በዳንኤል ክብረት: -
ከግንቦት 9 እስከ 11 ቀን ድረስ በትግራይ ክልል አኩስም ከተማ ‹ሀገር አቀፍ የግእዝ ዐውደ ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ በዓይነቱ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ሲዘጋጅ የመጀመሪያ የሆነው ዐውደ ጥናት የትግራይ ክልል ባሕል ቱሪዝም ኤጀንሲ ከፌዴራል ባሕል ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን ያዘጋጀው ነበር፡፡
የክልሉ ባሕል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች እንደገለጡት ይህ ዐውደ ጥናት በትግራይ ክልል ደረጃ ሲከናወን ለስድስተኛ ጊዜ ነው፡፡ የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው በሀገር አቀፍ ደረጃ መከናወኑ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ከጎንደርና ከሌሎችም አካባቢዎች የተጋበዙ ጉምቱ ጉምቱ ሊቃውንት የተገኙ ሲሆን እስከ ዛሬ ትውፊታውያን ሊቃውንት እንዲህ በብዛትና በዓይነት ተገኝተው ከዘመናውያን ምሁራን ጋር ሲገናኙ ዕድል ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በዚህም የክልሉ ባሕል ቱሪዝም ኤጀንሲና የፌዴራሉ ባሕል ቱሪዝም ሚኒስቴር ተመስጋኞች ናቸው፡፡
ከተለያዩ ዩኒቨረሲቲዎች ባለሞያዎች እንዲጋበዙ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንዲገኙ መደረጉ፤ መርሐ ግብሩ ግንቦት 11 ከሚከበረው የቅዱስ ያሬድ በዓል ጋር እንዲሠምር መደረጉ፣ ለበዓሉም የተሰጠው ቦታ ሊቃውንቱ ሁሉ ቅኔ ሲያዘንቡበት የዋሉት ጉዳይ ነው፡፡ ቅኔ ልብስ ቢሆን ኖሮ የክልሉና የፌዴራሉ ቢሮዎች እስከ እድሜ ልካቸው የሚሆን ልብስ በሁለቱ ቀን ጉባኤ ያገኙ ነበር፡፡ በበዓሉ መጨረሻ የሐን፣ ማይ ኬራህንና ሙራደ ቃልን ለመጎብኘት መርሐ ግብር መዘጋጀቱ ዝግጅቱን ሙሉ አድርጎት ነበር፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ቀርበው ነበር፡፡
የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ሀብት ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ያበረከተው አስተዋጽዖ(ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም)፣ የግእዝ ጥናት ከጥንት እስከ ዛሬ(ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ)፣ የግእዝ ቅኔያት ይዘትና ቅርጽ (ዶ/ር ሥርግው ገላው)፣ የ‹‹ትቤ አክሱም መኑ አንተ›› መጽሐፍ ትንታኔ(ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ)፣ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ሃይማኖታውያን ያልሆኑ መጻሕፍት (ዳንኤል ክብረት)፣ ግእዝና ቅዱስ ያሬድ(መ/ር ተስፋይ ሀደራ) ቀርበው ነበር፡፡
በመጨረሻም ለወደፊቱ የግእዝ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት በምን መልኩ መቀጠል እንዳለበት፣ ግእዝ በሀገር ፖሊሲ ደረጃ እንዴት ሊታቀፍ እንደሚገባው፣ ልዩ ልዩ አካላት ስለሚኖራቸው ድርሻ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡
ክልሉም ሆነ የፌዴራሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ግእዝን በተመለከተ የያዙት አቋም የሚበረታታና የሚደገፍም ነው፡፡ ግእዝ የሀገሪቱ የእምነት፣ የባሕል፣ የዕውቀት፣ የሥራ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ፣ የፍልስፍና፣ የኢኮኖሚና የማኅበራ ግንኙነት ቋንቋ ሆኖ ከ2000 ዓመታት በላይ በመኖሩ በውስጡ የያዛቸውን ዕውቀቶች ፈትሾ ለሀገር ጥቅም ማዋል ይጋባልና በነካ እጃችሁ ወደፊት ቀጥሉ እንላለን፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ‹‹የጎረቤት ጠበል የቆዳ መንከሪያ ነው›› ብሎ ነው መሰል የአኩስም ዩኒቨርሲቲ ከተሳትፎ መራቁ ሁሉንም ሰው ያስገረመ ነበር፡፡ ከእርሱ ይልቅ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በግእዝ ተናግረው በግእዝ የሚያሳምኑ እሳት የላሱ ወጣቶችን ይዞ መጥቶ ያሳየው ተሳትፎ እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ነበር፡፡ ወጣቶቹ ግእዝ ተምረው በግእዝ አፋቸውን የፈቱ እስኪመስል ድረስ ያቀርቡት የነበረው ዲስኩር ተስፋ የሚያለመልም ነበር፡፡
Source: Daniel Kibret Blog
No comments: