10 የሱዳን ወታደሮች በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ተገደሉ

አፍሪካን ፕሬስ ኤጀንሲ እንደዘገበው 10 የሱዳን ወታደሮች በኢትዮ -ሱዳን ድንበር አካባቢ ከተገደሉ በሁዋላ በድንበር አካባቢ ውጥረት ሰፍሯል። እሁድ እለት ደግሞ ተጨማሪ 13 የሱዳን ወታደሮች መቁሰላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ጥቃቱም በኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ሳይፈጸም እንዳልቀረ ተዘግቧል።
የሱዳን ኮማንዶ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሃይሉን እያሰባሰበ መሆኑን የገለጸው ዘገባው፣ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መካሄዱን ጠቅሷል። ሱዳንና ኢትዮጵያ የድንበር ከተሞቻቸውን ከታጣቂዎች ጥቃት ለመከላከል በሚል  አንዱ በሌላው አገር ድንበር ጥሶ በመግባት እርምጃ እንዲወስድ መስማማታቸው ይታወቃል።
የሱዳን መንግስት ወታደሮቹ መገደላቸውን አምኖ፣ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ተገደሉ የሚለውን እንደማይቀበለው አስታውቋል። የሱዳን መንግስት ጦር ቃል አቀባይ ኮሌኔል አልስዋርሚ ካሊድ ሳድ እንደተናገሩት ወታደሮቻቸው የተገደሉት
ማንነታቸው ካልታወቁ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር ሲዋጉ መሆኑን ተናግረዋል። ግጭቱ የተነሳው ባሶንዳ እየተባለ በሚጠራው በሁለቱ ድንበር አካባቢዎች መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ታጣቂዎቹ ባሶንዳ የሚገኘውንና በሱዳን መከላከያ ሰራዊት ስር የሚገኘውን የእርሻ ቦታ መልሰው ለመውሰድ አላማ ነበራቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባላስልጣናትም ስለጉዳዩ እንደተነገራቸው ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን የተናገረው አንድም ነገር የለም።
በሱዳን ወታደሮች ላይ ለደረሰው ጥቃት ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ያለ  ሃይልም እስካሁን አልቀረበም።
Source: www.geeskaafrika.com 

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog