አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ደብተራቸውን ተቀሙ

•‹‹እቃችንን ሽጠን ፈቃዳችን እንመልሳለን›› ነጋዴዎች:: 
ደብረ ማርቆስ፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን ከአምስት በላይ ወረዳዎች ውስጥ መንግስት የአርሶ አደሮችን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እየሰበሰበ መሆኑ ተሰማ፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን፣ ባሶ ሊበን፣ አንደድና ሌሎችም ወረዳዎች የመሬት አስተዳደርና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሰራተኞች መሬቱን እንደገና ለማጥናት እንዲሁም የግልና የመንግስት ይዞታን ለመለየት በሚል የይዞታ ማረጋገጫ ደብተሮችን እየሰበሰቡ መሆኑን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡
ምንም እንኳ የይዞታ ደብተሩን ሰብሳቢዎቹ በይፋ ለጥናት እንዲሁም የመንግስትና የግል ይዞታን ለመለየት ነው ቢሉም ካድሬዎች ‹‹ኢህአዴግን ካልመረጣችሁ መሬታችሁን እንነጥቃችኋለን፡፡ መሬት የምንሰጠው እኛን ለመረጠ ብቻ ነው፡፡›› በሚል እያስፈራሯቸው እንደሆነ አርሶ አደሮቹ ባደረሱን መረጃ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሳሙኤል የተባሉ የህግ ባለሙያ ከስፍራው እንደተናገሩት ደግሞ፣ ‹‹ደብተሩ ገበሬዎች መሬቱ የራሳቸው ስለመሆኑ ለማረጋገጥ፣ ለግንባታ ወይንም ለሌላ ነገር ቢሰጥ ካሳ ለማግኘት፣ በህገ-ወጥ መንገድ ቢያዝም ለመከራከሪያነት የሚያገለግል በመሆኑ የይዞታ ማረጋገጫውን የሚሰበስቡት በይፋ ከሚሰጡት ምክንያት በስተጀርባ መሬትን ለ2007 ምርጫ መያዢያነት ለመጠቀም ስላሰቡ ነው፡፡ ደብተር ከሌላቸው ግን መሬቱ የእነሱ አይደለም ማለት ነው፡፡ አርሶ አደሩ የይዞታ ደብተሩ ከእጁ ከሌለ የመሬት ባለቤትነቱ ተስፋውን ስለሚያጣ የግዱን ይመርጠናል ከሚል ፖለቲካዊ ምክንያት ነው›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

የአርሶ አደሮችን የይዞታ ደብተር መሰብሰቡን ተከትሎ በአርሶ አደሩ ውስጥ ስጋት ከመፈጠሩም ባሻገር አንዳንዶች ከአሁኑ መሬታቸውን እንደተነጠቁ መናገራቸውንም ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል በአምስት ቀን ውስጥ የመመዝገቢያ ማሽን (ካሽ ሪጅስተር) ካልገዛችሁ 50 ሺህ ብር ትቀጣላችሁ የተባሉ የደብረ-ማርቆስ ከተማ ነጋዴዎች እቃዎቻቸውን ሸጠው ፈቃዳቸውን ለመመለስ መገደዳቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የመመዝገቢያ መሳሪያውን እንዲገዙ የተጠየቁት ቸርቻሪዎችም ጭምር ሲሆኑ በተደጋጋሚ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በተሰበሰቡበት ወቅት ‹ካፒታላችን ዝቅተኛ ነው፣ የንግድ ስርዓቱ የሚያሰራ አይደለም፤ እንዲሁም ዓመታዊ የንግድ እንቅስቃሴያችን ከ500 ሺህ ብር በታች ነው› በሚል ያመለከቱ ቢሆንም መስማማት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡ በዚህ የተነሳም ‹‹እቃችን ሸጠን የንግድ ፈቃዳችን እንመልሳለን!›› የሚል ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን የመረጃው ምንጭ አብራርቷል፡፡

Source: ነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ


No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog