አሳሳቢው የመምህራን ፍልሰት

ቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ውስጥ መምህራንና ተማሪዎች በመማር ማስተማሩ ሒደት ለመምከር ተሰባስበዋል፡፡
የ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› 2013/14 ሪፖርት ይፋ መሆንን ተከትሉ ውይይቱን ለማድረግ ለተወከሉት ተማሪዎች ሴራሊዮናዊው አወያይ ቼርኖር ባህ ‹‹መምህር መሆን የሚፈልግ አለ?›› ሲል ጥያቄውን ሰነዘረ››፡፡ ከደቂቃዎች ዝምታ በኋላ አንድ ተማሪ ‹‹እኔ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ጥያቄ ለመምህራኑ እንድጠይቅ ግን ፍቀድልኝ›› አለች፡፡ ሚስተር ባህ መድረኩን ሰጣት፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከማላዊና ከፓኪስታን ለተወከሉት መምህራን ‹‹ከእናንተ ውስጥ ልጁ መምህር እንዲሆን የሚፈልግ አለ?›› ስትል ጠየቀች፡፡ አንድም መምህር አዎ ሲል አልተደመጠም፡፡ 

ቤተሰብ በልጁ ላይ ከሚፈጥረው የ‹‹መምህር አትሆንም›› ተፅዕኖ በተቃራኒ ልጁ መምህር እንዲሆንለት የሚፈልግ እንዲሁም በፍላጐት ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ አሉ፡፡ ሆኖም ዛሬ ዓለም እያስተናገደች ያለችው ከፍተኛ የመምህራን እጥረትና ፍልሰትን ነው፡፡ በየትምህርት
ቤቶችም ውስጥ ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑንና አገሮች እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጓቸውን መምህራን እንኳን ሊያሟሉ እንደማይችሉ የ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› 2013/14 ሪፖርት ያሳያል፡፡ አገሮች መምህራንን በብሔራዊ ደረጃ እያሠለጠኑ ቢሆንም መምህራኑ በዘርፍ የማይቀጥሉበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ አዲሰ አበባም የችግሩ ተቋዳሽ ሆናለች፡፡

ቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት በአገሪቱ ካሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማሩ ሒደት ባስመዘገበው ጥሩ ደረጃ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ሽፋን አግኝቷል፡፡ በ2005 ዓ.ም. በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናም ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከአዲስ አበባ 1ኛ፣ በብሔራዊ ደረጃ 2ኛ ወጥቷል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ በመምህራን ፍልሰት ከሚቸገሩ የከተማዋ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የለቀቁ መምህራን እስኪተኩ ድረስ በቀሩት መምህራን ትብብር ክፍት ክፍለ ጊዜዎችን እየሸፈነ ለውጤት ቢበቃም የመምህራኑ ፍልሰት ለአስተዳደሩም ሆነ ለመምህራን ፈተና ሆኗል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ዳንኤል መኰንን እንደሚሉት፣ ከመስከረም 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከ20 በላይ መምህራን ለቀዋል፡፡ መምህራን እንደለቀቁ ወዲያው ምትክ ማግኘቱም ቀላል አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቱ ለክፍለ ከተማው አሳውቆ ክፍለ ከተማው መምህር እስኪመድብ በሚኖረው የሳምንትና የሁለት ሳምንት ክፍተት ሌሎች መምህራን በሳምንት ከሚያስተምሩት የትምህርት ክፍለ ጊዜ በላይ ተጨማሪ ይሰጣቸዋል፡፡ መምህራኑ በእሺታ ክፍተቱን ለመሙላት የሚሠሩ ቢሆንም በመሰናዶ ትምህርት ደረጃ መምህሩ ላይ ጫና መፍጠር የትምህርት ጥራቱን ያስጠብቃል ወይ? የሚለው ለመምህራኑም በጥያቄ የሚቀመጥ ነው፡፡ ሆኖም ተማሪዎቹ እንዳይጐዱና ከሌሎች ተማሪዎች ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ያግዛል በሚል ቀሪ መምህራን ደርበው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ደረጃ የመምህራን ፍልሰቱ የሚፈጥረውን ክፍተት ለመሙላት ቢጥሩም ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን ግን አቶ ዳንኤል ይናገራሉ፡፡ 
በከተማዋ ከሚገኙ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ባንዱ በርእሰ መምህርነት የሚያገለግሉትና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ መምህር፣ መምህሩ የተሻለ ገቢ ፍለጋ ከሥራው የሚለቅበትን ምክንያት ያስቀመጡት የሳቸውን ደመወዝ ዋቢ በማድረግ ነው፡፡ ከ25 ዓመት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ደመወዛቸው ከታክስ በፊት 2,800 ነው፡፡ 300 ብር ለቤት ኪራይና 100 ብር ለወንበር አላቸው፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ ከሁለት አሠርት በላይ ቢያስተምሩም፤ ከሚወጡት ኃላፊነት አንፃር የሚያገኙት ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዓመት በፊት ለቤት ኪራይ 1,800 ብር ይከፍሉ እንደነበር የሚያስታውሱት መምህር የባለቤታቸው 1,400 ብር ደመወዝ ተጨምሮም ‹‹ለኪሴ›› የሚሉት ገንዘብ ተርፏቸው እንደማያውቅ፣ ሙያውን ስለሚወዱት ግን እስካሁንም እንደሚያገለግሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹መምህርነት ጊዜያዊ መጠለያ የሆነበት ዋናው ምክንያት ተመጣጣኝ ደመወዝ ስለማይከፈል ነው›› ይላሉ፡፡ 
እንደ እሳቸው ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለመምህሩ የሚከፈለው ደመወዝ አግባብ ቢመስልም መምህሩ በሚያገኘው ገቢ ደስተኛ አለመሆኑን ሥራውን በመልቀቅ እያሳየ ነው፡፡ አብዛኞቹ መምህራን ወደ ሌላ ሥራ ሊያሰማራቸው በሚችል የትምህርት ዓይነት በየዩኒቨርሲቲዎች በማታው ክፍለ ጊዜ ይማራሉ፡፡ እንደተመረቁ ሥራቸውን ይቀይራሉ፡፡ ሥራ መቀየር ምርጫ ቢሆንም መምህርነት፣ በመምህርነት ሥልጠና ለመግባት ያለውን የቅበላ መስፈርት ከፍተኛ ከማድረግ ጀምሮ ደመወዙና የሚያገኘው ጥቅማ ጥቅም ተወዳዳሪ ቢሆን መምህርነት በፍላጐት የሚመጣበት ዘርፍ ይሆን ነበር ይላሉ፡፡ የቅበላ መስፈርቱንም ‹‹ሞራል የሚነካ›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ 
የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው የወቅቱ የመሰናዶ መግቢያ 2.4 ቢሆን በ2.00 እና በ2.4 መካከል ያመጡ ተማሪዎች በመምህርነት በዲፕሎማና ሠርተፊኬት መሠልጠን ይችላሉ፡፡ በተቃራኒው በሕክምናና በምሕንድስና የመሳሰሉና በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ በተሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች ለመግባት ለመሰናዶ የሚያበቃ ውጤት ከማምጣት ባለፈም የ12ኛ ክፍልን ብሔራዊ ፈተና በከፍተኛ ውጤት ማለፍ ግድ ነው፡፡ ይህም ትውልድ ለሚቀርጸው የመምህርነት ሙያ የተሰጠውን ዝቅተኛ ግምት ያሳያል፡፡ ዘርፉ ‹‹የማይፈለግ›› ወይም ‹‹ትኩረት የተነፈገው›› መሆኑ የሚጀምረውም ከቅበላ መስፈርቱ ነው ይላሉ፡፡
አንድ ዓመት ያህል በመንግሥት ትምህርት ቤት አገልግለው መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የተቀጠሩት አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ ከመምህርነታቸው የለቀቁት በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አንደኛው በመምህሩና ተማሪው መካከል ያለው ግንኙነት መስመር የለቀቀና ተማሪው ለመምህሩና ለሥነ ሥርዓት የማይገዛ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ደመወዙ ነው፡፡ በሌላ በኩል መምህርነትን ሥራ ለማግኘት እንጂ መርጠውት ስላልገቡ በዘርፉ ሊቆዩ አልቻሉም፡፡ ‹‹እኔ እስከማውቀው ጓደኞቼ ሁሉ መምህርነትን ፈልገውት አልገቡም፡፡ ከገቡም በኋላ እየለቀቁ በተለያየ ሙያ ተሰማርተዋል፤›› ይላሉ፡፡ 
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ትውልድን የሚቀርፀውን መምህር በሥራው ለማቆየትና ፍልሰትን ለመቀነስ ዘርፉ በከፍተኛ ውድድር የሚገባበት፣ ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈልበት መሆን ይገባዋል፡፡ እሳቸው በተማሩባቸው በ1980ዎቹ እንኳን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደመምህርነት ዘርፍ የሚመድባቸው ተማሪዎች መጀመርያ ዓመት ላይ ከመባረር የተረፉ ግን ዝቅተኛ ውጤት ያላቸውን ነው፡፡ ይህ ልማድ ዛሬም በቅበላ ላይ ይታያል፡፡ ‹‹ክብር ባልተሰጠው ሙያ ማንስ መቆየት ይፈልጋል?፡፡ በፍላጐቱና በጥሩ ውጤት ለገባው መምህርም ቢሆን ክብር ያሳጣል፡፡››
ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መምህራን የሚያሠለጥነው ኮተቤ መምህራን ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነው፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ ተፈሪ በለው የመምህራን ቅበላ መስፈርት በመምህራን ፍልሰት ላይ ያለው ተፅዕኖ በጥናት ባይረጋገጥም እንዲሻሻል ሁሌም የሚያነሱት ጥያቄ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ወደዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በዲፕሎማ ደረጃ የሚገቡ ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ መምህር የሚሆኑ ሲሆን በዲግሪ ደረጃ ከሚሠለጥኑት ደግሞ መምህር መሆን የሚፈልጉት ብቻ ተጨማሪ አንድ ዓመት ሠልጥነው ወደሙያው እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ 
በዲግሪ ደረጃ ያለው ፖሊሲ ፍላጐትን ያማከለ ነው፡፡ በዲፕሎማ ደረጃ የሚሠለጥኑት መምህራን ግን ሥራ ከያዙ በኋላ በሌላ የትምህርት ዘርፍ የማታ እየተማሩ ሥራ ሊቀይሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ሆኖም በዲፕሎማ ደረጃ አዲስ አበባ ላይ የመምህራን ችግር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ 
አቶ ተፈሪ እንደሚሉት ለመምህራን ፍልሰት እንደምክንያት የሚነሳውን የደመወዝ ማነስ አገሪቱ ካለችበት ደረጃና ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ሲነፃፀር ደህና የሚባል ነው፡፡ ሆኖም ከተሸከመው ኃላፊነት ጋር ሲነፃፀር አይሄድም፡፡ 
በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታየውን የመምህራን ፍልሰት በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዋና የሥራ ሒደት አቶ አማኑኤል ኤሮሞ ‹‹የመምህራን ፍልሰት ጉዳይ የሁላችንም ጭንቀት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ተማሪ ትምህርት ቤት አስገብተን ያለ መምህር ዋጋ የለውም›› በማለት የመምህራን ፍልሰት አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ከ2006 ዓ.ም. መስከረም ወዲህ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 50፣ በነፋስ ስልክ ላፍቶ 57 መምህራን መልቀቃቸውን አውስተዋል፡፡  
የመምህራን ፍልሰት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካም መሆኑን የሚገልጹት አቶ አማኑኤል፣ ለመምህራን ፍልሰት ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆኑም ሚዛን በሚደፉት በደመወዝ ጭማሪ ጥያቄና በሙያው ፍላጐት ዙርያ በአዲስ አበባ ደረጃ ጥናት ሊደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
እንደ መፍትሔም በትምህርት ቤት መልካም አስተዳደርና ምቹ አገልግሎት እንዲኖር እንዲሁም ከደመወዝ ጭማሪ አኳያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተወያዩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog