ዳንኤል ክብረት: -
ሰሞኑን ከአንድ ሰው ‹የማጭበርበር› ነገር ጋር በተያያዝ ከዚህም ከዚያም አስተያየት ይሰጣል፡፡ አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙኃንም ትኩረታቸውን በሰውዬው ላይ አድርገው እንዴት እንዲህ ሊያደርግ ቻለ? ለምን እንዲህ አደረገ? ምን ነክቶት ነው? እያሉ ጉዳዩን ከማኅበረሰብ ሳይንስ፣ ከሥነ ልቡና፣ ከእምነትና ከባሕል አንጻር እየተነተኑ ይገኛሉ፡፡
እኔ ግን ይህን ጉዳይ ስከታተል ትዝ የሚለኝ አንድ የሀገራችን ተረት ነው፡፡ ሰውዬው መንገድ ላይ ሲሄድ በሩ ወለል ብሎ የተከፈተ ቤት ያገኛል፡፡ ለጥቂት ቆም ብሎ ሁኔታውን ሲያይ ማንም በአካባቢው ዝር የሚል አልነበረም፡፡ ነገሩ የተከፈተ በር ብቻ ሳይሆን ‹የተከፈተ ዕድልም› የሆነለት ሰውዬ የተከፈተው ቤት ውስጥ ዘው ብሎ ይገባል፡፡ማንም አልነበረም፡፡ ወዲያና ወዲህ እየተንጎራደደ ቤቱን ቃኘና ዓይኑ ያረፈበትን ዕቃ ይዞ ላጥ አለ፡፡ መንገድ ላይ ያዩት ሰዎች የሚያውቁትን ዕቃ አንድ ሰው ይዞ ሲሸመጥጥ በማየታቸው ይጠራጠሩና ያስቆሙታል፡፡ ፖሊስም በነገሩ ይገባበታል፡፡ ሰውም ከዚህም ከዚያም ይወርድበታል፡፡
ግርግሩ በዚህ መልክ እየቀጠለ ዕቃቸው የተሰረቀባቸው ሰዎች ኡኡ እያሉ ይደርሳሉ፡፡ ሲደርሱም የቤት ዕቃቸው በአንድ በማያውቁት ሰው ትከሻ ላይ ያገኛሉ፡፡ ግርግሩን ሰንጥቀው ይገቡና ‹‹ሞላጫ ሌባ›› እያሉ ሌባውን በጥፊ ሲመቱት ሌባው ተናድዶ ዕቃውን ያወርድና ጥፊውን በጥፊ ይመልሳል፡፡ ፖሊስ በድርጊቱ ተገርሞ ከዚያ ሁሉ ሰው ይልቅ ለባለቤቶቹ ጥፊ ለምን መልስ እንደሰጠ ሲጠይቀው ‹‹ቤታቸውን ከፍተው እየሄዱ ሰው ሌባ ያደርጋሉ›› አለ ይባላል፡፡
የሰሞኑ ሁኔታም ይህን ነገር እንድናየው የሚያደርግ ነው፡፡ ለመጭበርበርና ለመታለል የሚችል አሠራር፣ አካሄድና አፈጻጸም የዘረጋነው እኛው ነን፡፡ ነገሮችን በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመርኩዘን ከመወሰን ይልቅ በሚወራ ወሬ፣ በሚገነባ ገጽታና ከሚዲያ በምንሰማው ነገር ላይ ብቻ የመመራትን አሠራር ያሰፈንነው እኛው ነን፡፡ ዛሬ ቀን ጥሎት የተጋለጠው ሰው ላይ በወደቀ ዛፍ ላይ የሚበዛውን ምሣር ሁሉ እናዘንብበታለን እንጂ ሌሎች ወደፊት እንዳይከሰቱ የሚያደርግ አደረጃጀት፣ አሠራርና አስተሳሰብ ግን አልዘረጋንም፡፡
እንዲያውም የዚህን ሰው በዚህ መልኩ መምጣት ለሀገራችን ተቋማትና ኃላፊዎች ‹በረከተ መርገም› የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ‹ዓመት ባል ካልመጣ ሁሉ ሴት፣ ክረምት ካልመጣ ሁሉ ቤት› የሚባል አባባል አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ባይኖሩ የኃላፊዎቻችንን፣የምሁሮቻችንንና የመሥሪያ ቤቶቻችንን የተዝረከረከ አሠራር እንድናይ ማን ያደርገን ነበር፡፡ እዚህ ሀገር ምን ዓይነት ሰዎች ምን ዓይነት ቦታ እንደሚይዙ አሳይቶናል፤ ሴትዮዋ ‹አፍ ያለው ያግባሽ ከብት ያለው› ስትባል ‹‹አፍ ያለው ያግባኝ፣ አፍ ያለው ከብቱን ያመጣዋልና›› ያለችው እውነቷን ነው እንድንል አስችሎናል፡፡ አፍ ካለ፣ መናገር ከተቻለ፣ መስጠት ከተቻለ፣ እዚህ ሀገር ውስጥ ዕድሉም መንገዱም ወለል ብሎ እንደሚከፈት አይተናል፡፡ ሚዲያዎቻችንም የማጣረት፣ የመመርመርና ከግራ ቀኝ የማየት ዐቅማቸው የት ድረስ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ ‹ማን ምን አለ› እንጂ ‹ያለው ልክ ነው ወይ?› ብሎ ለማረጋገጥ ጥቂት እርምጃዎች መሄድ የሚችሉ ሚዲያዎች እንደዋልያ ‹ብርቅዬ ድንቅየ›› መሆናቸውን ተምረንበታል፡፡
እንዲህ ያለ ሰውማ ይምጣ፡፡ እዚህ ሀገር ድፍረት እንጂ ዕውቀት፣ ትውውቅ እንጂ ዕውውቅ፣ ዘመድ እንጂ ችሎታ፣ ቅልጥፍና እንጂ ጉብዝና ዋጋ እንደሌላቸው እናይ ዘንድ፡፡
እኔን ምን አገባኝ የሚሉት አጉል ወግ
እርሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደ በግ
የሚል ግጥም ልጽፍ ተነሣሁኝና
ምን አገባኝ ብዬ ተውኩት እንደገና
ብሎ የጻፈውን ባለ ቅኔ እውነት እንድናየው አድርጎናልና እንዲህ ያለ ሰውማ ይኑር፡፡
ምሁሮቻችን ያላስተማሩት ተማሪ ከፊታቸው ቆሞ አስተምራችሁኛል ሲላቸው፣ ተማሪዎቹ ብቃት አንሷችሁ እኔን ማየት ሳትችሉ ቀርታችሁ ነው እንጂ አብሬያችሁ ተምሬ ነበር ሲላቸው፣ የዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደሮች ረስታችሁኝ ነው እንጂ ሸልማችሁኝ ነበር ሲላቸው፣ በቅቼ ተሠውሬ ነው እንጂ አብሬያችሁኮ ነው የምሠራው ሲላቸው፤ የቤተ መንግሥት ሰዎች በእሳት ሠረገላ ገብቼ አላያችሁኝም እንጂ ከአቶ መለስ ጋር አብሬ ነበርኩኮ ሲላቸው ዝም ያሉት ‹ዝምታ ወርቅ ነው›› ብለው አይደል፡፡ የዝምታችን ነገር የት ድረስ እንደሚደርስ፣ ስሕተትን የመቻል ዐቅማችን የት ድረስ እንደሆነ፣ የተበላሸን ነገር የመሸከም ችሎታችን ምን ያህል እንዳደገ፣ ውሸትን የመቀበል ብቃታችን ጨምሮ ጨምሮ እዚህ መድረሱን በሚገባ አሳይቶናል፡፡ ኑርልን ባክህ፡፡
ባለፈው ጊዜ በዓለም ዋንጫ ጉዟችን አንድ ተጨዋች ሁለት ቢጫ ካየ በኋላ እንደገና ተሰልፎ በመጨዋቱ ፊፋ ቀጣን፡፡ ይህ ቅጣት ብዙ ሰዎችን አሳዘነ፡፡ ያ ቅጣት ግን ብናውቅበት ኖሮ በረከተ መርገም ነበር፡፡ የፌዴሬሽናችንን አሠራር ቁልጭ አድርጎ በአደባባይ ያሳየን፡፡ እንኳንም ተጨዋቹ ተቀጣ፣ እንኳን ፌዴሬሽኑም ተዝረከረከ፡፡ ያንን ዝርክርክነት እንዴት አድርገን እናየው ነበር፡፡ ከዚያ በፊትምኮ ከዚያ የባሱ ዝርክርክ አሠራሮች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በድብብቁ አሠራራችን ምክንያት ‹ሽል ሆነው ከመግፋት ይልቅ ቂጣ ሆነው እየጠፉ› ሳናያቸው ኖርን፡፡ ያንን አጋጣሚ ማለፍ ግን አልተቻለም፡፡ ዓለም ያወቀው፣ ዓለም ሊያውቀውም ግድ የሚለው ጥፋት ነበረና፡፡
የሚገርመው ነገር እንዲያ ዓይነት አገርን አንገት ያስደፋን ጥፋት ሲሆን እንዳይፈጸም፣ ካልሆነም እንዲታረም የሚያደርግ አሠራር ባለመዘርጋታችንና አመለካከታችንንም ባለማስተካከላችን በሴቶች እግር ኳስ ላይ ተደገመና የፓስፖርት መጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባትን ተጨዋች ለማሰለፍ ሜዳ ውስጥ እስከማስገባት ደረስን፡፡ ይኼኛውን ዝርክርክነት ለማወቅ የቻልነው ለማወቅና ለመታወቅ የግድ የሚለው ዓለም አቀፋዊ አሠራር በመኖሩ የተነሣ ነው፡፡
ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ(ገሞራው) ‹በረከተ መርገም› በሚለው ግጥሙ ላይ ‹ድኻው ምን አረገ ሊቆቹን ነው መርገም› ይላል፡፡ አሁን መረገም ያለበት ተቋማዊ አሠራራችን፣ አስተሳሰባችን፣ የመረጃ አያያዛችን፣ ነገሮችን በንሥር ዓይን ከማየት ይልቅ በተወራውና በተባለው ብቻ መመራታችን፣ የዘመድ አዝማድ አካሄዳችን፣ የተጠጋጋውን ሁሉ የሚያምነው አሠራራችን ነው፡፡ መረገም ያለበት ለመታለል፣ ለመሞኘት፣ ለመሸወድ፣ ለመጭበርበር እጅግ ቀላልና እጅግም ዝግጁ የሆነው ቢሮክራሲያችን ነው፡፡
ይህን መሰል ሰዎች መምጣታቸው በሀገራችን እጅግ ተወዳጁ ምግብ ‹ምላስና ሰንበር› መሆኑን እንድናውቅ አድርጎናል፡፡ ምላስና ሰንበር ካለህ የፈለግከውን ተናገር - ትሰማለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ የፈለግከውን ነኝ በል - ትታመናለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ የፈለግከው ቦታ ደርሻለሁ በል - ትደነቃለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ እንደ ኢዲ አሚን ሁሉንም መዓርግ ለራስህ ስጥ - ትሞገሳለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ ዐዋቄ ኩሉ ነኝ በል - ተከታይ ታገኛለህ፡፡ የዚህን መሰል ሰዎች መነሣት ይህንን አሳይቶናል፡፡ እንኳንም ተነሣችሁ፡፡
ደግሞስ እነርሱ ባይኖሩ ይህንን መሰሉን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የተወካዮች ምክር ቤት፣ ዋናው ኦዲተር፣ ያልደረሰባቸውን የተበላሹ አሠራሮች እንዴት እናያቸው ነበር? ኧረ እንኳን ኖራችሁ፤ ለኛ በረከተ መርገም ናችሁ፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው
Source: www.danielkibret.com
No comments: