“የተሳፋሪው ፍላጎት የሆነ መሬት ላይ ማረፍ ብቻ ነበር”
በሃዋሳ ከተማ በተለምዶ ኬሮ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተወልዶ ያደገው ወጣት ምህረቱ ገብሬ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀድሞው ሀዋሳ ኮምቦኒ የመጀመርያ ደረጃ ት/ቤት ነው የተከታተለው። የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያና የመሰናዶ ትምህርቱንም በቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ት/ቤት አጠናቋል። ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2001 ዓ.ም በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላም፤ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት አገልግሏል፡፡ በመቀጠልም ነጻ የትምህርት ዕድል በማግኘት፣ ወደ ጣሊያን አምርቶ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡
በቅርቡ ለእረፍት ወደ አገሩ የመጣውና በሃዋሳ ቆይቶ ወደ ጣሊያን ለመመለስ አውሮፕላን የተሳፈረው ምህረቱ፣ ባለፈው ሰኞ በረዳት አብራሪው ተጠልፎ ጄኔቭ እንዲያርፍ በተደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩት 200 ገደማ ተሳፋሪዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በጣሊያን የሚገኘው ምህረቱ፣ የጠለፋውን አጋጣሚ በተመለከተ ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው በኢ-ሜይል ለላከለት ጥያቄዎች የሰጠውን ምላሽ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል፡፡
የጉዞው አጀማመር ምን ይመስል ነበር?
አርፍዶ ወደ አውሮፕላን ጣቢያ መምጣት የሚያደርሰውን ጣጣ ስለማውቀው፣ አውሮፕላኑ ከሚነሳበት 50 ደቂቃ ያህል ቀድሜ ነበር የተገኘሁት፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ማለት ነው፡፡ ያው ጉዞው ሲጀመር እንደሌላው ጊዜ ሁሉ ስርአቱን የጠበቀና ሰላማዊ ነበር። አውሮፕላኑ ከበራራ ሰዓቱ ሰባት ደቂቃ ያህል ዘግይቶ ነበር የተነሳው።
አውሮፕላኑ ውስጥ አቀማመጥህ እንዴት ነበር? የት አካባቢ ነው የተቀመጥከው?
የመቀመጫዬ ቁጥር 27F ነበር። የተሳፈርንበት ቦይንግ 767 በርዝመቱ ትይዩ 7 የመቀመጫ መደዳዎች አሉት። ሁለት ሁለት መደዳዎች በሁለቱም ጥጎች እና ሶስት መደዳዎች መሃል ላይ። እኔ የተቀመጥኩት ከመሃል ሶስቱ መደዳዎች የመሃለኛዋ ወንበር ላይ ነበር። ከበስተግራዬ ያለችው ወንበር ላይ የተቀመጡት ሪካርዶ የተባሉ የ85 አመት የዕድሜ ባለጸጋ ጣሊያናዊ ነበሩ፡፡ በቀኜ በኩል እንዲሁ በግምት በስድሳዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌላ ጣሊያናዊ ተቀምጠው ነበር፡፡ ተዋውቀን ነበር፣ አሁን ግን ዘንግቼዋለሁ። ኢትዮጵያን ተዟዙረው እንደጎበኟት እያጫወቱኝ ነው ጉዞውን የጀመርነው፡፡
ጉዞውስ እንዴት ነበር?
እንደማስታውሰው ጉዞው ሲጀመር ሰላማዊ ነበር። ከፓይለቱ ጋርም ግንኙነት (ኮሙኒኬሽን) ነበረን፡፡ እኔ ድካም ስለተሰማኝ ወዲያው አሸለብኩ፡፡ በረራው ከተጀመረ በግምት ከ1 ሰዓት በኋላ የሱዳን አየር ክልል ውስጥ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ. . . መብራት ሲበራ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ የምግብ ሰዓት መድረሱ ገብቶኛል። ወደ ፊት አሻግሬ ሳይ ሆስተሶቹ እያስተናገዱ ከእኔ ፊት 4ኛ ይሁን 5ኛ ረድፍ ደርሰዋል። ሁሉም ተዘገጃጅቶ እየተጠባበቀ ነበር። በዚህ መሃል የፕሌኑ ፍጥነት ሲጨምር ይታወቀኛል፡፡ ከፍታዉም ሲጨምር በጆሮዬ ላይ በሚሰማኝ ስሜት አስተዋልኩ። በተሳፋሪዎች ፊት ላይ የመረበሽ ስሜት ሲፈጠር አየሁ። እኛ ኢኮኖሚ ክላስ ስለነበርን ከፊት ምን እየተካሄደ እንደነበር አላየንም። በኋላ ስሰማ ከፊት የነበሩትም የቢዝነስ ክላስ ተሳፋሪዎች ምንም መረጃ አልነበራቸውም፡፡
ከዚያም በድምጽ ማጉያው የሆነ ድምጽ ተሰማ፡፡ የረዳት አብራሪው ድምጽ ነበር።
“ተሳፋሪዎች ከ 12 ደቂቃዎች በኋላ ሚላን እናርፋለን” አለ ረዳት አብራሪው፡፡ ጥቂት ቆይቶም፣ “ስለተፈጠሩ አንዳንድ መጉላላቶች ይቅርታ እንጠይቃለን” ሲል አከለ-በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ። የረዳት አብራሪውን ንግግር ተከትሎ የተወሰኑ ተሳፋሪዎች ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ አንዳንዶችም ጮክ ብለው ሲያወሩ ይሰሙ ነበር፡፡ ከኔ በስተግራ በኩል ሶስት አራት መደዳዎችን አልፎ ከፊቴ ተቀምጦ የነበረ አንድ ወፍራም ሰው፣ በጣሊያንኛ ቆጣ ብሎ እየጮኸ ተናገረ - “መጀመሪያ ሚላን ሳይሆን ሮም ነው ማረፍ ያለብን ፣ ወደ ሮም ውሰዱን!” በማለት። ሌሎችም የሰውየውን ሃሳብ ደገፉ፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ተሳፋሪ ወደ ሮም ነበር የሚጓዘው። ረዳት አብራሪው ሚላን ላይ እንደምናርፍ መናገሩ ብዙዎችን አበሳጭቶ ነበር፡፡
እውነቱን ለመናገር፣ እኔ ግን ሚላን እንደምናርፍ ስሰማ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔ ሚላን ወራጅ ነኝ፡፡ ረዳት አብራሪው የነገረን አስራ ሁለቱ ደቂቃዎች እየተገባደዱ መሆናቸው ሲገባኝ፣ ከአውሮፕላኑ ለመውረድ መዘገጃጀትና ጓዜን መሸካከፍ ሁሉ ጀመርኩ። ሆኖም አስራ ሁለቱ ደቂቃዎች አልፈውም አውሮፕላኑ አላረፈም፡፡ ካሁን አሁን ሚላን አውሮፕላን ማረፊያ ደረስን እያልን ስንጠባበቅ፣ ሌላ አስራ ሁለት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ አሁንም ሌላ አስራ ሁለት ደቂቃዎች---
ተሳፋሪው ሁሉ ግራ በመጋባት ሰዓቱን ደጋግሞ መመልከትና እርስ በርስ በጥርጣሬ መተያየት ጀመረ። ከአስራ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሚላን ላይ ያርፋል የተባለው አውሮፕላን፣ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በአየር ላይ ቆየ፡፡ የሚገርመው ያን ያህል ጊዜ አየር ላይ መቆየቱ ብቻ አይደለም፡፡ አበራረሩ የተለየ ነበር፡፡ አንዴ ፍጥነቱን ጨምሮ ይከንፋል፣ ከዚያ ደግሞ ፍጥነቱን ይቀንስና ተረጋግቶ ይበራል፡፡ እንደገና ይፈጥናል፣ እንደገና ይረጋጋል፡፡ ግራ ገብቶን እያለን፣ ከመቅጽበት አውሮፕላኑ ማረፊያው ላይ ደርሶ ማኮብኮብ ጀመረ፡፡ ያንን ያህል ግዙፍ አውሮፕላን፣ በዚያች ጠባብ ቦታ ላይ ያለችግር ማሳረፍ መቻሉ፣ የረዳት አብራሪውን ብቃት ያሳያል፡፡ ለማንኛውም አውሮፕላኑ በሰላም አረፈና እኛም እፎይ አልን፡፡
አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ የተሳፋሪዎች ስሜት ምን ይመስል ነበር?
የሚገርመው ነገር፣ አውሮፕላኑ እንዳረፈ በተሳፋሪው ፊት ላይ ከታየው ደስታና እፎይታ በተጨማሪ፣ ተሳፋሪው ለረዳት አብራሪው የሰጠው አድናቆት ነበር፡፡ አብዛኛው ተሳፋሪ ስለረዳት አብራሪው ችሎታ ነበር ተደንቆ የሚያወራው፡፡ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተውጠው፣ ለረዳት አብራሪው ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባና በፉጨት የገለፁም ነበሩ፡፡ እኔም በደመነፍስ ሳጨበጭብ ነበር፡፡ ሚላን ምድር ላይ በሰላም እንዲያሳርፈኝ ለፈጣሪዬ ያደረስኩትን ጸሎት የማውቀው እኔ ነኝ፡፡
ሚላን እንዳረፋችሁ ነበር የምታውቁት ማለት ነው?
የሚገርመው እኮ እሱ ነው!... አውሮፕላኑ መሬት ከነካ በኋላ ሁሉ፣ ተሳፋሪው በሙሉ ጣሊያን ሚላን እንዳረፈ ነበር የሚያውቀው፡፡ ሚላን እንደምናርፍ ነው ረዳት አብራሪው የነገረን፡፡ ትኬት ከፍለን የተሳፈርነውም ወደ ጣሊያን እንጂ ወደ ስዊዘርላንድ ለመሄድ አልነበረም። በዚህ ቅጽበት ጄኔቭ የምትባል ከተማ በምን ተአምር እንሄዳለን ብለን እናስብ?
ጄኔቭ መሆናችሁን ያወቃችሁት እንዴት ነው?
አውሮፕላኑ በሰላም ካረፈ በኋላ ተሳፋሪው ከጭንቀቱ ተገላግሎ መረጋጋት ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ሞባይል ስልኮቻቸውን አውጥተው መነካካት ያዙ። በሞባይላቸው የኢንተርኔት መስመር በመጠቀም ጎግል ማፕ የተሰኘውን የአገራትና የከተሞች ካርታ የሚያሳይ ድረገጽ፣ ጂ ፒ ኤስ ከሚባለው አቅጣጫ ጠቋሚ ቴክኖሎጂ ጋር አያይዘው ሲመለከቱ፣ ፊታቸው ላይ ድንገተኛ መደናገር ሲፈጠር አየሁ፡፡ አንዱ ተሳፋሪ ሞባይሉ ላይ ያየውን መረጃ በመጠራጠር፣ የሌላኛውን ሞባይል ማየት ጀመረ፡፡ “የት ነው ያለነው?” ለሚለው ጥያቄ እርግጠኛ የሆነ መልስ የሚሰጥ ጠፋ፡፡ ግማሹ “ ኦስትሪያ ነን!” ሲል፣ ገሚሱ “የለም ፈረንሳይ ነን!” ብሎ ይመልሳል፡፡ አንዳንዱ “ጀርመን ውስጥ ነው የምንገኘው!” ይላል፡፡ ሌላው “ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ነው ያረፍነው!” እያለ ይናገራል፡፡ ጭንቀትና ውጥረት የፈጠረው መደናገር ሊሆን እንደሚችል ያሰብኩት በኋላ ነው፡፡
ጄኔቭ ማረፋችሁንና አውሮፕላኑ መጠለፉን ያወቃችሁት እንዴት ነበር?
እያንዳንዱ ተሳፋሪ አውሮፕላኑ ያረፈበትን አገርና ከተማ በተመለከተ የየራሱን መላምት እየሰነዘረ ግራ ተጋብቶ ጥቂት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ በዚህ መሃል ነው፣ ድንገት የአውሮፕላኑን ዋና አብራሪ ድምጽ የሰማነው። በረራው ከተጀመረ አንስቶ የዋና አብራሪውን ድምጽ ስንሰማ ለመጀመሪያ ጊዜያችን ነበር፡፡ ዋና አብራሪው በጣሊያንኛ ቋንቋ ነበር የሚያወሩት፡፡ በጣሊያን ቆይታዬ የቀሰምኳት ቋንቋ ብዙም የምታወላዳ አልነበረችምና፣ ደቂቃዎችን ከፈጀው የአብራሪው ንግግር የተወሰነችዋን ተረድቼ፣ ቀሪውን ከጎኔ ከተቀመጡት ጣሊያናውያን ጠይቄ ለመረዳት ሞከርኩ፡፡
አብራሪው ወደመጸዳጃ ቤት ሲወጡ ረዳት አብራሪው በር እንደዘጋባቸው፤ አውሮፕላኑን ለሰዓታት ሲያበር የቆየው ረዳት አብራሪው እንደነበር፤ አውሮፕላኑ ያረፈው ጄኔቭ መሆኑን፤ በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን መግለጻቸውን እንዲሁም እያንዳንዱ ተሳፋሪ የስዊዘርላንድ ፖሊሶች ለሚያደርጉት ምርመራ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ነገሩኝ፡፡ ተሳፋሪው ስለ ጠለፋው ያወቀው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
ተጠልፋችሁ ያላሰባችሁት ቦታ እንዳረፋችሁ ስታውቁ ምን ተሰማችሁ?
እውነቱን ለመናገር በወቅቱ የሁሉም ተሳፋሪ ጸሎትና ምኞት በረራው በሰላም መጠናቀቁና አውሮፕላኑ አደጋ ሳያጋጥመው ማረፉ ብቻ ነበር፡፡ የተሳፋሪው ፍላጎት የትም ይሁን የት፣ ብቻ የሆነ መሬት ላይ ማረፍና ከጭንቀት መገላገል ነበር፡፡ አስበው እስኪ… ከአብራሪውም ሆነ ከሆስተሶቹ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት በሌለበት አደናጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ለሰዓታት የበረርነው፡፡ ከዚያ ደግሞ… ሮም የማረፍ ዕቅዱ ተሰርዞ፣ ከ12 ደቂቃዎች በኋላ ሚላን እንደምናርፍ ድንገት ተነገረን፡፡ ይሁን ብለን ተቀብለን፣ አስራ ሁለቱን ደቂቃ በጉጉት ስንጠባበቅ ደግሞ፣ ለተጨማሪ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜ በረራው ቀጠለ፡፡ በዚያ ላይ በረራው ጤነኛ አልነበረም፡፡ አንዴ የሚፈጥን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚረጋጋ ምቾት የማይሰጥ በረራ ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ተሳፋሪ፣ የትም ቢሆን ማረፍን እንጂ፣ማረፊያ ቦታውን አይመርጥም፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ተሳፋሪዎች ጉዳዩን ያወቅነው፣ ጠለፋው ከተጠናቀቀና አውሮፕላኑ ጄኔቭ ውስጥ በሰላም ካረፈ በኋላ ዋና አብራሪው ሲነግሩን በመሆኑ እምብዛም አልተደናገጥንም፡፡
ከአውሮፕላኑ ስትወርዱ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አውሮፕላኑ ጄኔቭ ካረፈ በኋላ በግምት ለአንድ ሰአት ያህል በሩ ሳይከፈት ቆሞ ቆየ፡፡ ዋና አብራሪው ሁሉንም ነገር በግልጽ ከነገሩን በኋላ፣ ከእግር ጣታቸው እስከ ራስ ጸጉራቸው የብረት ጭንብል የለበሱ ሰዎች፣ በሩን በርግደው በፍጥነት ወደ ውስጥ ገቡ። አገባባቸውና መላ ሁኔታቸው አክሽን ፊልም የሚሰሩ ነበር የሚመስሉት፡፡ ሁኔታው እጅግ ያስጨንቅ ነበር፡፡ በመካከል አንደኛው ፖሊስ በእጁ በያዛት አነስተኛ የድምጽ ማጉያ ፈረንሳይኛ በሚመስል እንግሊዝኛ መናገር ጀመረ።
“ዚስ ኢዝ ኤ ፖሊስ ኦፔሬሾን። ዶንት ሙቭ!... ፑት ዩር ሃንድስ ኦን ዩር ሄድ!... ዶንት ሜክ ሙቪ ባይ ሞባይል (በሞባይል አትቅረጹ ማለቱ ነው)” ሲል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ሁሉም እጆቹን አናቱ ላይ ጭኖ ድምጹንም አጥፍቶ አቀረቀረ፡፡ ተሳፋሪው በፖሊሶቹ መሪነት አንድ በአንድ ከአውሮፕላኑ እየወረደ፣ ሁለት ሁለት ጊዜ ተበርብሮ ተፈተሸ፡፡
ፍተሻው እንደተጠናቀቀም በትላልቅ ሽንጣም አውቶብሶች እየጫኑ ወደ ተርሚናሉ ወሰዱን፡፡ ተርሚናሉ ላይ ስንደርስ የሚገርም አቀባበል ተደረገልን፡፡ የምንበላው ቁርስና ሻይ ቡና እንዲሁም ለብርዱ ብርድልብስ ተዘጋጅቶ ጠበቀን፡፡ የህክምና ባለሙያዎችና የስነልቦና ባለሙያዎች እርዳታ ሊሰጡን እየተጠባበቁ ነበር፡፡ አስገራሚ አቀባበል ነው የተደረገልን።
ኢትዮጵያውያንስ አላገኛችሁም?
ተርሚናሉ ዉስጥ ገብተን ትንሽ እንደቆየን አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ እኛ ሲመጣ ተመለከትን፡፡ ለጊዜው ስሙ ትዝ አይለኝም። ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደመጣ ነገረንና ስለሁኔታው ጠየቀን። “አይዟችሁ!... ደርሰንላችኋል!...” የሚል መንፈስ ያለው ማበረታቻ ሰጠን፡፡ ከዚያም የግል ሞባይሉን ከኪሱ አውጥቶ አገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቻችን ጋ ደውለን ደህንነታችንን እንድናረጋግጥ ራሱ እየደወለ ያገናኘን ጀመር፡፡
በዚህ ጊዜ ነው፣ በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የመጡት፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበርን ኢትዮጵያውያንን አነጋግረው አረጋጉን፡፡ በስተመጨረሻም ከተርሚናሉ እንዲወጡ ስለታዘዙ የማስታወሻ ፎቶግራፍ አብረውን ተነሱና ጉዳያችንን በቅርብ እንደሚከታተሉ ነግረውን አበረታቱንና ሄዱ፡፡ ሌሎች ሁለት የኤምባሲው ባልደረቦችም፣የሚፈቀድላቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ እየተገኙ ድጋፍ በማድረግ እስከመጨረሻው አብረዉን ነበሩ።
በእለቱ ስለተከሰተው ሁኔታ ምን ትላለህ?
እናቴ እንደነገረችኝ፣ በህፃንነቴ የወራት ዕድሜ ላይ እያለሁ፣ የሆነ ቀን ከታላቅ ወንድሜ መላኩ ገብሬ ጋር ከጎማ ላስቲክ የተሰራ አልጋ ላይ ተኝቼ ነበር። ቡና ስታፈላ ምንጊዜም ዕጣን ማጨስ እማትዘነጋው እናታችን፣ ያጨሰችዉን እጣን እኛ የተኛንበት አልጋ አጠገብ አስቀምጣው ኖሮ፣ እሷ ጎረቤት ደርሳ ስትመለስ ቤቱ በጭስ ተሸፍኖ ጨልሞ ጠበቃት። ጩኸቷን ለቀቀችው። ጩኸት ሰምቶ የመጣ ጎረቤት ነው አሉ ፈልጎ አግኝቶኝ በመስኮት ወደ ውጭ የወረወረኝ። ምህረቱ የተባልኩትም በዚያ ምክንያት ነው። እንዳጋጣሚ እሳቱ ቀድሞ የተያያዘው ወንድሜ በተኛበት በኩል ስለነበር እሱን ማትረፍ አልተቻለም።
የፈጣሪ ምህረት ዛሬም አልተለየኝም፡፡ በአውሮፕላኑ ላይ ሊደርስ ከሚችለው አሰቃቂ አደጋ አትርፎኛል። እንደትላንትናው ሁሉ ነገዬም በፈጣሪ እጅ እንደሆነች አምናለሁ። እርሱ ይሁን ያለው ሁሉ መልካም ነው። ቸርነቱ አይለየኝና ፍቃዱ ሆኖ ለነገ ካበቃኝ ለልጆቼ የምነግረው ተጨማሪ ታሪክ አግኝቻለሁ።
ደህና ነኝ እንኳን ብላት የማታምነኝ እናቴ ብርሃነማርያም ኪአን፣ እጮኛዬ ዮዲት ቦርሳሞን፣ ወንድሞቼን፣ ብቸኛዋን እህቴን፣ አክስቶቼን ከነቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቼን፣ስለደህንነቴ የሚጨነቁልኝን ሁሉ ደህና መሆኔን ንገርልኝ። ከሁሉ አስቀድሞ ስለሆነውም ስለሚሆነዉም ክብር ሁሉ የእርሱ ነውና ፈጣሪ የሚገባዉን ክብር እና ምስጋና ይውሰድ።
Source: Addis Admass