በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ሲቪል መሀንዲስ እንደሆኑና ከአውስትራሊያና ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መመረቃቸውን ሲገልፁ የቆዩት የዶ/ር ኢንጂነር ሳሙኤል ዘሚካኤል የትምህርት ማስረጃዎች ሀሰተኛ እንደሆኑ ሬድዮ ፋና ትላንት ዘገበ፡፡
ኢ/ር ሳሙኤል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቃለ-ምልልስ ከሰጡ በኋላ እንግዳ አድርገዋቸው እንደነበር የገለፁት የ“አዲስ ጣዕም” አዘጋጆች፤ ኢ/ር ሳሙኤል በ1996 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ድግሪያቸውን ሲቀበሉ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንደነበሩ፣ ከአውስትራሊያና ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መመረቃቸውንና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዳገኙ መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡ አዘጋጆቹ የመረጃዎቹን ትክክለኛነት ሲያጣሩ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1991 ጀምሮ ሳሙኤል ዘሚካኤል በሚባል ስም የተመዘገበና የተመረቀ ለማወቅ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡
ከአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ እንዳገኙ ቢገልፁም ዩኒቨርሲቲው በተባለው ዘርፍ ስልጠና እንደማይሰጥ አረጋግጧል ያሉት አዘጋጆቹ፤ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለሁ በሚሉት ጉዳይ ላይ አንዴ በተልዕኮ ተምሬ ተመርቄያለሁ ቢሉም ማስረጃ አላቀረቡም ብለዋል፡፡ “በእርግጥ ኢ/ር ሳሙኤል አነቃቂ ንግግሮችን በተለያዩ መድረኮች ላይ ያደርጋሉ” ያሉት አዘጋጆቹ፤ የታዋቂ የግለሰቦችን ስም እየጠሩ የተጋነነ ነገር እንደሚናገሩና የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ያለ ምንም ማስረጃና ለፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚያበቃ መስፈርት ማዕረጉን እንደሰጣቸው ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የተማሪዎችን ቀን ምክንያት በማድረግ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲም ቀጠሮ ተይዞላቸው እንደነበር የገለፁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር፤ ሰሞኑን ከተናፈሰው ወሬ ጋር በተያያዘ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረዙን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን ለአቶ ሳሙኤል በተደጋጋሚ ብንደውል ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡
Source: Addis Admass
No comments: