ተፈውሶልኛል፡፡ እህቴ የት እንደነበረች፣ ስለታጋይነት ሚናዋና የት እንደተሰዋች ለማወቅ ችያለሁ። መፅሀፉን ልክ እንደ ድርሳነ ቅዱሳን ትራሴ ስር አድርጌው ነው የምተኛው” በማለት ውስጣዊ ስሜቷን ገልፃልኛለች፡፡ “እህቴ የታለች ብዬ ጠይቄ ነበር፣ ‹እህትሽ የነበረችው ከኢህአሰ ጋር ነው፤ እኛ ኢህዴን ነን፤ እኛ ጋር አልመጣችም› የሚል መልስ ስላገኘሁ፣ እህቴ ልክ ውሻ ስታባርር እንደሞተች ታሪክ አልባ ሆና ቀረች  እያልኩ አዝን ነበር፡፡ አሁን ግን ስለሷ በማወቄ ተደስቻለሁ” ብላለች፡፡ 
ደራሲው ወደ አሲምባ ይጓዛል
በመጪው ሀሙስ ከድላይ እህትና ከቤተሰቦቿ ጋር እገናኛለሁ፡፡ በአማራ ክልል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አዘጋጅነት ዛሬ በመፅሀፉ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ ነገ ወደ ወልዲያ እሄዳለሁ፡፡ ወልዲያ ለኔ ትልቅ ትርጉም ያላት ቦታ ነች፡፡ የመኖር ሁለተኛ እድል የሰጠችኝ ቦታ ነች፡፡ 
ይመር ንጉሴ ማርኮ ከወሰደኝ በኋላ የተደበቅኩባትን ያቺን ቤት አያታለሁ፣ ከይመር ንጉሴ ቤተሰቦችም ጋር እገናኛለሁ፡፡ ይመር ንጉሴ ወደ አሲምባ ሊሸኘኝ ሲዘጋጅ፣ ማንነቴን ለመለወጥ ሲባል ጸጉሬን የተላጨሁባትን ቦታ ተመልሼ አያታለሁ። ከዚያ በመፅሀፉ ላይ መቀሌ የፓናል ውይይት ስለተዘጋጀ እዚያ እሄዳለሁ፤ በዚያው ወደ አዲግራትና ወደ ትውልድ ቦታዬ ዛላምበሳ ጎራ እላለሁ፡፡ በመጨረሻም ወደ ታሪካዊቷ አሲምባ ሄጄ ዳህዋንንም እጎበኛለሁ፡፡ አሁን በእግሬ መሳሪያ ተሸክሜ ሳይሆን በመኪና ነው የምሄደው፡፡
Source: Addis Admass

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog