የታሰሩት ጋዜጠኞችና ጦማርያን ጉዳይ እያነጋገረ ነው

-ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በነፃ እንዲለቀቁ እየጠየቁ ነው::
-መንግሥት አደገኛ ወንጀል ፈጽመዋል እያለ ነው::
የመብት ተሟጋቾች ነን ከሚሉ የውጭ ድርጅቶች ጋር በገንዘብና በሐሳብ በመስማማት፣ ሕዝብን ለአመፅ ለማነሳሳትና ለማተራመስ በኢንተርኔትና በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ቀስቃሽ መጣጥፎችን ለማሰራጨት ሲዘጋጁ ተደርሶባቸዋል በሚል፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ጋዜጠኞችና ጦማርያን (Bloggers) ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡


ሚያዝያ 25 እና 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በ48 ሰዓታት ውስጥ በዕለተ እሑድ ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በቀረቡበት ወቅት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ፖሊስ፣  ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ ድርጅቶች ጋር በገንዘብና በሐሳብ ተስማምተው ሕዝቡን ለአመፅ ለማነሳሳት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ከሚል የወንጀል የጥርጣሬ ውጪ ያለው ነገር ስለሌለ፣ ‹‹ወንጀሉ ምድነው?›› የሚል ጥያቄ ከማንሳት ጀምሮ የተለያዩ መላ ምቶችን በማንሳት የተለያዩ አካላት እየተነጋገሩበት ነው፡፡

ሲፒጄ (ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት)፣ ‹‹ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ የከፋ ከሚባሉ ዕርምጃዎች አንዱ ነው፤›› በማለት በጋዜጠኞቹና በጦማርያኑ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰደውን ዕርምጃ አውግዟል፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁም ጠይቋል፡፡
አምኒስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፣ ‹‹ይኼ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የማሰር የረዥም ጊዜ ልምድ ነው፤›› በማለት ጋዜጠኞቹንና ጦማርያኑን ማሰር ተገቢ አለመሆኑን አስታውቆ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡
ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያን መንግሥት በማውገዝ የጋዜጠኞቹንና ጦማርያኑን መታሰር የሚያነሱትን ወቀሳና ጥያቄ ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ለውጭ ሚዲያ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ በአደገኛ ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ ፖሊስ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ዙሪያ ምርምራ እያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሒዩማን ራይትስ ዎች ሚያዝያ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ የተባሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ጋር ባደረገው የስልክ ውይይት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የታሰሩትን ጋዜጠኞችና ጦማርያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ጆን ኬሪ ተጠርጣሪዎቹን እንዲፈቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊት እንዲያደርጉ በስልክ ያስተላለፈውን መልዕክት አስመልክቶ አቶ ጌታቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹መንግሥት የጋዜጠኞችን የመናገር መብት አላፈነም፣ አንዳንዶች ሙያውን ተገን በማድረግ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ሲሳተፉ ይገኛሉ፣ ይኼን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አይፈቅድም፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ትዕዛዝን አንቀበልም፤›› ብለዋል፡፡ 
በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞችና ጦማርያን ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በሦስት የምርመራ መዝገብ ተከፋፍለው ሲሆን፣ ቀደም ሲል በአዲስ ነገር ጋዜጣ፣ በፎርቹን ጋዜጣና በአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ላይ ይሠራ የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ነው የተባለው ጦማሪ ዘለዓለም ክብረትና የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ አንድ ላይ ናቸው፡፡
በሁለተኛው የምርምራ መዝገብ የተካተቱት የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ የነበረችው ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀና ጦማሪ አጥናፉ ብርሃኔ ሲሆኑ፣ የአየር መንገድ ሠራተኛ ነው የተባለው ጦማሪ አቤል ዋበላ፣ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉና ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን በሦስተኛው የምርምራ መዝገብ ተካተው ለሚያዝያ 29 እና 30 ቀን 2006 ዓ.ም. መቀጠራቸው ታውቋል፡፡
በምሥረታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋማ) የጋዜጠኞቹንና ጦማርያኑን መታሰር በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚገባው ጠቁሞ፣ መታሰራቸው ግን እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡ ባስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡
በአገር ውስጥ ያሉ የግል የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት መገናኛ ብዙኃን፣ ከመንግሥትና ከቅርብ ወዳጆቻቸው እንዳገኙት አድርገው በተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞችና ጦማርያን ላይ እያስተላለፉት ያለው መረጃ፣ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ ፍርድ ቤቱ በምርመራ መዝገቡ ላይ ካሰፈረው የተለየ በመሆኑ፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በቀጣይ የሚቀርበውን የምርምራ ውጤት ከመጠባበቅ ባለፈ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog