የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የምክር ቤት አባል አቶ አሥራት ጣሴ ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ በመባላቸው፣ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. በፖሊስ ጣቢያ ታሰሩ፡፡
አቶ አሥራት ለእስር የበቁበትን ፍርድ ቤት የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት፣ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 198 የጥር ወር 2006 ዓ.ም. ዕትም ላይ በጻፉት ጽሑፍ ምክንያት ነው፡፡
አቶ አሥራት በመጽሔቱ ላይ ባሰፈሩት ‹‹…..አሁን ደግሞ ከሰሞኑ ‘አኬልዳማ’ ድራማ በድጋሚ በተከታታይ እየቀረበ ነው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅትን በስም ማጥፋት ወንጀል በፍርድ ቤት ከሶ ገና ውጤት ባልተገኘበት
ወቅት ነው፡፡ እሱም ፍትሕ ከኢሕአዴግ ፍርድ ቤቶች ይገኛል ተብሎ ሳይሆን፣ በታሪክ ምስክርነት እንዲመዘገብ ሲባል ነው፤›› በሚለው ዓረፍተ ነገር ፍርድ ቤትን ዘልፈዋል በሚል ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርበው እንዲያስረዱ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ ፍትሕ ብሔር ችሎት አስጠርቷቸው ነበር፡፡
ወቅት ነው፡፡ እሱም ፍትሕ ከኢሕአዴግ ፍርድ ቤቶች ይገኛል ተብሎ ሳይሆን፣ በታሪክ ምስክርነት እንዲመዘገብ ሲባል ነው፤›› በሚለው ዓረፍተ ነገር ፍርድ ቤትን ዘልፈዋል በሚል ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርበው እንዲያስረዱ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ ፍትሕ ብሔር ችሎት አስጠርቷቸው ነበር፡፡
በቀጠሯቸው ቀን ከጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጉ ጋር የቀረቡት አቶ አሥራት በጠበቃቸው አማካይነት እንደገለጹት፣ ወደ ችሎቱ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተላለፈበት የሕግ አንቀጽ አግባብነት ያለው ስላልሆነ፣ ክሱ ተሰርዞ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እሳቸው ተናገሩ ወይም ጻፉ የተባለው ነገር በችሎት ተገኝተው ወይም የክሱ አካል ሆነው ያደረጉት አይደለም፡፡ በችሎትም አልተገኙም፡፡ የክሱ አካልም አይደሉም፤›› ሲሉ ጠበቃው አስረድተዋል፡፡
የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ የሚሠራው በችሎት ተገኝቶ የችሎቱን አሠራር የሚያውክ ወይም ሌላ ተቃራኒ ነገር ላደረገ አካል እንጂ፣ ላልነበረና ፍፁም ግንኙነት ለሌለው አይሆንም በማለት፣ ድርጊቱን የፈጸሙት በሌላ ቦታ ከፍርድ ቤቱ ውጪ በመሆኑ ሊጠሩ እንደማይገባ ጠበቃው አብራርተዋል፡፡ የሕግ ትርጉሙ በጣም ተለጥጦ በማያገባቸውና ሊያስጠራቸው በማይችል ጉዳይ መጠራታቸውን የተቃወሙት ጠበቃው፣ እንዲጠሩበት የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ከፍርድ ቤት ውጪ ለተከናወነ ድርጊት እንደማይሠራ ጠቁመዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ከአኬልዳማና ከአንድነት ሌላ ክርክር አላችሁ የላችሁም?›› ብሎ ሲጠይቅ ‹‹የለንም›› ያሉት ጠበቃው፣ አቶ አሥራት በመጽሔቱ ለማብራራት የሞከሩት ከጀሃዳዊ ሐረካት ጋር በተያየዘ ኢሕአዴግ የሚፈራው ሰላምን እንጂ ሽብርተኝነትን አለመሆኑን ለማሳየት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዘገባው ስለአጠቃላይ ሁኔታ እንጂ ጉዳዩን ስለሚያየው ችሎት አለመሆኑን፣ የኢሕአዴግ ፍርድ ቤት ሲሉም ኢሕአዴግ መንግሥት ሆኖ በማቋቋሚያ አዋጁ ስላቋቋማቸው ፍርድ ቤቶች እንጂ ስለአንድ ችሎት ነጥለው አለመሆኑን ጠበቃ ተማም አስረድተዋል፡፡
በከሳሽ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲና በተከሳሽ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት መካከል ያለው ክርክር ውጤት ሳይታወቅ፣ ‹‹ከኢሕአዴግ ፍርድ ቤቶች ፍትሕ አይጠበቅም ማለት ምን ማለት ነው?›› በማለት ፍርድ ቤቱ ሲጠይቃቸው፣ አቶ አሥራት የተናገሩት ስለጀሃዳዊ ሥርዓት እንጂ ከአኬልዳማ ጋር የሚገናኝ አለመሆኑን በድጋሚ አቶ ተማም ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በሰጠው ፍርድ ፍርድ ቤቱ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚያናጋ ሥራ ተሠርቶ ሲያጋጥመው ወይም ሲሠራ ሲያይ የማስጠራት ሥልጣን አለው ብሏል፡፡ አቶ አሥራት በጻፉት ጹሑፍ የተናገሩት ፍርድ ቤቶችን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል መሆኑን፣ ያነሱት አኬልዳማም ሆነ ሌላ ነገር ፍርድ ቤቱ ከያዘው ጉዳይ ውጪ አለመሆኑንና በፍርድ ቤቱ ላይ ጫና የሚያሳድር ዓረፍተ ነገር ተጠቅመዋል ብሏል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረት የመናገር፣ የመጻፍና ሐሳባቸውን የመግለጽ መብት ያላቸው ቢሆንም፣ ሌላኛውን ወገን እስካልነኩ ድረስ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ አቶ አሥራት ፍርድ ቤትን የመድፈር ወንጀል መፈጸማቸውን በመግለጽ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡፡ በመሆኑም አቶ አሥራት እስከ የካቲት 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩና የቅጣት ማቅለያ ሐሳባቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የአቶ አሥራት ጣሴ ጠበቃ አቶ ተማም ይግባኝ እንሚጠይቁ አስረድተዋል፡፡
Source: Reporter
Source: Reporter
No comments: