ኢትዮጵያ ዉስጥ የመሬትና ዉሃ ቅርምት ማኅበረሰቡን እየጎዳ እንደሚገኝ ዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች ሂዉማን ራይትስ ዎች አመለከተ። ድርጅቱ ይህን አመልክቶ ባወጣዉ ዘገባ በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያና ኬንያ ዉስጥ 500,000 አርብቶ አደሮች ለችግር መጋለጣቸዉን ገልጿል።
ሂዉማን ራይትስ ዎች፤ ኢትዮጵያ፤ የመሬትና ዉሃ ቅርምት ማኅበረሰቦችን ጎዳ በሚል ዛሬ ባወጣዉ ዘገባ፤ አዳዲስ ከሳተላይት የተገኙ ምስሎች በታችኛዉ ኦሞ ሸለቆ አካባቢ ነባር ማኅበረሰቦች ይጠቀሙበት የነበረዉን መሬት ለስኳር ልማት በስፋት መመንጠሩን ማሳየታቸዉን አመልክቷል። ላለፉት አምስት ወራትም 7,000 የሚሆኑ የቦዲ ጎሳ አባላት ጋ በቂ ምክክር ሳይደረግ ተግባሩ መከናወኑን ዘርዝሯል። የድርጅቱ የአፍሪቃ ጉዳይ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮ፤ ድርጅታቸዉ በUNESCO በዓለም ቅርስነት
በተመዘገበዉ አካባቢ ለበርካታ ዓመታት የሚከናወነዉን እንደሚከታተል በማመልከት፤«የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ግድቦችን በኦሞ ወንዝ አካባቢ በመገንባት ላይ ይገኛል። የወንዙ ዉሃም ለስኳር ተክሉ ወደግድቦች ለመስኖ ተቀልሷል። እናም ባጠቃላይ እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች በኦሞ ሸለቆ በሚገኙ ነባር ኗሪዎች ህይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አስከትለዋል። እዚያ ወደሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ይኖራሉ። አብዛኞቹም እዚያ መሬታቸዉ ሲመነጠር አይተዋል፤ ወደሌላ ስፍራ አንዳንዴም ወደመንደሮች ተወስደዉ በግዳጅ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። እናም የኑሯቸዉ ሁኔታ እጅግ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነዉ።»
ዘገባዉ እንደሚለዉ የመሬት ምንጠራዉ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሞ ሸለቆ ያቀደዉ ሰፊ የልማት ተግባር አካል ነዉ። የግድብ ግንባታዉን ጨምሮ፣ የስኳር ተክል ልማቱም ሆነ ለገበያ የሚዉል የእርሻ ምርት ማምረቻዉ በኦሞ ወንዝ የሚገኘዉን አብዛኛዉን ዉሃ ይጠቀማል የሚል ስጋትም አለዉ። ይህም በአካባቢዉ በኢትዮጵያም ሆነ በጎረቤት ኬንያ የሚገኙና ዉሃዉን ለኑሯቸዉ የሚጠቀሙ ወገኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚጎዳ አመልክቷል። ዘገባዉ የኢትዮጵያ መንግስት መሬቱንና የተፈጥሮ ሃብቱን ማልማት እንደሚችል ያ ግን በአካባቢዉ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን መብት በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ያስገነዝባል። እንዲህ ያሉ የልማት ተግባራት ሲከናወኑ የሚከተል የጎንዮሽ ችግር አይጠፋም እና ይህ እንዴት ይታያል ለሚለዉ፤ ሌቭኮቭ ችግሩ የሚከናወንበት መንገድ ነዉ፤ ነዉ የሚሉት፤
«እርግጥ ነዉ የኢትዮጵያ መንግስት እንደማንኛዉ መንግስት ለኤኮኖሚ እድገት ዉሃዉንም ሆነ የተፈጥሮ ሃብቱን ማልማት ይችላል። ችግሩ የሚከወንበት መንገድ ነዉ። በኦሞ ሸለቆ የሚገኙ አብዛኞቹ ማኅበረሰቦችም በአካባቢዉ እንደሚገኝ ነባርና ይህን መሬት ለበርካታ መቶ ዓመታት ሲጠቀም እንደኖረ ዜጋ መብት አላቸዉ። የሚያሳዝነዉ ነገር በመከናወን ላይ ያለዉ ሂደት የእነሱን መብት ከግምት ያላስገባ መሆኑ ነዉ። አብዛኞቹ ሰዎች አልተጠየቁም፤ ካሳ አላገኙም፤ የኗኗራቸዉ ሁኔታ ዳግም በማይመለስ መልኩ በፍጥነት ሲለወጥ ነዉ የሚያስተዉሉት።»
ከዚህም ሌላ ይኸዉ ምክንያት ጎረቤት ኬንያ ዉስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦችንም ህይወት እየጎዳ እንደሚገኝም አመልክተዋል። የኦሞ ወንዝ የቱርካና ሃይቅ ዋነኛ ምንጭ መሆኑን በመግለፅም ወደ300,000 የሚሆኑ እና ኑሯቸዉ በቱርካና ሃይቅ ላይ የተመሠረተ ወገኖች መጎዳታቸዉን ዘርዝረዋል። ሂዉማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይህን ጉዳይ ደጋግመዉ ማንሳታቸዉና ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ይታያል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ዘገባዎቹ ከእዉነት የራቁና የተዛቡ መሆናቸዉን ነዉ የሚገልፀዉ። የልማት ተግባራቱን የሚያከናዉነዉ የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል መሆኑንም ይናገራል። ሌስሊ ለፍኮዉ ማኅበረሰቡም እንዲህ ባሉ ተግባራት ሃሳቡን የመስጠት መብቱ መከበር አለበት ባይ ናቸዉ፤
«ችግሩ እንዲህ ባሉ ልማቶች ማኅበረሰቡም የራሱን ሃሳብ የመስጠት መብት አለዉ፤ መንግስት የእነዚህ በሁኔታዉ በጣም የሚነኩ እና የሚጎዱ ወገኖችን አስተያየት፣ ሃሳብና ግብዓት ሙሉ በሙሉ ይህን ችላ ብሏል፤ ይህ ደግሞ ከባድ ችግር ነዉ። ሰዎች መሬታቸዉ ሲነጠቅ፤ ሌላ አዲስ ስፍራ ለመስፈር ሲገደዱ እንዴት ህይወታቸዉን ማቆየት እንደሚችሉ ይቸገራሉ። ምክንያቱም በአኗኗራቸዉ ላይ ፍፁም ለዉጥ ነዉ። ለዚህ ደግሞ አልተዘጋጁም።»
እናም ሁኔታዉ በከፍተኛ ግፊት በአካባቢዉ በሚኖሩ ወገኞች ላይ መጫኑንም አያይዘዉ ጠቅሰዋል። አንዳንድ ዘገባዎች ኢትዮጵያ አፍሪቃ ዉስጥ ከሚገኙ የዓለማችን 10 ድሃ ሃገራት አንዷ መሆኗን ይጠቅሳሉ። መንግስት የሚያከናዉናቸዉ የልማት እንቅስቃሴዎች ሀገሪቱን ወደመካከለኛ ገቢ ወዳላቸዉ ሃገራት ተርታ ያደርሳሉ ባይ ነዉ። እንዲህ ያሉት ተግባራት የጎንዮሽ ችግር ማስከተላቸዉ እየታየ ከሆነ ድርጅቱ የሚያቀርበዉን ዘገባ መንግስት ከግምት እንዲያስገባ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? ሌስሊ ሌፍኮዉ፤
«ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ማለቴ በዘገባችን ምን ለማቅረብ እንደፈለግን የተሻለ ግንዛቤ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ልማትንም ለማከናወን የተሻለ መንገድ መኖሩን ይገነዘባሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በመንግስት አስተዳደር ዉስጥ የሚገኙ ሰዎችም ዘገባዎቹን በጥንቃቄ በመመልከትና በማንበብ ለሁሉም የሚጠቅም ልማትን ለማከናወን አቅጣጫቸዉን ይለዉጣሉ ብዬ በጣም ተስፋ አደርጋለሁ። በተለይ በፕሮጀክቱ ኑሯቸዉ በቀጥታ ተፅዕኖ የሚያርፍበትን ወገኖች።»
Source: DW
No comments: