በኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ በዓባይ ወንዝ አጠቃቃምና የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሰባት ነጥቦች መግባባት ላይ ደረሱ፡፡
የግብፅ ሚዲያዎች መግባባቱን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ፣ አንዳንድ የኢትዮጵያ የውኃ ሀብት ባለሙያዎች ደግሞ የመግባቢያ ነጥብ ቁጥር አምስት ይዘት ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተገናኝተው ባደረጉት የጎንዮሽ ውይይት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በፀጥታና በአካባቢያዊ ግንኙነቶች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ኮሚሽን ለመመሥረት ተስማምተዋል፡፡
የዓባይ ወንዝ ለግብፃዊያን የመኖራቸው ወይም የህልውናቸው ጉዳይ መሆኑን፣ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የልማት ጥያቄ እንደሆነ መግባባታቸውን የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
የዓባይ ውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ባደረጉት ውይይትም በሰባት ነጥቦች ላይ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ የመነጋገርና የመተባበር መርህን ማስፈን፣ ለክልላዊ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት ፋይናንስ በቀላሉ ማግኘት፣ የአካባቢውን የውኃ ፍላጎት ለሟሟላትና የውኃ እጥረትንም መቅረፍ፣ የዓለም አቀፍ የሕግ መርሆችን መቀበልና ማክበር የመጀመርያዎቹ ሦስት ነጥቦች ናቸው፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ጀምረው ያቋረጡትን የሦስትዮሽ ውይይት በፍጥነት በመጀመር የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብን ተግባራዊ ማድረግ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምንም ዓይነት ጉዳት በግብፅ የውኃ አጠቃቀም እንዲያደርስ፣ የግብፅ መንግሥት በገንቢ ውይይት እንዲገዛና የኢትዮጵያንም የልማት ፍላጎት እንዲያከብር፣ እንዲሁም በሦስትዮሽ የጋራ ማዕቀፍ ውስጥ በቀና ልቦና መተባበር የሚሉት የተቀሩት የመግባባቢያ ነጥቦች ናቸው፡፡
ሁለቱ መሪዎች የደረሱበትን መግባባት ተከትሎ የሁለቱም አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲሱ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰሜህ ሐሰን ሹክሪ ሁለቱ መሪዎች በመተማመንና በመግባባት የተመሠረተ ውይይት ማድረጋቸውንና ይህም ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ከተስማሙባቸው ነጥቦች በአምስተኛው ነጥብ ማለትም የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምንም ዓይነት ጉዳት በግብፅ የውኃ አጠቃቀም ላይ አያደርስም የሚለውን ነጥብ አስመልክቶ የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳያደርስ ተደርጎ በጥንቃቄ ዲዛይን የተደረገ ነው፤›› ማለታቸውን ዘገባዎቹ አስነብበዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የውኃ ሀብት ባለሙያዎች ግን፣ የመግባቢያው አምስተኛ ነጥብ በተጠቀሰው ሁኔታ የተደረገ መሆኑን ይጠራጠራሉ፡፡
ለዚህ የሚሰጡት አስተያየት ሦስቱ አገሮች በሱዳን ካርቱም ሲያደርጉት የነበረው ውይይት የተቋረጠበት ምክንያት መሆኑን ነው፡፡ በውይይቱ መግባባት ካልተቻለባቸው ጉዳዮች አንዱ ግድቡ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ በሚለው ነጥብ እንጂ፣ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረስ በሚለው ኢትዮጵያ ባለመስማማቷ ሆኖ እያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህንን ሊቀበሉ ይችላሉ ብሎ መገመት እንደሚከብዳቸው ያስረዳሉ፡፡
ይህ መግባባት በተጠቀሰው መንገድ ተደርጎ ከሆነ ግን ለኢትዮጵያ ጉዳት እንዳለው፣ ምክንያቱ ደግሞ የታላቁ የህዳሴ ግድብ በራሱ በዓመት ስድስት ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ በመቀነስ በግብፅ ላይ ጉዳት የማድረስ አቅም አለው የሚል ነው፡፡
Source: Reporter
No comments: