-አና ጎሜዝ ወደ እንግሊዝ መመለስ አለባቸው እያሉ ናቸው::
ከዱባይ ወደ አስመራ ለመሄድ የመን ሰንዓ ላይ በየመን የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ታስረዋል የተባሉት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጥተዋል መባሉን እንደ ሰማ የእንግሊዝ መንግሥት አስታወቀ፡፡
ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ጸሐፊ ሚስተር ኢያን ኮክስ አቶ አንዳርጋቸውን በሚመለከት ለሪፖርተር በላኩት መግለጫ እንዳስረዱት፣ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰነዓ ውስጥ መጥፋታቸው ተገልጾላቸዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእንግሊዝ ባለሥልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ያሉበትን ሁኔታና ሥፍራ ለማወቅ የየመን ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና በእንግሊዝ የሚገኙትን የየመን አምባሳደርን ማነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡
ኢያን ኮክስ አንዳንድ ከሚወጡ መረጃዎች ለመረዳት እንደቻሉት፣ አቶ አንዳርጋቸው ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ በመሆኑም ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ፣ አቶ አንዳርጋቸው በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እንደሚገኙ ከሪፖርቶች መረዳት መቻሉን ገልጾ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ማረጋገጫ በአስቸኳይ እንዲሰጠው መጠየቁን አስታውቋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የእንግሊዝ ባለሥልጣናት በእንግሊዝ የየመን አምባሳደርን አነጋግረዋቸው፣ አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸውን ለቤተሰቦቻቸው መንገራቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባል የሆኑትና የኢትዮጵያን መንግሥት በመንቀፍ የሚታወቁት ሚስስ አና ጎሜዝ፣ አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ማረጋገጣቸውን ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊልያም ሔግ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡
ሚስስ ጎሜዝ በይፋዊ ድረ ገጻቸው ባሰፈሩት ደብዳቤ አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው እንደተሰጡ መረጃ ማግኘቻቸውን ገልጸው፣ በዚህም መደንገጣቸውንና የእንግሊዝ መንግሥት ምንም ዓይነት ዕምርጃ ባለመውሰዱ መናደዳቸውንም አስረድተዋል፡፡
ሚስ ጎሜዝ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የሕይወትና የአካል አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል፣ እንዲሁም ባላመኑበትና ባልፈጸሙት ወንጀል ክስ ሊቀርብባቸው እንደማይገባ ገልጸው፣ በተቻለ መጠን ወደ እንግሊዝ የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቀዋል፡፡
በ1997 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የነበሩት ሚስስ ጎሜዝ፣ የእንግሊዝ መንግሥት የኢትዮጵያ ዋነኛው ለጋሽና የፖለቲካ ደጋፊ በመሆኑና ተፅዕኖውም ከማንም አገር የላቀ በመሆኑ፣ አቶ አንዳርጋቸውን ማስፈታት አለበት ሲሉ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው ተሰጥተዋል መባሉን በተመለከተ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጡም፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የሚፈለጉ በመሆናቸው ተላልፈው መሰጠት እንዳለባቸው ለውጭ ሚዲያ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ኢትዮጵያና የመን በ1991 ዓ.ም. በተፈራረሙት የፀጥታና የደኅንነት ስምምነት መሠረት፣ የመን አቶ አንዳርጋቸውን ለኢትዮጵያ አሳልፋ እንደምትሰጥ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል የእንግሊዝ ዜግነት ስላላቸው ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠት የለባቸውም የሚሉ ሲኖሩ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እስከገቡ ድረስ ተጠያቂነት እንዳለባቸው የሚከራከሩ አሉ፡፡
Source: Reporter
No comments: