የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ባንክ በማቋቋም በ2006 ዓ.ም. ወደ ሥራ ለመግባት አቅዶ ጀምሮት የነበረውን እንቅስቃሴ አቋረጠ፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባለፈው ዓመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ ወታደራዊ ባንክ ለመመሥረት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ገልጸው ነበር፡፡
ወታደራዊ ባንኩን የመመሥረት እንቅስቃሴው በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩን የመመሥረት እንቅስቃሴ ለምን እንደተቋረጠ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች ግን ወታደራዊ ባንኩን ለመመሥረት የተጀመረው እንቅስቃሴ የተቋረጠው በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ባንክ ለመመሥረት ከጀመረው እንቅስቃሴ ቀደም ብሎ በተመሳሳይ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋም ለመመሥረት ለብሔራዊ ባንክ የፈቃድ
ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ እንደተደረገበት ተናግረዋል፡፡ ወታደራዊ ባንክን ለመመሥረት የሚያስችል የሕግ አግባብ በኢትዮጵያ አለመኖሩን በምክንያትነት ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ባንክ ለመመሥረት ሕጉ ይደግፈኛል በማለት አጥኚ ኮሚቴ በማቋቋም ሲሠራና ከብሔራዊ ባንክ ጋርም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሲመክር እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ባንክ ለመመሥረት በዋነኛነት የፈለገበት ምክንያት የሠራዊቱን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ፣ የሠራዊቱ አባላት በቁጠባ ላይ የተመሠረተ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ወታደራዊ ባንኩ በዋነኝነት የተፈለገበት ምክንያት ለቁጠባና የሠራዊቱን ፍላጐቶች ለማሟላት መሆኑን ለሪፖርተር ያረጋገጡት ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ፣ ይህንን ውጥን እውን ለማድረግ ከንግድ ባንክ ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
Source: Reporter
No comments: