የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ተማሪዎች ተጋጩ

በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢንቫይሮመንታል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ‹‹ኢንቫይሮመንትን በሚመለከት የምንማረው ትምህርት ስለሌለ ካሪኩለሙ ተቀይሮ ኃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ በሚል ይቀየርልን›› በማለት ከጥር 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የፖሊስ ሠራዊት ጋር መጋጨታቸውን፣ በሥፍራው የተገኙ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ 

ዩኒቨርሲቲው ፈንድ ስለሚያገኝበት ብቻ ኢንቫይሮንመንታል ኢንጂነሪንግ በሚል ስያሜ የማይማሩትን ትምህርት እንደተማሩ በማስመሰል ዲግሪ የሚሰጣቸው ከሆነ፣ በማይታወቅና ምንም ጥቅም በሌለው የትምህርት መስክ ከመቀመጥ ባለፈ ሌላ ጥቅም እንደማያገኙበት በመግለጽ፣ ካሪኩለሙ እንዲቀየር አጥብቀው መጠየቃቸውን ሪፖርተር ያጋገራቸው አንዳንድ ተማሪዎች አስረድተዋል፡፡ 

ተማሪዎቹ ለዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ተገቢ የሆነ ምላሽ በማጣታቸው፣ ከዩኒቨርሲቲው በ18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ሐረር ከተማ በመሄድ ጥያቄያቸውን በመገናኛ ብዙኃን ለመንግሥት ለማሰማት በሰልፍ መንገድ ሲጀምሩ፣ ፌዴራል ፖሊስ አወዳይ ከተማ ላይ እንዳስቆማቸው ተናግረዋል፡፡ 
ፖሊስ ጉዳዩን በመመካከርና አስፈላጊም ከሆነ ለክልሉና ለፌዴራል መንግሥት ወይም ለትምህርት ሚኒስቴር ማቅረብ እንደሚችሉ በማስረዳት፣ ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እንዲመለሱ ማድረጉን የገለጹት በአካባቢው የነበሩ የሪፖርተር ምንጮች፣ ተማሪዎቹ ብሶታቸውን በመፈክርና በተለያዩ መንገዶች የገለጹ ቢሆንም፣ የከረረ ግጭት ውስጥ አለመግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደ ሐረር እንዳያልፉ የከለከሏቸውን ፖሊሶች በሞባይል ፎቶ ሲያነሱ የነበሩ ተማሪዎችን ሞባይላቸው ተነጥቆ ለጊዜው ታስረው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ 
ሌላው በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተከስቷል የተባለው ችግር የምግብ መመረዝ ሲሆን፣ ከሙስሊሞች ካፊቴሪያ ጀምሮ በሌሎች ካፊቴሪያና ምግብ ቤቶችም በመዛመት ከ600 በላይ ተማሪዎች መታመማቸውን አንዳንድ ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ 
በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ያለው ክሊኒክ በቂ ባለመሆኑ ወደ ሐረር ሆስፒታልና ሌሎች ሆስፒታሎች መወሰዳቸውንም አክለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ‹‹አይዟችሁ ተረጋጉ ታይፎይድ ነው›› በማለት ተፈጥሮ የነበረውን ጭንቀትና ግርግር ለማረጋጋት ሲጥር እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች በንፅህና ሊያዙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 
ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ካሪኩለምን በሚመለከት ስላነሱት ጥያቄና በምግብ መመረዝ ምክንያት ታመዋል ስለተባሉት ተማሪዎች ሁኔታ እንዲያብራሩ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ግርማ አመንቴ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ዲፓርትመንቱን በሚመለከት ማንኛውም ተማሪ የአካዳሚክ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢንቫይሮንመንታል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎችም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን የአካዳሚክ ካሪኩለሞች የሚታዩበት የራሳቸው የሆነ አካሄድ አላቸው፡፡ የካሪኩለሙ ‹ሀርሞናይዜሽን› የሚሠራው በትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ዝም ብሎ ተነስቶ የዲግሪ ስም የሚቀየርበት አግባብ እንደሌለ ለተማሪዎቹ በማስረዳት ስምምነት ደርሰዋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ 
የውኃ ሴክተር ካሪኩለሞች እንዲስፋፉ የተደረገው በአገር አቀፍ ደረጃ መሆኑንና ከውኃ፣ ከኢነርጂና መስኖ ሚኒስቴር ጋር የተያያዘ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ትምህርቱ የሚሰጠው በሐሮማያ ብቻ ሳይሆን በጅማና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎችም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አገር አቀፍ ፕሮግራም በመሆኑም አንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ተነስቶ ስም የሚቀይርበት ሁኔታ እንደሌለ አክለዋል፡፡ ካሪኩለሙን የማስማማት ሥራ በትምህርት ሚኒስቴር ስትራቴጂክ ሴንተር እየተሠራ መሆኑን ነግረዋቸው፣ ተማሪዎቹ ተስማምተው ወደ ትምህርታቸው መመለሳቸውን ዶ/ር ግርማ አብራርተዋል፡፡ 
ከምግብ ጋር በተገናኘ ተማሪዎች መታመማቸውን ያረጋገጡት ዶ/ር ግርማ፣ 90 በመቶ የሚሆኑት ወዲያው ሕክምና አግኝተው የዳኑ ቢሆንም፣ ሁለትና ሦስት ቀናት ከታመሙት ተማሪዎችና ከምግቡ የምርመራ ናሙና ተወስዶ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ አዲስ አበባ የምግብና ሥነ ሕይወት ምርምር ማዕከል (ፓስተር) መላኩን ገልጸዋል፡፡ ውጤቱንም እየጠበቁ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ተማሪዎች ጤነኛ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡           
Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog